The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ረሃቡና እድገታችን፡ ተጠያቂው ማን ነው? | ክፍል ሁለት | የተንሸዋረረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ

በአብዱረዛቅ ሑሴን

የፈረደበት ሁለት ዲጅት እድገት መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ለሚከሰቱ መልካምም አስከፊም ክስተቶች እንደ ምክንያት አለአግባብ ሲጠቀምበት ይታያል፡፡ ከመጠን ያለፈ የኑሮ ውድነትን፣ ወያዣው የጠፋውን የዋጋ ግሽበትን እና ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆልቆለ የሚሄደውን የማህበራዊ አገልግሎት ጥራት ጉድለት እድገቱ ያመጣው እንደሆነ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እታች እስካለው ካድሬ ሽንጣቸውን ገትረው ይሞግታሉ፡፡ ይባስ ብሎ ይህን የሁለት ዲጅት እድገት ለአገዛዛቸው ትክክለኛነት እንደ ማረጋገጫ በመውሰድም አምባገነንነትን ያለ ገላጋይ ይግቱናል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት የህብረተሰቡን ኑሮ ሳያዛባና ዲሞክራሲን ሳይሸረሽር ማስኬድ እንደሚቻል እስክንጠራጠር ድረስ እድገት ማለት የኑሮ ውድነት መጨመር፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የማህበራዊ አገልግሎት መዛባት እና የአምባገነንነት መፈርጠም አስመስለውት እድገትንና እርግማንን እያምታቱ ይኖራሉ፡፡ የኢኮኖሚ እድገት እነዚህን አላስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ሲያስከትል ከሚከተሉት ፖሊሲ ችግር ሊሆን እንደሚችል ለደቂቃም ማሰብን አይፈልጉም፡፡ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ሳይሆን በቀደዱለት ቦይ እንደሚፈስ የወራጅ ውሃ የሚሽጎደጎደው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሃያ አምስት አመት የአንድ ፓርቲ አገዛዝና ከስር አመታት የ#ሁለት ዲጅት; እድገት በኋላም ህዝቡን መመገብ አቅቶት በምግብ እጦት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በሞት አፋፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሃገሪቱ ውስጥ ለሚታየው ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መዛባቶች ብቻ ሳይሆን አሁን ለተከሰተው ረሃብና እልቂትም ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይህ ፅሁፍ ይሞግታል፡፡

File Photo

File Photo

.
ገዢው ፓርት ወደስልጣን ከመጣ ወዲህ የሚያወጣቸው የኢኮኖሚክ ፖሊዎች ግብርናና ገበሬውን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ መገንባትን እንደ ዋና ግብ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ ከ80% በላይ የሆነውን የገጠር ነዋሪንና የኢኮኖሚውን ግማሽ እጁን የያዘውን ግብርናን መሰረት ማድረጋቸው የእድገት ፖሊሲያቸውን “pro-poor” እያሉም ባገኙት አጋጣሚ ያሞካሹታል፡፡ ይህ ለግብርና የተሰጠው ትኩረት ተገቢ ሊባል የሚችል ቢሆንም በአብኛው የፖሊሲ ዶክመንቶች ላይ አብዝቶ ማይወሳው የአገልግሎት ሴክተሩ ኢኮኖሚውን ሲዘውረው ይታያል፡፡ “የፓሊሲ ሳይሆን የአፈፃፀም ችግር ነው ያለብን” ለሚሉን ሹማምንቶቻችን ይህ ሁኔታ ከበቂ በላይ ግልፅ ምሳሌ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ግብርና ላይ እያተኮረ በተግባር ግን የአገልግሎት ሴክተሩን እያሳደገ ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተንሸዋረረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢባል በደንብ የሚገልፀው ይመስለኛል፡፡
.
የመጀመሪያና ሁለተኛ ሴክተር የሚባሉትን ግብርናና ኢንዱስተሪን ዘሎ ሶስተኛውን የአገልግሎት ሴክተር ተመጣጣኝ ባልሆነ ሁኔታ ማሳደግ ለብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በርን ወለል አድርጎ እንደመክፈት ነው፡፡ የአገልግሎት ሴክተር ሲባል ኮንስተራክሽን፣ ንግድ፣ ትራንስፖርትና ኮሚውኒኬሽን፣ ሆቴል፣ የፋይናንስ ተቅዋማት፣ ሪል እስቴት እና የመሳሰሉት የሚያጠቃልል ሲሆን ይህ ሴክተር የግብርናና ኢንዱስትሪው እድገት ጋር ተመጣጥኖ ሳያድግ ሲቀር የኑሮ ውድንት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ያልተመጣጠነ የከተማውች እድገትን ያስከትላል፡፡ አስተውለን ከተመለከትንም መንግስት የእድገቱ ማሳያዎች ብሉ በሬዲዮም በቴሌቪዥንም የሚያደነቁረተን ከላይ የተጠቀሱትን እንደሆነ በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡ ግብርናን አልሞ አገልግሎት ሴክተሩን የሚያሳድገው በደመ ነፍስ የሚመራው ኢኮኖሚ ከጎኑ ነኝ ብሎ የሚፎክርለትን ገበሬና የገጠሩ ህዝብ ህይወትን መለወጥ ስላልቻለ በስሙ የሚነገደው ገበሬ በድህነት ሲከፋም በረሃብ እየረገፈ ይገኛል፡፡
.
ሚዛኑን የሳተውና ጤናማ ያልሆነው የኢኮኖሚ እድገት ከተማ ላይ ካለው ድሃ በላይ የገጠሩን ህዝብና ገበሬውን በብዛት ይጎዳዋል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱን አምራች ከሆኑት ግብርና እና ኢንደስትሪ አርቆ ወደ አገልግሎት ሴክተር ማዞሩ ለነዚህ ለሃገሪቱ ጀርባ አጥንነት ለሆኑና ዘላቂነት ላለው ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት ለሆኑት ሴክተሮች በቂ ትኩርት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል፡፡ ግብርናውን እና ኢንደስትሪውን ለማሳደግ መዋል የሚገባው ሀብት፣ ንብረት እና እውቀት አቅጣጫውን በመቀየር አገልግሎት ሴክቱርን እያፈረጠሙት ይገኛሉ፡፡ ይህም በቀጥታ በግብርናና የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦት እንዳያድግና እንዳይሻሻል እክል በመሆን ሴክተሮቹ አቅፈው የያዙትን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍልና በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያለው ህዝብ የችግር ተጋላጭነቱን ይጨምሩበታል፡፡ የኑሮ ውድነትም፣ የዋጋ ግሽበቱም፣ ረሃቡም ማን ላይ አሳማሚ ዱላቸውን እያሳረፉ እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡
.
ሌላው አገልግሎት ሴክተር መር የሆነ ኢኮኖሚ ችግሩ ከከተሜነት ጋር ይገናኛል፡፡ ሴክተሩ ሲፈጥረው ከተማዎችን እንደ ማእከል ይጠቀማል፡፡ የስራ እድሎች፣ ህይወትን የመለወጥ እድሎችና የተሻለ የማህበራዊ አገልግሎት አማራጮች ከተማዎች አካባቢ በብዛት እንዲሰበሰቡ ያደርጋል፡፡ በገጠር ያለው አምራች የወጣት ሃይል ግብርናውን ትቶ ወደ ከተሞች እንዲተም፤ የግብርና ምርቶችም ከአዝመራው እንደተሰበሰቡ ለገበሬው ቅርበት ካላቸው ገበያዎች በመለቀም ወደ ከተማ ማእከሎች እንዲጋዙ ያደርጋቸዋል፡፡ በሂደት አምራች ሃይሉን እያጣ የሚሄደው የግብርና ሴክተሩ ምርታማነቱ እንዲመናመን ይሆናል፡፡ በምርት መሰብሰቢያ ወቅት የእህል ገበያ ስለሚቀንስ፣ ገበሬው ዋጋን በመተመን ላይ በቂ መደራደሪያ አቅም ስለሌለው እና ምርቱን ለረጅም ግዜ ሊያስቀምጥ የሚችልበት ማከማቻ ስለማይኖረው በብዙ ድካም ያመረተውን ምርት በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ ያስገድደዋል፡፡ ወጣት አምራች ሃይሉን በማጣት ምርታማነቱ የሚቀንሰው፣ ለክፉ ጊዜ እንዲሆነው ምግቡን ማከማቸት የማይችለው እና በገበያው ላይም ዝቅተኛ የሽያጭ ዋጋን የሚያገኘው ገበሬ አይደለም አሁን እንደተከሰተው የከፋ ድርቅ ቀርቶ ትንሽ ሰው ሰራሽ መስተጓገሎችን የመቋቋም አቅም አይኖረውም፡፡ መንግስት ከወረቀት ላይ ፉከራው በዘለለ በገጠር ላለው ወጣት በግብርና ህይወትን መለወጥ እንዲችል ፖሊሲያዊ ድጋፍ እስካልሰጠው ድረስ፣ ምርቱን ጠብቆ ሊያቆይበት የሚችልበትን የእህል ማከማቺያዎች ግንባታ ላይ እስካላገዘው ድረስ እና በገበያ ላይ ዋጋ መተመኑ ላይ ገበሬውን አቅም እስካላጎለበተ ድረስ ግብርናው የሀገሪቱ የእድገት መሰረት እንዲሆን መመኘት ከእውነታ የራቀ ህልም እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ገበሬውም ለድህነትና ረሃብን ለመሰሉ ቀውሶች ተገላጭነቱ እየበረታ ይሄዳል፡፡
.
ድርቅ በአብዛኛው ተፈጥሮአዊ ስለሆነ መከላከሉ ቢያዳግትም ረሃብ ግን ሰው ሰራሽ ነው፤ መከላከልም ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት መቼም ብር ያዘንብ ይሆን እንጂ ዳመናን ሰብስቦ ዝናብ አያዘንብም የሚል አይጠፋም፡፡ ዝናብን በአመት ለጥቂት ቀናት የሚያገኙ ሀገራት እንዳሉና ህዝባቸውን ግን አጥግበው ማብላት የቻሉ ብዙ ሀገራት እንዳሉ ማስታወሱ መልካም ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገት አለ ሲባል ወይ ግለሰቦች የሃብት ክምችት ይኖራቸውና በድሎትም በችግርም ጊዜ ቢያንስ እራሳቸውን እየመገቡ ይኖራሉ፡፡ ሁሉም ሰው እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ከባድ ስለሚሆን በተለይ አሁን የተከሰተው አይነት ከአቅም በላይ የሆነ ድርቅ እና ተመሳሳይ ክስተቶች ሲከሰቱ መንግስት ችግሩን በቅድሚያ ተንብዮ ቅድመ ዝግጅት ከማድረግ አንስቶ የችግሩ ተተቂዎችን በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ይጠበቃል፡፡ የኛዎቹ የፃፉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር አቅቷቸው ሚዛኑን የሳተ ፖሊሲ በመከተል የምርት አቅርቦት ዋና ምንጭ የሆኑትን ሴክተሮችን በመዘንጋት የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ አካሄድ መከተል ሳያንሳቸው ሳያቅዱት ተሳካልን በሚሉት “የሁለት ዲጅት” እድገት ትርክት ማማ ላይ ተቀምጠው በረሀብ በሚያልቀው ሚስኪን ህዝብ ላይ ይሳለቃሉ፡፡ ከኢኮኖሚያዊ አልፈው የፖለቲካዊ አካሄዳቸው ሞዴል አድርገው የሚወስዷት ቻይና አሁን የደረሰችበትን የእድገት ጉዞዋን ስትጀምር ግብርናውን በማሳደግ በምግብ ራስን መቻልን ካረጋገጠች በኋላ እንደነበር ማን በነገራቸው? የአካሄድ ለውጥ አሳይቷል የተባለለት የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንደሌሎች ቀደምቶቹ ያቀደውን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ልማት የትኩረት አቅጣጫ በመዘንጋት የአገልግሎት ሴክተሩን መሰረት ያደረገውን እድገት አጠናክሮ ሲቀጥል ታይቷል፡፡ ይህን መሰረታዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአቅጣጫ ለውጥ ከአተገባበር ቆራጥነት ጋር ታግዞ ወደ ስራ እስካልተገባበት ድረስ የዝናብ መጥፋትን እየጠበቀ የሚመጣው ድርቅ የብዙሃንን ነፍስ አደጋ ላይ እየጣለ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡

– See more at: http://www.zehabesha.com/

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: