The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

“የማንነት ጥያቄ በሃይል አይገታም” – በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የጠለምት ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ

Telemet

የካቲት 30 ቀን 2008 ዓ/ም ኢትዮጵያን በማፈራረስ፣ ሃብቷን በመዝረፍ፣ ሕዝቧን በማሳደድ፣ በማፈናቀልና በማሰቃየት ለ 25 ዓመታት ያህል በመሳርያ
ሃይል አስገድዶ በመግዛት ላይ ያለው ጠባብ በሄርተኛው ወያኔ፣ በሕዝብና በአገር ላይ እየፈፀመ ያለው ግድያ፣ እስራት፣ እንግለት፣ሰቆቃና ግፍ በቀላል ቋንቋ ለመግለጽ ያዳግታል።
ገና ጫካ እያለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ቃለ መሃላ አድርጎ የመጣው ዘረኛው ወያኔ በሕዝብና በሃገር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት መቆምያ አጥቶ እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ታላቋን ትግራይ ለመመሥረት በሚል ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የተመረዘው ወያኔ(ህውሃት) በለምነታቸዉ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጠቃሚነታቸው ዉብ በሆኑ ወንዞችና ጅረቶች የተከበቡና እስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች ለትግራይ ክ/ሃገር አጎራባች ከሆኑት ክፍላተ-ሀገራት ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱን ይታወቃል።

ወያኔ ኢትዮጵያን በጠመንጃ ሃይል ስልጣን ከተቆጣጠረበት ከ1983 ዓ/ም ጀምሮ የታላቋን ትግራይ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ለምና ወሃ-ገብ የሆኑትን የጎንደር ወረዳዎች፣ ወልቃይት፣ ጠገዴንና ጠለምትን ከወሎ ክ/ሃገር ደግሞ ወደ አራት የሚሆኑ ወረዳዎችን በትግራይ ክ/ሃገር ሥር እንዲሆኑ አድርጓል;

ጠለምት፣ በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በጎንደር ክ/ሃገር የሚገኝ አማራ፣ የአማራ ባህልና ወግን የሚከተል ሕዝብ ለመሆኑ ታሪክ ያረጋገጠው ሃቅ ነው። የጠለምትን መልከዓ-ምድር አቀማመጥን ስንመለከት፤ በሰሜን ተከዜ ወንዝን ተከትሎ ትግራይ፤ ክ/ሃገርን በምሥራቅ እንዲሁ ተከዜን ወንዝን ተከትሎ ተንቤን አውራጃ(ትግራይ) እና ዋግ አውራጃ(ወሎን)፤ በምዕራብ ወልቃይትና ጠገዴ፤ በደቡብ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸጉ በጎንደር ክፍለ-ሃገር የሚገኙ የሰሜን ተራራዎች ስንሰለት ያዋስናል።

የተለያዩ የውጭ ወራሪ ጠላቶች በተለያዩ ጊዜያት አገራችን ኢትዮጵያ ለመውረር ሲመጡ፤ ጀግናው የጠለምት ሕዝብ የአገሩን ነፃነትና ዳር ድንበር ለማስከበር በተለያዩ የጦር ሜዳዎች በቆራጥነት በመዝመት በኢትዮጵያ ታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ታላቅ አንጸባራቂና አኩሪ ታሪክ የሠሩ፤ በ5 ዓመት የጣሊያን ወረራ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙ እውቅና ስመ ጥር አርበኞችን ያፈራ ሕዝብ ነው።

የጠለምት ሕዝብ ልክ እንደ ወገኖቹ ወልቃይትና ጠገዴ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የሚያዋስነው ተፈጥሮአዊ ድንበር የማይሞተውና የማይዋሸው የተከዜ ወንዝ ሲሆን ረጅሙ ገናናው የኢትዮጵያ ታሪክም የሚመሰክረው ይኸኑን ዕውነታ ነው። ለግንዛቤ ያህል፤ ሩቅ ሳንሄድ፤ በዘመነ መሳፍንት ጊዜ የአማራ ተወላጆች የነበሩ መሪዎች እንደ ራስ ወልደሩፋኤል፣ ልጃቸው ራስ ገብሬ፣ ራሰ ኃይለማርያም እና ደጃዝማች ውቤ ይገዙት የነበረው ግዛት ከባንብሎ (ከጎንደር ከተማ በስተሰሜን በኩል በግምት 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝው ጉርድ መሬት) እስከ ተከዜ ወንዝ ያለውን ሠፊ ግዛት ነበር። ይኸም ሠፊ ግዛት አሁን የምናውቀውን ወገራ አውራጃ (ወገራ፣ ዳባት፣ ጠገዴ፣ ወልቃይትና ሰቲት ወረዳዎች) እና ሰሜን አውራጃ (ደባርቅ፣ ድብባሕር፣ ጠለምት፣ ጃናሞራና በየዳ ወረዳዎች) የሚጠቀልል ነበር። እንድያውም ታላቁ መሪ ደጃዝማች ውቤ ይገዙት የነበረው ግዛት ይህ ብቻ ሳይሆን፤ ትግራይንና ባሕረ-ነጋሽን (ኤርትራን) ጨምሮ ነበር።

ዘመነ መሳፍንት አክትሞ፤ ታላቁና ገናናው የኢትዮጵያ መሪ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት፤ እንዲሁም በአፄ ዮሐንስ አራተኛ፤ በአፄ ምንሊክ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ እና በኮሎኔል መንግሥቱ ዘመናት የትግራይና የጎንደር አማራ ሕዝብ ተፈጥሯዊ ድንበር ተከዜ ወንዝ እንደሆነ ታሪክ ያረጋገጠው ሃቅ ከመሆኑም ባሻገር የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት መስራች አባል የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ኢንጅነር ግደይ ዘራዓፅዮን፣ አቶ ገብረመድህን አርአያ፣ አቶ አስገደ ገብረስላሴና የትግራይ ጠቅላይ ግዛት አገረ ገጅ የነበሩት የተከበሩ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ያረጋገጡት ነው።

TPLF(ወያኔ) የትግራይ አገዛዝ ተከዜን ወንዝ የተሻገረው “ታላቋን ትግራይ” ለመመሥረት ባቀደው እቅድ መሠረት፤ ለምና ወሃ-ገብ የሆኑትን የጎንደር ወረዳዎችን ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምትን በተቆጣጠሩበት በ17 ዓመት የሽፍትነት ጊዜና ከ25ዓመት በፊት መላ ኢትዮጵያን በሃይል በመዳፉ ሥር ባሰገባበት ወቅት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ይወያኔ ታጋይዮች የነበሩና ደጋፊዎቻችወን አምጥቶ በወልቃይት፣ በጠገዴና በጠለምት አስፍሮ ለዘመናት በጋራ አብሮ ይኖር የነበረን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና እንዲጠላላ አደረገ።ወደ። የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) ከላይ የተገለፁትን ወረዳዎች ተቆጣጠሮ ወደ ትግራይ ክልል ካስገባቸው ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ 1983 ዓ/ም መጨረሻ አካባቢ፤ አንድ የወያኔ ባለሥልጣን ታማኝ ካድሬውን ወደ አዳርቃይ ከተማ ልኮ ነበር። ካድሬውም በከተማው የሚገኙትን ታላላቅ አዛውንቶች ስብስቦ በማናገር ላይ እያለ “ የትግራይን ድንበር” እስከየት እንደሆነ ታውቃላችሁ ወይ? ብሎ ሲጠይቅ፤ ንግግሩን በጽሞና ይከታተሉ የነበሩት የአገሬው ሰመ ጥሩ አዛውንት “ ልጄ! የትግራይ ድንበር አልፈህ የመጣኸው ተከዜ ወንዝ ነው” ብለው ነበር የመለሱለት።

TPLF(ወያኔ) ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ፤ የጠለምትን ሕዝብ በመዳፉ ሥር ካስገባ በኋላ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዲሁም የአማራን ሕዝብ ለማጥፋት ባለው እቅድ መሠረት፤ በጠለምት ያሠፈራቸውን ቅጥረኞችን በማስታጠቅ፤ በጠለምት ሕዝብ ላይ ወደር የሌለው ጭፍጨፋ (genocide) እና የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) በማያቋርጥ ሁኔታ አካሂዷል። እያካሄደም ነው። ይኽ ሁሉ ዘግናኝ ግፍ የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ፤ የጠለምት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በማንሳቱና እኛ አማራ፤ ቋንቋችን አማርኛ ነው፤ ክልላችንም ከላይ በታሪክ ተደግፎ እንደተገለፀው ጎንደር ነው ብሎ ስለጠየቀ ነው።

የጠለምት ሕዝብ የደረሰበትንና የሚደርስበትን ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተቀናጀ መንገድ ለመግለጽና ለማስረዳት፤ በመታገል ላይ ካለው ወገናችን አጋርነታችን ለማሳየትና ብሎም ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ከሚታገልው ስፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመቆም አስከፊዉንና ዘረኛዉን የወያኔ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨርሻ አሽቀንጥሮ እንዲጥል ለመቀስቀስ እንዲረዳ በማስብ፤ እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የጠለምት ተወላጆች አስቸኳይ ስብሰባ አድርገን የሚከተለውን የአቋም መግለጫና ሕዝባዊ ጥሪ አቅርበናል።

1. የአማራ ሕዝብ አካልና የጎንደር ክ/ሃገር ክልል የነበሩት ወረዳዎች(ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት) እና የወሎ ለም 4ቱ ወረዳዎች ያለሕዝብ ውሳኔና ፈቃድ በወያኔ አስገዳጅነትና ያለ አግባብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለሉ መደረጉን እናወግዛለን።

2. በፀረ-ኢትዮጵያው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) ከፍተኛ ጭፍጨፋ (genocide) እና የዘር ማጥፋ ( ethnic cleansing) የተካሄደበትና የሚካሄድበት ጀግናው አማራው የወልቃይትና የጠገዴ ሕዝብ ከወያኔ አስከፊና ዘግናኝ አገዛዝ ለመውጣት የሚያካሂደውን ትግልና የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን፤ እስከ መጨረሻው ድረስ ከጎኑ እንቆማለን።

3. የተቀደሰውና ታሪካዊው ዋልድባ ገዳም በትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) መደፈር፣ መዘረፍ፣ምፍረስ፣ የአረጋዊ አባቶች መንገላታት፣ መሰደድና መገደል በጥብቅ እናወግዛለን። የወያኔ ጣልቃ ገብነትን እያወገዝን በቅዱስ ገዳምት ያሰፈረዉን ወታደራዊ ሃይል እንዲያነሳና እኩይ ተግባሩን እንዲያቆም እናሳስባለን።

4. እርዝመቱ 1600 ኪ/ሜትር የጎን ስፋቱ ከ20 እስከ 60 ኪ/ሜትር የሆነውን ለም ወሃ-ገብ የአገራችን ዳር-ድንበር መሬት የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) በገጸ-በረከት መልክ ለሱዳን መስጠቱ አጥብቀን እናወግዛለን።

5. በኦሮምያ ክልል በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ላይ እየተፈፀመ ያለዉን ግድያ፣ ጭፍጨፋ፣ እስራትና እንግልት በጥብቅ እያወገዝን ገዳዮቹን ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።

6. የጠለምት ሕዝብ ሆይ! የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) አገዛዝን አሽቀንጥረህ በማጣል የአማራ ማንነትህንና የመሬት ባለቤትነትህን ለማስመለስ የጀምርከውን ትግል አጠናክረህ ቀጥል፤ እኛም ልጆችህ እስከመጨረሻው ድረስ ከጎንህ መሆናችን እናረጋግጣለን።

7. በአገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ የጠለምት ተወላጆች በሙሉ በያላችሁበት በመሰባሰብና በመደራጀት፤ የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) በወገናችን የጠለምት ሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ (genocide) እና የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) በማጋለጥና፤ ከወያኔ ጨቋኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል በማንኛው መልክ እንድትድግፉ፤ ጥሪ እናቀርባለን።

8. የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኛ የሆነውን ፀረ-ኢትዮጵያው የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (ወያኔ) እና ተላላኪዎቹን በመራራ ትግላችን አስወግደን፤ እኩልነት፣ ፍትህና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ስርዓት ለመመሥረት እንደ ሰደድ እሳት በመቀጣጠል ላይ ያለውን ሕዝባዊ አመጽና ትግል በማጠናከር በጋራ እንድትታገል አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን።

ያለ አግባብ ከጎንደር የተወሰደው መሬት በመራራው ትግላችን ይመለሳል!
የወልቃይት፤ የጠገዴና የጠለምት ሕዝብ የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ በቆራጥ ትግላችን እውን ይሆናል! ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
E-mail: telemtgondar@gmail.com

posted by Geremew Aragaw

 

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: