The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የዞን ዘጠኝ እስረኞች ሙሉ ለሙሉ ከተፈቱ በኋላ፤ የጋራ መልእክት አስተላለፉ!!

(ኢ.ኤም.ኤፍ) አሁን ሁሉም የዞን ዘጠኝ የሰላም አርበኞች ነጻ ወጥተዋል። በእስር ላይ የሚገኝ የነበረው የመጨረሻው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉም የዋስ መብቱ ተጠብቆ በውጭ ሆኖ እንዲከላከል ተብሏል። የሃያ ሺህ ብር ዋስትና ማስያዙ እንዳለ ሆኖ፤ ከአገር እንዳይወጣም ተወስኖበታል። ከ15 ቀናት በኋላም መከላከያውን ለልደታው 19ኛ ችሎት ያቀርባል። በዛሬው ዜና ሃተታችን የመጨረሻው ታሳሪ በፍቃዱ ኃይሉ ከእስር ቤት እንደወጣ የጻፈውን ደብዳቤ እና የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በአንድነት ያስተላለፉትን መልእክት እናስነብባችኋለን። በቅድሚያ የበፍቃዱ ጦማር እንዲህ ይላል። “የእናቴ ልጅ ነኝ!” ይላል የጦማሩ ርዕስ።

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ (ከቤቱ)

እቤቴ ከገባሁ ጀምሮ ወዳጅ ዘመዶቻችን ሁሉ ‹‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ›› እያሉኝ ነው፡፡ የ‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ› መልዕክቶቹ ግን ብዙውን ጊዜ በተጨማሪ ምክሮች ይታጀባሉ፡፡ በነገራችን ላይ፣ በተለይ እንደኔ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ላሉት ሰው መታሰር የሚከፋው የእነርሱ እንግልት ባሰበ ጊዜ ነው፡፡ እኔ ትልቅ ፈተና ገጥሞኛል ካልኩ፣ የእነርሱ፣ በተለይም በየሳምንቱ ‹‹አልቀርም›› እያለች የምትመላለሰው እናቴ ነገር ነው፡፡ እናም ‹እንኳን ተፈታህ› ባዮች ሁሉ የማይዘነጓት የእስር ቤት ሕመሜን፣ እናቴን ነው፡፡ ‹‹እባክህን፣ ለእናትህ ስትል እንዲህ ዓይነቱ ነገር ይቅርብህ›› ይሉኛል፡፡

በፍቃዱ ከተፈታ በኋላ ከእናቱ ጋር የተነሳው ፎቶ።
እናቴ፣ የተወለደችው እና እስከ ዐሥራምናምን ዕድሜዋ ድረስ የኖረችው ሰሜን ሸዋ (መንዝ አካባቢ) ነው፡፡ በአካባቢው ባሕል መሠረት (አሁንም ድረስ) ሴቶችን ያለዕድሜያቸው በቤተሰብ ፈቃድ መዳር የተለመደ ነገር ነው፡፡ እናቴም ከዚህ ዓይነቱ ወግ ማምለጥ የምትችልበት ዕድል አልነበራትም፡፡ ወላጆቿ ገና በጨቅላነቷ ዳሯት፡፡ እናቴ፣ ዕኩያዋ ያልሆነውን ባሏን አልወደደችውም ነበር፡፡ በአካባቢው ባሕልና ወግ መሠረት አለመውደድ ደግሞ አይፈቀድላትም ነበር፡፡ ስለዚህ የወላጆቿን ፈቃድ ሽራ የራሷን ዕጣ ፈንታ በራሷ ለመወሰን ወሰነች፡፡ ይህ ውሳኔዋ ወላጆቿን የሚያስከፋ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሹኑ ተቀባይነት የማያገኝ ውሳኔ እንደሆነ አልጠፋትም፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈሪ ዕቅድ አውጥታ ተገበረችው፡፡ የልጅነት ስሟ ገበያነሽ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ያደረገችው ስሟን ወደ ዘነበች መቀየር ነው (በነገራችን ላይ በእኔና በአባቴ ስም መሐል የምጽፋትን ‹ዘ› የወሰድኩት ከሷ ስም ነው)፡፡

ከዚያም አገሯን ጥላ ኮበለለች፡፡ የኮበለለችው ደግሞ ምንም፣ ማንንም ወደማታውቅባት፣ ማንም ወደማያውቃት አዲስ አበባ ነው፡፡ ዝርዝሩ የማያልቅ ፈተና ያለበት ውጣ ውረድ ነው፡፡ የሆነ፣ ሆኖ ነፍሷን አትርፋ ራሷን አዲስ አበባ ላይ ማደላደል ቻለች፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ነበር ከአባቴ ጋር የተገናኙት፣ የተዋደዱት፣ የተጋቡት እና ልጆች ያፈሩት፡፡ ወላጆቿ በወቅቱ አዝነውባት ይሆናል፤ ነገር ግን ተጨንቀው እሷን ፍለጋ ብዙ ሲንከራተቱ እና ሲንገላቱ እንደነበርም በታሪክ ስትናገር አውቃለሁ፡፡ ሲያገኟትም ከአባቴ ትዳር ይዛ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ነበር፡፡ ከመደሰት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ለእናቴም የእራሷን ሕይወት ለመምራት፣ እነርሱን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሚያስከፋ እና የሚያስጨንቅ ውሳኔ መወሰን ነበረባት፤ መጨረሻውም አስደሳች ሆኗል፡፡ መጨረሻው ምንም ሆነ ምን እናቴ የማትፈልገውን ሕይወት ‹‹እምቢ አልኖረውም›› ብላ መጀመሯ ተገቢ ነበር፡፡

እኔም የወላጆቼ ልጅ ነኝ፤ ታሪካቸውን በተለያየ ቀለም በተደጋጋሚ እየሰማሁ ነው ያደግኩት፡፡ የተሠራሁትም ከነርሱ ታሪክ እና ከሌሎችም ብዙ የሕይወት ልምዶች ነው፡፡ የናቴን እምቢተኝነት፣ የማይፈልጉትን ላለመሆን አደጋ መጋፈጥ፣ ይመጥነኛል የሚሉትን ሕይወት እስከሚገኝበት አጥናፍ ድረስ መፈለግ ተፈልፍዬ የተቀረፅኩበት ‹ሳይኮአናሊቲካዊ› ሥረ-መሠረቴ ነው፡፡ እናቴ፣ ወላጆቿን ታከብራለች፣ ትወዳለች፤ ሕይወቷን ግን ስለነርሱ አልኖረችም፡፡ እኔም በሕይወቴ የምወስዳቸውን እርምጃዎች የምረዳቸው በዚሁ ቋንቋ ነው፡፡ እናቴን እወዳታለሁ፤ ነገር ግን ‹የሱን ሕይወት ትቶ የኔን ድርሻ ይኑርልኝ› ትለኛለች ብዬ አልገምትም፡፡ ማረሚያ ቤት እያመላለስኩ ባስቸገርኳት ግዜም ይሁን ሰዎች በወቀሱኝ ጊዜ ለራሴ የምሰጠው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እኔ የናቴ ልጅ ነኝ፤ እራሴን የምሆነውም ከርሷ በወረስኩት ባሕሪዬ ነው፡፡

(ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት እናቴን አስፈቅጄ ነው፡፡)
————
ዞን ዘጠኞች ደግሞ በጋራ አመስግነዋል፤ ከምስጋናው በፊት ግን ጥቂት ትንታኔ አቅርበዋል። ያንብቡት።

በድንገት ከያለንበት ተይዘን እንደታሰርነው አፈታታችንም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውብን እያለ ግማሾቻችን “ክስ ተቋርጦላችኋል” ተብለን ተፈታን፣ ግማሾቻችን ደግሞ “ነፃ ናችሁ” (ከሳሽ በነፃነታችን ላይ ይግባኝ መጠየቁ እንዳለ ሁኖ) ተብለን ይሄው ወጥተናል፡፡ ቀሪ ክስ ይዘን በዋስ ወጥተን እየተከራከርንም ያለን አለን፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የሁላችንም ዕምነት ግን አንድም ቀን ሊያሳስረን የሚገባ ወንጀል አለመፈፃችን ማመናችን ነው፡፡ መፈታታችን ጥሩ ሁኖ፤ መታሰር በፍፁም የማይገባን ነበርን፡፡ መፃፋችን እና ሕግ እንዲከበር መጠየቃችን ሀገሪቱ አገራችን እንድትሻሻል እና ሁላችንም ዜጎች የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸው ከመሻት ባለፈ ሌላ ነገር አልነበረውም/የለውም፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋችን ተገርፈናል፣ ተዘልፈን-ተሰድበናል፣ ታስረናል ተሰደናልም፡፡ ይህ በፍጹም አይገባንም ነበር፡፡

የዞን ዘጠኝ ጋዜጠኞች እና ጦማርያን - ከ'እስር ከተፈቱ በኋላ ለመታሰቢያ የተነሱት ፎቶግራፍ።
የእኛ መታሰር ፖለቲካዊ ንቃት የፈጠረላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደስ ይለናል፡፡ በእኛ መታሰር ምክንያት ለመጠየቅና ለመፃፍ በጣም እንደሚፈሩ የሚነግሩን ሰዎች ስናገኝ ደግሞ እናዝናለን፡፡ የመታሰራችን ጉራማይሌ ስሜት እንደዚህ ነው፡፡ ሳይገባን በመታሰራችን የነቁ መኖራቸውን በማወቃችን የምነደሰተውን ያክል፤ ሳይገባን በመታሰራችን የተሰበሩና ከተዋስኦ መድረኩ የራቁ እንዳሉ ስናውቅ እጅግ እናዝናለን፡፡

መታሰር በደል ነው፡፡ ብዙ ነገር ያጎድላል፡፡ መታሰር መልካም ነው፡፡ ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እኛ በመታሰራችን ሀገራችን የበለጠ እንድናውቃት ሁነናል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት አሁንም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተናል፡፡ ሕግን መከታ አድርገው የኖሩ “ስም የለሽ” ዜጎች ሕጉ ሲከዳቸውና እነሱ ላይ “በላ” ሲያመጣባቸው ታዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ ፍትህ የሌለባት ሀገር ለዜጎቿ የማትመች አገር እንደሆነች አይተናል፡፡

በእስራችን ወቅት የተለያዩ በደሎች በተቋም ደረጃ ደርሰውብናል፡፡ ግን አገር ነውና ከይቅርታ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለበደላችሁን አካላት እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁንም፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ባለማድረጋችንና ሕግን መሰረት አድርገን በመኖራችን ስላስከፋናችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን፡፡

በዚህ ሁሉ መሃል ግን እናንተ አላችሁ፡፡ ጓደኞቻችንም ናችሁ፤ ዘመቻ አድራጊዎችም ናችሁ፤ ቤተሰቦቻችንም ናችሁ፤ ጠያቂዎቻችንም ናችሁ፤ ጠበቆቻችንም ናችሁ፣ የመንፈስ አጋሮቻችንም ናችሁ ርቀት ሳይገድባች የጮሃችሁልን አለም አቀፍ የመብት ጠያቂዎችም ናችሁ … በመታሰራችን የተረዳነው አንዱ ትልቅ ነገር የናንተን መልካምነት፣ የናንተን አጋርነት እና የናንተን የማይሰለች ድካምና ፍቅር ነው፡፡ እናንተ ባትኖሩ “አጭሩ” የእስር ጊዜያችን ይረዝምብን ነበር፤ “ቀላሏ” እስር ትከብድብን ነበር፡፡ ምስጋና ለናንተ፤ እስራችን “አጭር” – ፈተናችን “ቀላል” እንዲሆን አድርጋችሁልናልና፡፡

እናንተ ወዳጆቻችን ለሁሉም ነገር – እልፍ ምስጋና

እናመሰግናለን!
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

EMF

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: