The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

በዑስማን ሳልህ ኤርትራን ያስገነጠለች ካይሮ በጅዋር መሐመድ “ኦሮሚያ” ላይ ይቀናት ይሆን?

jawar

የአባይ ጉዳይ ለግብፆች የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የደንነታቸው ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል። “ግብፅ ያለ አባይ አሸዋ የሞላባት ሳጥን ናት” የሚለው  አገላለፅ ለጉዳዩ የሚሰጡትን ክብደት የሚያሳይ አባባል ነው።ስለዚህም  የአባይ መፍለቂያና ዋና ባለድርሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን  አባይን መጠቀም በማትችልበት ደረጃ ማዳከም ፣ ከተቻለም ጨርሶ ማፈራረስና ማጥፋት በካይሮ ዉጪ ፖሊሲ በቆሚነት እና በቀዳሚነት ቁጥር አንድ  አጀንዳ ሆኖ ግብፅ በሀገራችን ላይ በቀጥታም ፣በተዘዋዋሪም ተደጋጋሚ በደሎችን ፈፅማለች።

የግብፅና የኢትዮጵያ የአባይ ውዝግብ የሚጀምርው ግብፅን ለሰባት አመታት ቁም ስቅሏን ካሳያት ድርቅ ጋር ተያይዞ ነዉ።  እ.ኤ.አ. ከ1066 ዓ.ም እስካ 1072 ዓ.ም ግብፅ ዉስጥ ተከስቶ የነበረው ከባድ እርሀብ መነሻው ተፈጥሮአዊ ክስተት ቢሆንም  “አቢሲኒያዎቹ የአባይን የፍሰት አቅጣጫ አስቀይረውት ነው”  ብለው በመገመት በወቅቱ የግብፅ ከሊፋ የነበረው ከሊፋ ሙስታንሲት (1036-1094)  አምባሳደሩን በርካታ የወርቅ ስጦታ አሸክሞ ለአቢሲኒያው ንጉስ  ይመረሀና ክርስቶስ (1039 –  1077)  ልኮት እንደ ነበር ታሪክ ዘግቧል።  ሌላው ግብፅ በቱርኮች አገዛዝ ሥር በነበረችበት ወቅት ሲሆን “የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በነፃነት ካልተንቀሳቀሱ የአባይን የፍሰት አቅጣጫ እቀይራለሁ” የሚል እ.ኤ.አ. 1798 ዓ.ም  ከኢትዮጵያው ተክለ ሃይማኖት ለግብፁ አብዱላ ፖሻ የተላከው የማስፈራሪያ መልክት ነው። ምናልባት ከዚህ ሌላ ሊጠቀስ የሚችለው ከኢጣልያ ወረራ በኋላ “ቀጣዩ የኤርትራ እጣ ፈንታ እንዴት ይሁን” በማለት ተነስቶ በነ ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አሸናፊነት በተደመደመው የይገባኛል ክርክር ወቅት ግብፅም “ኤርትራ ለኔ ትገባለች” ብላ ወደ አባይ ለመጠጋት የሞከረችው ድፍረት ነው። ከነዚህ ሶሥት ታሪካዊ “የዲፕሎማሲ”  እሰጥ እገባዎች ቀጥሎ የተከሰተው ሰይፍ መዞ በጉልበት ጉዳዩን እልባት ለመስጠት መሞከር ነበር።

ግብፆች ዘወትር እንቅልፍ የሚነሳቸውን የአባይን አጀንዳ ለአንዴና ለመጨርሻ ለመዝጋት በመቀጠል የወሰዱት አቋም ኢትዮጵያን በሀይል ጠቅልሎ የአባይን ምንጭ መቆጣጠር ነበር። ለዚህም እ.ኤ.አ. ከ1832 እስከ 1876 ዓ.ም በ 44 ዓመታት ዉስጥ ለ16 ግዜ ትላልቅ ጦርነቶችን አድርገው ሁሉንም ጦርነቶች በዝረራ ተሸንፈዋል።ከነዚህም ውስጥ ወሳኝና የመጨረሻዎቹ  እ.ኤ.አ. በ1875 ዓ.ም  ጉንደት ላይ እንዲሁም ከአምስት ወራ በኇላ እ.ኤ.አ. በ1876 ዓ.ም ጉራ ላይ የአዉሮፖና የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር ልምድ ያላቸዉንን መኮንኖች ቀጥረዉ ጦርነት ገጥመዉ የአያቶቻችንን ጠንካራ ክንድ ቀምሰዉ የተመለሱበት ነው። ከዚህ መራር ሽንፈታቸው በኋላ ከአባይ ምንጭ እንደወረደ የመጠጣት ህልማቸው መክኖ  ኢትዮጵያን ቀጥታ ወርሬ ፣ አባይን ከምንጩ ልቆጣጠር የሚለው አጀንዳ ተዘጋ።

የግብፆች ኢትዮጵያን ቀጥታ የመውረሩ ድፍረት በጀግኖች አባቶቻችን እልባት ካገኘ በኋላ “እሳትን በሳት” ወደሚልና ዛሬ ላይ ቁመን ስናየው ውጤታማ የሆነችበትን ፖሊሲ ተከለች። ኢትዮጵያን ከዉስጦ በሚነሱ ሀይሎች  የማዳከምና የማፈራረስ ፖሊሲ። ይህንንም ተከትሎ የግብፅ የደንነት ክፍል የኢትዮጵያን  የውስጥ ደህንነት ሊያናጋ የሚችል ክፍተት ሲያፈላልግ ኤርትራን አገኘ። በነ ጸሓፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ብርቱ ትግል ፣ በተባበሩት መንግስታት  ውሳኔ በኢትዮጵያና በኤርትራ  እ.ኤ.አ. በ1952ዓ.ም  ተመስርቶ በ1962 ዓ.ል. የፈረሰው ፌዴሬሽንን ተከትሎ የተከፉ ወገኖች የግብፅን ቀልብ ሳቡ።በወቅቱ  የግብጹ ፕሬዘደንት በነበረው ጀማል አብደል ናስር “ኤርትራ አረባዊት ናት መገንጠልና የራስዋን እስላማዊ መንግስት ማቋቋም አለባት” ተባለና እ.ኤ.አ. በ 1961 ዓ.ም  “ተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ ወይንም በአረብኛ አጠራሩ  “ጀብሃት ታሕሪረል ኤሪቲሪያ”  (ጀብሃ)  የተባለ  ለኢትዮጵያ ካንሰር የሆነ እስላማዊ ቡድን በካይሮ ከተማ ተመሰረተ።  እንግዲህ ይህ ቡድን  “ሰልፊ ነጻነት” ፣ “ህዝባዊ ኃይሊ” እና “ዑበል” በተባሉ ዞንን ባማከሉ ሀይሎች ተቦድኖና እርስ በርሱ ሲጨፋጨፍ በርካታ አመታትን አሳልፎ በስተመጨረሻዉ “ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ” (ሻዕቢያ) በሚል ሀይል ተተካ። ሻዕቢያም በግብፅ ሎቢነት ዛሬ በዘሩት ልክ እያጨዱ ያሉትን ኢራቅና ሶሪያ ጨምሮ ከበርካታ አረብ ሀገራት፣ እንዲሁም ወቅቱ ደርግ በነበረዉ የፖለቲካ አሰላለፎ ቅሬታ ከነበራቸዉ ምራባዊያን ትጥቅና ስንቅ በገፍ እየቀርበለት ኤርትራን ገንጥሎ የግብፅን ኢትዮጵያን የማፍረሱን የመጀሐሪያዉን ተልኮ አሳካ።

ለመጀመሪያው  አክራሪ እስላማዊ ቡድን(ጀብሃ)  መጠንሰስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው የሚባለውና በኢሳያስ የሚመራውን “ህዝባዊ ግንባር” (ሻዕቢያ)ን የመሰረተው ፣ ከዛም በኋላ ድርጅቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠናከር ፣ ከላይ በተጠቀሱት አረብ ሀገራት  ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኝ  የውጪ ፖሊሲውን ስራ ሰርቷል ተብሎ የሚጠቀሰውና በተገነጠለው አካል ገድሉ የሚዘመርለን ዑስማን ሳልህ ሳቤ  የሚባል ከሳሆ ጎሳ የሚወለድ ሰው ነው። የዚህን ሰው ስም ማንሳት ያስፈለገው ስግለሰቡን ማንነት ለመተንተን ወይንም ስለፈፀመው የባንዳነት ገድል ለመዘከር አይደለም። በመሰረቱ አንድ ግለሰብ ከትውልድ ሀገሩ ውጪ በሆነ ሀገር የገዛ ሀገሩን እንዲያፈርስ ሲታጭ ግለሰቡ ሀገሩ ላይ ደባ ለመፈፀም  ወይንም በባንዳነት ለማገልገል  የሚያስችል የወደቀ ስብህና እንዳለው ማጣራት እንጅ የግለሰቡ ሌሎች ማንነቶቹ ጠቀሜታቸው እምብዛም ነው። ዋናው ስራ የሚሰራው በቀጣሪው ስለሆነ የተሰጠው ግዳጅ ውጤታማነት ከቀጣሪው የደህንነትና የሎጅስቲክ አቅርቦት ጋር ብቻ ስለሚገናኝ።እንግዲህ ግብፅ ይህንን መሰል ባንዳዎችን ተጠቅማ ከ 25 ዓመት በፊት ኤርትራ የምትባል እልውናዋን እንደ ግብፅ በኢትዮጵያ መፍረስ ላይ የተንጠለጠለ ፣ ለራሶ  ቆሚ አጋር ሆና እስከ ኢትዮጵያ መፍረስ ድረስ አብራት የምትጎዝ  ለኢትዮጵያ  ግን ነቀርሳ የሆነች  ሀገር መሰረተች።
በዚህም ኢትዮጵያ በጅጉ ተጎዳች ። ኤርትራ ሁለቱን ወደቦች ይዛ እንድትገነጠል ተደረና 100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ 1ሚሊዮን በታች ሕዝብ ባላት ፣  በቆዳ ስፋቶ ደግሞ ዛሬ የትግራይ ክልል የሌሎችን መሬትም ዘርፋ  ካላት መጠን በግማሽ ያነሰች  ጅቡት እግር ስር ወድቃ እንድትንደባለል ሆነ ። ዛሬ ኢትዮጽያ ኬንያን ሳይጨምር እ.ኤ.አ በ 1945 ተመስረቶ  ግብፅ ካይሮ መቀመጫዉ ያደረገዉ የአረብ ሊግ አባል በሆኑ ሀገሮች የተከበበች ወደብ አልባ ሀገር ናት። ኤርትራም ምንም እንኮን ዛሬ ታዛቢ ብቻ ብትሆንም  ኢሳያስ በሞተ በማግስት ሙሉ አባል እንደምትሆን ይጠበቃል። እንግዲህ የቀረችዋ ኢትዮጵያ በሆነ ምህታታዊ ሀይል በአንድነቱ ብትቀጥል ግብፅም ሆና መላዉ አረብ ሀገራት የማያዉቁት አንዳች ሚስጥረ አይኖራትም። በሆነ አጋጣሚ ከግብፅም ሆነ ከአንደኛው የአረብ ሀገር ጋር ጦርነት ዉስጥ ከገባን ደግሞ ከካይሮው የአረብ ሊግ ቢሮ ወደ ጅቡቲ በምትደረግ አንዲት የስልክ ጥሪ ሞቹ “ሸቀጥ” ያለውን ወደብ የመግዛቱ ነገር እንዲያከትም ሊያደርገው ይችላል።

ኤርትራ ለግብፅ ቆሚ አጋር ትሆናለች የሚለው ግምገማ ታሳቢ የሚያደርገው ማንም እንደሚገነዘበው ከግብፁ አጀንዳ ባሻገር ሻብያዎቹ  የመገንጠሉን ሒሳብ ያሰሉት ከ”ነፃነቱ” በኋላ ለሚኖርዉ ብልፅግናቸው የወደብ ሽያጭንና ሀገራቸውን የኢንደስትሪ ከተማ በማድረግ ላይ ነው። ለወደብ ችርቸራው የተቀረውን ኢትዮጵያ ከታሪካዊ ወደቡ በመነጠል ዝግ እንዲሆን ተደርጎል።ስለዚህ የኤርትራው ወደብ ለተቀረው ኢትዮጵያ ካለው ቀረቤታ አንፃርና ከህዉሃት ጋር ከነበረው ግኑኝነት በወቅቱ ሌላ አማራጭ  ሊታሰብ ይችላል ተብሎ አይገመትም።መለስ ዜናዊን ጨምሮ የህውሃት የበላይ ሀላፊዎች ኤርትራዊያን በመሆናቸው ህውሃት ላይ ከፍተኛ መተማመን ነበረ። እንደውም አንዴ አንድ በመለስ ዜናዊ ሞት በሀዘን ተኮማትሮ ያየሁት ኤርትራዊ አንተ ደግሞ ምን ቤት ነህናነው እንዲህ በሐዘን የምትወዘወዘው  ብየ ስጠይቅ “ለኤርትራ ኢሳያስ ከሰራው መለስ ዜናዊ የሰራው ይገዝፋል። መለስ ባይኖር ኖሮ ኤርትራ ሁለት ወደብ ይዛ አይደለም አንድም ይዛ መገንጠሉ ከባድ ይሆን ነበር” ብሎ እንቅጮን ነግሮኝ እኔም አምኘዋለሁ።ስለዚህ ከላይ ያለው ግምት ቢወሰድ አይደንቅም። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ነባር ሕዝቦች በዘርና በቋንቋ ተከፋፍለው ፣ በመሀላቸው ጠላትነት ነግሶ እርስ በርሱ እየተባላ እንዲበጣጠሱ፣ኢኮነሚያቸው ደቆ  “የአባት ሀገር ኤርትራ” ጥገኛ  እንዲሆኑ የሚያመቻቸው  ቻርተር (የዛሬው ሕገ መንግስት)  የተቀረፀት በእራሳቸው በሻብያዎች እና የኢትዮጵያና የአማራ ጠላት በሆነው በኦነግ መሆኑን መረሳት የለበትም። በተሰኔው ስብሰባ ኢሳያስና መለስ ኤርትራን  ሌንጮ ለታ ደግሞ ኦነግን ወክሎ መገኘቱን ልብ ይላል።

የሆነው ሆነና በነ ዑስማን ሳልህ ሳቤ ባንዳነት ግብፅ ኤርትራ ገንጥላለች።እስከ አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ ኢትዮጵያን የማዳከሙ ጉዳይ እውነት ቢሆንም ሻብያ ያቀደው “ኤርትራን አፍሪካዊ ሲንጋፖር” የማድረጉ ጉዳይ ለግዜው መክኖል።አልተሳካም። እንደውም ለ40 ዓመት የኢትዮጵዊያንን ደም እንደ ጎርፍ አፍስሳ ነፃ የወጣችው ኤርትራ በተቃራኒው ደህይታና ህውሃት በኢትዮጵያዊያን ውስጥ ተደብቆ ባሰኘው ሰሀት እንደ እፃን በሚኮረኩማት ደረጃ አንሳ፣ የኢኮነሚ አዉታር የሆነዉን ወጣት ሀይሏን በጦር ካምፕ አጉራ እንደቆቅ የሰቀቀን ሕይወት በመግፋት ላይ ትገኛለች።“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ አበው ዛሬ የኤርትራዎቹ እቅድ በትግራይ ህውሃቶች ሙሉ በሙሉ የተጠለፈ ይመስላል። የኤርትራ የኢንደስትሪ ብልፅግና ህልም  የትግራይ  ህልም ሆኖል። ኢትዮጵያን የማፈራረሱም አጀንዳም ወደ ትግሬዎች ዞሮ  ትግራይ የኢንደስትሪ ማህከል ሌሎች ክልሎች ደግሞ የትግራይን ሸቀጥ ተቀባይ ይሆኑ ዘንድ ከትግራይ ዉጭ ያለው የሕዝብ ንብረት እየተዘረፈ መሬቱ እየተቸረቸረ የትግራይ ኢምፓየር ምስረታ ላይ እንገኛለን። በዚህም በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል “ታላቋ ትግራይ” የምትባል ሀገር እንደ መጋረጃ ተዘርግታ ስለምትገኝ የኤርትራ ህልውና ከኢትዮጵያ መፍረስ ጋር ተሳስሮል ለማለት ያስደፍራል።

ይህንን በዚህ እንቆጭና ወደ ሁለተኛው አጀንዳ እንግባ። ለግብፆች ኤርትራን ማስገንጠሉ አንዱና ዋናው እቅድ ነው ብሎ መውሰድ ቢቻልም መደምሚያው ነው ተብሎ ግን አይታሰብም። ይህንንም በኤርትራው ግንጠላ ወቅት በሻብያ ውስጥ ያደፈጠው የግብፁ የደህንነት ቡድን ከኤርትራው ድሉ በኋላ  ለሁለተኛውና  ለመጨረሻው ኢትዮጵያን የማፍረሱ አጀንዳ “ኦሮሚያ” የተሰኘ ክልል እንዲዘጋጅ አድርጎል።  ይህ ወደ ዳግማዊ ዑስማን ሳልህ ወደ ሆነው የኦሮሞው ፅንፈኛ ጀዋር መሐመድ ጉዳይ በአዲስ መስመር ያሸጋግረናል።

ግብፅ በይደር ያስቀመጠችውን የ”ኦሮሚያዉን” አጀንዳ ኢትዮጵያ አባይን ግድብ ልገድብ ነው ባለችበት ወቅት ወደፊት እንደመጣ እ.ኤ.አ. ሰኔ3 ቀን 2013 ዓ.ም የሙርሲ መንግስ  በቀጥታ ስርጭት ሲመክሩበት መላው ዓለም ተመልክቷል። በዛን ወቅት በግብፁ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ሊወስዱ ይገባቸዋል ከተባሉት እርምጃዎች ዋናው  “ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከኤርትራ ፣ ከጅቡቲና ከሶማልያ ግኑኝነት በመፍጠ ወደ 35 ፐርሰንት የሚጠጋውና የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባር(ኦነግ) የሚባል ታጣቂ ቡድን ያለውን የኦሮሞን ማሕበረሰብን መጠቀም”  የሚለው ነበሩ። ይህንንም ተከትሎ እ.ኤ.አ. በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በ UNHCR  ቤሮ ፊት ለፊት ካይሮ ውስጥ በሚገኘው የኦሮሞ ማሕበረሰብ  በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ “የአባይ ግድብ ኦሮሞን እንደማይመለከት”ና ከግብፅ ጎን እንደሚቆሙ ገለፀ።  በመቀጠልም በዛው በወር ሰውዲ አረብያ ውስጥ በኢትዮጵያዊን ላይ ጥቃት ሲፈፀም የኦሮሞው ማሕበረሰብ “እኛ ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያዊያን አይደለንም” (We are not Ethiopians. We are Oromos)  የሚል መፈክር ይዞ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገውን የቱርኩ አልጀዚራ ከፍተኛ ሽፋን ሰጦት እንደነበር እናስታውሳለን። በተያያዥነት  እ.ኤ.አ. ጥቅምት 28, 2014 ዓ. ም ካይሮ ውስጥ  የሚኖረው የኦሮሞ ማሕበረሰብ ዳግመኛ በ UNHCR ቢሮ ፊት ለፊት ያካሄደው ሰላማው ሰልፍና “እኛ ኦሮሞዎች ከምንወዳት ኦሮሚያ ሀገራችን በሀይል ተባረርናል” በማለት ባለ 8 ነጥብ  የአቆም መግለጫ በማውጣት ካይሮ ለሚገኘው የ UNHCR እርጂናል ቢሮ ማስገባቱ፣  እ.ኤ.አ በግንቦ ወር በ2014 ዓ.ም ተሀሪረ እስኮር የአረብ ሊግ ፊት ለፊት በኦሮሞ ማሕበረሰብ  የተደረገው ተመሳሳይ ሰልፎች፣ አልጀዚራ የተሰኘው የቱርኩ ሚዲያ ኦሮሞ አካባቢ የሚፈጠሩ ኮሽታወችን እየተከታተለ ከማራገብ አልፎ  በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ “ኦሮሞ ፈርስት ነህ” ወይስ “ኢትዮጵያ ፈርስ” አይነት ጨዋታ ውስጥ መግባቱ  በሙሉ የሚያሳዩት ቀጣዩ የግብፅ ካርድ “ኦሮሚያ” የሚባለውንና የኢትዮጵያን ኦድ ለሁለት የሚከፍለውን ክልል የመገንጠልና ግብፅ “ምንግዜም ለህልውናዋ አደጋ አድርጋ የምታስባትን” ኢትዮጵያ ጨርሳ  ለማፈራረስ የወጠነችው ደባ መሆኑን መገምገም ይቻላል።

ከላይ ለመሞገት እንደተሞከረውና መሬት ላይ ያሉ ሀቆች የሚያሳዩት የኦሮሞው ማሕበረሰብ የካይሮን ቀልብ ስቦል። ስለዚህ ከሰሞኑ የኦሮሞ ተቆውሞ በስተ ጀርባም ግብፅ አታደፍጥም ተብሎ አይታሰብም።በውጤቱም በአባይ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ይዛው የነበረው አቋም መንሸራተት ጀምሮ እናያለን። እንደሚታዎቀው “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን” የተባለውን ፕሮጀክት ተከትሎ የተነሳው ተቋውሞ ጀርባውን ትተን አጀማመሩ ላይ  ከፊት ይዞት የተነሳው መፈክር “አርሶ አደሩ ከእርስቱ ሊፈናቀል ነው” የሚልና ጥያቄው የሰባዊ መብት ጥያቄ ነው በሚል ነበር። በኢሳት የተመራው የግንቦት ሰባት አርበኞች ቡድንና ሀገር ወዳድ ነን የሚለው የአንድነት ቡድን ባልተገመተና ባልተጠበቀ ፍጥነት ከሜንጫው ፖለቲከኛ ጃዋር ማህመድና ከኦነግ ጋር አብሮ ዓለም አቀፍ ሰለማዊ ሰልፎችን አደረገ። የኦሮሞ ሕዝብና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በህውሃት ላይ ጫና በማድረሱ የማስተር ፕላኑ እቅድ መነሳቱን ተከትሎ የኦሮሚያን አንድነት ያስጠበቀው የጅዋር ቡድን የግንቦት ሰባትና የአንድነቱን ቡድን በጠረባ አራግፎ  አጀንዳው “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ትሁን” “ኦሮሚያ ለኦሮሞ ብቻ” ፣ “የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ የፓለቲካ ተጠቃሚ ይሁን” እና መሰል አጀንዳዎች ዞሮ ድርድሩን ከህውሃት ጋር አደረገ።እንግዲህ ይህ አጀንዳ የተደናገጠውን የህዉሃትን ይሁንታ ካገኘ “የኦሮሚያ” መገንጠልና የግብፅ ኢትዮጵያን የማፍረሱ ጉዳይ ያለቀለት ይሆናል ማለት ነው።

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሰው በዑስማን ሳልህ የተጠነሰሰው ኤርትራን የማስገንጠሉ ኦፕሬሽንና ዛሬ በጀዋር መሐመድ እየተካሄደ ያለው “ኦሮሚያን” የማስገንጠሉ ኦፕሬሽን የሚያስተሳስራቸው አጀንዳ ቢኖር የግብፅ ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳ ብቻ ነው።ከዚህ ውጭ ሁለቱ እንደ ሕዝብ “ተገዛን” ፣ “ተጨቆንን” ብለው የሚጠቅሱት ከእውነት የራቀ ቢሆንም “የኦሮሚያው” ደግሞ አይን ያወጣ ቅጥፈት ነው። የኤርትራ ጉዳይ አንግበው የተንቀሳቀሱ ቡድኖች እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት ከላይ እንደተጠቀሰው ኤርትራን በጣልያን ለ50 ዓመት ቅኝ መገዛቷን ነበር። የጅዋር “ኦሮሚያ”ግን በዚህ መልክ እንኮን ሊጠቀስ የሚችል ምንም አይነት ታሪካዊ መሰረት የላትም። ሌላው ዑስማን ሳልህና ጎዶቹ የጥንቷ ባሕረ ነጋሽ የአሁኗ ኤርትራ ነባር ሕዝቦች ናቸው። ጅዋርና ጎዶቹ ግን ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት “ኦሮሚያ” የሚሉት አጥር ውስጥ ኦሮሞ የሚባል ሕዝብ እንዳልነበረ እነሱም አይክዱም።  ይህ ማለት እንግዲህ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል ድፍረትን አያመጣም።እዚህ በምራቡ አለም ውስጥ አምስትና ስድስት ዓመት  ተቀምጦ ፣ዜግነት የወሰደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ “እኛ እንግሊዛዊያን” “እኛ አሜሪካዊያን” “እኛ ካናዳዊያን” ሌላም ሌላም እያለ ከ400ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረውን የኦሮሞ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያዊነት የሚጠራጠረ ጅል ብቻ ነው። ነገር ግን ዲሲ(DC) ከብዛታችን አንፃር ሁለተኛዋ የኢትዮጵያዊያን ከተማ ናት ተብሎ ዲሲን እንገንጥል አይነት ድፍረት እንደማይሞከር ሁሉ ኦሮሞም “ኦሮሚያ” ያላትን ክልል ለመገንጠል ማሰብ ድፍረትም ቅሚያም ነው። ሚኒሶታ በርካታ ኦሮሞዎች አሉ ተብሎ “ሚኒሶታ ኬኛ” እንደማይሞከር ሁሉ ሸዋ ብዙ ኦሮሞ ስላለ “ሸዋ ኬኛ” አያስኬድም።በቱርክ ከተመራውን ግራኝ መሐመድ ጀርባ አድፍጦ የወረሩትን ማሀል ኢትዮጵያ በዋናነት በግብፅና በቱርክ ተመርቶ ኤርትራን ከገነጠለውና ተወካዩን ዛሬም ድረስ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ከተከለው ሻብያ ጀርባ አድፍጦ ከነባሩ ሕዝብ እጅ ለመንጠቅ የሚደረግ ደባ እንጅ አንዳች ታሪካዊ መሰረት የለውምና።

ታሪክን ካነሳን ዘንድ በ15 ኛው መቶ ክ/ ዘመን ሸዋን ጨምሮ ሌሎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አውራጃወች ምን ይመስሉ እንደነበር ታሪክን እንምዘዝ። ከግራን መሐመድ ወረራ በፊት ማለተም የበረይቱማና የቦረን ልጆች (ኦሮሞዎች) ወደማህል ኢትዮጵያ ከመፍለሳቸው በፊት አፂ ናኦድ  ለአፂ ልብነ ድንግል ያወረሰውን ግዛት ታሪክ ፀሐፊው አቶ ይልማ ደሬሳ “የኢትዮጵያ ታሪክ በ16 ኛው ክ/ዘመን” በሚል መፀሐፋቸው በዚህ መልኩ ይተርኩልናል።“በስተ ሰሜን የዛሬው ሐማሴን ሠራዬ አካለ ጉዛይ ሣህልና የባሕር ወደቦች ከሱዋኪም እስከ ገርዳፏይ ድረስ ያለው አገር ባሕር ምድር የሚጠራው ሲሆን ዋና ከተማው ደብሮአ ነበረ። ትግሬ ከሞላ ጎደል የዛሬውን ወሰኑን እንደያዘ ነበር ። እዚህጋ የዛሬውን የሚለው  መፀሐፉ የታተመው እ.ኢ.አ. በ1959ዓ.ም የነበረውን የትግራይ ግዛት የሚያመለክት ነው። በቅርቡ VOA ላይ ቀርበው የነበሩትና በወቅቱ  (ከ1953-1966)  የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ጠቅላይ ገዥ የነበሩት የአፄ ይሃንስ የልጅ ልጅ ልኡል ራስ መንገሻ ስዩም  እንዳስረዱት ከመረብ በታችና ከተከዜ በላይ ያለውን የትግራይ ታሪካዊ ግዛትን ነው።ይህ ግዛት በአፄ ልብነ ድንግል ዘመንም የትግሬ ገዢ በነበሩት ትግሬ መሆኒ የሚተዳደር ነበር።ከትግሬ በስተ ደቡብ ምዕራብ ጸለምት ፣ስሜን(ወልቃይት)ና፣ጠገዴ የንጉሰ ነገስቱ ግዛት ነበሩ። በጌምድርና ጎጃም የዛሬዎቹን (1959ዓ.ም የነበረውን ለማለት ነው ) ወረዳዎች እንደያዙ ነበሩ።ከትግራይ በስተ ደቡብ አዘቦ የጁና ወሎን ጨምሮ አንጎት ይባል የነበረው ሲሆን ይህም ከዋናዎቹ የንጉሱ አውራጃዎች አንዱ ነበር። ከአንጎት በስተ ደቡብና ከአዉሳ በስተ ምስራቅ እንዲሁም በምስራቅና በደቡብ ከዳውሮ ግዛት የሚዋሰነው የሸዋ ግዛት ለንጉሰ ነገስቱ ዋና ምሽግ ሆኖ የቆየነው። በ13ኛው መቶ ዘመን የዛጏዬ መንግስት ወድቆ የሰለሞን ነጋሲ ወገን የሆነው አፄ ይኮኖ አምላክ አልጋውን ከተረከበበት ዘመን አንስቶ የነገስታቱ ዋና ሰፈር ሆኖ የቆየው የሸዋ አውራጃ እና ደቡብ አንጎት ነበር።በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ አፄ አምደ ጽዮንና አልጋ ወራሹ  አፄ ሰይፈ እርዕድ ቀጥሎም በ15ኛው መቶ ዘመን ውስጥ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ በየ ዘመናቸው ሱልጣናዊ ግዛቶቹን እየወጉ ይፋትን ፣ደዋሮን ፣አዳልልና ሐረርን እስከ ዉቅያኖሱ ፈጠግራንና ባሌን ያስገበሩት ሰፈራቸውን ሸዋ አድርገው ነው።”በዛ ወቅት ከላይ የተጠቀሰው  በትግሬ ግዛት ዉስጥ የሚገኙ አገሮችና ሹማምቶች አብዛኛውን ጊዜ በትግሬ መሆን ሥልጣን ሥር የሚታዘዙና የሚተዳደሩ ሲሆን አንዳንድ ግዜ ደግሞ የቀጥታ ግኑኝነት እያደረጉ በንጉሰ ነገስቱ ይታዘዙ ነበር። የተቀሩት አውራጃዎች ግን ሙሉ ለሙሉ በንጉሰ ነገስቱ ስር እንደነበሩ ተገልፆል።

ሀሳቤን ለማጠቃለል  በአንድ ወቅት አምባሳደር እምሩ ኢሳት እንግዳ አድርጎ ጋብዞቸው ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ስዊዝ ባንክ አስቀምጠው ነበር ተብሎ ስለሚታማው ገንዘብ ጉዳይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር። የአምባሳደሩ መልስ የነበረው “ንጉሳዊያን እኮ ኢትዮጵያን እንደ ግል ንብረታቸው ነበር የሚቆጥሩት ስለዚህ እንዴት አድርገው ነው የራሳቸውን ንብረት የሚዘርፉት” ይዘት ያለው መልስ ነበር የሰጡት።እንግዲህ ከላይ ታሪክ ጠቅሰን እንዳየነው በወቅቱ ከነበረው ከትግራይ አውራጃ ውጪ ያሉ የኢትዮጵያ አውራጃዎች በሙሉ ከአማራው ማሕበረሰብ በተገኙት ነገስታት ዉስጥ የሚተዳደሩ ነበሩ ። የአማራ ሕዝብ እነዛን አውራጃዎች ከነባር  የኢትዮጵያ ሕዝቦቻ ጋር አብሮ የሚጋራና የአባቶቹም እርስት የነበሩ ናቸው። አማራ በብሔር ይሰባሰብ፣ አማራ ይደራጅ ፣አማራ እንደ ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት (ሞረሽ)  አይነት ሲቪክ ማህበራትንና እንደ የቤተ አማራ ንቅናቄ(ቤአን) ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ  ይክተት እያልን ያለነው የአማራ ብሔርተኝነት ከጎጣዊ ብሔርተኝነት ከፍ እንደሚል ስለምናምን ነው።ባለቤት ቤቱን አይዘርፍም፣ አያፈርስም፣ አጥሩን ያጠብቃል እንጂ አይነቃቅልም ። ባለቤት ልጆቹን ይከባከባል እንጂ በትኖ ለችግር አይዳርግም ። የባለቤትን መዘናጋት አይቶ አጥሩን የሚደፍርና የሚንድ ፣ንብረቱን የሚዘርፍ ሌባ ብቻ ነው ብለን ስለምናምን ነው።

ቸር እንሰንብት!!!

(ግዜነው ደም መላሽ)

EMF

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: