The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

አንድነት ከማን ጋር? – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

ቡዕ ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፮

አንድነት ከማን ጋር?

• የተለያዩ ወገኖች የሚያቀርቧቸው የአንድነት ጥሪ ጥያቄዎች፣ የዐማራውን መቀበሪያ ጉድጓድ፣ ዐማራው ራሱ እንዲቆፍር የሚያዘጋጁ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ያሻል!

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማን ለማሥፋፋት የወጣውን ማስተር ፕላን ተግባራዊነት በመቃወም ሕዝባዊ አመጽ መቀስቀሱ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝን የሚቃወሙ፣ የፖለቲካ፣ የሲቪክ እና የሙያ ማኅበራት ድርጅቶች የሚያሰሙት የአንድነት ጥያቄ ይበል የሚያሰኝ ነው። ጥያቄው ዕውነት እንደሚሉት ከሐቅ የቀረበ ከሆነ ደግሞ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከልብ የሚቀበለው ጥያቄ ነው። ለጥሪው አዎንታዊ መልስ መስጠት ያለብንም፣ አንድነት መልካም ነገር ስለሆነ ነው። «አንድነት» ቃሉ ራሱ ለጆሮ የሚጥም፣ ለኅሊና የሚስማማ ነው። መልካምነቱም፥ አንድነት፣ ውበት፣ ኃይል፣ ጥንካሬ እና የማድረግ ብቃትን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ነው።
ለዚህ ዓይነቱ ጥሪ የትናንቶቹም ሆኑ የዛሬዎቹ የዐማራው ልጆች፣ ቀስቃሽ የሚያሻቸው አይደሉም። ምክንያቱም ዐማራው ሲፈጠር ጀምሮ አንድነት፣ ኅብረት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚሉት ጽንሰ ኃሣቦች ለአስተሳሰቡ እና ለአመለካከቱ ምሕዋር በመሆናቸው ነው። እናም ዐማራው ስለአንድነት ጥሪ ተቀባይ ሳይሆን፣ ጠሪ ነው። ይህም ባለፉት 25 ዓመታት ሁሉም ነገዶች የወያኔ እጄታ ሆነው በዐማራው ላይ የጥፋት እጃቸውን አንስተው ሲገድሉት፣ ሲያስሩት እና ሲያፈናቀሉት፣ ዐማራው በተቃራኒው «አንድነት ወይም ሞት!»፣ «ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት!» ብሎ የቆመ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ አቋሙም በትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ እንደ ዐማራው የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል የተፈጸመበት፣ በአውራ ጠላትነት ተፈርጆ በፕሮግራም ሠፍሮ በተግባር ከ5ሚሊዮን በላይ ሰው የጠፋበት ነገድ የለም። በወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል ስም የሚያመክን ክኒን የተሰጠው፣ ኤች.አይ.ቪ. ቫይረስ በመርፌ ሆን ተብሎ የተስፋፋበት ሌላ ነገድ የለም።

ዐማራውን ለዚህ ዓይነቶቹ የጥፋት ዘመቻዎች የዳረገውም «አንድነት»፣ «ኢትዮጵያዊነት» የሚሉት ጽንሰ ኃሣቦች አራማጅ በመሆኑ ነው። የትግሬ-ወያኔ ለተነሳበት ኢትዮጵያን በነገድ ከፋፍሎ ለማጥፋት ላነገበው ዓላማው፣ ዐማራው ተባባሪ እንደማይሆነው አስቀድሞ ያውቃል። በመሆኑም የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያን በነገድ ከፋፍሎ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በጠራው የሽግግር ጊዜው ምክር ቤት፣ ተወካይ ያልነበረው ዐማራው ብቻ እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ምክር ቤት የተገኙ የነገድ ድርጅቶች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ፣ የፀረ-ዐማራ ግለሰቦች እና ቡድኖች ስብስብ ነበር። ይህ ስብስብ ኢትዮጵያን አፍራሽ ለሆነው የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ መደላድል በመሆን፣ ዛሬ አገሪቱ ለምትገኝበት የውድቀት ደረጃ እንዳበቃት ማንም ይስተዋል አይባልም። የትግሬ-ወያኔ ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ከፋፍሎ ዛሬ ለምናየው ሁለንተናዊ ጥፋት ዳርጎናል። ይህ ከታሪካችን አንዱ አሣፋሪ ምዕራፍ ነው። መነጣጠል ውድቀት መሆኑን መማር የነበረብን ከወደቅን በኋላ ሳይሆን፣ አስቀድሞ ነበር። ይህንንም ከቀደሙት አባቶቻችን መማር ነበረብን። የውድቀታችን መሠረቱ አባቶቻችን የሠሩትን እና የነገሩንን እንደተረት አይተን፣ ጥራዝ-ነጠቅ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን የነገሩንን ፈጠራ እና ልብ ወለድ እንደ ደረቅ ሐቅ አምነን፣ የእነርሱ ተከታይ በመሆናችን ነው። የእኛም ትውልድ ካለፈው መራራ ጉዟችን እንደተረዳነው፣ ኢትዮጵያውያን ውሕድ አካሎች እንጂ፣ የተነጣጠልን አይደለንም። ስለዚህ በዚህ ወቅት የተናጠል ጉዟችን የትም እንደማያደርስ ተገንዝበን በአንድነት ለመሰባሰብ መፈለጋችን እሰየው የሚባል ነው። ዞሮ ዞሮ ፈጽሞ ሣያደርጉ ከመቅረት ዘይግቶም ቢሆን ወደ ትክክለኛው መንገድ መምጣት የተሻለ ነውና። ስለዚህ የአንድነት ጥሪው የዘገየ ቢሆንም፣ ለወቅቱ ችግር መፍቻ ተገቢው መልስ ነው።

የአንድነት ጥሪው ግን ከዕውነት፤ ከልብ የቀረበ መሆን ይገባዋል። ዐማራው ምንጊዜም ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት የቆመ መሆኑ ባያጠራጥርም፣ በእርሱ ፈጽሞ ጥፋት እና በእርሱ መቃብር ላይ የሌሎች ማንነት እንዲለመልም የሚሻ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ባለፉት 25 ዓመታት ዐማራው በዘረኛው የትግሬ-ወያኔ እና የእርሱ እጄታ በሆኑ ቡድኖች የደረሰበት ሁለንተናዊ ግፍ የሚዘነጋ አይደለም። ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ነገዶች እና ጎሣዎች ተወላጆች ሆን ተብለው ተነጥለው የመፈናቀል፣ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች የተፈጸሙባቸው ዐማሮች፣ ባለፉ ጊዜያት የደረሱባቸውን በደሎቻቸውን ሁሉ ያለምንም የወደፊት የኅልውና ዋስትና ትተው ወደማያስፈልግ የይስሙላ እንድነት እንዲመጡ መጠበቅ የለበትም። ስለሆነም የሚቀርቡት የአንድነት ጥያቄዎች የዐማራ ነገድ አባሎችን እና በእነርሱ ስም የተደራጁ ድርጅቶችን መሠረታዊ ሥጋቶች የሚያለዝቡ ሊሆኑ ይገባል ብለን እናምናለን። በመሠረቱ ዐማራው ለዕኩልነት፣ ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሰላም፣ ለመቻቻል፣ እንዲሁም አብሮ ለመኖር ባይተዋር አይደለም። በታሪክም እንደሚታወቀው ዐማራው ለእነዚህ ዕሴቶች ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ እና ለመክፈልም የተዘጋጀ ነገድ ነው። ሆኖም ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት በአገራችን የተካሄዱት የፖለቲካ ትግሎች ዐማራውን ያገለሉ እና በጠላትነት የፈረጁ መሆናቸውን ዐማራው ከደረሰበት እጅግ መራራ የሆነ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተምሯል። ይህ ክፉ እና ዘግናኝ ጥፋት ከዐማራው ትውልድ አዕምሮ ሳይጠፋ እና ያንን የሚያስረሳ ሁኔታ ሳይፈጠር፣ እኒህንም በደሎች ለመካስ ምን ምን ነገሮች መሠራት እንዳለባቸው በጋራ ሳንመክር፣ «የእንተባበር» ጥሪዎች ከዚህም ከዚያም ይነሣሉ። አሁን ባለንበት ወቅት እንኳን «የእንተባበር» ጥያቄው መነሻ በሆኑት ሕዝባዊ አመጾች መቀጣጠል የተነሳ ዐማራው በዘሩ ተለይቶ የጥፋቱ ሰለባ ሲሆን እያየን ነው። በተቃራኒው ግን፣ የአንድነት ጥሪ የሚያቀርቡ ወገኖች በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥፋት ከማውገዝ እና የደረሰውን ችግር ሕዝብ እንዲያውቀው ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ጥፋቱን ለመሸፋፈን ሲሞክሩ ይታያሉ። ስለሆነም ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርበው የአንድነት ጥሪ ከልብ ሣይሆን አፋአዊ፣ ለሥልጣን ለተዘጋጁ ወገኖች መረማመጃነት ዐማራውን ለጥይት ማብረጃ ለማድረግ እንጂ፣ ከዕውነት ለሕዝቡ ነባር አንድነት ዳብሮ መቀጠል ከመነጨ ውስጣዊ ፍላጎት የመጣ አለመሆኑን እነዚህ ቡድኖች የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በተጨባጭ ይመሰክራሉ።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ይህን ለማለት የተገደደው በሚከተሉት አብይ ምክንያቶች ነው።

አንደኛ፦ «የኦሮሞ ተወላጆች የአዲስ አበባ ከተማን ለማስፋፋት የተዘጋጀውን ማስተር ፕላን ተግባራዊነት በመቃወም አስነሱት» እየተባለ በስፋት የሚዘገቡት ዜናዎች እና ዘገባዎች፣ እንቅስቃሴው በኦሮሞ ተወላጆች ብቻ እንደተጀመረ፣ የእንቅስቃሴውም ብቸኛ ተዋንያን ኦሮሞች እንደሆኑ የሚሳይ ነው። አንድ እንቅስቃሴ የሚጀመረው ከአንድ ቦታ፣ በአንድ ሰው ወይም ቡድን መሆኑ ነባራዊ ዕውነታ ነው፤ ይህን መለወጥ አይቻልም። እንቅስቃሴው ሁሉን-አቀፍ እንዲሆን ግን ማሳወቅ እና ማስተባበር ከእንቅስቃሴው ጀማሪዎች ይጠበቃል። ለዚህም የሚረዳው የእንቅስቃሴውን ዓላማ አገር አቀፍ አድርጎ ማሳየት ነው። ሆኖም ይህ ሲደረግ አይደመጥም። የሚደመጠው ዜና የአንድ ነገድ እንቅስቃሴ፣ መስዋዕትነት የሚከፍሉትም የአንድ ነገድ አባሎች እንደሆኑ ነው። ይህን ለማረጋገጥ የአቶ በቀለ ገርባን መግለጫ ማዳመጥ ይበቃል። የአንድነት ጥሪ የሚያቀርቡ ቡድኖች እና ድርጅቶች ኃሣባቸውን፣ «የኦሮሞ ሕዝብ ትግል» ብለው ጀምረው፣ የሚጨርሱት «ድል ለኦሮሞ ሕዝብ» እያሉ ነው። የሚያቀርቡትም ጥሪ «የኦሮሞን ሕዝብ እንቅስቃሴ ተቀላቀሉ» የሚል ነው። ገና ከመነሻው ይህ አባባል አግላይነት አለው። አቅጣጫውም «ትግሉን የሚመራው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፣ እናንተ ተከተሉን እንምራችሁ» የሚል እንደምታ አለው። ከልብ በአንድነት ለመታገል ከፈለጉ ግን መባል ያለበት ትግሉ የትም ይሁን የት፣ መሪው ማንም ይሁን ማን፣ ፀረ-ወያኔ መሆኑን ማሳየቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ያገባል።

ሁለተኛ፦ በእንቅስቃሴው በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ደረሰ ከሚባለው ጥፋት የበለጠ የተጎዱት የዐማራው ነገድ አባሎች ናቸው። ለአብነትም ያህል ይህን እንቅስቃሴ መነሻ በማድረግ በአገር ቤት የሚታተመው «የቀለም ቀንድ» የሚባለው ጋዜጣ በቁጥር 22 ቅጽ 3 በታሕሣሥ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ዕትሙ፥ በአመያ ወረዳ በሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች፦ ማለትም «አብቤ መድኃኒዓለም»፣ «ኩኖ ቁሊት (ቀርሳ ቁሊት)» እና «መሪ መገሪ (ባሬዳ)» በተሰኙት ነዋሪ የነበሩ የዐማራ ነገድ ተወላጆች ንብረት ውስጥ 1,000(አንድ ሺህ) ቤቶች ማጀት በጎረሰ፣ ደጃፍ በመለሰ ያለ የሌለ ንብረታቸው ከነቤቶቹ ተቃጥለው ወደ አመድነት ተቀይረዋል። በእያንዳንዱ የቀበሌዋ ነዋሪ ዐማራ ከ70,000 (ሰባ ሺ) እስከ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ብር የሚገመት በርበሬ ተቃጥሏል (አባሪ ፎቶግራፍ ይመልከቱ)። የሦስቱ ቀበሌ ነዋሪዎች ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተሰድደው ለርሃብ እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል። ከቤቶቹ መቃጠል ሌላ የአምስት ዐማሮች ሕይዎት አልፏል። በጋዜጣው ዘገባ መሠረት፣ የዐማሮቹን ቤቶች እየነጠሉ ያቃጠሉት ሰዎች የኦሕዴድ እና የኦነግ አባሎች መሆናቸው፣ ለዚህም በፖሊስ ምርመራ ወቅት መታወቂያቸው መያዙን ጋዜጣው ይፋ አድርጓል። «የዐማሮቹ ቤቶች ተነጥለው እንዲቃጠሉ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? ዐማራዎቹ ምን ወንጀል ሠርተዋል?» የሚሉትን ጥያቄዎች ቤቶቻቸው ለተቃጠሉባቸው ሰዎች ጋዜጠኛው ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ አንድና አጭር ነው። መልሳቸው «ወንጀላችን ዐማራ መሆናችን ብቻ ነው» የሚል እንደሆነ ጋዜጣው ዘግቧል። አዎ! ዐማራው አገር የሌለው፣ ያገኘ የሚያርደው የፋሲካ በግ ከሆነ ዓመታት ተቆጠሩ። ይህ ግፍ እና በደል በዜና ዘጋቢዎች እና በፖለቲከኞች ንግግሮች ትኩረት አልተሰጠውም። በተጨማሪም በንቅናቄው ዐማራው ሆን ተብሎ የጥቃቱ ሰለባ መሆኑ አይዘገብም። ስለሆነም የሚቀርበው የ«እንተባበር» ጥሪ «እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳበላ ግፋው» ዓይነት ነው።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ አመያ ወረዳ በጅምላ ከተቃጠሉት የዐማሮች መኖሪያ መንደሮች አንዱ (ምንጭ፦ የቀለም ቀንድ ጋዜጣ)

ሦስተኛ፦ የትግሬ-ወያኔ ሰሜን ጎንደርን ወደ ትግራይ ለማጠቃለል ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ጥቂት የቅማንት ተወላጆች፣ ጎንደር ተወልደው ካደጉ ትግሬዎች ጋር አቀናጅቶ ባዘጋጀው የመነጣጠል ሤራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዐማራ በጭልጋ፣ በደንቢያ፣ በመተማ፣ በቋራ እና በጎንደር ከተማ በግፍ ተገድሏል። ከሁሉም በላይ ከ80,000(ሰማንያ ሺህ) ስኩዬር ኪሎሜትር በላይ ስፋት ያለው የምዕራብ ኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ገጸበረከትነት ቀርቦ እያየን እና እየሰማን የምንጮኸው ድምፅ ጎልቶ አይሰማም። ስለዚህ ዝምታው «በዚህ አካባቢ ተጎጂውም ዐማራ፣ መሬቱም የጎንደር ነው» የሚል እንደምታ ያለው አስመስሎታል። አንድ የሚያደርገን ከዚህስ የከበደ ምን ብሔራዊ አጀንዳ ይኖራል? የብሔራዊ አንድነት መገለጫ ከሆኑት አንዱ ዳር ድንበር መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም የሰሞኑ የ«አንድ እንሁን» ጥያቄ ይህን አጀንዳ የኔ ብሎ መያዝ ይገባዋል ብለን በጽኑ እናምናለን።

ከሁሉም በላይ የአንድነት ጥሪው ተገቢውን መልስ እንዲያገኝ፣ ካለፉት የእርስ በእርስ መጠላላፎች ተምረን ወደፊት በአዲስ መንፈስ እና ወኔ ለመጓዝ እንድንችል፣ ሁሉንም የትግሬ-ወያኔ ተቃዋሚ ኃይሎች ሊያሰባስብ የሚችል የግንኙነት እና የአሠራር ሥልት ሊነደፍ ይገባል። ለዚህም ጊዜ ሳይወስድ የሚመለከታቸው አካሎች ተገናኝተው በአንድነት ሊሠለፉ የሚያስችሏቸውን ጉዳዮች ነቅሰው ከማውጣት ጀምሮ፣ ከትግሬ-ወያኔ በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ አመላካች የሆነ ንድፈ-ኃሣባዊ ቀመር ሊያወጡ ይገባል። ከዚህ ስምምነት ላይ እንዲደረስ «በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል» የሚሉ ኃይሎችን እና ቡድኖችን አሰባስቦ ወደ ተፈለገው ግብ ሊያመሩ እንዲችሉ የሚገናኙበትን እና የሚወያዩበትን መድረክ የሚያመቻች አንድ ወገን ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። ይህን ኃላፊነት አባቶቻችን እንደሚሉት «ሊታረቅ የፈለገን ንጉሥ፣ እረኛ ሽማግሌው ይሆናል» ነውና፣ ዕውነት አንድነቱን፣ መስማማቱን እና አብሮ መሥራቱን ከልብ ከፈለግነው፣ የ«አንድ እንሁን»ን ጥሪ ከተቀበልነው፣ አስማሚ እና መድረክ አዘጋጁ ማንም ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ቀና ከመሆን የሚመነጭ ሊሆን ይገባል። ስለሆነም ይህን መድረክ የማመቻቸቱ እና የማገናኘቱን ኃላፊነት፣ (1) ከሕጋዊው እና የስደተኛው ሲኖዶስ አባቶች፣ (2) ከእስልምና እምነት መሪዎች (3) ከፕሮቴስታንት እና ከካቶሊክ እምነቶች አባቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ኃላፊነቱን ቢወስድ ሁሉንም የሚያስማማ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። የመወያያ አጀንዳዎችን ለመቅረፅ፣ «ያገባኛል» የሚሉ ወገኖች የየራሳቸውን ኃሣቦች አዘጋጅተው ለዚህ ኮሚቴ ቢሰጡ ሂደቱን ለማፋጠን ይጠቅማል። ኮሚቴውም ከሁሉም ወገኖች በተወከሉ ሙያተኞች እየታገዘ ሥራውን በአስቸኳይ ቢጀምር ለሚፈለገው የአንድነት ጥሪ ተገቢ መልስ ለመስጠት ከማስቻሉም በላይ፣ የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ግብዓተ-መሬት ያፋጥናል። ዐማራው ከአንድነት የበለጠ እና የከበደ አጀንዳ የለውም። አባቶቻችን «የሞትንም እኛ የነገሥንም እኛ» እንደሚሉት፣ ያለፈውን ጥፋት ለፍትሕ ጉዳይ ትተን፣ ወደፊት የሁላችንም መኖሪያ ለምትሆነው አገራችን አንድነት እና ሰላም መቆም እንችላለን። ስለዚህ ከየአቅጣጫው የሚቀርበውን የአንድነት ጥሪ የምንቀበለው፣ በአንድነቱ ዐማራው ባያተርፍም ተጎጂ እንደማይሆን ስለምናምን ነው።

የኢትዮጵያ አንድነት በቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ተጠብቆ ይኖራል!

 

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: