The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ያልተጠናቀቀ ጦርነት፣ያልተቋጨ ትግል! (አገሬ አዲስ)

1-ethiopian-order-battle-the-second-italo-ethiopian-war

የዛሬ መቶ ሃያ ዓመት አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የወጠኑት ሴራ የከሸፈበት፣በምድረ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦር ሜዳ የጣሊያን ወራሪ ሃይል ድባቅ ተመቶ ያገራችን ነጻነት የተከበረበት የድል ቀን በመሆኑ በየዓመቱ እናከብረዋለን።የአድዋ ጦርነትና የተገኘው ድል የመጀመሪያ ሳይሆን የመጨረሻው እንደሆነ ታሪክ ይዘግባል። ሆኖም ግን የጦርነትና የወረራ መጨረሻ አልሆነም።

ከአድዋው ጦርነትና ድል በዃላ የወራሪው የጣሊያን ሃይል ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ መሬት ሳይወጣ በኤርትራ ክፍለሃገር ለአርባ ዓመት ተንሰራፍቶ ለመኖር ሲችል ይህም ለሁለተኛው ጊዜ የወረራ እቅድ የመዘጋጃ ዕድል ፈጥሮለታል።የአድዋውን ጦር መርተው ለድል ያበቁት አጼ ሚኒሊክ በገጠማቸው የትጥቅና ስንቅ እጥረት፣በድርቅና በበሽታ መከሰት የብዙ ሕዝብ ሕይወት በማለፉና ወታደራቸውም ቀጣይ ጦርነት ለማካሄድ አቅም ስለተሳነው፣በተጨማሪም በምስራቅና ደቡብ የኢትዮጵያ ድንበርና  እንዲሁም በመሃል አገር በተፈጠረው የጠላት ሰርጎ ገብ አደጋ ምክንያት በችግር ላይ ችግር ስለተከሰተባቸው ጠላታቸውን ሙልጭ አድርገው ከቀይ ባሕር ወዲያ ሳያሶጡ  ፊታቸውን ወደ መሃል አገር ለመመለስ ተገደዋል።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የጠላት ወራሪ ሃይል ለዳግመኛ ወረራ የመዘጋጃ ዕድል ከፈተለት። ለአርባ ዓመታት ሲዘጋጅ ቆይቶ በአጼ ሃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ተመልሶ መላ አገሪቱን ለመውረር መንቀሳቀስ ጀመረ።በዚህ ጊዜ ቀድሞ ከነበረው ዝግጅት የላቀ አዲስ የጦር ሃይል በአየር ሃይልና ዘመናዊ መሳሪያ፣በመርዝ ጭስና ቦምብ የታገዘ ብዛት ያለው ወታደር ከአገሩ ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ከያዛቸው አገሮች ጭምር፣ከኤርትራ፣ከሶማሊያ፣ከሊቢያ የመለመላቸውን ባንዳ ሰራዊት አሰልፎ ተንቀሳቅሶ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት ገጠመ።ከአምላኩና ከአንድነቱ በስተቀር ዘመናዊ መሳሪያ ያልታጠቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቂት የሰለጠኑ ወታደሮችና በጣት የሚቆጠሩ ዘመናዊ ከባድ መሳሪያዎችን ይዞ ወረራውን ለመቋቋም ከመሪዎቹ ጎን ተሰለፈ።

የጠላት ሃይል እንደ እባብ እየተሳበ የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ ትግራይ መሬት እንደገባ ንጉስ ሃይለሥላሴ እንደ ቀድሞው የአድዋ የድል ባለቤት እንደ አጼ ምኒሊክ ወታደራቸውን መርተው ማይጨው ላይ ጦርነት ገጠሙ።ብዙ ትንቅንቅና የጨበጣ ውጊያ ሳይቀር አካሂደው የጠላት ጦር በመሬት ሳይሆን በአየር ላይ ባለው የበላይነት፣  ከሚያወርደው የቦምብና የመርዝ ጭስ ጉዳቱ ስለበዛ ለመቋቋም ሳይቻል ብዙ መስዋእት ተከፍሎ የኢትዮጵያ ወታደር ለመበታተንና ለማፈግፈግ ተገደደ፤ንጉሱም ባገራቸውና በሕዝባቸው ላይ የደረሰውን በደል ለዓለም ፍርድ ለማቅረብ ለመሰደድ ተገደዱ።ያፈገፈገው የኢትዮጵያ ተዋጊና የጦር አለቆቹ የጠላትን የበላይነት አምነው ባለመቀበል የውጊያ ስልታቸውን በመቀየር በዱር በገደል የሽምቅ ውጊያ ለማካሄድ ወስነው ጫካ ገቡ።ለአምስት ዓመት በዚህ የአርበኝነት ትግል ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ  ጠላትን እንቅልፍ ነሱት። በመጨረሻም የዓለም ሁኔታ ተለዋወጠና በወራሪ የአውሮፓ መንግስታት መካከል የጥቅም ግጭት በመነሳቱ እርስ በርሳቸው መባላት ሲጀምሩ ለኢትዮጵያኑ አርበኞች ትግል ስኬታማ ውጤት አመጣላቸው።አገራቸውን ከጠላት መንጋጋ አላቀቁ።ይህም ለኢትዮጵያኑ በጣልያን ወራሪ ሃይል ላይ ሁለተኛ ድል ሆነ።

የአውሮፓ ወራሪ ሃይሎች በኢትዮጵያ ባይሳካላቸውም በሌላው የአፍሪካ፣፤የደቡብ አሜሪካ፣የኤሽያና የካሪቢያን አገሮች ላይ የዘረጉት የቅኝ አገዛዝ መረብ ሳይበጠስ ለመቆየት ችሏል።የኢትዮጵያውያን ትግልና ድል ለነዚህ አገር ሕዝቦች እንደምሳሌ በመሆን ለነጻነታቸው የሚያደርጉትን ትግል እንዲቀጥሉበት ያደፋፈራቸው ሲሆን ለማይቀረው ነጻነትም አብቅቷቸዋል።

በአድዋና በማይጨው ጦር ሜዳ የተካሄደው የነጻነት ትግልና ድልም ሆነ በየአገሩ የተካሄደው የነጻነት ትግል ዘላቂ ነጻነት አስገኝቷል ማለት አይቻልም።ምንም እንኳን አገሮች የራሳቸውን ባንዲራ ለመስቀል ቢችሉም በወራሪ የቅኝ ገዥዎች እግር የተተኩት አገር በቀል መሪዎቹ ከወራሪዎቹ የባሱ የጥቁር ፈረንሳዮች፣እንግሊዞች፣ጣሊያኖች፣ደቾች፣ ቤልጅጎች፣…ወዘተ ሆኑና አረፉት።ቃንቋቸው፣ባሕላቸው፣ ስማቸው ሳይቀር  አስተዳደራቸው ሁሉ የወራሪዎቹ  አይነት ሆነ።ሕዝብ በገዛ አገሩ ተወላጆች መከራውን ማየት ጀመረ።በቀጥታ ወረው ለመበዝበዝ ያልቻሉት አውሮፓውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛቸውን በመዘርጋት የጥቅም አጋር የሚሆኗቸውን አገር በቀል ከሃዲዎች ስልጣን ላይ እንዲወጡ  አደረጉ።በቀጥታ ወታደራቸውን በጦርነት ከማሰለፍና ከማስጨረስ ይልቅ ዓይን የጣሉበት አገር ሕዝብ በራሱ ወገኖች እየተገደለ፣አገር ወዳድ መሪዎች ከስልጣን እየተወገዱና ወደ ስልጣንም እንዳይጠጉ በማድረግ ልዩ ልዩ ዘዴ በመፍጠር  ጥቅማቸው እንዲከበር አደረጉ።በየጊዜው የማሳሳቻ እቅድ እያወጡ ሕዝቡን አወናበዱት።በዘመናችን አሁን ሰፍኖ የሚታየው የግሎባላይዜሽን(globalization) ቅምርም የዚህ የብዝበዛ ስልት አካል ነው።በህወሃት/ኢሕአዴግ የሚመራውም ስርዓት የዚሁ የወረራና የብዝበዛ አካልና የአንድ ሳንቲም ገጽ ነው።

በየአገራቱ የሚታየው ትርምስ፣ጦርነት፣ስደት፣ ድህነት ሁሉ የዚሁ የእጃዙር ቅኝ አገዛዝ  ከይሲ አስተሳሰብ የወለደው መከራ ነው።አገራት ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሊሆኑ የሚችሉት እኛም ኢትዮጵያውያን ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆነን መኖር የምንችለው በአገራችን ጉዳይ ላይ  ለመወሰን ስንችል፤ነጻ አገራዊ ኤኮኖሚና ፖለቲካ አመለካከት ስንከተል፤ከውጭ ተጽእኖ ስንላቀቅ፣ከሌሎች አገራት እርዳታና ዳረጎት ስንገላገል፣ያለንን የተፈጥሮ ሃብትና ጸጋ ፣ተፈጥሮ ያደለንን ለም መሬትና ወንዞች ተጠቅመን ድህነትን፣እርሃብን ድል ስንመታ ብቻ ነው ዘለቄታ ያለው ድልና ነጻነት ተጎናጽፈናል ብለን ለመናገር የምንችለው።ያ እስካልሆነ ድረስ ባንዲራ ብቻ ስላውለበለብን ነጻ ነን ማለት አይቻልም።ለዘላቂው ነጻነት በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጠላቶች ማንበርከክ ይኖርብናል፤ያም ሊሳካ የሚችለው እንደ አደዋው ጊዜ ተባብረን፣በአንድነት ስንታገልና የተጋረጠብንን አደጋና ጠላት ስናስወግድ ነው።ያ ሲሆን ብቻ ነው አፍን ሞልቶ ነጻ ሕዝብ ነን ማለት የምንችለው።

አሁን በየአቅጣጫው የተቀጣጠለው የሕዝብ መነሳሳትና እንቅስቃሴ በጠላቶቻችንና በእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ሳይጠመዘዝ በእውነተኛ ሰብአዊና አገር ወዳድ ትግል አቅጣጫ እንዲቀጥልና ለድል እንዲበቃ ነጻነትና እኩልነት አፍቃሪው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚችለውን ማበርከት ይኖርበታል።ወራሪዎችና አገልጋዮቻቸው ሕዝቡን በክልል፣በቋንቋ በሃይማኖት ለመከፋፈልና ለማዳከም የሚያደርጉትን ጥረትና ሙከራ በህብረት ተቋቁመን አሳፍረን ልንመልሳቸው ይገባናል።አለበለዚያ አገረ ቢስ ሆነን፣ከአገር ይልቅ የመንደር ነዋሪዎች ሆነን፣ እጣ ፈንታችን ከትልቅነት ትንሽነት ይሆናል።የዓለምም መሳቂያ መሳለቂያ ሆነን እንቀራለን። ከዚህ አይነቱ አደጋ ለመታደግና እንደ አደዋው ድላችን ለሌሎቹ ምሳሌ ለመሆን የዘመናችንን፣የራሳችንን አደዋ መድገም ይኖርብናል። የአባቶቻችን ታሪክ እንደምሳሌ መውሰድ እንጂ እጃችንን አጣጥፈን  እያወደሱ ብቻ መኖር ጥቅም የለውም። ሌላው በሰራው ጀግንነት መመጻደቅና መኩራትም ተገቢና ትክክል አይደለም።የሃይማኖት አባቶችም ከአቡነ ጴጥሮስ ተጋድሎ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል፤ ክርስቶስ ያልተሰቀለበትን የወርቅ መስቀል አንዠርግጎ በስጋዊ ድሎትና ጥቅም እየተነታረኩና አገር አጥፊ ለሆነ ስርዓት እየጸለዩ መኖር ምድራዊ ሃጢያት መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል።ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ሌላው ቢቀር “አትግደል” “አትስረቅ” የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ የሚጥሰውን መንግስት ሊያወግዙት ይገባል።የእስልምና ሃይማኖት ተከታይም እግሩን ኢትዮጵያ ላይ ተክሎ ልቡን  ወደ ሳውዲ ማድረጉ የሚጎዳው መሆኑን አውቆ ትኩረቱ ለተወለደባትና መስጊድ ባቋቋመባት አገር ላይ ሰላምና መከባበር የሚኖርበትን መንገድ ቢከተል እራሱን አድኖ ሌላውንም ማዳን ይሆናል።ከአገር በላይ አገር የለምና ክርስቲያኑም ሆነ እስላሙ ከሃይማኖት በፊት ለኖረችና ወደፊትም ለምትኖር አገሩ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።መስጊድም ሆነ ቤተክርስቲያን ሊገነባ የሚችለው አገር ሲኖር ነው።ለክርስቲያኑ እየሩሳሌሙ፣ ለሙስሊሙም መካው ኢትዮጵያ አገሩ መሆን ይኖርባታል።

በምሁር ደረጃም የሚገኘው ወገን ትክክለኛ የምሁርነትን ምነነት በሚገልጸው አመለካከትና ተግባር ላይ ቢሰማራ፣ሕዝብን ከመከፋፈል ይልቅ ስለመቻቻል፣አብሮነትና አንድነት ጥቅም፣ስለደግነት በማስተማር ግንባር ቀደም ቢሆኑ አደራቸውን ተወጡት ማለት ነው።የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም የሚያነጣጥሩት በምንም መንገድ፣በውጭ እርዳታም ቢሆን ስልጣን ላይ የሚወጡበትን ሳይሆን በሕዝብ ድጋፍና ምርጫ በስልጣን ላይ ተከብረውና ሕዝብ ወዶና ተቀብሏቸው የሚኖሩበትን ቀና አስተዳደር የሚመርጡ ቢሆን ከአድዋው ጀግኖች ባላነሰ ደረጃ ሕዝብ ሊኮራባቸውና በታሪክ ሊያስታውሳቸው እንደሚችል አውቀው አስተሳሰብና አካሄዳቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል።ነጋዴና ሃብታም የድካሙን ውጤት በሰላም ደስ ብሎት ሊጠቀም የሚችለው ሰላም የሰፈነበት፣ሕዝብ ተስማምቶና ተደስቶ የሚኖርበት ስርዓት ሲኖር ብቻ እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል። መሪዎች ከሕዝብ እየዘረፉ በውጭ አገር ባንክ የሚያጠራቅሙት ገንዘብ የዃላዃላ የባንኮቹ ባለንብረቶች ሲሳይ እንደሚሆን ከነሞቡቱ ሴሴሴኮ፣ከቦካሳ፣ከፊሊፒንሱ ፈርዲናንድ ማርቆስ…ወዘተ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል።ወይም ሕዝብ ስልጣኑን ሲረከብ በሕጋዊ መንገድ የሚያሰመልሰው እንደሚሆን በቅድሚያ ተረድተው ከአድራጎታቸው ቢቆጠቡ ለእነሱም ለቤተሰባቸውም የተሻለ ይሆናል።

ለዳግመኛ የዘመናችን፣የእኛ ለሆነው የየካቲት ድል ተባብረን እንታገል!

የጋራ ቤታችንን፣ኢትዮጵያን ከመፍረስ አደጋ እናድናት!

አገሬ አዲስ

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: