The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ዶሮ ብታልም ስለጥሬዋ | ለፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ እና ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ‘አማራ የሚባል ሕዝብ የለም’ አባባል የተሰጠ ምላሽ

በአበበ ተድላ፣ ሰኞ ታኅሣሥ 11 ቀን 2008 ዓም

 

የሰውን ስነልቦና ማወቅ ሰዎች የሚናገሩትና የሚሰሩት ለምን እንደሆነና የምን ሃሳብ ነፀብራቅ እንደሆነ ለመረዳት ይረዳል። ይሄንን ምእራባዊያንን ለምርጫም ለህክምናም ለሌላም ነገር ይጠቀሙበታል። ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል እንደተጠቀምንበት አላውቅም ግን ወደ ዋና ጉዳዬ  ወደ ገደለው ልግባ።

mesfin

የሞተው ለገሰ ዜናዊ ወላጆቹ የጣልያን ባንዳ ሹምባሽ ስለነበሩ ከልጅነቱ ጀምሮ “አንተ ባንዳ” ሲባል ነው ያደገው። ስለዚህ ይሄንን ህመሙን ለማዳን ባንዳ ላለመባል መጀመሪያውኑ ቤተሰቦቹን ባንዳ ያሰኘው የወላጆቹ አላማ ሳይሳካ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር መኖርዋ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ስራ ዳር ማድረስ አለበት። በዚህም ምክንያት “የኢትዮጵያ መሪ” ተብሎ “ኢትዮጵያ” የሚባለውን ስም ሳይጠራ “ሃገሪቱ” እንዳለ፤ “ኢትዮጵያዊነት ላይ ሙጭጭ ብለዋል” ያላቸውን አማራ እስከህይወት ፍጻሜው ሲያጠፋ እና ሲያስጠፋ ኖሮ ከበሽታው ሳይድን ሞተ።

ፕ/ር መስፍን እና ፕ/ር ጌታቸውም እንዲሁ ከተለያየ ብሄር ስለተወለዱ ህይወታቸውን ሙሉ ምርምር አካሂደው በመጨረሻ ሰበር ዜና ብለው ያቀረቡልን ውጤት የነሱን ስሜት ሊያረጋጋ የሚችል የመሰላቸውን “አማራ የሚባል ህዝብ የለም” የሚለውን ሃሳብ ነው። ወገን እንግዲህ ሰው ከታመመ መርዳት ነው; የአእምሮ ህመም ደሞ ሲጀመር ችግር እንዳለባቸው ስለማይገባቸው ህክምናው ትንሽ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በቃ ታመዋል መታከም አለባቸው። ዝም ግን ሊባሉ አይችሉም፤ ምክንያቱም ጊዜ ወይንም አጋጣሚ ያገኘ እብድ በሽተኛ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ከተቻለ ማከም አለበለዚያ ተይዘው እስከሚድኑ ከህዝብ መገለል አለባቸው፤ አለበለዚያ ጉዳታቸው የከፋ ነውና። ከምንም በላይ ጥፋታቸውን የሚያከፋው ደሞ ይሄንን የህይወት ሙሉ የጥናት ውጤት ልፋታችን ያሉትን (ለነገሩ ሳይለፋ የሚታወቅ ሃቅ ነው) ህዝቦች  በተለያየ ምክንያት ስለተቀላቀሉ “ይሄ ብሄር” ብሎ ጠርቶ “የሱ ቦታ እዚህ ነው በኢትዮጵያ ውስጥ” ማለት ስለማይቻል “የአማራ የኦሮሞ ወይም የትግሬ ወዘተ” ማለት አንችልም ብለው መደምደም ሲገባቸው (ያለጥናት ይሄም ማንም መንገደኛ ይነግራቸዋል) እነሱ ግን ይሄ አስተሳሰብ አማራ ላይ ብቻ እንዲሰራ አድርገው ሌሎችን ፈርተው ይሁን ምን ይሁን በማይታወቅ ምክንያት “አማራ የለም ሌላው ብሄር አለ” አሉን። ትልቅ ሰው በባህላችን ስለማይሰደብ እንጂ አሳፋሪዎች እላቸው ነበረ!

ሰው ያደገበት ሁኔታ ምን ያህል አስተሳሰቡን እንደሚቀይረው የታወቀ ቢሆንም ይቺን ምሳሌ ልጨምር። አንዱ አዲስ አበባ ሲያድግ በጣም የሽንት ቤት ችግር ያለበት ቦታ ስላደገ፤ በለስ ቀንቶት አድጎ ገንዘብ ኖሮት ቤት ሲሰራ መጀመሪ ያስጨረሰው ሽንት ቤቱን ነው። ትልቁ ደስታውም ሽንት ቤቱን ማየት እና ማሳየት እንደነበረ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል።

በተመሳሳይ ምሳሌ ብዙ አማራውች በትህነግ (ወያኔ) እና አጋሮቹ በደል ብዛት ምክንያት አሁን ላለው ስርአት ያለን ተቃውሞ ተመሳሳይ ቢሆንም በአብዛኛው አማራ ያለበት ቦታ ያደገ አማራ እና በተለይ አሁን ትህነጎች መስመር ሰርተው “ያለክልሉ ያለ” ተብሎ ያደገ አማራ ስለ ብሄር አከላለሉ የሚያደርገው ተቃውሞ ደረጃ ይለያያል፦ የደረሰበት ያውቀዋልና። በገዛ ሃገር አገር አጥቶ ከመኖር የበለጠ ህመም እንደሌለ ይሄ ስርአት ሚሊዮን አማራዎችን በገዛ ሃገራቸው ያል ክልላቸው የሚኖሩ እያሉ ሃገር እንዳሳጣ እና ለእልቂት እንደዳረገው ኖሮ አይቶታልና። ታዲያ ዶሮ ብታልም ስለጥሬዋ ይሄንን ርእስ አይገልጠውም ትላላቹ?

Getachew Haile
“ምን ይሻላል ለምትሉ” ሁሌ የምንለውን አሁንም ደግሜ አቀርበዋለው። በፖለቲካ ብላቴናዎች ብንሆንም እነሱን እንደምንሰማው እኛንም ቢያዳምጡን፣ የምንለውን ቢሰሙን፣ ለዘመናት አጠናን ካሉት የተሻለ ሃሳብ ሊያገኙም ይችሉ ይሆናል። ጆሮ ይስጡን እንጂ መፍትሄውን እኛ ጋር ሊሆን ይችላል!

ሁሌም እንደምንለው ኢትዮጵያ ውስጥ አማራም፤ ትግሬም፤ ኦሮሞም ሌላም ወደ ሰማኒያ የሚጠጋ ብሄር አለ። በዛው ልክም ደግሞ ከተለያዩ ብሄሮች ተቀላቅለው የተወለዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ለዚህም እኮ ነው “የትህነግን የአፓርታይድ አከላለል ልክ አይደለም፤ አንደኛ አማራ ተወካይ በሌለበት ነው የተሰራው፤ ሁለተኛ የተቀላቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ሃገር ያሳጣል፤ አንዱን ወይንም ከዛ በላይ ወገናቸውን ክደው አንዱን እንዲመርጡ ህዝቦችን ያስገድዳል” ያልነው። የተቀላቀሉ ብሄሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ እና አማራም ከተቀላቀሉት አንዱ ሆኖ ሳለ “አማራ ብቻ የለም” ማለት ግን አይቻልም። አማራ ተቀላቅሎ ከጠፋ ሌላው ከአማራ ጋርም የተቀላቀለው ጠፍትዋል ማለት ነው እንጂ አማራ ብቻውን እንዴት ይጠፋል? የለም ይባላል? ብሄር መጥራት እናቁም የሚል የፖለቲካ አቅዋም ማራመድ ሌላ ጉዳይ ነው ግን “ብሄር መጥራት እናቁም” ማለት አማራን ብቻ ለይቶ “አማራ የለም” ማለት አይደለም። እንዲህ የሚያደርግ ሰው  በአማራ ላይ ትህነግ ለሚያደርሰው ጥቃት አባሪ እንደሆነ ነው የምንቆጥረው።

መፍትሄው እንዲህ ነው፤

“ኢትዮጵዮያ ውስጥ ብዙ የተቀላቀለ ብሄር አለና ብሄር ሳይጠራ ኢትዮጵያዊ ብቻ ተብለን እንኑር” የምትሉ መብታቹ ነው፤ ሃሳባቹን አራምዱ፤ ዲሞክራሲ ካለ ህዝቡ የወደደውን ይመርጣል። እንዲሁም “ብሄሬ እንዲጠራ” የሚለውን ቡድን “ፈጽሞ አይቻልም” እንዳትሉት። ነገር ግን “ብሄር የለም” ማለት አማራን ብቻ እንዲመለከት ማድረግ ለዚህም መረጃ “ድሮ አማራ ያልነበረ አማራ ሆነ” ብላቹ በተመሳሳይ ድሮ ኦሮሞ ያልነበረ ዳሞት፤ ፈጠጋር፤ አንጎት፤ እናራያ፤ ወዘተ ዛሬ ተቀይሮ “ኦሮሞ” የተባለ መሆኑን ለትግሬውም እንዲሁ ሌላውን ውጠው ትግሬ እንደተባለ አለመናገር ግን ሸፍጠኝነት ነው።

“ብሄራችን ቀድሞ እንዲጠራ እንፈልጋለን” ለምትሉም መብታቹ ነው። ይህንን አላማቹን አስፋፉ፣ ስበኩ፣ ችግር የለብንም። ግን አንድ ብሄር የራሱን መብት ይከበር ሲባል የሌሎች አብረው የሚኖሩ ብሄሮች መብት ተጥሶ ወይንም በገዛ ሃገራቸው በናንተ መልካም ፍቃድ እና ችሮታ ብቻ እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው አይነት ስርአት ለመዘርጋት አትሞክሩ እንጂ።  “ምሁራን ነን፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት እንዲከበር እንታገላለን፤” የምትሉ ኦሮሞውንም፣ ትግሬውንም፣ ገና እየተደራጀ ያለውንም አማራ፣ “የብሄሬ መብት ይጠበቅ ማለት ትችላላቹ። ግን የብሄሬ መብት ይጠበቅ ስትሉ የሌላውን ብሄርም ይሁን የተቀላቀሉትን መብት አለመጣሳቹን አስቡ” ነበር ማለት የነበራቸው እንጂ በደፈናው “አማራ የለም” በማለት ሰዎችን ከብሄርተኝነት ሃሳብ እናወጣለን ብላቹ እንዳታስቡ። ይሄ አማራው ተለይቶ በአማራነቱ በመላው ኢትዮጵያ ጥቃት እየደረሰበት “ድሮ ጨቋኝ ነበር” እየተባለ ጥላሸት የሚቀባበትን ህዝብ ራሱን ለማደራጀት ሲል አንዴ “የለም”፣ አንዴ “አማራ እንዴት ይጠባል”፣ እያሉ አማራን እንዳይደራጅ እና ራሱን ከጥፋት እንዳያድን ማድረግ አማራን ይጎዳል፣ ሌሎችን ይጠቅማል እንጂ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም፤ አማራ በሆነው ባልሆነው ሲወዛገብ ጠባቦች የማጥፋት ስራቸውን ይቀጥላሉና። እንዴት ነው “ኦሮሚያ” ብለው የከለሉት ውስጥ ያለው መሬት “የኦሮሞ እንጂ በውስጡ ያሉ ህዝቦች አይደለም” ተብሎ ሌላውን እንግዳ ያደረገ ተፅፎ ያለን ስርአት ሳይቃወሙ ምሁራን ተብዬውች “አማራ አለ፣ የለም” የልጅ እቃ እቃ ጨዋታ  ውስጥ የሚገቡት? በኔ ይሄ እንዲያውም “አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ መሬት የሆነ ብሄር ብቻ ነው” ማለት የአንድን ብሄር የበላይነት ስርአት መዘርጋት እንጂ እኩልነት አይደለም፤ ወይንም ቁርጥ ባለው “አገርህ አይደለህም” ልክ ሌላ ሃገር ኬንያ ወይንም ግብፅ እንዳለው ተደርጌ “ባልንህ እስከኖርክ አብረህ ትኖራለህ” ተብዬ በገዛ ሃገሬ ስደተኛ እንደሆንኩ በግልፅ ሊነገረኝ ይገባል፤ ከዛም ምላሼን ሰጣለው። አንድ ሰው ከሆነ ክልል ጋር ራሱን ካላስተሳሰረ ኢትዮጵያዊ መሆን በህገመንግስት ተብዬው መከልከሉን መቃወም ሲገባቸው ምሁራን የተባሉ፣ በተለይ አማራው ወደኃላ ተመልሶ “አማራ አለ፣ የለምን” ክርክር ከምሁር አንጠበቅም (ሌላውማ ህገመንግስት ተብዬውን ራሳቸው ስለፃፉት አፈፃፀም እንጂ ህገ መንግስቱ ችግር የለበትም ይሉናል አማራ በሌለበት እንዳፀደቁት እየታወቀ) ።  “አማራ ባህሉን ጫነብኝ” ብለው የተቆጡ መልሰው የአማራን ባህል ወስደው “ለምን አማራን አዲስ ባህል ተሰጠው” ብለው አማራ እንዲጠፋ እየተደረገ ያለውንና እየተወሰደበት ስላለው ባህሉ መጮህ ነው የሚገባቸው የአማራ ምሁራን ነን ተብዬዎች ወይንስ “አማራ አለ የለም” ወደሚል የጅል አታካራ ገብቶ አማራውን አወናብዶ ራሱን ከተደገነበት ጥፋት ማዳን እንዳይችል ነው ማድረግ ያለባቸው?

አማራነት ብቻ ነው በደም ውስጥ ያለውም እንበል፤ አማራ ከሌላ ብሄር ጋር የተቀላቀለብኝ ነኝ እንበል፤ “አማራ” ተብሎ አንድ ህዝብ ተለይቶ ሲጠቃ እንክዋንስ አማራነት እያለብኝ፤ ሰው በመሆኔም እታገላለው። “አማራ ነን” ወይንም “ለሰው ልጅ መብት እንከራከራለን” የሚሉ ኢትዮጵያዊያን፣ ሌሎች በብሄር የተደራጁ ኢትዮጵያዊያን አማራውን መብቱን ሳያከብሩ፣ ተወካይ እንክዋን ሳይኖረው፣ ያልነበረ መስመር  ትህነግ እና ወዳጆቻቸው አስምረው፤ “የብሄር ብሄረሰብ መብት አከበርን” ማለታቸውን ደጋግመው ሊቃወሙ ሲገባ፣ ይባስ በተለይ በዚህ ሰአት በማያስፈልግ “አማራ አለ፣ የለም” በሚል ጊዜያችንን ያባክናሉ።  የብሄር ብሄረሰብ መብት ሲባል አማራን አይጨምርም እንዴ? በኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት መኖር “አማራን እኩል ሆኖ ይኑር” የሚል መብት ሊሰጥ አይገባም እንዴ? ይሄንን እውነት ተናግረን ችግሩን ከነመፍትሄው ብናቀርብም ከመስማት ይልቅ “ጠባቦች፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች” ሌላም ሌላም እንባላለን፤  ዋናዎቹ ጠባቦች ራሳቸው ሆነው ሳለ።

እንግዲህ አማራውን ስቃዩን ያረዘመበት  “በኢትዮጵያዊነት ጎራ ስር ነን፤ በብሄር አንደራጅም” ያሉት “በኢትዮጵያ  ስም እንደራጅ” ይሉና የአማራን በደል ግን አይናገሩም። የአማራ ድርጅት ላለመባል “ኢትዮጵያን አልፈልግም” ብሎ መስመር አስምሮ ባንዲራ ፈጥሮ የሚታገለውን ግን ለማባበል ብዙ ርቀት ሄደው ስለሱ ቡድን አብረው ይጮሃሉ። ይሄም አልበቃ ብሎ አልፎ ተርፎም “አማራ የለም” ይሉታል። በብሄር የተደራጁት ደሞ የነሱን ብቻ መብት እንዲከበር ፈልገው አማራውን አገር አሳጥተው አንገቱን አስደፍተው ሊያጠፉት እየሰሩ ነው። ታዲያ የት አለ ኢትዮጵያዊነት? የታለ የብሄር መብት የተከበረው? እንዲህ ያለ ትክክለኛ ጥያቄ ከነመፍትሄው የምናነሳውን ፕ/ር ጌታቸውና ሌሎች “ጸረ-ኢትዮጵያ” አሉን እንግዲህ ማን እንደሆነ ጸረ-ኢትዮጵያ ልብ ያለው ልብ ይበል። ይሄ የሶሻሊስት አመለካከት “ከኔ ሃሳብ ውጪ ያለው ጠላቴ ነው፤ መጥፋት አለበት” አስተሳሰብ ካልለቀቀን ወደፊት መራመድ በጣም አስቸጋሪ ነው።

“ብሄራችን የተቀላቀለ ነው መደራጀት፤ ያለብን በኢትዮጵያዊነት ነው፤” ብለው የሚያምኑ ማለት የነበረባቸው ደግሞ “አሁን ያለው ስርአት ከተለያየ ብሄር ለተቀላቀሉ ህዝቦችን መብት የሚነፍግ እና አንድ ብሄር የግድ ስለሚያስመርጥ የተሳሳተና መቅረት ያለበት ነው፤” ማለት እንጂ ይሄንን ሃሳብ ለመናገር “አማራ የለም፣ ሌላው ብሄር አለ” ማለት ሚዛን አይደፋም። እኩልነት መብት ከሆነ አብረን ነን። ነገር ግን “የሁላችንም መብት የተከበረባት ሃገር ይኑረን” ብላቹ ነው መነሳት የነበረባቸው እንጂ፣ ገና ለገና ስትነሳ “በብሄር መደራጀት ልክ አይደለም” ብለህ አማራውን ብቻ ለይተህ “የለህም” ካልክ እንዴት ነው ከአማራው ጋር አብረን ሰርተን ነፃ እንውጣ የምትለው?  ወይ “ምንም ብሄር አንጥራ” ካላቹ ሁሉንም ብሄር አትጥሩ። ብሄር ጠርቶ አማራውን ለይቶ “የለም” ማለት ግን የትም አያደርስም፤ ምናልባት አማራውን ለመጉዳት ካላሰባቹ በስተቀር።

ስለዚህ ሲጠቃለል አማራም፤ ኦሮሞም፤ ትግሬም ሌላም አለ በጣም በርካታ ብዙ ሚሊዮን ከተለያየ ብሄር የተቀላቀሉም እንዲሁ አሉ። ከተቻለ “ብሄሬ ተጠርቶም” ይበል “ብሄሬ ሳይጠራ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሌሎችን መብት ባልነካ መልኩ ብዙሃን ድምፃቸው እየተከበረ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው በብዙሃኑ ተፅእኖ ሳይደርስባቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አስማምቶ አንዱ አንደኛ ዜጋ አንዱን ሁለተኛ ዜጋ ሳያደርግ የሚያስችል ስርአት መፍጠር ነው። ይሄ ስላልሆነ “ከአማራ በስተቀር ሌሎች በብሄር ስለተደራጁ ብቸኛ ከተለያየ ብሄር የተቀላቀልነው ሃገር ኖሮን ለመኖር የምንችለው አማራ የለም ብለን አማራው እየጠፋም አማራው ሳይደራጅ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ይቆይልን” የሚለው አያስኬድም፤ አማራ ከጠፋ ኢትዮጵያም ትጠፋለችና። ይልቅስ “አማራውም ሌላውም ብሄር አለ፤ የተቀላቀሉም ብሄሮች አሉ፤ ስለሆነም አሁን ያለው ስርአት ለሁሉም መብት ስለማይሰጥ ልክ አይደለም” ብላቹ ስርአቱን ተቃወሙ እንጂ “አማራ የለም” በሚል ስርአቱ ሊያጠፋው የወሰነበት አማራ ላይ ሌላ አጥቂዎች አትሁኑ።

በተመሳሳይ መልኩ “በብሄር ተደራጅተን ብሄራችን ተጠርቶ እንኑር” ያላቹም እሰየው ቀጥሉ። ግን እናንተ የረገጣቹትን ሁሉ “የኛ” ብላቹ በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ “ያለክልሉ የሚኖር” አስብላቹ እየገደላቹ እያሰደዳቹ፤ እናንተ “በአማርኛ አንማርም፣ አንሰራም፣ ቋንቋችን ስላልሆነ” ብላቹ በሚሊዮን የሚቀጠር አማራን በናንተ እንዲማር እንዲሰራ አስገድዳቹ፤ አማራው ባልተወከለበት የአፓርታይድ ድንበር አበጅታቹ፣ ምን አይነት እኩልነት እንደምታወሩ አይገባኝም። ስለዚህ እኩልነት ከተባለ አማራውም እኩል መብቱ የተከበረበት እና በገዛ ሃገሩ በሌሎች መልካም ፍቃድ ሳይሆን ሃገሩ ስለሆነ በራሱ መልካም ፍቃድ የሚኖርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ምንም እኩልነት እንደሌለ እወቁት። እኩልነት ከሌለ ደሞ አመፅ፣ ጦርነት፣ ሞት ይቀጥላል። ይሄንን ደሞ የደም ጥማት ያለበት ሰይጣን ካልሆነ ሰው ይፈልጋል ብዬ አላስብም።

አማራው መውሰድ ያለበት እርምጃ መጀመሪያ መደራጀት ፤ በዚህ ሰአት “አማራ አለ፣ የለም” ብሎ የሚከራከሩትን ጅሎች ረስቶ፣ እንዲሁም የአማራ መደራጀት ለኢትዮጵያ መጥፋት ሳይሆን ለኢትዮጵያም ለአማራም እንደሚበጅ አስረግጦ፣ አማራ ተደራጀ ማለት ትህነግ እና ኦነግ ከኤህነግ ጋር ሆነው ያንተ ነው ብለው የሰሩለትን ድንበር ይቀበላል ማለት እንዳልሆነ ታውቆ፤ ከላይ እንዳልኩት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ተከብሮ አብረን እንኑር በሚለው ሃሳብ ይስማማል። ይሄንን እምቢ ብለው “አሻፈረኝ ደም የማፍሰስ አባዜ አለብን” ብለው “እኩል ሳይሆን የበላይ መሆን አለብን” ብሎ፤ “የኛ መሬት ሳይሆን የኔ ብቻ ነው” ብሎ ከገፋ መደራጀትህ ለመቼ ነውና ተገደህ ደም አፍስሰህ ያባቶችህን ድንበር አስከብረህ የ 3000 አመት ሌሎች አንፈልግም ያሉትን የኢትዮጵያ ታሪክን ተረካቢ መሆንህን አረጋግጠህ ለመኖር መቁረጥ ነው። ከዚህ ውጪ ስትልመሰመስ ምክንያት ስትደረድር ብትኖር የበለጠ መቀበሪያ ጉድጓድህን ትልቅ ታደርጋለህ እንጂ ለአማራም ለኢትዮጵያም አይበጅም።

አሁን እነ ፕ/ር መስፍን፤ ፕ/ር ጌታቸው ወይንም ሌሎች “ወይ አማራ ከተደራጀ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” የሚሉ ወይን ገፍተው “እንዲያውም አማራ የለም” የሚሉትን ትልቁን ስህተታቸውና ጦሱ በተለይ ለድሃው የሚያተርፈውን በዚህ መልኩ ላሳጥረው፥ ቢሆን ቢሆን የሁሉም ብሄር መብት ተከብሮ “ብሄር መጥራት መውረድ ነው” ለሚሉም “ኢትዮጵያዊ ብቻ” ብለው ራሳቸውን “ኢትዮጵያዊ” ብለው በተመሳሳይም ብሄሬ ይጠራ ለሚለውም በምርጫው ብሄሩ ሲፈልግ መታወቂያው ላይ ተፅፎለት (ምርጣው እስከሆነ) ለሁሉም ዜጋ መብት ተከብሮ የምንኖርባት ሃገር ቢኖረን ምንኛ ደስ ባለን። ይሄ ግን ትህነግ ስልጣን ላይ እያለና ከሱ በኋላ ለመተካት የሚንደረደሩትም ተመሳሳይ አቋም እስካላቸው ህልም ነው። ስለዚህ “አማራ ቢሸፍት እስከኢትዮጵያዊነት” ነውና አማራው ኢትዮጵያዊነቱን ሳይተው ኢትዮጵያ ሁሉም በእኩልነት የሚያምን በውስጥዋ ያለ ህዝብ ሁሉ ሃገር መሆንዋን ተቀብሎ ተደራጅቶ ራሱን ማዳን ነው። አማራው ከተደራጀ አሁን እንዲህ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ሁሉ ለመነጋገር ዝግጁ ይሆናሉ። አሁን ግን ማንን አይተው ማንን ፈርተው? “ኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት ይስፈን” ስንልም ሆነ “የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትይስፈን” ስንል ሰምተውን “አማራንም ይህ እኩልነት ይመለከተዋል” ይላሉ። አለም ጉልበት ላለው እንደምታሸረግድ አትርሱ። ስለዚህ አማራው ካልተደራጀ በአማራው ደም ሁሉም ጎጆውን እስኪያቀና ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ስምዋ ብቻ ይቆያል። በዚህም አያበቃም ሁሉም በውስጡ ያሉትን በተለይ አማራውን እያጸዳ አዲስ ሃገር ለመስራት እየተንደረደሩ ስለሆነ ግፋ ቢል የድንበር ግጭት ይጠብቃቸዋል እንጂ ኢትዮጵያ ከተበታተነች እንደ ትንሽ ሃገር መቆም ይችላሉ። አማራ ግን ልክ ኤርትራ የተባለችው ለኢትዮጵያ እንዲህ የቤት ስራ ሰጥታን እንደምትስቅብን ትህነጎችም ሸርፈው ሸርፈው የአማራ ብለው ከልለው ያስቀሩት ወደፊት እንክዋን ትንሽ ሃገር ሆኖ መቆም እንዳይችል ልዩ ዞን እያሉ፤ ትንንሽ ቁጥር ያላቸውን ሌላ የከለሉት ውስጥ ሳያደርጉ “አማራ” ብለው የከለሉት ውስጥ በመስራት ረዥም የቤት ስራ እየሰጡን ነው። ሲጀመር አማራ በሌለበት ስለሆነ የተከለለው አማራን ተሸፍሽፎ የቀረ 4ቱ ክፍለ ሃገራት ላይ ብቻ ትህነግ እንደወሰነው እንዳለ ሆኖ አማራ ብለው ከከለሉት እንዳያቹት ጎንደርን ትግሬ፣ ቅማንት፣ ሌላም እያሉ ያፋርሱታል። ጎጃምን አገው፣ ቤኒሻጉል፣ አማራ ብለው ያፋርሱታል። አንጎትን/ላኮመልዛን (አሁን ወሎ) አገው፣ ትግሬ፤ኦሮሞ፣ አማራ ብለው ያፋልሱታል። ሸዋን አማራ፣ ኦሮሞ፣ ወዘተ ብሎ አጣልቶ እንዳያቹት አማራ ብሎ የከለለው ቦታ ሁሉ ግጭት ፈጥሮ መጨረሻ ይቺንውንም እንክዋን ሳይኖረን አማራ ተበትኖ ጠፍቶ ታሪክ ሊያደርጉን እየሰሩ ነው (አስታውሱ እነ ሃረር፤ ባሌ፤ ፈጠጋር፤ እናራያ እነሱ ባይሉም ሃገራችን እንደሆነ ግን ጠንቅቀን እናውቃለን)። ልብ በሉ ልክ ዩጎዝላቪያ ላይ ሰርቦች ላይ የምእራባዊያን ዱላ እንደበረታ ችግር ቢነሳ አማራ ላይ ከምእራባዊያን ዱላ እንደሚበረታ እንዳትረሱ። ሰርቦችን በመጨረሻ ዩጎስላቪያ የሚለውን ስም እንክዋን እንዳይጠቀሙ ተከልክለዋል። ምን ይታወቃል ኢትዮጵያ ድንበርዋ ሲሰፋ ሲጠብ ኖርዋል ብለን አነስ ያለች ኢትዮጵያ ይኑረን እንክዋን ብንል ኢትዮጵያ የሚለው የነፃነት ነፀብራቅ ስሙ ስለሚያማቸው አገራቸውን ዩጎስላቪያ እንዳይሉ እንክዋን እንደተከለከለት ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንክዋን መጠቀም መከልከል ሊጠብቀን እንደሚችልም አትዘንጉት። ስለዚህ አማራ ጠላቱ ብዙ ሆኖ ሳለ በገዛ ህዝቦቹ እንዳይደራጅ ሰንካላ እየተፈጠረበት ከቆየ አይደለም ኢትዮጵያ አማራ በራሱ እንደህዝብ መቀጠሉ ጥያቄ ውስጥ ይገባል እና ልብ ያለው ልብ ይበል። እናማ የአማራ ምሁር ነን የምትሉ አስቡበት።

እባካቹ ይቺን ፅሁፍ የፖለቲካ ብላቴና ምላሽ ብሎ ፅፎላቹሃል ብላቹ ለፕ/ር መስፍን እና ለፕ/ር ጌታቸው ላኩልኝ። የፌስ ቡክ ተከታያቸው ስላልሆንኩ ለነሱ መላክ አልችልምና።

ወገን መጀመሪያ አስተሳባችንን እናጽዳ እንጂ ፖለቲካን የልጅነት ህመማችንን እና ያለብንን የስነልቡና ችግር የምናድንበት፤ ወይንም ላንዳንዶቹ ደግሞ የሃብት ማግኘት ጥማት ፍላጎታቸውን ማርኪያ፤ በሌሎች ደም ሃብት ለማካበት የምንጠቀምበት ዘዴ አናድርገው። መነሻውን መድረሻውን በግልፅ ያላስቀመጠ፤ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን እና ቅሬታዎችን በግልፅ አቅርበን ሳንወያይ እንዲያው በድፍንፍኑ “አንድ ላይ ነን” ብለን ውጤታማ እንሆናለን ማለት ዘበት ነው። ስለጋና ዲያስፖራዎች ስለሃገራቸው ምን እንዳደረጉ እና አሁን ለሰፈነው አንጻራዊ ዲሞክራሲ በምን ውስጥ እንዳለፉ ምን እርምጃ እንደተወሰደ እንድታነቡ ጋብዤ ልሰነባበት።

ጆሮ ያለው ይስማ!

አበበ ተድላ

zehabesha.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: