The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የተራበች ኢትዮጵያ ከአንተነህ መርዕድ

በሞት አፋፍ ላይ ቀናቸውን በፀጋ የሚጠባበቁ የሰማንያ አምስት ዓመት ካናዳዊ አዛውንት የስቃይ ማስታገሻ መድሃኒታቸውን እየሰጠኋቸው እያለ “ከየት አገር ነህ?” ሲሉ ጠየቁኝ በደከመ አንደበታቸው። የተለመደ የነጮች ጥያቄ በመሆኑ እንደወትሮዬ “ከአፍሪካ ነኝ” አልኳቸው። ብዙዎቹ እያንዳንዱ አገርን ለይተው የማያውቁ ስለሆነ ለወትሮው በቂ መልስ ነበር። “ከአፍሪካ ውስጥ ከየትኛው አገር ነህ?” ሲሉኝ በዋዛ እንደማንላቀቅ ተገነዘብሁ። ብዙዎቹ አዛውንቶች አገሬን ስጠራላቸው “የአበበ ቢቂላ” ወይንም “የሃይለስላሴ አገር” በማለት በአድናቆት ታሪካችንን አጥርተው የሚያውቁ ስለሚያጋጥሙኝ ስለራሱ ታሪክ ደንታ በሌለው ትውልድ የሚሰማኝን ሃዘን ያቃልሉልኛልና “ኢትዮጵያዊ ነኝ” በማለት ፈካ ብዬ ነገርኳቸው። ራሱን ኢትዮጵያዊ ብሎ መጥራት በሚያሳፍረው፣ የማንነት ቀውስ ውስጥ የወደቀ በበረከተበት ወቅት ማንነታችሁን ተቀብሎ በሚያምን ሰው ፊት ማንነታችሁን ስትገልፁ ምን ያህል እንደሚያኮራችሁ ስሜቱን የምትጋሩኝ ጥቂት አትሆኑም።

የኢትዮጵያን ስም ስጠራ የሞት ጥላ ያንጃበበበት የሚመስለው ፊታቸው ፈካ። በፀጥታ በሃሳብ ጭልጥ ብለው ከሄዱበት መለስ አሉና “ለመሆኑ ርሃቡስ ቀረ አይደል? የሰላሙስ ጉዳይ እንዴት ነው?” ሲሉ ለራሴም መልስ አጥቼለት የኖርሁትን አስፈሪ ጥያቄ ባላሰብሁበት ቦታና ጊዜ ሲወረውሩብኝ ባለሁበት ደርቄ ቀረሁ። የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ኢትዮጵያ በርሃብ ምሳሌነት ተደጋግሞ ክፍሏ ውስጥ መጠቀሱ እንዳሳፈራት የስምንት ዓመት የጓደኛዬ ልጅ የነገረችኝ ለት እንደደነግጥሁት ነው አሁንም የተሰማኝ። ሬድዋን፣ በረከት፣ ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ደብረፅዮን፣ አባይ ፀሃዬ ሆነ መንግስቱ ኃይለማርያም እንድዛች ልጅ የሃገራቸው ውርደት አጥንታቸው ድረስ እንደማይሰማቸው ተግባራቸው ምስክር ነው።

እድሜ ባጎደጎደውና ውስጥን ጠልቆ በሚመለከተው ዐይናቸው እየፈተሹኝ መልሴን በጉጉት እንደሚጠብቁ አየሁ። ምን ብዬና የቱን ለመልስላቸው?
የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን በምግብ ራሳችንን የመቻላችንን ዲስኩር ውይንስ እውነተኛውንና ከአስር ሚሊዮን ያላነሰ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ርሃብተኛ የሚሸነቆጥበትንና የሚሞትበትን ዜና፤
የአዳዲስ ገዥዎቻችንን ጥጋብ፣ የህወሃትን፣ የብአዴንን፣ የኦህዴድን፣ የደህዴድን የምስረታ በዓል ድግስ “የጄኔራሎቻችንን” ፎቆች መበርከት፣ የሳዑዲዎችን ኢትዮጵያ በበቀለ ሩዝና ስጋ መጥገባቸውን ውይንስ አፋር፣ ዋግ ህምራ፣ ኦጋዴን፣ ትግራይ፣ ወሎና ድቡብ ላይ የእናታቸውን የደረቀ ጡት እየመጠመጡ ላይመለሱ ስላሸለቡ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ የነበሩ ህፃናት ልንገራቸው?
በአገራቸው ለመኖር ተስፋ አጥትው ተስፋ ፍለጋ ሲንከራተቱ የባህር አሳ ሲሳይ፣ ለአይሲስ የጭካኔ እርድ ሰለባ ስለሆኑ፣ ለኩላሊታቸው ሲባል እየታረዱ በረሃ ላይ ያለቀባሪ ስለቀሩ ከርታታ ኢትዮጵያውያን ወይንስ ርሃቡም ፣ ግድያውም፣ እስሩም፣ ስደቱም እንዲቀጥል አውቀንም ሆነ ሳናውቅ እርስ በርሳችን ስንናቆር፤ የትግል ስልትና የአመለካከት ልዩነታችንን በውይይት ከመፍታትና ወደ እውነተኛው ችግራችን ከማተኮር ይልቅ ከትናንቱ “ግደለው ፍለጠው” አሳፋሪ ታሪካችን ባልተናነሰ ሁኔታ እንካ ስላንትያ ስለተጠመድነው ስለከንቱዎቹ ስለኛ ልንገራቸው?

በሞት አፋፍ ላይ ላሉት ለኒህ ቅን አዛውንት እውነተኛውንና መሪሩን ሃቅ በዚች ወሳኝ ጊዜያቸው ብነግራቸው ከአፋቸው የሞትን መድሃኒት የነጠቅሁአቸውን ያህል ቢሰማቸውም እውነቱን ለመናገር ወሰንሁ።
“አሁንም ርሃቡ አለ። ህዝቡም የአካል ሆነ የመንፈስ ሰላም እንደራቀው ነው” አልሁና ተገላገልሁ። ሌላ ጥያቄም መሰንዘር፣ ሌላ መልስ መስማትም አልፈለጉምና ዐይናቸውን ከኔ ነቅለው መሬት ላይ ተከሉ፤ አንገታቸውን ደፍተው ራሳቸውን አቀረቀሩ። ፊታቸው ክስም አለ። መርዶ ነጋሪነቴ ቢያስጠላኝም በሆዴ ይጄ የምንጓለለውን እውነት ከልቦናው መስማት የሚፈልግ የአገሬ ልጅ ቁጥር በሳሳበት ሰዓት ባዕድ ከምንላቸው ውስጥ ሰሚ በማግኘቴ ግርምት ይሁን ደስታ የማይታወቅ ስሜት ተሰማኝ።

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ይህንን ዓለም ለመጨረሻ ጊዜ ቢሰናበቱም ህሊናቸው እንደቆሰለ እንዲሄዱ ማድረጌ እረፍት ነስቶኝ ነበርና ስለአዛውንቱ ቤተሰቦቻቸውን በመጎትጎት የተረዳሁት እውነት ደግሞ ጭርሶ አስደነገጠኝ። በ1977 ዓ ም በኢትዮጵያ የተከሰተውን ርሃብ በዜና ማሰራጫዎች ሲመለከቱ ስሜታቸው በሃዘን ስለተነካ ቤታቸውን ሸጠው በጉልምስና ደክመው ያገኙትን ንብረት ለኢትዮጵያውያን እርዳታ አውለው እድሜአቸውን በአፓርትመንት ኪራይ ያሳለፉ ትልቅ ሰበዊ ፍጡር ናቸው።

አዎ በርካታ ካናዳውያን፣ አሜሪካውያን እንደ እኒህ አዛውንት ብዙ ብዙ አድርገዋል። በትናንቱ ርሃብም ዘረፋውን የተለማመዱ የህወሃት ባለስልጣናት አሁንም ከራብተኛው እየነጠቁ አሜሪካና ካናዳ ውስጥ ህንፃ እየገነቡ፣ የንግድ ተቅዋማት እየመሰረቱ መሆናቸውን ለእኒህ ንፁህ ሰው ብነግራቸው ሃዝናቸው የከፋ እንደሚሆን አውቃለሁ። ቢሆንም በህይወታቸው ያደረጉት ትልቅ ልግስና እንዳለሙት የብዙዎቻችንን ህይወት እንደታደገና ርሃቡም ዳግም ላይመጣ እንደሄደ ሊሰሙ ሲጓጉ የመጨረሻዎቹን የህይወት ሰዓቶቻቸውን በመሪር ሃዘን ደመደምሁባቸው። ደግነቱ የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያና የአውስትራልያን መራብ ከሃይለማርያም ደሳለኝ አልሰሙም፤ ከሰሜን አሜሪካና ከአውሮፓ የሄዱ ህሊና ቢሶች የራብተኞችን መሬት ለመንጠቅ አዳራሽ ተሰብስበው ለአምባገነኖች ሲያጨበጭቡ አላዩም። ምን ይህ ብቻ! ከወያኔ በተቃራኒው ቆመናል የምንለው ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያንም የርሃቡን ፍፃሜ ለማቅረብ ዘላቂ ዴሞክራሲን ለማስፈን ከመረባረብ የበለጠ ርሃቡን ለፖለቲካ ፍጆታና ለጠረጴዛ ዙርያ ጨዋታ ማዳመቂያነት ልናውለው የምናደርገውን ድካም ቢያዩ ምንኛ ባዘኑ።
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሰማንያኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ሊከበር ሲደገስ ብዙ መቶ ሺዎች ወሎና ትግራይ በርሃብ በሞት ይረግፉ ነበር። እንዳይታወቅና እንዳይነገርም ትግል ተደርጓል።
አስረኛው የአብዮት በአል ሊከበር ውስኪና ለልዩ ልዩ የድግስ ፍጆታ የሚውል እቃ በሚሊዮን ዶላር ተገዝቶ የሃይለስላሴ አገዛዝና ድርጊት ያወገዙ ደርጎችና ካድሬዎቻቸው በጥጋብ ሲምንርሸነሹ ወሎ፣ ትግራይ፣ ጎንደር፤ ጎጃም፣ ኦጋዴንና ደቡብ ርሃብ ገብቶ በየሰዓቱ ሺዎችን ይቀጥፍ ነበር። እንዳይታወቅ፣ እንዳይነገር የተደረገው ጥረት ሁሉ አልሰራም። ተጋለጡበት።
ልክ በዚያው ወቅት በነቦብ ጊልዶፍ ሆነ በምእራቡ አለም የተለገሰውን እርዳታ ወያኔ ዘጠና ከመቶውን ለራሱ እንዳዋለው ከገብረመድህን አርአያ የበለጣ ማስረዳት ተገቢ አይሆንም።
አሁን ደግሞ የሃይለማርያምና የሬድዋን ግሳት፣ የአለቆቻቸው የህወሃት መኳንንት ሽርጉድ ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጋውን ኢትዮጵያዊ ርሃብትኛ ሊድብቁት አላስቻላቸውም። “የፍየል ጅራት ገበናዋን እንኳ አይከድንም” እንደሚባለው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ከማዳፈን ይልቅ ያጋልጣል።

ሌላም ጉልህ ድርቅ አለኮ በኢትዮጵያ! የህዝቡ መከራው አላበቃ ብሎ የዓለም መዘባበቻ፣ የራሱ አምባገነኖች መጫወቻ ሲሆን ንፁህ ህሊና ያለውና ማስተዋልን የተላበሰ ዜጋ ቁጥር ተመናምኖ አገሪቷ እጆቿን ዘርግታ ብትጮህም አምላኳ መልሱ ዘገዬ “ኢትዮጵያ ታበፅህ እደዊሃ” እየተባለ አድገናልና። የልጆቿም ልብ ደንጋይ ሆነ። ወንድም ወንድሙን ለመግደል በሞቱም ለማትረፍ ልክ እንደ ትናንቱ ሲወራጭ፣ የዘረኝነት ጦር ሲስብቅ እንጂ ፊቱ ላይ ያለውን ግዙፍ ችግር ሊያስወግድ በህብረት ሲንቀሳቀስ አይታይም።
ከአርባዎቹ አመታት በፊት ሆነ አሁን እንደ አሸን የተፈለፈሉ “ተቃዋሚዎች” ንግድ ፈቃዱን ብቻ ግድግዳ ላይ ሰቅሎ በኪሳራ ተቀምጦ ቀን እንደሚጠብቅ ነጋዴ የመግለጫ ግብር ለመክፈል ብቻ ብቅ ከማለት የዘለለ፣ ከነሱ ተሽሎ ይንቀሳቀስ ይሆናል ያሉትን ለበጥለፍ በግልፅ ሆነ በተዘዋዋሪ ከመንቀሳቀስ የተሻለ አጀንዳና ሃሳ ጠፋባቸው እንዴ?

አገሪቱ ወደ እስርቤትነት ተቀይራ መቶ ሺዎች ንፁሃን በግፍ ሲማቅቁባት፣ ሚሊዮኖች ሲሰደዱ፣ አስር ሚሊዮኖች በርሃብ ሲሰቃዩ፣ ኢትዮጵያ ወና ስትቀር ያላወራጫቸው፣ ያላንገበገባቸው ህሊና መቼ ነው የሚነቃው?
በየጊዜው የስልጣን ማማ ላይ ያሉ አምባገነኖችን ብቻ ተጠያቂ ያደረገ፤ የራሳችንን ድክመት ማየት የተሳነው ባህሪያችን የት ያደርሰናል? መለስ ዜናዊ ህወሃትን ከመራበት ዘመን በላይ የየድርጅቶች መሪ ሆነው የጓደኞቻቸው አለቃ ብቻ እንደሆኑ እንኳ የማያውቁ፣ ዴሞክራሲያዊ አሰራር በውስጣቸው የሌለው “ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች” ለስንት ጊዜ በትግል ስም ሲነግዱ ይኖራሉ። ወያኔ እንኳ ቢያንስ ለአፉ መተካካት የሚል ማማለያ የሚታኘክ ፅንሰ ሃሳብ አቀቦ የሚሞኝ ለማሞኘት በመሞከሩ የተሻለ መስሎ ሊታይ ሞክሯል። ለነገዋ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ተስፋ ለመሆን መጀመርያ እነሱ ዴሞክራሲውን ይለማመዱትና ይታዩ። ርሃቡ የእህል ብቻ አይደለም ጎበዝ። በሁሉም ዘርፍ ድርቅ መትቶናል። ሁላችንም የውድቀታችን ተዋናዮች ነን። የዓለም ህዝብም ታዳሚያችን።
ድራማው እዚህ ላይ ያብቃ! ተዋናዮቹ መተወኑ ባይሰለቸንም ታዳሚው ዓለም ስልችቶናል!
ኢትዮጵያ በልጆችሽ እንዳፈርሽ አትቅሪ!
እንባሽን የሚያብሱልሽ ይብዙ!
አሜን!!
Amerid2000@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: