The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የመቀሌ አማርኛ በአዲስ አበባ

 

mekele
ከአቻምየለህ ታምሩ

እዚህ የለጠፍኳቸውን የባቡር ጣቢያ ስሞችን ስመለከት አዲስ አበባ ወደ መቀሌ የሄደች መስሎ ተሰማኝ። መቀሌ ብዙ ድጅቶች ከትግርኛ ይልቅ በአማርኛ ማስታወቂያ መለጠፍ ይቀናቸዋል። መቀሌ ውስጥ አማርኛ የቢዝነስ ማስታወቂያ መጻፊያ ቋንቋ ነው። መቀሌ በአማርኛ የቢዝነስ ማስታወቂያ እንደመጻፏ መጠን ለቃላትና ለሆሄያት ግድፈት ግድ የላትም። መቀሌ የአማርኛ ሆሄያትን በማሳከር ባለሁለት ዲጂት እድገት ያስመዘገበች ከተማ ትመስላለች።

ምስጉን ተስፋይ የሚባል የአዲግራት ልጅ አንድ የግጥም መድበል አሳትሟል። የግጥም መበሉን ያሳተመው በአማርኛ ነው። የምስጉንን ግጥሞች አንብቦ መረዳት የሚችል ቢኖር እንደኔ አይነት በአማርኛ አፉን የፈታ ሳይሆን የትግራዋይ አማርኛ [Tigrian Amharic ] የሚችል ሰው ብቻ ነው። ምስጉስ ተስፋይ መጽሀፉን ሲጽፍ አማርኛውን በማረም ያገዘውን ወንድሙን አመስግኗል። ግን ወንድሙም ልክ እንደ ምስጉስ የትግራዋይ አማርኛ ተናጋሪ በመሆኑ የተነሳ የግጥም መድበሉ የአማርኛ እርማት የተደረገለት ሳይሆን የአማርኛ መፋለስ ተደርጎለት ለመታተም የበቃ ነው የሚመስለው። ሁለቱም የትግራዋይ አማርኛ «ጸሀፊ» በመሆናቸው ለምስጉን ያልታየው የአማርኛ እርማት ችግር ለወንድሙ ሊታየው አይችልም።

መቀሌ ከተማ በየንግድ ተቋሙና በየአደባባዩ ከተለጠፉ የንግድ ማስታወቂያዎች መካከል ባልተሳካ አማርኛ ከተጻፉት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤«ሞቫይል ቆፎ ንሸጣለን»፤ «ካራ ቡላ ናጫወታለን»፤ «ሞቫይል ካርድ አሎ»፤ «ሞቫይል ቆፎ ንጠግናለን» «ተራንስ ፎርሜሽን» «ኤመይል ንከፍታለን» «ባለማጮሶ ንመስግንናለን»፤ «ዃረንቡላ አንጫወታለን»፤ «የተዘጋ ዋሃ ንሸጣለን» [የታሸገ ውሀ እንሸጣለን ለማለት ነው] ወዘተ።

መቀሌ በአማርኛ ለሚጻፉ ማስታወቂያዎች ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋም ለሚጻፉ ማስታወቂያዎች ግድ የላትም። የቢዝነስ ማስታወቂያዎችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈው የሚለጥፉ የአውሮፓን የእግር ኳስ ጨዋታዎችን የሚያሳዩ የDSTV ቤቶችና ፊልም የሚያከራዩ ሙዚቃ ቤቶች ናቸው። «Prison Break» የተሰኝውን የእንግሊዝኛ ፊልም የሚያከራዩ አራት መደዳውን የተሰደሩ ሙዚቃ ቤቶች ማስታወቂያውን የሚያስቅ እንግሊዝኛና አማርኛ ቀላቅለው ጽፈውት ተመልክቻለሁ። የመጀመሪያው «ዱካን [በትግርኛ ሱቅ ማለት ነው» ማስታወቂያውን <«prison brike» ዚህ ይገኛሉ> ብሎ ለጥፎታል። ሁለተኛው ቪዲዮ አከራይ ደግሞ «perison braik» በዝካረ ይገኛሉ ይላል። ሶስተኛው ቪዲዮ ቤት ሙሉ በሙሉ «የእንግሊዝኛ» ቃላትን ተጠቅሞ «price break four rent» ይላል። አራተኛው ነጋዴ ደግሞ በፋንታው «prisim brek» ፊልም ናከራያለን ሲል ለጥፋል።

ሌላ መቀሌ የማቀው በተለምዶ ሀውዜን አደባባይ ከሚባለው የከተማይቱ አነስተኛ አደባባይ በስተቀኝ አቅጣጫ በግምት አንድ መቶ ሜትር ያህል ገባ ብሎ በግራ በኩል «ናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» የተሰኘ ካፌና ሬስቶራንት በሩ ላይ የተለጠፈበት ቤት አለ። እኔና ጓደኛዬ «ናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» በተደጋጋሚ እየተገናኘን የቤቱን «ስፔሻል ምግብ» ተመግበናል። አዲስ አበባ ላይ «ምሿለኪያ» የሚል የባቡር መተላለፊያ ተጽፎ ሳነብ ቀጥታ ወደ ጭንቅላቴ የመጣው መቀሌ ከተማ የማቀው «የናቲ ምሿለኪያ ካፌና ሬስቶራንት» ነበር። ለዚያም ነው የጽሁፌን ርዕስ «የመቀሌ አማርኛ በአዲስ አበባ» ብየ የሰየምሁት።

መቀሌን ዞሮ ለጎበኘ የመቀሌ የንግድ ማስታወቂያዎችን ከፕሮፓጋንዳ መለየት ያስቸግረዋል። በተለይ ዋናው የህወሀት ጽህፈት ቤት አካባቢ በሚገኙ የንግድ ቤቶች ላይ የሚለጠፉ የንግድ ምልክቶችን ላስተዋለ ንግድ ቤቶቹ እቅና አገልግሎት መሸጣቸውን ትተው ፕሮፓጋንዳ መሸጥ የጀመሩ ነው የሚመስሉት። ሰላሳ ዘጠነኛው የህወሀት ልደት መቀሌ ከተማ ሰማህታት አዳራሽ ሲከበር ህወሀት ጽህፈት ፊት ለፊት ባለ አንድ ካፌ ደጅ ተቀምጠን እኔና ጓደኛዬ ሻይ ቡና እያልን ባካባቢው የሚካሄደውን እንቅስቃሴ እየታዘብን ነበር። ሻይ ቡና በምንልበት ካፌ በር ላይ «መለስ ጅግና እዩ፤ጀግና አይሞትም» ከሚለው የትግርኛ መፈክር ስር «Meles is alive» የሚል የእንግሊዝኛ ፍቺ ተሰጥቶት መፈክሩ ተሰቅሎ ነበር። ይህ መፈክር ዋናው ህወሀት ጽህፈት ቤት ውስጥም ተሰቅሎ እንደነበር ለማወቅ ችያለሁ።

ባጠቃላይ መቀሌን ለሚያውቅ ሰው ትናንትና የተለቀቁት የአዲስ አበባ ባቡር ጣቢያ ስሞች ሆሄያት መጣመምን ሲመለከት ወይ የባቡር ጣቢያ ስሞቹ መቀሌ ሄደው የተጻፉ ይመስለዋል አልያም የመቀሌን ማስታወቂያዎች የሚያትሙ ባነር ጻፎች አዲስ አበባ መጥተው የጣቢያ ስሞችን ለመጻፍ የተደረገውን ውድድር «አሸንፈው» ከመቀሌ ይዘውት በመጡት የሆሄ መቅረጫ የአዲስ አበባን የባቡር ጣቢያ ስሞች ወደ ማተሙ ገብተዋል ብሎ ሊያስብ ይችላል። በአዲስ አበባና በመቀሌ በተፈጸሙ የሆሄያት ግድፈቶች መካከል ግን አንድ ልዮነት ይታየኛል። የመቀሌ ማስታወቂያዎች ግድፈት አማርኛ ሆሄያትን ብቻ አይደለም፤ የመቀሌ ማስታወቂያዎች ለእንግሊዝኛም ግድ የላቸውም። የአዲሳበባዎቹ ግን የአማርኛ ሆሄያቱ ስህተትም ቢሆኑ የእንግሊዝኛ ስሞች ግን በስህተት የተጻፉትን የአማርኛ ሆሄያት ተከትሎ በትክክል የተቀረጹ ናቸው።

በመጨረሻ ከማስታወቂያ ሆሄያት ጀርባ ስላለው እውነት አንድ ቁምነገር ላክል። አንድ የመሰረተ ልማት አውታር ተሰርቶ ሲጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት የጥራት ፍተሻ [ Quality Control] ይካሄድበታል። ፍተሻው የመሰረተ ልማቱ ፊዚካል ግንባታ ደረጃውንና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ መካሄዱን ብቻ ሳይሆን በየቦታው የሚሰቀሉ የአውታሩ ምልክቶችና የማስታወቂያ ሄሆያትን ትክክለኛነትም ያካትታል። በአንድ ባቡር አውታር ላይ የሚካሄድ የማስታወቂያ ሆሄያትንና ምክቶች ፍተሻ የመጨረሻው ደረጃ ፍተሻ ነው። ይህንን ደረጃ ያላለፈ አውታር የጥራት ደረጃ ፍተሻውን እንዳላለፈ ይቆጠራል። በዚህ መሰረት ትናንትና ስራ ጀመረ የተባለው የአዲስ አበባው ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የመጨረሻውን የጥራት ፍተሻ ምዘና አላለፈም ማለት እንችላለን። የመጨረሻውን የጥራት ፍተሻ ምዘና ያላለፈ አውታር ማስተካከያ ተደርጎበት ካልሆነ ስራ እንዲጀምር አይደረግም። ይህ አስተምህሮ የEconomics of infrastructure ሀ ሁ ነው።

እኔ የገረመኝ ከውጭ ማንም ሰው አይቶ የሚለየውን የሆሄያት ግድፈት እንኳ ተመልክቶ ማስተካከል ያልቻለ የጥራት ማረጋገጥ ምዘና፤ ውስብስብ የሆነውን፣ ጥልቅ ሞያዊ ክህሎት የሚጠይቀውንና ከባዱን የባቡሩን መስመር ፊዚካላዊ ጥንካሬ ፈትሾ የባቡር መስመሩ ግንባታ ደረጃውን መጠበቁን አለመጠበቁን እንዴት ብሎ ማረጋገጥ ይችላል? በእውነት የባቡር መስመሩ የጥራት ፍተሻስ ተካሂዶበታልን? እንዴት ተብሎ ስንት መሀንዲሶች ባሉባት አገር የባቡሩ አውታር በአይን የሚታየውን የጥራት መመዘኛ [ማለት መስመር አመላካች ሆሄያት በሚገባ ያልተሟሉለት ሆኖ ሳለ] ፈተና እንኳ ያሳልፍ በአይን የማይታዩ የጥራት ፍተሻዎችን እንዳለፈ ተቆጥሮ የመጨረሻውን የጥራት ደረጃ ምዘና ያላሟላ ሀዲድ ላይ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ይጀመራል? ሁሉ ነገር ፖለቲካ ሆኖ ጥራትና ልቀት የሚባል ነገር ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር አፈር ድሜ በላ። አውሮፓና አሜሪካ ቀርቶ የትም ሶስተኛ አለም ውስጥ የመጨረሻውን የጥራት ምዘና ደረጃ ያላሟላ የባቡር አውታር እንደኛ አገር ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ስራ እንዲጀመር አይደረግም። በእውነት የባቡሩ አውታር ላይም የተደረገ ፍተሻ በተሰቀሉ የአውታሩ ምልክቶችና የማስታወቂያ ሄሆያት ላይ እንዳየነው አይነት ከሆነ፤ ከጣራው በላይ ዳንኪራ የተደለቀለቱ የባቡር ትራንስፖርት በቅርቡ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ሰባራ ሀዲድ ብቻ ታቅፈን እንቀራለን። ይህንን እድሜ ያለው ያያል!

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: