The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

“ለሌሎች ዜጎች የተሰጠ ይቅርታ ለእኔ ባለቤት ጋዜጠኛ ውብሸት ለምን ይከለከላል እያልኩ ሁሌም እብሰለሰላለሁ” የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ

በሰኔ 2003 ዓ.ም በእነ ኤሊያስ ክፍሌ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው አቶ ኤሊያስ ክፍሌ፣ ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ፣ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚዓብሔር፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ መከሰሳቸው ይታወሳል። ከዚህ የፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ አስራ አራት ዓመት በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነባቸው መሆኑ ይታወቃል። … በዚህ መዝገብ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱን ሳይጠቀም የተሰጠው ፍርድ እንደፀና በእስር ቤት ይገኛል። ውብሸት በጊዜው በአገር ሽማግሌዎች በኩል ይግባኝ ከምትጠይቅ የተወሰነብህን ውሳኔ ተቀብለህ መንግስትን ይቅርታ መጠየቁ ይሻላል የሚል ምክር መለገሱን ያነሳል። የተሰጠውን ምክር በመቀበል፣ ለመንግስት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል የይቅርታ ደብዳቤ ቢያስገባም፣ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም። የይቅርታ ደብዳቤውን ምላሽ እየጠበቀ ባለበት ወቅትም መጠየቂያው ጊዜ መቃጠሉን ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች አስታውሰዋል።

በአገር ቤት የሚታተሜው ሰንደቅ ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት  ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። ይህ ጠቃሚ እና ወቅታዊ መረጃ በመሆኑ በኢ.ኤም.ኤፍ በኩል ለህትመት አብቅተነዋል።

ሰንደቅ፡- አሁን አንቺና ልጅሽ ያላችሁበት ሁኔታ እንዴት ነው?

ብርሃኔ፡- ውብሸት ከታሰረ አራት ዓመት ሆኖታል። እንደአባወራ እንደቤት አስተዳዳሪ እኔ ልጄ ከተለየነውም አራት አመት ሆነን። በተለይ ልጄ ውብሸት ሲታሰር የሁለት ዓመት ልጅ ስለነበረ ከአባት የሚያገኘውን ድጋፍና ፍቅር ለማግኘት አልታደለም። እንደማንኛውም አባት ትምህርት ቤት እንዲወስደው፣ እንዲያመጣው ይፈልጋል። አባት ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘው በትምህርት ቤት መግቢያና መውጫ ሰዓት ሲመለከት በአትኩሮት ነው። አንዳንዴ ከእኔን እጅ እጁን አስለቅቆ ይፈዛል እየተጠማዘዘ አባትና ልጅ አብረው ከት/ቤት ሲወጡ ሲገቡ ያያል። እንደትልቅ ሰው የውስጥ ስሜቱን አውጥቶ ማስረዳት ቢያቅተውም ምን እያሰላሰለ እንደሆነ ግን ይገባሃል። አባቴ ቢኖር እኔንም ወደ ት/ቤት ይወስደኛል፣ ያመጣኛል እያለ እንደሆነ ትረዳለህ። በተለይ እኔ ያጣውንም ነገር ስለምረዳው ምንም ማድረግ ባለመቻሌ ደግሞ ይከፋኛል።

ሰንደቅ፡- ውብሸት ጋር ያለው ስሜትስ ምን ይመስላል? በቅርብ ካየሽው ምን ያህል ጊዜ ሆነሽ?ብርሃኔ ተስፋዬ የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት

ብርሃኔ፡- ውብሸት ያለው ስሜት ጠንካራ ቢሆንም ያሳዝንሃል። ቤተሰቦቹ እንዳይጎበኙት በጣም በእድሜ የገፉ ናቸው። የሚኖሩበት አካባቢ ከአዲስ አበባ በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ይርቃል። ከታሰረ ጀምሮ አይተውት አያውቁም። አባትየው ውብሸት በእስር ቤት ውስጥ እያለ ሳያዩት ነው ያረፉት። እናቱም በእድሜ የገፉ በመሆናቸው ሄደው ሊጠይቁት አልቻሉም። ይህን ሁሉ ችሎ፣ ልጁ መናፈቅ፣ ስለልጁ ማሰብ ሌላው ፈተናው ነው። አንድአባወራ በቤቱ ሳይኖር የሚያጎለውን ስለሚረዳ ምን እንደጎደለብንም ሰለሚያውቅ፣ እኔ እና ልጄ እንዴት ብለን ኑሮን እንደምንገፋ ሲያስብ በጣም ይጨነቃል።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት ለፍትህ ሚኒስቴር የይቅርታ ደብዳቤ ማቅረቡ ይታወሳል። ይህ ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ብርሃኔ፡- ለፍትህ ሚኒስቴር ያቀረበው የይቅርታ ደብዳቤው ተቀባይነት አላገኘም የሚል ድፍን የሆነ ምላሽ ተሰጥቶት ነበር። በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ እና በአትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ ለሚመራው የሀገር ሽማግሌዎች ጥምረት ያስገባው የይቅርታ ጥያቄ ገና በሂደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው።

ሰንደቅ፡- በይቅርታው ሂደት ላይ ያለሽ መረዳት እንዴት ነው?

ብርሃኔ፡- በመጀመሪያ ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው የተሰጠው ፍርድ ምንም ይሁን ምንም ውሳኔውን በሕግ የበላይነት የተቀበለ ነው። በፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ተቀብሎ፣ መንግስትን ነው ይቅርታ የጠየቀው። መንግስት ታራሚዎች ይቅርታ ሲጠይቁ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት። ሰው የሚታሰረው ለቅጣት ሳይሆን ሰርቷል ከተባለው ጥፋት እንዲማር ነው። ስለዚህም ይቅርታ ይደረግልኝ ብሎ መንግስትን መጠየቅ፣ ጠያቂው ለመማር ዝግጁ ነው ማለት ነው። ውብሸትም ሰርቷል ተብሎ ከተነገረው ስህተት እማራለሁ ብሎ ይቅርታ ከጠየቀ መንግስት የይቅርታ ደብዳቤውን ለምን ሊቀበለው እንዳልፈለገ ለእኔ ግልጽ አይደለም።

በተለይ ከሽብር ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች ይቅርታ አይሰጣቸውም የሚል ነገር ከተለያዩ ቦታዎች ሰምቻለሁ። መቼም መገናኛ ብዙሃን ለሚከታተል ሰው በሽብር የተወነጀሉም ሆነ በሽብር ፍርድ ተሰጥቷቸው ታስረው የነበሩ ታራሚዎች በአደባባይ ይቅርታ ተደርጓላቸው ከማረሚያ ቤት ሲወጡ እኔም ሌላውም ሕዝብ ሰምተናል፣ አይተናል። ለሌሎች ዜጎች የተሰጠ ይቅርታ ለእኔ ባለቤት ጋዜጠኛ ውብሸት ለምን ይከለከላል እያልኩ ሁሌም እብሰለሰላለሁ።

መቼም መንግስት ለሁሉም ቤተሰብ እኩል ነው ብዬ አምናለሁ። ሆኖም ለእኔ እና ለልጄ መንግስት የይቅርታ እጁን ለምን እንደነፈገን ግን አይገባንም። ውብሸትስ ምን የተለየ ሰራ ሰርቷል? የይቅርታ ጥያቄው ከቀረበ ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ወስዷል፣ ሌሎች በተመሳሳይ ክስ የፍርድ ውሳኔ አግኝተው፣ ይቅርታ የተሰጣቸው ጊዜን ስትመለከተው እጅግ ፈጣን ነው። ለምን ይቅርታ በፍጥነት አገኙ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን፣ በአንድ ስርዓት ውስጥ ሁለት አሰራር ስለሆነብኝ ነው።

ሰንደቅ፡- በሽማግሌዎቹ በኩል ስለየተደረጉ ጥረቶች የምታውቂው ነገር አለ?

ብርሃኔ፡- ከእነሱ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ቀጠሮ እየጠበቁ መሆናቸውን አውቃለሁ። በቅርብ ጊዜም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ያላቸውን ተስፋ ነግረውናል።

ሰንደቅ፡- ወደግል ሕይወትሽ እንመለስና አራት አመት ብዙ ጊዜ ነው። ከልጅሽ ጋር በምን ገቢ ነው የምትተዳደሩት?

ብርሃኔ፡- እስከተወሰነ ጊዜ ሁለት ዓለም ዓቀፍ ሽልማቶች ያገኘ በመሆኑ ከሽልማቱ ባገኘነው ገንዘብ ነበር የምንተዳደረው። እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ያግዙናል። እንዲሁም የሙያ ጓደኞቹ ያግዙናል፣ የእሱንም የጤና ሁኔታዎች ይከታተላሉ። አሁን ላይ ግን ነገሮች ሁሉ ከብደውናል።

Ethiopian Journalist arrested

Ethiopian Journalist arrested

ሰንደቅ፡- መንግስት ምን እንዲያደርግልሽ ነው የምትፈለጊው?

ብርሃኔ፡- በነበረው የፍርድ ሂደትም ሆነ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ምንም ማለት አልፈልግም። ባቀረበው የይቅርታ ደብዳቤ ላይ እንዳሰፈረው፣ ቤተሰቡን ለማስተዳደር እና ልጁን ለማስተማርና ጥሩ ዜጋ ለማድረግ መንግስት በይቅርታ እንዲፈታው ጠይቋል። እኔም በበኩሌ ባለቤቴ ጋዜጠኛ ውብሸትን መንግስት በይቅርታ እንዲፈታውና ልጄም ወደተረጋጋ ስነልቦና እንዲመለስ፣ ቤተሰባችንም ወደነበረበት የተረጋጋ ሕይወት እንድንመለስ እጠይቃለሁ።

EMF

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: