The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ሚሚየን እንዳያስሩብን ፈራሁ

እውነት ከ ምድር ቤት
እትየ ሚሚ በጋዜጠኞች ክብ ጠረቤዛ ላይ እሁድ ጃንዩሪ 3,2016 ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ለነጻነት የተደረገ ትግል አልነበረም ነገር ስልት ነበር፡፡ ያለፈውን ስረአት ለመጣል የተደረገው ትግል እራሱ የነጻነት ትግል አልነበረም፡፡ የኤርትራ ትግል ብቻ ነበር ለነጻነት ሲደረግ የነበረው በሚል ስትፈላሰፍ ሰማኋት፡፡ አይ ጆሮ ደጉ! ሰምቶ አይፈነዳም እኮ፡፡
Mimi
 
ከዚ በፊት ለሚሚ ጠረቤዛ ምን ያደርግላታል የሚል ጽሁፍ ማንበቤን አስታዉሳለሁ፡፡ በዛሬው ፕሮግራም ላይ ከሚሚየ ጋር አብሮ የነበረው አንድ አጋሯ ብቻ ነበር፡፡ ድሮ ድሮ ሌሎች ለምን መገኘት እንዳልቻሉ ትናገር ነበር፣ አንደኛው ስልጠና ሄዶ ሌላኛው መኪና አደጋ ሌላኛው ራቅ ያለ ቦታ ለመስክ ስራ ወጦ እየተባለ አንድ በአንድ ይልተገኙበት ምክንያት ይዘረዘር ነበር፡፡ዛሬ ግን ምንም ሳትለን ከፊቷ አንድ ሰውየ እንዳለ ነገራን ብቻ ነበር ወደ አበይት ጉዳዩቹ የገባቸው፡፡ እኔ ታድያ መቼም መስጋት ልማዴ ነውና ለቀጥታ ስርጭቱ ለመድረስ ሲሉ ያን ወደቢሮ የሚወስደውን ዳገት በሩጫ ሲወጡ መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ያለፈቃድ ወጡ በሚል እስኪጣራ አስሯቸው እንዳይሆን በሚል ልቤ ሲሸበር ነበር የቆየው፡፡በነገራችን ላይ አንድ የዛሚ ጋዜጠኛ ወደ ቢሮ የሚወስደውን ዳገት ጥድፍ ጥድፍ እያለች ስትወጣ ፖሊስ ተመልክቶ ኖሮ ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣሽ ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ ለስምንት ወር አስሮ ሲያጣራ ከቆየ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ፍርድቤት ነጻ ብሎ ለቋታል፡፡ እና ወዳጄ ስትቸኩል እረጋ በል የሚለው ዘይቤ የሚሰራው ይሄኔ ነው፡፡ ዛሬ ይህ ጉዳይ ይነሳ ይሆናል ብየ ጠብቄ የነበረ ቢሆንም እነሱ ሆየ እንዳውም መንግስት እስሩ ላይ ለምንድን ነው የማይጠነክረው እስኪጣራ ሁሉም ተሰባስቦ ይግባ አይነት መፈክር እና ድንፋታ ነው ሲያሰሙን ያረፈዱት፡፡
 
ጋዜጦች ይዘጉ፤ መጽሄቶች ይታገዱ፤ ስልጠናዎች ይሰረዙ፤ የሚጽፉ እጆች ይቆረጡ አይነት ጥሪ ለማድረግ ማንም የማይቀድማት እትየ ሚሚ፤ በአንድ ወቅት የርሷን የሬዲዮ ጣቢያ የብሮድካስት ባለስልጣን ሊዘጋ እንደሆነ ደብዳቤ ሲጽፍላት፣ “ፍትህ በሃገሩ የለም እንዴ? ዛሚ የመንደር ሱቅ ነው እንዴ እንደዚ በአንድ ደብዳቤ የሚዘጋው?” የሚል ተጠቃሁ የደራሽ ያለህ የሚመስልን ጩኸት የሰማ በቃ ሚሚየ ትምህርት ወሰደች ብሎ ነበር፡፡ እርሷ እንደው ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሆና ጭራሽ በሳለ ቢላዋ ሁሉም ካልተቆረጠ አይነት ጭልፊት ሆና ቀጠለች፡፡
 
በጠረቤዛው ዙርያ የነጻነት ትግል ጉዳይ እንደዚ የተካረረው አንዱ የተቃዋሚ ሊቀመንበር ትግሉ የነጻነት ትግል ይሁን የሚል ጥሪ አስተላልፏል በሚል ነው፡፡ መንግስት ምን እስኪሆን ነው የሚታገሰው ይላታል በጠረቤዛው ዙሪያ ያስቀመጠቸው(ወንበር መኖሩን እኔ እንጃ) ብቸኛው “ጋዜጠኛ”፡፡ በነገራችን ላይ ልሳሳት እችላለሁ ግን ጆሮየ ፈጥሮበት ነገር አያልፈውም እና ይህ ብችኛ ጋዜጠኛ እየዘላበደ እያለ ሲጋራ ለመለኮስ ላይተር ችር ችር ችር.. ሲል ይደመጣል፡፡ ይችን አንድ ሰአት እንኳን ብትታገስ ምናለ! አይ ክፉ አመል? ካልሆነ ደግሞ በአንድ ግዜ ቦግ አድርጎ ለሚለኩስ ላይተር በጀት እንዲያዝ ማድረግ፡፡ በቻይና እቃ እሷም ተንቃ እኛም ተሳቀን ከምናልቅ፡፡
 
ይህን ጥሪ በጋዜጣዊ መግለጫ አስተላልፈዋል በሚል እንደዚ ውግዝ የሚደርስባቸው የሰማያዊ ፓርቲ ለቀመንበር ናቸው፡፡ ታድያ እንደሚነግሩን ከሆነ እነዚህ በክቧ ጠረቤዛ የተሰባሰቡት ጋዜጠኞች የርሳቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመከታተልና አሉኝ የሚሉት ጥያቄም ካለ ለመጠየቅ በስፍራው አልተገኙም ነበር፡፡ እንግዴህ በስፍራው ያልተገኘነው ተከልክለን ነው አላሉንም፡፡ ስለዚህ ያልሄዱት በቦታው መገኘት ልማታዊነት መስሎ ስላልታያቸው ይሆናል ብሎ መጠርጠር ይቻላል፡፡ እናም ለዚህ ታላቅ ትችት መነሻ የሆናቸውን ዜና ያገኙት ከአንድ የህትመት ዉጤት ላይ እንደሆነ ነግረዉናል፡፡ ያንን ስሙን ሊነግሩን ያልፈለጉትን የህትመት ዉጤት ዋቢ በማድረግም ሊቀመንበሩን ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃ እንደኖረች አልሰሙም ወይ በሚል በጽኑ ሲወርፏቸው አርፍደዋል፡፡ ከራሳችን አልፈን ለአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት መሆናችንን ያራከሰ መግለጫ በሚል ሰውየውን በቃላት ሲያብጠለጥሉና የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ መግለጫ ተሰድቧል ሲሉ ተደመጡ፡፡ ማሳረጊያቸውም ያው በገደምዳሜው የይታሰርልን ጥሪ ሆኖ ተደመደመ፡፡
 
እንደነገርኳችሁ እኔ ስጋት ቶሎ ያጠቃኛል እና የዛሬን የክብ ጠረቤዛ ዉሎ ሲያዳምጡ የነበሩ ቀን ከሌት ሲዘመርላቸው ወይም ሲያዘምሩን የኖሩት “የነጻነት ታጋዮች” ምናልባትም በታላቅ ሃዘን ተዉጠው “እንዴት ነው እትየ? ምነው እሱ? እኛ ለ አስራሰባት አመት ለነጻነት ስንታገል ዉለን እንደዚ ባንዴ ያን የመሰለ መሪር የነጻነት ትግል እንዲህ እንደዋዛ በአንድ ጀምበር ፍጹም አልነበረም ብለሽ የካድሽው? እንደዚህ ስትይ ለዚህ ትግል የተሰውት ሰማእታት አጽም ትንሽ እንኳን አልጎረበጠሽም ወይ? እኛ የተረፍነው በህይወት እያለን እንደዚ ካልሽማ ትንሽ ዞር ብንል ምን ልትጨምሪ ነበር?” ብለው እስኪጣራ ከክቡ ጠረቤዛ ወደ ጠባቡ ቤት ተሸጋግረሽ ቀጣይ የምደባ ቦታሽን ተጠባባቂ የሚል የቃል ትዛዝ እንዳይመጣ ነው፡፡ እንግዴህ መቼም ባለፈው ግዜ በደብዳቤ አይቻልም ስላለች ነው ነገሩ ወደ ቀጭን የቃል ትዛዝ ይሆናል ተብሎ የተገመተው፡፡ ለእንደዚህ አይነቱ ትዛዝ ይግባኝ ብዙም የሚያስኬድ አሰራር እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በግዜ ግለ ሂስ ማድረግ ነው የሚያዋጣው፡፡ ያለዚያ አሳሪዎቹን ከእሰሩልኝ ጥሪው ይልቅ የእሰሩኝ ጥሪው የበለጠ ሊያስጎመዥ ይችል ይሆናልና፡፡
 
በሌላ አጀንዳ ከተነሱ ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ ሰሞኑን ተደረሰ የተባለው ስምምነት ነበር፡፡ እነ አልሲሲ እንደዚ አይነት ስምምነት ተስማማን ብለው በራሳቸው የመገናኛ ብዙሃን ለተናገሩትና የነሱ ሜይን ስትሪም ሚዲያ እይተቀባበሉ ለዘገቡት ዜና፤ ሚሚየ የኛዎቹን ሚዲያዎች የበሬ ወለደ ወሬ ፈጣሪዎች ብላ ውርጅብኙን ታወርድባቸው ገባች፡፡ አሁንማ በጣም ተደራጅተው እስከ ሳታላይት ቲቪ ድረስ አላቸው በማለት በቁጭት ስትንገበገብ ትደመጣለች፡፡ እንግዴ አገር ውስጥ ያሉት በሙሉ ተዘግተው ስላለቁ እከሌን ዝጉልኝና ለብጫየ ልጨፍር ማለት ስለማይቻል ነው ንዴቷ ብው ብሎ ላይተሯን ቦግ ያስደረጋት የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል፡፡ መጠርጠር በህግ ካልተፈቀደ ትቸዋለሁ፡፡
 
አንዱ ናይጀሪያዊ ኮን አርቲስ የተጫወተውን ድራማም እርሷ በተለመደ መልኩ መቀመጫውን አየርላንድ ያደርገ … በሚል አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁን እና ሌሎችንም የተረጋገጡ ውሸቶችን በዚህ መረጃ እንደ ብርሃን ፈጥኖ በሚሰራጨበት ክፍለዘመን ያለ አንዳች ይሉኝታ ስታሽጎደጉዳቸው ለሰማ ወይ ግዜ ደጉ ስንቱን ታሰማናለህ ማለቱ አይቀርም፡፡ በዚህ አርስት ላይም ለፉክክር በሚመስል ድምጸት የዶ/ር ብርሃኑም በሌላ መቀመጫውን ጎረቤት አገር ባደረገ ሚዲያ የአመቱ ምርጥ ሰው መባላቸው ጉዳይ ተነስቶ በጽኑ ሲብጠለጠል ነበር፡፡ ሁኔታውን ያየ ጠ/ሚ ከ ዶ/ሩ ጋር ባደረጉት ውድድር አንድ እኩል የወጡ ነው የሚመስለው፡፡ ተቀማጭነቱን አዲስ አበባ ያደረገው የርሳቸው ሬዲዮ ግን ያመቱን ምርጥ ያስታቀፈው ለማን እንደሆነ አልነገሩንም፡፡
 
የሚገርመው ግን ውሸት እራሱ ያልቃል እንዴ? እኔ ከዚህ በፊት ባለኝ መረጃ እንደማያልቅ ነበር የማቀው፡፡ ወደመጨረሻ ላይ እኮ መጀመሪያ ተወርቶበት ያለቀን ጉዳይ በድጋሚ አንስተው የተናገሩትን ይደግሙት ገቡ፤ ይቺ አንድ ሰአት አልሞላ አለች፡፡ እነሱ እራሳቸው ፍጹም የመሰላቸት መንፈስ ታየባቸው፡፡ ልማታዊነትን በተሰላቸ መልኩ ማስቀጠል ስለማይችል ለሚቀጥለው ሳምንት የክብ ጠረቤዛ ዉሎ በርካታ አዳዲስ ዉሸቶችን የመፈብረክ ስራ ላይ ትኩረት ተሰጦ ሊሰራበት ይገባል የሚል ልማታዊ አስተያየት እንስጥ እንዴ?
 
ቸር እንሰንብት
posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: