The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

አዳፍኔንም መክሸፍንም ነው ያየሁበት – ዳዊት ዳባ

ዳዊት ዳባ:: Tuesday, September 01, 2015

መማር ካለብኝ እየጠየኩ; እየተከራከርኩ; እየተወቀጥኩም እማራለው እንጂ ዝም ብዬ አልማርም። ዝም ብዬም አልስማም። ዝም ብለህ ተገዛ፤ዝም ብለህ እመን;ዝም ብለህ ተከታይሁን…. ብቻ ዝምብለህን አስከትለው የሚመጡ ነገሮች ሁሉ አልቀበልም፡፡ ከመፀሀፉ ልዋስና ያዳፍኔ ባህሪዎች አድርጌ ነው የምወስዳቸው። ናቸውም። ለማዳፈን መሳርያ እንጂ ቃላትና ከመሳርያ ውጪ ያሉ ተጽኖ ማሳደርያ መንገዶች ጉልበት አይሆኑም ትክክል አይመስለኝም። እንደውም የገዘፈ ጉልበት እላቸው። ይህው አሁን ማን ይድፈር። ፀጥ እረጭ። እኔም መክሸፍን ለመተቸት በሞከሩት ላይ የመልስ ምቱን ስላየው ሳልፈራ ግን አይደለም። ግን የግድ ማድረግ ነበረብኝ። የመጀመርያው ምክንያቴ መፀሀፉ ውስጥ ዋና የሆነውን ቁምነገር እኔ በተለየ አቅጣጫ የተረዳሁት ወይ አየው የነበረ ስለሆነ ነው።  በዋናነት ግን ማጥቃት ስላለበት ነው። የተለመደ እየሆነ የመጣው ጦር ውርወራ ስላለው ነው።

 

“እንዴት” የሚለውን መንደርደርያ ገና አብዘተን በማንጠይቅበት ሁኔታ ሌሎች በሁሉ ነገሮች ላይ ጠይቀው መልሶች አሏቸው። ዛሬም መልስ መፈለጉን በርትተውበታል። እንዳንቀደም  ካደረጉን ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋንኛው “እንዴት” ሲሉ አብዝተው የሚጠይቁ በመሆናቸው ነው። ጠቃሚ ነው ጎጂ የሚለው እንዳለ ከዶሮ ጋር እንዴት ፍትዎት እንደሚፈፀም ሁሉ መልስ አለ። እንዴት ያሳ መረቅ እንደሚሰራ ፤ የተሰበረ ቦርጭማ እንደሚጠገን፤ የእግር ጠረን መከላከል እንደሚቻል። አገዛዝን መገርሰስ እንደሚቻል። ብቻ ለሁሉም ነገሮች አጥጋቢ ካነሰም መነሻ የሚሆን መልስ ሰርተዋል። ይህ የሚስረዳን አብዝተው ‘እንዴት” ሲሉ መጠየቃቸው ብቻ ሳይሆን፤ መፍትሄ ፍለጋ ላይ፤ ለአዲስ ሆነ ለተሻሻለ ፈጠራ ባጠቃላይ ለሁለንተናዊ የሰው ልጅ እድገት  መነሻም ሚስጥር አድርገው እንደወሰዱትም ነው።

ወደኛ ሲመጣ በዋናነት  “ማወቅ”፤ “እውቀት” አድርገን የወሰድነው፤ ጌዜ ወስደን ልንመረምረው፤ ልንወያይበት፤ ልናነብበት፤ አልፈንም ቡጢ መሰናዘር ድረስ የሚመስጠን ታሪክ ነው። “መቼ?”፤ “ማን?”፤ “እንዴት”፤ “ምን”  ከሚሉ መጠየቂያዎች ከተነሳን ሁሌም በሚሰኝ ደረጃ ስለዛሬ ወይ ስለነገ ሳይሆን  ስለትናንትና ነው።  ለዛሬና ነገ መፍትሄ ከትናንት መነሻ ማድረጉ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ ካልተቀዳ ማለታችን  መፍትሄ ፍለጋ ላይ ከባድ ችግር ሆኗል። ይህ በራሱ ክፉም ከባድም ችግር ሆኖ እያለ የባሰ የከፋ የሚያደርገው አብዝተን ከትናንት ጋር ፍቅር ላይ በመውደቃችንና  ዛሬን ወይ ነገን አናውቀውም። በቂ በሚሰኝ አኳሐን ጠይቀንበት ችግሩም መፍትሄውንም ልንረዳው ሆነ ሊታየን አልቻለም። ከሞከርንም መፍትሄ ብለን የምንሰራው ወደፊት ሊያስኬደንና የማያዳግም መሆን አይደለም አንድ ክረምት ሊያሻግረን አልቻለም። እዚህ ላይ ከትናንት ስላልተነሳን ነው የሆነ ጊዜ ላይ እንግዳ በሆነው ሶሻሊዝም የተጠመቅነው የሚል መከራከርያ ዋና ሆኖ መምጣቱ አይቀርም። እሱም ቢሆን ሲጀምር የኛ አይደለም። ይባስ ብሎም ከትናንትና የተቀዳ ነው። ለዛሬና ለነገ በተገቢው ከታሰበበት አይደለም ከሌላ አገር የተቀዳ ከኛም ከትናንት ልንቀዳው ወይ ፍፁም ተመሳሳይ ሆኖ ልንጠቀምበት የሚቻለን መፍትሄ  የለም። “ ሶሻሊዝም የተንኮታኮተበት አንዱ ምክንያት አንዴ የሆነ ጊዜ ላይ የተቀመጠ መፍትሄ ሁሌም ሁሉም ቦታና ችግሮች ላይ  ይስራል የሚል ይዘት ስላለው ነው።

እዚህ ጋር ነበርኩ። ስጨምር ስቀንስ እያለው ነው መስኮቴን አንኳክቶ ባልንጀራዬ መፀሀፉን ያዋሰኝ።  ከዛም ማንበብ ነው የቀጠልኩት። ከላይ ያለው ሀሳብ በወረቀት ለማስቀመጥ እንዳሰብኩት ቀላል ባይሆንልኝም የዛሬ አይደለም። ውስጤ ብዙ ቆይቷል። በተለያየ መንገድ ስገለፀው የነበረ ነው። ታዲያ አዳፍኔን ይህን ሀሳቤን ይመታዋል። ይገለባብጠዋል።

“በዋናነት የመክሸፍ ምንጭ ሁለት ይመስለኛል። አንደኛው ትናንትን አለማስታወስ ሁለተኛው ነገን አለማሰብ።” ገጽ 61 ሁለተኛ ምእራፍ ላይ።

እዚህ ላይ ነገን አለማሰብ የሚለው ምክንያት ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መፀሀፍ ትኩረት ያደረገውና አጉልቶ የሚያሳየን ትናንትን አለማወቅ የሚለውን ነው።  እኔ ዋና መሆን አለበት ብዬ የታሰበኝ የነበረው ደግሞ  ዛሬን

አናውቀውም ነው። ነገንም እንዲሁ። መፀሀፉ ደግሞ ዛሬን ብቻ ነው የምናውቀው ነው የሚለው። ለዚህ ነው ገለባብጦብኛል ያልኩት። የተራራቁ በቀላሉ ሊስማሙ የማይችሉ ልዩነቶች ሆኑብኝ። እንዳናምታታ ትናንት መታወቅ የለበትም አይደለም ክርክሬ። አንድ ህዝብ ትናንትናን ማወቅ ያለበት ምን ያህል ነው? ስንል እኛ የሚያስፈልገንን ያህል አይደለም  ከበቂ በላይ ትናንትን እናውቀዋለን ነው መልሴ። ትናንት ለመኖር ግድ እንደሚሉት አየርና ምግብ አይነት አድርገንዋል ነው። ትናንት ሙሉ ጉልበታችን፤ እውቀታችን፤ ጊዜያችን የሚጠፋበት ሆኗል ነው። ዛሬን በትንሹ ላዛውም በዜናና በመተረክ ደረጃ ነው

የምናውቀው። ያሉ ችግሮች ላይ መፍትሄን ከመስራት አኳያ ገና አናውቀውም ነው። ነገንም እንዲሁ።  ይህ የሆነበት ምክንያት ሁለንተናዊ በሆነ ሁናቴ በትናንት በመያዛችን ነው የሚል ነው መደምደሚያዬ።

በዛ ላይ ትናንትን ከዛሬም ከነገም በተሻለ የምናውቀው ቢሆንም አልፈየደም። ከባህሪው ላዛሬና ለነገ ልንጠቀምበት የምንችለው  መፍትሄ አናገኝበትም። ካለም እጅግ በጣም ትንሽ ነው። ዛሬ መፍትሄያችንን የሚሻው ችግር ከትናንትን መሰረት ያደረገ ሲዋረድ የመጣም ቢሆንም እንኳ። ሂደት ነውና ችግሩ  ዛሬ የተለየ ባህሪና ቅርጽ ይይዛል። ስለዚህም ዛሬ ችግሩ ያለውን ይዘት ባህሪና ቅርጽ ዋና ትኩረት በማድረግ መስራት ነው ትክክል የሚሆነው ነበር እሳቦቴ። ዘላቂነት እንዲኖረውና የማያዳግም እንዲሆን ደግሞ ነገን ግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ መስራቱ   ነው ትክክለኛ አካሄድ አድርጌ የወሰድኩት። በነገራችን ላይ ዋና የሆነውን የፖለቲካ ልዩነት በተመለከተ በዛም በዚህም በኩል ያሉት ችግሩ ትናንትን አለማወቃችን ነው በሚለው ይስማማሉ። አለመግባባቱም መፍትሄውንም ያከበደው ትናንት ስለማናውቅ፤ ስለምንክድ፤ማመን ስለማንፈልግ፤ ስለምንዋሽ ነው በሁሉም ጎን ያሉ የሚያቀርቡት መከራከርያ። ትናንትን በራሳቸው አረዳድ ማየቱ እነዳለ ማለት ነው። ስለዚህ በታሪክ ላይ አንድ አይነት የጋራ ግንዛቤ ላይ መድረስ ካልተቻለ ወይ ንቅንቅ። መቼም ደግሞ የምንደርስ አይመስለኝም።

አለመሳሳቴን እርግጠኛ ለመሆን በመጀመርያ ያደረኩት በመፀሀፉ ትናንት አለማወቅ ምክንያቶች ሆኖው የቀረቡ ጉዳዬች መመርመር ነበር። መፀሀፉ በተናጠል በግለሰብ ደረጃ ማየት አለው። በግለሰብ ደረጃ ዛሬን አይደለም ነገም ላይ ችግር የለብንም። ሆዳችንን በመቀነት ቋጥረን ለነገ ቅሪት የምንሰበስብ ብዙ ነን። ችግሩ የጋራ ለሆኑ ጉዳዬች አገር፤መብት፤ መልካም አስተዳደር፤ መልካም አገልግሎት፤ ፍትህ፤ እኩልነት……የመሳሰሉ በጋራ ካልሆነ በቀላሉ የማንነቀንቃቸው ችግሮችና መፍትሄዋቻቸው ላይ ነው። ዘሬ መሀይም የሆነው። እንዴት?፤ ምን? መቼ?፤ከየት፤ ማን?፤ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ? ለሚሉት መልስ የለንም። መፈለጉም ጠቃሚ ሆኖ የታየ አይመስልም።

ትናንትናን ማወቁ “እውቀት ነውና የማሰብ ችሎታችንን በማሳደግና በማስፋት፤ በማነቃቂት፤ የችግሩን የሗላ ታሪክ አጥንቶ በተገቢው ለመረዳትና ዛሬ ላለብን ችግርና ተሻግረንም ለነገ ሁሉ መፍትሄ ለመስራት የሚኖረው ጠቀሜታ አሌ የማይባል ነው። በዚህ መንፈስ የቀረበውን ሙሉ በሙሉ እስማማበታለው። ዛሬና ነገን እንደሌሉ አድርገን ከሰጠነው ቦታ አኳያ ግን ጥቅሙ አይመጥንም። ትናነት መኖሩ በራሱ የዛሬ ቸግር ላይ መፍትሄ ለመስራት ሳንካ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች ስንደምር ደግሞ ጥቅሙን የበለጠ ያሳንሰዋል።

በመፀሀፉ ትናንተናን ባለማስተወሳችን በሚል ምሳሌ ተደርገው ከቀረቡት ምክንያቶች አንዱን ላንሳና ለሌሎቹም መልስ የሰጠሁበትን መንገድ ላስቀምጥ።

እናት ኢትዬጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤

ባንዳ ነግሶ አርበኛ እንዲሳደድና እንዲያዝን የሆነው ትናንትን ካለማወቅ አይመስለኝም። በጊዜው ትናንት ዛሬ በነበረ ጊዜ ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ አለመቻል ነው ችግሩ። ይህ ድርጊት ነገ ላይ የሚያስከትለውን ጦስ ባለማጤን የተሰራ ስህተት ነው።  እንደውም ንጉሱ በግል ከገቡበት ችግር አኳያ መውጫ መፍትሄ ወደሗላ ሄደው ከትናንትና  ያሰቡና ምን አልባትም የተመከሩ መሆኑ ለስህተቱ ምክንያት የሆነ  ይመስላል። አርበኞቹም ያኔ ዛሬን ቆም ብለው አስበው ቢሆን ኖሮ ጥቃቱን በተሻለ መከላከል ወይ ማስቀረት ይችሉ ነበር። ትናንት መንግስትና ንጉሱ ላይ በነበረ እሳቦት መዘነጋተቸው ነው ያስጠቃቸው። ባጠቃላይ ትናንት ችግር ከነበረ መፍትሄ ካልተሰራለትም መፍትሄው ስህተት ከሆነም፤ በቂም ካልሆነ ትናንት

ዛሬ በነበረበት ጊዜ የመስራት ችግር እንዳለን እንጂ የሚያሳየው ክትናንትና ወዲያን አለማወቅን አይደለም። ችግሮች ትናንት የጀመሩ የትናንት መሰረት ይኑራቸው ዛሬ ነገን ሁሉ ግምት ውስጥ አስገብቶ በጊዜው መፍትሄ ሊሰራላቸው ይገባል። ለዛሬ ከተላለፈ የትናንት መሆኑ ቀርቶ የዛሬ የኛ ያሁኖቹ ችግር ነው። ዛሬም ነግን እያሰብን ካልሰራነው የልጆቻችን ችግር ይሆናል። ለልጆችን ካወረስነው ደግሞ መፍትሄ  ለመስራት ቁርጠኝነቱና መስራት የሚያስችለን እውቀቱ አለን የለንም ከሚለው ጋር ነው ቀጥተኛ ቁርኝቱ።

ትናንትናን እንጂ ዛሬን ላለማወቃችን አሳማኝ ምሳሌዎች።

እስከዛሬ በስነ ፅሁፍ፤ በኪነ ጥበብ፤በኪነ ስእል ስራዎቻችንን በሙሉ አይቶ ምን ያህሉ ስለዛሬ፤ ምን ያህሉ ስለነገ፤ ምን ያህሎቹ ደግሞ ስለትናንት ያወራሉ የሚለውን ማየት ይቻላል። ማወቅ ያለብን ዛሬን እንደትናንት መተረክ ዛሬን ማወቅ በጭራሽ አይደልም። የዛሬን ችግር ባግባቡ ተረድቶ ሙሉ የሆነ መፍትሄ ምን አልባታም ካንድ በላይ  ማስቀመጥና የተሻለውን መርጦ ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለም ስራውን ዛሬ መጀመር ነው ዛሬን ማወቅ።

ሌላው ጥናት ነው ሊባል ባይችልም  ለስምንት አመታት ሻይና ቢራ እያስተናገድኩ የብዙ ደንበኞች የሚወያዩበትን፤ የሚከራከሩበትን፤ የሚጣሉበትን፤ የበዛ ጊዜ የሚሰጡትን ጉዳይ ለማየት ሞክሬያለው። ስለአገርና ህዝብ ከሆነ   እጅግ የበዛውን ጊዜ የቀደመ ታሪክ ላይ መሆኑን ተገንዝቤያለው። በተመሳሳይ ዛሬ ላይ የየለትና በቅርብ መነጋገርያ በሆኑ አንኳር ጉዳዬች ላይ እንደምንወያይም እንዲሁ። ጠቅለል ሲደረግ ዛሬ ላይ በትንሹ መፍትሄ ድረስ በማይሄድ  ነገን ላይ እስከጭራሹ እንደማንነጋገር ነው የተረዳሁት። ስለትናንት መወያየቱ ከድህንነት አኳያ ችግር ስለሌው ብቻ ግን አይደለም። ውይይቱ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችለው እውቀት ሁሉም አለኝ ብሎ ስለሚያስብ በእርግጥም ስላለው ነው። የግድ የታሪክ ምሁር ያህል ሁላችንም ማወቅን አያሻም። አይፈልግምም።

ለነዚህ ረጅም አመታት እኔም ድርሻ ያደረኩበት ውይይት ሁሌ ትናንት ላይ ብቻ መሆኑ ስለመረረኝ የሆነ ጊዜ ላይ ስለትናንት ማውራቱ ብቻ ፋይዳ የለውም። ከዛሬ ጀምሮ መፍትሄ ድረስ በሚሄድ ስለዛሬና ስለነገ እንወያይ የሚል ሀሳብ አቅርቤ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። መነሻ የሚሆን ሀሳብ ለማቅረብ ቢሞከርም ውይይቱ ብዙ አልሄድ አለ። ጊዜ አልበቃው ይል የነበረ ውይይት ዝምታና መፋጠጥ ስለበዛበት ቀስ ብሎ ወደድሮው ልምድ ተመለሰ። ይህ የሆነው በትንሹ ካስር አመት በፊት  ነው።

መንገድ በመንገድና ህንፃ በህንፃ ሆነች ተብላ ብዙ የተወራለትን አዲስ አበባ ላይ ለዚህች ትንሽ ስራ የብዙ ዜጎችን ሂወት በእጅጉ ተመሳቅሏል። ብዙ እውቀት፤ገንዘብና ጉልበት ፈሶበታል። መነሻ ፍላጎቱማ ሀሳቡም ዛሬ ነበር የተባለ ችግርን ለመቅረፍ ነው።  ባጠቃላይ ለነገ አይደለም ላዛሬ ችግር በማይሆንበት መንገድ ግን አልተሰራም። ለምን ማፍረስም መስራትም እንደጀመሩ በቅጡ እንኳን አያውቁም ነበር። አለማወቃቸውን እነሱም እያመኑ ነው። ትራፊክ ተጨናነቀ፤ የሚኪና አደጋ በዛ፤ ማቆሚያ የለም። ታክሲዎች ለመጫንና ለማውረድ ማቆም እንዳለባቸው እንኳ አልታሰበም። አረንጓዴ ቦታ አልተተውም። የሚባለው እውነት ከሆነና በሐይለስላሴ ጊዜ የተሰራ እቅድ ተጠቅመው ከሆነ ለምን ይህ እንደተፈጠረ ችግሩን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ያው ተሰሩ የተባሉ ህንፃዎች መንገዶቹ ጫፍ ላይ ተደርድረዋል። ለማስተካከል እንደጋና ማፍረስ፤ እነደገና ማመሳቀልን ይፈልግብናል ማለት ነው።

አሜሪካኖች እኛ ዜግነት ለማግኘት አጥንተን የምንፈተነውን ፈተና ለሙከራ ተፈትነው ብዙዎቹ እንደማያልፉ ሲነገር ሰምቻለው። ለተላላቅ ሰዎቻቸው መዘክር፤ መታሰቢያ፤ ላይብረሪ ቢሰሩ የተሰራለትን ግለሰብ ጋር ተያያዥነት ያለቸውን ታሪክ መሰብሰብ ትንሿ ሀላፊነት ነው። እነዚህ ማእከላት ወና ትኩረት አድርገው የሚሰሩት ስለዛሬና ነገ ነው።  ሌላ ብዙ አመት ደግሞ ታክሲ እየሰራው ብዙ አሜሪካኖችን አመላልሻለው። ብቻቸውን ሆነው በስልክ ወይ ካንድ በላይ ሆነው ሲሳፈሩ የሚወዩበትን አርስትና ይዘት ምን እንደሆነ ለማወቅ ሆን ብዬ አድምጫለው።  አርእስቱ ቢለያይም ስለ ትናንትና ታሪክ ሲያወሩ የሰማሁበት ጊዜ እጅግ በጣም ውስን ነው። አብዛኞቹ ሰረተኞች ስለሆኑም ይሆናል በስራ ደረጃም ሆነ ከስራ ውጪ ባለ ጉዳይ ላይ መፍትሄ ድረስ በሚሄድ እንደውም ብዙውን ጊዜ መፍትሄ ላይ እንደሆነ ግን በእርግጠኛነት መናገር እችላለው።

መጻፌ ካልቀረ ብዬ ነው እንጂ እንደሁሌው ከዚህ በላይ የፃፍኩትን ሁሉ እራሴን ችዬ ብጽፍበት እችል ነበር።  ይሻል የነበረውም እሱ ነው። በዋናነት አዳፍኔ ላይ ለመፃፍ ምክንያት የሆነኝ ከዚህ በታች የማስቀምጠው አንድ ገፅ ላይ ያለች ሀሳብ ብቻ ነች። ቁንፅል ብትሆንም  ትልቅ ጉዳይ አድርጌ ወስጃታለው።

‘እራሱን እንደነጻ ስው፤ እንደግለሰብ ማየትና በዚያው መሰረት መወሰን የማይችል ፍጡር ከአየራልንድም ይምጣ ከስኮትላንድ ፤ ከኢትዮጵያ ይምጣ ከኬንያ ወይም ከሱማልያ ገና ዝቅተኛ የሰውነት ደረጃ ላይ ያለ ነው።ገና የራሱ ባለቤት አልሆነም ማለት ነው። ወደግለሰብነት ደረጃ ላይ ያልደረሰና የግለሰብነት የሀላፊነት ባለቤትነትን ያልተረዳ በሰውነት ደረጃው ዝቅተኛ ነው። አስከትለው ስልጣን መቼ ትለቃለህ ተብሎ ደንግጦ የሞተው መሪ ሲጠየቅ ድርጅቴ ነው የሚወስነው ሲል የመለሰው ላይ ያብራራሉ። በማስከተል “ይህንን ያልተማረ ወይም ያልተገነዘበ ግለስብ ከእንሰሳት ደረጃ አልወጣም። ነግረ ግን በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩና የሚማሩ ሰዎች በጎሰኛነት ሕመም ተይዘው ማደግና መሻሻል የሚባሉት ነገሮች በየት በኩል ግብቶ ቦታ ያገኛል።” እያሉ ይቀጥላሉ።

በጥንቃቄ እንዳያስጠይቅና አሻሚ ለማድረግ አስበው እሳቸው በደብተራ አፃፃፍ በሚሉት ነው ያስቀመጡት። ለነገር ከሆነ የዝንብ ጠንጋራን ለሚያውቅ አይደለም ለማንም ቀና አሳቢ ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ግን ግልፅ ነው። ለነገሩ መለስ ዜናዊም ቢሆን ያን በማለቱ ተሳስቷል ሊባል ይችላል እንጂ ከሳቸው እኩል ሰው ነው። ዝቅ ብለው እሳቸውም አባባሉን

ብልጠትና ውሸቱን እንደሆነ ገልፀዋል። ታዲያ ብልጥ ስለሆነ ነው ከሰው ያነሰው።  ወይስ ስለዋሸ?። እዚህ ላይ መለስ ማደነጋርያ ሆኖ ነው የገባው። ጎሰኛ አስተማሪና ተማሪዎቹም እንዲሁ።

ለማንኛውም ጎሰኛ የተባሉት መምህራንና ተማሪዎች ለዚህ ደረጃ የደረሱት ሆነ ሂወታቸውን እየኖሩና እየመሩ ያሉት እራሳቸውን ችለው እያሰቡና እየወሰኑ ነው። እኔ ነበርኩ የማስብና የምወስንላቸው መቼም አይሉም። በጎሳ ያስባሉ ሲባልም ጭንቅላታቸውን የሸረሪት ድር በመሰለ ነገር አገናኝተው አንድ ትልቅና ውስብስብ አይምሮ ፈጥረዋል ለማለትም አይደለም። ይህ ቢሆንም ምንኛ ድንቅ ነበር። ኢትዬጵያ አይደለችም አለም በታደለች። ስላሴዎችን መሰሉ። ለማለት የተፈለገው በኢትዬጵያ ስም ብቻ ካልሆነ ትናንሽ ማንነቶችን ለምን ይፈጥራሉ ነው። የሚጋሩት የተለዩ ችግሮች ቢኖርም እንኳ በኦሮሞነት ወይ በትግሬነት ችግርም ቢኖርባቸው መናገር ወይ ለመሰማት መተባበር የለባቸውም ነው።

ዛሬ በወያኔ ኢሕአዲግ ስርአት ነፃነቴን አጥቻለው የምንል ግለሰብ ወይስ እኛ?። እኛ ነን። የጋራ ችግረችንን አውቀን፤ መፍትሄው ስንሰራ ተባብረንና መክረን አስማምተን ነው። ታዲያ ዝቅተኛ የሰውነት ደረጃ ላይ ነን ማለት ነው?።ትግሉ ውስጥ ድርሻ ያለው ሁሉ በግሉ ችግር አለ መፍቴሄም ይሻል፤ ለዚህም ትግሉ ላይ የድርሻዬን ማበርከት አለብኝ ብሎ በደንብ አስቦበት ውሳኔ አድርጎ ይሳተፋል። ከሌሎች ጋር አስተዋፆውን ያስተባብራል። ታዲያ በሰውነትህ ያንስክ ነህ የሚያስብለው የትኛው ተግባሩ ነው። እኩል የተሻለስ የሚያደርገውስ?። ሰው መህበራዊ ፍጡር የሆነውስ በምንድን ነው?።

ጎሳም እንደቤተሰብ፤መንደር፤ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ያንድ አገር ህዝብ፤ ጥቁር ህዘብ፤ ጋናዊ፤ አረብ፤ክርሲቲያን…ማህበረሰብ ነው። ልዩነቱ በብዛቱ፤  በቆዳ ቀለሙ፤ በእምነቱና በሚኖርበት ቦታ ነው። ሁሉም ከግለሰብ በላይ የሆኑ የሰዎች ስብስብ ነው። እንደተለያየ ማህበረሰብነቱ ልዩ ባህሪ ያላቸው የጋራ ችግር ይኖረዋል። መጨፍጨፍ አድሎ መንቋሸሽ ….ሊኖርበት ይችላል። ወይ አለ ብሎ ካመነ  በጋራ ሆኖ  ቢታገል፤ ድምፁን ቢያሰማ፤ ቢቃወም፤ ቢዋጋ ጭምር በእንሰሳት ደረጃ ያለ የሚያደርገው ምኑ ነው። ግለሰብ ሆኖ የዚህ የዛ ስብስብና ማህበረሰብ ሳይሆን የሚኖርስ ማነው። በቤተሰቡ ላይ የተቃጣን አደጋ በተለየ የማያይ አለ። በቤተሰብ ደረጃ የተለየ ፍላጎትስ የሌለው። ታዲያ  ፀሀፊው ከኔ  ከሰው ጋር እኩል አይደሉም ሲሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው?።

ጎሳ ምንድን ነው፤ ጎሳስ ማነው የሚለው እንዳለ ጠቅለለል ባለ ሌኔ ይህ እነሱ ማለት! አራት አይን ያላቸው።እጃቸው ወገባቸው ላይ ያለ።ጅርባቸው ላይ አምስት ቀንድ ። አረንጓዴ ግራጫና ሀምራዊ ቀለም ያላቸው። ጭራቅ አይነት አስፈሪ አውሬዎች ናቸው የሚለው ገለፃ ተሻሽሎ መጣ ነው ።ከዚህ ደረጃ ተነስቶ ተሻሽሏል ማለት ለፈለገ ይችላል። ለኔ ግኔ ከኛ በላይ ጥሩ አሳቢና የተማረ ኢትዬጵያዊ የለም ከሚሉ።  አሉልን ከምንላቸው አንዱ አይደለም ሁለቱም ፕሮፌሰሮች መስፍን ወልደማርያምና፤ ጌታቸው ሀይሌ ይህን ተራኪዎች መሆናቸው አሳፍሮኛል። በቃ አሁን ሴጣን የሚለውን አውሬ ነው። ነገር ግን ሰው የሚመስል በሚል ነው ያሻሻሉት። ይህ ክሽፈት የተባለው ምን ያህል የከፋና ለምን እንደከሸፍን ምንጩንም ያየሁበት ነው።

ለነገሩ ይህ ልዩ ፍጡር ቆንጆ ገፀ ባህሪ ለልጆች ይወጣዋል። የልጆች ስለሆነና የኦሮሞ ህዝብ የተሳለበት ስለሆነ ጥሩ ገፀ ባህሪና  ብናላብሰው ጀግና ብናደርገው በልጆች በፍቅር የሚወደድ ካርቱን ይወጣዋል። ለነገ የተሻለ ዜጋ በመፈጠሩም አስተዋፆ አለው። ፍልሙ ሲጀምር አስገራሚ በሆነ ሁናቴ ባህሩ ይናጥና ከውሀ ውስጥ አውሬው ሲወጣ እናደርጋለን።

ግጥም አድርጌ እንደ ኦሮሞ አስባለው። እወስናለው። ነግር ግን እንደ ኦሮሞ ብቻ አላስብም። እንደ ዳዊት አስባለው። እንደ ዳባ ቤተሰብ፤ እንደኮንጎ ሰፈር ልጅ፤እንደጥቁር፤ እንደአፍሪካዊ አስባለው። እንደጁም አስብ ነበር። አሁን እንደ ፍልስጤምና እንደአፋር አስባለው እወስናለው…..። ፍትህ የተጓደለበት የተጨቆነ፤ የሚገደል.. ባለበት ሁሉ ሳልፈልግ በመንፈስ እዛ አለው። ስለዚህም ያ አውሬ እኔ ነኝ። ከርሶ በሰውነቴ አንሳለው ማለቴ ነው። እንደ ኢትዬጵያው የሚለውን አውቄ ነው የተውኩት። ሰው ለመሆን የግድ እንደ ኢትዬጵያዊ ማሰብ የለብኝም። ኢትዬጵያዊ ስለሆንኩ ግን ማሰብን ፈልጌ የምተወው ፈልጌ የማደርገውም አይደለም።

ሐይለስላሴ የናታቸውን ማንነት አልደበቁም። የደበቁት ታሪከኞች ናቸው። በይበልጥም የንጉሱ ታሪክ ላይ የፃፉ። ያም ሆኖ ይህ ተደበቀ ታወቀ ይህን ያህል ፋይዳ የለውም። አሳሳቢው ሌላስ ስንት ነገር አውቀው ደብቀውናል የሚለው ነው። የየጁ

አሮሞዎች ኢትዬጵያን አስተዳድረው ነበር የሚል አዲስ ታሪክ ብቅ እያለ ነው። እዚህ ታሪክ ላይ ትልቁ ጉዳይ ኦሮሞዎች መግዛት አለመግዛታቸው ሳይሆን ወይ ጎንደር ማእከል መሆኑ አለመሆኑ ወይ ስፋቱ አይደለም። ያስተዳደሩት ለምን ቀበሌ አትሆንም ዋናው ቁምነገር። እውነት ከሆነ ለመቶ ሀያ አመት በስምንት ገዳ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል። ይሄ ለኢትዬጵያዊያን እጃችንን ጭንቅላታችን ላይ አድርገን የሚያስጨበጭብ ብቻ ሳይሆን የሚያስጮህን ነው። ሀውልት ሊቆምለት የሚገባስ ይህ ነበር።

ከዚህ በታች ያሉትን ቁም ነገሮች በኦሮመነት አይደለም በጊዜው የወሰድኳቸው። በኢትዬጵያዊነትም አይደለም።   በጣም ልጅ እያለው ለክረምት አያቶቼ ጋር ሄጄ የተለዩ ስለሆኑ ወድጃቸዋለው። እያደኩ ስሄድ ደግሞ እጅግ ጥሩ፤ ትክክለኝ ነገሮች አድርጌ አስቤያቸዋለው። ስለዚህም ውስጤ ትልቅ ቦታ ይዘዋል። አሁን ግን በኦሮሞነት አስቤና ወስኜ እፅፋቸዋለው።

ፈታና ደስታ ያለበትን ጊዜ መርጠው በሰከነና ስርአት ባለው መልክ አንድን ችግረ ከስሩ መርምረው መፍተሄ መስራት እንደሚችሉ አይቻለው። ችግሮችን ለሌላ ጊዜ መቆየት ድረስ በግዚያዊ መፍትሄ ሰርተውለት ጊዜ ወስደው አክርመው ማየት እንደሚችሉና በመጨራሻ መፍትሄ እንደሚሰሩለትም እንዲሁ። ዛና የሚያደርገው ጊዜ ከሶስት ወር በሗላ የታህሳስ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ ሊሆን ይችላል። ከያዙት ቁምነገር ጋር የሚያያዙና የሚመሳሰሉ ድንቅ ታሪኮች፤ አባባሎች፤ ቀልዶች ሁሌም በገፍ አላቸው። ጉዳዬ የግለሰብ ከሆነ ባለጉዳዬች እኩል መናገር ያለባቸውን ሁሉ እንዲናገሩ፤ እንዲከራከሩ ይደረጋል። እኔም፤ ሴቶች ልጆችም ውጡና ውጪ ተጫወቱ አልተባልንም።

ለተፈጥሮ መቆርቀርና መውደድ በገዘፈ መንገድ አይቻለው። ፀሎታቸው ሁሉ ስለተፈጥሮ ደህንነት ነው። ለደስታና ለዝና ሲሉ ለገደሉት እንሰሳ አምላክን ለመለማመን የፀሎትና የልመና ዝግጅቱ አንድ ዲል ያለ የሀብታም ሰርግ አድርጋችሁ ውሰዱት። ስለዚህ ዝም ብሎ መግደል ክልክል ነው። ውሻ ባጮጮሁ ወይ እራት ላይ መረሳቱን ካስታወሱ ለሊት ላይ ተነስተው ምጣድ ይጣዳሉ።ለውሻ ምግብ ማዘጋጀት የሰው እኩል የሁል ጊዜ ስራ ነው።  እንክብካቤው ስላላቸው ዶሮዎች በየቀኑ እንቁላል ይጥላሉ። በቀን ሁለቴ የሚጥሉ ሁሉ ያየው ይመስለኛል። በስራ ላይ የዋለ እንሰሳ የተለየ እንክብካቤ አለው። ፈረስ በፍቅር ይወዳሉ። ይንከባከባሉ። ያስውባሉ። እንሰሳትን ለስራ ስትጠቀምም ሆነ ስታግድ ለመመለስና ለመግራት ያህል እንጂ መደብደብ ሁሉንም ጨርቃቸውን ነው የሚያስጥላቸው። እንዲህ አድርግህ እንደመታህው በሽታ ወይ አምላክ ይምታህ ብሎ ሊያስረግምህ ይችላል። ሲያውሱ እንዳትመታብኝ፤  በተለየ ለብቻው እንድትመግበው ሲሉ ማሳሰብ ሁሌም የማይረሱት አደራ ነው። እረኛ ሆነህ ከብቶቹ ታከው የማይበላም ቢሆን እያደገ ያለ እፀዋትን ካጠፉ ያስገስፃል። ሲያደርጉ አይቼ ግራር ከስሩ ስቆርጥ አላፍ ገበሬ ዠልጦኛል። ከቆረጡ በምትኩ ወይ መልሶ ማደግ አለበት ይላሉ…..።

ለህፃናት ለሴቶችና ለአቅመ ደካሞች ከለመድኩትና ከማውቅ በተለየ እንክብካቤ ያደርጋሉ። ህፃናት በፍቅር ይወዳሉ። ዱላ እጅግ ያልተለመደ ነው። ህፃናቱ ከፍ ሲሉ ሴቶችም ነፃነታቸው በተሻለ ከኢኮኖሚ ነፃነት ጋር ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ መቼም ይገባናል። ከቁም ነገር ቆጥረውን በየቀኑ ቁጭ አድርገው ህፃናትን ያወሩናል። ያጫውቱናል። በመጠየቅና በተረት፤ ታሪክ በመንገር ያስተምራሉ። የሚለብሷቸው ልብሶች  አብዛኛው ከተሜ ከሚለብሳቸው በላይ ወጋቸው ውድ ነው። በነሱ የፍትህ ሰስርአት ሽምግልና ልጆችም ሴቶችም እኩል ይዳኛሉ። ቤተሰብ ሲያወራ እንደሰማሁት ትንሽ መሬትና ጥቂት ከብቶች የነበራት አርበኛዋ አያቴ ያልወለደቻቸውን ሀያ ስድስት ህፃናትን አሳድጋለች።

ባህላዊም ቢሆን የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁስ ድንቅ የጅ ስራ ውጤቶች ናቸው። ዱላ መያዝ እንወዳለን። ዱላው ዝም ብሎ ከዛፍ ላይ ተቆርጦ የሚያዝ እንዳይመስለን። በፍለጋ ለማዘገጃት የሚወስደውን ጊዜ  የሚደረግለትን እንክብካአቤ ብታዩት ሁልሽም በኖረኝ የምትይው ነው። ከልብስ ከለር ጋር አስማምቶ ለመያዝ በአይነት ነው ያላቸው። የተለየ አይነት የበዓላት አከባበር አላቸው። በተለይ መስቀል። አዲስ አመታቸው ነው መሰለኝ። በአሉን ሰዎች ብቻ አይደሉም እንሰሳቱም ናቸው የሚያከብሩት። አንዱ ችቦ አዲስ አበባ ደመራ ብለን በየቤታችን የምንሰራውን ያክላል። መሸከም ስለማልችል እሱ በትከሻ ይዞ እኔ የጎረምሳውን ልብስ ይዥ ነው በመከተል ችቦው የኔ የሚሆነው። ጅራፉ አራት መአዘን ነው።  የሚተኩሱት ወደፊት ወደላይና ወደታች ነው። ከፈለጉ ወደላይ ወደታች ወደጎን አከታትለው ሶስቴ ይተኩሳሉ። ይህቺ በሁለት ክረምት በልጅነቴ ካየሗት በትንሹ ነው። የኖረበት ብዙ ሊል ይችላል።

የኦሮሞ ህዝቡ ድሮም ዛሬም ቅሬታ ይዞ ነው የሚኖረው። በኔ ግንዛቤ አናኗሩ የዚህ አይነት የስልጡን ህዝብ ነው።  ቅሬታው  ኑሩ የተባልነው ወደሗላ የሚመልስንና ሗላ ቀር ነው የሚል ነው። የተሻል ካላችሁ አምጡ። አለበለዛ ተውን የራሳችን ይሻለናል ነው። እውነታቸውን ነው ብግድ ካልኖራችሁ ስንለው የነበረው አሁን እኛም የከሸፈ ነው እያልን ነው። ያኔ እኔ የማውቃቸው በሙሉ እራሳቸውን ኢትዬጵያዊም አድርገው ነው የሚያዩት። አርበኛ፤ወዶ ዘማቾች፤ ሚሊሻ፤ ወታደሮች ብብዛት አሉበት። ለዝች አገር ነብስና አካላቸው የገበሩም ብዙ ናቸው።

ለፈለገ መፃፍን መተቸትን አልከለክልም። ዳዊት ይህን ሰለፃፍክ ወይ ይህን ወይ ያንኛውን ስላልክ ወይ ስላደረክ ከኔ ወይ ከኛ ታንሳለህ ሊለኝ ለሚፈልግ  ሁሉ መልሴ አንድ ነው። ይህንን ለናትህ ንገራት። ለምን እራሱ አምላክ አይመጣም። በተመሳሳይ አንተ ዘረኛ ነህ ለሚለኝ ሲጀመር እኔ ካንተ በሰውነት እበልጣለው ብሎ ማሰብ ነው ዘረኝነት ነው መልሴ። በዛ ላይ መብራት ይዘህ በገበያ መሀል ስትፈልግ ብትኖር የኦሮሞ ዘረኛ የለም። ምን አልባት ብሶተኛ ያስኬዳል።” ጠባብ ነህ”። እኔ ጠብቤ ሳይሆን አንተ ጠብህ ነው ሊሆን የሚችለው። የምናወራው በሁሉም መልክ ስለሰፊ ጉዳይ ነው።  ጤፍን በሲኒ መስፈር ልምድ አድርገህ እንዳይሆን። ቆም ብለህ እራስህን ጠይቅ ነው መልሴ። የበታችነት ይሰማሀል። አልክ? ይጥላኝ ብልህ መፍጠርህም አይደንቀኝ።  ያው ከዚህ የተለየ አይኖርም ብዬ ነው።

 

ዘርኝነት ድንቁርና ነው። ደንቁራችሁ አታዳናቁሩን።

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: