The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ካሳ ከበደና የሻእቢያ ኮሶ (ደምስ በለጠ)

Kassa Kebede

ከጋዘጠኛ ደምስ በለጠ

በቅርቡ ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ ስም ፤ ዋሽንግቶን ዲሲ ውስጥ ቪዥን ኢትዮጵያ የሚባል ድርጅትና ኢሳት/ግንቦት 7 ያዘጋጁት ፤ አንድ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር ። በአጠቃላይ ዋሽንግተን ዲሲንና የአበሻ ፖለቲካ ተዋንያኑን (ኤርትራን ጨምሮ ማለቴ ነው የሃበሻ ስል) የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ፤ ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ የነበሩትን በኢንተርኔት መስኮት ሲመለከት ፤ ዋሽንግቶን ውስጥ ስብሰባ ከተደረገ በፍፁም የማይቀሩ ግለሰቦችን ፤ ጋዜጠኞችን ፤ ጥቂት የግንቦት ሰባት ደጋፊዎችን እና የሻእቢያ የሰሜን አሜሪካ ተወካዮችንና ተራ የሻእቢያ አባላትን በቀላሉ በስም እየለዬ መጥራት ይችላል ።

ውድ አንባቢዎቼ፤ በተለይ የዋሽንግተን ነዋሪ የሆናችሁ ፤ በረጅም ጊዜ ልምድ እንደምታውቁት ፤ ስብሰባ በተጠራበት ቦታ ሁሉ የማይቀሩና ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እጃቸውን እያወጡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ፤ ንግግር ወይም አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችን ታውቋቸዋላችሁ ብየ እገምታለሁ ። እነዚህ ሰዎች የአዘጋጆቹን ፍላጎት፤ በተለያየ መንገድ አስቀድመው ይረዳሉ ። ከዚያም ስብሰባው ላይ እሳተ-ነበልባል የሆነ ንግግር ያደርጋሉ ። የስብሰባውን አዳራሽ ፤ በተለይ የሰብሳቢዎቹ እጅ ፤ እስኪቃጠል ድረስም ያስጨበጭባሉ ። አዘጋጆቹን አስደስተው ፤ ራሳቸውም የሚፈልጉትን ትኩረትና የሚወዱትን ጭብጨባ ጠጥተው ፤ ደስ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ ። ታዲያ ለትግሉ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ፤ ከዚህ ከፍም ዝቅም አይልም ። እንደዚሁ ሁሉ ፤ ሆይ ሆይታ በሞቀበት ፤ ጭብጨባና ከንቱ ውዳሴ በበዛበት ቦታ ፤ ማንም ያዘጋጀው ማ ፤ ጉዳዩን ሳይመዝኑ ፤ አይምሮአቸውን ለተፈላጊው ጉዳይ አዘጋጅተው ፤ ታጥበውና ታጥነው የጠሯቸው የፖለቲካ መድረክ ላይ ሁሉ ፤ የፕሬዚዲየሙን ወንበር ለማሞቅ የሚገኙ ምሁራን ሰዎችንስ አስተውላችኋል ?

በዚህ የሻእቢያና የግንቦት ስብሰባ ላይ ፤ የውጪ እንግዶቹንና አንዳንድ ያልገባቸው ወገኖችን ትቼ ፤ በኔ በኩል ያስተዋልኩት እንዲህ አይነቶቹን ሰዎች ነው። “ቪዥን ኢትዮጵያ” የሚባለው ቡድን ፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ፤ የቶሎ ቶሎ ስም ወጥቶለት ለሻእቢያ ተልእኮ የስጦታ መጠቅለያ ወረቀት ሆኖ የቀረበ ድርጅት ነው። በግንቦትና በኢሳት ፊታውራሪነት ፤ ራሱን እንዲያቀርብ የተዘጋጀው ይህ ድርጅት ውስጥ ፤ በሃገርና በህዝብ ላይ የተሰራውን የሸፍጥ ተግባር ደግሞ ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አይኑን አፍጥጦ አይቶታል ። በተለይ ሻእቢያን ወክሎ የመጣው ግለ-ሰብ እዚያው እፊታቸው፤ “ሻቢያን ለመንካት ያሰበ ቢኖር “ራሽያን ሮሌት” እንደመጫወት ይቆጠራል፤ እወቁት” ብሎችኋል። “እደግመዋለሁ” እያለም ያንኑ አባባሉን ደግሞ ነግሯችኋል። ኢትዮጵያውያን ናችሁና ባዘጋጃችሁት መድረክ ላይ የሻእቢያን መልእክት አገጫችሁን ከፍ አድርጎ ይዞ የሚፈልገውን ሁሉ እንደኮሶ ግቷችሁ ሄዷል። እናንተም የሻእቢያ ፕሮፓጋንዳና ጉድፍ ማስተላለፊያ ቱቦ ሆናችሁ አገልግላችኋል። ህሊናቸሁ ምን እየተደረገባችሁ እንደሆነ ካልገለፀላችሁ ጊዜ ይገልፅላችዋል። ከንቱ ውዳሴና ሙገሳ እንደ ጤዛ ብልጭ ብለው የሚጠፉ ነገሮች ናቸውና።

“… በመንፈሳዊው አለም ሰው የለ ፤ በፖለቲካው አለም ሰው የለ፤ በሽምግልናው አለም ሰው የለ ፤ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የሰው ምድረ-በዳ ሆነች? እያልኩ አወጣለሁ አወርዳለሁ… እንደኔው የሚጨነቁ ሰዎችም ያሉ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ የእግዚአብሄር አገር ነች ፤
ልጆቹዋ ግን ሰይጣን አድሮባቸዋል ።……
ኢትዮጵያ ግን የምታደላላቸው ልጆች የሏትም ፤
የሚያሳዝኗት ግን ሞልተዋል ፤……
ኢትዮጵያ የወላድ አገር ነች ፤
ግን የሰው ምድረ-በዳ ሆናለች።”

የላይኛው ቃልም ሆነ ቅኔ፤ እዚያው ስብሰባው ላይ እንግዳ ከነበሩት መስፍን ወ/ማርያም “የክህደት ቁልቁለት” ከተሰኘው መፅሃፍ የወሰድኩት ነው።

የዛሬው ርእሴ “ቪዥን ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት አይደለም ። ምንም ስላልሆነና ከስጦታ መጠቅለያ ወረቀትነት ባሻገር ህልውና ስለማይኖረው ። እዚያው እነሱ ከኢሳት ጋር የጠሩት ስብሰባ ላይ የጋበዟቸው እንግዳ ናቸው የዛሬው ዋናው ርእሴ። ዶ/ር ካሳ ከበደ። ሳስበው ውዬ ሳስበው ባድር የካሳ ከበደ የኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገትሮ ተከራካሪነት አልገባህ ብሎኝ ከረምኩ።

ዶ/ር ካሳ እኮ የደርጉ ዘመን አንቱ የተባሉ ባለስልጣን ናቸው ። ስጋ ሜዳ በኋላ ላይ ታጠቅ ጦር ሰፈር የተባለውን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለማስገንባት በጊዜው የሃገሪቱ መሪ በነበሩት ፤ በኮለኔል መንግስቱ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰው ናቸው ። የሃገሪቱን አንድነት ከገንጣይና ከሶማሊያ ወራሪ ለመከላከል ፤ በዚሁ በታጠቅ ጦር ሰፈር 3 መቶ ሺህ የኢትዮጵያ የገበሬ ልጅ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶበታል ። ይህ የገበሬ ወታደር ከሶስት ወራት ስልጠና በኋላ ፤ በሰሜንም በምስራቅም ያለክፍያ የሐገሪቱን አንድነት ትጠብቃለህ ተብሎ ተማግዷል ። ለዚህ ለአንድነት የፈሰሰ ደም ፤ በተለይ ደግሞ ከሻእቢያ ጋር እየተዋጋ መስዋእትነት ለከፈለው ህዝባዊ ሚሊሺያ ፤ ካሳ ከበደ ፤ እንደ ደርግ ባለስልጣን ሃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል ። በሰሜን የተደረገው ጦርነት ደግሞ የተካሔደው ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ከመራው ፤ ከሻእቢያ ጦር ጋር ነው ። እንዴት ሆኖ ነው ዛሬ ካሳ ከበደ ፤ ለሻእቢያው ቁንጮ ፤ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራካሪ ሆነው የተገኙት?

ከዚህ ሌላ፤ ካሳ ከበደ በተባበሩት መንግስታት ፅ/ቤት የዚያን ጊዜው መንግስት ፤ ማለትም የደርግ መንግስት የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ፤ አምባሳደር በመሆንም ሰርተዋል ። በጊዜው ኢትዮጵያን በመወከል ፤ የሐገራችንን በጎም ሆነ መልካም ገፅታ የመወከል አደራ ፤ በኢትዮጵያ እና በህዝቧ ተሰጥቷቸው የነበሩ ሰው ናቸው ። (የደርግ ድንቁርና እንዳለ ሆኖ) በተሰጣቸው አገራዊ አደራ የተነሳም ፤ ላገለገሉት መንግስት መርሕ ቆመው መስራት ተገቢ ነበር ። የገንጣዮችን የነሻእቢያን ደባም ፤ አቅማቸው በፈቀደ በማክሸፍ ጥረት ላይ መንግስታቸውን ወክለው ሰርተዋል ብዬ እገምታለሁ ። ታዲያ እንዴት ተደርጎ ነው የዚያ መንግስት ፓርቲና የኢሠፓ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የውጪ ግንኙነት ሃላፊ ፤ ዛሬ ለገንጣዩ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገታሪ ሆነው የተገኙት ?

ወይስ ዶ/ር ካሳ ከበደ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ስርዓት ግፍና በደል ደርሶበታል ብለው አስበው ይሆን ? ከሆነስ የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃነት ፤ በኢሳኢያስ አፈወርቂ በኩል ላመጣው እችላለሁ ብለው ገምተው ነው ? ለኢሳኢያስ አፈወርቂ ሽንጥ ገታሪ ለመሆን የቆረጡት ። እንዴትስ ተደርጎ ቢታሰብ ነው ፤ የገንጣዩ የሻእቢያ መሪ ኢሳኢያ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል አላማ የለውም ተብሎ በኢሳኢያስ አፈወርቂ ተነግሮ ፤ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ፤ በካሳ ከበደ በኩል የሚነገረን ።

በዚህም ብዬ በዚያ ባስበው ፤ ባወጣው ባወርደው ፤ ምክንያቱ በፍፁም አልመጣልህ አለኝ ። በነገራችን ላይ ፤ ካሳ ከበደ ፤ ከወንድምዎ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር በመሩት የመንግስት ስርዓት ውስጥ እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ ደልቶት አልኖረም ። ወንድምዎ ስል ግን ፤ ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታማ የነበረውና በኋላ ላይ “የአጥፍቶ መጥፋት” ደራሲ ፤ የፃፈውን መፅሐፍ ተመርኩዤ እንዳልሆነ በቅድሚያ ይታወቅልኝ ። ዛሬ እትሙን ባላስታውሰውም እርስዎ ራስዎ እዚህ አሜሪካ ከመጡ በኋላ በጦቢያ መፅሄት ላይ ፤ አንድ ቃለ መጠይቅ አድርገው ማንበቤ ግን ትዝ ይለኛል ። በዚያ ቃለ መጠይቅ ላይ ኮለኔል መንግስቱ በስጋ ባይወለዱኝም የርእዮተ-አለም ወንድሜ ናቸው ማለትዎን ግን በደንብ አስታውሳለሁና ነው ።

ስለዚህ ካሳ ከበደ ሆይ ፤ ሰው ምክንያታዊ ነውና እኔም ካሳ ከበደና ኢሳኢያስ አፈወርቂ ምን አገናኛቸው ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ ወደኋላ ተጓዝኩና ፍተሻ ገባሁ ። አቧራ ከለበሱት መረጃዎቼ ውስጥ አንድ ነገር አገኘሁና መልሱ ይህ ይሆን እንዴ ? ስል ጠረጠርኩ ። ጥርጣሬየን እርስዎ ደህና አድርገው ያውቁታል ። ከአንባቢዎቼ ጋር ግን ልካፈለው ወደድኩ ። ምንም ቢሆን ፤ በአንድ ዘመን ላይ የትከናወነ ታሪክ ፤ ምናልባት በጊዜ ምክንያት ይደበዝዝ ይሆናል እንጂ ፤ ጨርሶ ሊጠፋ ግን አይችልም ።

ዶ/ር ካሳ የዛሬን አይድርገውና በስራ ምክንያትም ሆነ በግል በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ፤ መጡ መጡ ተብለው ፤ ተፈርተው ፤ ታፍረው ተከብረው ሁሉም ሰው ሽር ጉድ ይልልዎ እንደነበር አይዘነጋዎትም ። መጨርሻ ላይ ግን ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንዴት አድርገው ነው በዚያው በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ጥለዋቸው የወጡት ?

ቃሬዛውና የሂልተን ሆቴል ብርድ ልብስ !

ከዛሬ ሃያ አራት አመታት በፊት የሆነ ታሪክ ነው ። የመጨረሻውን “ኦፕሬሽን ሰለሞን ” የተሰኘውን ተልእኮ በመሪነት ይወጣ ዘንድ ፤ የእስራኤል መንግስት ፤ ኡሪ ሊብራኒን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ፤ ልዩ ወኪል በማድረግ ሾሞታል ።

“ኦፕሬሽን ሰለሞን” የመጨረሻው ሰአት ላይ ከመድረሱ ሶስት አመታት በፊት ፤ ይላል ስቴፓን ስፔክል ፤ የአሜሪካ አይሁዶች ማሕበር ሰዎች ፤ ጌሊ ኩሊንክና ናትሻፕረን ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሳ ከበደን አግኝተው ሲወያዩ “አንተ ሕልውናህ ከዚህ ከምትሰራው ተልእኮ ጋር የተያያዘ ነው ። የተፈለገው ግብ ላይ እንድንደርስ ከተባበርከን ፤ በአስፈላጊው ሰአት ልንደርስልህ እንደምንችል ፤ እርግጠኛ ሁን ። ብለውት ነበር ።

የእስራኤሉ “ኦፕሬሽን ሰለሞን” ሹመኛም ፤ ስለ ካሳ ከበደ ማንነት የራሱን ግምት የሰጠው እንዲህ በማለት ነበር። “ገና መጀመሪያ ላይ ከካሳ ጋር ፤ እንደተገናኘን ለኔ የሚስማማኝ የራሴ ሰው እንደሆነ አወቅኩኝ። …ለዚህ አለም ኑሮ የተስተካከለ ስብእና ያለው ፤ ነገር ግን ንቁና ተጠራጣሪ ቀበሮ፤ ጨካኝና ግትር መሆኑን ካላወቅህ ይጎዳሃል።” ነበር ያለው ፤ ይላል መፅሐፉ ።

ኡሪ ሉብራኒ የሰጠው አስተያየት እንዳለ ይቀመጥና ፤ ፈላሻዎቹን ከኢትዮጵያ የማውጣቱ ተግባር “በኦፕሬሽን ሰለሞን ዘመቻ” እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት ፤ የመጨርሻው ሰአት ላይ ፤ ኡሪ ሉብራኒ ሁለት መኪናዎች አስከትሎ ፤ የመጨረሻዎቹን ተጓዦች እያሳፈረ የነበረው ሲ 130 ሄርኩለስ አውሮፕላን ውስጥ ሁለት በቃሬዛ ላይ የተኙ ፤ ህሙማንን ለማሳፈር ዝግጅቱን አጠናቀቀ ።እነዚህ በሽተኛ ተጓዦች ከሂልተህ ሆቴል በተወሰደ ብርድ ልብስ ተጠቅልለዋል ።

ህሙማኑ ሲጫኑ ያዩ የሞሳድ አባላት ኡሪ ሉብራኒን ፤ “እነዚህ ሰዎች እንዲህ በጠና ከታመሙ ለምን እናጓጉዛቸዋለን ? ከህመማቸው ሲያገግሙ ቢመጡ አይሻልም ? ብለው ይጠይቁታል ። ማን ያውቃል ፤ ከሞት ተርፈው ፤ እንነሱም በስትሬቸር ወደ እስራኤል ገባን ፤ ብለው ለማውራት ያስችላቸው ብዬ ነው የፈቀድኩት ፤ ሲል ተናገረ ።……….እነዚህ ሁለቱ ከሂልተን ሆቴል በቃሬዛ ብርድ ልብስ ለብሰው የተጓዙት ህሙማን ከኢትዮጵያ ፀጥታ ሃይሎች እይታ እንዲያመልጡ ፤ በስራኤል የፀጥታ ሰራተኞች በጥንቃቄ በተቀነባባረ ዘዴ ፤ ወደአውሮፕላኑ የተሳፈሩት ሰዎች ናቸው ። ኡሪ ሉብራኒ አውሮፕላኑ ህሙማኑን እንደያዘ በፉሪ ተራራ አናት ላይ እያዘገመ ፤ ከአይናቸው እስኪሰወር ሲያዩ ከቆዩ በኋላ አብረውት ለነበሩት ባልደረቦቹ “ ካሳ ከበደ እንደፈለገው በቃሬዛ (ስትሬቸር) ላይ እንደተኛ ወደ እስራኤል ሊገባ ነው” አለ ፤ እየሳቀ ይላል ፤ መፅሐፉ ። እነዚህ በሂልተን ሆቴል ብርድ ልብስ ተጠቅልለው የነበሩት ህሙማን ፤ ካሳ ከበደና የኢትዮጵያ ደህንነት ም/ሚንስትሩ መርሻ ቀፀላ ነበሩ ።

ካሳ ከበደ ስንትና ስንት ጊዜ በክብርና በአጃቢ ከተሸኙበት የቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ፤ እንዲህ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው ነው ከኢትዮጵያ የወጡት ። በሰሜን አቅጣጫ ፤ በእስራኤሎቹ ሄርኩለስ አውሮፕላን ወደ ቴልአቪቭ ሲነጉዱ ፤ ለአንድ ሳምንት ብቻ የቆየው የሃገሪቱ ጊዜያዊ መንግስት አባላት ቤተ-መንግስቱ ካፊቴርያ ውስጥ ካሳ ከበደን ፤ ለስብሰባ እየጠበቋቸው ነበር ። ይህ ከመሁኑ ከአንድ ሳምንት በፊትም ፤ ኮለኔል መንግስቱ በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል ፤ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ዚምቧቡዌ ሸምጥጠው ነበር ።

እዚህ ላይ የፍቅሬ ቶለሳ አንድ ቅኝት ትዝ አለኝ ።

“ሞኝ ዋርካ ሊተክል
ግንዱን ተሸክሞ ያምጣል።
ብልጥ ዋርካውን ኪሱ ከቶ
ፈጠን፤ ቀልጠፍ ብሎ ይራመዳል።”

እንግዲህ ፤ ከላይ ያቀረብኳቸውን መረጃዎች ያገኘሁዋቸው ስቴፓን ስፔክል ከተባለ ደራሲ መፅሓፍ ላይ ነው ። “ ኦፕሬሽን ሰለሞን ያልተነገሩ ምስጢሮች” ይላል የመፅሐፉ ርእስ ። ደራሲው ስቴፓን ስፔክል ፤ በዚህ መፅሃፉ ላይ ፤ ከፈላሻዎቹ ጋር በተያያዘ የነበሩትን ጉዳዮች ፤ ከዋሽንግተን እስከሞስኮ ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ቴልአቪቭ ፤ የነማን እጅ እንዳለበትና እነማን ምን ሚና እንደነበራቸው በሚገባ ገልፆበታል ። ስለዚህም በአሜሪካዊው ኸርማን ኮህንና በእስራኤላዊው ኡሪ ሉብራኒ መካከል በሚደረጉ የንግግር ልውውጦች ፤ ካሳ ከበደን “ዘ ብሮከር ፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ “ኮካኮላ” የሚል የሚስጥር ስምም ሰጥተዋቸው ነበር ። ይህ ቅፅል ስም የወጣላቸው ፤ ካሳ ከበደ ፈላሻዎቹን ከማስለቀቅ ጋር ባላቸው ሚና ፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደግሞ በጥቁረታቸው የተነሳ ከኮካኮላ ቀለም ጋር አያይዘውት ይሆናል ብየ እገምታለሁ ። የፈላሻዎቹ ጉዳይ ፤ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ሻሚር ፤ እስከ ከፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ የደረሰ ጉዳይም ነበር ።

“አሜሪካውያኑም ሆኑ እስራኤሎቹ ፤የካሳ ከበደ መፃኢ እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅና ለጉዳት እንዲጋለጥ አይፈልጉም ። ቦብ ፍሬዘር በጉዳዩ ላይ ሲናገር ‘የኋላ ኋላ የካሳ ከበደ ማረፊያው የተደላደለና ከላባ የተሰራ ምቹ ፍራሽ እንዲሆን ለማድረግ ዝግጁ ነን ብሏል ።’

በጉዳዩ ዙሪያ በአዲስ አበባ ፤ በዋሽንግቶንም ሆነ በቴል አቪቭ ሁሉም የየራሱን የካርታ ጨዋታ መቀመር ይዟል ። የዛሬው ርእሴ መሪ ተዋናይ ዶ/ር ካሳ ከበደም የራሳቸውን ጆከር ካርታ መዝዘዋል ።

ደላላው የጠየቀው ክፍያ ስንት ነው?

ለኢትዮጵያ መንግስት የሚከፈለውን ገንዘብ ካሳ ከበደ ሲደራደሩ ፤ ለራሳቸውም የሚገባውን ድርሻ እንዴት እንዳስቀመጡ ፤ ስቴፓን ስፔክል እንዲህ ሲል ዘግቦታል ።

“አርብ እለት ይላል “ኦፕሬሽን ሰለሞን ያልተነገረው ሚስጥር’ መፅሃፍ ደራሲ ፤ አርብ እለት ፤ ከኡሪ ሉብራኒ ጋር ተገናኝቶ ፤ በገንዘቡ መጠን ዙሪያ የጀመረውን ውይይት በመቀጠል ፤ ፈላሻዎቹን በአየር ትራንስፖርት ለማጓጓዝ ፤ የሚያስፈልገውን ዋጋ በማውጣት በአጠቃላይ 60 ሚሊዎን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግስት እንደፋይናንስ ድጋፍ እንዲከፈልና ለራሱም የልፋቱ ዋጋ እንዲታከልለት ካሳ ከበደ ጥያቄ አቀረበ ።” ይላል ።

አዎ፤ የካሳ ከበደ ጆከር ካርታ፤ የልፋታቸውን ዋጋ ከእስራኤላውያኑ መጠየቅ ነበር ። ከአመታት በፊት ለሌላ ተልእኮ ወደአሜሪካ ጎራ ብለው የነበሩት ካሳ ከበደ “American “Association for Ethiopian Jews” ከሚባል ድርጅት ጋር ግንኑነት አድርገው ፤ ለልፋታቸው ዋጋ ጠይቀው ፤ ቃል ተገብቶላቸው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ፤ እንደ እስቴፓን ስፔክል መፅሃፍ ። ለመሆኑ ካሳ ከበደ ፈላሻ የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ፤ የልፋታቸው ዋጋ ስንት ነበር ?

መፅሐፉ የገንዘቡን መጠን ፍንጭ ሲሰጥ …….. “የአይሁድ አጀንሲው ፕሬዚደንትም ሆኑ ገንዘብ ያዡ ፤ የቀረበውን የክፍያ መጠን ግዙፍነት ቢሰሙ ፤ ብዙ የተገፋበትን ጥረት በድንጋጤ ፤ ወደ ቀድሞው ስፍራው ሊመልሱት ይችላሉ ።” ካለ በኋላ ፤ በመቀጠል ፤ “በተለይ ካሳ ከበደ ጉዳዩን እንዲያቀላጠፍና እንዲያሳካ ላደረገበት $3.4 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ለመክፈል እንደተስማሙ ቢሰሙ ፤ በጉዳዩ ላይ የሚያደርጉት መንቀርፈፍና የሚፈጥሩት ማነቆ ፤ ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት ፤ ለጊዜው ዩሪ ሊብራኒ ፤ በጉዳዩ ላይ ከነሱ ጋር አለመነጋገርን መረጠ” ይላል ።

በመጨረሻም ! መርጃዎቼን ካገኝሁበት ከስቴፓን ስፔክል መፅሐፍ ላይ የሚቀጥለውን ርእስ ልዋስ ነው።

ካሳ ከበደ “የመክፈቻ ቁልፍ” መሆኑ አብቅቷል።

ዶ/ር ካሳ ከበደ፤

1ኛ) የኢትዮጵያን ህዝብ ፤ በቀውጢው ሰአት ፤ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት እርስዎ ፤ በብርድ ልብስ ተጠቅልለው ፤ ሜዳ ላይ ጥለውት ነው እኮ እንደ ኮለኔል መንግስቱ የፈረጠጡት።

2ኛ) ከስጋ ሜዳው ማሰልጠኛ ወጥተው በኤርትራ በረሃና ተራሮች ላይ ፤ የትም ወድቀው የቀሩት ኢትዮጵያውያን የገበሬ ልጆች ደም እኮ ፤ እስካሁን ድረስ አልደረቀም።

3ኛ) ፈላሻዎቹን ኢትዮጵያውያን ወደሌላ አገር ለማስተላለፍ ፤ የልፋቴ ዋጋ ይከፈለኝ ብለው ዋጋ የጠየቁ ሰው ነዎት እንደ መፅሃፉ መረጃ።

አሁን ምን ተገኝቶ ነው ኢሳኢያስ አፈወርቂ በኔ ይሁንብህ ካሳ ! እኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እቅድ የለኝም ብሎ ለእርስዎ የሚነግርዎ ? እሺ ፤ እርስዎ እንዳሉት ፤ ነገረዎ ብለን እንውሰድልዎ ። ከስቴፓን ስፔክል መረጃ ተነስተን ፤ ያለፉትን ሁኔታዎች ሁሉ ስንገመግም ፤ እርስዎ ዛሬ ማን ስለሆኑ ነው የእርስዎን ቃል የምናምነው ? ወይስ ገንጣዩ ኢሳኢያስ አፈወርቂ ፤ ለእርስዎ ከነገረዎት ቃል ጀርባ ፤ እንደ መጨረሻዋ ሰአት ሁሉ ፤ አንድ የተደበቀ ነገር አለ ?

ዶ/ር ካሳ ከበደ ፤ መቼም ኢሳኢያስ አፈወርቂ ገንዘብ ከፍሎዎታል ብዬም አልጠረጥርም ፤ ለራሱም በአረቦች ድጎማ የቆመ ፤ መናጢ ድኻ መንግስት ነውና ። ኢሳኢያስን በከንቱ ውዳሴ መደለል ፈልገው ከሆነ ደግሞ ፤ እሱ መንግስቱ ኃ/ማርያም አይደለምና አይሸነግሉትም ። እርሱ ራሱ ከልጅነቱ ጀምሮ በዚህ ተግባር ጥርሱን ነቅሎ አድጎበታል ።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ፤ ዶ/ር ካሳ ከበደ የእርስዎ መክፈቻ ቁልፍነት አክትሟል ። የሚያመጡት ለውጥም የለም ። እውነትም ይሁን ሐሰት የተናገሩት ሁሉ የሚደመጥበት ፤ ያዘዙት ሁሉ የሚፈፀምበት ፤ የረገጡት መሬት የሚንቀጠቀጥበት ፤ ዘመን “Gone with the wind” ። የኮለኔል መንግስቱ ፀኃይ የጠለቀች ጊዜ የርስዎም አብራ ጠልቃለች ።

በተረፈ ቸር ይግጠመን እላለሁ ።
በዚህ አጋጣሚም ፤ ለነፃነት ዘለቀ ሰላምታዬን ያቅርቡልኝ አደራ ።

በፅሁፉ ላይ አስተያየትም ሆነ ትችት ካላችሁ እነሆ ኢሜል አድራሻዬ anbesawyibra@gmail.com

ላስ ቬጋስ ኒቫዳ

 

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: