The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የገበሬው ልጅ ሞላ አስገዶም (ከደምስ በለጠ)

mola-asgedom

ከሳምንት በፊት ከወደ አስመራ አንዲት “ሰበር ዜና” የምትል እንደ አዋጅ ቢጤ የሚቃጣት ዜና ተናኘች ። በዚህች ዜና ላይ አሳቤን እስከ አስመራ ድረስ ወስጄ ፤ እያንዳንዳቸውን ተጣመሩ የተባሉትን ድርጅቶች ለመቃኘት ሞከርኩ ። ይህን ሳደርግ ሁልጊዜ ሻእቢያ ከሚጎነጉናቸው ትብብር ፤ ጥምረት ውህደት ፤ አሊያንስ ፤ እየተባሉ ከተፈለፈሉ ያለፉ ታሪኮች በመነሳት ነው ። ይህ አይነት ጥምረት ሊቋቋም እንደሚችልም በቀደሙት ፅሁፎቼ እንደ ትንቢት አድርጌ ገልጬም ነበር ። በዚህኛው ጥምረት ወይም ንቅናቄ ፤ ሻእቢያ የፈጠራ ጥበቡን በጥቂቱም ቢሆን ለማሻሻል የሞከረ ይመስላል ።

ጥምረቶቹ ውስጥ ይካተታሉ ብዬ ገምቻቸው ከነበሩት ድርጅቶች ውስጥ የደቡብ ህዝቦችንና የቤኒሻንጉል ድርጅቶችን ለጊዜው አላካተታቸውም ። “አገር አድን ንቅናቄ” የተባለው እንከን ባይገጥመው ኖሮ ፤ እነዚህ ድርጅቶች ወደፊት አገር አድን ንቅናቄውን ለማጠናከሪያ የሚመዘዙ የሻእቢያ የፖለቲካ ጆከር ካርታዎች ነበሩ ። ለዛሬው ግን ከአማራ ንቅናቄ እስከ አፋሮች ህብረት የዘለቀ ንቅናቄ የተባሉ ቡድኖችን ከቶበታል ። አዲስ ድርጅት መጣ ፤ ወይም ቀድሞ የነበረው ዘለቀ ፤ ዘፈኑ ሁሉ ሻእቢያ ዘንድ ያው ሸሙናዬ ነው ። ድርጅቶቹን ጉልቻዎች አድርገን ብንወስዳቸው ፤ የሾርባው ቀማሚና ፤ አድራጊ ፈጣሪ ግን ሻቢያ እንደሆነ ከልምድ ያየነው ነው ።

ከሰበር ዜናዋ ላይ ተነስቼ ይህን እያሰብኩ እያለሁ ፤ ተፈጠረ በተባለው ንቅናቄ ላይ ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ አጠር ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው ሰፊ የሆኑ ጉዳዮችን ከላይ ከላይ ብቻ ገረፍ ገረፍ አድርገው ነው ያለፉት እያልኩ እያሰብኩ እያለሁ ፤ ቀጣዩዋ የአዲስ አመቷ ዋዜማ ምሽት ከሞላ አስገዶም ጀብዱ ጋር ሁሉንም ነገር እንክትክቱን አወጣችው ።

ያም ሆነ ይህ ህዝብ የማወቅ መብት አለውና ፤ ጋዜጠኞችም የማሳወቅ ግዴታ አለብንና ፤ ወደ ሌሎች ጉዳዮች ከማለፌ በፊት ፤ የጋራ ንቅናቄው ውስጥ ተካተቱ ስለተባሉት ርድጅቶች ምንነት የማውቀውን እነሆ ።

1ኛ) የዴሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይ (ዴምህት – TPDM) ድርጅታዊ ማንነትን ከዚህ በፊት ራሱን በቻለ ፅሁፍ ብገልፀውም ፤ የአዲሱ አመት ዋዜማ ክስተት ፤ ከሞላ አስገዶም ተግባር ጋር ፤ የበለጠ እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ እንዲታየን መንገዱን ሁሉ ከፍቶልናል ፤ ስለዚህ ድርጅት በቂ ግንዛቤ ይኖራል ብዬ ስለገመትኩ በዚሁ ልተወው ።

2ኛ) አርበኞችና ግንቦት ሰባት እያንዳንዳቸው ሊኖራቸው የሚችለውን የሰው ሃይልም እንዲሁ ገልጬ ፅፌ ነበር ። ለማስታወስ ያህል ፤ በአጠቃላይ ከሁለቱ ድርጅቶች ከ150 ያልዘለለ የሰው ሃይል ሊኖራቸው እንደሚችልም ጠቁሜአለሁ ። ከወደ አስመራም ይህ ውህደት በራሱ ችግር ላይ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች እያየንም እየሰማን ነው ። የአርበኞች ግንባር ሰዎች ከግንቦት 7 ጋር በተደረገው ውህደት ደስተኞች እንዳልሆኑ ታውቋል። ተራ አባላቱም ሆኑ የስራ አስፈጻሚ ሰዎች ባገኙት አጋጣሚ እየኮበለሉ እንደሆነም እየታየ ነው። እኔ ራሴ በሚገባ ላለፉት 10 አመታት ከአርበኞች ጋር የማውቀው የአርበኞች ግንባር መሪ የመአዛው ጌጡ የግል ሾፌርና የስራ አስፈፃሚ አባል ፈቃዱ ቸሬ በሱዳን በኩል አምልጦ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። በዚህ ላይ የአርበኞች ግንባር መሪዎች የነበሩ ሰዎች አንዳቸውም በየትኛውም ጥምረትም ሆነ ሌሎች አቢይ ክንውኖች ላይ ፤ ድምፃቸው እንደማይሰማ እያየንም እየሰማንም ነው ።

ከአስመራ በሚወጡ መረጃዎች ፤ አርበኞች ግንባር ከግንቦት 7 ጋር ያለፈቃዳቸው ውህደት አድርጉ ተብለው በሻእቢያ ትእዛዝ እንደተሰጣቸው ሰምተናል። ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት እያደረጋችሁ መረጃ ታስተላልፋላችሁ ተብለውም የእጅ ስልካቸውን እንዲያስረክቡ ተደርገዋል። ስለድርጅት በሚገባ የሚረዳና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችን ግንኙነትን ታሪክ ጠንቅቆ የሚረዳ ሰው እነዚህን ምልክቶች ሲያስተውል የአርበኞች ግንባርና የግንቦት 7 ንቅናቄ ውህደት ገና ረግረግና መሰረት ያልያዘ መሆኑን መረዳት አይሳነውም። በውህደት የቆዩባቸው ያለፉት 6 ወራትም ሁለት ራሳቸውን ችለው ለቆዩ ድርጅቶች ፍፁም ውህደት አድርገዋል ብሎ ለመናገር በቂ ጊዜ አይደለም ። ስለዚህ “አርበኞች ግንቦት 7” በራሱ እንደ ውህደት እግሩ በፅናት ያልቆመ “ወፌ ቆመች” እየተባለለት ያለ ርድጅት ነው ።

3ኛ) መግለጫው እንደሚያሳየው የአፋሮቹ ድርጅቶች ወደጋራ ንቅናቄ የመጡት ራሳቸውን ችለው እንደ አንድ ድርጅት ሳይሆን እነሱም የተለያዩ የአፋር ድርጅቶች ህብረት (አዎ ህብረት የሚለው ቃል ይሰመርበት) ሆነው ነው። የአፋር ድርጅቶች አሉ ይባላሉ እንጂ አንድም ቦታ ይህን ሰሩ ሲባል ታይቶም ተሰምቶም አይታውቅም ። ስለዚህ የአፋር ድርጅቶች አሉ እየተባለ የሚወራው ከአስመራ የኮምፔሽታቶ ጎዳና ባዶ ወሬነት በላይ አይዘልም ። አሉ ብለን ብንወስድ እንኳ ፤ አንድ ሳይሆኑ በህብረት ስለመጡ ፤ እነዚህ ድርጅቶች በራሳቸው የፀና አንድነት የሌላቸው ስለሆኑ ፤ እንዴት ተደርጎ ነው “ኢትዮጵያን አገር አድን” የሚባለው አዲስ ንቅናቄ ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው የሚችለው? ቦዶ ናቸው ።

4ኛ) የዚህ የአዲሱ “አገር አድን ንቅናቄ” አንዱ አባል ድርጅት ደግሞ “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ” የተባለው ድርጅት ነው ። ይህ ድርጅት በሃሬናው ባላምባራስ ፤ በኮለኔል ፍፁም ይስሃቅ ኢንጂነርነት ተጠፍጥፎፈ የተሰራ ድርጅት ነው ።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው ።

ወቅቱ ግንቦት ሰባት ፤ ወታደራዊ ኃይሉን ማደራጀት የጀመረበት የመጀመሪያዎቹ ወራቶች ላይ ነው ። ግንቦት 7 በስድስት ወራት ውስጥ መንግስት መገልበጥ እንደሚችል (ሰበር ዜና) ያወጀበት ወቅትም ነበር ። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከዚህ አዋጅ ከጥቂት ወራት በኋላ ፤ ከግንቦት ሰባት ጋር በመተባበር መንግስት ለመገልበጥ አሲራችኋል ተብለው ፤ እነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታሰራሉ ። (ይህ ክስተት በራሱ ኤርትራ ውስጥ ሰፊ ታሪክ አለው ። ሌላ ጊዜ የምመለስበት ጉዳይ ይሆናል ።) ከነአሳምነው ፅጌ መታሰር በኋላ ፤ 6ቱ ወራትም ቀናቸውን ቆጥረው ያለምንም ኮሽታ ያልፋሉ ። ይህ በግንቦት 7 ደጋፊዎች ላይ ፤ ከፍተኛ የሆነ መደናገርን ፈጠረ ፤ ተስፋውም ሟሸሸ ።

ግንቦት 7 ፤ ይህን አላስፈላጊ ሁኔታ መሸፋፈን ስለነበረበት ፤ ከአገር ውስጥ ፤ ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ ሰዎች ተመልምለው በአስቸኳይ ወደ ኤርትራ እንዲገቡ እቅድ አወጣ ። ወደ ኤርትራ ሲገቡ ምን ተስፋ ተሰጥቷቸው እንደነበር ፤ ተመልምለው ወደ ኤርትራ ከገቡት ሰዎች የሰማነውናቸው ሁኔታዋች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ዛሬም በህይወት ስላሉ ምስክርነታቸውን መስጠት ይችልሉ ። ወደፊትም የምንሰማቸው ጉዳዮች እንደሚኖሩ ይታወቃል ። ሆኖም ግን በዚያው ሰሞን ሌላ “ሰበር ዜና” ታወጀልን ። የወያኔ ቤተ-መንግስት ጥበቃ ዋና አዝዥ የነበሩ ግለ-ሰብ የግቦት ሰባትን ተዋጊ ኃይል ተቀላቀሉ ። ይህ ግለሰብ ኮለኔል አለበል አማረ ይባላሉ ሲል እወጃው አስታወቀ ።

እንደተባለውም ኮለኔል አለበል አማረ ኤርትራ ገብተው ተገኙ ። መጀመሪያ ላይ ከአንዳርጋቸውና ከሌላ አንድ ሰው ጋር መስራት ይጀምራሉ ። በኮለኔል አለበል በኩል ወደ አንድ ሺህ ሰዎች ፤ በጎንደር በኩል ይመጣሉ ተብሎ ቃል ተገብቶም ነበር ። ሌሎች አምስት መቶ ሰዎች በአፋር በኩል አዘጋጅቻለሁ ያለ ሌላ ግለ-ሰብ ፤ እንዲሁ ከግንቦት ሰባት ለትራንስፖርትና ለተለያዩ ወጪዎች ገንዘብ ሲከፈለው ቆይቶ ፤ የመጨረሻው ሰአት ሲደርስ ፤ አንድም ሰው ሳያቀርብ እንደአስማተኛው ሁዲኒ ፤ እልም ብሎ ጠፋ ። ከደቡብ አፍሪካም የተወሰኑ ሰዎች ይመጣሉ ተብሎ ነበር ።

ከኬንያ ወደ ኤርትራ ለመግባት የተመለመሉት ሰዎች ደግሞ 10 ነበሩ ። እነዚህ 10 ሰዎች ከተመለመሉ በኋላ የወር ወጪያቸው በግንቦት 7 እየተከፈላቸው ለወራት ኬንያ ውስጥ በእንክብካቤ ተይዘው ቆይተዋል ። ሆኖም ግን የመጨረሻዋ ሰአት ደርሳ ፤ ወደኤርትራ ለመሄድ ቪዛ እንዲወስዱ ሲጠሩ ፤ ጥሪውን አክብረው የተገኙት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ ።

ከነዚህ ሁለት ሰዎች አንዱ ነው ፤ በአስመራና በሃሬና ከአንዳርጋቸው ጋር ቦክስ የገጠመው ። ወድ አንባቢዎቼ ይህን ግለሰብ በክፉ እንዳታዩት እጠይቃለሁ ። የራሱ ምክንያቶች ነበሩትና ፤ ሲያስፈልግ እመጣበታለሁ ። አንድ የማከብርለት ሁኔታ ግን አለ ። አንባቢዎቼም የአክብሮቴን ምክንያት ትጋሩኝ ዘንድ ላካፍላችሁ ። ይህ ወንድም በኬንያ ስደት ላይ የነበረ ሰው ነው ። በUNHCR የውጭ እድል አግኝቶ ፕሮሰስ ጀምሮ ነበር ። ይህን እድል ትቶ ነበር ወደ ትግል ሜዳ ለመግባት የወሰነው ። ፕሮሰስ ያልነበረቻው 8ቱ ደሞዝተኞች ግን ፤ ጉዟቸው የምር ሆኖ ከኤርትራ ኤምባሲ ቪዛ እንዲቀበሉ ሲጠሩ ፤ እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅ ፤ የውሃ ሽታ ሆነው በአየር ላይ በነው ጠፉ ። ሆኖም ግን ያን ሰሞን የተወሰኑ ሰዎች ከኢትዮጵያ በጎንደር በኩል ወደኤርትራ ገቡ ።

እነዚህ ሰዎች ከኢትዮጵያ እንደገቡ ፤ የሻእቢያው የሃሬና ተጠሪ ኮለኔል ፍፁም ፤ ኮለኔል አለበል አማረንና ሌላውን ሰው ጠርቶ ፤ ግንቦት ሰባቶች የሚታመኑ አይደሉም ። ከCIA ጋር እንደሚሰሩ የኤርትራ መንግስት ደርሶባቸዋል ። ከኛ ጋር የሚኖራቸው ቆይታ የኛ መንግስት ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ብቻ ነው ። ስለዚህ እናንተ ሁለታችሁ የአማራ ድርጅት አቁቁሙ ሲል ይመክራቸዋል ። ኮለኔል አለበል አማረ ፤ ይህን እቅድ ተቀብሎ ፤ ድርጅቱን በሻእቢያ ድጋፍ ያቁቁማል ። አብሮት እንዲያቁቁም የታጨው ሰው ፤ ይህን የሻእቢያ እቅድ ስለጠላው ብዙም ሳይቆይ ፤ ድምፁን አጥፍቶ ፤ ኤርትራን ለቆ ይወጣል ።

ግንቦት 7 ወጫቸውን ከፍሎ ለግንቦት 7 ጦር ተመልምለው መጡ ከተባሉት ሰዎች ውስጥ 7ቱን ኮለኔል አለበል አማረ ፈልቅቆ በማውጣትና ራሱን የአማራው ድርጅት መሪ በማድረግ ድርጅቱን ይመሰርታል ። የዚህ ድርጅት መሪ ኮለኔል አለበል አማረ ኤርትራን ለቆ ዛሬ ስዊድን ውስጥ በስደተኝነት ነዋሪ ነው ። ድርጅቴን አስወጥቼ ወደ አገር ቤት አስገብቸዋለሁ ሲል ማወጅ ከጀመረ ይኽው ድፍን ሁለት አመቱ። ይህ የአዲሱ “አገር አድን የጋራ ንቅናቄ” አባል ድርጅት ከስሙ በስተቀር ይኼ ነው የሚባል መሪም ሆነ አባላት የሌለው ድርጅት ነው። በሰው ህይልም ምንም የሌለው ባዶ ነው። ሌላ ባዶ።

ከነዚህ ባዶ ድርጅቶች ተነቃንቆ ተነቃንቆ ነው እንግዲህ አዲሱ “ኢትዮጵያን አድን የጋራ ንቅናቄ” ተቋቋመ ተብሎ (ሰበር ዜና) የሰማነው ። ዜናውን በሰማን በሁለተኛው ቀን ነው ደግሞ የንቅናቄው ም/ሊቀ-መንበርና የዴምሕት መሪ ሞላ አስገዶም ከ683 ወታደሮቹ ጋር የኤርትራን ድንበር ከውስጥ ወደ ውጪ በርቅሶ የወጣው ።

ሞላ አስገዶምን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በሃሬና የዴምህት ካምፕ ውስጥ ነበር። የተገናኘነው ወደ አርበኞች ግንባር ካምፕ ከመድረሳችን በፊት እዚያው ሃሬና ካለው የዴምህት ካምፕ ውስጥ ነው ። ሃሬና ውስጥ የዴምሕትና የአርበኞች ግንባር ካምፖች ርቀት በእግር ከአስር ደቂቃ በላይ አይወስድም። ወደ አርበኞቹ ግንባር ካምፕ ስሄድ የመጀመሪያዬው ጉዞዬ ነበር ። በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የተሰማሩትን አርበኞች ለማየት የነበረኝ ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። ሃሬና ከመድረሳችን በፊት ጉልች የምትባለውን ትንሽ ከተማ እንዳለፍን መኪናዎቻችን እንዲቆሙ ተደርጎ ሜዳ ላይ ከአንድ ሰአት በላይ እንድንቆይ ተደረገ ። የቆምንበትን ምክንያት ጠየቅሁ ። አርበኞቹ እናንተን ለመቀበል እየተዘጋጁ ስለሆነ አንዳንድ ነገሮችን እስከሚያጠናቅቁ ትንሽ ለመጠበቅ ነው የሚል መልስ ተሰጠኝ ።

የሆነው ግን ሌላ ነበር ። መጀመሪያ የተወሰድነው ወደ አርበኞች ግንባር ሳይሆን ወደ ዴምሕቶች ሃሬና ካምፕ ነበር ። እዚያ እንደደረስን ለኛ ብቻ ሳይሆን ከአስመራ ጀምሮ አብረውን ለተጓዙት የሻእቢያ ከፍተኛ የሲቪል ባለስልጣናት፤ የሙዚቃ ባንድ አባላትና የሻእቢያ የጦር መኮንኖች ቁርስ ተዘጋጅቶ ጠበቀን። ሞላን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት እንግዲህ እኛን እንግዶቹን ለመቀበል ሲደረግ በነበረው መስተንግዶ በዚህ የቁርስ ግብዣ ላይ ነው። ያኔ ታዲያ ከመተዋወቅ በስተቀር ለጥቂት ጊዜ እንኳ ቁጭ ብለን ያወጋንበት አጋጣሚ ትዝ አይለኝም ። የያኔው የዴምሕት መሪ ሟቹ ፍስኃ ኅ/ማርያም ስለነበር ማናቸውም ንግግሮች ሁሉ የሚደረጉት በሱ በኩል ብቻ ነበርና ሞላ አስገዶም አንፀባርቆ ሊታይ የሚችልበት አጋጣሚም አልነበረም ። ሆኖም ከፍስኃ ኅ/ማርያም ሞት በኋላ ካደረግኳቸው ተደጋጋሚ ጉዞዎቼ በአንዱ ላይ ከሞላ አስገዶም ጋር የመገናኘት እድል አጋጥሞኝ ነበር ።

በዋሽንግቶን ዲሲ አካባቢ በራዲዮ ፤ ለመላው አለም ደግሞ በኢንተርኔት ፤ አስተላልፈው የነበረውን የራዲዮ ፕሮግራሜ ወደ አስመራ በተደጋጋሚ አደርጋቸው ከነበሩ ጉዞዎቼ ጋር ፤ መጣጣም አልቻሉም ። ለኔ ያኔ ዋና ጥረቴ የነበረው የራዲዮ ቅስቀሳውን ስራ ወደ አገርቤት ማስገባት ነበር ።

እኔ አደርገው ከነበረው ጥረት በተሻለ በጊዜው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ከነበሩት ከአቶ አሊ አብዶ ጋር አቶ ስለሺ ጥላሁንና ኤልያስ ክፍሌ ስምምነት ላይ ደረሱ ። ለአርበኞች ግንባር የራዲዮ ፕሮግራም እንዲጀመር ፈቃዱ እንዲገኝ አደረጉ ። ይህ በአርበኞች ግንባር አባላት ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጠረ ። ስለሆነም ለራዲዮ ዝግጅቱ ስራ ስቱዲዮ ያስፈልግ ነበር። እዚህ በአሜሪካ ፤ በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ የነበረውን የራዲዮ ስቱዲዮ ፤ ነቅዬ ወደ አስመራ አዛወርኩት ። ትንሽ ማስፋትም ያስፈልግ ስለነበር አቶ ስለሺ ጥላሁን ከለንደን የላከው ሌላ ተጨማሪ መሳሪያ ጋር በማዳመር ስቱዲዮውን ለአርበኞች ከፈትኩ ። ለፕሮግራም አዘጋጆቹም አስፈላጊውን የመጀመሪያ ደረጃ ስልጠና ሰጠሁ ። ከዚህ በኋላ ወደ ዋሽንግተን ኑሮየ መመለስ ነበረብኝ ።

እኔ ከተመለስኩ በኋላ ስለሺና ኤልያስ ከኢሳኢያስ ጋር ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። በዚህ ቀጠሮ ላይ የአርበኞች ግንባር አመራርም አብሮ ከነኤልያስና ከነስለሺ ጋር ፤ ወደ ቤተ-መንግስት እንዲገባ ተፈቅዶለት ነበር ። ከነኤልያስ ጋርም እስከቤተመንግስት ድረስ ሄዷል ። ኋላ ላይ ግን ፕሬዚደንቱ ለናንተ የያዙት ሰአት አልቋል በሚል ሰበብ የአርበኞቹ መሪዎች ኢሳኢያስን ሳያዩትና ሳያገኙት ተመልሰዋል። ይህን ሁሉ እቅድ እነሞላ አስገዶም ሰምተውታል። ዴምሕት ከማንም የተሻለ ዝግጅትና ወታደራዊ ሃይል እያለው እንደ አርበኞች ግንባር ፍላጎታቸውን የሚያሰማላቸው ሰው ስለሌላቸው ፤ የመንፈስ ቅናት ሳያድርባቸው አልቀረም ። ስለዚህ በራሳቸው ጥያቄ ስለሺንና ኤልያስን ለማግኘት ፈልገዋል ። የምሳው ግንኙነትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር ።

ይህች ቀን ደግሞ ለኔ የሄድኩበትን ጉዳይ ጨርሼ ምሽት ላይ ወደ ዋሽንግተን የምበርባት ቀን ነበረች። ከሞላ አስገዶምና ከረዳቱ ጋር መገናኘት የነበረባቸው ደግሞ ስለሺ ጥላሁንና ኤልያስ ክፍሌ ነበሩ ። እኔም ሳልጋበዝ በቦታው ተገኝቻለሁ ። የአበሻ ግብዣ ነዋ ! ዴምሕቶች ከስለሺና ከኤልያስ ጋር ቀጠሮ እንዳላቸው ኮለኔል ፍፁም ሲረዳ እሱም እንደኔው ድንኳን ሰባሪ ሆኗል። አንባቢዎች እንደምትገምቱት የሁለታችን አመጣጥ በግብ የተለያየ ነበር ። በምሳው ላይ ኮ/ል ፍፁም ዝም ብሎ የባጡን የቆጡን መዘበራረቅ አበዛ ። ምንም አይነት ፍሬ ያለው ንግግር እንዳይደረግ ፍላጎት እንደነበረው በግልፅ ይታይ ነበር ። ኮለኔሉ ቀልድና ቧልት ቢያበዛም ቀልዱም ሆነ ቧልቱ ለዛቢስ ነበር ። በመኻከል የስለሺ ስልክ አቃጨለና ስለሺ ስልኩን ይዞ ወደ ውጪ ወጣ አለ ። ቀጠለና የኮለኔል ፍፁምም ስልክ እንዲሁ አቃጭሎ እሱም እንዲሁ ወጣ። እኔ እልያስ ክፍሌ፤ ሞላ አስገዶምና ረዳቱ ጠረጴዛው ላይ ቀረን። የሞላ ረዳት አጋጣሚውን በመጠቀም ኤልያስን እጁን ይዞት ወደ ጓሮ ወጣ አለ።

እኔና ሞላ አስገዶም ብቻችንን ቀረን። የምናወራው ነገር ስላልነበረ ወጋችን እንዲሁ ጉንጭ አልፋ የባጡን የቆጡን ወሬ ነበር ። በአጠቃላይ ሞላ አስገዶም ንግግር ለማሳመር የሚጥር ሰው አይደለም። ብዙ ማውራትም ተፈጥሮው አይደለም። ማዳመጥ ላይ ግን ንቁ ሰው ይመስላል ። ወታደራዊ ብቃቱንም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ ያስመሰከረ ጀግና ወታደር ነው። በትእዛዝ ቁሙ እስከሚባሉ ድረስ በረዳት አዋጊ ደረጃ ባረንቱ ድረስ ዘልቆ የገባውን ጦር ከመሩት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው። ወታደራዊ ችሎታውን ወዳጆቹም ሆኑ ጠላቶቹ በሚገባ ያውቁታል።

ኤልያስና የሞላ አስገዶም ረዳት ኮለኔል ፍፁም ሳይጋበዝ እዚህ ምሳ ላይ የተገኘው ከነኤልያስ ጋር ሊደረግ የሚችለው ንግግር ላይ መሰናክል ለመሆን እንደሆነ ገብቷቸዋል። በነኤልያስም በኩል ይኽው ግንዛቤ ተይዟል። ስለዚህም ኤልያስና የሞላ ረዳት ጊዜ ሳያጠፉ ቶሎ ተመለሱ። ባይነጋገሩም ሞላና ረዳቱ መልእክቱ በሚገባ በአጭሩ መድረሱ ላይ ተግባብተዋል። እኔም የሆነ ነገር እንዳለ ስለተሰማኝ፤ ምሳው አልቆ ጉዳዩን ልሰማ ጓጉቻለሁ። ኋላ ላይ ከኤልያስ እንደተረዳሁት መልእክቱ፤ “መታገል እየፈለግን ያለ ምንም እንቅስቃሴ በየካምፑ ተወዝፈን ነውና የምንውለው፤ እንዋጋ ዘንድ ኢሳኢያስ አፈወርቂን ጠይቁልን” የሚል ነበር ። (አንድ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄም ነበር። ከዛሬው ፅሁፌ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌለው አስፈላጊነቱ አልታየኝም) ከዚህ የምሳ ግንኙነት በኋላ ኤልያስንና ስለሺን እዚያው አስመራ ትቻቸው፤ የዛኑ ለት ማታ የተሳፈርኩበት አውሮፕላን ፀጥተኛውን የአስመራ ምሽት ሰንጥቆ ወደ ዋሽንግተን ይዞኝ እብስ አለ ።

ሞላ አስገዶም በ 1973 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ገና በልጅነቱ ነው ወያኔን የተቀላቀለው ። ከዚያ የወጣትነት እድሜው ጀምሮ ህይወቱ በውትድርና ያለፈ ሰው ነው ። የውትድርና ችሎታ አንድም በተፈጥሮ አለያም በትምህርት የሚገኝ ነው ። ሞላ አስገዶም በተፈጥሮው ወታደር ነው ። ወታደራዊ ችሎታውንም ፤ ለምሳሌ ከላይ እንደገለፅኩት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ፤ በባሬንቱ በኩል የሻእቢያን ጀርባ ሰንጥቆ በመግባት አሳይቷል ።

ሞላ አስገዶም ፤ ባለፈው ሳምንት በኤርትራና ሱዳን ድንበር ላይ ፤ የፈፀመው ታሪክ ደግሞ ማንም ወደደም ጠላም አሌ የማይለው ወታደራዊ ችሎታውን ያሳዬበት ሁኔታ ነው ። አንድ ባታሊዮን ጦር ይዞ ፤ የኤርትራን ድንበር ከውስጥ ወደ ውጪ በርቅሶ መውጣት ፤ የወታደራዊ ስትራቴጂ ችሎታንና ብቃትን ያሳያል ። በምእራቡ አለም በስደት ላይ የምትኖሩ ፤ ህሊና ያላችሁ ፤ ኢትዮጵያውያን ወታደራዊ ጠበብቶች እንዳላችሁ አውቃለሁ ። በወታደራዊ ጥበብ አኳያ ይህን ድርጊት እንድትተቹበት በዚህ አጋጣሚ እጋብዛለሁ ።

እንዲህ እንደ ሞላ አይነት ወታደራዊ ተግባር ሲፈፀም ፤ ወታደራዊ ጠበብቶች ፤ “የጀነራሎች አርት(art)” በማለት ይጠሩታል ። ወታደሮችህን በሚገባ ማዘጋጀት ፤ የዘመቻ ፕላንህን በሚገባ መምራት ፤ የሃይልህን እንቅስቃሴና አሰፋፈር ጠንቅቆ ማወቅ ፤ በመጨርሻም የጠላትህን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር ፤ ከአንድ ወታደራዊ መሪ የሚጠበቅ ነው ። ሞላ አስገዶም ይህንን ሁሉ ፈፅሞ ፤ የሻእቢያን ድንበር አጥር ፤ እጅግ ውሱን የሆነ መስዋእትነት ብቻ ከፍሎ ፤ 683 ወታደሮቹን ይዞ ወደ ሱዳን ገብቷል ። ይህ ማንም የማይክደው ሃቅ ነው ። የፈቀደም ፤ ያልፈቀደም፤ ደስ ያለውም ፤ ደስ ያላለውም ፤ አይኑን አፍጥጦ አይቶታል ። ይህ ወታደራዊ ታሪክ በታሪካችን መዝገብ ውስጥ የራሱን ስፍራ ይዟል ። ሃውልቱን ተክሏል ። የዚህ ወታደራዊ ተግባር ፤ ኀውልት ባለቤት ደግሞ ፤ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለደው የገበሬው ልጅ ፤ ሞላ አስገዶም ነው ። አበቃ ።

ከዚህ በኋላ የሞላ ድርጊት ያላስደሰታቸው ሰዎች በሹመት ድልድል አኩርፎ ነው ፡ በሙስና ተዘፍቆ ነው ፤ ከሃዲ ነው ፤ በማለት ስሙን የማጠልሸት ዘመቻ እየሞከሩበት ነው ። ያም ሆኖ ታዲያ እያበራ ያለን ኮከብ ላለማየት ፤ የራስን መዳፍ ፤ አይን ላይ መጋረድ ይቻል እንደሁ እንጂ ፤ ኮኮብን ተንጠራርቶ ማጥቆር ግን አይታለምም ።

ሞላ አስገዶም በምርጫው ላይ በሹመት አኩርፎ ነው ? በየትኛው ሹመት ? ሻእቢያ ዘንድ ሹመት የሚመጣው ከላይ በትእዛዝ ነው ። ሞላ አስገዶም ለ13 አመታት ይህን ያውቀዋል ። እንኳን ሞላ ቀርቶ ፤ እኔ ተመላላሹ ፤ ማን እንደሚሾም ትንቢት ተናግሬበት ተፈፅሞ አይተነው የለም እንዴ ?

በሙስና ነው ለተባለው አንድም ማስረጃ እስካሁን ድረስ የቀረበ የለም ። የግንቦት ሰባት ካዝና ደግሞ ከዴምሕት ካዝና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ። ከእነ ኮለኔል ፍጹም ተርፎ ፤ ሞላ አስገዶም ሊምቦጫረቅበት የሚችል ገንዘብ ለመሆኑ ከየት ይመጣል ?

ከሁሉ የሚደንቀው ሞላ አስገዶም ከዳ የሚለው አባባል ነው ። ሞላ ማንን ነው የከዳው ? “ግንቦት 7ን” ? “አገር አድን ንቅናቄውን ?” ወይስ ሻእቢያን ?

አዎ ሞላ አስገዶም ሻእቢያ ላይ ክህደት ፈፅሟል ። ለ13 አመታት ሻእቢያ ሞላ ላይ ፤ በተለይ ባለፉት ሰባት አመታት ፤ ተስፋ ጥሎበት ቆይቷል ። ሻእቢያ በአደባባይ ወጥቶ ሞላ ክዶኛል ሲል ግን አልሰማንም ። ይህን ክህደት እያራገቡልን ያሉት ደግሞ ፤ በጉዳዩ ላይ ምንም ጥልቅ የማያደርጋቸው ክህደቱ ያልተፈፀመባቸው ሰዎች ናቸው ። ለምን ? የሻእቢያ አፈ-ቀላጤውች ስለሆኑ ነው ወይስ ሌላ ?

ዛሬ ላይ ሞላ ከሃዲ ነው እያሉ ወሬ የሚያጮሁ ሰዎች የግንቦት 7 ሰዎች ናቸው ። የግንቦት 7 ሰዎች ፤ ከአንዳርጋቸው ጊዜ ጀምሮ ፤ በዴምሕት ላይ ለመፈናጠጥ ተስፋ አድርገው ነበር ። አንዳርጋቸው ከኢሳት ጋር ያደረጋቸውን የቴሌቪዥን ቃለ-መጠይቆች በሙሉ ወደኋላ ተመልሶ መመልከት ይቻላል ። ዴምሕት ጀርባ ላይ ለመፈናጠጥ ደግሞ ፤ አስፈንጣሪ (bouncer) ድርጅት ማግኘት የግድ ነበር ። በነመአዛው ጌጡ የምትመራው አርበኞች ግንባር ለዚህ ተስማሚ ነበረችና ዶ/ር ብርሃኑ በሌሉበት ሊቀ-መንበር ሆነው ተሾሙባት ። በተወካይ ( በነአምን ዘለቀ ) አማካይነት ውህደት ተደረገ ። ሁሉም ነገር በእቅዱ መሰረት የሚሄድ መሰለ ። የመጨረሻው ታሪካዊ ሁኔታ ላይ ለመገኘትና ፤ የታላቁ ታሪክ ባለቤት ለመሆን ዶ/ር ብርሃኑ ሁለት አጃቢዎቻቸውን ይዘው ወደ አስመራ አቀኑ ። “የኢትዮጵያን አገር አድን ንቅናቄም” ጳጉሜ 3 ቀን ተመሰረት ተባለ ። ( ሰበር ዜና )። ጳጉሜ አምስት ቀን በአዲሱ አመት መባቻ ላይ ፤ የንቅናቄው ምክትል ሊቀ መንበር ሞላ አስገዶም ፤ ለመፈናጠጫ የታሰበው የንቅናቄውን መሰረት ዴምሕትን ንዶ ፤ ከስራ አስፈጻሚው 37 አባላት ውስጥ 26ቱን ይዞ ዴምሕትን ጭንቅላቱን ሰይፎት ወጣ ።

በዚህ አይነት ፤ የተናደው ምኞትና ተስፋ ፤ የግንቦት 7 እንጂ የሞላ አስገዶም አልነበረም ። በዚህ ሁኔታ ፍርስርሱ የወጣው ፤ የሻእቢያ ድንቅ ፈጠራ “የአገር አድን ንቅናቄው” ብቻ አልነበረም ፤ የግንቦት 7 ተስፋም ጭምር እንጂ ። ይህ ከሆነ ክህደት እየተባለ የሚወራው ፤ ሞላ አስገዶም ግንቦት 7 ላይ ክህደት አልፈፀመም ። ተግባራቸውና የመረጡት መንገድ ነው የከዳችው ። ሞላ አስገዶም ዴምሕትን በዘመን ፤ የላብና የደም መስዋእትነት ከፍሎበታል ። ለምንድነው ለእናንተ ፍላጎት የሚዋጋው ወይም የሚሞተው ?

አንዳንድ ታዛቢዎች እንዲያውም እንዲህ እያሉ ይተቻሉ ። “ያለፈ የፖለቲካ ታሪክ ስንመለከት ፤ ቀስተ-ደመና የምትባል አንዲት ትንሽ ድርጅት ተይዞ ቅንጅትን ለማፍረስ ተጠቀሙባት ። ወደ ውጪ እንደወጡ ቅንጅትን አፍርሰው ግንቦት 7ን ገነቡበት ። አርበኞች ግንባርን ፤ ከአርበኞቹ ሰረቁት ። ዴምሕትን ግን አልሆነላቸውም ።”

እንደሚታወቀው ሞላ አስገዶም ሃሬና ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን ተዋጊዎች ነው ይዞ የሄደው ። አሁን እየደረሱ ያሉ ዜናዎች እንደሚያመላክቱት ፤ ከተሰነይ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው የዴምህቱ ካምፕ ፤ እንዳለ ተበትኗል ። በካምፑ ውስጥ የቀሩት አቅመ-ደካሞችና ህፃናት ልጆች የታቀፉ ሴቶች ብቻ ናቸው ። ወታደሮቹ ካምፑን ለቀው ከነመሳሪያቸው በተለያየ አቅጣጫ ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ ዘልቀው በመግባት ላይ ናቸው ። ከሶስት ቀናት በፊት ፤ ባለፈው ሃሙስ የሞላ አስገዶምን ፈለግ በመከተል የራሳቸውን ቡድን ፈጥረው ከካምፑ የተበተኑት ተቀላቅለዋቸው ፤ ከሻእቢያ ወታደሮች ጋር በድንበር አካባቢ ውጊያ እያደረጉ ናቸው ።

ባለፈው ወር ጓዛቸውን ጠቅልለው ገቡ ፤ ከተባሉት ሶስት የአሜሪካ ዘማች በረኸኞች ውስጥ ፤ አንዱ ትላንት ወደ አርብ ወደ አሜሪካ መግባት ነበረባቸው ። ከሞላ አስገዶም ጥሎ መሄድ ጋር በተያያዘ የሚጣራ ጉዳይ ስላለ ፤ ላልተወሰን ጊዜ ከአስመራ እንዳይወጡ ተደርጓል ።

እንደተለመደው አንድ ጉዳይ ልተንብይና የዛሬውን ፅሁፌን ላብቃ ። አሟረተ አትበሉኝ እንጂ ፤ በሻእቢያ ምክንያት ፤ በቅርቡ ከዚህ ከአሜሪካ በሄዱት ወገኖች ላይ ፤ ሊከሰት የሚችል አዲስ ሁኔታ ይኖራል ። በዚህ ላይ ከሻእቢያ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ሁሉ ፤ ወርድና ስፋታቸው በሻእቢያ እየተለኩ ስለሚዘጋጁ ፤ የፈለጉትና ያሰቡት ስለማይሆን ፤ ከሚቀጥለው የኢትዮጵያ አዲስ አመት በፊት ፤ አስመራን ለቀው ወደየመጡበት
ይመለሳሉ ።

ሲፕቴምበር 19/2015
ላስ ቬጋስ ኒቫዳ

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: