The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የተደበቀው ረሃብ ሲገለጥ – 15 ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ አደጋ ላይ ነው!

(EMF) ዘንድሮ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ፤ መንግስት ከጅምሩ ለመሸፋፈን ሞክሮ እንደነበር ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትር ደሳለኝ ኃይለማርያም ስለድርቁ ሲጠየቁ፤ “ድርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም የተከሰተው። አውስትራልያም ድርቅ ገብቷል።” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት። የኮምዩኒኬሽን ሚንስትር የነበሩት ሬድዋን ሁሴንን በአፋር አካባቢ የከብቶችን መሞት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ከብብቶቹ የሞቱት አርሶ አደሩ በወቅቱ ውሃ ስላላጠጣቸው ነው።” የሚል ምላሽ ሰጥተው ክፉኛ ሲወቀሱ ከርመው፤ በዚያው ከስልጣናቸው ወርደው የወጣቶች ስፖርት ሃላፊ ተደርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ – ድርቁ የአፋር አካባቢን አልፎ በተለይ በአማራና በትግራይ በሰፊው እየተንሰራፋ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ጭምር እየገለጹ ነው። በፌደራል መንግስት እና በውጭ ተራድኦ አማካኝነትት አስቸኳይ እርዳታ የማይደረግ ከሆነ፤ የተረጂው ቁጥር 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንንደሚችል ይፋ ሆኗል። በድርቅ የተመታውም ሆነ፤ ለረሃብ የተጋለጠው ህዝብ ብዛት እስካሁን በኢትዮጵያ ከተከሰቱት የ19965 እና 1977 የከፋ እንደሆነ ይፋ እየሆኑ ያሉት የመረጃ ምንጮች ይገልጻሉ። ኢህአዴግ “አገሪቱን ልማት በልማት አድርጌያለሁ። ባለሁለት ዲጂት እድገት አስመዝግቤያለሁ። በዚህም ምክንያት ህዝቡ መቶ በመቶ መርጦኛል።” በሚልበት ወቅት ይህ ረሃብ በመከሰቱ ያሳፈረው በሚመስል ሁኔታ፤ እየደረሰ ያለውን ረሃብ ለመሸፋፈን መሞከሩን ቀጥሎበታል። በትግራይ የተከሰተውን ረሃብ በመታዘብ ሪፖርተር ጋዜጣ ካወጣው ዝርዝር ሪፖርት ውስጥ ከዚህ በታች ያለውን ቀንጨብ አድርገን ልናስነብባችሁ ወደድን።

The new famine in Ethiopia

የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ለማቆየት ሲሉ እስከ 7,000 ብር እና ከዚያ በላይ ዋጋ የሚያወጣ በሬያቸውን በ1,500 ብር ለመሸጥ መገደዳቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ከብት (በሬና ላም) ዋጋ አጥቷል፡፡ ከአንድ ከብት ይልቅ ፍየል የተሻለ ዋጋ አለው፤›› ሲሉም በገበያ በኩል ያለውን ችግር አመልክተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከመቐለ ከተማ 43 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የአጉላዕ ከተማ ጀምሮ በሰሜን ምሥራቁ ከፍል በተደረገው ቅኝት፣ በአብዛኛው አካባቢ ድርቁ ያስከተለው ተፅዕኖ ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው መገንዘብ ተችሏል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ የውኃ እጥረት በመከሰቱ፣ አርሶ አደሮች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አፅቢ ወንበራ ሁሉ በሌሎችም ወረዳዎች በተለይም በክልተ አውላሎ፣ ደብረ ብርሃን (ከለሻ እምኒ)፣ አጎሮ፣ ውቅሮ፣ ፈንታ አውላሎ፣ ኢሮብ የመሳሰሉት ወረዳዎች ክፉኛ የተጠቁ ቦታዎች ናቸው፡፡ እንዲሁም በደቡባዊ የትግራይ ክልል በተለይም በራያ አዘቦ፣ በአላማጣ፣ በማይጨውና በአጎራባች አካባቢዎች ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ በክልሉ ካሉ 46 ወረዳዎች በ21 ወረዳዎች የሚገኙ 109 ቀበሌዎች እስካሁን አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን፣ ከክልሉ መንግሥት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

አብዛኛው አካባቢ ቀድሞ የታረሰና በዘር የተሸፈነ ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ የእርሻ መሬቶቹ የቀጨጨ ቡቃያ ከማብቀል አልፈው ለውድማም ሆነ ለጎተራ የሚበቃ ፍሬ መስጠት አልቻሉም፡፡ አጉላዕ፣ ደሴ፣ አጉሮ፣ ቢርኪ የሚባሉ አካባቢዎች ከመቐለ ተነስቶ በአፋር በርሐሌና አፍዴራ አድርጎ፣ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በሚዘልቀውና በቅርቡ በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የተገነባውን መንገድ ተከትለው የሠፈሩ ናቸው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ከብቶች ተለቀው ይታያሉ፡፡ ከብቶቹ ማፍራት ያልቻለውን የገብስ፣ የስንዴና የሌሎች ቡቃያ በቁሙ እየጋጡት ይስተዋላል፡፡ ይባስ ብሎ አንድ እርሻ ሙሉ በሙሉ በከብቶች የተበላ በመሆኑ፣ ከወራት በፊት ምንም ያልበቀለበት እስኪመስል ድረስ ወደ አፈርነት ተለውጧል፡፡

በዝናቡ እጥረት ምክንያት የተከሰተው ድርቅ አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል የነካ ሲሆን፣ ይኼንን ተከትሎ ጠቅላላ የተጎጂውንና የዕርዳታ ፈላጊውን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ ምናልባት ቀድሞ ከተገመተው በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን፣ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በተለይ ቀደም ብሎ ይፋ የተደረጉት የአፋርና የሶማሌ ክልሎችን ጨምሮ የምሥራቅና የሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ጉዳይ አሳሳቢነት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልልንና በከፊል የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት በቅርቡ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሥሩ ያሉ ተቋማትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህ ቁጥር በቅርቡ ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችል ተንብየዋል፡፡ የአሁኑ ድርቅ አገሪቱ ባለፉት 30 ዓመታት ካጋጠሟት የድርቅ ክስተቶች ሁሉ የከፋ እንደሆነም በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ወራት በተለይም የዝናብ እጥረቱ ካጋጠመ ጀምሮ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በከብቶች ላይ ከተከሰተው የሞት አደጋ በኋላ፣ መንግሥት ድርቁ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በራስ መቋቋም እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ችግሩ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ በመጨመሩ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በፍጥነት ማዳረስ ሲጀምር ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጥሪ መደረጉም ይታወሳል፡፡

በእርግጥ እስካሁን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ያሳየው ምላሽ እዚህ ግባ ባይባልም፣ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ግን የእንግሊዝ መንግሥትን ጨምሮ የተወሰኑ ለጋሾች መጠነኛ ዕርዳታ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

በትግራይ የህወሃት ተቃዋሚ ፓርቲ የዓረና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ፣ ‹‹ችግሩ የተከሰተባቸው የአፋር፣ የሶማሊ፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ቀደም ብለው እንቅስቃሴ በመጀመር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በትግራይ ግን ለሕዝብ እንኳን ደፍረው ይፋ ያደረጉት በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎች መሞት የጀመሩት በነሐሴና በመስከረም ወር መጀመርያ ነው፤ የኢሕአዴግ መንግሥት ከደርግም ሆነ ከኃይለ ሥላሴ ስህተቶች እየተማረ አይደለም፡፡ ሦስቱም ሥርዓቶች ድርቁንና ረሃቡን ለመደበቅ ሞክረዋል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ችግሩ አፍጥጦ ስለወጣበት እንጂ ለመደበቅ ሞክሮ ነበር፤›› ሲሉ ይከሳሉ፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: