The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ዝምታው እስከ መቼ? – አንተነህ ገብርየ

Ethiopia _ Satenaw

 

ኣባይ የኢትዮጵያን ለም አፈርና ሌሎች ማእድናትን ህወሃት የኢትዮጵያን ሀብትና ታሪካዊ ቅርሶችን ይዘው ወደ ውጭ ይኮበልላሉ።እኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በጀግኖች ወላጆቻችን ታሪክ እየተኮፈስን ኢትዮጵያን ከጥፋት ልናድናት አልቻልንም ዝምታው እስከ መቼ?

አንተነህ ገብርየ  2008 ዓ/ም

መግቢያ፦ ደርግ መኢሶንን እና ኢህአፓን አናርኪስቶች፤ኢዲዩን አድሃሪ፤ተገንጣይ ወንበዴዎች (ሻእብያና ህወሃት(ወያኔን) ተዋጋ ረገመ ፤ እንዲወገዙ አደረገ በንግግር ብጥልጥላቸውን አወጣው በርግማን ግን ሊሞቱ አልቻሉም። ሻእብያና ወያኔ ዛሬም አሉ እየረገምናቸው እንገኛለን-ግማሾቹ ተራጋሚዎች ሻእብያን ወዳጅ በማድረግ ህወሃት(ወያኔን) ለማውረድ ኤርትራ ውስጥ እየታገሉ ይገኛሉ።ከነዚህ አናሳዎች ባልተናነሰ ሁኔታ የኢትዮጵያን ጥፋት አራማጆችም ነብስና ስጋ ዘርቶላቸው በትግሉ ጎራ ባይሰለፉም ከሕብረተሰቡ ውስጥ ተሰግስገው የትግል ሂደቱን በማንኮላሸት ላይ ይገኛሉ።የትግሉን ሂደት ብቻም ሳይሆን የስቪክ ማህበራትንም እንዳይደራጁ ስለሀገራቸው እንዳያስቡና እርስ በርሳቸው እንዳይተባበሩ የመከፋፈል በሽታ ወጥሮ ይዟቸው እናገኛቸዋለን።በተለይ ከውድቀቱ መማር የተሳነው የኢህአፓ መስራችና ከ43 ዓመት በላይ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት የመራው ኢያሱ አለማየሁ በየማህበራዊ ገጾችና በመገናኛ ብዙሃን ብቅ እያለ የሚተፋው መርዝ ዛሬም ከጥፋቱ የማይታረምና የኢትዮጵያን ጥፋት በአለ የሌለ አቅሙ ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ውድቀት እየጠበቀ የሚገኝ ግለሰብ ነው።ኢያሱ አለማየሁ ጅብ ከማያውቁት አገር ሄዶ ቆዳ አንጥፉልኝ አለ እንዲሉ ታጥቦ የማይጠራና ትውልድ ሊረሳው የማይችል ከገማ እንቁላል የከፋ ታሪክና ጠባሳ አስቀምጦ እንዲህ መመጻደቁ የባለ ሁለት አገር ዜግነቱን ተማምኖ እንደሆነ በግልጽ መናገር ይቻላል።የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ነውና የአንድ ዘመን ትውልድን አስበልቶ እንደነ ክቡር ቢወደድ አዳነ መኮንን የመሰሉ አንጋፋ አርበኛና ታጋይ ጀግኖችን አስገድሎ በኢህአፓ ታጋዮች ደም በተገኘ ገንዘብ ለድርጅት ጽ/ቤት ተብሎ የተገዛን ቤት በግል ንብረትነት ወርሶ ኢህአፓን ከሁለትና ከዚያም በላይ ከፋፍሎ ራሱን አንግሶ ብቅ ለማለት ሲከጅለውና ሲጃጃል ልክ-ልኩን ልንነግረው ይገባል።

ወደ መነሻ ነጥቤ ልግባና የአባይ ወንዝ እና ህወሃትን የጠቀስኩበትን ምክንያት ላስረዳ፦

አባይ፦አፈሩን፤ሰውን፤እንሰሳውን፤ግንዱን፤ሳር ቅጠሉን ከኢትዮጵያ ጠራርጎ በመውሰድ የደረቀውንና የአቧራ ብቻ የሚቦልበትን የግብጽና የሱዳን በርሃማ መሬት በማለምለም ክረምትና በጋ በማምረት ህዝባቸውን ያለምንም ችግር እንዲመግቡ አስችሏቸዋል።በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያን የነጣችና በየአመቱ የድረሱልኝ ጥሪ የምታሰማ ችጋራም አገር አድርጓት ይገኛል።አሁን ደግሞ የባሰውን አባይን እንገድባለን በማለት ህዝቡ ለነፃነቱና ለመብቱ እንዳይታገል ፊቱን ለማዞርና አቅጣጫውን ለማስቀየር በረቀቀ ዘዴ የተወጠነው ሴራ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ 1/ ህዝቡ የሚያካሂደውን ትግል ለማንኮላሸት፤2/በህዝቡ ውስጥ ያለውን አመለካከት ለመፈተሽና አሸባሪ የምትለውን የህወሃት ታቤላ ለመለጠፍ እነሆ እስከ ዛሬ ማንህም አድርጎት የማያውቀውን አባይን ገድበን የውሃ ጥማትህን፤የኤሌክትሪክ ችግርህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልናስወግድልህ ስለሆነ ገንዘብህን አምጣ በማለት የወደደውን በፈቃዱ፤ያልወደደውን በግዱ ገንዘቡን እየዘረፉት ይገኛሉ።

Ethiopia _ Satenaw

በመሠረቱ ህወሃት አባይን በመገደብ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ለመቅረፍ አስቦ ሳይሆን መጀመርያ የህዝቡን ድኽነት ለማፋጣን ገንዘብ የሚመዘብርበት ስልት ሲሆን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ግድቡ ሥራ ላይ ቢውል እንኳን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአጎራባች አገሮች በመሸጥ ሰፍሳፋ የሆነ የንዋይ ጥማትን ለማርካት የታለመ እንጅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።በሌላ መልክ እንይው ከተባለም የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ግጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሰበባ-ሰበቦችን በመጫር ህዝብን እልቂት ውስጥ ለመክተት የታሰበ ከመሆን አይዘልም።ሳትዋጋ ንገስ ቢሉት የግድ ተዋግቸ እንደሚባለው ሆኖ እንጅ የአባይ ገባር ወንዞች ላይ ብቻ በመስራት ሀገርን የሚጠቅም ተግባር መፈጸም በተቻለ ነበር።ግብጽና ሱዳን ይህን ያጡታል ማለት ባይቻልም የህግ መከታ ለማግኘት ግን ዋና ቁልፍ ጉዳይ ይሆናል።ያም ሆነ ይህ ግን ህወሃት ተሸክሞት የመጣው የውጭ ጠላቶቻችን ተልዕኮ አገርን የማጥፋት ስለሆነ ድርጅቱ ገና ሲመሰረት በክፋት ያደጉ ከጸረ-ሕዝብ ቤተሰብ የበቀሉ፤ከመጣው የሀገር ጠላት ጋር ሁሉ በመሰለፍ ሀገርን የጎዱ፣ሕዝብን ያስፈጁ የተሰባሰቡበት ስለሆነ ከህወሃት በጎ ነገርን መጠበቅ «ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል» ብሎ እንደማሰብ አይነት የዋህነት ነው።

አባይን ለመገደብ ህወሃት መጀመርያ ከእቅዱ በስተጀርባ ያለውን ምሥጢር ግልጽ ማድረግ፤ኢትዮጵያውያንን ማሳመንና ማሳተፍ፤በተለይ ዲያስፖራውን የተተኮሰ ጥይት ነው ብሎ ከማንበሳበስና በዘር ከመከፋፈል መጽዳት፤እንደገናም ወደ አባይ እየሄዱ የሚጨመሩ የአባይ ገባሮችን በሥራ ላይ ማዋል አለመቻል የሚያመላክተው ይህ ፀረ-ሕዝብ ሥርዓት የሚመራው በሆዳሞችና ፀረ-ሀገርና ፀረ-ሕዝብ በሆኑ በሕግና ሥርአት ሳይሆን በቡድነኝነት፤በመሣርያ ኃይልና በጉልበት ብቻ የሚያምኑ በመሆናቸው ነው።አባይን ለሁለትና ሶሥት ቀናት የሚፈጀውን ጉዞ በእግር እየተጓዝኩ በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል ያለውን የአባይን አጠቃቀም ተመልክቻለሁ።ሱዳኖች መቶ በመቶ(100%) በኢትዮጵያውያን ጉልበት የተጠቀሙበት ሲሆን እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ለሱዳኖች ጉልበታችን በርካሽ ከመሸጥ በስተቀር ከሱዳኖች ተመክሮ ወስደን ቃሪያና ቲማቲም እንኳን ማምረት አልቻልንም።ኢትዮጵያ እንደዚህ ላለው የተቀደሰ ምግባር የሚመራ መንግሥትም አግኝታ አታውቅም ክፉ አለመታደል ነው።

ሀወሃት፦ ከፍ ብየ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አስመራና አዲስ አበባ ሆነው የሚገዙት የዘመኑ የታሪክ ግርዶች ታሪክን ዘወር ብሎ ለማወቅ አንደበታቸው በሸፍጥ የታፈነ አይናቸው ብርሃን የማይወድለት ተከፍተው(አንተ የባንዳ ልጅ)እየተባሉ ያደጉ አያት ቅድመ አያቶቻቸውም ለጋብቻ እንኳን ተከልክለው ከኢትዮጵያዊ ማሕበረሰብ ተነጥለው የኖሩ በመሆናቸው የወላጆቻቸውን ጥቃት ለመበቀል ጊዜ ገዝተው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እየዘረጉ እየተቀጡ የተመለሱ ጠላቶቻችን ከምዕራባውያንና ከዐረቦች ጋር በመወገን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ፊውዳላዊ አገዛዝ ዘመን በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ዝርክርክነት በመጠቀም ሻእብያና ህወሃት ኢትዮጵያን የማጥፋት በተለይም(የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትና የአማራውን ነገድ ሕዝብ) አጀንዳቸውን በግልጽ አስቀምጠው ሌሎች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕብረ-ብሔራዊ መልክ በተደራጁ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች አስርጎ በማስገባትና ሆዳም አማራዎችን እንደ ዋለልኝ መኮንን የመሳሰሉ ጥራዝ ነጠቅ የአማራ ልጆችን በማማለል ዛሬ ከዚህ ላደረሳቸው ድል በቅተዋል።

ለአብነት ያህል ፦  ለኢዲዩ መፍረስ ከራስ መንገሻ ስዩም ጎን የተሰለፉና ራሳቸው ራስ መንገሻ ናቸው፤ለኢህአፓ መፍረስ(መበተን)የትግራይና ኤርትራ ተወላጆች ናቸው ኢያሱ ዓለማየሁን፤እነብርሃነ መስቀልን፤ተስፋየ ደበሳይን…ወዘተ ማስቀመጥ ይቻላል።አማራና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖትን ማጥፋት በኢህአፓ ፕሮግራም ውስጥ እንደነበረ ያትውልድ ላይ ክፍሉ ታደሰ ከጻፈው መጽሐፍ ማየት ይቻላል።ዋለልኝ የአማራ ገዥ መደብ እያለ አማራውን ጥፋተኛ አድርጎ ሲከስ አንድም ሊጠቅሰው የሚችል አማራ ገዥ መደብ በዚያ ወቅት አልነበረም። አጼ ዮሀንስ፤ምኒልክ፤ኃይለሥላሴ፤መንግስቱ ኃየለማርያም አማራ ናቸው ከተባለ ሌላ ተአምር ነው። አቶ በቀለ ገርባ የተባለ ኦሮሞ በቅርቡ በኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን አማራው ኦሮሞውን በድሏል ስለዚህ ይቅር እንዲልና እንዲክስ ጠይቋል ይህ ሰው ከህወሃት እስር ቤት ይዞት የመጣ በሽታ ካልኖረው በስተቀር ይህ አዲስ ትውልድ የአማራ ነገድ ሕዝብ ወጣት በምን ሂሳብ ነው የኦሮሞን ሕዝብ የሚክሰውስ ሆነ ይቅርታ የሚጠይቀው?እብደት ይሏል ይህ ነው ፖለቲካውም እንዲሁ በመሰሉ ሸውራራ አመለካከት ባላቸው ሰዎች እጅ ገብቶ ነው እየተመራና የህወሃትን እድሜ እያራዘመ የሚገኘው::

የህወሃት ወረራ በኢትዮጵያ፦የሶማሌ ወረራ፤የኤርትራ ወረራ፤የቱርክ ወረራ፤የኦሮሞ ወረራ፤የግራኝ መሀመድ ወረራ፤የዩዲት ጉዲት ወረራ፤የግብጽ ወረራ፤የመሐዲስቶች ወረራ፤የጣሊያን ወረራ፤የእንግሊዝ የመቅደላ ድርጊት ያልበገራት ኢትዮጵያ እንዴት በህወሃት ልትወረር ቻለች?የሚል ጥያቄ ሲነሳ የአሁኑ ትውልድ አገሩን የማይወድ በፍርሃት ቆፈን የተያዘ ሞራለቢስ በመሆኑ አይደለም።ህወሃትን እንደ ኢትዮጵያዊ በመቁጠርና በመጀመርያ አገባብ ላይ በኋላ እየተከሰተ የመጣውን የህወሃትን አውሬነትና ድብቅ አጀንዳ ሕዝቡ ስለማያውቅ ነበር  የተሞኘው።

1.ህወሃት ባርነትን በዘመናዊ መንገድ በማስፋፋት የውስጥ ሰላማቸውን በማጥፋት የሥራ እድልን በመንፈግና የድርጅቱ አባል ካልሆናችሁ በማለት ሰርተው እንዳይበሉና በሀገር ውስጥ እንዳይኖሩ የተሰወረ ሴራ በማሴር በተለይም ታዳጊ ወጣቶችን ከሀገር የሚያስወጡ ደላላ ድርጅቶችን በሕጋዊ መንገድ በመክፈት በከፍተኛ ቁጥር የሚገመቱ ወጣቶች አገር ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል።በስደት ጉዞ ላይ ወጣቶችን ምን ጠበቃቸው?ድግስ?አይደለም ሁላችንም ስለምናውቀው ጊዜ ይመልሰው።የሰውን ልጅ ርካሽ ጉልበት ለማስመዝበርና ስደተኛ ወገኖች ለቤተሰብ የሚልኩትን ዶላር ለመቀራመት፤ጌቶቻቸውን ምዕራባውያንንና ዐረቦችን ለማስደሰት በራሱ ዜጋ ላይ እንዲህ የጨከነ አረመኔያዊ ተግባር መፈጸም እንሰሳዊ ድርጊት ነው።

2.ህወሃት በሀገር መከላከያ ስም የተመሠረተውን ጦር ለገበያ ያቀረበ ማፍያ ድርጅት ነው። የተለያዩ መረጃዎች እንዳረጋገጡት የተባበሩት መንግሥታት ሥር ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት በፀጥታ አስከባሪነት ስም ወደ የተለያዩ አገሮች ይላካል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተገቢውን ክፍያ ይፈጽማል ክፍያው ግን በግዳጅ ላይ ለተሠማራው የመከላከያ ሠራዊት አይሰጥም የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች ወደ ኪሳቸው የሚያስገቡት ገንዘብ ነው።የሠራዊቱ አባላት በየትኛውም አገር ሄደው የሞት ጽዋው ሲገጥማቸው ቤተሰቦቻቸው እንዳያውቁ ይደረጋል።ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዳይሆን እንጅ ከታች እስከ ላይ ባለው መዋቅር ሥር የአመራሩን ቦታ የያዘው የአናሳው ቡድን የትግራይ ተወላጅ የሆነው ብቻ ነው።ግልጽ የሆነ የዘር መድሎ ቢኖርም ሠራዊቱ ለሆዱ ያደረ በመሆኑ እየተገዛና እየሞተ መቆየትን መርጧል።ብረት በእጁ ይዞ ከፍርሃት ቆፈን ያልወጣ ሠራዊት አገር መከላከሉ ቀርቶ መጀመርያ ራሱን እንኳን ለማዳን ያልቻለ ሠራዊት ጠንከር ያለ በትር ቢያርፍበት ለመከላከል የሚኖረው አቅም የደከመና በውስጥ ቅራኔ የታጀለ በመሆኑ እንደ አንድ የአገር መከላከያ ሠራዊት መቁጠር አይቻልም።የሠራዊቱ አዛዦች በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት የግል ባለሀብቶች ላቅ ያለ ንብረት ያካበቱ ሲሆን ይህ ንብረት ደግሞ በወር ከሚከፈላቸው ደመወዝ እየቆጠቡ ያስቀመጡት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ደመወዛቸውማ የኑሮ ውድነት እንዲህ ጣራ በነካበት ወቅት የረባ የፍየል ሙክት እንኳን ሊገዛ የሚችል አይደለም።ለክብረቱ ምንጩ ከላይ የጠቀስኩት የተባበሩት መንግሥታት ለሠራዊቱ የሚከፍለውን ዶላር ወደ ግል አካውንት በማስገባት ነው።አንዱንም የጄኔራልነት ማእርግ ሊያስገኝ የሚችልን መስፈርት ሳያሟሉ በየጊዜው የሚሾሙ ጄኔራሎች ችሎታቸው ወታደራዊ ብቃታቸው ሳይሆን ለስርአቱ ታማኝ መሆን ፖለቲካው ውስጥ ጣልቃ መግባት፤የአንድ ሠፈር ሰው፤በዘር ማመን ፤ ዘርፎ ማዘረፍን መቻል አልፎ ተርፎም የንግዱን ዓለም በቁጥጥር ሥር ማስገባት መሆኑን ያስመሰከሩ የውሸት ጄኔራሎች ክምር ነው ህወሃት ይዞ የሚገኘው።

3.ምርትን ወደ ውጭ ማጋዝ፦ሥራ አጥነት የድርጅት አባል በመሆንና ባለመሆን መለኪያ ሆኖ የህወሃትና የጀሌዎቹ አባል ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ሥራ ስለማያገኝ የሥራ እድገትና ዘወሮ ስለማይኖረው እጣ ፈንታው አገር ጥሎ መሰደድ ስደትን ያለመረጠው ወገን ደግሞ ሞቴን በሀገሬ በማለት ርሃብን እና የህወሃትን ደንቆሮ ካድሬ ጩኸት ተቋቁሞ በተለያዩ ቀዳዳዎች የሚያገኛትን ገቢ በመጠቀም በቀን አንድ ጊዜ በላ ሳይሆን እህልን አሽትቶ ይውላል ያድራል።ገዥዎቹ ደግሞ በምግብ ራሳችን ችለናል እያሉ ያደነቁሩታል።ይህ አዲስ ናፋቂ የሆነ የእኩያን ድርጅት ሕዝባዊ(ኢትዮጵያዊ) መንፈስ የራቀውና በአንድ ለአምስት የስለላ አውታሩ ምክንያት ከሕዝቡ የተነጠለ በመሆኑ የሕዝቡን ውሎና አዳር ሊያውቅ የሚችልበት መካኒዝም የለውም።ይኸውም የሰሞኑ ድርቅ በኢትዮጵያ መከሰትና ሰውና እንሥሣት እያለቁ አንዳችም ነገር የተከሰተ የለም በማለት በደረቅ ውሸት ሲሞግቱን ተስተውለዋል።ኢትዮጵያዊ የሆነው ባለሀብትም ሆነ መሬትን በነፃ የተቸራቸው የውጭ አገር ባለሀብቶች ምርት ያመርታሉ ያ የተመረተ ምርት ግን የት ነው የሚገባው የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መልሱን በቅርብ ለማግኘት አካባቢያችን መፈተሽና እያንዳንዱን ግሮሰሪና የምግብ መደብር ስንመለከት አገር ወለድ ምርቶች ስቶር አጣበው እናገኛቸዋለን።(በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ)እንዲሉ አምራችንና ምርትን እንዳይገናኙ አድርጎ ለሥርአቱ ቅርበት ያላቸው ያመረቱትን ምርት ኢትዮጵያዊ ወገን ገብያ ወጥቶ እንዳያገኛቸው ማድረግ እጅግ የከፋ ፀረ-ሕዝብነት ነው።መሠረቱ ከውጭ ምንዛሬ ፍለጋ ቢሆንም ምዝበራው ልክ ሊኖረው ይገባ ነበር።በንግድ ሥራ የተሠማሩ ዲያስፖራዎችም ነገሩ ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን ከሥርዓቱ ጋር ያላቸው ወዳጅነትና በቀላሉ ሀብታም መሆንም በመቻላቸው ተመለሱ ቢሏቸው አይመለሱም።የሚገርመው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ተቀምጠው ወይም ወደ ውጭ አገር መጥተው በቁጥር የማይናቁ ኢንቨስትመንቶችን እያካሄዱ የሚገኙ ሲሆን የገንዘቡ ምንጭ በዝርፊያ የተገኘ ወይስ ሰርተው የሚል ጥያቄ ሲነሳ ያለምንም ስጋት የሕዝብ ገንዘብ ዘርፎው የመጡ የህወሃት ባለሥልጣናት ወይም የባለ ሥልጣናት ቤተሰቦች ከመሆን አያልፉም።

4.የህወሃት ሥርዓት በሙስና(corruption)የተጨማለቀ በመሆኑ አንዱ ሌላውን ሊነካው አይችልም መገማገም የሚባል የለም ግምገማ ካለም ሙስናን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በሌላ ጉዳዮች ዙርያ ያጠነጠነ ይሆናል እንጅ በሙስና ጉዳይ የሙስናዋን ካርድ ያልጨመጠ የለም ልዩነቱ በትልቁ ዘራፊና በትንሹ ዘራፊ የሚዘረፈው የሀብት መጠን ነው።በአንድ ወቅት 10.000.00 ቶን ቡና የገባበት ጠፋ ተባለ አሁንም እንደጠፋ ነው፤በቅርቡ ደግሞ በስኳር ኮርፖሬሽን ስም አባይ ጸሐየ ከሰባት(7.000.000.00)ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰበትን ደብዛ አጥፍቶት ተገኘ ተባለ ማጣራት አልተደረገም ቀደም ባሉት ሁለትና ሶስት አመታት ከመለስ ጀምሮ የኢህአዲግ አባላት እያንዳንዳቸው በውጭ አገር በከፈቱት አካውንት የስቀመጡትን የዶላር መጠን የሚያሳይ ሰነድ ወጥቶ ተመልክቸ ነበር ለሰነዱ ማስተባበያ ከነዚህ ዘራፊዎች ወገን የቀረበ ነገር የለም።ይህ ብቻ አይደለም ነጋ ጠባ የሚወራው ስለ ሙስና በግልም ሆነ በቡድን በድርጅት ደረጃም ለዘረፋ የተሰለፉ መንግሥታዊ ተቋሞች አስቀምጦ በደረቁ መጮህ ማንን ለማጭበርበር እንደታሰበ የሚገባቸው አይደሉም።ኢትዮጵያ ውስጥ ነጋ ጠባ በሚዲያው ሕዝቡን የሚያደነቁሩት ኢትዮጵያ በልማት ያደገች በምግብ ራሷን የቻለች መንግሥቱ ልማታዊ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ውስጣቸው ሲፈተሽ ደግሞ ሥራአት አልበኝነት የነገሰበት፤በዝርፊያ አገር የሚጠፋበት፤ሕዝብ መብቱ ዜግነቱና ሰብአዊነቱ የተገፈፈበት፤ፍትህና ስርአት የተጓደለባት ዜጎች ስሜታቸውን ለመግለጽና ለመተንፈስ የማይችሉባት አገር ስለሀገር ሀብት ብክነትና ሙስና በስፋት የሚታይበት ትናንት ነፃ የወጡ የምእራብ አፍሪካ አገሮች ጭራ የሆነች አገር እንድትሆን የግድ ብሏል። ስለ ሙስና ጉዳይ አንስቶ የህወሃትን ጉድ መዘርዘር ጣናን በጭልፋ! ይሆናል እንጅ ብዙ ማለት ይቻላል።

ለዛሬው ይህን ካልኩ በሌላ ርእስ የተዘጋጁ ጹሑፎቼን አቀርባለሁ፡

ደህና እንሰንብት!!

posted by Gheremew Araghaw

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: