The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

150 ሚሊዮን ብር የዘረፉትን ህጉ የማያስራቸው ለምን ይሆን? – ከተማ ዋቅጅራ

dollar

በአለም ታሪክ ያልታየ በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ የሚታይ የሙስና  ወንጀል በግልጽ በዜና አውታሮች መስማታችን የሚደንቅ ነው። የትኞቹም  ያደጉ አገራት ለባለስልጣኖች በተንቆጠቆጠ ቤት የማኖሩ ስራ ያልተሰራ አዲስ ነገር ይዞልን ብቅ ብሏል። ወያኔ የሙስና ደፋሩ 150 ሚሊዮን ብር የህዝብ ንብረትን ዘርፎ ለስድስት ጡረታ ለወጡ ባለስልጣን ለያንዳንዱ ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር በማውጣት በስልጣኑ የሙስና ወንጀሎችን በግልጽ እየሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያኖች ልናስተውል የሚገባን ቁም ነገር ስልጣንን ተገን አድርገው ሙስና የሚሰሩትን ለፍርድ የሚቀርቡበት ግዜ ቅርብ እንደሆነ አውቀን ወያኔ ሆን  ብሎ ለማደናገሪያ ሃሳቦችን በማምጣት የኖረበትን የሙስና ስራ ህጋዊ ለማስመሰል መጣሩ ከውስጥም ከውጪም ወያኔን ከስሩ ለመንቀል የሚታገሉት ሃይሎች መምጣታቸውን ስላወቀ የህዝብ ሃሳብ ለመበታተን የሚጠቀሙበት ዘዴ እንደሆነ ልናውቅ እና ልንረዳው ይገባል። በትግሉ ጎራ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ መስዋትነት በመክፈል ለእድገታቸን እና ለነጻነታቸን እውነተኛ ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን ኢትዮጵያዊ እያደነቅሁ እስቲ  የደቡብ ኮሪያ መንግስት እና ህዝብን አገራቸውን እንዴት እንደለወጡ በጥቂቱ እንመልከት። ደቡብ ኮሪያ በከፍተኛ ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ግዜ ኢትዮጵያ ደቡብ ኮርያን ለመርዳት ወታደሮች ልካ እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። በደቡብ ኮሪያ ታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ብዙ አገሮች ወታደሮችን በመላክ እርዳታቸውን ቢያደርጉም በጦርነት ወቅት አንድም ወታደር ያልተማረከባት አገር ብትኖር የኢትዮጵያ ብቻ እንደነበረ የደቡብ ኮሪያ የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። ደቡብ ኮሪያ በጦርነት ከወደሙ አገራት አንዷ ነች። ደቡብ ኮሪያ ጃፓን እንዲሁም  ቻይና  የደበደቧት አገር ስትሆን  በከፍተኛ ሁኔታ አገሪቷ በኬሚካል  ቦንብ በመደብደቧ መሬቷ ምንም ነገር ማብቀል አይችልም ውሃዎቿም ስለተበከሉ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ ለመጠጥነት አይውልም ምናልባትም ይህንን ውሃ የጠጣ ሰው በሰአታት ልዩነት ወደ ሆስፒታል ነው የሚሄደው ወደ ህክምና መሄድ የማይችል ከሆነ ግን ከስድስት ሰአት በኋላ ሊሞት ይችላል። ጃፓን በቴክኖሎጂ በፍጥነት  በማደጓ  እና የኢኮኖሚዋ ሁኔታ በአለም ካደጉትና  ሃብታም አገር ተርታ በመሰለፏ ምክንያት በደቡብ ኮሪያ ላይ ባደረሰችው በደል ወደ 41 ቢሊዮን ዶላር  የሚገመት ካሳ ከፍላለች። የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት አንድም ሳንቲም ሳይነኩ ምናልባትም ከአለም ትልቁን የኢንዱስትሪ መንደር የሚባል ከፍተውበታል። ለዚህ ታላቅ አገራዊ ስራ የተነሱት በዚህ የስራ ዘመቻ ወቅት ፕሬዝዳንቱ አንድ አዋጅ አውጀው ነበረ እንዲህ የሚል << ጃፓን ህዝባችን ላይና አገራችን ላይ ባደረሰችው ጉዳት ሳቢያ ካሳ የሚሆን ብር ከፍላለች ይሄ ሃብት የሃገር ሃብት ነው። ይሄ ሃብት የህዝብ ሃብት ነው። በዚህ ብር አገራችንን የሚለውጥ ስራ እንሰራለን ነገር ግን ከዚህ አገራዊ ልማት ከሚውለው ገንዘብ ላይ አንድ ሳንቲም ወስዶ ለግሉ አድርጎ የተገኘ በሞት ቅጣት እንዲቀጣ >> የሚል ጠንካራ ህግ አውጥተው አገራቸውን ሊለውጡበት የሚችሉትን የእንዱስትሪ ተቋማትን በመመስረት በአገራቸው ግዙፉን የኢንዱስትሪ መንደር መሰረቱ። ደቡብ ኮሪያ እውነተኛ እና ለህዝቡን  የሚወድ ለህዝቡ የቆመ መሪ ሙስና የማይሰራ ብቻ ሳይሆን የሚጸየፍ ስለነበረ በአጭር ግዜ ህዝብን ወደ ስራ በማስገባት የኤሌክትሮኒክስ አምራች፣ ከከባድ እስከ ቀላል መኪናዎች አምራች ፣ የተለያዩ  ማሽነሪዎች አምራች…… ባጠቃላይ አገሪቷን ሊያሳድጉ እና ሊለውጡ የሚችሉበትን የስራ  ስርአት በመቀየስ መንግስታቸው የወሰደው ቁርጠኝነት አገራቸውን ከአደጉት አገር ተርታ እንድትሰለፍ ያስቻለ መሪ ነበሩ። ይሄንን ታላቅ ስራ ሰርተው ከጨረሱ በኋላ አገሪቷን መለወጥ ቢችሉም ቅሉ የአለም የሃብት ደረጃ ማግኘት አልቻሉም ምክንያቱም የሃገር ሃብት የሚመዘነው በባንካቸው የተቀመጠ ወርቅ ወይንም የመአድን ሃብት ባለመኖሩ የሃብታም አገር ደረጃዎችን ማግኘት አልቻለችም። የደቡብ ኮሪያ መሪ በድጋሚ ለህዝባቸው ንግግር አደረጉ << ስለተወሰደው ቆራጥነት ስለተወሰደው መሰዋትነት ስለነበረው ታማኝነት በህዝቦቼ ኮርቻለው በወሰድነው የጋራ የስራ ዘመቻ አገራችን ሊያስፈልጋት የሚችሉትን ነገሮች ሰርተን በአገራችን ማምረት ብንችልም አገራችንን በስራችን የለወጥናት ቢሆንም ነገር ግን በአለም የሃብት ደረጃዎች ውስጥ መግባት አልቻልንም ይህም የሆነበት ምክንያት ደግሞ በባንካችን የተቀመጠ የወርቅ ክምችት ባለመኖሩ ነው። ስለዚህም አሁን ህዝቤን የምጠይቃችሁ በኋላም እጥፍ ሆኖ  የሚመለስላችሁ ለአገራችሁ ለማበደር በእጃችሁ ያለውን የወርቅ ጌጣ ጌት እያስመዘናችሁ እንድትሰጡ እጠይቃለው ብሎ ለህዝቡ ይናገራል። ህዝቡም አንድም ሳያስቀር በሚደንቅ ሃገራዊ ፍቅር ተሳትፎ በእጃቸው ያለውን ወርቅ በሙሉ እያስመዘኑ ገቢ አደረጉ። መንግስታቸውን በታማኝነቱ፣ በአገር ወዳድነቱ፣  አገሩን ለመለወጥ ባለው ቁርጠኛነት ሃሳብ  ህዝቡ ይወደው ስለነበረ ያላቸውን ሁሉ መሪያቸውን  ስለሚያምኑት እና ስለሚወዱት ያለአንዳች መጠራጠር አደረጉት። የደቡብ ኮሪያ ንጉስ ከህዝቡ የሰበሰበውን ወርቅ ወደባንካቸው በማስገባት የአገሪቷ የእድገት ሁኔታ ታይቶ በወቅቱ በአለም 15ተኛ ደረጃ የሃብት ሰንጠረዝ ውስጥ መቀመጥ ችለዋል። በጣም የሚገርመው ግን የደቡብ ኮሪያ መሪ ለህዝቡ ያለውን ፍቅር  ከነገራቸው በኋላ ህዝባቸው ከመንግስታቸው ጎን በመሆን  አጋርነታቸውን በማሳየት  በመቆማቸው  ያለውን አክብሮ  ከነገራቸው በኋላ  አሁን የምንፈልገውን ስራ  ሰርተናል ድህነትንም አሸንፈናል አገራችንን  መለወጥ ችለናል የምትወዷት አገራችሁም በሃብት ደረጃ ውስጥ ገብታለች ስለዚህ አሁን የሰጣችሁትን ወርቅ መታችሁ ከአገራዊ ክብር እና ከአገራዊ ምስጋና ጋር መውሰድ ትችላላላቹ ሲለቻው ህዝቡ የሰጡት መልስ ግን እኛ የምንፈልገው እኛ መድመቅ ሳይሆን አገራችን መድመቋን ነው የኛ ሃብታም መሆን ሳይሆን አገራችን ሃብታም መሆን ነው የሃገር እድገት የሁላችን እድገት ነውና  የአገር ሃብት የሁላችን ሃብት ነውና  የሰጠነው ወርቅ በሙሉ ለአገራችን ሃብት ሆኖ ይመዝገብ እንጂ አንዳች አንፈልግም መንግስታችን አገራችንን ለዚህ ትልቅ እድገት ስላበቃሃት እናመሰግናለን ብለው ተመሰጋግነው ተለያይተዋል። እናም የደቡብ ኮሪያ መንግስት ያደረገውን ለአገሩ የከፈለውን እውነተኛነት እና ህዝብ ወዳድነት እንዲሁም ታማኝነት ስናይ በልባችን ሳናደነቅ አንቀርም ታዲያ የኛዎቹ መንግስት ተብዬዎች ምን ነክቷቸው ነው?  ህዝባችን በእራብ እየረገፈ  አስራ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ከፍተኛ የምግብ እርዳታ  ያስፈልገዋል እየተባለ  ህዝባችን ኑሮ ከብዶት የቀን ገቢው ከአንድ ዶላር በታች እየሆነ በመጣበት ሰዓት  ጡረታ ለወጡ  ባለስልጣኖች 150 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ እየተሰራ ያለው ቪላ ቤቶች ሳስብ የሚያሳምም ጉዳይ ነው። ህዝባችንን ከድህነት አስወጥቶ አገራችንን ወደ ተሻለ  የእድገት ደረጃ ማሳደግ ሲገባቸው በራሳቸው ተሹመው ለራሳቸው ሰርተው ለራሳቸው ሃብት አከማችተው ይሄ አልበቃ ብሏቸው በመጨረሻም ጡረታ ሲወጡ የህዝብን ሃብት እና ንብረት ዘርፈው በተቀማጠለ ቤት መኖር የሚፈልጉ ባለስልጣን እና መንግስት ኢትዮጵያ  ውስጥ መኖራቸው የሚያሳዝን ጉዳይ ቢሆንም ነገር ግን ሁሉንም የሚያይ አምላክ ፈጥኖ  የደሃውን እንባ እና መከራ አይቶ  ለኢትዮጵያ  በመድረስ ዋጋቸውን እንደሚሰጣቸው እናውቃለን። እኛ ግን የሚጠበቅብንን እናድርግ። ኢትዮጵያኖች አሁን ከኛ የሚጠበቀው ግፈኞች በምንም መልኩ በአገራችን ነግሰው መቀመጥ እንደሌለባቸው መታገል ብቻ ነው። ካለበለዛ  ወያኔዎች ገና ህዝባችንን እየዘረፉ እና እያሰሩ፣ እያስለቀሱ እና እያስራቡ እራሳቸውን በሃብት ወንበር አስቀምጠው የግል አውሮፕላን ገዝተው ለሰሩት የተሳካ የዘረፋ እና የወንጀል ስራ  ይቅርታ ለካ የሚባለው ልማታዊ ባለስልጣ ነው ለልማታዊ ባለስልጣኖች ቦይንግ አውሮፕላን ገዝተን ሸልመናቸዋል ብለው እንደሚናገሩ አልጠራጠርም።  ምክንያቱም ዘረፋን፣ ወንጀልን፣ ሙስናን፣ እንደ ህጋቸው ከተቀበሉ ቆይተዋልና ነው። እንግዲህ እንንቃ  እኛ በግ አይደለንም በግ ብቻ ነው ከአራጁ ጋር የሚውለው። ከተማ ዋቅጅራ 12.11.2015 Email- waqjirak@yahoo.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: