The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ዐቢዎታዊ ዲሞክራሲና ወያኔ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

COVER

ዐቢዮት ማለት ዐመፅ ወይም እምቢ አሻፈረኝ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ ቃሉ ዐበየ ከሚለው የግእዝ ቃል ግስ የወጣ ቃል ሲሆን ዐመፀ፣ እምቢ አለ፣ ተበተ፣ ተኩራራ ማለት ነው፡፡ ሕዝባዊ ዐቢዮት ብለን ስንል ሕዝባዊ ዐመፅ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ማለታችን ነው ማለት ነው፡፡ ዐቢዮት ሌላም መለያ ባሕርይ አለው ድንገተኛነቱና ሊያመጣ የፈለገውን ለውጥ በኃይል በተቃውሞ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለማምጣት ለማስፈን መራመዱ ነው፡፡ ስለሆነም “ዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ” ብለን ስንል አስቀድሞ የነበረውን ሥርዓት እምቢ አሻፈረኝ በማለት ይሆነናል ይሻለናል በማለት በኃይል በድንገት እንዲሰፍን የተደረገ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ማለታችን ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር መሬት ላይ ስላለው ሀቅ ስናወራ ግን ዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) እና ወያኔ ማለት መልከ ጥፉ ሴትና ጆሮዋ ላይ ያንጠለጠለችው የወርቅ ጉትቻ ማለት ናቸው፡፡ ይህቺ መልከ ጥፉ ያደረገችው ጉትቻ ውድ ዋጋ ያለው የወርቅ ቢሆንም መልከጥፉነቷን ሊለውጠው አይችልም፡፡ እንዲያውም የሚያያት ሁሉ ያ ጌጥ ያለቦታው እንደተንጠለጠለ እንዲያስብና መልከ ጥፉነቷን በአንክሮ እንዲያስታውስ ያደርግባታል እንጅ ተፈጥሯዊ ማንነቷን በመለወጥ ረገድ ምንም የሚረባት ነገር አይኖርም፡፡ ሴትዮዋ ግን መልከ ጥፉነቷን ለውጦ ውብ ሊያደርጋት እንደማይችል እያወቀችም ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም፡፡ የዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) እና የወያኔ ዝምድናና ግንኙነትም ሳትጨምሩ ሳትቀንሱ እንደ ወርቁና ፉንጋዋ ሴት ነው፡፡ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንደሚባለው ሁሉ ወያኔም ያለበትን መልከ ጥፉነት በስም ለመደገፍ በማሰብ ካልሆነ በስተቀር ዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) እና እሱ ምንም የሚያገናኛቸው የሚያዛምዳቸው የሚያቀራርባቸው አንድም ነገር የለም፡፡

ስለ “ምርጫ” 2007ዓ.ም. ለመዘገብ የአሜሪካ ድምፅ የኢንግሊዝኛው ክፍል ዘጋቢ እዚህ መጥታ በነበረችበት ወቅት የወያኔ አፈቀላጤ አቶ ሬድዋን ሑሴንን ቃለመጠይቅ ስታደርግ “ዐቢዮታዊ መስፍነ ሕዝብ (revolutionary democracy) ማለት ምን ማለት ነው?” ብላ ጠይቃቸው ሲመልሱ ምን አሉ? “ዐቢዮታዊ መስፍነ ሕዝብ (revolutionary democracy) ማለት አንድን ለውጥ በሁለት መንገድ ማምጣት ይቻላል አንደኛው የራሱን ተፈጥሯዊ ሒደት ጠብቆ ከሁኔታዎች ጋር ተገናዝቦ በራሱ የጊዜ ሒደት የሚመጣው የሚፈጠረው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ይሄንን ተፈጥሯዊ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሒደት ሳይጠብቅ በዐቢዮታዊ እንቅስቃሴ (in revolutionary movement) እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ እናም እኛ በዚህ ሀገር ላይ ያመጣነው ያሰፈነው ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ተፈጥሯዊ ሒደቱን ጠብቆ ከነባራዊ ከሁኔታዎች እድገት ጋር ተገናዝቦ በራሱ ጊዜ የተፈጠረ የመጣ ሳይሆን ይሄንን ረጅም ጊዜ የሚፈጀውን ተፈጥሯዊ ሒደት ሳንጠብቅ ዐቢዮታዊ በሆነ እንቅስቃሴ ወይም መንገድ ክስተት ሊባል በሚችል ሁኔታ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) በዚህ ሀገር እንዲሰፍን ስላደረግን ይሄንን ዲሞክራሲያችንን ዐቢዮታዊ (revolutionary) ብለነዋል” ነበር ያሉት እውነታው ግን ከዚህ ምን ያህል የራቀ እንደሆነ ቀጥለን እናያለን፡፡

EPRDF1 የወያኔ ባለሥልጣናት እንደ የሰው ልጅ ከሰው ልጅም ኃላፊነት እንደሚሰማውና ቀና ዓላማ እንዳለው ዜጋ በሎጂክ (በአመክንዮ) እና በሞራል (በቅስም) ስሜትና ድንጋጌዎች ለመመራት የኅሊናን ወቀሳ ለማድመጥ በፍጹም ስለማይፈቅዱና ዕኩይ ዓላማቸውም ይሄንን እንዲያደርጉ ስለማይፈቅድላቸው የሚናገሩት ዐይን ያወጣ ሐሰት በሰው ዘንድ የሚያስገምታቸው የሚያቀላቸው የሚያዋርዳቸው መሆኑ ሲጀመር ጀምሮ ቅንጣት እንኳን አሳስቧቸውም አስጨንቋቸውም አያውቅምና ፍጹም ፈጠራና የሌለን ነገር እንዳለ ያለውን ሀቅና እውነታ ደግሞ እንደሌለ አድርገው ያለ አንዳች የስሜት መሸማቀቅ እውነት እንደሚናገር ሰው በልበ ሙሉነትና ኩራት መናገር ይችላሉ፡፡

እነዚህ ንኮች “በዚህች ሀገር ዐቢዮታዊ በሆነ መንገድ ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብን) አሰፈንን” እያሉ ባሉበት ሁኔታ በተመሳሳይ ሰዓትም በተለይ ከምርጫ 97ዓ.ም. በኋላ ምን ማለት ይዘዋል? “በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተማረና ፀረ ዲሞክራሲ የሆነ ባሕል ያለው በሆነበት ሁኔታ ዲሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስፈን ማለት የማይታሰብና ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ስለሆነ ወደፊት ሕዝቡ እየተማረ እየሠለጠነ ሲመጣ ከዚህ ለውጡ ጋር አብሮ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው” በማለት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሁለት ፍጹም የተለያዩና የሚቃረኑ ነገሮችን ወይም አስተሳሰቦችን ይናገራሉ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የትኛው ባሕሉ ነው ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) የሆነውና ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብን) በኢትዮጵያ እንዳታሰፍኑ እንቅፋት መሰናክል የሆነባቹህ?” ተብለው ቢጠየቁ ምን ብለው እንደሚመልሱ ግን እግዚአብሔር ይወቅላቸው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚሉት ፊደል የቆጠረ ባይሆንም ተማረ ከሚባለው በየጥኛውም የዓለም ክፍል ካለ ማኅበረሰብ እጅግ በላቀ ሁኔታ የበሰለና አስተዋይ በተፈጥሮው የተማረ ሕዝብ ነውና፡፡ ከባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓቶቹ ለምሳሌ የአማራው እሰጥ አገባ፣ በላ ልበልሀ፣ ሸንጎ፣ የኦሮሞው ገዳ፣ የጉራጌው ቂጫ የተቀሩትም እንደዚሁ የመሳሰሉ የፍትሕን የበላይነት የተቀበሉና ፍትሕን የማስፈኛ የማረጋገጫና ሕዝብ የመዳኛ ሥርዓቶች ባሕሎች ወጎች ባለቤት በሆነበት ሁኔታ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቁርአን ከአውሮፓ ፈላስፎች እስከ ታሪክ ጸሐፍቶቻቸው ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቅዱስነት፣ ፍትሕና ርትዕ አዋቂነት፣ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ሰላማዊነት የመሰከሩ ያረጋገጡ በሆነበት ሁኔታ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው ዘመናዊ የአሥተዳደር ሥርዓትን ለሙሴና በእርሱም በኩል ለዓለም ያስተዋወቅን እኛ በሆንበት ሁኔታ፣ ወያኔን የሚያህልን የቆሻሾች የደናቁርት የባለጌዎች የነውረኞችን ግፍ እርግጫ ዘለፋ ትፋት ንቀትና ውርደት እየተቀበለ ተሸክሞ ምንም እንዳልከፋው እንዳልጎደለበት አንጀት በሚበላ ትዕግሥትና ሰቆቃ በዝምታ ተሸክሞ እየተረገጠ ያለ አስተዋይ አርቆ አሳቢ ታጋሽ ሕዝብ በሆነበት ሁኔታ ይህ ሕዝብ ምን እንከን ምን ፀረ ዲሞክራሲ ባሕል ኖሮበት እንደዚህ ንቀው ስሙን ሊያክፋፉት ሊያጠፉት ሊዘልፉት ሊያዋርዱት እንደቻሉ ሕዝቡ ባጋጠመው በድረክና እነኝህን ባለጌዎች ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ በመጠየቅ በማፋጠጥ የጠፋ ስሙን ማስመለስ ይኖርበታል፡፡ የእነሱ ርካሽና ነውረኛ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ የእነሱ ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) አስተሳሰብና አንባገነንነት እንዲሸፈን እንዲደበቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሌለበትን እንከንና ነውር መሸከምና መዋረድ አለበት ወይ?

ለማንኛውም ይህ አባባላቸው አሰፈንን የሚሉትን ዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ ሐሰትነት በገዛ አንደበታቸው በተናገሩት ቃል ቁልጭ አድርገው ያሳይተዋል አረጋግጠዋል በራሳቸው ላይ ወስክረዋል፡፡ ዐቢዮታዊነቱ ቀርቶ በተፈጥሯዊ ሒደቱ እንኳን እያደገ እየጎለበተ እንዲሔድ ፍጹም የሚፈቅዱ ባለመሆናቸው ሁሉም ነገር ከትናንት ዛሬ ከፍቶ ትናንት የነበረው ዛሬ ላይ ጠፍቶ ነው ዕያየን ያለነው፡፡ በመሆኑን ዐቢዮታዊ መስፍነ ሕዝብ (revolutionary democracy) ወያኔ ፉንጋነቱን ይደብቅለት ዘንድ ያንጠለጠለው ጌጥ ከመሆን ያላለፈ ተቀጽላና ባዶ ቃል ብቻ ነው፡፡ ሳይገባውም ይሄንን ስም አንጠልጥሏልና ያውልቅ ያውርድ ይፍታና ያስቀምጥ፡፡ የሚገባው ሲመጣ ያጌጥበታል፡፡

እነዚሁ ስድ ገዥዎቻችን ከዚህም በተጨማሪ ዲሞክራሲ ብለው ስለሚሉት እየቀጨጨ እየኮሰመነ ጭራሽም እየጠፋ መሔድ ምነው? እንዴት? ለምን? ተብለው ሲጠየቁ የሚመልሱት አንድ ሌላ መልስ ደግሞ አላቸው “ዲሞክራሲ ሒደት ነው በአንድ ጀምበር ሊሰፍን ሊረጋገጥ የሚችል ሥርዓት አይደለም፤ እነ አሜሪካ ሁለት መቶ ዓመታት ነው የፈጀባቸው” ምንትስ በማለት ለአፋኝ እረጋጭ ፈላጭ ቆራጭነታቸው መሸሸጊያና ማምለጫ ጥግ በመፈለግ ሲቅበዘበዙ ሲክለፈለፉ ይታያሉ፡፡ መጀመሪያዉኑም “የራሱን ሒደት ሳይጠብቅ ስንት ዘመን ሊፈጅ ይችል የነበረውን ዐቢዮታዊ በሆነ መንገድ ባቋራጭ እንዲሰፍን አደረግን!” ምትስ እያሉ የወሸከቱት እነሱው ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ “አይ! አይደለም በአሜሪካ ሁለት መቶ ዓመታት ወስዷል የእኛ ማኅበረሰብም ያልተማረ ከመሆኑም አንጻር ከዚያ በላይ ሊወስድበት ይችላል” የሚሉቱም እነሱው ናቸው “አንቺው ታመጭው አንቺው ታሮጭው” እንደተባለው ነው ነገሩ፡፡

ይሁንና ቀደም ብየም እንደገለጽኩት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕግና ለሥርዓት ካለው ከፍ ያለ ግምትና ከሚሰጠው ላቅ ያለ ዋጋ የተነሣ፤ የዲሞክራሲያዊ (የመስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት መሠረትም በሕግ የበላይነት ማመን የሕግ የበላይነትን መቀበል በመሆኑና ሕዝባችንም ያውም በትምሕርት ሳይሆን በባሕል ደረጃ ይህ ሀብት ይህ እሴት ያለው በመሆኑ ለአዋጅ መንገሪያ ከሚፈጅ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓትን በተደላደለ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ማስፈን ይቻላል፡፡ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ በሚገባ አለው፡፡ የሕዝብና የሀገር ጥቅም የጠላቶቻችን ቅጥረኛ በሆኑት ዕኩያኑ ተደፍልቆ ሕዝብ ለሀገሩና ለራሱ ይበጃል ብሎ የሚያስበው ዘላቂ ሰላምና እድገት ሊያመጣ የሚችለውን በጎ ሐሳብ ጥሎ የዕኩያኑን ዕኩይ እርስ በእርሱ አፋጅቶ ሊያጠፋው የሚችለውን መርዘኛ ሐሳብ ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ እንዲቀበል እንዲይዝ ከባድ ጫናና ወከባ እየተፈጸመበት ንጹሕ ቀናና አዋጭ አስተሳሰቡን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገበትና እየተበረዘ እንዲመጣ ተገደደ እንጅ እንደ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዲሞክራሲያዊ (በመስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል የጋራ መግባባትና ስምምነት ነበረው፡፡ ልቡናው ለዲሞክራሲያዊ (ለመስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት ምቹ የሆነ ሰፊ መስክ አለው፡፡

በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት በመስፈኑ የሚጎዱ አካላት ካሉ ጠባቦችና የጠላቶቻችን ቅጥረኞች ዕኩያኑ ብቻና ብቻ ናቸው፡፡ ይሄንንም ጠንቅቀው ስለሚያውቁም ነው ይህችን ሀገርና ሕዝቧን የእነሱ ጥቅም ሊጠበቅ በሚችልበት መልኩ ለመቅረጽ ከፍተኛና አደገኛ ጥረት እያደረጉ ያሉት፡፡ ዲሞክራሲ በሀገራችን በትክክል ሰፍኖ የዲሞክራሲን ፍሬዎች እንዳናጣጥም ደንቃራ እንቅፋት መሰናክል የሆኑንና የሚሆኑን እነኝሁ የጠላቶቻችን ቅጥረኛ የሆኑት የአንባገነኑ አገዛዝ የወያኔና የሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ፀረ ሰላም፣ ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ኢትዮጵያ፣ ፀረ ስምምነትና ፍቅር፣ ፀረ አንድነት መርዘኛ ስብከትና እንቅስቃሴ ብቻ ነው፡፡

እኔ ከወያኔ ድንቁርናና እራስወዳድነት እጅግ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፡- የሥልጣኔ ውጤት የሆኑ ሌሎቹን የሠለጠነው ዓለም አስተሳሰቦችን ትምህርቶችንና የኪነ ብጀታ (የቴክኖሎጂ) ውጤቶችን ሲቀበል እነ አሜሪካ ይሄንን ዕውቀት ሥልጣኔ የኪነ ብጀታ (የቴክኖሎጂ) ውጤት ለማግኘት ይሄንን ያህል ዘመን ፈጅቶባቸዋልና እኛም ያንኑ ያህል ዘመን ሳንፈጅ በዚህ የሥልጣኔ አስተሳሰብ ትምህርትና የኪነ ብጀታ (የቴክሎሎጂ) ውጤት መጠቀም የለብንም አንችልም!” ሳይሉ እየተጠቀሙ ሌላኛውን የሠለጠነው ዓለም የሥልጣኔ ውጤት የሆነውን ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብን) ግን “እነሱ ያን ያህል ዘመን ፈጅቶባቸዋልና እኛም ያንን ያህልና ከዚያም በላይ መፍጀት አለብን” ማለታቸው ነው፡፡

እንግዲህ “ከደንቆሮ ታዲያ ምን ይጠበቃል?” ካላላቹህኝ በስተቀር ይሄ አይገርምም? ብዙ ምሳሌዎችን ልንጠቅስ እንችላለን በምህንድስናው፣ በህክምናው፣ በሙዚቃው (በዘፈኑ)፣ በምጣኔ ሀብቱ አስተዳደር ወዘተረፈ. በየመስኩ ያለውን ትምህርት በየ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ እየወሰድን ከተመረቅን በኋላ ወጥተን ሥራ እንደያዝን ያንን የተማርነውን ዕውቀትና ሞያ ቢቻል እንዲያውም ከተማርነውም በላይ ሁሉ ተግባር ላይ እንድናውል ይፈለጋል ይጠበቅብናል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን፣ ፍትሕን፣ የሰብአዊ መብትን የመሳሰሉ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ውጤት የሆኑትን ተግባር ላይ ለማዋል ግን “አይ! ሒደት ነው እነሱ ጋር የፈጀውን ጊዜ መውሰድ ግድ ይለናል!” ይላሉ፡፡ ሒደቱንማ ከእነሱ ዘንድ ጨረሰ እኮ! ለምን ታዲያ ሌላውን የሥልጣኔ ፍሬ ከእነሱ ዘንድ የፈጀውን ጊዜ ያህል ፈጅተን ካልደረስንበት በስተቀር አንጠቀምም አትሉም?

የሚያስፈልገው ነገር ሌላውን የሥልጣኔ ፍሬ ተምረነው እንድንተገብረው እንደሚደረገው ሁሉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን፣ ፍትሕን፣ የሰብአዊ መብትን የመሳሰሉ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ፍሬዎችንም ለእያንዳንዱ ዜጋ በሚገባ ጥርት ባለ መልኩ ተነግሮት እንዲያውቀው እንዲገነዘበው እንዲማረው ማድረግና እንዲኖርበት እንዲተገብረው እንዲተዳደርበት መፍቀድ ማስቻል ብቻ ነው የሚያስፈልገው ነገር፡፡ እንዲህ ማድረግ ቢቻልም ነበር “ዐቢዮታዊ ዲሞክራሲ” ብሎ ማቅራራት መፎከር ይቻል የነበረው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕግ የበላይነት ያለው ግንዛቤና ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስመሰግን ከመሆኑ አንጻር ችግር ያጋጥማል ተብሎ ባይታሰብም “አዲስ የሆነ ነገር” ማደናገሩ አይቀርምና ከመደናገር የተነሣ መወለካከፎች ቢያጋጥሙ ሲኖርበት ከሚወስደው የተግባር ትምህርት ሥርዓቱን ጠንቅቆ የመረዳት ዕድል ያገኛል፡፡ ለነገሩ እንዲያው ነገሩን አልኩ አንጅ እኮ ፍጹም (perfect) እንከን የለሽ የሆነ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) እማ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት የተነሣ የትም ቢሆን የለም ኖሮም አያውቅም ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በወጉ መኮነንን ለማግኘት ነው ምኞት ጥረታችን እንጅ በየትም ሀገር የሌለውን ፍጹም እንከን የለሽ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓትን ማምጣት እንችላለን እናሰፍናለን በሚል አይደለም የምንደክመው፡፡ ስለሆነም ወያኔ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ታማኝ ላለመሆኑ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ እያለ ተጠያቂነትን ከሱ ለማሸሽ ከሚጠቅሳቸው ውኃ የማይቋጥሩ ምክንያቶች በግልጽ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር እያደረገ ያለው ነገር ሁሉ አንባገነናዊና ኢፍትሐዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሆን ብሎ የሚፈጽመው ሸፍጥ መሆኑን ነው፡፡

እሽ! እስኪ እንዲያው የወያኔን ባለሥልጣናት አንድ ጥያቄ ልጠይቅ “ ያለው ሁኔታ እንዲህ ከሆነና ዲሞክራሲው (መስፍነ ሕዝቡ) ለወደፊት በርቀት የተቀጠረ ከሆነ ታዲያ እንዴት ባለ ሥርዓትና የምርጫ ሒደት ነው ይሄ በምርጫ 2007ዓ.ም. መቶ ከመቶ አገኘነው ያላቹህትን የምርጫ ውጤት ያገኛቹህት? ” ማፈሪያ ሁላ፡፡ እኔ እንዲያው በጣም የሚቆጨኝ የሚያንገበግበኝ ነገር የስንት ሊቃውንት የስንት ምሁራን ስንት ለሰማይ ለምድር የሚከብዱ የተከበሩ ሰዎችን ያፈራች የወጡባት የተከበረች ሀገርና የተከበረ ሕዝብ ስንት ታሪክ ያላት ሀገር ጠዋት ያወሩትን ማታ በማይደግሙ ጨዋነት ሥነ ሥርዓት የሚባል ነገር ጨርሶ ምኑንም በማያውቁ የነውረኞች የዋልጌዎች የስዶች የደናቁርት መንጋ እንዲህ ተረግጠን መገዛታችን ብቻ ነው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

 

Single Post Navigation

Leave a comment