The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የአንዱዓለም ተፈራ የአገር አንድነት አስተሳሰብ እና  የቅማንት ህዝብ መፃኢ ዕጣ-ፈንታ

 

ከብርቱካን ወለቃ

eskemecheአንዱዓለም ተፈራ የሚባሉና የኢህአዴግንና የፌደራል ሥርዓቱን የሚቃወም ጹህፍ በ‹‹እስከመቸ›› የሚባል ድህረ-ገጽ የሚያዘጋጁ ‹‹ፀኃፊ››  በቅማንት ህዝብ ላይ ኢትዮሚዲያ ዶት ኮም (www.ethiomedia.com ) ላይ በተደጋጋሚ የሚለቋቸውን ፁህፎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት እንደሌሎች ሁሉና በተለመደው መንገድ ግላዊ ስሜታቸውን ለማርካት የሞነጫጨሩት ስለመሰለኝ ምንም ነገር ሳልል ረዘም ላለ ጊዜ አልፌው ነበር፡፡ ጉዳዩ እየተደጋገመ ሲመጣ ግን ዝም ስለተባሉ ‹‹እትንን እትን ካላሉት—›› እንደሚባለው የሚሉትን ተግንዝቦ ሀይ የሚላቸው ሰው የሌለና እሳቸው የሚሉት ነገር ብቻ ትክክል የሆነ እንዳይመስላቸው ይህን መልስ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡ እኝህ ግለሰብ በመጋቢት 21/2007‹‹የቅማንትን ክልል መመስረት በሦስት መንገዶች›› በሚል ርዕስና በነሀሴ ወር 2007 በዚሁ ድህረ-ገፅ ላይ ‹‹የማይለቀን የቅማንት ጉዳይ፤ ብለው ብለው ለአቤቱታ ወደእኛ መጡ›› በሚል ርዕስ ፅፈዋል፡፡ በዚህ ጸህፌ በመጀመሪያ በፃፉት ርዕሰ-ጉዳይ ላይ መልስ ይሆን ዘንድ ይህን አጭር ፁህፍ ለመፃፍ ተግድጃለሁ፡፡ እርግጥ ነው ለእንዲህ አይነት የወረደ አስተሳሰብ መልስ መስጠት ጊዜን ማባከንና እንደሳቸው ሀሳብ የወረደ ሊመስል ቢችልም ግለሰቡ ራሳቸውን አዋቂና የፖለቲካ ተንታኝ  አድርገው እንዳይመለከቱ መልስ  ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡ በእርግጥ ለሁለተኛ ጊዜ በፃፉት መጣጥፍ ላይ እጅግ በሚምር ቋንቋ ተከሽኖ መልስ ተሰጥቷቿል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እኔም በቀጣይ የግሌን ሀሳብ እጨምራለሁ፡፡

ግለሰቡ ‹‹የቅማንትን ክልል መመስረት በሦስት መንገዶች›› በሚል ርዕስ የፃፉት ፁህፍ ማጠንጠኛው ጊዜ ባለፈበትና በ19ኛው ክ/ዘመን የፖለቲካ ርዮት ዓለም (political ideology: Establishing strong and united nation through putting multiethnic people together) ላይ የተቃኘ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ለእኝህ ግለሰብ የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጠው አንድ ህዝብ፣ አንድ ሀይማኖት፣ አንድ  ቋንቋ በሚለው የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ተገዥነት በ1960ዎቹ አካባቢ ነፃ ሲወጡ በመሬት ላይ የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይገነዘቡ ያራመዱት የነበረው አገር የመገንባት አስተሳሰብ ቀጥታ ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እኝህ ግለሰብ አማራ እና ቅማንት የሚባል ህዝብ መኖሩን በራሳቸው አንድበነት ስለአንድ የጭልጋ አካባቢ ግለሰብ ሲያወሩ ‹‹በአባታቸው ከቅማንት በእናታቸው ደግሞ ከአማራ የተወለዱ ግለሰብ እንደሆኑ ይነግሩንና ከዚህ ግለሰብ የተወለዱት ልጆች ደገሞ የቅማንት ዝርያ ቢኖራቸውም የሚያደሉት ለዐማራነታቸው ነው›› ይላሉ፡፡ ይህን ካሉ በኋላ ቀጠል ያደርጉና  እንዲህ ይላሉ‹‹በእርግጥ ለእኔ ቅማንት ከአማራ የሚለየው በምንድነው?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ይሁን እንጅ አማራ የሚባለው ህዝብ ከቅማንት የሚለይበትን ምክንያት ፈፅመው ማወቅም ሆነ ጠይቆ መረዳትን አይሹም፡፡ ምክንያቱም ለእሳቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ህዝቦች በተለይ ደግሞ የአገው አካል የሆነው ቅማንት የአማራ ተቀጥላ እንጅ ራሱን የቻለ ህዝብ ነው ብሎ ማሰብ እጅግ ከመክበድም አልፎ የራሳቸውን ዘር ዝቅ ማድረግ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ለእኝህ ግለሰብ በኢትዮጵያ የሚገኙ ህዝቦች በሙሉ መጤ ሲሆኑ ነገር ግን እራሳቸው ተገኘሁበት የሚሉት ህዝብ ግን ኢትዮጵያ የምትባልን ምድር ጠፍጥፈው የሰሩና በካስማ ወጥረው የዘረጉ ያክል ብቸኛ ባለመበት እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ‹‹ኦሮሞ ፣ቅማንት ትገሬ ፣ ሲዳማ፣አፋር ነኝ›› የሚል ህዝብ ካለ ደግመ ወደ ማዳጋስካር ወደ ግብፅ  ወደ የመን እንዲመለሱ ይመክራሉ፡፡

የአማራ ክልል ለምን እንደተቋቋመ ምንም ነገር ሳይተነፈሱ ‹‹የቅማንት ራስን በራስ ማስተዳደር በወያኔ/ኢህአዴግ/ የተጠነሰሰ አማራን የማዳከም ሴራ ነው›› ይሉናል፡፡ ለዚህ ግለሰብ ለእሱ መብት የሆነው ለሌላው ግን ወንጀል እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ህወሀት በዚች አገር ከመምጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንዴት ሲኖሩ እንደነበር የኢትዮጵያ ህዝቦች ህያው ምስክር ናቸው፡፡  ቅማንት የሚባል ህዝብ በማንነቱ ምክንያት እንዴት እየተዋረደ፣ እየተሰደበ እንደኖረና በዚህም ምክንያት ቋንቋውንና ማንነቱን ረስቶ በደባል ማንነት ስር ሲርመጠመጥ እንደነበር ሊነግሩን አይመኙም፡፡ለእነሱ ያ በህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረ ግፍ ኢትዮጵያ የምትባልን አገር አንድ ለማድረግ ስለነበር የተደረገው ሁሉ ትክክል ነበር፡፡  እነሱ ‹‹የደጉ ዘመን›› ብለው የሚጠሩት ዘመን ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የመከራ፣ የስቃይ፣ የግፍ ዘመን ነበር፡፡ ቋንቋቸው ከሰው ፊት እንዳይነገር ‹‹የወፍ ቋንቋ›› ሲባልና አማርኛ ለመናገር የሚኮላተፈው ሁሉ ገመድ አፍ፣ ተብታባ ሲባል እንደነበር ለእዚህ ግለሰብ አይገባውም፡፡

ቅማንት የሆነ ግለሰብም ይሁን ሌላ በዘሩ የተነሳ በነበረው ሥርዓት ተፅዕኖ ምክንያት ሆዱ እያወቀ ያለሆነውን ‹‹አማራ ነኝ›› ሲል እንደነበር ለዚህ ሰውየ መናገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡ ሁሉም የሰው ልጅ በስላሴ ዓምላክ መፈጠሩ ተዘንግቶ ከእንጨትና ከእሬት የተገኘ ፍጡር በማድረግ ለዘመናት በማንነቱ ሲሸማቀቅ የነበረው ይህችን አገር አንድ ህዝብ አንድ ቋንቋ አንድ ሀይማኖት እያሉ ህዝቡን ረስተው ሲገዙት የነበሩ ገዥዎች እነማን እንደሆኑ ሊነግሩን አይፈልጉም፡፡ ለዚህ ግለሰብ ግን ያ ዘመን ሁሉም ህዝብ ተዋርዶ ገዥዎችና የዚያ ሥርዓት ደጋፊዎች የበላይ እንዲሆኑ የተደረገበት ዘመን  የአንድነትና የመልካም ዘመን ነበር፡፡ ራሳቸው የሚሰድቡትና ኢትዮጵያን ከፋፈለ ብለው የሚጠሩት የፌደራል ሥርዓትና የትግራይ ነፃ አውጭ ብለው የሚኮንኑት የፖለቲካ ድርጅት  ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ተከባብረው እንዲኖሩ መፍቀዱ ለእሳቸውና እሳቸው ለተገኙበት ህዝብ ትልቅ ስደብ እና ያን ‹‹ታላቅ›› የሚሉትን ህዝብ ያዋረደ ከሌሎች በእኩል አይን እንዲታይ ያደረገና ለኢትጵያ መፃኢ ዕድልም አደገኛ እንደሆነ ሳያሰልሱ ይነግሩናል፡፡

 

እኝህ ግለሰብ የቅማንትን የራስ አስተዳደር ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በሦስት መንገዶች እመለከተዋለሁ ይላሉ፡፡

ይህውም፣

1ኛ ከህገ-መንግሥቱ አንፃር

‹ኦሮሞ  ነኝ›  ፣ ‹ቅማንት ነኝ› ‹ወላይታ ነኝ› ማለት  ኢትዮጵያዊነትን የሚደመስስ አስተሳሰብ ነው ይሉና አማራ ነኝ ብሎ መቀጠል ግን ኢትዮጵያዊነት የሚያስቀጥል አስተሳሰብ በመሆኑ ተመራጭና ጤነኛ አስተሳሰብ እንደሆነ ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ በራሱ የነገድ ሥም የሚጠራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን እንደካደ ሊያስረዱን ይሞክራሉ፡፡‹‹ቕማንት ቕማንት ነኝ ብሎ ኢትዮጵያዊነቱን ከሚያጣ ይልቅ አማራ ነኝ ብሎ ኢትዮጵያዊ መሆን ይሻለዋል›› ይላሉ (ገጽ 1 ፓራግራፍ 4 መስመስር 4 እና 5)፡፡ ቅማንት ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ ሽናሻ ነኝ ማለት ኢትዮጵያዊነትን ስለሚደፈጥጥ ኢትዮጵያዊ  ብቸኛው የዘር ሀረግ ‹አማራ› ብቻ እንደሆነ በግልፅ ይነግሩናል

ለቅማንት ህዝብ ቅማንት ነኝ ማለት.፣ ለኦሮሞው ኦሮሞ ነኝ ማለት ፣ለትግሬው ትግሬ ነኝ ማለት ወዘተ ነውርና ፀረ-አንድነት ሲሆን ለአማራ አማራነ ነኝ ማለት ግን ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠነክር አስተሳሰብ እንደሆነ ሊሰብኩን ይሞክራሉ፡፡ ለእኝህ ሰው ኢትዮጵያ አንድ የምትሆነው ሁሉም ማንነቱን ረስቶ አማራ ነኝ ሲል ብቻ እንደሆነ ይመክሩናል፡፡ ይህን  በተመለከተ መጋቢት 21/2007 ዓ.ም ‹‹የቅማንትን የክልል አስተዳደር በሦስት መንጎዶች›› ባሉበት መጣጥፋቸው ላይ በግልጽ  እንዲህ ይሉናል፡፡ ‹‹—— ለአንድ የቅማንት ተወላጅ ቅማንት ነኝ ማለቱ እንጅ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቱ ዋጋ የለውም›› ይላሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ቅማንት ኢትዮጵያዊ ለመሆን ከፈለገ ማንነቱን ረስቶ በኢትዮጵያዊነቱ ይጠራ እንደማለት ነው፡፡ እኝህ ግለሰብ ጎንደር ውስጥ ሲያድጉና ወላጆቻው ራሳቸው በፈጠሩት ስለቅማንት ማንነት የተዛባ ተረት ተረት ሲግቷቸው በማደጋቸውና በኢትዮጵያ ስለ አንድ ብሔረሰብ ታላቅነትና የኢትዮጵያ ብቸኛ ባለቤትነት አጣመው ስላሳደጓቸው በምንም መልኩ የቅማንትን ማንነት መቀበል አይፈልጉም፡፡ በተቃራኒው እርሳቸው የተገኙበት ብሔር ሲጠራ በኩራት ደረታቸውን በትቢት ይወጥራሉ፡፡  የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ‹‹ለምን ጠየቀ?›› ብለው በተቆረቆሩበት አስተሳሰብ ስለአማራ የራስ አስተዳደር መመሥረት ምንም ነገር ማለት አይፈልጉም፡፡ ለዚህ ግሰብ ለአማራ ይህ ተፈጥሯዊ መብት ሲመስላቸው ለቅማንት ግን የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡ ወረድ ይሉና እርሳቸውን ያናደደቻቸው ሌላው ነገር በአማራ ክልል የሚገኘው ቅማንት አማራ እንዲሆን አለመደረጉ እንጅ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኩናማዎች፣ ሳሆች ኢሮቦች በስማቸው መጠራቸውን አይቃወሙም፡፡ እንዲያውም ይህ አለመደረጉ እጅግ እንደሚያማቸው ይገልጣሉ፡፡ እገረ-መንግዳቸውን ግን አማራ እየተባለ የሚጠራው ህዝብ የጋፋት የሽናሻ፣ የወይጦና የሌሎች ህዝቦች ስብስብ መሆኑን ሳይደብቁ በጹህፋቸው በሌላ አስተሳሰብም ቢሆን ነግረውናል፡፡

2ኛው ትግራይን ከማስፋፋት አንፃር

እኝህ ግለሰብ የቅማንት ቅማንት ነኝ ማለት የህዝቡ መብት መሆኑን በመዘንጋት የቅማንት ጥያቄ መነሻውና መድረሻው የትግራይን ግዛት ከማስፋፋት ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ፡፡ ለእኝህ ግለሰብ ቅማንት ቅማንት የመሆን ተፈጥሯዊ መብቱን በግልፅ ይደመስሱታል፡፡ ቅማንት ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ የቅማንት ህዝብን የውስጥ አስተዳደር ጥያቄ የሚያይዙትና የሚያዩት ከትግራይ የቦታ መስፋፋት ድብቅ ዓላማ ጋር ያቆራኙታል፡፡ ይህ ማለት ቅማንት የሚባል ህዝብ በኢትዮጵያ ያልነበረ ነገር ግን ወያኔ/ኢህአዴግ/ ለግዛት ማስፋፋት ዓላማው ሲል ብቻ ከ20 ዓመት ወዲህ  የፈጠረው ህዝብ እንደሆነ በግልፅ ይነግሩናል፡፡ የዛሬን አያድርገውና እኝህ ግለሰብ ጎንደር ውስጥ ሲያድጉ ቢያንስ በ24 ሠዓት ውስጥ ቅማንትን የሚያንቋሽሽ ፀያፍ ቃል ወይ ራሳቸው ይሉታለ አለያ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከጎረቤታቸው ሲነገር ሲሰሙ እንዳደጉ የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ አሁን እያራመዱት ላለው ጭፍን የዘር ጥላቻም መሰረቱ ያደጉበት ቤተሰብና ማህበረሰብ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ታዲያ በዚህ መንግድ ያደገ ግለሰብ የቅማንትን ህዝብ የመብት ጥያቄ በተንሸዋረረ አመለካከታቸው ቢያዩት የሚያስገርም አይደለም፡፡የሚገርመው ግን ዛሬም የኢትዮጵያን አንድነት በ1960ዎች በነበረው አስተሳሰብ ለማስቀጠል ታች ላይ ማለታቸው ነው፡፡ ግለሰቡ ማወቅ አይፈልጉም እንጅ ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያን አንድነት በአንድ ህዝብ ሥም አስቀጥላለሁ ብሎ ማሰብ ቐዠት ብቻ  ሳይሆን የጤንነት መጓደል ጭምር ነው፡፡

አቶ አንዱዓለም ‹‹ተስፋፊው የትግራይ ገዥ ከተከዜ አልፎ አስከአባይ ድረስ ለመቆጣጠር ያለውን ዓላማ ለማሳካት ቅማንትን አንደመሸጋገሪያ ድልዲይ ለመጠቀም ሲል ከተኙበት ቀስቅሶ የራስ አስተዳደር ጥያቄ እንዲያነሱ አደረጋቸው›› ይሉናል፡፡ ይሁን እንጅ ገዥው የአማራ ክልል መንግሥት የቅማንትን ህዝብ ያለፈቃዱ ‹‹ከዛሬ ቀን ጀምሮ አማራ ሆናችኋል›› ብሎ ከህዝብና ቤት ቆጠራ ሲሰርዛቸው ያ ለዚያ ታላቅ ህዝብ ለሚሉት መስፋፋት አልነበረም ይሆን?፣ ዘር ማጥፋትም አይደለም?፡፡ ይህን ድርጊት ተገቢና ትክክል አደርገው ስለሚያስቡ የአማራ መንግሥትን መክሰስ ፈፅሞ አይፈልጉም፤ በተቃራኒው ተገቢና  በልባቸው ጀግኖች እያሉ የሚያወድሷቸው ይመስለኛል፡፡ እስኪ እርሳቸው የተገኙበት ህዝብ የቅማንት ዕጣ ፈንታ ቢገጥመው ምን ይሰማቸው ይሆን? አማራ የሚባል ህዝብ ተሰርዞ ኦሮሞ ወይም ትግራዋይ ሆነሀል ቢባል አፈሙዝ ከማዞር የሚያግዳቸው ነገር ይኖር ነበር? ይህ ሆኖ አይደለም ሥልጣን የህዝብ በመሆኑ ከውጭ አገር ሆነው እያስነሱ ያሉትን አቧራ እያሸተትን ነው፡፡ ቁም ነገሩ  ግን ከአቧራነት የሚያልፍ አይደለም፡፡ ‹‹የቅማንት ክልል ለማን ይጠቅማል?›› ብለው በጠየቁበት አንድበታቸው የአማራ ክልል መመስረት ‹‹ለማን ይጠቅማል?›› ብለው ለመጠየቅ ድፍረቱን አላገኙም፡፡ ያሉት ምንድነው ‹‹የቅማንት ክልል ከተመሰረት የአማራ ክልል የቱ ሊሆን ነው? ነበር ያሉት፡፡ ቀጠል በማድረግ ‹‹የቅማንት ደካማ ክልል መመስረት ምን ጊዜም የማያባራ ንትርክ ከአማራው ጋር ይፈጠራል›› በማለት ስጋት አስመስለው ጎንደሬ አማራ የቅማንት ክልል ከተመሰረተ ለጦርነት እንደሚዘጋጅ ሊያስፈራሩን ይሞክራሉ፡፡ ከዚህ የአማራ ህዝብ ቁጣ እና ወረራ ለመዳን የቅማንት ህዝብ ትግሬዎችን አድኑኝ ለማለት ይገደዳሉ በማለት ትንቢታቸውንና ስጋታቸውን ይነግሩናል፡፡ ስለዚህ ነገ የራስክን ክልል በመመስረትህ በአማራ ህዝብ ሊደርስብህ ከሚችለው ቁጣ ለመዳን የራስ አስተዳደር ጥያቂያችሁን ቅማንቶች አቁሙ ይላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከእኛ አንኳ ብታመልጡ በመጨረሻ በትግሬዎች ተደፍጥጣችሁ እስከውዲያኛው  ከምደረ-ገጽ መጥፋታችሁ አይቀርምና እነሱ ከሚያጠፏችሁ እኛ እንደጀመርነው እንጨርሳችሁ ለማት ይዳዳቸዋል፡፡ በክልሉ ለሚኖሩ ሌሎች ህዝቦችም ማለትም ለአገው ለሽናሻ ለወይጦ  ለሻንቅላ ህዝቦች በቅማንት ሊደረስ የሚችለው እንዳይደርሰባችሁና የመምጫችን ቀን ስለማይታወቅ  ከአሁኑ ንስሀ ግቡ በማለት ይመክራል፡፡ የሚያሳዝነው ከወላጆቻው የወረሱት ፀያፍ የህዝብ ስም አጠራር አንኳ አላስተካከሉም፡፡ አሁንም የሌለን ህዝብ ‹‹ሻንቅላ›› እያሉ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያላቸውን ንቀት ይነግሩናል፡፡ ሻንቅላ ማነው ‹ነብዩ› አንዱዓለም?

‹‹የቅማንት ክልል መመስረት ዋና ምክንያቱ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር የፖለቲካ ቅማራ ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ ግን በነካ ብዕራቸው የአማራ ክልል መመስረት የየትኛው ተፈጥሯዊ ህግ ውጤት እንደሆነ ቢነግሩን? አቶ አንዱዓለም በአግባቡ አልተረዱተም እንጅ  ወያኔ/ኢህአዴግ/ ያልነበረን የአማራ ህዝብ ራሱን የቻለ ብሔረሰብ ነው ብሎ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎታል፡፡  የደርግ ፕረዚዳንት የነበሩት መንግሰቱ ኃ/ማሪያም‹‹ እውን አማራ የሚባል ህዝብ አለ?›› ያሉትን ሀቅ ኢህአዴግ ደምሰሶታል፡፡ እውነታው ግን የመንግሥቱ ኃ/ማሪያም ጥያቂያዊ ንግግር ነበር፡፡

3ኛው ዐማራውን ከማዳከምና ከማጥፋት አንፃር

የቅማንተን ክልል መመስረትን ያየበት ሦስተኛው መንገድ ወያኔ አማራን ለማጥፋት ካለው ዓላማ ጋር ያያዙታል፡፡ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹የትግሬዎች ነፃ አውጭ ሲቋቋም ከመጀመሪያዎች አራቱ ግቦች አንዱ በአማራው መቃብር ላይ የትግራይን ሪፑብሊክ እንመስርታለን የሚል ነው›› ይላሉ (ገፅ 3 ፓራግራፍ 2)፡፡ ቀጠል በማድረግ ‹‹ይህ የቅማንት ክልል መመስረት የትግሬዎች ነፃ አውጭ ግንባር ትግራይን ለማስፋፋት እንደሆነ ከላይ በተራ ቁጥር 2 አሳይቻለሁ ይላሉ፡፡

ለእኝህ ግለሰብ በኢትዮጵያ የፀደቀው ህገ-መንግሥት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሲደርሳባቸው ከነበረው ግፍ አውጥቶ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲያመጣ ታስቦ በህዝቦች ይሁንታ የመጣ ሳይሆን አማራ የሚባልን ታላቅ ህዝብ ለማዳከምና ብሎም ለማጥፋት  በወያኔ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ይሉናል፡፡ ምክንያቱም ይላሉ ‹‹ለወያኔ ከደርግ ይልቅ መሰረታዊ ጠላቱ አድርጎ የሚያየው የአማራን ህዝብ ነው›› ይላሉ፡፡  ነገር ግን ሰው በላው ደርግ የወያኔ ጊዚያዊ ጠላት ነበር በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ ይህን ዐማራን የማጥፋት  ተልዕኮውን ለማሳካት ‹‹ወያኔ ቅማንትን ጠፍጥፎ ሰራው›› ይላሉ፡፡ በክልሉ የተለያዩ ህዝቦችን በመፍጠር የአማራን ቁጥር አሳነሰ ይላሉ፡፡ ለአቶ አንዱዓለም ትልቁ ጭንቀት የአንድ ብሔረሰብ እንደህዝብ ራሱን አሳውቆ መቀጠልና ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ተፈጥሯዊ የሆነውን መብቱን ረስተው የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር መመስረት የአማራን ህዝብ ቁጥር ማሳነሱ ላይ ያንገበግባቸዋል፡፡ የወያኔ የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር መፍቀድ አማራን ለማጥቃት ነው ባሉ አንደበታቸው የቅማንትን ዘር ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ግፍ ለምን ማንሳት አልፈለጉም? ለአንድ ህዝብ ብቻ መቆርቆር እውን የኢትዮጵያን እነድነት ያረጋግጣል?

ለዚህ ግለሰብ አንድነት ማለት ቦታ እንጅ ሰው አይደለም፡፡ ይህን እውነታ እንዲህ በማለት ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ወያኔ ‹‹ከየትኛው ቦታ አማራ ተባሮ የቅማንት ህዝብ እንዲሰፍር ይደረጋል?›› ብለው ሲጠይቁ አሁን ቅማንት ሰፍሮ የሚገኝበት ቦታ የአማራ ቦታ እንጅ የቅማንት አይደለም ማለታቸው እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅማንት አገር የሌለው በእነአንዱዓለም በጎ መግባር የተቀመጠ ህዝብ ነው ማለታቸው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም እንአንዱዓለምና መሰሎቹ ያደራጇቸው የአማራ ህብረት አባላት (በኢትዮጵያ)  ‹‹ቅማንት አገር ስለሌለው ወደመጣበት ግብፅ እንመልሰዋለን እንዳሉት ማለት ነው፡፡ የቅማንት ጥያቄ የመብት እንጅ የቦታ ማስፋፋት እንዳልሆነ እያወቁ ቅማንት የሚባል ህዝብ በጎንደር ምድር ላይ ፍፁም ቦታ አንደሌው አድርገው ይነግሩናል፡፡ ምን ይደረግ ‹‹በኋላ የበቀለ ቀንድ በፊት የበቀለውን ጆሮ በለጠው›› አይደል ከእነተረቱ፡፡ ምን ይሁን! የቅማንቶች ምድር ጎንደር ለዚህ ግለሰብ ያለፈ ታሪክ ሆነባቸውና ከነአካቴው የቅማንትን በጎንደር ምድር ቦታ የሌለው ህዝብ እንደሆነ ሊነግሩን ሞከሩ፡፡ የዛሬን አያድርገውና እንኳን የጎንደር ምድር ራሳቸውም የተገኙበት ህዝብ መሰረቱ ቅማንት አንደሆነ የሚጠፋቸው አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት በተደረገ የሀይማኖትና የፖለቲካ ተፅዕኖ ተገዶ ማንነቱን የቀየሩትን የአቶ አንዱዓለም ዘመዶች ሥርወ-ግንዱ ቅማንት ነበር፡፡

በፁህፋቸው መጨረሻ ‹‹በትግሬዎች ነፃ አውጭ ግንባር የቅማንት ክልል ተፈጥሯል፤ ታዲያ ይህን እንዴት መታገል ይቻላል?›› ብለው ይጠይቁና  የህን አገር አፍራሽ ተግባር መቃወም  የሁሉም ግዴታ እንደሆን መልሱን ራሳቸው ይመልሱታል›፡፡ መፍትሄውም ‹‹የትግሬን ነፃ አውጭ ድርጅት ተባብሮ መደምሰስ ነው›› ይላሉ፡፡ የትገሬ ነፃ አውጭ ከተደመሰሰ የቅማንት ማንነትም አብሮ ይደመሰሳልና ማለታቸው ነው፡፡

በዚህ ፁህፋቸው አቶ አንዱዓለም ሁለት ትልልቅ ስህቶችን ፈፅመዋል፡፡

1ኛውና የመጀመሪው  ስህተታቸው የቅማንት ህዝብ እንደህዝብ በራሱ የማይነቀሳቀስ በድን አካል አድርገው በማየታቸው የቅማንት ህዝብ ማንም ሲፈልገው በባዳነት የሚጠቀምበት አስመስለው መሳላቸው ነው፡፡ ግን እኝህ ግለሰብ የዘነጉት አብይ ቁም ነገር ቢኖር ራሳቸው አስር ጊዜ የትግራይ ነፃ አውጭና ከፋፋይ ብለው በሚጠሩት ድርጅት ተመሰረተ በሚሉት የፌደራል ሥርዓት ውስጥተሸቀዳድሞ ስልጣን ላይ ፊጥ ያለው እርሳቸው የተገኙበት ህዝብ አካል የሆነው ቡድን እንደሆነ ረስተውት ሳይሆን ‹‹በብቸኝነት ለምን እኛ ብቻ አገሪቱን አልተቆጣጠርንም›› ከሚል ጭፍን የሥልጣን አባዜ ነው፡፡ ዛሬ የአማራን ክልል የሚመራው በመንደርና በጎጥ በተሰባሰቡ ቡድኖች መሆኑን እያወቁ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ማለት አይፈልጉም፡፡ ባንዳነት የራስን መብት ማስከበርና በፌደራል ሥርዓቱ መሳተፍ  ከሆነ የመጀመሪያወ ባንዳ ማን እንደሆን ለማወቅ ምንም አይነት የሂሳብ ቀመር አያስፈልገውም፡፡ ለእኝህ ግለሰብ ቁም ነገሩ የህዝብ ቁጥር ብቻ ስለሚመስላቸው የቅማንትን ህዝብ ከአማራው ህዝብ ጋር በማነጣጠር ‹‹የትም አትደረሱም›› ለማለት የሞክራሉ፡፡ ቁም ነገሩ ቁጥር ቢሆን ኑሮ እስራኤል የምትባል አገር እና አስራኤል የሚባል ህዝብ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የአረብ ህዝብ ተከቦ ህልውናውን ባላስከበረ ነበር፡፡ ከፈለጉ እኝህ ግለሰብ የሚናፍቁትን ጦርነት ጊዜ ሳይወስዱ ማወጅ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚናፍቁት ጦርነት የቅማንትን ህዝብ ብቻ ለብልቦ የሚቆም መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ በጎንደር ምድር ላይ ወይ አብረንና ተከባብረን እንኖራለን አለያ ደግሞ በግፍ የሚመጣ ጦርነትን መመከት የሚያቅተው ያለ ህዝብ ያለ አይመስለዎት፡፡

2ኛውና ሌላው ስህተታቸው የዚህ ፁህፍ ማጠንጠኛቸው ህወሀት/ኢህአዴግ/ የአማራን ህልውና ለመፈታተን የተፈጠረ ድርጅት በማስመሰል የሚደስኩሩትና የዚህ ህዝብ ህልውና መደፈር ለኢትዮጵያ አንድነት መደፈር ብቸኛ ምልክት አድርገው የሚያራምዱት የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ ‹‹ተደፈረ፣ በወያኔ የጥፋት በትር ሥር ወደቀ›› የሚሉት ህዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ  20 በመቶ  ሊሆን ቢችል ነው፡፡ ሌላውን በማግለል እንደገንጣይና ከፋፋይ መመለልከት ጊዜው ያለፈበትና ውኃያማይቋጥር አስተሳሰብ መሆኑን የተገነዘቡት አይመስልም፡፡ የእንዲህ አይነት የተቸካይነት (inflexible) አመለካከት ይበልጥ የኢትዮጵያን ህዝብ ይከፋፍል ካልሆነ በስተቀር የአነድነት ስሜትን ማምጣት አይችልም፡፡

ለአንዱዓለምና ለመሰሎቹ የራሳቸውን የተንሸዋረረ አመለካከት አስተካክሎ ወደ አማካኝ ቦታ ከመምጣት ይልቅ ይህ አመለካከት ወያኔነትና የወያኔነት አቀንቀኝነት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ግድ የለኝም፡፡ በኢትዮጵያ ብሔር. ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የሚያምን ድርጅት ሁሉ ደጋፊ ነኝ፡፡ እኝህ ግለሰብ አልተረዱትም እንጅ ወያኔ/ኢህአዴግ/ የሚሉት ድርጅት ለዐማራ ህዝብ የማንነት እውቅና በመስጠት የቅማንትን ህዝብ ከአማራ መንግሥት ደጅ እንዲጠና እንዳደረገው የተገዘቡ አይመሰልም፡፡ ለሳቸው ጥያቄ የሆነባቸው አማራ ባለመብት መሆኑ ሳይሆን ቅማንት መብቱን መጠየቁ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ መብት ለእነሱ ተጥሯዊ  መብት ሲሆን ለቅማንት ግን የማይታሰብ እውነታ አድርገው ያዩታልና፡፡

ይህን በዚህ ላብቃና ግለሰቡ ለሁለተኛ ጊዜ ‹‹የማይለቀን የቅማንትጉዳይ፤ ብለው ብለው ብለው ወደእኛ ለአቤቱታ መጡ›› በሚል ርዕስ www.ethiomeida.com ላይ በፃፉት ዙሪያ ሰፊ መልስ ይዠ አስክመለስ ድረስ ቸር ይግጥመን!

ከብርቱካን ወለቃ

ይህን ፀሁፍ መነሻ አድርጎ መልስ መፃፍ የሚፈልግ ሁሉ በፌስ ቡክ አድራሻየ ወይም birtukanwoleka@gmail.comበሚለው አድራሻ ሊፅፈልኝ ይችላል፡፡

posted by Gheremew Araghaw

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: