The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ለኦነግና ኦነጋዊያን – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

እንደሚታወቀው በተማሪዎች የተጀመረው ተቃውሞ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍልም ተቀላቅሎት ሲደረግ የቆየው ሕዝባዊ ተቃውሞ እነሆ ሁለት ወራት እየሆነው ነው፡፡ እያየነው እንዳለነው እስከአሁን ተቃውሞው ያመጣው ውጤት ወይም ለውጥ የለም፡፡ ወደፊትም ሕዝቡ በዓመፁ የመቀጠል ብርታት የሚኖረው ከሆነ “በእኔ ግምት ይኖረዋል ብየ ስላልገመትኩ ነው ምክንያቶች አሉኝ” እንዲያው ከሆነ ግን ወያኔ ሁሉንም ለቃቅሞ እስኪፈጅ ድረስ ሳይሰለች መፍጀቱን ይቀጥላል እንጅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቶት “እሽ! ተሳስቻለሁ ይቅርታ! ካሳም እከፍላለሁ! ያላቹህት ሁሉ ይሁን!” ብሎ እጅ የሚሰጥበት ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡

ይህ መሆኑን የሚወድ ዜጋ ይኖራል ብየ ለመገመት ይቸግረኛል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ኦነግና ኦነጋዊያን ውጤቱ እንዲህ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ እንዴት? ቢባል ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፡፡

ጥያቄውና ችግሩ የመላው ኢትዮጵያውያን ሆኖ እያለ የኦሮሞ ብቻ እንደሆነ በመወሰዱ፣ እንዲያ ተደርጎ እንዲታሰብ ጥረት በመደረጉና ተቃውሞው በምክንያቱ ወይም በመንስኤው ላይ ሳይሆን በውጤቱ ላይ ያተኮረ በመሆኑ፡፡
ይሄንን ተቋውሞ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲቀላቀለው እንዲዋሐደው እንዲተባበረው ኦነግና ኦነጋዊያን መሥራት ያለባቸውን የቤት ሥራ ሥላልሠሩና መሥራትም ስላልፈለጉ ነው፡፡
እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ዕንይ፡-

በአንደኛ ተራ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው ጉዳይ ላይ እንደሚታወቀው የመሬት መፈናቀልና የመሬት ባለቤትበት ዋስትና የማጣት ችግር የኦሮምኛ ተናጋሪ ተቃውሞ አድራጊዎቹ እየገለጹት እንዳሉት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች ችግር ፈተና ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ገበሬዎችና የከተማ ነዋሪዎችንም ጭምር ነው፡፡ በከተማ መስፋትና መሬታቸው ለባለሀብቶች በመሸጡ ምክንያት እየተፈናቀሉና እንዳይሆኑ ሆነው እየቀሩ ያሉ ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ያሉ ዜጎች ሁሉ እንጅ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች ብቻ አይደሉም፡፡

ምሳሌ፡- ባሕር ዳር ብንሔድ ተመሳሳይ ችግር በከተማው መስፋትና ከገበሬዎች እየተነጠቀ ለባለሀብቶች በሚሰጠው መሬት ምክንያት ከገበሬዎች ጋር በተፈተረ አለመግባባትና ችግር ምክንያት ገበሬዎች ለጅምላ እስር ተዳርገዋል፣ የተገደሉ አሉ፣ አማራጭ አጥተውና ተገደው የካሳ ገንዘብ ተቀብለው መሬታቸውን ለመልቀቅ የተስማሙትም የማትረባ የካሳ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ይህቺ ገንዘብ ከወራት ላለፈ ጊዜ የማታቆይ በመሆኗ ለከተማ ኩሊነት የተዳረጉ ገበሬዎች በርካቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም ባለፈው ጊዜም ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት መቃወም ካለብን መቃወም ያለብን በጎጥና በዘር ሳንወሰን ሕዝቡን የሀገሩና የመብቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደረገውን፤ ወያኔን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገውን የወያኔን ሸፍጠኛ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓት ነው እንጅ የከተማ መስፋት አቅድን መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ችግራችን የከተማው መስፋት ላይ ከሆነ አንደኛ አስተሳሰቡ ካለው ተፈጥሯዊና ነባራዊ እውነታ ጋር የሚጋጭ የማይስማማ የደነቆረ አስተሳሰብ በመሆኑ፡፡ ሁለተኛ ይህ አስተሳሰብ ወያኔ ሲወድቅና ወደፊት ሌሎች መንግሥታት ሲመጡም ከነሱም ጋር የማያስማማ የደነቆረ የጥፋት አስተሳሰብ በመሆኑ፡፡ ይሄንን ተቃውሞ አመክንዮዊ የማያደርገው ሌላው ምክንያት ደግሞ ወያኔ እንደሚለው አዲስ አበባ ራሷ ባለቤትነቷ ኦሮሚያ ብሎ የሚጠራው ክልል ነው ይላልና ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት በአመክንዮ ያልተደገፈ ተቃውሞን ይዞ መነሣት ተቃውሞውን ጽናትንና በዘላቂነቱ ላይም ወያኔን እስከማስወገድ ሊደርስ የሚያስችለውን አቅም ያሳጣዋል፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎቹ እንደሚሉት የተቃውሞ ምክንያታቸው የአዲስ አበባ የማስፋፊያ አቅድ ብቻ ከሆነ በእርግጥም ይሄ ተቃውሞ ብስለትና ትክክለኛነት የጎደለው የትም የማይደርስ ማረሻውን ወስደውበት እያለ ለመርፌው የሚያለቅስ የጅል ለቅሶ ከመሆን የዘለለ አይደለም፡፡

ምን ማለቴ ነው፡- ወያኔን እንቃወም ካልን ልንቃወመው የሚገባን ሕዝብ ይሁንታ ያልሰጠው ያልመረጠውና በኃይል ሥልጣንን ይዞ ረግጦ የሚገዛ ጨካኝ አንባገነን አገዛዝ በመሆኑ፣ በሀገርና በሕዝብ ህልውና ላይ የሚቆምር ወራዳ፣ ነውረኛ፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይ የሀገርና የሕዝብ ጠላት በመሆኑ ነው እንጅ በዚህ አልነበረም፡፡

ተቃውሞ አድራጊዎችን መጠየቅ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር፡- እሽ ወያኔ ሸፍጠኛ የመሬት አስተዳደር መመሪያው እንዳለ ሆኖ እየጠየቃቹህት እንዳለው የአዲስ አበባን የማስፋፊያ አቅድ የምሩን “ትቻለው ሰርዣለሁ!” ብሎ ቢል በቃ ተቋውሟቹህን ታቆማላቹህ ማለት ነው?

ዕያየነው እንዳለው ወያኔ ተቋውሞውን ለማብረድ ሲል የማስፋፊያ አቅዱን እንደሰረዘ መግለጹንና “የማስፋፊያ አቅዱን ከሰረዝኩ ሌላ ምን ችግር አለባቹህ? ለምንድን ነው አሁንም ተቋውሞ የምታደርጉት?” ብሎ ሲጠይቅ ተቋውሞ አድራጊው ጥያቄው ያደረገው “የታሰሩት ይፈቱ! ለሞቱት ካሳ ይሰጥ!” የሚል ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይሄ ማለትም ወያኔ ይሄንን ቢያደርግ ሌላ ችግር የለብንም ማለታቸው ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ይህ ተቋውሞ የተከፈለለትን ዋጋና የተገኘውን ሐሰተኛና ጊዜያዊ ውጤት ተመጣጣኝ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ይህ ከተፈለገው ውጤት እጅግ የበዛ መሥዋዕትነት ዋጋ የመክፈል ችግር ወይም ኪሳራ ሊፈጠር የቻለውም አመራር ለመስጠት እየሞከሩ ካሉት ኦነግና ኦነጋዊያን የአመራር ብቃትና ብስለት አለመኖር ችግር የመነጨ ነው፡፡ በእውነት ነው የምላቹህ በሰው ደም ይቀልዳሉ ምን እንደሚፈልጉና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ አይደሉም፡፡ ለዚህ ነው ከላይ ተልካሻ ምክንያት አንግቦ መነሣት ተቃውሞው ከአስፈላጊው ግብ እንዳይደርስ ሕዝቡም ጽናት እንዲያጣ ያደርጋል ያልኩት፡፡

ስለሆነም ይሄንን ተቃውሞ እያስከፈለ ካለው መሥዋዕትነት በተመጣጣኝ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ በመሆነ መልኩ ማስኬድ ከተፈለገና ውጤት እንዲያስመዘግብ ከተፈለገ የተቃውሞውን ምክንያት ከተልካሻነቱና ከኢአመክንዮአዊነቱ ወደ በሳልና አመክንዮአዊነት ደረጃ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

እንዴት ነው ወደዚህ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚቻለው? ከተባለ ተቋውሞው በመጀመሪያ ደረጃ ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይፈልገው፣ ሳይፈቅደው፣ ሳይመርጠው በኃይል ተጭኖን በኃይል እየገዛ ያለ አንባገነን አገዛዝ መሆኑን አበክረን በማንሣት ሥልጣንን ለሕዝብ እንዲያስረክብ በመጠየቅ ነው ጥያቄያችንን ተቋውሟችንን ወደ ተገቢው ደረጃ ከፍ ማድረግ የምንችለው፡፡ ይሄንን ጥያቄ ካነሣን ወያኔን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥልጣኑን መብቱን ነጥቆ የወያኔ አሽከር የሚያደርገውን ሸፍጠኛ የመሬት አሥተዳደር ሕግና ሥርዓቱን እንዲያነሣ እንዲቀይር መጠየቁ የግድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡

ይህንን ማድረግ ባይቻልና ችግሩ ሀገር አቀፍ ሆኖ እያለ ልክ በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ ላይ እንደተፈጸመ በማስመሰል ትልቁን ጥያቄ አኮስሶ ቆንጽሎ የጎጥና የዘር ችግር እንዲሆን እንደተደረገ ቢቀጥልና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የዚህ መሬት ጉዳይ የማይመለከታቸው ጭራሽም እንደ ባዕድ እንደ ወራሪ ተቆጥረው “ባሕላችንን ቋንቋችንን… ሊያጠፉብን!” ምንትስ እየተባለ ኢትዮጵያዊያንን ባይተዋር እንዳደረገ፣ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ነገሬ ጉዳየ ብሎ እንዳያስበውና እንዳይተባበር እንዳደረገ ከቀጠለ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ ልነግራቹህ የምችለው ይህ ተቋውሞ የትም አይደርስም!

በሁለተኛው ነጥብ ላይ የተነሣውን ስናይ፡-

ሁሉም ባይሆኑም የተቃውሞ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ወገኖች በተለያየ መንገድ እየገለጹት ካለው መፈክራቸው እስከ ግባቸው ድረስ ከሚናገሩት ተነሥተን ስንናገር ፍላጎታቸው ኦነግ ዓላማው አድርጎ ሲሰብከው የኖረው ጉዳይ እንዲፈጸም ነው፡፡ በብዙኃን መገናኛዎች ይሄንን ተቋውሞ ለመምራት ጥረት እያደረጉ ያሉ እራሳቸውን እንደ ኦሮሞ የሚቆጥሩ ድቃይ ኦሮሞ ልኂቃን ኦነግ መሆናቸውን በግልጽ ባይነግሩንም ኦነጋዊያን መሆናቸውን ግን በተለያየ ጊዜ ይፋ ካደረጉልን ዓላማና ግባቸው በመነሣት አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

ኦነግና እነዚህ ወገኖች ብልህና አስተዋይ ባለመሆናቸው የአመራር ብቃት የሌላቸው በመሆናቸው ምክንያት ይሄንን ቀርቃማ አጋጣሚ ከንቱ ሊያስቀሩት እንደሆነ እያየን ነው፡፡ እነዚህ የተማርን ነን የሚሉ ግለሰቦች “ችግሮችን እንዴት እንፍታ?” በሚለው ነጥብ ዙሪያ ከአንድ ካልተማረ ደንቆሮ ደጋፊያቸው የተሻለና የተለየ ሐሳብ ማመንጨት የማይችሉ እጅግ በሚገርምና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ መማራቸው ምንም ያልፈየደላቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ዋነኛው ምክንያትም እነኝህ ግለሰቦች በግልም ይሁን በቡድን በተለያየ መንገድ ሲገልጹልን በደም ፍላትም ሲዝቱብን እንደኖሩት አቋም ዓላማ ግባቸው ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ ፀረ ወዘተረፈ. እንደሆነ ሲያረጋግጡልን መቆየታቸው ነው፡፡ አስቀድሞ በሽግግሩ ወቅትም በተለያዩ ቦታዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም እጃቸው በደም የተጨማለቀ መሆናቸውን እስከ አሁንም ድረስ ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀላቸው ይቅርታ አለመጠየቃቸውንና መጠየቅም የማይፈልጉ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡

ይህ ሁሉ ነገር እያለ እነሱም ብልጥ ሆኑና ምን ሲያደርጉ ምን እያሉም ሲዝቱብን እንደኖሩ ጨርሶ እረስተውት ተቋውሟቸውን እንድንቀላቀልና ተባብረን ወያኔን እንድንከላ እንድናስወግድ አበክረው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ያለ ትብብር የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ግንባር ሳይፈጥር አንድ ዓላማ ሳያነግብ ወያኔን ማስወገድ መንቀል አለመቻሉን መረዳታቸው መልካም ነገር ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ዓለማ አንግቦ አንድ ግንባር ፈጥሮ በወያኔ ላይ እንዲያነጣጥር የሚያደርገውን የቤት ሥራ ሳይሠሩና ይሄንን የቤት ሥራም ለመሥራት ጨርሶ ፍላጎቱ ሳይኖራቸው ይሄንን ትብብር መጠየቃቸው ግን የቂል ቂል ያሰኛቸው እንደሆነ ነው እንጅ ብልጥ የሚያሰኛቸው አይመስለኝም፡፡

እነሱ ማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ያልተለዩ የጥፋት ኃይሎች መሆናቸውን ነጋሪ መፈለጋቸው እጅግ ያስገረመኝ ጉዳይ ነው፡፡ እነኝህን ወገኖች መጠየቅ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር እስኪ እንዲያው በሞቴ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ እናንተን ከወያኔ የተለያቹህ የሚያደርጋቹህ ምንድን ነው? ከወያኔ ጋር የአንድ ሳንቲም ገጽታ ሆናቹህ እያለ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲተባበራቹህ ለመጠየቅ ምን የሞራል (የቅስም) ብቃት አላቹህ? ወያኔ በቆመበት የጥፋት ጎራ ከወያኔ ጋር ቆማቹህ አብሯቹህ የቆመውን ወያኔን ለመውጋት ለማጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ትብብር መጠየቅ ይቻላል ወይ? የትኛው አመክንዮ የትኛው የሞራል (የቅስም) ሕግ ነው ይሄንን የሚለው?

እውነት ይሄንን ሕዝባዊ ተቋውሞ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ተቀላቅሎት የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የምትፈልጉ ከሆነ ማድረግ የሚገባቹህ ጉዳይ መሥራት የሚገባቹህ የቤት ሥራ ከወያኔ ጋር አንድ የሚያደርጋቹህን የጥፋት ዓላማና ተግባር የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አታላቹህ ግባቹህን ለማሳካት ከመፈለግ ከመቋመጥ ሳይሆን ለናንተም ለሁላችንም የማይጠቅም ከንቱ የጥፋት ዓላማ መሆኑን በሚገባ በመረዳት ጣል እርግፍ አድርጋቹህ በመተው የአንድነቱን ኃይል ፈጥናቹህ ተቀላቀሉ፡፡ ይሄኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእናንተ ላይ ያለበትን ከፍተኛ የጥርጣሬ መንፈስ ይገፍና እርስ በእርስ መፈራራቱን መጠላላቱን ትቶ መተማመንን ይፈጥርና ፊቱን በአንድ ወደ ወያኔ እንዲያዞርና ወያኔን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ ለመቅበር እንዲችል ያደርገዋል፡፡

ይሄንን ወሳኝ እርምጃ ሳትወስዱና መውሰድም ሳትፈልጉ ሰይጣናዊ ዓላማቹህን በልባቹህ እንደቋጠራቹህ “የኢትዮጵያ ሕዝብ! የኢትዮጵያ ሕዝብ!” እያላቹህ ብታላዝኑ ግን ከንቱ ማላዘን በመሆኑ የሚሰማቹህ አይኖርምና በከንቱ አትድከሙ ማለትን እወዳለሁ፡፡ ሕዝብን በከንቱ በማስጨረሳቹህም እጅግ አዝናለሁ፡፡

እራሳቹህን በዚህ መልኩ አርማቹህ አስተካክላቹህ ተከታዮቻቹህን በተገቢው መንገድ መምራት ሳትችሉ ቀርታቹህ በጠባብነት ገመድ አንቃቹህ በእርስ በእርስ ጥላቻ ወጥራቹህ እንቅስቃሴው ምንም ስኬት ሳያስመዘግብ በወያኔ ተደፍጥጦ ቢቀር ነገ ይህች ሀገርና ሕዝቧ በከንቱ እንዲያልቁ፣ እንዲቆስሉ፣ እንዲታሰሩ፣ እንዲንገላቱ፣ ግፍ ሰቆቃ እንዲፈጸምባቸው ላረጋቹሀቸው ወገኖች ከወያኔ እኩል ተጠያቂ ያደርጓቹሀል፡፡

ይሄንን ወሳኝና ጠቃሚ እርምጃ መውሰድ ባለመቻላቹህ ሕዝባችን በወያኔ ላይ ሊወስደው የሚገባውንና የሚችለውን እርምጃ በመውሰድ ወያኔን በአፍ ጢሙ ደፍቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር እራሱን ነፃ እንዳያወጣ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለዘለዓለማዊ ቂም በቀል ዳርጎ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልን የብሔር ወይም የእርስ በእርስ ግጭትንና እልቂትን በመፍራት ወያኔ የሚያደርስበትን ልክ የሌለው ግፍ በጸጋ እየተቀበለ እንዲኖር በወያኔ ላይ እንዳይነሣ አድርጎ አስሮና ኮድኩዶ ይዞታልና የእርስ በእርስ ግጭትን ወይም እልቂትን በመፍራት በዝምታ የወያኔን ግፍ እየተቀበለ ላለው ግፍ ሁሉ ተጠያቂዎች ናቹህ፡፡

ሕዝባችን እስከዛሬም ይሄንን የወያኔን ትቢያ ቡድን መንቀል መደምሰስ ማጥፋት ተስኖት አልነበረም ይሄንን አደጋ በመፍራት እንጅ፡፡ ወያኔም ያለውን ደካማ አቅም ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው እንደእናንተ ያሉትን የጥፋት ኃይሎች በመጠቀም ይሄንን የእርስ በእርስ እልቂት አደጋን በመጋረጥ ሕዝባችንን እርስ በእርሱ አነካክሶ እንዲፈራራ በማድረግ ዕድሜው እንዲራዘም ሲያደርግ የቆየውና አሁንም ያለው፡፡

እናንተ ይሄንን መውሰድ ያለባቹህን እርምጃ አለመውሰዳቹህ ወያኔ ይሄንን ሕዝባዊ ተቋውሞ አቅጣጫ በማሳትና እሱ ተጠቃሚ ወደሚሆንበት አደገኛ ሁኔታ ለመውሰድ እንዲቀለው አድርጋቹህታል፡፡ እውነት ይሄንን የወያኔን ሰይጣናዊ ሸፍጥ የምትጠሉና እንዲሆንም የማትፈልጉ ከሆናቹህ እባካቹህ ስለ እግዚአብሔር ብለን እንለምናቹህ ፈጥናቹህ ሳትዘገዩ ከወያኔ ጋር አንድ የሚያደርጋቹህን የጥፋት ዓላማ ጥላቹህ የአንድነት ኃይሉን ተቀላቀሉና የወያኔን ሰይጣናዊ ሸርና ሸፍጥ እናክሽፈው ነቅለን ለመጣልም እንቻል???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: