The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ እንደ አገር ትቀጥል ይሆን ? – ግርማ ካሳ

07a6fd15-78ba-417b-990d-3f971b848a62

ከ25 አመታት በፊት ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከፋፍሎ ለመግዛት በሚል የዘረጋው የዘር ፖለቲካ ወይንም የነርሱን አባባል ልጠቀምና “የብሄር ብሄረሰቦች” ፖለቲካ፣ ብዙዎች ኢትዮጵያን እንደ አገር ሊያጠፋ የሚችል ትልቅ አደጋ “time bomb” እንደሚሆን ሲያስጠነቅቁ ነበር።

በኦሮሚያ ገጠሮችና አነስተኛ ከተሞች እያየን ያለነው እንቅሳሴ፣ መቶ በመቶ በኦሮሞ ብሄረተኝነት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው። ተቃዋሚዎቹ ኦሮሚያ ሪፑብሊክ የተባለች አገር ለመመስረት፣ ለ40 አመታት ሲታገል የነበረዉን፣ ከሕወሃት ባልተናነሰ በብዙ ወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ ጭካኔ የፈጸመዉን፣ የኦነግን ባንዲራ ሲያዉለበልቡ ነው እያየን ያለነው።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው እንደ አገር መቀጠል የሚቻለው ? ሁላችንም የምናሰላው በዘር ሂሳብ ከሆነ እንዴት ነው ለመስማማትና ሁሉም ሰጥቶ በመቀበል መርህ አሸናፊ የሆነበትን መፍትሄ ለመፈለግ የምንችለው ? አንድ ሰው ሁሉንም ነገር በዘር አጥር ብቻ ተወስኖ የሚያይ ከሆነ፣ ከርሱ ዘር ዉጭ ያለው ሌላው ማህበረሰብ አይታየውም። የሌላው ማህብረሰን ጥያቄ ለማስተናገድ ፍቃደኛ አይሆንም።

በዚህ በኦሮሚያ በተነስው እንቅስቃሴ ዙሪይ በተለይም አላማዉና ግቡን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተለያዩ መልሶች ነው የሚሰጡት።

የመብት፣ የፍትህ የሰብዓዊነትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ነው የሚሉ አሉ። ያ ከሆነ ጥያቄዎቹ ሌሎች ማህበረሰቦችንም ስለሚመለከት፣ ትግሉ ከኦሮሞነት አልፎ ኢትዮጵያዊነት ማድረግ ይቻል ነበር። ግን ያንን ማድረግ አልተቻለም።

ጥያቄዎቹ በኦሮሞ ማንነት ዙሪያ ከሆኑ፣ የኦሮሞ ባህል፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ እንዲከበርና ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው፣ ኦሮሞው በፌዴራልም ሆነ በክልል በአፋን ኦሮሞ አገልግሎት እንዲያገኝ ..በአጭሩ የኦሮሞ ብሄረሰብ መብት እንዲከበር ከሆነ ፣ ሌላው ማህበረሰብም የሚሰማማበት ጉዳይ ነው። ችግር ሊኖረው አይገባም ነበር። ግን በዚህ ጉዳይ መመካከር አልተቻለም።

ጥያቄዎቹ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። ለምሳሌ በቦረና ጉጂ ዞኖች እነ አላሙዲን ወርቅ እየወሰዱ ነው። ከወርቁ የተገኘው ገንዘብ ግን በቦረናና ጉጁ የሕዝቡን ኑሮ ሲያሻሻል አናይም። በቂ ዉሃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች ….የሉም። አሁንም ህዝቡ በድህነት ዉስጥ ነው ያለው። ይሄ ደግሞ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው። የአገሪቷን ሃብት የተቆጣጠሩት እጅግ በጣም ጥቂት ግለሰቦች ናቸው። በኢኮኖሚ ዙሪያም ያለው ኢፍትሃዊነትና አድልዎ ኦሮሞው በተናጥል ሳይሆን ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በጋራ መጠየቅ የሚችለው ነገር ነበር። ግን ያንን ማድረግ አልተቻለም።

ጥያቄው አሁን ያለችዋ ኦሮሚያ ግዛቷ ሳይሸራረፍ፣ አዲስ አበባን አካታ እንድተቀጠል ከሆነ፣ ሕዝቡ ሳይመክርበት በኦነግና በሕወሃት በሕዝቡ ላይ የተጫነን ዉሳኔ እንዲቀጥል መፈለግ ነው። በዚህ ሌላው ማህበረሰብ ሊስማማ አይችልም።በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው ፌዴራል አወቃቀር ለዉይይት፣ ለድርድር በሕዝቡ ፊት መቅረብ አለበት። የአዲስ አበባ፣ የአዳማ፣ የቢሾፍቱ፣ የዱከም፣ የሰበታ፣ የቡራዪ፣ የሞጆ፣ የሆለታ፣ የጂማ ….ሕዝቦች አሁን ኦሮሚያ በምትባለው ክልል ዉስጥ መቀጠል እንደሚፈልጉ ሊጠየቁ ይገባል። ህዝብ ሳይፈለግ በግዴታ አንዱ ክልል ዉስጥ መካተት የለበትም። ህዝብን ማዳመጥ የግድ ነው። ሕዝብ አሁን ያለው አወቃቀር ከደገፈ መልካም። ካልሆነ ግን እኛ የፈለግነው ካለሆነ እንረብሻለን በማለት፣ በብሄረሰብ መብት ስም፣ የሕዝብን ፍላጎት ለመግፋት መሞከር ነው። እርግጥ ነው ኦሮሚያ ዉስጥ በኦሮሞ ብሄረተኝነት ጥያቄ ዙሪያ በብዙ ገጠሮችና ትናንሽ ከተሞች ሕዝብን ማንቀሳቀስ ተችሏል። ግን በብዙ ሌሎች የኦሮሚያ ገጠሮች፣ ትናንሽና ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሕዝቡ አካል የሆኑ ሌሎችም እንዳሉም መረሳት የለበትም።

እንደዚያም ሆኖ ግን ሕዝብ ዴሞክርሲያዊ በሆነ መንገድ ፍቱን መፍትሄ እስኪሰጠው በኦሮሚያ ያሉት ኦሮምኛ የማይናገሩት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መብታቸው ተከበሮ፣ በኦሮሚያ አማርኛም ከአፋን ኦሮሞ ጋር የሥራ ቋንቋ ሆኖ፣ ስልጣን ከክልሉ ወደ ዞኖች በስፋት እንዲወርድ ተደርጎ፣ በጊዜያዊነት አሁን ያለችዋ ኦሮሚያ እንድትቀጠል መስማማት ይቻላል። ግን ያንን ማድረግ አልተቻለም። (እዚህ ላይ በጊዜያዊነት የሚለውን አሰምርበታለሁ)

ታዲያ ለምን መስማማት አልተቻለም? እንዴት የኦሮሞዎች እንቅስቃሴ በአክራሪዎች ሊጠለፍ ቻለ ? መፍትሄው ምንድን ነው ? ምንድን ነው መደረግ ያለበት?

አንደኛ አሁን ያለውን የኦሮሞ እንቅስቃሴ የሚመሩ ወገኖች ሌላውን ማህበረሰብ መግፋት በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው። በተለይም ይሄ የሚያውለበልቡት የኦነግ ባንዲራ በጣም በጣም ከሌላው ማሀብረሰብ ጋር በቀጥታ የሚያጋጫቸው ነው። እኔ በግሌ ይሄንን ሰንደቅ ሳይ በበደኖ ገድል ዉስጥ ነፍሰ ጡር እህቶችን ጨመሮ፣ በሕይወት የተወረወሩ ወገኖችን ነው የሚያስታወሰኝ።

ሁለተኛ የኦሮሚያ መሬቶች የኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን መሆኑን መቀበል አለባቸው። ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ሳይሆን ኦሮምዎችንም ጨምሮ በዉስጡ የሚኖሩ ነዋሪዎቿ ናት። በኦሮሚያ የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያዉያንን እንደ ኬንያዉያን መቁጠር ጸረ-ኦሮሞ፣ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነው።

ሶስተኛ ሌላዉን ማህበረሰብ አግለው፣ እኛ ብቻ በተናጥል እናሸንፋለን ከሚል የተሳሳተ አመለካከት መላቀቅ አለባቸው። እንደ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂማ፣ ቢሾፍቱ …ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ሳይዙ፣ በትላልቅ ከተሞች የሚኖረውን ህዝብ ድጋፍ ሳያገኙ፣ በገጠርና በትናንሽ ከተሞች አሁን እንደሚደረገው እንቅስቃሴዎች ቢያደርጉ እስከየት ድረስ ሊዘልቁ ይችላሉ? ሰላማዊ ዜጎችን በጨካኞቹ የአጋዚ ወታደሮች ከማስጨረስ ዉጭ። ይልቅ፣ ብስለትና ጥንቃቄ ባለው መልኩ፣ ሌላዉን ማሀበረሰብ በማቀፍ ትግሉን ወደ ትላልቅ ከተሞች ማዞር ይገባል።የታጋዮች ካምፕ በሰፋ መጠን የሚከፈለዉም መስዋእትነት በእጅጉ ይቀንሳል። ለኦሮሞ ወጣቶች በርግጥ የሚያስቡ ከሆነ ይህ የኦሮሞዎች እንቅስቃሴን ሌሎች እንዲቀላቀሉት ማድረግ አለባቸው።

አራተኛ እንቅስቃሴው ሰላማዊ መሆን አለበት። የወታደሮች አስክሬን መጎተት በአገራችን ያልተለመደ ጸያፍ ተግባር ነው። ንብረቶችን ማቃጠል፣ አጋዚዎችች የበለጠ እንዲገድሉ፣ እንዲያስሩ፣ እንዲያሸብሩ ቀዳዳን መክፈት ነው። አጋዚዎች አሥር ወጣት ይገድላሉ።  ለምን ሲባሉ መሬት ላይ ሲጎተት የነበረውን ወታደር ያሳዩና “ይኸው ሰላማዊ ስዎች ሳይሆን ይሄንን የሚያደረጉ ሽብርተኞች ናቸው። ራሳችንን የመከላከል ግዴታ አለብን” የሚል ምላሽ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል።

አሁን የምንመክረው አንድነትን ነው። ዘር መቁጠር ጉዳት አለው ነው እያለን ያለነው። አገራችንን ለመበጥበጥና እርስ በርሳችን እንድንፋጅ ለማድረግ ወያኔዎች ያስቀመጡትን “time bomb” እናክሽፍ ነው የምንለው። 95% በመቶ አፋን ኦሮሞ ተነጋሪዎች ባሉበት ቦታ ብቻ የሚነሱ ተቃዉሞዎችን በማድረግ ለዉጥን ከመጠበቅ፣ በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ መረዳት ይገባል ባይ ነን። አዲስ አበባን ጨመሮ በአራቱ የኦሮሚያ ዞኖች የሚኖረው ሕዝብ የኦሮሚያ ክልል አንድ ሶስተኛ ይሆናል። ኢኮኖሚን ደግሞ ከግምት ካስገባን ከ 75% በላይ የሚሆነው የኢኮኖሚክ እንቅስቃሴ ያለው ሸዋ ዉስጥ ነው። በዚህ አካባቢ ግማሹ አንደኛ ቋንቋው አፋን ኦሮሞ አይደለም። አብዛኛው ነዋሪ የኢትዮጵያ ብሄረተኛ ነው። ይሄንን ህዝብ እንደሌለ መቁጠርና መግፋት ያለ ምንም ጥርጥር ለሽንፈት የሚዳርግ ነው። ከስሜት ወጣ ብለን በርጋታ ይታሰብበት እንላለን።፡የዘር ነገር አያዋጣንም።ኦሮሞ፣ አማራ ፣ ትግሬ መባባል አያዋጣንም። እልህ ጥላቻ አያዋጣንም። ለዘመናትት ተከባብረን፣ ተዋልደን የኖረን ነን። የሚለያየንን ሳይሆን አንድ ያደረገንን ነገር ማሰቡ ይበጃል ባይ ነን።

ለማጠቃለያ ይሄን እጽፋለሁ። በአጭር ጊዜ ዉስጥ መልኩን እየቀየረ ያለው እንቅስቃሴ ለሁሉም የሚበጅ ጥቅም ሊያመጣ በሚችል መልኩ በቶሎ ካልተመራ፣ አቅጣጫው ወደ ቀናው መንገድ ካልተመለሰ፣ በኦነጋዉያን እና አክራሪዎች ዘረኛ የጥላቻ ፖለቲካ አገሪቷ ወደ ከፋ ቀዉስ ዉስጥ ነው የምትገባው። ሶስት ነገር ነው ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡

ገዢው ፓርቲ እንደለመደው ጭካኔዉን አብዝቶ፣ በተናጥል በኦሮሞዎች ላይ ኢሰብአዊ እርምጃዎችን በመዉሰድ ተቃዉሞዉን በኃይል ይጨፈልቀዋል። ይሄንንም ማድረግ ጀምሯል። ብዙ ዜጎች እየተገደሉ ነው። ልክ እንደጋምቤላ የኦሮሚይ ክልል ሙሉ በሙሉ በነሳሞራ እጅግ እንድትወድቅ ልትደረግ ትችላለች። ወታደራዊ ቀጠና ትሆናለች ማለት ነው። እየሆነችም ነው።

ተቃዉሞው አይሎ፣ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በሃረርጌ ብዙ ቦታዎች የኦህደዴን አስተዳደር በመገልበጥ፣ የአጋዚ ወታደሮች እንዳይንቀሳቀሱ መንገዶችን በመዝጋት፣ ብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከወያኔዎች ቁጥጥር ዉጭ ማድረግ ይቻል ይሆናል። ወያኔዎችም በሁሉም ኦሮሚያ ሕግን ስርዓት ለማስጠበቅ አቅም ሊያጡ ይችላል። በሌላ በኩል በወላጋ፣ በአንዳንድ የአርሲ ቦታዎች በሃረርጌ ያለው እንቅስቃሴ በሁሉም ኦሮሚያ ድጋፍ ስለሌለው፣ ተቃዋሚዎች ሁሉንም ኦሮሚያ ሊቆጣጠሩ አይችሉም። በተለይም ትልልቅ ከትሞች ባሉበት ቦታዎች። ስለዚህ የተወሰኑ ቦታዎች በተቃዋሚዎች፣ የተወሰኑ በአገዛዙ ቁጥጥር ስር ሆነው ይቀጥላሉ። ይሄ ደግሞ በአጭሩ ሲሪያና ሊቢያ ተኮነ ማለት ነው።

ወያኔዎች ነገሩን መቆጣጠር ሲያቅታቸው አዲስ አበባን ለቀው ወደ ትግራይ ይሄዳሉ። ያኔ “ጸር-አማርኛ፣” እና የነርሱን አባባል ልዋስና “ጸረ-አቢሲኒያ” ዘመቻዎች ይጠናከራሉ። ላለፉት 25 አመታት በብዙ የኦሮሚያ ግዛቶች ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ የጸር-ማጽዳት ሥራ እንደተሰራው፣ ከዚህ በፊትም በጭክኔ የሌሎች ማህበረሰብ አባላት እንደተገደሉ፣ እንደተጨፈጨፉ (በደኖ፣ አርባ ጉጉ፣ አመያ ..ይመስክሩ) ፣ የዘር ፖለቲካ መጥፎ ነገር ነውና፣ ያኔ የነበረው የዘር ፖለቲካ አሁንም እስካለ ድረስ፣ ያኔ የተከሰተው አሁንም የማይከሰትበት ምክንያት አይኖርም። በዚህ ሂደት እነርሱ አዲስ አበባን እና ሙሉ ሸዋን ከአማርኛ የጸዳ ለማድረግ ሲሞክሩ፣ ሌላው እሺ ስለማይላቸው ፣ የዘር መተላለቅ ይከሰታል።

በዚህም ሆነ በዚያ አማራጩ በጣም የከፋ ነው የሚሆነው። ኦነጋዉያን የሚያራምዱት የዘር ፖለቲካ ኦሮሞዉን አይጠቅምም። ኦሮሞዉን ከሌላው ለመለየት የሚደረግ ፖለቲካ ኦሮሞዉን አይጠቅምም። ኦሮሞው ከሌላው ጋር እንዲጋጭ፣ በሌሎችም ማህበረሰቦች በጥራጥሬ በፍርህት እንዲታይ መደረጉ ኦሮሞዉን አይጠቅምም። ኦሮሞው ያመረተዉን መሸጥ አለበት። የኦሮሚያ ከተሞች እንዲያድጉ ንግድም ቱሪዝም ያስፈልጋቸዋል። ተነጥሎ መቀመጥ ፣ ሌላውን መግፋት፣ በርን ሌሌላው መዝጋት፣ ትልቅ ኪሳራ ነው። እነ ነቀምቴ፣ እነ አማቦ፣ ከነአዋሳ ይማሩ እላለሁ።

(ከዚህ በታች የምታዩት ፎቶ ምን ያህል በኦሮሚያ ያለው እንቅስቃሴ በአክራሪዎች፣ በኦነጋውያን እንደተጠለፈ ነው)

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a comment