The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ግልጽ ማሳሰቢያ ለሕዝባዊ ግንባርና ለመሪው አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ!

Issayas

  የሕዝባዊ ግንባር መሪ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ አምና ከኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ነጋሪነ ወግና ምርጫየ ኩነት) ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ግልጽ ካደረጉልን ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው እርስዎም ሆኑ ሕዝባዊ ግንባር ሲጀመር ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥልንና ብሔረሰቦቿን የሚከፋፍል ቋንቋንና የብሔረሰብ አሰፋፈርን መሠረት ያደረገን የወያኔን የራስ ገዝ (የፌዴራል) አሥተዳደር ሥርዓት አጥብቃቹህ ስትቃወሙትና ስታወግዙት የነበረ ጉዳይ መሆኑን መግለጽዎ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ጦርነት በጠላትነት ስሜትና በመጠፋፋት ፍላጎት የሚደረግ አስከፊ ገጽታ በመሆኑ በሠላሳው ዓመት የጦርነት ዘመን ለተፈጠሩ ስሕተቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከ መካስ ድረስ ፍላጎቱና ዝግጁነቱ እንዳለዎትም መግለጽዎ ይታወሳል፡፡

አቶ ኢሳይያስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይንን ቃልዎን ከልቡ ማመን ይፈልጋል፡፡ ከልብዎ ውስጥ ያለው እውነታ ይሄ ከሆነ አሁን በቅርቡ መቀመጫቸውን በሀገርዎ ያደረጉና ኅብረት የፈጠሩ እነ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ጋነን፣ ቤነን፣ ሲነግ የተባሉ ከኢትዮጵያ መገንጠልን ዓላማቸው ያደረጉ የትጥቅ ትግል ቡድኖች እርስዎና ሕዝባዊ ግንባር በጥብቅ ለምትቃወሙትና ለማትወዱት ለማትፈልጉት ማለትም ዓላማና አቅዳቸው ለኢትዮጵያ አንድነት አደጋ በመሆናቸውና የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሔረሰብ ከፋፍሎ መለያየትን ለሚፈጥር የአሥተዳደር ሥርዓት የሚታገሉ በመሆናቸው እነኝህ አካላት እንዲህ ዓይነት አቋምና ዓላማ ይዘው በሀገርዎ ድጋፍ እየተደረገላቸው መቀመጫ ማግኘታቸው እርስዎና ሕዝባዊ ግንባር አንድነቷ የተጠበቀ በጎሳና በብሔረሰብ ያልተከፋፈለች አንድ የሆነ ሕዝብ ያላት የተረጋጋች ኢትዮጵያ እንድትኖር አቋምና ዓላማ ይዘው እያደረጉት ያለውን ታላቅ ድጋፍና ትብብር እንዲሁም እየከፈሉት ያለውን ዋጋና መሥዋዕትነት ከንቱ የሚያስቀርና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድም እጅግ በጥርጣሬ እንዲታዩ ከማድረጉም በላይ እየተካሔደ ያለውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ትግልን የሚያዳክም፣ የሕዝብን አመኔታ አግኝቶ በተፈለገው ፍጥነት ውጤት ማምጣት እንዳይችል ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ ያለ ዋነኛ ችግር ስለሆነ እነዚህ ተገንጣይ ኃይሎች ይሄንን ዕኩይና ለማንም የማይጠቅም የደነቆረ አስተሳሰብ ጥለው የአንድነቱን ኃይል የመቀላቀል ፍላጎት ጨርሶ የሌላቸው ከሆኑ እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ከሀገርዎ ፈጥነው በማባረር አንድነቷ የተጠበቀች፣ ጎሳዎቿና ብሔረሰቦቿ ሳይከፋፈሉ አንድነታቸው፣ እኩልነታቸው፣ ነጻነታቸው ተከብሮ ለሚኖሩባት ሰላማዊትና የተረጋጋች ጠንካራ ኢትዮጵያ መፈጠር ላለዎት አቋምና ዓላማ ታማኝነትዎን በተግባር እንዲያረጋግጡ እንጠይቃለን፡፡

ይሄንን ወሳኝና የግድ ሊወሰድ የሚገባውን አስፈላጊና ጠቃሚ እርምጃ ከወሰዱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ያለውን የጥርጣሬ መንፈስ እንዲወገድና መተማመን እንዲፈጠር ማድረግ ያስችላል፡፡ ተከትሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለው ፈጥኖ ለትግሉ በሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍና ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወያኔን ወደመቃብሩ ለማውረድና ለመቅበር የሚያስችለን ይሆናል፡፡

እርምጃውን ባይወስዱና መውሰድም የማይፈልጉ ቢሆኑ ግን ነገሩ ሁሉ የልጆች ጨዋታ ከመሆኑን በላይ የተናገሩት ነገር ሁሉ ሐሰትና አስመሳይነት የተሞላበት፣ ሸፍጥ ያዘለ የቃላት ጨዋታ እንደነበር የሚያረጋግጥ መሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ግንዛቤ ተወስዶ በስንት ፈተና ውስጥ አልፎ መልክና መሠረት የያዘው ትግል ከንቱ ሆኖ የሚቀርና ቀጠናው ማናችንም ተጠቃሚ ወደማንሆንበት ወደባሰ የችግሮች ማጥ ውስጥ የሚሰጥም መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

Issayas

እርስዎ ይሄንን እርምጃ ባልወሰዱበትና በድንቁርናቸው ትንሽም ቢሆን ሐፍረት በማይሰማቸው ኢትዮጵያን ለመበታተን ጠንቀኛ ፍላጎት ያላቸውን የጥፋት ኃይሎች እየደገፉ በሀገርዎ እያስተናገዱ ባሉበት ሁኔታ “ለኢትዮጵያ አስባለሁ፣ ኢትዮጵያን መካስ እፈልጋለሁ” የሚለው አባባልዎ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል? ይሄንን አባባልዎንስ አምኖ ማን ሊታለልልኝ ይችላል ብለው ያስባሉ?

እርግጥ ነው የእነዚህ የጥፋት ኃይሎች እስከ አሁን ባለው ጊዜ በሀገርዎ እንዲቆዩ ማድረግዎ ሁሉም የትግል ኃይሎች መቀራረብን መግባባትን ፈጥረው ወደ አንድ የትግል ኃይል እንዲመጡ ለማድረግ አስፈላጊ ይሆን ይሆናል፡፡ የጥፋት ኃይሎቹ ግን ከድንጋይ በባሰ መልኩ ሊያመጡት የሚችሉት ለውጥ እጅግ አዝጋሚ ከመሆኑ የተነሣና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁለትና ሦስት ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ያልተወለደ ዜጋ አለመኖሩንና ከጎሳም ከብሔረሰብም ያልተቀላቀለ ከአንድ ጎሳ ወይም ከአንድ ብሔረሰብ ብቻ የሆነ አንድ ዜጋ እንኳን ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ በደም የተዋሐደውን ሕዝብ በጎሳና በብሔረሰብ በመለያየት ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል እግጅ ስሕተትና አግባብ አለመሆን በመረዳት፣ ሌሎችንም ነባራዊ ሁኔታዎችን በመገንዘብ፣ የ21ኛውን መቶ ክፍለ ዘመንና መጻኤውን ዓለማቀፋዊ ሁኔታ አጢነው መገንዘብ የሚገባቸውን ቁምነገር መገንዘብ ፈጽሞ የማይችሉ ዘገምተኞች ሆነው እርስዎ በሀገርዎ ሲያስቀምጧቸው ሊያመጡት ይችላሉ ብለው የገመቱትን ለውጥና አንድነት ማምጣት ሳይችሉ ቀርተው ሰሞኑን ተገንጣይ የጥፋት ኃይሎች ኅብረት ፈጥረው ያንን የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካት ከግብ ለማድረስ እንደሚታገሉ አስታውቀዋል አውጀዋል፡፡

በእነዚህ ዘገምተኞች እንቅፋትነት የተነሣ የሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) በዘር ልዩነት ላይ ሳይሆን እንደምዕራባዊያኑ በአስተሳሰብ ልዩነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ሊያድግ አልቻለም፡፡ ፖለቲካቸውን (እምነተ አሥተዳደራቸውን) ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ጎሳን ከጎሳ በመለያየት በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሲያደርጉ “ፊውዳል” እያሉ ከሚኮንኑት ሥርዓት የተለየ እንዳልሆነና የፊውዳላዊ ሥርዓት ሌላኛው ገጽታ እንደሆነ ጭንቅላታቸው በጭራሽ መገንዘብ የሚችል አይደለም፡፡ እነዚህ ዘገምተኞች አንድን ዘር ከሌላኛው ዘር እንኳን ተዋሕዶ ተዋልዶ ተነካክቶ እንኳን እንደማያውቅ እያራራቁ ማየታቸውን ለተመለከተ የሰው ልጆች ምንጫቸው አንድ አባትና እናት መሆናቸውን ፈጽሞ የሚያውቁ አይመስለውም፡፡

እናም አቶ ኢሳይያስ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አቋም ዓላማቸውን በኅብረት መግለጫቸው ግልጽ እንዳደረጉት እንዲህ በመሆናቸው የእርስዎን ድካም ምኞትና ፍላጎትን ከንቱ አደረጉት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ አካላት የወደፊት ዓላማ አቅዳቸው እንዲህ መሆኑን ካስታወቁ በኋላ አሁንም በሀገርዎ እንዲኖሩ ቢፈቅዱና ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግዎን ቢቀጥሉ ግን ሀገራችንንና ሕዝባችንን በተመለከተ ያለዎት ዓላማና አቋም እንደገለጡልን እንዳልሆነና ከገለጹልን ተቃራኒ መሆኑን የሚያረጋግጥ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ አመኔታና ድጋፍ ፈጽሞ የሚያገኙ አይሆንም፡፡

ይህ እንዲሆን ይፈልጋሉ የሚል ግምት አይኖረኝም፡፡ በመሆኑም ሳይዘገዩ አፋጣኝ እርምጃ ወስደው የተናገሩት ቃል ሐሰት ሳይሆን እውነት መሆኑን በማረጋገጥ ወያኔንና ቱልቱላዎቹን ያሳፍሩልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ ይሄንን ካደረጉ ቀሪውን ነገር ለእኛ ይተውት፡፡

እንግዲህ ሁሉንም ከዚህ ቀን ጀምሮ በሚወስዷቸው ወይም በማይወስዷቸው እርምጃዎች የምንረዳው ይሆናል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: