The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ክፉ ቀንና መንስኤው ወያኔ!

ክፉ ቀንና መንስኤው ወያኔ!

ethiopian-famaine-998x1024

ከሰዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን

“ክፉ ቀን” የሚለው ሥያሜ ሀገራችን ካየቻቸው አስከፊና ሕዝብ ያለቀባቸው ረሀቦች ዋነኛው እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሚገርመው ይህ በአስከፊነቱ የሚታወቀውና ሕዝብን በተለይም እንስሳትን ምጥጥ አድርጎ የፈጀው ረሀብ ግን የተከሰተው በድርቅ ወይም በአየር መዛባት ምክንያት አልነበረም፡፡

ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ ሲያስብ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካና እስያ በቀላል ግጭት ቅኝ ሀገር መያዝ እንደቻሉ ሁሉ በኢትዮጵያ ይህ መልካም ዕድል እንደማያጋጥመው ጠንቅቆ ዓውቆት ስለነበር ሐበሻን ለማንበርከክ ጦርነት መግጠሙ የማይቀር ከሆነ አስቀድሞ የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አቅም ለማዳከም የሚያስችል ስልት መንደፍና መተግበር እንዳለበት አምኖ አቅድ ነደፈ፡፡ አንዱና ዋነኛውም የሀገሪቱ ሀብት የሕዝቡ አቅም መሠረት የሆነውን ግብርናዋን ማሽመድመድ አከርካሪውን መስበር ነበር፡፡
ይህንን ሲያስብ ግብርናዋን ለመጉዳት ማድረግ ያለበት ነገር ሆኖ ያገኘው የከብት ሀብቷን መጨረስ ነበር፡፡ ይህንን ለመፈጸም ሲል ከህንድ ሀገር ሦስት የታመሙ ከብቶችን በምጽዋ በኩል አስገብቶ ከደማቸው እየወጉ የኞቹን ደኅናዎቹን ከብቶች ወጓቸው በሽታውም በአጭር ጊዜ ተዛምቶ ከኢትዮጵያም አልፎ ታንዛቲያ ድረስ ወርዶ አጠቃላይ የቀጠናውን ከብት ፈጀው፡፡ ውጤቱም ፋሽስቶቹ ከጠበቁት እጅግ የበዛ ሆኖ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ “ክፉ ቀን” በመባል የሚታወቀውን ረሀብና ችጋር አመጣ፡፡ ሕዝቡ የሚያርስበትና ሌሎች የግብርና ሥራውን የሚከውንበት ከብት በማጣቱ ግብርናው ተስተጓጉሎ የሚላስ የሚቀመስ በመጥፋቱ እንደ ቅጠል እረገፈ የሀገሪቱ አቅም ተሽመደመደ፡፡
ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጅ በዚህ “ክፉ ቀን” በመባል በሚታወቀው የረሀብ ዘመን ከረሀቡ ክብደት የተነሣ ወደ ሰላሌ አካባቢ ልጇን የበላች እንደነበረች የሚናገሩ አሉ፡፡ ማንና የት እንደሆነች የሚጠቀስ ነገር ግን የለም፡፡ እንዲህ ብለው የሚያወሩ ሰዎችን ቀርቤ ለመረዳት በጠየኩ ጊዜም ከወሬ በዘለለ ተጨባጭ የሆነ ነገር ሊነግረኝ የቻለ ሰው አላገኘሁም፡፡ ይሄንን ነገር በመጻሕፍቶቻቸው ሳይቀር ያስቀመጡ አሉ አሁንም ግን ተጨባጭ አይደለም፡፡ እንዲያው ዝም ብለው ሁሉንም ነገራችንን ማንነታችንን ከአይሁዶች ጋራ ማመሳሰል የተጠናወታቸው ሰዎች በረሀብ ጊዜ ልጅን በመብላትም እኛን ከአይሁድ ጋር ለማመሳሰል የፈጠሩት ወሬ ይመስለኛል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ታሪክ አለ በእስራኤል ሀገር ነው በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን ከባድ ረሀብ አጋጠማቸውና የሚላስ የሚቀመስ ከመጥፋቱ የተነሣ የእርግቦች ኩስ እንኳን ሳይቀር በዋጋው የማይቀመስ የሆነበትና ይሄንንም ኩስ ሸምቶ የመብላት ዕድል የነበራቸው ባለጸጎች ብቻ የነበሩበት ሁኔታ የተፈጠረበት ረሀብ ነው፡፡
በዚያ ረሀብ አብዛኛው ሕዝብ ግን ነፍሱን የማቆያ አማራጭ አልነበረውም ነበር፡፡ ቢሆንም ቅሉ “በቃ! እንግዲህ ረሀቡ ይግደለን እንጅ ምን እናደርጋለን?” በማለት ለመሞት እራሳቸውን አላዘጋጁም ከእነሱ ውስጥ ባስ ያላቸው ምን አደረጉ? የገዛ ልጃቸውን እንደ በግ አወራርደው ቀቅለው በመመገብ ረሀባቸውን ለማስታገስ ሞከሩ፡፡ 2ኛ ነገ. 6፤25

ሐበሻ ግን ይሄንን ያደርጋል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው ምክንያቱም የእኛን የረሀብ ታሪክ ተሞክሮዎችን ያየን እንደሆነ እንኳንና የገዛ ልጆቹን ሊበላ ቀርቶ ከብቶቹን እንኳን በልቶ ረሀቡን ለማስታገስ የሚጨክን አንጀት የሌለው አንዳንዴም ከከብቶቹ ቀድሞ የሚረግፈው እሱ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ይህ ነው የእኛ የረሀብ ዘመን ተሞክሮ፡፡
ይህ ሁሌታ ያለንን የሰብአዊነትና የሞራል (ቅስም) ብቃት ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ አንድ የሀገራችንን የጋማ ከብት፣ የአራዊት፣ የአይጡን የጉርጡን ብዛት ያየ የውጭ ዜጋ ነው አሉ “እንዴ! እነኝህ ኢትዮጵያዊያን ይሄ ሁሉ ምግብ እያለ ነው የሚራቡት?” ብሎ በግርምት ጠየቀ፡፡ ሐበሻ ግን እንዲህ ባለ የጨከነ የረሀብ ወቅት እንኳንና በባሕሉና በሃይማኖቱ “የማይበሉ” ብሎ እርም ያደረጋቸውን እንስሳት ይቅርና የሚበሉትን የገዛ ከብቶቹን እንኳን ለመብላት የሚጨክን አንጀት የለውም፡፡
ምክንያቱም ያ ችግር የራሱ ወይም የሰው ልጆች ችግር ብቻ ሳይሆን “እየመገብኩ እገለገልባቸዋለሁ” ብሎ የያዛቸውንና ከብቶቹም “የሰው ልጅ ይመግበናል እኛም እናገለግለዋለን” ብለው አምነውት የተጠጉት ምግባቸውንም ከእጁ የሚጠብቁት እንደቤተሰቡ አባል አድርጎ የሚቆጥራቸው የቤት እንስሳቱም ወይም ከብቶቹም ጭምር ነውና፡፡
በእርግጥም እንደዚያ ያለ የጨከነ ረሀብ በሚመጣበት ጊዜ ያጋጠማቸውን የረሀብ ችግር ስቃይ የሚገልጹበት አፍና አንደበት አጥተው ኅሊናን በሚነካ መልኩ ሲጥመነመኑና ሲንጠራወዙ በየሜዳው እየተፈነገሉ ሲወድቁ በዐይኑ ዕያየ ረሀቡን ለማስታገስ ቢበላቸው ምንም ያህል ቀን ፈቀቅ ላያደርገውና ከዚያ ቆርጦ ከመጣ ረሀብ ላያድነው ነገር ሊጨክንባቸው የሚችልበት አንጀት ኖሮት አያውቅም፡፡ ስለሆነም በአንዳንድ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ በረሀብ ወቅት የሚሞተው ቀድሟቸው ነው፡፡ ከብቶቹ በከረመ ድርቆሽ ጭድ ገለባ የሚሰነብቱበት ዕድል ስለሚኖር፡፡

እናም ክፉ ቀን በአጭሩ ይሄንን የመሰለ ገጽታ ነበረው፡፡ አሁን ደግሞ እንደምታዩት ሕዝባችን ዝም ከተባለ ያንን ታሪክ ሊደግም ለሚችል ለአስከፊ ረሀብ ተጋልጧል፡፡ ብዙዎች ድርቁን ማለትም የክረምት ዝናብ መዛባቱን ተከትሎ ለተከሰተው ረሀብ ተፈጥሮን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ድምዳሜ ነው፡፡ የአየር መዛባት የሚከሰተው በሀገራችን ብቻ አይደለም፡፡ ለድርቅ መከሰት መንስኤ የሆኑ ኤልሚኖም ሆነ ላሚኛ የተሰኙ የአየር መዛባቶች በሌሎች ሀገሮችም ማለትም አውሮፓም አሜሪካም ኤስያም በሌሎች አፍሪካ ሀገራትም በሁሉም ቦታ እንደ እኛ ሁሉ አዘውትሮ ይከሰታል የማይከሰትበት ቦታ የለም፡፡

እነኝህ የአየር መዛባቶች የሕዝብ እልቂት ስፈጥሩ የሚታዩትና የተሰበረ ስም ጥለው የሚሔዱት ግን በእኛ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ለምን? እንዴት? ብለን መጠየቅ ካልቻልን በተሟላ የአእምሮና የሥነልቡና ጤና ላይ እንዳልሆንን መረዳት ይኖርምናል፡፡

ለአሁኑ አንዱን ምክንያት ዕንይ፡-
የሀገራችን ግብርና ኋላ ቀር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ገበሬው እያመረተው ያለው የግብርና ምርት እንኳንና ከራሱ ፍጆታ የሚተርፍ ለራሱ ፍጆታም እንኳን የሚበቃ አይደለም፡፡ ከአንዱ የክረምት ወቅት ወደሌላኛው የክረምት ወቅት የሚደርሰው ተንገዳግዶ ነው፡፡ የተለያዩ ምርቶቹን ለገበያ የሚያቀርበውም ስለተረፈው ሳይሆን አንዲት ቅያሪ ጨርቅ፣ ጨው፣ ዘይት፣ ሳሙና ወዘተረፈ. ለመገብየት ገንዘብ ስለሚያስፈልገው ነው እንጅ ትርፍ ምርት ኖሮት አይደለም፡፡ የዚህ የገበሬው አቅም አጠቃላይ ገጽታም ሀገራችንን በምግብ እራሷን ያልቻለች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡

የሚያሳዝነው ሀገሪቱ አቅም ሳይኖራት ቀርቶ እንዲህ ብትባል ብትሆን የሚቆጭ ነገር ባልነበረ፡፡ የአፍሪካ የውኃ ማማ ያሰኛትን የውኃ ሀብትና ከአራት ሚሊዮን (አእላፋት) ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ሊለማ የሚችልና አፍሪካን ሊመግብ የሚችል መሬት እያላት ነው አስቂኝና እንቆቅልሽ በሆነ መልኩ ለዚህ ችግር ተዳርጋ ያለችው፡፡
ስለዚህ ተወቃሾቹና የሕዝብን አቅም በማንቀሳቀስ ችግሩን መቅረፍ ሲኖርባቸው ይሄም ደግሞ ተቀዳሚና አንገብጋቢው ተግባራቸው ማድረግ ሲገባቸው ለሥልጣናቸው ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ይሄንን አንገብጋቢ ጉዳይ ቸል በማለታቸው የሀገራችን ችግር ብቻ ተደርጎ እስኪቆጠር ድረስ በተደጋጋሚ እንድንጎዳበትና እንድንሰበርበት ካደረጉ ተጠያቂዎች የሀገሪቱ መንግሥታት ናቸው የሚሆኑት፡፡
በወቅቱ ይህ ችግር አሳሳቢ የነበረ ባይሆንም የዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የወደፊቱን በማሰብ የመስኖ ልማትን በአንክሮ አስቦበት ነበር፡፡ ዐባይን ጨምሮ ሌሎችን ወንዞች ለመገደብ በመንቀሳቀስ ለግድቦች ግንባታ የሚሆን ብድርና እርዳታ ተፈልጎ በእነ ግብጽ እንቅፋትነት ማግኘት ባለመቻሉ አቅዱ ሊፈጸም ሳይችል ቀረ፡፡ ዐፄው ለዚህ ጉዳይ ደፋ ቀና ሲሉ ሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው አለና ድርቅ ተከሰተ ለመንግሥታቸው መውደቅም አንደኛው ምክንያት ሆነና አሸኛቸው፡፡

ገልብጦ የገባው የደርግ ሥርዓትም ሕዝብና ሀገርን የጎዳበት አሁን ላለንበት ችግር ሁሉ ተዘፍቀን እንድንቀር ያደረጉ ጥፋቶች ቢኖሩበትም ለግብርና መሠረታዊ ሀብት በሆነው የመሬት ሀብት ላይ የወሰደው ስር ነቀል “የመሬት ላራሹ!” የመሬት ሥሪት ሥርዓት አዋጅና በኋላም ያንቀሳቀሰው የሜካናይዝድ (ዘመናዊ አደረጃጀት የያዘ) የግብርና የእርሻ ልማት ለስኬት ያበቃውና እመርታን ያስመዘበበት ለሀገርም እጅግ ጠቃሚ የነበረ መሆኑ አሌ ሊባል የማይቻል ነው፡፡

ደርግ የ1967ዓ.ም. በኋላም የ1977ን ዓ.ም. ድርቅና ረሀብ ማየቱ በዚህ የልማት እንቅስቃሴው ላይ ጠንክሮ እንዲንቀሳቀስ አስገድዶት ነበር፡፡ በሀገራችን ምዕራባዊ ክፍል ያለውን ሰው ያልሰፈረበትን ሰፊ ከአዲስ አበባ ናዝሬት የሚደርስ መሬት ሌላም እንዲሁ ሰፋፊ መሬቶች ላይ የሜካናይዝድ (ዘመናዊ አደረጃጀት የያዘ) እርሻ እየከወነ የ1977ቱ ዓ.ም. ረሀብ እንዳይደገምና ሀገሪቱ በምግብ እራሷን ከመቻል አልፋ የግብርና ምርትን ለውጪ ገበያ ልታቀርብ የምትችልበትን ርእይ ለማሳካት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ እየተቃረበ እያለ በወያኔ ተገረሰሰ፡፡

እግጅ የሚያሳዝነው በቆዳ ስፋቱ የአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትን የቆዳ ስፋት የሚበልጡትን የነዚያን ዘመናዊ እርሻዎች ማሽነሪዎች (ማሳልጦች) ወያኔ እየጫነ ወደ ትግራይ አጋዛቸው፣ የአንድ አነስተኛ ከተማ ሕዝብ የሚያክለው ሠራተኛ ተበተነ፣ እነዚያ ስንት የተደከመበባቸውና ስንት ተስፋ የተጣለባቸው ስንት የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ዘመናዊ እርሻዎችም ጠፍ ሆነው እንዲቀሩ ተደረገ፡፡

የዚህ ምክንያትም ግብጽ “እነኝህ እጅግ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች፣ የጣና በለስ ፕሮጀክት (የሥራ አቅድ) ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የሜካናይዝድ (ዘመናዊ አደረጃጀት የያዘ) የመስኖ እርሻ ልማት ከተስፋፋ የውኃ ዋስትናየን ያሳጣኛል!” የሚል እጅግ ከባድ ሥጋት ላይ ጥሏት ስለነበር ያለምንም ጥያቄና መልስ ሎሌዋን ወያኔን እንዲዘጋ ስላዘዘች ነበር እነዚያ ስንት የተደከመበባቸውና ስንት ተስፋ የተጣለባቸው ስንት የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ዘመናዊ እርሻዎችም ጠፍ ሆነው እንዲቀሩ ተደረጉት፡፡
ወያኔ የግብጽ ጥቅም አስከባሪ ጠባቂ ቅጥረኛ በመሆኑም ነው በጥቂቱም እንኳን ቢሆን 12 ሽህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ምርታችንንም በመጠኑ ያሳድጋል ተብሎ ለመስኖ እርሻ ታስቦ በ5 ዓመታት ሊጠናቀቅ ሲገነባ የነበረው የቆጋ አነስተኛ ግድብ በ12 ዓመቱም እንኳን ሳይጠናቀቅ ይፈጃል ተብሎ ከታሰበው ወጪ ከሁለት እጥፍ በላይ ከ1.2 ቢሊዮን (ብልፍ) ልብ በሉ ሚሊዮን (አእላፋት) አይደለም ያልኩት ቢሊዮን (ብልፍ) በላይ ገንዘብ ፈጅቶም ገና አልተጠናቀቀም “አንዳንድ ችግሮች ስላጋጠሙን ነው አጋምሰነዋል!” እያሉ ያሾፋሉ፡፡ እንግዲህ ወያኔ “አላሰበም” እንዳይባል ነው ይህችን የጀመራት እንጅ ሥራ ላይ እንደማይውልስ እኛም ቀድመን እናውቅ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ይህ የግድቡ ቦታ “የጅኦሎጂ (የሥነምድር) ችግር አለበት ቦታው ለግድብ አይሆንም ውኃ ያሰርጋል” በሚል ምክንያት ቀሪው ግንባታም ሳይጠናቀቅ ሊተውት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ምክንያት እውነት እንዳይመስላቹህ ግብጽ ስለተቆጣች ነው፡፡ ቀድሞ ነገር እንዴት ይሄንን ያህል ገንዘብ የሚፈስበት ሥራ ለሥራው ተስማሚ ስፍራ መሆኑ ሳይጠና ሳይታወቅ ሳይረጋገጥ ይጀመራል?

እንዲህ እንዲህ እያለ የሀገራችን ግብርና ዘመናዊ መልክ ሊይዝና ከረሀብ ችጋር ተመጽዋችነት ሊታደገን ሲሞክር ሲቀጭ ሲሞክር ሲቀጭ ይሄው በቀላሉ በአንድ የክረምት ወቅት መዛባት እየተሸመደመድን ዛሬም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት አንገታችንን ሰብረን በልመና ለመቆም እንደተገደድን አለን፡፡

አሁን 15 ሚሊዮን (አእላፋት) ሕዝባችን ለረሀብ ከተጋለጠበት ወቅት ጋር ፊት ለፊት ተፋጠናል፡፡ መፋጠጥም ብቻ አይደል እንስሳት እንደቅተል እረግፈዋል ሰዎችን እየሞቱ ነው፡፡ እንደአያያዙ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ካልተረባረበልን ዓይነተው የማናውቀው እልቂት ሊከሰትም እንደሚችል ከፍተኛ ሥጋት አለ፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ ፈጥኖ እንዳይረዳንም ወያኔ ሀገሪቱ በምግብ ራሷን መቻሏ ብቻ ሳይሆን የአየር መዛባት ቢያጋጥምም በዘንድሮው የምርት ዘመን ከአምናው የተሻለ ምርት ሊገኝ እንደሚችል ማረጋገጡን ካወጀ ሁለት ወር አልሞላውም፡፡ ረሀቡ ያለበትን ደረጃና የተጋለጠውን የሕዝባችን ቁጥርም ለመደበቅ የሚያደርገውን ከፍተኛ ጥረት እየተመለከታቹህ ነው፡፡ በረሀቡ ያለቁ እንስሳትን እየሰበሰበ በመደበቅ ሥራም ተጠምዷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አገዛዙ በዚህ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው ጉዳይ ዝርፊያን ሕጋዊ መልክ አስይዞ ጡረታ ለሚወጡ ባለሥልጣናቱ ስለገነባላቸው የአውሮፓን ደረጃ የጠበቁ በብዙኃን መገናኛዎች ከገለጹት ብዙ እጥፍ ወጪ የፈሰሰባቸው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችና ባለሥልጣናቱ በእነዚህ ዘመናዊ ቤቶች ሲኖሩ አዝመንምኖ ሊያኖራቸው የሚችለውን ባጀት (የገንዘብ ምድብ) በምን ስም ምንስ ያህል መድቦ እንሚያምነሸንሻቸው እንጅ ሕዝባችን እያለቀበት ያለው ረሀብ አይደለም፡፡
እዚህ ላይ የገረመኝ ነገር ለጡረተኛ ባለሥልጣናት ይሄ ሁሉ የሚደረገው ለምን ምንስ ስለሆኑ ነው? ሀገርን ስላገለገሉ ተብሎ ነው? አየ ማገልገል! እሽ ባይሆንም ነው ብለን እናስብና ሌላው ዜጋስ ማንን ነው የሚያገለግለው? ሀገርን አይደለም? ነው ወይስ እነሱ ያለደሞዝ ነበር የሚያገለግሉት? እውን አሁን እነሱ “ሀገርን ስላገለገሉ” ተብሎ ይሄ የሚደረግላቸው ከአንድ ነፍሱን ለሀገሩ ሲል ሳያመነታ ለመሠዋት ተዘጋጅቶ ከተሰለፈ ተራ ወታደር የላቀ ለሀገር መሥዋዕትነት የመክፈል ሁኔታና አጋጣሚ ውስጥ በመሆናቸው ነው ወይ በተለየ ዓይን ታይተው ይሄ ችሮታ የሚገባቸው?

ባለሥልጣናት ከአንድ መተኪያ የሌላትንና ከነገሮች ሁሉ የመጨረሻው ትልቅ ዋጋ ያላት አንዲት ነፍሱን ለሀገር (ልብ በሉ ለሀገር ነው ያልኩት ለወያኔ ጥቅም አይደለም) ለመሠዋት ከተዘጋጀ ተራ ወታደር ከሚከፍለው ዋጋ የላቀ ዋጋ ለሀገር የሚከፍሉ ካልሆነስ በምን ሒሳብ በምን አግባብ በምን ሕጋዊ አኪያሔድ በመን አመክንዮ ነው ከሀገሪቱ አቅም በላይ ያውም ከፍተኛ የድርቅና የረሀብ አደጋ ላይ ባለንበት ሰዓት ይሄንን ያህል ጥቅም ለየራሳቸው ሊቀራመቱ ያሰፈሰፉት?

ነው ወይስ ነፍሱን እስከመስጠት ድረስ ለሀገሩ ታምኖ ለተሠማራ ተራ ወታደርና በተለያየ መስክ ሆኖ ሀገሩን ለሚያገለግል ዜጋ ሁሉ ነው ጡረተኛ ሲሆን ለመስጠት ይሄ ችሮታ የተመቻቸው? ከሆነ እሰየው የሚያሰኝና ፍትሐዊ አሠራርም ነው፡፡ መጥፎው ዜና ግን ይሄ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ዕድል የተመቻቸው ያለችሎታቸው ዕውቀታቸውና ሰብእናቸው የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል ጨምድደው ይዘው ሀገርን ሲያከስሩ ሕዝብ ሲያደኸዩ ሲያስርቡ ሲያሰቃዩ እራሳቸው ግን በምቾትና በድሎት እየተምነሸነሹ ሲኖሩ ለነበሩ የወያኔ ባለሥልጣናት ብቻ ነው፡፡ አሠራሩም ኢፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ፊውዳላዊ (ባላባታዊ) አሠራር ነው፡፡

በፊውዳላዊ (በባላባታዊ) ሥርዓት ነው ሹማምንቱ የሕዝብን ሀብት እንዳሻቸው በመቀራመት ለየራሳቸው የሚወስዱት፡፡ ያውም እነሱ ይወስዱ የነበሩት ከእርሻ መሬት ያለፈ አልነበረም፡፡ እነዚህ እኮ መሬቱን መዝረፍ አልቀራቸው የሀገርን ካዝና መዝረፍ አልቀራቸው እስኪ ምን የቀራቸው ነገር አለ? ሕዝብ በችጋርና በረሀብ እየተጠማዘዘ “አይ! የለም አልተቸገርክም አልፎልሀል!” እያሉ እያሾፉ ሁሉንም ነገር ለራሳቸው የሚያግበሰበሱ ጅቦች እኮናቸው፡፡ ኧረ ጅብ አንድ ሽህ ጊዜ ይሻላል፡፡
ይሄንን እየተባባሰ የመጣ ዝርፊያቸውን ዝም እያልን ያሳለፍን እንደሆነ አትጠራጠሩ የባሪያ ንግድን ጀምረው የኢትዮጵያን ሕዝብ በይፋ ለባርነት ይቸበችቡታል፡፡ ብቻ የሚገዛ ይኑር እንጅ ይንን ከማድረግ አይቆጠቡም፡፡ እጅግ የሚገርም እኮ ነው! “የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለሆንን ከመንግሥት ካዝና እንደፈለግን መዝረፍ እንችላለን” ይባላል? በየግል የዘረፉትንስ መቸ ሊበሉት ነው?

የሞላው የተረፈው ሀገር መንግሥት በፍትሐዊና በተአማኒ ምርጫ ተመርጦ ለዚያ ሥልጣን ለበቃና ሀገሩን በታማኝነትና በትጋት ሲያገለግል ለኖረ ባለሥልጣኑ እንዲህ ዓይነት ችሮታ ሲያደርግ ባይ ባልገረመኝ፡፡ ተገቢ ነውም ብየ ባደነኩ ነበር፡፡ አሁን በኢትዮጵያ አቅም ያውም ሲያደማት ሲያቆስላት ለኖረ የጅብ መንጋ ይሄ እንዲሆን የምንፈቅደው እስኪ በምን አግባብ ነው በሉ?

እኔ በድርቅ ምክንያት 15 ሚሊዮን (አእላፋት) ሕዝብ መራቡ አይገርመኝም፡፡ አገዛዙ እየተከተለው ባለው ውንብድና የተሞላበት ኢፍትሐዊ የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) አኪያሔድ ለረሀብ ተጋለጠ ከምንለው 15 ሚሊዮን (አእላፋት) የላቀ ሕዝብ በየጓዳው በረሀብ እየተቆላ ነውና፡፡ ይሄንን ወገናችንንስ ማን ቆጠረው?
ዓለም አንድ መንደር የሆነችበት ዘመን ላይ መሆናችን፣ መረጃ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደሌላኛው ጫፍ በሰከንድ (በአሐዲት) ውስጥ መተላለፍ የሚቻልበት ዘመን ላይ መሆናችን በጀን እንጅ እኮ እንደወያኔ ቢሆን ኖሮ እኮ ወሬያችን ሳይሰማ 15 እና ከዛ በላይ አእላፋት ሕዝብ ጭጭ ብሎ ክፉ ቀንን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም እንደግመው ነበር፡፡ እናም ወገኖቸ ይሄንን ጉዳይ እኛው እራሳችን ብንይዘው መልካምና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

በመሆኑም በተለይ ከሀገር ውጪ ያላቹህ ምሁራንና ተደማጭነት ያላቹህ ወገኖቻችን የሀገራቹህና የሕዝባቹህ አምባደር (እንደራሴ) እና ዲፕሎማት (መልእክተኛ) በመሆን ያለውን ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ ተረባርበው እንዲታደጉን ሳትታክቱ እንድትጥሩ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አደራ አለባቹህ፡፡ መቸም ያው ውርደት ነው ነገር ግን ሕዝባችን ከሚያልቅ ውርደትም ቢሆን ምን ይደረግ? ለዘላቂው መፍትሔ ቆርጠን ከተነሣን ይሄንን አዋራጅ የረሀብ ክስተት አሽቀንጥረን የምንጥልበት ቀን ሩቅ አይደለምና ግድ የለም የዛሬን በለጋሾች ፊት ተዋርደን እንለምን ወያኔ እያለ ምን ክብር ኖሮን ያውቅና ለየትኛው ክራችን እንቆርቆር እንቆጭ?

አንድ ነገር አስቀድሜ ላሳስባቹህ የምሻው ጉዳይ ቢኖር ወያኔ በምግብ እራሳችንን የቻልን መሆኑን ማወጁ፣ የረሀቡን ገጽታ ለመደበቅ የሚያደርገው ጥረትና የገዛ ድርጅቶቹንና የአጋር የደጋፊ ባለሀብቶችን እድገት የሀገር እድገት አስመስሎ ለተከታታይ ዓመታት 11% እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ ሲለፍፍ መክረሙ ሕዝባችን ያለበትን ትክክለኛ ገጽታ አስረድታቹህ ለማሳመንና እርዳታን ለማግኘት እንዳትችሉ እንዳትታመኑ ወይም ብዙ ሊያደክማቹህ ይችላልና ተስፋ ሳትቆርጡ ጠንክራቹህ በመሯሯጥ ሕዝባችን በረሀቡ ሳያልቅ እርዳታውን እንድታደርሱለት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

እኔ በግሌ ይሄ ግዙፍ ረሀብ በወያኔ ምክንያት የመጣ የተፈጠረ የተከሰተ ረሀብ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ይሄንን ስላቹህ ለድርቁ መከሰት ምክንያት የሆነውን ኤልሚኞን (የሕንድ ውቅያኖስ የአየር ሙቀትን) ያመጣው ወያኔ ነው እያልኳቹህ እንዳልሆነ ልብ እንድትሉ እሻለሁ፡፡ እኔ እያልኩ ያሉሁት ይህ የአየር መዛባት የተከሰተው በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ነው የተከሰተው፡፡ እዚህ አህጉራችንም እስከ ደቡባዊ የአፍሪካ ሀገራት ድረስ ነው የተከሰተው፡፡ እነዚህ ሀገራት ግን ለእኛ ዓይነት የረሀብ አደጋ አልተዳረጉም፡፡ እንዴት? ሌላ ምንም ምሥጢር የለውም ግብርናቸው ወይም የገበሬዎቻቸው አቅም እንደኛ ገበሬና ግብርና በአንድ የክረምት ወቅት መዛባት የሚሽመደመድ ከእጅ ወደ አፍ ስላልሆነ ነው፡፡ ለነገሩ የእኛ ግብርና አቅም ገና ከእጅ ወደ አፍ ደረጃም እንኳን አልደረሰም፡፡

የሀገራችንን ግብርና እንዲህ ደካማ ሆኖ እንዲቀር ከዚህ ችግሩ እንዳይላቀቅ ያደረገው ሌላ ማንም ሳይሆን ወያኔ ነው፡፡ በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች፡-
አገዛዙ እየተከተለው ባለው አጥፊ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ሥሪት ሥርዓት ምክንያት ነው፡፡ እሱ ምንድን ነው፡- እንደምታውቁት የወያኔ የመሬት ሥሪት ሥርዓት “ሁሉም የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው የግል የሚባል መሬት የለም!” የሚል ነው፡፡

ከሀገራችን ሕዝብ 85% ገበሬ ወይም የገጠር ኗሪ ነው፡፡ ይሄንን ያህል ከፍተኛ ድርሻ የያዘውን የኅብረተሰብ ክፍል ወያኔ መቆጣጠር እንዳለበት በማመኑ ለገበሬው የህልውናው መሠረት የሆነውን “ዋነኛ ሀብቴ” የሚለውን ንብረቱን መሬቱን ነጥቆ “የመንግሥትና የሕዝብ ነው” ብሎ አወጀና የኑሮ ዋስትና ሥጋት ላይ ጣለው፡፡ አገዛዙ ይሄንን በማድረጉ ገበሬውን የፈለገውን ያህል ቢበድለው ከመዳፉ እንደማይወጣ በማሰብ ሊወጣ ቢሞክርም መሬቱን እንደሚነጥቀው በማስፈራራት ሳይወድ በግዱ አንገቱን ደፍቶ እንዲገዛለት እያደረገው ይገኛል፡፡ “መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው” ማለት በተግባር ካለው የመሬት አጠቃቀም አንጻር ምን ማለት እንደሆነና የመንግሥት ያልሆነ የሕዝብ የሆነ መሬትም የትኛው እንደሆነ ምንም የሚታወቅ ነገር በሌለበት ሁኔታ “የሕዝብ” የሚለው ቃል ትርጉም አልባ ነው፡፡ “የሕዝብ” የምትለዋ ቃል ለማደናገሪያ የገባች ቃል ናት፡፡ አሁን ባለው አገዛዝ የመሬት ሥሪት ሥርዓት የግልም የሕዝብም የሚባል መሬት የለም ሁሉም የመንግሥት ነው፡፡ ባያድለንና አገዛዙ ሕዝባዊ ባለመሆኑ ነው እንጅማ እኮ የሕዝብ ማለት የመንግሥት የመንግሥት ማለትም የሕዝብ ነበር፡፡ ሕዝባዊ የሚባል የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት ባለበት ሀገር የሕዝብ ያልሆነ የመንግሥት የመንግሥት ያልሆነ የሕዝብ የሚባል ምንም ነገር የለምና፡፡ እናም መንግሥትንና ሕዝብን እንዴትና ለምን ነጣጥሎ ለማየት እንደተፈለገ እራሱ ግልጽ አይደለም፡፡ ለነገሩ የወያኔ አገዛዝ ሕዝባዊ ስላልሆነ ነጣጥሎ ማስቀመጡ ትክክል ነው፡፡

ወያኔ መሬት “የመንግሥትና የሕዝብ” እንደሆነ አድርጎ የደነገገበትን ምክንያት ሲያብራራ፡- “ገበሬው የእርሻ በሬቱን እየሸጠ ከተማ በመግባት ችግር ላይ እንዳይወድቅ መሬቱም በጥቂቶቹ ገንዘብ ባላቸው ባለሀብቶች እጅ ብቻ እንዳይገባ በማሰብ ነው” ይላል፡፡ ነገር ግን ይሄንን አባባሉን ሐሰት እንደሆነ የሚያጋልጠው “መሬቱን እንዳይሸጥ እንዳይለውጥ የከለከልኩት ከመሬቱ ተፈናቅሎ ችግር ላይ እንዳይወድቅና ህልውናው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለራሱ ህልውና በማሰብ ነው” የሚለው ወያኔ ለወራት የማትበቃ መናኛ ፍራንክ ካሳ እያለ በመወርወር የገበሬውን መሬት እየነጠቀ እትብቱ የተቀበረበትንና ከአያት ቅድመ አያቶቹ ከወረሰው ርስቱን እያፈናቀለ በገፍ ለባዕዳን ለባለሀብት እየቸበቸበበትና በገዛ ሀገሩ ተፈናቃይ ስደተኛ ለማኝና የከተማ ጎዳና ተዳዳሪ እያደረገው ያለው እራሱ በመሆኑ ከላይ የተሰጠው ምክንያት ነጭ ውሸት መሆኑን ማረጋገጥ ያስችላል፡፡
“ገበሬው እየሸጠ ከተማ ይገባል” የሚለው አባባል የሀገራችን ገበሬ መሬትን እንደምን አድርጎ እንደሚያይ፤ ለመሬቱ ያለውንና የሚሰጠውን ዋጋ ካለማወቅ ካለመገንዘብ የተነገረ አባባል ቢመስልም ችግሩ ይሄ እንዳልሆነ ግን ከመሬቱ አፈናቅለው ለባለሀብት በመቸብቸባቸው ተረጋግጧል፡፡ የሀገራችን ገበሬ ለመሬቱ የሚሰጠውን ግምት ክብርና ዋጋ ያህል ለምንም ነገር አይሰጥም ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ በገበሬው እምነት መሬት መሸጥ ማለት “ከርስት መነቀል” የሚባልን ከፍተኛ ነውርና ሀቅን ክብርን ሀገርን እንደ መሸጥ እንደ መካድ የሚቆጠር እንደሆነ የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ አመለካከት በሰረፀበት ኅብረተሰብ ውስጥ መሬቱን እየሸጠ ከተማ በመግባት ራሱን ለችግር ይዳርጋል የሚለው አባባል ታላቅ ፌዝና በተለይም እሱ ራሱ እያፈናቀለ የትም በመጣል ለባዕዳን ባለሀብት የሚሸጥበት አገዛዝ ሥጋት ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል፡፡
ይህ “መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው” የሚለው አዋጅ በርካታ ችግሮችን ነው የፈጠረው፡፡ ከማውቀው ብጀምር የኔ ዘመዶች ሰፊ የደን መሬት ነበራቸው፡፡ ወያኔ ሥልጣን ይዞ በመሬት ላይ ያለው አቋም እንዳለው እንዳወጀው መሆኑ እንደታወቀ “ስንት የደከምንበት ሀብታችን መወረሱ ነው!” በሚል ሥጋት ተፋጥነው ነበር ደኑን በመቁረጥ ለዳቦ ቤቶችና ለጣውላ ቤቶች የሸጡት፡፡
ይህ ድርጊት በእኔ ዘመዶች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በወቅቱ በገበሬው ዘንድ በሰፊው የተፈጸመ ድርጊት ነበር፡፡ አዋጁ ገበሬውን ለገዛ መሬቱ የነበረውን የባለቤትነት ስሜት እንዲያጣ ነበር ያደረገው፡፡ ከዚያ በኋላ ገበሬው እምነት አድሮበት መሬቱ እሴት እንዲጨምር ሊያደርግ የሚችልበትን ወኔና ጥረት አሳጥቶታል፡፡ ቀድሞ ከዚያ አዋጅ በፊት በመሬቱ ላይ ደን እየተከለ ሌሎችንም የግብርና ሥራዎች ተግቶ እየሠራ መሬቱን ያለማ ይንከባከብ የነበረውን ገበሬ ለመሬቱ ዴንታ ቢስና ተስፋ ቢስ እንዲሆን ነበር ያደረገው፡፡
ወያኔ ዘግይቶም ቢሆን አዋጁ ምን ዓይነት ችግርና አደጋ እንዳደረሰ ተረድቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የሀገርን ሳይሆን የግል ጥቅሙን ማስጠበቅ ካለበት ሌላ አማራጭ እንደሌለው በማመኑ አዋጁን ሳይቀይር ቆይቷል፡፡ “መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው መሸጥ መጥ አይቻልም” ብሎ በማወጁ ገበሬው የባለቤትነት ስሜት እንዲያጣ በማድረጉ ተከትሎት በተፈጠረው ችግር በሀገሪቱና በገበሬው ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ኪሳራ ተጠያቂ እንደሆነ ጣት ሲጠቆምበት በአዋጁ ምክንያት አደጋው የደረሰና ሊቀጥልም እንደሚችል ቢያምንም በዚያ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” አስተሳሰቡ ምክንያት የአንዲት ሀገር መንግሥት ነኝ ከሚል አካል በማይጠበቅ መልኩ የግል ጥቅሙ ከሀገር ጥቅም ስለበለጠበት ይሄንን ጎጂ አዋጅ ከመቀየር ይልቅ “የባለቤትነት ካርድ” የሚባል ፈሊጥ በማምጣት ገበሬውን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል ያለውን የካርድ እደላ ማድረግ ውስጥ ነበር የገባው፡፡

ከዚህ የወያኔ የካርድ ዕደላ ድርጊቱ የምንረዳው ሀቅ ምንድን ነው? አገዛዙ ገበሬው መሬቱን “የራሴ ነው” ብሎ ሲያስበው ከነበረው አስተሳሰብ ወጥቶ “የመንግሥት ነው” መባሉ ጉዳትና ችግር እንዳመጣ በሚገባ መረዳቱን ነው፡፡ ይሁን እንጅ የራሱ ጥቅም ስለበለጠበትና “ለገበሬው መሬቱን የግሉ ካደረኩ ይቆጣጠረኛል እንጅ ልቆጣጠረው አልችልም፣ የገዛኛል እንጅ ልገዛው አልችልም፣ በምርጫ በዓትም በምንም ነገር ላስፈራራውና ድምፁን እንዲሰጠኝ ላስገድድበት የምችልበት መሣሪያ መንገድ አይኖረኝም!” ብሎ በማሰቡ አዋጁን እንዲቀለብስ ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ገበሬው ካርድ እየተሰጠው “እስካለህ ድረስ ያንተ ነው ለልጅህም ማውረስ ትችላለህ!” መባሉ አሁንም እየተፈናቀለ ለባዕዳንና ለባለሀብቶች መሬቱ ተሸጦ ከመፈናቀል ስላላዳነው የካርዱ ጥቅም ጨዋታና ቀልድ እንደሆነ እንዲረዳ አድርጎታል፡፡ በእርግጥም ነው፡፡
እንግዲህ ወያኔ “ለዚህ ያደረሰኝ” እያለ የሚሸነግለው ገበሬ በዚህ መልኩ እያጉላላው እያንገላታው እያሰቃየው የኑሮ ዋስትና አሳጥቶ እየተጫወተበት እንጅ የውለታውን አይደለም የመብቱን ያህል እንኳን ሊፈጽምለት አልቻለም አልፈቀደም፡፡ ገበሬው ላይ ያለው ሀቅ ባጭሩ ይሄው ነው፡፡
እኔ በግሌ የመሬት ሥሪትን በተመለከተ የሚታሰበኝ መሬት የመግዛትና መልሶም የመሸጥ መብትን ለባዕዳን የተከለከለ ለዜጎች ብቻ የተሰጠ መብት ሆኖ “መሬት ላራሹ” የሚለው ሙሉ የባለቤትነት መብት ለገበሬው ቢሰጥና ገበሬው የመሸጥ የመለወጥ መብት ቢኖረው ለመሬቱ ባለው አመለካከት የተነሣ ለመሸጥ አይደፍርም አንጅ የሚሸጥ ቢሆንም እንኳ አደጋ ወይም ችግር ያጋጥማል ብየ አልጠብቅም፡፡

ሲጀመር ሁሉም ገበሬ መሬቱን ሊሸጥ አይችልም፡፡ ይህ ከአመክንዮና ከገበያ ሥርዓት ውጪ የሆነ አስተሳሰብ ነውና፡፡ ቤትን የመሸጥ የመለወጥ መብት ስለተሰጠ ሰው ሁሉ ቤቴን ልሽጥ እንዳላለና ሊልም እንደማይችለው ቢልም ሊሆን እንደማይችለው ሁሉ “መሬት መሸጥ መለወጥ ይቻላል!” ስለተባለም ሁሉም ሰው መሬቱን ይሸጣል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሲበዛ ደካማ አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት መሬቱን ማረስ ወይም ማልማት ያልቻለ ገበሬ መሬቱን ቢሸጠው መሬቱ የተሻለ አቅም ባለው ዜጋ እጅ ገብቶ መልማት መቻሉ ሀገርን የበለጠ ይጠቅማል እንጅ አንድም ሊጎዳ የሚችለበት ምክንያት የለም፡፡ መሬት እንደሌላ ሸቀጥ ተሸጦ ከሀገር የሚወጣ ንብረት አይደለምና መሸጡ ሊያሳስብ የሚችል አይሆንም፡፡

የሀገራችን ሕዝብ ዳታ (አኀዝ) 85% የገጠር 15% የከተማ የሚለው መለወጥና መመጣጠን ካለበት ከግብርናው በተጫማሪም ሌሎች የምጣኔ ሀብት አማራጮችን መያዝ ካለብን የመሬት መሸጥ መለወጥ መብት ተረጋግጦ አቅም ያላቸው ወይም እራሱ ገበሬው አቅም ፈጥሮ የዘመነ ግብርና ሊከውኑ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል፡፡ አሁን ገበሬው እየተፈናቀለ መሬቱ ባልረባ ዋጋ ለባለሀብት ተሸጦ የሀገሪቱ ሀብት ከገበሬውም ከመንግሥትም (ከሀገሪቱ) ሳይሆን ባዕዳን ያሻቸውን ምርት እያመረቱ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የባዕዳን ሲሳይ ሆኖ ከሚቀር ገበሬው ባሻው ዋጋ ሸጦ ገንዘቡ ወደ ገበሬው እጅ ገብቶ ገበሬው እንዲሠራበት ቢደረግ መሬቱን የገዛው ዜጋም የተሻለ ምርት አምርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢችል ነው የሀገሪቱ ሀብት ለሀገሪቱ የሚሆነው፣ ሀብት ሊፈጠር፣ ምጣኔ ሀብቱ ሊንቀሳቀስ ሊጎለብት ሊያድግ፣ ይሄ 85 ለ 15 የሚለው አኃዝም ሊለወጥ የሚችለው፡፡

ከተሞች ሲስፋፉ እንቅስቃሴው ይሟሟቃል ሀብት እየተፈጠረ ይሄዳል በዚያ በኩል ደግሞ ግብርናው እየተለወጠ እየዘመነ የኅብረት ሥራዎች እየተስፋፉ ይሔዳሉ፡፡ አዲስ ዓይነት አሠራር አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ አዲስ ዓይነት አመለካከት ለመፈጠር ዕድል ይሰጣል፡፡ በምዕራቡ ዓለም ይህ አሁን ያለው ስኬት ሊገኝ የቻለው በዚህ ዓይነት አሠራር ነው እንጅ በሌላ ተአምር አይደለም፡፡

በመሆኑም ገበሬው አያደርገውም እንጅ ቢያደርገውም እንኳን ውጤቱ የሚያስደስት እንጅ የሚያስፈራ አይደለም፡፡ ገበሬው ባለው አመለካከት የተነሣ ባያደርገውም መሬት መሸጥ መለወጥ የሚችለው የገበሬው የግል ሀብት ሆኖ በአንዳንድ ልዩ ምክንያቶች ተገቢው ካሳ ተከፍሎት ካልሆነ በስተቀር መንግሥትን ጨምሮ ማንም ሊነጥቀው የማይችለው የመሬቱ ባለቤት እንደሆነ መረጋገጡ በሚፈጥርለት መነቃቃትና በራስ መተማመን የባለቤትነት ስሜት በመሬቱ ላይ የሚያፈሰው የሀብት የጉልበት የእውቀት ፍሰት ቋሚና ዘላቂ ሥራ እንክብካቤና ጥበቃ ለሀገርና ለግብርናችን ከፍተኛ ጥቅምና ዐቢይ ለውጥ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡

በዛም ሆነ በዚህ የምንጠቀምበት እንጅ የምንጎዳበት አይሆንም፡፡ በሌላም በኩል ገበሬው የነጻነቱ የመብቱ ባለቤት ስለሚሆን ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) የመንግሥት ሥርዓት ለመመሥረት የሚያበቃ ዕድልም ይሰጠናል፡፡ ወያኔ ይህችን ስለሚያውቅም ነው “ገበሬውን የህልውናው መሠረት በሆነው በመሬቱ ልይዘው ካልቻልኩ ህልውናየ አደጋ ላይ ይወድቃል” ብሎ አስቦ የመሬቱን ባለቤትነት ነጥቆ አስገድዶ ሊገዛውና ይሄው እስከአሁንም ሊቆይ የቻለው፡፡ ወያኔ በሥልጣን ላይ እስካለ ጊዜ ድረስም መሬት የገበሬው የግል ሀብት መደረጉን የህልውናው አደጋ አድርጎ ስለሚያስብና መያዣ ስላደረገው ይህ ሁኔታ ይለወጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በዚህ አዋጅ ምክንያት የገበሬውም ሆነ የሀገራችን እጣ ፋንታና ምጣኔ ሀብት ጫጨ ቀጨጨ መነመነ እንጅ አልዳበረም አልደረጀም ሊዳብርም ሊደረጅም አይችልም፡፡

ገበሬው ያለችው መሬት ከበሬ ግንባር የማትሻልና የተበጣጠሰ ነው፡፡ ሀገራችን ለእርሻ ከዋለው መሬት አንጻር ባላት የገበሬ አሰፋፈር በሄክታር 55.13% ከዓለማችን እጅግ የተጠቀጠቀውና አንድ ሄክታር ሊይዝ ከሚገባው እጅግ የበዛ አሰፋፈር ካላቸው የዓለማችን ሀገራት አንዷ ናት፡፡ የገበሬው የእርሻ መሬቱ ባለቤትነት ተነጥቆ የባለቤትነት ስሜት በማጣቱ ለመሬቱ ሊያደርገው የሚገባውን እንክብካቤና እሴት መጨመር ትቶ ለራሱ ፍጆታ እንኳን ለማምረት የማይበቃ በሆነበት ሁኔታና ወደ ዘመናዊ እርሻ ሊሸጋገር የሚችልበት መንገድ ተዘግቶ ባለበት ሁኔታ ይህቺ ሀገር ከዚህ ችግር ትወጣለች ብሎ ማሰብ በፍጹም የማይታሰብ ነው፡፡ እናም ሕዝባችንንና ሀገራችንን ችግር ላይ የጣላትና ከዚህ ችግርም እንዳትወጣ አድርጎ ለረሀብ እየዳረገን ያለው ወያኔ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ሲሆን፡፡

ወያኔ ለግብጽ ባለው ቅጥረኝነቱና ሎሌነቱ የጠላትና የባዕዳንን ጥቅም የሚያስጠብቅ የባንዶች አገዛዝ ቡድን እንጅ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ የሚቆረቆር የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም የሚያስጠብቅ የኢትዮጵያ መንግሥት መሆን ስላልቻለና ስለማይችልም በቅጥረኝነቱ የተነሣ እንኳንና ሜናካይዝድ (ዘመናዊ አደረጃጀት የያዘ) የመስኖ እርሻዎችን ሊያስብ ይቅርና ስንት ተደክሞበት ስንት የሀገር ሀብት ፈሶበት የተሠራውን እንኳ ያጠፋ ያፈረሰ ወደፊት የሚመጡ መንግሥታትም የመስኖ እርሻን መሥራት ማስፋፋትና ሀገሪቱን ከችግሯ እንድትወጣ ማድረግ እንዳይችሉ ከግብጽ ጋር ባደረገው በዐባይ ወንዝ ላይ የሚሠራን ግድብ ውል ስምምነት ውኃውን ለመስኖ እርሻ መጠቀም እንዳይችሉ የሚከለክል ስምምነት የተፈራረመ ከሀዲና የጠላት ቅጥረኛ በመሆኑ፡፡

ሀገራችን በምግብ እራሷን የቻለች የመሆኗ ነገር አንገብጋቢ በሆነበት ሁኔታና እንዳላት የተፈጥሮ አቅምም አቅሟን ተጠቅማ የግብርና ምርቶችን ለውጪ ገበያም በማቅረብ ምጣኔ ሀብቷን መገንባት አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ገበሬው “የኛ ደጋፊ ካልሆንክ በስተቀረ!” እየተባለ ማዳበሪያ ምርጥ ዘርና ተጓዳኝ የእርሻ ግብአቶችን እየነፈገ ገበሬውን የሚያደኸይና ለችጋር ለረሀብ የሚዳርግ በመሆኑ፤ ወያኔ እንዲህ በማድረጉ ሀገራችን በምግብ እራሷን እንዳትችልና ሕዝቡም ለችጋር የሚዳረግ መሆኑን ጨርሶ ሊረዳ የማይፈልግ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” የሚልን አባባል መርሑ ያደረገ ደንቆሮ አገዛዝ በመሆኑ ይህ አስተሳሰቡም የህልውናችን አደጋ በመሆኑ፡፡

በእነዚህ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች የመራባችንና ለረሀብ የመጋለጣችን ምክንያት ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የአንድ ክረምት የአየር መዛባት ሲያጋጥመን መቋቋም ተስኖን ለረሀብ እየተዳረግን ያለነው፡፡ ስለሆነም ይህች ሀገር ከዚህ አስከፊ ችግር መላቀቅ ካለባትና ረሀብ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሸኘነው ክፉ እንግዳ እንዲሆን ለማድረግ ከፈለግን ብቸኛው መፍትሔ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱም በተቻለን ፍጥነት “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባዩን የጠላቶቻችን ቅጥረኛ ወያኔን ከነክፉ አስተሳሰቦቹ ወደመቃብሩ አውርዶ መቅበር፡፡

ይሄንን ካላደረግን በስተቀር ወያኔ በሕይዎት ወይም በሥልጣን እያለ እራሱና አጋር ባለሀብቶቹ ይበለጽጉ ይሆናል እንጅ ይህቺ ሀገርና ሕዝቧ ፈቀቅ ይላሉ ብላቹህ ተስፋ አታድርጉ፡፡ ብቸኛውን መፍትሔ ተፈጻሚ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ተፈጻሚ ለማድረግ ታጥቀን እንነሣ፡፡
እሚሰማ ከሆነ ለወያኔ ልነግረው የመምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ወያኔዎች ሆይ! ለሳራቹህ የምታስቡ ከሆነ ለዚህች ሀገርና ሕዝብ በፍጹም በፍጹም በፍጹም አትመጥኑምና ለዚህች ሀገር ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ብቃት ችሎታ ማንነት ጨርሶ የላቹህምና እንዲህ መሆናቹህንም ከማንም በላይ እራሳቹህ አሳምራቹህ ታውቁታላቹህና በአስከፊ ሁኔታ ወደ መቃብራቹህ ሊያወርዳቹህ ላለው እራስ ወዳድነት ጠባያቹህ ሳትሸነፉ ሥልጣናቹህን በሰላም ለሕዝብ አስረክቡ፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
amsalugkidan@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: