The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የግንቦት 7 የእቃ እቃ ጨዋታ (ከደምስ በለጠ)

ይህ አዲሱ 2008 የኢትዮጵያ አመት ከዋዜማው ጀምሮ ፤ በየሳምንቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያሳየን ነው ። የሐረር ሰው “አጃኢብ” ይላል ፤ ነገር አልጥም ሲለው ። ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆኑኝ ፤ ከጁላይ 18 ቀን ጀምሮ እያስተዋልኩ ያለሁት ጉዳይ ነው ። ጁላይ 18 ቀን 2015 እ.አ.አ ፤ በኢሳት ሰበር ዜና ፤እንዲህ ሰምተን ነበር ። “ወደትግል ለመግባት የመሪዎችንም መስዋእትነት ይሻልና የግንቦት 7 መሪዎቹ ወደ ትግል ገቡ” ነበር የተባለው ።“የግንቦት ሰባት አመራር ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ትግል ሜዳ ገባ” ሲባል ፤ በሁሉም አቅጣጫ ጭብጨባው ሰማይ እንዲደርስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም ። የጉዳዩን ታላቅነት ለመግለፅ ፤ የግንቦት ሰባቱ መሪ ደመወዛቸው ሁለት መቶ ሺህ ፤ ማእረጋቸው ፕሮፌሰር ፤ ችሎታቸው ከሰው የበለጠ ፤ እየተባለ ተጋኖ ተወጋ ። ወደዚህ ትግል የገቡትና በፎቶም ያየናቸው የግንቦት ሰባቱ ሊቀ-መንበር ብቻ ሳይሆኑ ፤የኢሳቱም ዳይሬክቲንግ ማናጀር ነበሩ ። ዜናውን ለማስታወስ ሊንኩን ይጫኑ

አሁን ደሞ ያ ሁሉ ጭብጨባ ተደርጎ ፤ ጉሮ ወሸባዬ ተዘፍኖ ሄደው ፤ ዛሬ የተመለሱት ዘማች አቶ ነአምን ዘለቀ ፤ እንደነገሩን የዘመቻ ተልእኳቸውን አጠናቀዋል። በዘመቱ በሁለተኛ ወራቸው በረኃ የገቡት ዘማች “ተልእኮዬን ጨርሻለሁ” ብለው ሲመለሱ ትንሽ ግር ማለቱ አልቀረም ። ተመላሹ ዘማች ፤ ገና እግራቸው አሜሪካን እንደረገጠ ፤ አንድ ወጥ የሆነ ቅጂ ፤ ቃለ- መጠይቅ በኢሳት ራዲዮ የተደረገ ነው ሲሉ በየድረ-ገፁ በተኑ ። ውለው ሳያድሩ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮም ቀርበው እንዲሁ ሌላ ቃለ-መጠይቅ አደረጉ ። የሚዲያውን መስክ የምንረዳ ሰዎች ይህን መሳይ ጉዳይ ሲከሰት ፤ “የሚዲያ ወከባ” እንለዋለን ። ያፈጠጠን ጉዳይ ለማስቀየስ ወይም ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ ፤ በሌለ ጉዳይ ላይ አቧራ ማስነሳት ማለት ነው ። ላብራራ።

ተመላሹ ታጋይ የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የአርበኞች ግንቦት ሰባት የውጪ ጉዳይ ሃላፊ፤ ጓዜን ጠቅልዬ ለትግል ገባሁ ብለውን በሰበር ዜና ሰምተን ነበር። ሰው ምነው ለድል ሳያበቁን ተመለሱ ብሎ ህዝቡ መጠየቁ አይቀርምና ፤ አስቀድመው በየሜዲያው ላይ ፤ ወከባ መፍጠር ተገቢ መስሎ ታይቷቸዋል ። “ጉሮ ወሸባዬ ባልዘፈንሽ ፤ ዘንድሮ ባላፈርሽ” ይላል የአገሬ ሰው። ምናልባት ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ፤ በራሳቸው ፈቃድ ፤ ይሸወዱ እንደሆን ነው እንጂ ፤የሚዲያ ወከባው ፤ በነቃው ሕ/ሰብ ዘንድ ውኃ አልቋጠረም ። ዛሬ ሰው ፤ እንደድሮው ዝም ብሎ “ይሁን እስቲ” እያለ ማለፉን ትቶታል ። መጠየቅ ጀምሯል ። እኔም እንዲሁ አንዳንድ ጥያቄዎችን ላነሳ ነው ። በአሜሪካ ድምፅ ከተላለፈውም ሆነ ፤በኢሳት ተደረገ ፤ ከተባሉት ቃለ-መጠይቆች ፤ ባዶ የሆኑትን ስሜት የማይሰጡ ፤ አባባሎች ትቼ ፤ የተወሰኑ ነጥቦችን ቀጥዬ አነሳለሁ ።

ኤርትራ ጋር ተስማምተን ነው የምንሰራው ። ነው ያሉን ከዘመቻ ተልእኳቸውን ጨርሰው የመጡት ፤ የኢሳት ሜዲያ ዳይሬክተር ። ይህ አባባል በራሱ ፤ዋጋ የሚያስከፍልበት ግዜ ሩቅ አይደለም ። ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ስምምነት አስታክከው ፤ የወያኔ አገዛዝን ፤ “ይህ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዝ” ብለው ያወግዙታል የኢሳት ሜዲያ ዳይሬክተሩ ። ወያኔ ዘረኛ ስለሆነ ወይም ዘራፊ ስለሆነ ፤ ግንቦት 7 ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሻእቢያ ጋር መስማማት አለበት ? የተደረገውስ ምን አይነት ስምምነት ነው ? እኝሁ የዘመቻ ተመላሽ ሰው ይባስ ብለው ፤ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ ፤ ሻእቢያ ወይም ኤርትራ ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የStakeholderነት
( ባለድርሻ አካልነት) መብት አለው ሲሉ ተናግረዋል ። ይህን ሊያሰኛቸው የቻለ አንድ ምክንያት መኖር አለበት ። በኢትዮጵያ ጉዳይስ ሻእቢያ ምን አይነት ባለድርሻ አካል ነው ? ሁሉም ኢትዮጵያዊ የማወቅ መብት አለውና ስምምነቱን ግልጽ ልታደርጉት ይገባል ። አንባቢ ሆይ ፤ የራስዎን ፍርድ ይሰጡ ዘንድ ፤ የአሜሪካ ድምፁንም ሆነ የኢሳቱን ቃለ- መጥይቆች በዚህ ሊንክ ላይ ያዳምጡ

እኔም ሆንኩ ፤ ሻእቢያን ከጠዋቱ በሚገባ የሚያውቁ ወገኖች ብሎም ከልብ አገራቸውን የሚወዱ ሰዎች ፤ ደግመን ደጋግመን ያስጠነቀቅነው ጉዳይ አለ ። ሻእቢያ የኢትዮጵያን መፈራረስ ሳያረጋግጥ እንቅልፍ ባይኑ አይዞርም ብለናል ።

ለዚህም ሻእቢያ ምክንያት አለው ። ኤርትራ ዛሬ አንድ ነፃ ሐገር ነች ። ኤርትራ ፤ ኢትዮጵያን ያህል ግዙፍ አገር ከጎኗ አስቀምጣ ሳትባንን የምታድርበት ሌሊት በፍፁም አይኖርም ። የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ፤ውሎ አድሮ የባህር በር ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ይሆናል ። ስለዚህ ሻእቢያ የኤርትራን ነፃነት ለማረጋገጥ ፤ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ወጥቶ በጥቃቅን መንግስታት እስክትከፋፈል ድረስ እንቅልፍ አይወስደውም ።

ግንቦቶች እንደግንቦት 7 ድርጅት ፤ ከሻእቢያ ጋር የመሰረታችሁት ፍቅር የራሳችሁ ሊሆን ይችላል ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፤ ከማንም ጋር ለመስማማት ግን ፤ ምንም አይነት ስልጣንም Mandate እንደሌላችሁ በግልፅ ልታውቁት ይገባል ። ተስማምታችሁ በምትሰሩበት ስምምነት ላይ “ባለ ድርሻ አካል” ተብሎ በአቶ ነአምን የተገለፀው ፤ ሻእቢያ ድርሻው ምን ያህል ነው ? ሻእቢያን የምናውቀው ሰዎች ደግሞ ፤ ምን ድርሻ ሊጠይቅ እንደሚችል መገመት አያቅተንም ። ኋላ ሂሳብ ማወራረድ እንዳይመጣ ፤ በኢትዮጵያ ላይ ያላችሁን ኢምንት የሆነ ድርሻ ፤ አግዝፋችሁ እንዳትመለከቱት እንመክራለን ። በኋላ ውርድ ከራሴ ።

አንባቢ እንዲያስተውለው የምፈልገው ጉዳይ የሚከተለው ነው ። ግንቦት ሰባት ሻእቢያን ባለድርሻ አካል ካደረገ ፤ ዋና ፅ/ቤታቸውን አስመራ ያደረጉት የኦሮሞ ነፃ አውጪና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባሮች ፤ የመገንጠል ጥያቄ ባቀረቡባቸው የኢትዮጵያ ግዝቶች ላይ ፤ ለሻእቢያ ምን ያህል ባለ ድርሻነት ሰጥተውት ይሆን ?

ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ በኢሳት ሜዲያ ዳይሬክትር አቶ ነአምን ዘለቀም ሆነ በዶክተር ብርሃኑ ነጋ የተሰጡት ቃለመጠይቆች ፤ እንደ አሸኛኘታችሁና ፤ እንደ ተመልሶ አመጣጣችሁ አስቂኝ ነው የሆነብኝ ።

ድሮ ልጆች ሆነን ከበደ ሚካኤል ለአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የአማርኛ መመሪያ መጻህፍት ያዘጋጁልን እንደነበር ብዙዎቻችን የምናስታውስ ይመስለኛል ። እነዚህ መፃህፍት በተረቶች የተሞሉ ስለነበር ፤ የዚያ ዘመን ልጆች ፤ በደስታ እናነባቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል ። ከነዚህ ተረቶች አንዷን በአጭሩ ላስታውስ ።

ቀበሮዋ በመንገዷ ላይ ስትጓዝ አንድ አጥር ግቢ ውስጥ የወይን ፍሬ ታያለች ። የወይን ፍሬው ያስጎምጃታል ። ቶሎ ወደ ግቢው ትገባና የወይን ፍሬውን ተንዠርጎ ከተሰቀለበት አልጋው ላይ ታየዋለች ። በጣም ጎመጀች ። አፏ ውኃ ሞላ ። ፍሬውንም ለማውረድ ወደ ላይ መዝለል ጀመረች ። ዘለለች ፤ ዘለለች ፤ ፍሬው ላይ ለመድረስ ግን አልቻለችም ። በመጨረሻ ፍሬውን እንደማታገኘው ስታረጋግጥ ፤ “ድሮም ዝም ብዬ ነው የለፋሁት ፤ ይህ የወይን ፍሬ እኮ አይጣፍጥም” ብላ መንገዷን ቀጠለች ፤ ይባላል ።

ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ ፤ ከዶክተር ብርሃኑ ነጋም ሆነ ከአቶ ነአምን ዘለቀ የሰማነው ፤ ኩብለላው እንኳን አሁን ሆነ የሚል ነው ። ጉዳዩን አስመልክቶ ዶክተር ብርሃኑ ትንሽ ቅመም ቢጤ ጣል አድርገውባታል ። “ይህ ክስተት ወደፊት አገር ውስጥ ሲገባ ቢሆን ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን ነበር” ፤ ብለዋል ። ይህች ቅመም ሻእቢያን እዘለኝ ተብሎ አገር ቤት ለመግባት ታስቦ እንደሆነ ፤ ሻእቢያ እንኳን እናንተን ሊያዝል ለራሱም መቆም ያቃተው ፤ እየፈራረሰ ያለ ፤ ለራሱ ህዝብ እንኳ መሆን ያቃተው መንግስት ነው ።

አዲሱ አመት መባቻ ላይ ፤ የንቅናቄውን ጥንካሬ ፤ የብዙሃኑን የመተባበር ጥያቄ የመለሰ ፤ እንዳይፈርስ መጠበቂያ የተደረገለት ፤ በፀና መሰረት ላይ የቆመ ፤ ሌላም ሌላም ያሉት ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሴፕቴምበር 9 ቀን 2015 ከንቅናቄው መመስረት በኋላ የሰጡትን ቃለ-መጠይቅ በሚቀጥለው ሊንክ ያዳምጡ ።

እንደገና ከሳምንት በኋላ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በሴፕቴምበር 9 ቀን 2015 ላይ ፤ 2ኛ ኢንተርቪው ከንቅናቄው መናድ በኋላ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ ደግሞ ፤ በሚከተለው ሊንክ ላይ ያዳምጡ ። ወደ ሊንኩ ከመሸጋገራችን በፊት ፤ በፊት አንድ ነገር ልበል ።

መርካቶን ከነግሳንግሷ የምታውቁ ፤ አለያም እንዴት የጩልሌ ሰፈር እንደሆነ የተነገራችሁ ወይም የስማችሁ ሁሉ የምታውቁት አንድ ነገር አለ ፤ መርካቶ መግዣ ፤ መርካቶ መሸጫ ። መርካቶ ማለት በቃ መግዛት መሸጥ ፤ መግዛት መሸጥ ማለት ነው ። ታዲያ የመርካቶ ሻጮች ፤ አንድ ነገር ለመግዛት ሄደህ እቃውን ሲሸጡልህ ፤ የእቃውን ጥራት ፤ ረዥም እድሜ ፤ የተሰራበትን አገርና ማቴሪያሉን ጭምር አጋነው ፤ ሰማይ አድርሰው ፤ዋጋውን ከፍ አድርገው ይሸጡልኻል ። ያንኑ እቃ ሳትጠቀምበት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልሰህ ግዙኝ ብትላቸው ፤ እቃው የማይረባ ፤ርካሽ ፤ የተሰራበት ማቴሪያልም እድሜ ቢስ ፤ ሰሪው አገርም ከአለም ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ፤ ሳያፍሩ አይንህ ላይ ይነግሩሃል ። ይህን ምሳሌ የተጠቀምኩት ፤ ከላይ ያለውንና ቀጣዩን ቃለ-ምልልሶች እንድታነፃፅሩበት ነው ።

ነአምን ዘለቀ ከኤርትራ ዘመቻ መልስ ትግሉ እመር ብሏል ፤ ብለውናል ። አድማጮችዎን እንዴት ቢገምቷቸው ነው ?

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ፦

1ኛ) ተማምናችሁበት የነበረው ፤ የዴምህቱ መሪ ሞላ አስገዶም 683 የሚሆን ተዋጊ ጦሩን ይዞ ሄዶ ፤
2ኛ) ትብብሩ ተቋቋመ በተባለ ማግስት ከሞላ መሄድ ጋር ፤ ፍርክስክሱ ወጣ ፤
3ኛ) ጓዛቸውን ጠቅልለው ለትግል ወደ ሜዳ ገቡ የተባለልዎት ታጋይ ፤ እርስዎ ራስዎ ፤ ከሁለት ወር ቆይታ በኋላ ተልእኮዬን ጨርሻለሁ ብለው ተመልሰዋል
4ኛ) የአማራውና የአፋሮቹ ንቅናቄዎች ፤ መሪዎች ወጣ ብለው ፤ እንደተባባሪ ድርጅት ፤ አንዲት ቅንጣት መግለጫ እንኳ ባልሰጡበት ሁኔታ ፤ መኖራቸው እንኳ አይታወቅም ፤ ታዲያ እንዴት ነው ትግሉ እመር ያለው ?

በነገራችን ላይ የዴምህት ሰራዊት ከሞላ አስገዶም በኋላ አሁንም እየተናደ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለ ሰራዊት ነው።

ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ሞላ አስገዶም ይዞት የሄደውን ተዋጊ ኤርትራ ቀርቷል እየተባለ ከሚነገረው ፤ ሰራዊት ቁጥር ጋር በማወዳደር ፤ እዚህ ግባ የማይባል ነው ፤ በማለት መከራከሪያ ለማቅረብ ይከጅላቸዋል ። ለመሆኑ ፤ እነዚህ ሰዎች ፤ የዴምህት ሰራዊት ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉን ? አንዳንድ ሰዎች ዩናይትድ ኔሽን 20 ሺህ ይገመታሉ ብሏል ይሉናል ። ዩናይትድ ኔሽን አስመራ ሄዶ ተዋጊዎቹን አስልፎ ቆጥሯል ? ወይስ ከዚህ በፊት ወደ አስመራ ሄደን ከነበርነው ሰዎች ከሚገኙ የፅሁፍና አንዳንድ የንግግር መረጃዎች ፤ ተነስተው ነው ይህን ግምት የሚሰጡት ? ይህም ቢሆን ግምት ነው እንጂ የተረጋገጠ ቁጥር አይደለም ። የአለም አቀፍ ድርጅቶች ፤ የሚሰጡት የግምት ቁጥር ሁሉ ፤ ትክክል ነው ብለን የምናምን ከሆነ ሞኝነት ነው ። የአንድ ነገር ቁጥሩ ከፍም ዝቅም የሚደረገው ፤ የአለም አቀፉ ድርጅት ፤ አሳዳሪ ከሆነው መንግስት ፤ ፍላጎት ጋር እየተጣጣመ ነው ።

ከዚህ ሌላ የሞላ አስገዶም ወደኢትዮጵያ መግባት ፤ ቀሩ የሚባሉት ተዋጊዎች ላይም ቢሆን የሚያሳድረው የስነ-ልቡና ተፅእኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም ። በታሪክ እንደምናስታውሰው ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረጉ ጦርነቶች ላይ ፤ የደርግ መኮንኖች እየከዱ ወደ ጠላት ወገን ይገቡ በነበረበት ወቅት ፤ አይደለም ወታደሩ ፤ ሲቪሉ ህዝብ ላይ ፤ ይፈጠር የነበረው የሞራል ውድቀት በቀላሉ የሚገመት እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ። የኢትዮጵያ ሰራዊትስ ብትንትኑ የወጣው ፤ ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ወደ ዚምባቡዌ ከኮበለሉ በኋላ መሆኑ እስካሁን ድረስ በብዙዎቻችን ዘንድ አሻራው ያልጠፋ ጉዳይ ነው ። ስለዚህ ዴምሕት አሁንም አለ እየተባለ የሚነገረውን ለማመን የምቸገርበት ደረጃ ላይ እገኛለሁ ። ሁሉንም በሂደት የምናየው ይሆናል ።

በመጨረሻም አቶ ነአምን እንዲያውቁልኝ የምፈልገው ፤ እኛ በሬ ወለደ ብለን ፅፈንም ፤ ተናግረንም እንደማናውቅ ነው ። በሬ ወለደ ብሎ ለመናገር ሻእቢያ የከፈለን ቤሳ ቤስቲን የለም ። እርስዎ በዳይሬክተርነት የሚመሩት ፤ ኢሳት ሜዲያ ግን ፤ ከሻእቢያ በየአመቱ $400,000 ሺህ ዶላር እንደሚያገኝ ፤ ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሾልኮ በወጣባቸው የድምፅ ቅጂ ላይ መስማታችን ፤ ፀኃይ የሞቀው ጉዳይ ነው ። ስለዚህ በሬ የሚያሳወልደው እየተከፈለው የሚሰራ ነው ።

በተጨማሪ አቶ ነአምን ዘለቀ ፤ እኛ እንድንመከር ያስተላለፉልን መልእክት ሰማሁ ። ያልተረዱትን ነገር እንዳለ ግን ልግለጽልዎ ። እኛ ሻእቢያን ሄደን አይተነው በተግባር ተመክረናል ። ይቻል እንደሁ ብለን እናንተን እየመከርን ነው ። ካልተቻለ ደግሞ እንዲህ እንደሰሞኑ የዘመቻ ጉዞዎ ፤ በየምክንያቱ ፤ በየሁለት ወራችሁ እየተመለሳችሁ የኔ ተልእኮ ይህ ነበር ፤ ያ ነበር ፤ ነገም ልሄድ እችላለሁ ፤ ልትሉን ትችላላችሁ ። ከዚያም የሚዲያ አቧራ በማስነሳት ልታስቀይሱ ትሞክራላችሁ ። እንዳው ለመሆኑ ግን ፤ ለምን መጀመሪያ ስትሄዱ ተልእኳችሁን አትናገሩም ነበር?

ባለፈው ሳምንት ፅሁፌ ላይ ፤ ከሚቀጥለው የኢትዮጵያውያን አዲስ አመት በፊት እንደምትመለሱ ተንብዬ ነበር ። እርስዎ ይህን በተናገርኩ በሁለተኛው ቀን ከአስመራ ከተፍ ሲሉ በእጅጉ ደነቀኝ ። ነገሩ ሁሉ የእቃ እቃ ጨዋታ ሆነ እንዴ ? ብዬም ታዝቤአለሁ ። ከዚህ ሌላ ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመለሱበትን ቀን ባለፈው ፅሁፌ ላይ ያስቀመጥኩት የጊዜ ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ የሚመለሱበትን ምክንያት ደግሞ ፤ ለእርስዎም ሆነ ለአንባብያን ልተንብይ ። በእቅድ የተያዘችው ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ፤ ሊመለሱ የሚችሉባት ምክንያት ፤ “የጤና እክል ደረሰብኝ” የምትል ትሆናለች ። ይህንን መረጃ ፤ ያገኘሁት ደግሞ ራሳቸው ዶ/ሩ የተናገሩትን በማጤን ነው ። መፃኢውን አዲስ አቧራ ደግሞ እንጠብቃለን ።

ሴፕቴምበር 26 2015 እ.አ.አ.
ላስ ቬጋስ ኒባዳ ።

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: