The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የምሥራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ተረጂዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል – ሪፖርተር

የአዘጋጁ አስተያየት፡

በራሱ የፖለቲካ ጥቅም ታውሮ ሕወሃት/ኢሕአዴግ የሃስት ነጋሪት ሲጎስም፣ ቃል አቀባያቸው ጌታቸው ረዳ በፉከራና ድንፋ ድርቁ “ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ አይደለም” በማለት ኅዳር 1፣ 2015 በጋዜጣዊ መግለጫቸው ቢያሰሙም፡ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ላይ የደረሰውን አደጋ መንግሥታቸው ሊገታው አለመቻሉን ዕርዳታ የሚፈልገውና የሚጠብቀው ሕዝብ በግልጽ አሳይቷል!

የኢትዮጵያ ሕዝብና ሕውሃት በደንብ ስለተዋወቁ፣ ለዚህ ነው ሕዝቡ የሕወሃትን ፕሮፓጋንዳ ባለማመን በድርቁ ግንባር ቀድም ተጎጂው ሕዝባችን ይጎዳል በማለት ለግንባሩ አመራርና ቅጥረኛ ፖለቲከኞች ጆሮውን ባለመሥጠት ሕዝባችን ለረሃብ ተጋልጧል በማለት ዘመቻውን እያፋፋመ ያለው! የሚቀለው ግን ተማምነን በግልጽነት ችግሩን እንደ አንድ ሕዝብ መጋፈጥ ነበር!

ይህ ሳይሆን በመቅረቱ ግን፣ ረሃብተኛው ሕዝብ በወር 15 ኪሎ ስንዴና አንድ ሊትር ዘይት እየተሰጠ ነፍሳችሁን በእጃችሁ ያዙ እየተባሉ ናቸው። ነገር ግን በጥጋብ አነጋገር አቶ ጌታችው ረዳ፣ “መንግሥት ለረሃብተኛው ሕዝብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በአለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሰው ማግኘት ያለበትንየካሎሪ መጠን ማግኘታቸውን ሳይቀር እየተከታተለም ነው” ማለታቸው ልባችን እንደነርሱ በጭካኔ ባለመደንደኑ፡ አባባላቸው እርግጠኛ ነን ተጎጂውን ሕዝብና ሌሎቹንም ኢትዮጵያውያን እጅግ የሚያሳዝን ነው!

መጭው የድርቅ ሁኔታ ለሃገራችን እጅግ አስጊና አስፈሪ ነው። ሰብዓዊነት የሚባል ነገር በሕወሃት ዘንድ የሚታወቅ ክሆነ፣ ለከት የለሽ ፕሮፓጋንዳቸውን፣ ቆርጦ ቀጥልነትንና ዘረኝነታቸውን ለጊዜው ጋብ አድርገው፡ በተጎዳው ሕዝብ ችግሮች ላይ ቢያተኩሩ፡ ምናልባትም የችግሩን አስከፊነት ባልተራዘመ ጊዜ ለመቋቋም ይቻላል። የድርጅቱ ችግር ግን አሁንም ቀና ብሎ ከሃገሪቱ ፊት የተጋረጠውን ርሃብና ችግር መጠን ለመለካት አለመቻል መሆኑን ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ ምክር ቤቱ ኅዳር 2 እና 3 ባደረጋቸው ስብሰባዎቹ 300 ሚሊዮን ኩንታል እህል በ2015/16 እንደሚመረት መወሰኑ ነው!

እንደ ድርቁ ስፋትና እንደ ገበሬው ችግሮች ከሆነ፡ የዚያ ግማሽ ከተገኘ ሕወሃት በቅጥፈቱ ሊቀጥል ይችላል!

አሁን ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ – መ/ቤታቸው ብዙ ጥረቶች ማድረጉ ቢታወቅም – “ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ ክትባት መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶች እንዲሁም ህፃናቶችን የመለየት ስራ[ስለ] መሰራቱ” ዛሬ – ድርቁ ከተተነበየ ከአሥር ወራት በኋላ – ይህንን መናገራቸው እጅግ ያሳስበናል! ‘ክመለየት አልፎ’ መ/ቤታቸው በአሁኑ ወቅት በሁሉም አካባቢዎች ብዙ ለመሥራት በቻለ ነበር!

ሰለ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህንን ስንል፣ የገንዘብና የባለሙያ ዕጥረትን ሳናስብ ቀርተን አይድለም! ነገር ግን ጤና ጥበቃ ብዙ የውጭ ዕርዳታ ሲፈስለት የኖረ መ/ቤት ነው፣ ምንም እንድኳ በዘመነ ዶ/ር ቴድሮስ ገሚሱ ገንዘብ የሕወሃትን የፕሮፓጋንዳ አውታሮች ፋናንና ዋልታን ለማጠናከር ውሏል። ዛሬ የመንግሥት ከሚባሉት የዜና ማሠራጫዎች ይልቅ፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከመጣው ዕርዳታ እየተሸረፈ የተገነቡት የሕወሃቶቹ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች እጅግ ዘመናዊ እንዲሆኑና የኢትዮጵያ ሕዝብ በፕሮፓጋንዳ እንዲታፈን ረድቷል – ምንም እንኳ ለሕወሃቶች ተአማኒነት ባያተርፍላቸውም!

አሁንም ያለውን ጊዜ በሚገባ ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማዋል እንዲቻል፡ በኛ በኩል የምንመክረው ፖለቲከኞች ይህንን ችግር በትኩረት ተከታተሉት! አክሙት! ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ እናንተ ተጠቃሚዎች ናችሁና!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ከኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ እያሳረፈ ያለው ተፅዕኖ እየሰፋ መምጣት የተረጂዎችን ቁጥር እንዲጨምር እያደረገ ነው፡፡

ሰሞኑን በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመቃኘት የተንቀሳቀሰው የጋዜጠኞች ቡድን ከተመለከታቸው አካባቢዎች መካከል፣ የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ ከወራት በፊት የነበሩት ተረጂዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃረን አልዪ እንደገለጹት፣ እስካሁን¬ 549,000 ተረጂዎች ተለይተው ዕርዳታ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድርቁ አሁንም ለውጥ ሳያሳይ በመቀጠሉ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ብቻ ከ320 ሺሕ በላይ ተጨማሪ ተረጂዎች የመንግሥትን ዕርዳታ የሚሹ በመሆናቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር 900 ሺሕ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ለእነዚህ ተረጂዎች የሚሆን ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ የተጠየቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞንም በተመሳሳይ በድርቅ የተጎዱ ተረጂዎች ቁጥር እንደጨመረ፣ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ቶፊቅ ገለጻ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ሲሰጣቸው የነበሩት ከ500 ሺሕ በላይ ተረጂዎች ነበሩ፡፡ በጥር ወር ግን የተረጂዎች ቁጥር ከ720 ሺሕ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሁለቱም ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች የተረጂዎቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ በሁለቱም ዞኖች እስካሁን ዕርዳታ ሲሰጣቸው የነበሩት የባሰ ችግር የነበረባቸው ናቸው፡፡ ድርቁ እየተራዘመ በመምጣቱ ግን የተሻሉ ናቸው የተባሉትንም ጭምር ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳም ባለፈው ዓመት 14,404 የነበሩ ተረጂዎች ቁጥራቸው ከ51 ሺሕ በላይ ሆኗል፡፡

እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ በ2007 የምርት ዘመን ይገኛል ተብሎ የታቀደው 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነበር፡፡ በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ግን ሊገኝ የሚችለው ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል ያነሰ ነው፡፡ በምዕራብ ሐረርጌም የሚጠበቀው ምርት ቀድሞ ከተገመተው በእጅጉ ያነሰ እንደሚሆን ታምኗል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ከሆኑ ወረዳዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሳርቱ ሙክታር እንደሚሉት፣ መንግሥት ዕርዳታ እየሰጣቸው ቢሆንም ዕርዳታው በቂ አይደለም፡፡ በአንድ ቤተሰብ 15 ኪሎ ስንዴ እየተሰጣቸው መሆኑንና ሦስት ጊዜ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከስንዴው ጋርም አንድ ሊትር ዘይት ቢሰጣቸውም ይህ ግን በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ የውኃ ችግሩ ግን እጅግ የከፋ መሆኑን የሚገልጹት የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪዎች፣ በአጋጣሚ በዘነበው ዝናብ በአንድ ኩሬ ላይ የተጠራቀመ ውኃ ለከብቶቻቸውም ለራሳቸውም ይጠቀሙበታል፡፡

ቀድሞ ለመጠጥ ይጠቀሙበት የነበረው ኩሬ በመድረቁ መንግሥት በቦቴ የሚያመጣውና የሚያሠራጨው ውኃ የማይዳረስ ስለሆነ፣ አንዳንድ ነጋዴዎች አምጥተው የሚሸጡትን አንድ ሊትር ውኃ በአንድ ብር እየገዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሃሮን አሊዪ እንደሚሉትም በአካባቢው ያለው የውኃ እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ካለው ሁኔታ አንፃር በዞኑ የከፋ ችግር ላለባቸው ወረዳዎች 30 የውኃ ማመላለሻ ቦቴዎች እንደሚያስፈልጉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹17ቱን አግኝተን በእነዚሁ ቦቴዎች እያከፋፈልን ነው፡፡ የጠየቅናቸው የውኃ ቦቴዎች ከመጡ የውኃ ሥርጭቱ መጠን ይጨምራል፤›› ይላሉ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያገኛቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም በምሥራቅ ሐረርጌ በድርቅ የተጎዱ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የሚደረግላቸው ዕርዳታ በቂ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ያለመሆኑን ነው፡፡ የሚሰጣቸው ዕርዳታ ባለመኖሩም አንዳንዶቹ ወደ ጂቡቲና ወደተለያዩ አካባቢዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደነ አቶ ዓሊ ኢንድሪስ ያሉት ደግሞ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ፕሮጀክት ላይ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው በቀን 30 ብር እየተከፈላቸው ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ከዚህ ሲብስም በደህናው ጊዜ ያደለቧቸውን ከብቶች እየሸጡ ነው፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎችም ከብቶቻቸው በድርቁ ምክንያት ስለተጎዱና ከችግር ለማምለጥ ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲያወጧቸው ዋጋ እየወደቀባቸው መቸገራቸውን፣ ሲብስም ቀድሞ እስከ 20 ሺሕ ብር ይሸጡ የነበሩትን ከብት ከአምስት ሺሕ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

በዚህ ወረዳ ከ77 ሺሕ በላይ ከብቶች አስቸኳይ የመኖ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢገልጹም፣ እስካሁን ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሂር ፊኒኖ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በቶሎ መኖውን ካላቀረበላቸውም በከብቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

አቶ አብደላ መሐመድ የሚኤሶ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ያለው ድርቅ የከፋ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕርዳታ ካላገኙም ችግር ውስጥ የሚወድቁ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ችግሩ ለከብቶቻቸው ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ እስካሁን በ2007 የምርት ዘመን ፍሬ ያላፈራውን የበቆሎና የማሽላ አገዳ እየመገቡ ያቆዩዋቸው ቢሆንም፣ ከብቶቻቸው አሁን ምንም መኖ የላቸውም፡፡

አቶ አብደላ ያሏቸውን ከብቶች ከሚኖሩበት መንደር ውኃ ወዳለበት አካባቢ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2007 የምርት ዘመን የዘሩት በቆሎና ማሽላ ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ፣ በእጃቸው የቀሩትን ከብቶች በአነስተኛ ትንሽ ኩሬ ውኃ እያጠጡ ከኩሬ ዳር ማደርና መዋል ከጀመሩ ሦስት ቀናት አልፏቸዋል፡፡

ይህችም ኩሬ ብትሆን ከአንድ ሳምንት በላይ የሚቆይ ውኃ የሌላት መሆኑን የገለጹት አቶ አብደላ፣ ሦስት ልጆቻቸውን ጥለው እሳቸው ከብቶቻቸውን ለማዳን ሲወስኑ ከከብቶቻቸው ሦስቱን ሸጠው ለቀለብ የሚሆን ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በመተው ነው፡፡

እንደ አቶ አብደላ ገለጻ እስካሁን አምስት ከብቶቻቸውን አርደዋል፡፡ ከሚሞቱ ብለው የወሰዱት ይህ ዕርምጃ በቀሪዎቹ ከብቶቻቸው ላይ እንዳይደርስም የቻሉትን ያህል ውኃ ወዳለበት መጓዝ ግዴታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ትልቁ ችግር ውኃ ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ሰዎችም ሆኑ ከብቶች ውኃ ለማግኘት በእጅጉ ተቸግረዋል፡፡ ድርቁ ያስከተለው ጉዳት ከዚህም በኋላ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዚህችው አነስተኛ ኩሬ ዳርቻ ሪፖርተር ያገኛቸው ሌላው አርሶ አደር እየደረሰ ያለውን ጉዳት በማየት ዕርዳታ ያልተደረገላቸው መሆኑን በሐዘኔታ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው የሚመጡት የመንግሥት ኃላፊዎች ችግሩን ሰምተው ይሄዳሉ እንጂ ዕርዳታ እያደረጉልን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የልጆቻችን ሰውነት ቀንሷል፡፡ ከትምህርት ቤትም እየቀሩብን ነው፤›› የሚሉት እኚሁ አርሶ አደር፣ ለውኃ ችግር መፍትሔ ካልመጣ አካባቢውን ለቆ መሄድ ግድ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የፈጣሪ ጉዳይ ስለሆነ ከዘራነው አላገኘንም፡፡ ከፈጣሪ በታች ያለን መንግሥት ነውና ዕርዱን ብለናል፤›› ያሉት አርሶ አደሩ፣ አሁንም ይህ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ይማፀናሉ፡፡

በሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ዕርዳታ እየተሰጣቸው አለመሆኑን ቢገልጹም፣ የሚኤሶ ወረዳና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ኃላፊዎች ዕርዳታ እየተሰጠ ነው ይላሉ፡፡

የሚኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ከማል፣ ‹‹በአጋጣሚ ያነጋገርናቸው በወረዳው ሊረዱ ይገባል ተብለው ከተያዙት ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ፤›› በማለት የአልተረዳንም ጥያቄ ለሚያነሱት አርሶ አደሮች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ የተሻሉ ናቸው የተባሉትም ዕርዳታ የሚሹ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ዕርዳታ ሊሰጣቸው ይገባል ከሚባሉት ውስጥ ይካተታሉ ብለዋል፡፡

ከዕርዳታ ሥርጭት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ ዕርዳታ እየተሰጠ አለመሆኑን ሲገልጹም ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ያላካተተ አሠራር እንዳለ ያመለክታሉ፡፡

የዕርዳታ አሰጣጡ ፍትሐዊ ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉም የሚናገሩ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ግን የዕርዳታ አሰጣጡ በግልጽነት የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ችግር ቢፈጠር ወዲያው ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር ተዘርግቷል ይላሉ፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር እንደገለጸው ለቁጥጥር ከአስተዳደር፣ ከዓቃቤ ሕግና ከሕዝብ አደረጃጀት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኤሶ ወረዳ ዲርባ ቀበሌ ደግሞ ከዕርዳታ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የቀበሌው የሥራ ኃላፊና የጎጥ አመራሮች እንዲታሰሩ መደረጉን፣ የወረዳው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የቀበሌው ሊቀመንበርና የጎጥ አመራሮች የታሰሩት በዕርዳታ ዕደላው ወቅት የአንዳንዱን ቤተሰብ ቁጥር በማሳነሳቸው፣ የአንዳንዶቹን ደግሞ ቁጥራቸውን በመጨመር የተሻለ መጠን ያለው ዕርዳታ እንዲሰጣቸው በማድረጋቸው ነው፡፡

ወረዳው ይህንን መረጃ በሕዝብ ጥቆማ ካገኘ በኋላ ባደረገው ማጣራት፣ ድርጊቱ መፈጸሙ በመረጋጡ ዕርምጃው ለመውሰድ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በሁለቱም ዞኖች ያለው የከፋ ድርቅ በሰው ሕይወት ላይ ሞት አላስከተለም ተብሏል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ብቻ እስካሁን ከ2,200 በላይ ከብቶች መሞታቸውን የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ድርቁ ባስከተለው ችግር የተሰደዱ አሉ የሚባለውን ያስተባበሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ በዚህ አካባቢ ያለ ነዋሪ ወደ ጂቡቲ መሄድና መምጣት የተለመደ በመሆኑ በድርቁ የተሰደዱ ናቸው ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ እንዳይሰደዱ በቂ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንፈልግም ብለው የሚሄዱ አሉ፤›› ብለዋል፡፡ በወረዳቸው ደረጃ የበለጠ ዕርዳታ የሚያስፈልገው ተረጂ ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ ስለሚጨምር ለዚህ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በሁለቱም ዞኖች መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በፈቃዳቸው አዋጥተው ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መጠባበቂያ ፈንድ ውስጥ ተይዟል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት ተከታታይ ዕርዳታዎችን እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት አስታውቀዋል፡፡

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: