The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ትምህርት ከሁቱትሲ – በአያሌው ዘለቀ

የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ/ም

Comment   ከእለታት አንድ ቀን ሻይ ቡና ለማለት ወደ ዩኒቨርሲቲው የመምህራን መዝናኛ በሔድኩበት ጊዜ ከአንድ የትምህርት ክፍል ባልደረባዬ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየተጨዋወትን ነበር።  በመሃል ላይ በእንግሊዘኛ ትምህርት ክፍል የሥነ-ፅሁፍ መምህር የሆነው መዘምር ግርማ ወደ ላውንጁ ሲገባ አየነው። በመቀጠልም ባልደረባዬ ‹‹መዘምር እኮ በጣም ትልቅ ሥራ  እየሰራ ነው›› ሲለኝ እኔም ‹‹የምን ትልቅ ሥራ?›› በማለት ጠየቅሁት። ‹‹አልሰማህም እንዴ? በሩዋንዳ ከዛሬ 20 ዓመት ገደማ በፊት ከተከሰተው የዘር ጭፍጨፋ አምልጣ ለወሬ ነጋሪ የተረፈች የአንዲት ቱትሲ ሩዋንዳዊት በመፅሃፍ መልክ የተረከችውን “Left to Tell” የሚለውን ታሪኳን ወደ አማርኛ እየተረጎመው ነው።” አለኝ። እኔም በመደነቅ ይህ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ትምህርት ሰጪና አስተማሪ ሊሆን እንደሚችል ነግሬው መፅሃፉ ተተርጉሞ ለንባብ እስኪበቃ ጓጓን።

በታህሳስ 2008 ዓ.ም. እነሆ ያ የጓጓንለት “Left to tell” በሚል በሩዋንዳዊቷ ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ የተተረከውና በራሷ ትውስታዎች ላይ ያጠነጠነው መፅሃፍ ‘ሁቱትሲ’ በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለሽያጭ መቅረቡን ሰማሁና አንድ ቅጂ ለእኔም ወስጄ አነበብኩት። በተለይ መፅሃፉን ማንበብ የጀመረ ሌላ ስራ እንኳን ቢኖረው መፅሃፉን አንብቦ ሳይጨርስ ወደ ሌላ ስራው መሄድ የማይታሰብ መሆኑን እኔ ራሴ ዋቢ ምስክር መሆን እችላለሁ። እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው የተርጓሚው የወንድማችን መዘምር የቃላት አመራረጥና አገባብ እንዲሁም የታሪኩ መሳጭነትና ልብ አንጠልጣይነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል። ይህም ችሎታ ከአንድ የሥነ-ፅሁፍ ሰው የሚጠበቅ ቢሆንም ለእንግሊዝኛው አቻ ፍች የሚሆኑ ተመጣጣኝ የሆኑ ቃላትና ሐረጋት መፈለግ በራሱ ምን ያህል አድካሚና ፈታኝ እንደሚሆንና ተርጓሚው እነዚህን ውጣ ውረዶች አልፎ ለዚህ ማብቃቱ በራሱ አድናቆት የሚሰጠው እንደሆነ ይሰማኛል።  መፅሃፉ ወደ አማርኛ መተረጎሙ በማህበረሰባችን ዘንድ ታሪኩን ለማንበብ ትልቅ እድል ሊፈጥር እንደሚችል እገነዘባለሁ። ወደፊትም መፅሃፉ ወደሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቢተረጎም የበለጠ ለብዙ አንባቢያን የመድረስ እድል ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ይህን ስል ግን መፅሃፉ ለትችት አይቀርብም ማለት አይደለም። እኔ እንኳ መፅሃፉን ሳነብ ያገኘኋቸው አንዳንድ ቃላት እውነት እነዚህ ቃላት በአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ አሉ ወይስ የሉም የሚል ጥያቄ አጭረውብኛል። በመሆኑም እነዚህን ቃላትና ሌሎችን ከአንባቢያን የሚሰጡ ግብረ-ምላሾችን ተርጓሚው በቀጣይ እትሙ ግምት ውስጥ ሊያስገባቸው እንደሚችል እምነቴ ነው።

የዚህ አጭር መጣጥፍ ዋና ዓላማ ከዚህ መፅሃፍ እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን ጠቃሚ ትምህርት እንወስዳለን? ይህ የዘር ፍጅት ታሪክ አንድምታ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እንዴት ይታያል? እንዲሁም በአፍሪካና በሌሎች ዓለማት አሁንም ቢሆን የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች መኖራቸው ስለሚታወቅ እነዚህን ሃገራት ከእነዚህ አስከፊ ጦርነቶች ለመውጣት ይህ መፅሃፍ ምን አስተዋፅኦ የኖረዋል? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ አጭር ትንታኔ መስጠት ይሆናል።

ተርጓሚው በማስታዎሻው ላይ እንደገለፀው በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ የዘር ጭፍጨፋ ይካሄዳል በሚል የፍርሃት ድባብ ውሥጥ ሆኖ አይደለም ይህን መፅሃፍ ለመተርጎም ያነሳሳው። ይልቁንም በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ልሂቃን የሚነሱ ክርክሮች መኖራቸውን እኔም እጋራለሁ። በአንድ ሃገር ላይ የተፈፀመ ድርጊት በደፈናው በሌላ ሃገር ላይ ይፈፀማል የሚል አጠቃላይ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም። ምክንያቱም ሃገራት የተመሰረቱበት ነባራዊ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበረሰብ ትስስርና ሌሎች ጉዳዮች ግምት ውስጥ ስለሚገቡ ነው። ይሁንና ይህ ማለት ግን በዘር ላይ የተመረኮዘና ፅንፍ የያዘ አመለካከት ስር ከሰደደና በአንድ ሃገር ላይ ካለ ቀስ በቀስ አድጎ ሩዋንዳ ላይ የደረሰውን አይነት መጥፎ የታሪክ አሻራ የማያደርስበት ምክንያት እንደሌለም ማወቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በመሆኑም የእነዚህ ዓይነት መጻሕፍትና ፊልሞች ለሌሎች በአስተማሪነት መዋላቸው ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ኢትዮጵያ የብዙ ዘውጎች ሃገር እንደሆነች ይታወቃል። ይህ የዘውግ ብዝሃነት ግን በአግባቡ ባለመያዙና በእኩልነት ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት ባለመፈጠሩ ህዝብና መሪዎች ሆድና ጀርባ ሆነው ለብዙ ጊዜ ቆይተዋል። ከኢትዮጵያ ታሪክ እንደምንረዳው ህዝቦች ከሰሜን ወደ ደቡብ እንዲሁም ከደቡብ ወደ ሰሜን አቅጣጫ በተለያዩ ምክንያቶች ተንቀሣቅሰዋል። ይህም እንቅስቃሴ ታላቅ የህዝቦች መስተጋብርና ውህደት ፈጥሮ አልፏል። ያም ሆኖ ከንጉሡ የዘውድ አገዛዝ ጀምሮ ህዝቦች የራሳቸውን ማንነት፣ ቋንቋ፣ እንዲሁም ባህል እንዲጠበቅላቸው መሪዎቻቸውን ከመጠየቅና አልፎም ተርፎ ወደ ትግል ከመግባት አላገዳቸውም። በተለይም በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ዋና ማጠንጠኛው የመሬትና የማንነት ጥያቀዎች እንደነበሩ በተለያዩ ምሁራን ተጠቅሷል። ይህም ትግል ወደ ህዝባዊ አብዮት አድጎ የንጉሡን ሥልጣን ማስወገድ ተቻለ። በንጉሱ መውደቅ ደስታው ሳያልቅ ህዝባዊ አብዮቱ በጥቂት የወታደር መኮንኖች ተቀልብሶ ሃገሪቱ ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ ገባች። ደርግ ከመነሻው ሥልጣን በያዘ ማግስት ፀረ-ህዝብ መሆኑን በተለያዩ ድርጊቶች አሳይቷል። 60 የሚሆኑ የንጉሡን ታላላቅ ሹማምንትና ሚንስትሮች በአንድ ሌሊት እንደገደላቸው ያስታውሷል። ከዚያም በኃላ በ1970ዎቹ ተጠናክሮ የቀጠለው የቀይ ሽብር እርምጃ ሌላው በኢትዮጵያ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ የታሪክ አሻራ ነው።

የደርግ ጭካኔና አምባገነንነት እየባሰ በሔደ ቁጥር በዚያው ልክ እድሜውም እያጠረ መምጣቱ አይቀሬ ሆነ። በመሆኑም በተለያዩ ስፍራዎች የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ በነበሩ ኃይሎችና በህዝብ ትብብር እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ነባራዊ ክስተቶች ደርግ ከሥልጣን ሊወገድ ቻለ።

ከደርግ ውድቀት ማግስት ማለትም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ብዝሃነትን ሊያስተናግድ የሚችል የመንግስት መዋቅር ሊኖር እንደሚችል ሐምሌ ወር ላይ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በተካሄደው ኮንፍረንስና ያን ተከትሎ በታወጀው ቻርተር እንዲሁም የክልሎች ማዋቀሪያ አዋጅ ላይ ፍንጭ ሊሰጥ ችሏል። ከዚያም በኋላ በ1987 ዓ.ም. በወጣውና አሁንም በስራ ላይ ባለው  ህገ-መንግስት ላይ በግልፅ ሃገሪቱ የፌደራል ሥርዓት ተከታይ እንደሆነች ተደነገገ። ይህም ሃገሪቷን በአፍሪካ ሦስተኛዋ የፌደራል ሥርዓት ተከታይ አድርጓታል። እዚህ ላይ እግረ-መንገዴን መጥቀስ የምፈልገው ነገር በተለይ የአፍሪካ ሃገራት አብዛኞቹ ማለት ይቻላል የተለያየ ብዝሃነት ስላላቸው የፌደራል ሥርዓት ወደ መመሥረት አልሄዱም። በዚህም ላይ በተለያዩ ምሁራን የተለያዩ ምክንያቶችን ተሠጥተዋል። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገልፁት አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ከድህረ-ቅኝ ግዛት በኋላ ፌደራሊዝምን ያልተከተሉት ሥርዓቱ ፅንፈኛ ብሔርተኝነትን (Ethnic Fundamentalism) ስለሚያስከትል፣ የሃገራትን አንድነትና ሉአላዊነት ፈተና ውስጥ ስለሚያስገባ እንዲሁም ግጭትን ይፈጥራል የሚል እምነትና አመለካከት ስላለ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የተከተለችው የፌደራሊዝም ዓይነት (Federal model) ብሔረሰባዊ ማንነት (Ethnic identity) ላይ የተመሰረተ የፌደራል ዓይነት መሆኑ በአፍሪካ ልዩ (unique) እንደሚያደርገው ብዙ ጥናቶች ያመላክታሉ። ፌደራሊዝም በአንድ ዓይነት ወጥ ህዝብ (homogenous people) ማለትም የጋራ ቋንቋ፣ ባህልና ሥነ-ልቦናዊ ትስስር ባሏቸውና በአንጻሩ የተለያየ ብዝሃነት ባሏቸው ህዝቦች ላይ ሲተገበር ከተለያዩ የፈደራል ሥርዓት ፍልስፍናና ንድፈ-ሃሳብ አንፃር የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ሊኖሩት እንደሚችሉና ይህም ሌላ ትንታኔ የሚያስፈልገው እንደሆነ በመጥቀስ በዚሁ አልፈዋለሁ።

የፈደራል ሥርዓት በኢትዮጵያ ያሉትን የተለያዩ ማንነቶች ለማስተናገድ የሚረዳና በአብዛኛው ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ በበጎ ዓይን የሚታይ ቢሆንም አወቃቀሩና አተገባበሩ ላይ ግን ሰፊ ክርክሮች እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ያለው የፈደራል ሥርዓት በዋናነት ብሔረሰባዊ ማንነትን ግምት ውስጥ ማስገባቱ ሥርዓቱ መተግበር ከጀመረ አንስቶ እስካሁኑ ጊዜ ድረስ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ የክርክር መነሻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ ግን በመርህ ደረጃ ፈደራሊዝም ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል የመንግስት ማዋቀሪያ ሥርዓት እንደሆነ አብዛኛው ይስማማበታል። ከዚህ አንፃር አሁን ባለው ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ ስመዝነው የፈደራል ስርዓቱ ማንነትን እውቅና ከመስጠት ባለፈ የአገሪቱን ህዝቦች ትስስር፣ አንድነት፣ አብሮ የመኖር ባህልና ሌሎች የጋራ የሆኑ እሴቶችን እያጠናከረው ነው ወይስ አይደለም? በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ። በእኔ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ከፈደራል ሥርዓት መርህና ባህርይ ጋር አብረው የማይሔዱ አዝማሚያዎች ይታያሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከታሪክ አጋጣሚ ያገኟቸውን የጋራ እሴቶችና ማህበራዊ ትስስር አብሮ የመኖር ባህል ላይ አጠናክሮ ከመሔድ ይልቅ አንዳንድ የታሪክ ክስተቶችን መነሻ በማድረግ ህዝቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ሊወስዱ በሚችሉ ድርጊቶች ላይ የተጠመዱ መኖራቸውን መካድ አይቻልም። እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምፈልገው እኛ ኢትዮጵያውያን ከባለፈው ታሪካችን መታረቅ ያለብን ይመስለኛል። ይህን የምለው በታሪካችን ላይ ያለን እሳቤ የተዛባና ለአሁን አብሮ የመኖር ባህላችንን የማያጠናክር ከሆነ ትርጉም አይኖረውም። ይህ ማለት ግን በደምሳሳው በታሪክ አጋጣሚ ተበድለው ያለፉት ማህበረሰቦች ይታለፉ የሚል እምነትም የለኝም። ያንን በደል እውቅና ሰጥቶ ነገር ግን ከዚያ ክስተት ትምህርት ወስዶ ለወደፊቱ እንዳይደገም መጣርና የአገር ግንባታ ሂደቱን ማጠናከር እንጂ አሉታዊ ክስተቶችን ብቻ እያነሱ የህዝቦችን ትስስር የሚያላላ ስራ ላይ መጠመድ ከራሱ ከፈደራሊዝም ሥርዓት ባህሪና መርህ ጋር ይጣረሳል።

በአገራችን ብዝሃነት በራሱ የግጭት መነሻ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን በአግባቡ ከመነሻው የብዝሃነት ፅንሰ ሃሳብና ትርጉሙ ከተዛባና ህዝቦች በዚህ በተዛባ አስተሳሰብና አመለካከት ከተመሩ የግጭት መንስዔ የመሆን ዕድል ይኖረዋል። መታወቅ ያለበት ብዝሃነት በራሱ በተፈጥሮው የግጭት መንስዔ ቢሆን ኖሮ ብዝሃነት ያላቸው ሃገራት ዛሬ በሙሉ ግጭት ውስጥ ባገኘናቸው ነበር። በተጨማሪም አንድ ወጥ ህዝብ ባላቸው (homogenous society) ላይም ግጭት ተከስቶ ታይቷል። ለዚህ ዓብይ ምሳሌ የምትሆነውን ሱማሊያን ማየት ብቻ በቂ ነው። በሩዋንዳ  ይህን የመሰለ ዘግናኝ ድርጊት የተከሰተው ሰፊ ብዝሃነት ስላለ አይደለም። እንዲያውም ሁለቱ የዘውግ ማህበረሰቦች ሁቱና ቱትሲ የጋራ የሆነ ቋንቋ፣ ባህልና የሥነ-ልቦና ትስስር ያላቸው መሆኑን እንረዳለን። ከዚህም የምንገነዘበው በአንድ ሃገር ውስጥ ግጭት የሚከሰተው  የግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ የተዛቡ አመለካከቶችንና እምነቶችን በጊዜው እንዲስተካከሉ ካለማድረግ የተነሣ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም የተነሣ አድገው፣ በስለውና ጎምርተው በህዝቦች መካከል ከፍተኛ ስጋት፣ ሽብርና አለመተማመንን ያስከትላሉ።

የ1994ቱ (እ.ኤ.አ) የሩዋንዳ የዘር ፍጅት የተከሰተው እንዲያው በአንድ ጀምበር በተከሰተ የማህበረሰቦች ግጭት እንዳልሆነ ከታሪኩ የምንረዳ ይመስለኛል። ምንም እንኳን የፍጅቱ ፊሽካ ማስነፊያ የሁቱ ዝርያ ያላቸው ፕሪዚዳንት ሃቢየሪማና ግድያ ቢሆንም። እንደሚታወቀው የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ሃገራት በፊት በባሪያ ንግድ ቀጥሎ ደግሞ በቅኝ ግዛት አፍሪካን እንዳልነበረ ምስቅልቅሏን አውጥተዋታል። ይህን በተመለከተ ዋልተር ሩድኒይ “How Europe underdeveloped Africa” በሚል የፃፈውን መፅሃፍ ብቻ መጥቀስ በቂ ነው። ቅኝ ገዥዎች በመጨረሻ አፍሪካን ለቀው ሲወጡ ትተዋቸው ካለፏቸው መጥፎ አሻራዎች መካከል የህዝቦችን አንድነት በሚሸረሽር መልኩ በዘውግ መከፋፈላቸው አንዱ ነበር። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገልፁት በአፍሪካ ለሚነሱ የተለያዩ ግጭቶች መንስኤ በዋናነት በአህጉሪቱ ባሉት አምባገነን መሪዎችና የዲሞክራሲ እጦት እንዲሁም በሌሎች ውስጣዊ ችግሮች ቢሆንም ቅኝ ግዛት ትቶት ያለፈው ጥቁር ጠባሳ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ (Time bomb) ዓይነት የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም። ሩዋንዳ ላይም  ከጀርመን እስከ ፈረንሳይ ያሉ ቅኝ ገዥዎች ያደረሱት አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም። በተለይ በጀርመኖች እግር የተተኩት ቤልጂዬማዊያን ቅኝ ገዥዎች ሁለቱን ማለትም የቱትሲንና ሁቱን ማህበረሰቦች ቅራኔ ውስጥ አስገብተዋቸዋል፡፡  በመካከላችው የዘሩት ጥላቻ በጊዜ ሂደት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ በኋላም ጊዜው ሲደርስ ፈነዳና ሁለቱን ዘውጎች ወደ ግጭት እንዲገቡ አደረጋቸው። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ መማር የሚጠበቅብንን ካሁኑ መማር መቻል ያለብን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ጠቃሚ ትምህርት ከሩዋንዳ መቅሰም ይገባናል ስል ሁለቱ ሃገራት ማለትም ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በተለያዩ ጉዳዮች የተለያዩ እንደሆኑ ግንዛቤ እንዲወሰድ እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ሩዋንዳ ሰፊ ብዝሃነት የሌላት ሁለት ወይም ሦስት የዘውግ ማህበረሰብ ያላት ስትሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ ደግሞ ከ80 በላይ የዘውግ ማህበረሰብ ያሉባት ሃገር ናት። ሩዋንዳ በቅኝ ግዛት ሥር የነበረችና በቅኝ ግዛት ሥር ስትማቅቅ የነበረች ሃገር ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ምስጋና ለአባቶቻችን ይግባቸውና በአድዋ ታሪክ ሰርተው የኢትዮጵያን ነፃነት እንዲጠበቅና ምንም ዓይነት ቅኝ ግዛት ያልነካት ሃገር ናት። እንዲሁም በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋታቸው ሳይቀር በጣም የተለያዩ ሃገራት ናቸው። ነገር ግን በአፍሪካ አህጉር መገኘታቸው በተለይም ኢትዮጵያ ግጭት ተለይቶት በማያውቀው የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መገኘቷ ሁለቱም ሃገሮች ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው በመሆኑ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ብቻ አይደለም ከሌሎችም ሃገሮች ሁኔታ ትምህርት ብትወስድ ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለባትና ህዝቦቿ የጋራ የሆነ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስችላል የሚል እምነት አለኝ ።

ተርጓሚው በማስታወሻው ላይ እንደገለፀው ‹‹…ህዝባችን ከመቼውም በላይ ከአንድነቱ ይልቅ በልዩነቱ ላይ ያተኮረበት በሚመስል ወቅት ላይ ብንገኝም ይህን የሩዋንዳውን ዓይነት ፍጅት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ላይ ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን በጽኑ መተማመኔ ነው፡፡›› የሚለውን አቋሙን እኔም በተወሰነ መልኩ የምደግፈው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የመኖር እሴት ያለውና በመቻቻል ለዘመናት አብሮ የኖረ ህዝብ ከመሆኑ አንጻር ወደዚህ ድምዳሜ ላይ ሊያደርሰን ይችላል። ነገር ግን ከአሁኑ የፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር አያይዘን ካየነው ደግሞ ከላይ ካስቀመጥነው ቀና ድምዳሜና የወደፊት ብሩህ አመለካከት (Optimistic approach) ብቻ ላይ ተመስርቶ ምንም ችግር አይመጣም ብሎ ማሰብ ደግሞ ስህተት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አሁን እያየን ያለነው የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እየጠነከሩ በሄዱ ቁጥር አብሮ የመኖር እሴትና የመቻቻል ባህል በዚያው ልክ እየደበዘዙ መሄዳቸው አይቀርምና። ለዚህም ችግር ከአሁኑ እያንዳንዱ ዜጋ ማበርከት የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት ያለበት ይመስለኛል።

በእኔ አመለካከት ከባለታሪኳ የምንወስደው ጠቃሚ ትምህርት አርቆ አሳቢነትን፣ ለሌሎች ማሰብን፣ አብሮ መኖርን፣ አስተዋይነትን፣ ትዕግስትን፣ ይቅርባይነትንና የመሳሰሉትን አንድ ዜጋ እንደ ሰው ሊላበሳቸው የሚችሉ እሴቶችን ማዳበር እንዳለብን ነው። ከዚህ አንፃርም እነዚህን እሴቶች በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ማምጣትና መተግበር መቻል አለብን።

ከላይ የጠቀስናቸውን ከአንድ ዜጋ የሚጠበቁ ባህሪያት በሰው ልጆች ዘንድ ሊሰርጹና ሊዳብሩ የሚችሉት ደግሞ አእምሯችንን ክፍት በማድረግና (Open-mindedness) ከራስ አልፎ ሌሎች የሚሉትን በጥሞና ማዳመጥን መልመድ ስንችል ነው። አንድ ሃገር በጽኑ መሰረት ላይ መቆም የሚችለው ከባለፈው ታሪክ መጥፎም ይሁን በጎ ተግባራት ትምህርት ወስደን (taking great lesson from the bad and good experiences of Ethiopia’s history of past) አሁን ላለንበት ተጨባች ሁኔታ እንደግብአት ተጠቅመን የሃገር ግንባታ ሂደት ማጠናከሪያ ማድረግ ስንችልና ይህም ተግባር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለወደፊቱ ሃገር ተረካቢ ትውልድ በአደራ መልክ ማስረከብና ማስቀጠል የምንችል ከሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም ትናንትን ረስቶ ዛሬን መኖር ስለማይቻልና ዛሬ እያሰብንና እየሰራን ያለው ሥራ የነገውን ሁኔታ በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆመው መሆኑን እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል።

ሃገራችን ከጥንት ጀምሮ የክርስትና እና የእስልምና እንዲሁም የሌሎች እምነቶች ተከታይ ህዝቦች በጋራ ሲኖሩባት የነበሩ አሁንም እየኖሩባት ያለች ሃገር እንደሆነች ግልጽ ነው። እነዚህም ሃይማኖቶች እንደየእምነታቸው የየራሳቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያላቸው መሆኑ ይታወቃል። ከላይ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የአብሮ መኖር እሴቶች ናቸው ካልኳቸው አንጻር ግን ምንም ዓይነት ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም። ከዚህ አንጻር እኛ ሰዎች የመንፈሳዊ ልዕልናችንን ከእለት እለት ከምናስበውና ከምንፈጽመው ድርጊት ጋር ማያያዝ አለብን። ይህን ካደርግን እነዚህ ለሰው ልጆች አብሮ የመኖር እሴት መገንቢያ የሆኑ ባህሪያትን በቀላሉ ማዳበር እንችላለን። እነዚህን ባህሪያት ባዳበርን ቁጥር ደግሞ ለራስ ብቻ መኖር አልፈን ለሌሎች መኖር ጠቃሚነትን እንረዳለን።

ይህ የሩዋንዳዊቷ ወጣትና የሩዋንዳ ታሪክ ለመላው አፍሪካውያን ትምህርት ሰጭና የማይደገም (never again) ማድረግ ጠቃሚ ይመስለኛል። ሆኖም እንደአለመታደል ሆኖ አሁንም ከዚህ አስከፊ ታሪካዊ ክስተት መማር ያቃታቸው እንደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ቡሩንዲ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሌሎችም በከፍተኛ የእርስ በርስ ግጭት ላይ ይገኛሉ። ይህ የሆነው በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነና ሰፊ የምሁራን ጥናት እንደሚጠይቅ በመገንዘብ ከሌሎች ዓለማት አንፃር ስናየው አፍሪካ አሁንም ከግጭት አዙሪት (Vicious circle of conflict) መውጣት እንዳቃታት አናስተውላለን። የአፍሪካ አገራት መሪዎች በአህጉሩ ለሚከሰቱ ግጭቶች አፋጣኝ የሆነና ጠንካራ ምላሽ ያለመስጠትና የጋራ ፀጥታ የማስፈን ሚና (collctive security initiative) ደካማ መሆን የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ማሳደሩ አልቀረም። በመሆኑም የአፍሪካ መሪዎች ከሩዋንዳ የዘር ፍጅትም ሆነ ከሌሎች መጥፎ ክስተቶች ተምረው ህዝባቸውን አስተባብረው ዘላቂ የሆነ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

መደምደሚያ

በአጠቃላይ ይህ መጽሃፍ ለእኛ ኢትዮጵያዊያንና ለአፍሪካ ህዝቦች ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥና ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ይመስለኛል። በማንነት መኩራት መብታችን እንደሆነ ከማወቅ ባለፈ የአንድ ማህበረሰብ ሁለተናዊ ማንነት ክብርና ሞገስ ሊኖረው የሚችለው ለሌሎች ማህበረሰቦች ማንነት ክብርና እውቅና ሲሰጥ እናደሆነ ግንዛቤ መውሰድ ጠቃሚ ነው። በሩዋንዳ ከ1994 (እ.ኤ.አ) በፊት የነበረውን የሁለቱ ዘውግ ማህበረሰቦች የተዛባ ግንኙነት ማስተካከልና በሃገሪቱ ሰፊ የውይይት መድረክ ተከፍቶ ሃገራዊ መግባባትና የእርቅ እድሎች ቢኖሩ ኖሮ ምንአልባት የዚያን አይነት ፍጅት ባልተፈጸመ ነበር። አገራችን የተለያዩ ዓይነት ብዝሃነት ያለባት ሃገር ናት። ይህ ማለት ግን ህዝቦችን  የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም። በመሆኑም እነዚህን የጋራ የሆኑ እሴቶች ማጠናከርና ማጎልበት ይጠበቅብናል። ይህ ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋ የዜግነት ድርሻ መሆን ይኖርበታል። በአገራችን ሰፊ የሆነ ሃገራዊ መግባባት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ከላይ እስከ ታች የተዘረጉ ህዝባዊ መድረኮች ሊኖሩ ይገባል። በዚህ ረገድ ምሁሩ የመሪነት ሚና ሊጫወት ይገባል። በተለይም በሃገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይም በእውነተኛና ሳይንሳዊ በሆነ ሥልት እንዲሁም መሬት ላይ እያየን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ጥናትና ምርምር ሊጠናከር ይገባል። አገራችን ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ሥርዓት ማስፈኗ በጎ ቢሆንም ከአወቃቀሩና ከአተገባበሩ ጋር የሚታዩ ተቃርኖዎችን ግን ማስተካከል ይገባል። የፌደራሊዝም ሥርዓትን ስኬት ሊወስኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገቢ ይመስለኛል። ፌደራሊዝሙን ዲሞክራሲ መር ፌደራሊዝም ማድረግ የግድ ይላል።በመጨረሻም የህዝቦቻችንን አብሮ የመኖር እሴትንና አንድነትን ሊያጠናክሩ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ በዚህ በወርሃ የካቲት ለ120ኛ ጊዜ የሚከበረው የአድዋ ጦርነት ድል በዓል ነው። በመሆኑም ይህ ብዙ ትርጉምና ፈይዳ ላለው ብሔራዊ ክብረ-በዓል እንኳን አደረሳችሁ እያልኩ በዚሁ አበቃሁ።

ቸር እንሰንብት!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

 

አያሌው ዘለቀ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር ናቸው፡፡

ጸሐፊው ማናቸውንም ከቀና አእምሮ የሚመጣን አስተማሪ አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ስለሆኑ በአድራሻቸውzelekeayalew@yahoo.com  ወይም ayalewzeleke1977@gmail.com  ይጻፉ፡፡

posted by Geremew Aragaw

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: