The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

“ግጭቱ ያሳስባል፤ መንግሥት የሰላም ጥሪ ያቅርብ” – ተቃዋሚዎች – አለማየሁ አንበሴ

ethiopian opposition party

በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ግጭቶች ለመፍታት፣ መንግስት የሠላም ጥሪ በማቅረብ ብሔራዊ እርቅ መፍጠር እንዳለበት ተቃዋሚዎች ገለፁ፡፡ ችግሮቹ የተከሰቱት የፌደራል አደረጃጀት ትክክለኛ አቅጣጫ ስላልያዘ ነው በማለት የገለፀው ኢዴፓ በበኩሉ፤ መንግስት ስርአቱን መመርመር አለበት ብሏል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “መንግስትያለው አማራጭ፣ የሰላም ጥሪ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ እያቀረበ መሆኑንም ዶ/ር መረራ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

የተከሰተው ችግር የፌደራሊዝሙ ስርአት በትክክለኛ አቅጣጫ ስላልተቃኘ ነው ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና ኋላቀር የመናናቅ ስሜቶችም፣ ችግሮችን እንዳባባሱ ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥት አካላት በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን አስመልክቶ የሚሰጡ መግለጫዎች ህብረተሰቡን የሚያረጋጋና የሚያሳምን አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “በተደጋጋሚ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” ማለታቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ችግሮችን ተወያይተን በጋራ እንፈታለን ቢሉ የተሻለ ነበር ብለዋል፡፡
ግጭቱን ለማስቆም ከተፈለገ መንግስት ከህዝቡ ጋር በሰከነ መልኩ መነጋገር ያሻዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በጦርነት መንግስትን እንጥላለን ከሚሉት ሃይሎች ጋርም ቢሆን እርቅ መፈፀምና ብሄራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡

ኢዴፓ ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ ተቃውሞና ግጭቶቹ አቅጣጫቸውን እየሣቱ አደገኛ አዝማሚያ እየያዙ መምጣታቸውን ጠቅሷል፡፡ መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ  እለታዊ ግጭቶችን በማብረድና በሃይል እርምጃ ላይ አተኩሯል ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ ይህም መንግስት ችግሩን ለመፍታት ትክክለኛ አቅጣጫ እየተከተለ አለመሆኑን ያሳያል ብሏል፡፡

በሀገሪቱ ብዙዎቹ ግጭቶች፣ በብሄረሰብ ተወላጅነት ሰበብ የሚከሰቱ መሆናቸውን ኢዴፓ ጠቅሶ፣ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት፤ የፌደራል አደረጃጀቱ በአንድነት ላይ ማተኮር ሲገባው፤ በልዩነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው ብሏል፡፡ መንግስት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ በፌደራል አደረጃጀቱ ላይ ያለውን አቋም መመርመር እንዳለበት ፓርቲው ገልፆ፤ በዘር ላይ የተመሰረተ ግጭትን ሁሉም ህብረተሰብ ሊታገለው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ ችግሮቹ ከልክ እያለፉ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት ነገሮችን በሃይል ከማዳፈን ይልቅ የህዝቡን ድምፅ ማዳመጥና ድርድርን ማስቀደም አለበት ብለዋል፡፡

በግጭቱ በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ የሚሆን አካል መኖር አለበት ብለዋል፡፡
አክለውም መንግስት የተፈጠረውን ችግር ሳያድበሰብስ የሰውን ልብና አዕምሮ በሚያገኝ መንገድ በእውነተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የተወያዩት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎች፤ ግጭቶች ስር ሳይሰዱ ሊፈቱ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ልማት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ተከታዮቻቸውን እንደሚያስተምሩ ገልፀዋል፡፡

አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ተከታታይ ስራ እንሰራለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም የማስተማር ስራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት፤ ባለፉት 4 ወራት በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ግጭት 200 ሰዎች ገደማ ህይወታቸውን አጥተዋል ብሏል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ፤ ሂውማን ራይትስ ዎች  ኒውዮርክ ተቀምጦ እንዴት ስለ ኢትዮጵያ ችግር ሪፖርት ያወጣል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ተቋሙ ያወጣው ሪፖርት “ፈፅሞ ሃሰት ነው” ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በኦሮምያ ጉዳይ ላይ ዘገባ ያቀረበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ፤ “ተቃውሞው ከሚገመተው በላይ ነው” ብሏል። ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ፍርሃት መንገሱንና መረጃ የሚጠየቁ ሰዎች ስማቸውን ለመግለፅና መረጃ ለመስጠት እንኳን እንደሚፈሩ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: