The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ጥቂት ስለ ሸዋሮቢት እስር ቤት – ናትናኤል ያለምዘውድ

ጥቂት ስለ ሸዋሮቢት እስር ቤት   Robit camp

ናትናኤል ያለምዘውድ

በንጉሱ ዘመን እንደተመሰረተ የሚነገርለት የሺዋሮቢት ማረሚያ ቤት ከአ.አ በደብረ ብርሃን ጠመዝማዛውን መንገድ ተከትሎ ከተጓዙ በኋላ ከተራሮች ግርጌ የሚገኝ ረባዳ መሬት ላይ የሰፈረ ማረሚያ ቤት ነው፡፡ በዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ አራት ዞኖች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ዞን የዐማራ ክልልና የደቡብ ክልል ረዥም ጊዜ ፍርደኞችን ጨምሮ ከ3-5 አመት ፍርደኛ የፌደራል ታራሚዎችን የያዘ ነው፡፡ በዞኑ ውስጥ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታራሚዎች ለብቻው በቆርቆሮ በተከለለ ስፍራ ከ150 በላይ ሆነው ቀናትን ያሳልፋሉ፡፡ ሁለተኛው እስከ 2 አመት ከ11 ወር ፍርደኞችን፣ ሶስተኛው ከአንድ አመት እስከ አንድ አመት ከአንድ ወር፣ የመጨረሻው ከሌሎች ዞኖች ለመፈታት 3 ወር የቀራቸውንና የአንድ አመት ፍርደኞች ይይዛል፡፡ ይህኛው ዞን ቤቶቹ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የተሰሩ ናቸው፡፡
ከሁሉም ዞኖች የመጀመሪያው (ዞን አንድ) በአንፃሩ በህንፃዎቹም ሆነ በግቢው ጥራት የተሻለ በመሆኑ በቅጣት ወደ ሌሎቹ ዞኖች የሚላክ እስረኛ ‹‹ክፍለ ሀገር ገባ!›› ተብሎ ይቀለድበታል፡፡
የእስረኞቹ አኗኗር ሁኔታ በቤትና በዞን የተከፋፈለ ነው፡፡ ከመጨረሻው ዞን አራት ውጭ ሁሉም ዞኖች፣ ከ1400 በላይ ታራሚዎች ይይዛሉ፡፡ እንደየ ቤቶቹ ስፋት ከ160-360 እና ከዛ በላይ ይኖርባቸዋል፡፡ አልጋ ለማግኘት ከ6 ወር እስከ አንድ አመት መጠበቅ የግድ ከመሆኑም በላይ መሬት ላይ ከ2 ፍራሽ ከ5-7 ሰው እንዲተኛ ይገደዳል፡፡ እንደዚህ ተፋፍጎ የሚተኛው ታራሚ ደቦቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ለሽንት የሚነሳ በእነዚህ ደቦቃዎች መካከል መራመድ አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ መካከል በሰላም ተኝቶ ማንጋት ከባድ ነው፡፡ አንዳንድ ቤቶች እስከ 8 ሰዓት ‹‹መሽናት ክልክል ነው›› የሚል ህግ አውጥተው ሮንድ አቁመው ያድራሉ፡፡ አካባቢው በጣም ሞቃት ከመሆኑ ባሻገር የሰው መተፋፈግ ሲጨመርበት ሁኔታውን እንደ አስፈሪ ቅዠት ያመሰቃቅለዋል፡፡
አንድ እንግዳ ሰው ወደ እስር ቤቱ ጎራ ቢልና ለአዲስ ገብ ታራሚዎች የሚሰጠውን መግለጫ ቢያዳምጥ በህግና በግዴታ ብዛት ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ስፖርት መስራት ክልክል ነው (ሩጫን አይጨምርም)፡፡ የስልክ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም፡፡ ማታ መፀዳዳት፣ መፅሃፍ ማስገባት፣ የውጭ ዜና አውታሮችን መከታተል፣ ከ200 ብር በላይ ማስገባት አይቻልም፡፡ ኢቲቪ (ኢቢሲ) በግዴታ ይከፈታል፡፡ ለነገሩ ወዶ የሚከታተለው ባለመኖሩ ማስገደዱ አዋጭ ‹‹ልማታዊ/አብዮታዊ›› ዘዴ ነው፡፡ አደረጃጀት ስብሰባ ግዴታ ነው፡፡ ግዳጅ (ለእርሻና ፅዳት) ግዴታ ነው፡፡
የማረሚያ ቤቱን አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት ያስችል ዘንድ ነጣጥለን እንያቸው፡፡
ማደሪያ ቤቶቹን ስንመለከት ህንፃዎቹ 11 ሜትር በ11 ሜትር ስፋት እና ከዚህም ሰፋ ያሉ ሲሆኑ እንደየስፋታቸው በርካታ ሰዎችን ይይዛሉ፡፡ 11 በ11 ሜትር ስፋት ያላቸው ከ160 በላይ ሲይዙ ትልልቆቹ ከ350 በላይ ይይዛሉ፡፡ ትልልቆቹ ሲባል ግዙፍ ቤት አትጠብቁ፣ ሁለቱ ትልልቅ የሚባሉ ቤቶች በአንድ ላይ ሲታዩ እንኳን 700 በላይ ታራሚዎች ይቅርና 400 ያህል ይይዛሉ ተብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ሁሉም ቤቶች በጎን የተጨመረ ለሽንት ቤት ተብለው የተሰሩ ክፍሎች ሲኖራቸው በህመም ምክንያት የግድ የሆነበት የጤና ኮሚቴንና የቤት አስተዳደርን ማስፈቀድ ይጠበቅበታል፡፡ አብዛኛዎቹ ክፍሎች ‹ኤየር ኮምዲሽነር› የላቸውም፤ ወይንም የተገጠመላቸውም አይሰሩም፡፡ ክፍሎች በኬሻ ኮርኒስ የተሸፈኑ ወይንም ከእነ አካቴው የሌላቸው ናቸው፡፡ ወለላቸው ለመወልወልም አይመችም፡፡ ጠረናቸው ይከረፋል፡፡
የውሃ አቅርቦት ችግር አለ፡፡ ቧንቧ በየቤቱ ሳይሆን ለመላው ዞን ሶስት ቧንቧዎች ብቻ አሉ፡፡ ለሚጠጣና ለንጽህና የሚሆን ውሃን በግል በገዙት ከሪካን ተራ ጠብቆ መቅዳት ግዴታ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ በወረፋ ምክንያት ተደጋጋሚ ጸብ መከሰቱ የተለመደ ነው፡፡
ምግብ በተመለከተ፣ ቁርስ ዳቦ በሻይ ቢሆንም 80 ፐርሰንት ታራሚው ሻይውን ለልብ ድካም አጋላጭ ነው ስለሚባል አይጠቀመውም፡፡ የዳቦው መጠንም ቢሆን ለኬጂ ተማሪ እንጂ ለአንድ ወጣት ቁርስ ተብሎ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ምሳና እራት አንድ እንጀራ በሽሮ ይታደላል፡፡ የእንጀራውም የወጡም ጥራት ዝቅተኛ ከመሆኑ በላይ ለጨጓራ በሽታ የሚያጋልጥ ነው፡፡ የምግብ ለውጥ (ዑደት) ባይኖርም ከስንትና ስንት ቀን በኋላ ጥቅል ጎመን፣ ድንችና ውሃ የቀላቀለ ቅጠላቅጠል (አትክልት) ወጥ ይመጣል፡፡ በዚህ ቀን በስፋት ሽርጉዱን፣ ግፊያውን ላስተዋለ ታራሚው ቀናትን ምግብ ባይኑ ያላየ ይመስለዋል፡፡ ስጋ በዓመት 3 ጊዜ (ምሳ ሰዓት ላይ) በዓመት በዓላት ቀን ይቀርባል፤ ለዘመን መለወጫ፣ ለገና እና ለፋሲካ በዓላት፡፡ የምግብ ችግር አሳሳቢ መሆኑን የሚያጎላው ታራሚው ያን ጣዕም የለሽ ምግብ መሰራረቁና በቅርቡ በ16/02/2008 በተካሄደው የ20 መሪዎች ስብሰባ ላይ የተነሳው ጥያቄ ዋነኛ ትኩረት መሆኑ ሲታይ ነው፡፡
ልብስ ማንኛውም ታራሚ የራሱን ልብስ የሚጠቀም ሲሆን ለመስክ ሰራተኞችና ለተማሪዎች ቱታ ይሰጣል፡፡ አልጋ ለደረሳቸው አንድ ብርድ ልብስ ይሰጣል፤ ብርድ ልብሱ አንድና ከዚያ በላይ ታራሚ ያስተናገደ አሮጌ ሊሆን ይችላል፣ ይሄንም እድለኞች ናቸው የሚደርሳቸው፡፡ ታዲያ ብርድ ልብሷ ጸረ-እንቅልፍ ተባይ አለባት፡፡
ለሽንት ቤትና ሻወር በፈረቃ የሚሰሩ ሁለት ህንጻዎች ሲኖሩ አንደኛው ህንጻ ለብቻው የተገነባና በውስጡ 14 መጸዳጃዎችን ሲይዝ ሁለተኛው ከሻወሩ ጋር የተገናኘና በውስጡ 30 መጸዳጃዎችን ይይዛል፡፡ ከመጀመሪያ ህንጻ 3ቱ፣ ከሁለተኛው 6ቱ አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው፡፡ መጸዳጃ ክፍሎች 80 ሴ.ሜ ስፋት በ1ሜ ከፍታ ያላቸው ናቸው፡፡ መተላለፊያ ኮሊደሮች በቆሻሻ ፍሳሽ የተሞሉ ናቸው፡፡ አጠቃላይ የሽንት ቤቱ ሁኔታ ከጽዳቱ ችግር በላይ ከዕይታ የተከለለ አለመሆኑ ሰላም ይነሳል፡፡
ሻወሩ ደግሞ 80 ሳ.ሜ በ80 ሳ.ሜ ስፋትና 140 ሳ.ሜ ከፍታ የሚኖራቸው 20 ክፍሎች የያዘ እና ሁሉም በርና የውሃ አቅርቦት የሌላቸው በመሆናቸው ሻወር ከመባል ይልቅ የጅምላ መታጠቢያ ቢባሉ ይቀላል፡፡ እርቃንን ከሰው ፊት መቆም በጣም ደስ የማይል ስሜት ቢፈጥርም መታጠብ ግዴታ በመሆኑ በጀሪካን ያንጠለጠሏትን ውሃ በጣሳ እየቀዳህ መታጠብ የመጨረሻ መፍትሄ ነው፡፡ ልብስ መታጠቢያ እንዲሆኑ የተዘጋጁ ቦታዎችም ውሃ የሌላቸው ሸካራና የተሰባበሩ በመሆናቸው አንድን ጀሪካ በቁመቱ ከሁለት ከፍሎ ሳፋ መስራት ብቸው መፍትሄ ነው፡፡
እስካሁን የተዘረዘሩት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በስነ-ልቦና ላይ ጫና ማሳደራቸው የሚታበይ ባይሆንም ከአስተዳደራዊ በደሉና ከህገ-ደንቡ አፋኝነት አንጻር ኢምንት ተብለው የሚገለጹ ናቸው፡፡ የአስተዳደራዊ በደሉን ከማየታችን በፊት ግን የህክምናውን ሁኔታ ብናይ መግቢያም ይሆናል፡፡
ህክምና በመደበኛነት በሳምንት 3 ቀናት (ሰኞ፣ ረቡዕ፣ አርብ) ይሰጣል፡፡ አንድ እስረኛ በእነዚህ ቀናት ለመታከም በቀዳሚው ቀን ምሽት መመዝገብ ሲኖርበት ተመዝግቦ ከመቅረቡ በፊት ስክሪን የሚባል ቅድመ ምርመራ በቃል ይሰጠዋል፡፡ ስክሪን ያለፈ ወደ ክሊኒክ ሄዶ ዋና ምርመራ አድርጎ አሞካክስሊን ይዞ ይመለሳል፡፡ አብዛኛው ታካሚ በሽታው ጨጓራ ቢሆንም ‹‹እንጀራ በዳቦ ይቀየርልኝ›› የሚል ጥያቄ ለማንሳት የተፈጠረ ተደርጎ ስለሚታመን በስድብ አሸማቆ ማስመለስ ዋነኛው መድሃኒት ነው፡፡ ቀዶ ጥገና፣ ራጅ፣ አልትራሳውንድ… የሚያስፈልጋቸው ህመሞችን ለመታከም የግድ አዲስ አበባ መሄድ አለበት፤ ይህ ደግሞ እድሉ የሎተሪ ያህል ጠባብ ነው፡፡ በቅርቡ በነሀሴ ወር አንድ የኪንታሮት በሽተኛ የሆነ ወጣት ክፉኛ ታሞ መቀመጥ፣ መጸዳዳት፣ መተኛት ተስኖት እየተሰቃየ ለህክምና ሄዶ ማስታገሻ ኪኒን እንኳ ሳይሰጠው ማባባሻ ግልምጫ ተሰጥቶት ተመልሷል፡፡
ቤቶች ፀረ ተባይ እንዲረጩ፣ ንፅህናውን የጠበቀ ፍራሽ እንዲሰጥ እና መሰል ለንፅህና የሚረዱ ተግባራት እንዲፈፀሙ በማድረግ የመከላከል ፖሊሲውን እውን ለማድረግ የሚታየው ‹‹ቁርጠኝነት›› ከቴሊቪዥን ዘሎ መሬት ላይ ጠብ ብሎ አያውቅም፡፡
አንድ ‹‹ታራሚ›› በሰራው ወንጀል ተፀፅቶ መልካም ዜጋ እንዲሆን ሰብአዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ቤተሰቡን በስልክ ማግኘት ካልቻለ፣ ጠያቂ ሲመጣም ሚስጥሩ ተጠብቆለት ካላወራ፣ ደብዳቤው በትክክል እንዲደርስ ካልተደረገ፣ በእውቀት እንዲታነፅ ካልታገዘ፣…በግቢ ደህንነቶች ክትትል፣ በአደረጃጀት መቀፍደድ፣ የውሸት ግምገማ በማድረግ፣ የኢቲቪን ፕሮፖጋንዳ በመጋት፣ ባዶ ግቢ ውስጥ ባዶ ቀናትን እንዲያሳልፍ በማስገደድ የተሻለ ዜጋ ማፍራት ዘበት ነው፡፡
ቤተ መፅሃፍቱ ባመዛኙ የሴቶች ገመና እና መሰሎቹን አካትቶ፣ አራት የታሪክ መፅሃፍቶችን ብቻ የያዘ ነው፡፡ በእርግጥም ወጣቱ ታሪኩን ሳያውቅ ባዶ ሜዳ ላይ እንዲበቅል የተፈረደበት ይመስላል፡፡ ቤተ መፅሃፍቱ ታዛቢን ፈርተው እንጂ ወጣቱ አንብቦ እንዲለወጥ የተቋቋመ አይመስልም፡፡ መቼም መፅሃፍ ማስገባት ክልክል የሆነበት ግቢ ውስጥ ወጣቱን ለመለወጥ አላማ ይኖራቸዋል ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡
በግጭት አፈታት ዙሪያ የሚወሰዱ እርምጃዎች እስር ቤት ውስጥ ለሰው የሚሰጠውን ክብር ለመመዘን ይረዱ ይሆናል፡፡ ፀብ ከተፈጠረ የተጣሉ ሰዎች የዱላ መዓት ይወርድባቸውና ጥፋተኛው ይለያል፡፡ ድብደባው የተለያየ ደረጃና አፈፃፀም አለው፡፡ እንዲያኮበኩቡ ያደርጉና በጅዶ፣ በልምጭ፣ በጥፊ፣ በካራቴ፣ እየተራረፉ ይቀጠቅጧቸዋል፡፡ ካስቸገራቸው ሁለት እጁን ወደ ኋላ፣ ሁለት እግሩን ወደፊት አድርገው ይቀጠቅጡታል፡፡ በዱላው ውርጅብኝ መናገርና መቆም ሲያቅተው ድብደባው ይበርድለትና እጁን (አንዳንዴ እግሩም) እንደተሳረ ሹል ድንጋዮች ከተነጠፉበት ጠባብ ጨለማ ክፍል (ቅጣት ቤት) ይገባል፡፡ ይች ቤት አራት ሜትር በአራት ሜትር ስትሆን አንዳንዴ ከ20 በላይ ቅጣተኞች ይገቡበታል፡፡ ብርሃን የሌለባት፣ ትኋን የሚርመሰመስባት፣ ምንም ነገር ማንጠፍ የማይቻልባት፣ ልብስ መቀየር፣ በየጊዜው መታጠብ የሚከለከልባት፣ የእስር ቤቱ እስር ቤት ናት፡፡ ከዚህ እስር ቤት የወጣ ከመቃብር ፈንቅሎ የወጣ ያህል ይሰማዋል፡፡
የሰው ልጅ ክብር ተሟጦ ያለቀ በሚመስለው ግቢ የአእምሮ ህመምተኞች፣ በሰዶም የሚጠረጠሩ ሰዎችም ሲኖሩ የአእምሮ ህመምተኞችን የእንቅልፍ ክኒን (ናርጋቲን) እየወጡ ማስተኛት የተለመደ የየለት ተግባር ነው፡፡ ወጣቱ እስረኛ በግብረ ሰዶም ተጠርጣሪው ጋር መተኛት ስለሚፀየፍ ተጠርጣሪው ብቻውን እንዲተኛ ይፈረድበታል፡፡ ፖሊሶች ግን ድርጊቱን ያወግዙታል፡፡ በእርግጥ ጤነኛው ታሳሪም እስር ቤቱን ከመጥላቱ የተነሳ የሽንት ቤት ቆሻሻ ሰውነቱን ተለቅልቆ እርቃኑን ሆኖ እስረኛውን ማሯሯጥና በበሽተኛ ሂሳብ ወደ አዲስ አበባ ለመዘዋወር ይሞክራል፡፡ ሌሎች እስረኞች ደግሞ አንገት፣ ሆድና ክንዶቻቸውን በምላጭ በመተልተል ደም እያዘሩ በዱላ በማሯሯጥ ወይም ዛፍ ላይ ተሰቅለው (ተንጠልጥለው) የተጓደለብን ፍትህ ካልተመለሰልን አንወርድም በማለት ያንገራግራሉ፡፡ የአስተዳደሮች መልስ ታዲያ ወንድ ከሆንክ ራስክን ፈጥፍጥ ወይንም ጉሮሮህን ቆርጠህ ሙት የሚል ነው፡፡ ለእነሱ የእስረኛው ስነ ልቦና መቃወስ ምናቸውም አይደለም፡፡ በእርግጥ የእየራሳቸው የስነ ልቦና ደረጃ ከታራሚው ቢያንስ እንጂ የሚስተካከል እንኳ አይደለም፡፡ የስነ ልቦና አማካሪዎች ቢኖሩም ጥርሳቸውን ከመፋቅ የዘለለ ተግባር ሲፈፅሙ አይታዩም፡፡ አንድ ሊፈታ የተቃረበን እስረኛ ከድርጊቱ ታቅቦ ጥሩ ዜጋ ይሆን ዘንድ አገልግሎት ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡ ወራትን ዓይንህ ለአፈር የተባለ ሰው የሶስት ቀን የምክር አገልግሎት በመስጠት ለመቀየር ወይስ ለማደንቆር! አንዳንዶች ከምክር አገልግሎት ሲመለሱ መለወጥ ይቻላል ካለ ራሱ የማይለወጥ የቁም እስረኛ ሆኖ የሚሰራ ለእኔ ብሎ ነው? እያሉ ያሾፉበታል፡፡ የህግ አማካሪ፣ ቅሬታ ሰሚ፣ በአካል (በስም) ደረጃ ቢኖሩም በራሳቸው ላይ ለቢሯቸው ስያሜ ካወጡት የመፃፊያ ዋጋ የሚበልጥ ተግባር ፈፅመው አያውቁም፡፡ እስር ቤቱ በሚጣሉ ፖሊስ (አባል) በተጋጩ፣ ከቤት አስተዳደር የተነጋገሩ እስረኞች ከጉልበት ቅጣት፣ ከጨለማ ቤት፣ ከዱላ፣ በኋላ ‹‹51›› የሚል ክስ ይመሰረትበታል፡፡
ክሱ የማረሚያ ቤቱን ደንብ መተላለፍ ሲሆን ቅጣቱ የአመክሮ አንድ ሶስተኛ ያስፈርዳል፡፡ አንድ አመት አመክሮ ያለው አራት ወር ይፈረድበታል፡፡ ጥፋቱ ከበድ ካለም ዱላው፣ የጉልበት ቅጣቱ፣ ጨለማ ቤት እስሩም ጨምሮ ክሱ ከበድ ይልበታል፡፡ ሙሉ አመክሮውን እስከማስፈረም ይደርሳል፡፡ በቅጣት ዙሪያ አንድ አይነተኛ ምሳሌ አለ፡፡ ከቤተ መፅሃፍት ተውሶ መፅሀፉ የጠፋበት እስረኛ የጉልበት ቅጣት የመፅሃፉን ዋጋ እስኪከፍል ጨለማ ቤት ከዛ ‹‹51›› ክስ ተመስርቶበት አመክሮውን ይነጠቃል፡፡ ወንጀሉ መፅሃፍት ማጥፋት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ያ የእስረኛ ዳግም መፅሃፍ ስለማያወጣ የአንባቢዎችን ቁጥር ለመቀነስ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ አመክሮ ማለት የፍርድን አንድ ሶስተኛ ማለት ሲሆን መልካም ስነ ምግባር ያሳየ እስረኛ በፍርዱ መጠን አንድ ሶስተኛው ተቀንሶለት እንዲፈታ የሚደረግበት አሰራር ነው፡፡ ይህን እድል ለማግኘት በተለያዩ የስራ መስኮች መሰማራትና በእስር ቤቱ ቆይታ ልክ ማገልገል ግዴታ ነው፡፡ እስረኛው በቤት አስተዳደር፣ በአስርና ሀያ መሪ የቤት ካውንስሊንግ፣ በረኛ (በር ጠባቂዎች) የቤትና ሽንት ቤት ፅዳተኛ፣ ጎለኛ (ለእስረኛ ወጥና እንጀራ የሚያመጡ)፣ መስክ በመስራት እድሉን ለመጠቀም ይሞክራል፡፡ በክስ እስኪነጠቅ ድረስ! መስክ ማለት ማረሚያ ቤቱ የእርሻ ማሳ ስላለው ይህን ማሳ መንከባከብና ከብቶችን መንከባከብ ይጨምራል፡፡ መስክ ሲባል ችግኝ መደብ፣ እሳር አጫጅ፣ ከብት አላቢ፣ ደረቅና ማንጎ የሚባሉ ክፍሎችን ሲይዝ መቆፈር፣ ማጨድ፣ ማረም፣ መቁረጥ፣ መመንጠር፣ እና መሰል ተግባራት ሲኖሩት ስራው እጅግ አድክሚ ነው፡፡ ከስራው በላይ ግን ለጆሮ የሚሰቀጥጠው የክፍያ መጠኑ ነው፡፡ አንድ መስከኛ በቀን 5 ብር ይከፈለዋል፡፡ የመቶ ብር ስራ ሰርቶ 5 ብር ለንጽጽር የማይመች ክፍያ ነው፡፡
ወፍጮ ቤት፣ ሚንስ ቤት በቀን 8 ብር፣ ጉልኛ ለቀን 2 ብር፣ ዘበኛ (በረኛ) 2 ብር፣ የቤት ጽዳተኛ 2 ብር፣ የሽንት ቤት ጽዳተኛ 5 ብር፣ ከፍተኛው ክፍያ 8፣ ዝቅተኛው 2 ብር ነው፡፡
በአጠቃላይ ሸዋሮቢት እስር ቤት 4400 በላይ እስረኛዎችን ይይዛል፡፡ እስር ቤቱ ይህን ያህል ዜጋ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ አጭቆ ያሳድራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥፋተኛን ማረም ይከብዳል፡፡ በእርግጥ ስርዓቱ ለችግሮች መፍትሄ መሻት ባይፈልግም ጦሱ ከህብረተሰቡ ጀርባ የማይወርድ በመሆኑ መንግስትን ትተን በየግላችን ተስፈኛ ወጣት የማፍራቱን ተግባር ከፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትግሉ ጋር ልናስኬደቀው ይገባል እላለሁ፡፡
አምላክ ሀገራችንን ይባርክ!

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: