The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

አብዮቱ ፈንድቶአላ፤ አደጋም አንጃቦአል ክፍል አንድ

“በፖለቲካው ዓለም ቆመን የምንቀሳቀስበት መሬትና ሜዳ፣ እግራችንንም ያሠፈርንባቸው ቦታዎች ሁሉ ሥር አንድ ታይቶ የማይታወቅ ኃይለኛ ምንም ጊዜም ሊፈነዳ የሚችል እሳተ ገሞራ እንዳለ ፈጽሞ መርሣት የለብንም፡፡ እንኩዋን ሳንጠነቀቅ ተጠንቅቀም ቢሆን ሳይታሰብ አንድ ቀን የሚፈነዳ ነው፡፡ በአለን ችሎታችንና አቅማችን እንቆጣጠረዋለን ብለን ብንገምትም፣ እሱን ጨርሶ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ በአንዴ ያልተሸነፈውና ተደብቆ የነበረ ሚት ብቅ ከአለ ደግሞ እሱን ምንም የሚያግደው ነገር የለም፡፡ አንዳች ዓይነት መጥፎ መንፈስ ብቅ ብሎና ተነስቶ ሁሉን ነገር እንደ አልነበር ያደርገዋል፡፡…” ፈላስፋው ኤርንስት ካሲየስ.

“….ሕግና ሥርዓት ከአለና ሁሉም እኩል በጋራ ያን ሕግ ከአከበሩት” ኢማኑኤል ካንት… በተራው እንደአለው “… እርስ በእራሳቸው በሠይፍ እና በሣንጃ የሚፈላለጉ አጋንቶችም እንኩዋን ቢሆኑ እኩል ተሰማምተው ያን ሕግ አክብረው አብረው ለመኖር የሚችሉ ናቸው።”

አንቀጽ 39 መቀየር አለበት፡፡ሕገ-መንግሥቱም እንደአለ እንደገና ተጠንቶ መጻፍ አለበት፡፡ ጸሓፊው

አ ዲ ስ አ በ ባ፡- አብዮቱ የፈነዳው፣ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ “… የተለያየ አመለካከትን የማይቀበል ሥርዓት የጊዜ ጉዳይ እንጂ መውደቁ አይቀርም፡፡ እኔ ምናባቴ ላድርግ፣… ጨንቆኛል!!” ከአሉ ወዲህ አይደለም፡፡

…ባንሣሣት አብዮቱ የፈነዳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞቱበት ቀን ነው፡፡

እንዲያውም ለቀብራቸው ዋዜማ ለአንዳንድ ሰዎች “…ጌታዬ!.. እረ የት ጥለህን ልትሄድ…ነው… ብላችሁ አደባባይ ወጥታችሁ በይፋ…አልቅሱ” ተብለው በቀበሌ በኩል ገንዘብ ለበረንዳ አዳሪዎችና ለመንደር ድሆች የታደለ እና የተበተነበት ቀን ነው፡፡

ይህ እኮ የትም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ነገር ነው! ይህ እኮ – ሰዎቹ ደፍረው የሠሩት – በታሪኩዋም ውስጥ የሌለ ፍጹም አዲስ የጥጋበኞች “ቀልድ” ነው፡፡

“…ለልጄ ሞት ቀብሩ ላይ ተገኝታችሁ አልቅሱልኝ…” ብሎ ገንዘብ የበተነ ትዕዛዝ የአስተላለፈ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ – ነጉሥታቱን እንተው – አንድም አገረ-ገዢ ወላጅ አባት ቢፈለግ – በየትኛውም ዘመን – አይገኝም፡፡

ለመሆኑ ይህን ቀልድ ከየት ነው ጎትተው የአመጡት!

ሰሜን ኮሪያን ይህንኑ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር በአለፈው ጊዜ አድርጋ በዓለም ላይ መሳቂያ መሳለቂያ ሆናለች!

በኢትዮጵያ አብዮቱ የፈነዳው ለአቶ መለሰ ቀብር ገንዘብ የታደለበት ቀን አይደልም፡፡

ይህን የሚሉ ሰዎች እውነት አላቸው!

ታዲያ ለመሆኑ መቼ ነው የፈነዳው!

አብዮቱ የፈነዳው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አዲስ አበባን ጎብኝተው ኢህአዴግ “…በሕዝቡ… ‘ያውም በ99.6 ከመቶ በሆነው’ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ ድርጅት ነው” ብለው የቀለዱበት ቀን ነው፡፡

በእርግጥ አብዮቱ የፈናዳበት ቀን እሱ ነው ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል፡፡

ምክንያቱም፣ ከአምስት አመት በፊት ይኸው ድርጅት፣ ከስንት ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ “አንድ” ተቃዋሚ ሰው ብቻ ገዢው ፓርቲ ሸንጎው ውስጥ አስቀምጦ፣ የተቀረውን ወንበር ለብቻው ሰብስቦ ይዞ እንደ ነበር አይረሳም፡፡

… ያኔም አሜሪካኖቹ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም መንግሥታት “…እንኩዋን ደስ ያላችሁ” የሚለውን መልዕክታቸውን ልከውላቸው እንደ ነበር – ይህ አይረሳም በደንብ ተመዝግቦአል፡፡ እሱ ከአልሆነ ምናልባት አብዮቱ በኢትዮጵያ የፈነዳው ቀደም ሲል በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ የተቃውሞ ድምጹን አሰምቶ፣…በጥይት ሳይሆን በዝናብ ተደብድቦ የተመለሰበት ቀን ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡

በእርግጥም ያ ቀን ያስፈራ ስለነበር እሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡

እንዲያውም አንዲት ውሻ፣ – የፈረስና የበቅሎውን፣ የአህያውን የ… መፈክር ተዘግቦ አልሰማንም እንጂ – “… አጥንት እንኩዋን በዓይኔ ሳላይ ይኸው አሥራ አምስት አመት ሆነኝ… አለፈ…” የሚል የእሮርታ ጨርቅ ወገቡዋ ላይ አሥራ አዲስ አበባ ላይ ሠልፍ ወጥታ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

ግን ያም ቢሆን ይህን ቀን በትክክል እና በእርግጠኛነት “…አብዮቱ የፈነዳበት ቀን ነው” ብሎ ለመመስከር በጣም ያስቸግራል፡፡

ጥንታዊውን የዋለድባን ገዳም ለሽንኮራ ነጋዴዎች የተሸጠበትን ቀን እሱ ነው ብለው በእርግጠኛነት ይህን ታሪካዊ ቀን የሚያነሱም ተመልካቾች አሉ፡፡

ከእነሱም ጋር … “ሦስት መቁዋሚያቸውን” ጥለው እርገማኑን ለቀው፣አንዳዶቹ እንደሚሉት፣ የፓትሪያርኩንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕይወት “ያስወሰዱበት ቀን” እሱ አብዮቱ የፈነዳበት ቀን ለመሆኑ ጥርጥር የለንም ብለው የሚያምኑም ሰዎች አልጠፉም፡፡

ግምቱና አመለካከቱ ቀላል ባይሆንም – እነሱ ዕውነት ከአላቸው፣ ሌሎቹስ ከዚህ የተለየ አሳብ አንስተው የሚናገሩትን ምን እንበላቸው!

የአንዋር መስጊድ በወታደሮች የተደፈረበትን ቀንና ሰዓት የሚጠቅሱ አሉ፡፡እያዳፉም ሰዎች ወስደው አሥረዋል፡፡

ቤተ-ክርስቲያን የተቃጠለበትን ቀን የሚያነሱም አልጠፉም፡፡ እነሱን ምን እንበላቸው! እነሱንስ ምን እናድርጋቸው፡፡

የኢትዮጵያ ባንዲራ “.. ጨርቅና ቀለም ነው…” ተብሎ ያ ትልቁ ሰንደቅ አላማ ተዋርዶ “በአንዳች በሰማያዊ ክብ ነገር…” የተተካበት ዕለትም አለ፡፡… ታቦት ለውጭ ነጋዴዎች የተሸጠበትን ቀን የሚጠቅሱም አሉ፡፡

አብዣኛዎቹ እሱ ሳይሆን “…የኢትዮጵያ ታሪክ ዝቅ ተደርጎ…አንድ መቶ አመት ነው” ተብሎ የተቀለደበት ጊዜ ነው ብለው ይሚሙዋገቱም አልጠፉም፡፡

ይባስ ብለው የተቀሩት ደግሞ “…ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል የተወሰነበት ቀን…” ያኔ ነው አብዮቱ በኢትዮጵያ የፈነዳ ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡

ሌላም ሌላም ሁኔታዎችን ሳይረሱ አንስተው የሚቆጥሩም አሉ፡፡

ለምሳሌ ጉርሻ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ ታሪክ በብዙ ብር የተሸጠበትን ቀን ይጠቅሱ፡፡ወይም የሳውዲ ነገሥታት መሬት ገዝተው አርሰው፣አጭደውና ከምረው፣ወቅተውና ፈጭተው በአይሮፕላን ጭነው ሕዝቡ እየተራበ የወሰዱበትን ያልረሱ፡፡ ያኔ ነው አብዮቱ ፈነዳ ብለው የሚጠቅሱም ፡፡

በእርግጠኛነት ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ እንደዚሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በገጠርና በከተማ በተራበበት ወቅት ሴት ልጃቸውን ሰንጋ ጥለው – ቁጥሩን አናውቅም – ታላቁ ቤተ-መንግሥት ቁጥር ግቢ በመቶና በሺህ በሚቆጠሩ የኢህአዴግን ክቡራት እና ክቡራንትን ጋብዘው በውስኪና በሻምፓኝ የተራጩበትን ቀን ያኔ አብዮቱ በኢትዮጵያ አለጥርጥር ፈናዳ የሚሉም አልጠፉም፡፡

እርግጠኛው ቀን የትኛው እንደሆነ እና መቼ እንደ ፈነዳ መናገር ባይቻልም “…ከእንግዲህ ወዲህ እኛ የወሰነውን ነገር ማንም የምድር ሆነ፣ የሰማይ ኃይል አይመልሰውም” የሚለውን አንዱ የወያኔ አዣዥ የተናገረው ቃል መሬት ላይ ሳይወድቅ ሁሉም በደንብ በማዳመጡ ነው!

ሃይማኖተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የንቀት አነጋገር ዝም ብሎ ከአዳመጠውና ከሕሊናው ጋር ተሙዋግቶ ለብቻው ውሳኔውን ከሰጠበትና የተቃዎሞ ድምጹን በቤቱም ሆነ በአደባባዩም ማሰማት ከጀመረ በሁዋላ ያኔ አብዮቱ ፈነዳ የሚሉ ሰዎች ትንሽ ዕውነት አላቸው፡

ምናልባት ይህኛው ቀን በዚህ በያዝነው አመት ወሳኝ ሳይሆን አይቀርም!

ምናልባት ፋሽሽቱ ሞሰለኒ ኢትዮጵያ ተከፋፍላና ተዳክማ ለማየት ፈልጎ የአገሪቱን ዜጎች ያኔ “…በኦሮሞና በአማራ በትግሬና በጉራጌ፣በኤርትራና በአፋር፣በሱማሌና ጊሚራ…” ለመሸንሸን እንደፈለገው፣ ወያኔና ሻቢያ ከኦነግ ጋር ሁነው በይፋ ያቺን አገር የቆራረሱበት ቀን ያኔ ነው አብዮቱ ፈነዳ የሚሉም አልጠፉም፡፡

ዝርዝሩ በዛ…

እረ! …ታዲያ በየትኛው ቀን ነው አብዮቱ የፈነዳው!

ቀደም ሲል እንደ ጻፍነው ፡- ገዢው መድብ የተከፋፈለበት ቀን ነው፡፡

ነገሩ፡- በንጉሡ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ላይና፣ እሳቸውን በተካው በወታደሩ መንግሥት፣ በደርግ በእነሱ ላይ የተቀጣጠለው የተቃውሞና የአመጽ እንቅስቃሴ፣ ማለት የሽም ሽር አብዮት፣ መቼ በእነሱ ላይ ያኔ “..ፈነዳ” ብሎ ዛሬ እንደ መጠየቅም ዓይነት ነው፡፡

ወጣቱ ኤሊያስ ካኔቲ፣ በሁዋላ የኖቤል ሽልማት አሸናፊው፣ ገና በሃያ ሁለት አመቱ አንዴ አይቶ ተገርሞ በጻፈው ጽሑፉ ላይ የሚከተሉትን ቃላቶቹን ስለ ሕዝብ “…ተቃውሞ ፍንዳታ” ሲያብራራ እንደዚህ አድርጎ ደብተሩ ላይ ወጣቱ ተመልካች ጥሩ አድርጎ አሥፍሮአል፡፡

ጊዜው 1927 ዓ.ም. እ.አ.አ. ነው፡፡ ሠራተኞች አድማ መተው በኦስትሪያ ዋና ከተማም በቬና ሆ! ብለው የተነሱበትም ቀን ነው፡፡

በዚያን ዕለት በአየው ግርግርና ሁካታ ተደንቆ ያ ወጣት ብዕሩን አውጥቶ እንደዚህ ይላል፡፡

እሱ እራሱም፣ ከሕዝቡ ቁጣ ጋር በከተማው መሓል የሚገኘው አንድ የፍርድ ሚኒስቴሩ ሕንጻ እሳት ተለኩሶበት ሲጋይና ተመልካቹም ሰብሰብ ብሎ “ሲጨፍር” ሳያስበው በነገሩ ተመስጦ ፣ እሱም በቁጣው ተማርኮ እንዴት የግርግሩ አካል ለመሆን እንደቻለም አንስቶ ወረድ ብሎ የሚከተሉትን ቃላቶች ለቆአል፡፡

“… በመጀመሪያ በጣም ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ ቢያንስ አምስት ወይም አሥር፣…እንዲያው ግፋ ቢል አሥራ ሁለት ነበሩ፡፡ ማንም ኑ ብሎ የጠራቸው ሰው የለም፡፡ በድንገት ግን ሳይታሰብ ከዚያም ከዚህም ብቅ ብለው በአንዴ አካባቢውን ሰው ሁሉ ሰብሰብ ብሎ ሞልቶት እንዳለ ድብልቅልቁን አወጣው፡፡

…ምንድነው ብሎ የጠየቀ ሰው የለም፡፡ በጥድፊያ እና በችኮላ ግን ሁሉም አንዳች ነገር እንዳያመልጠው ቦታው ላይ ተገኝቶ የግርግሩ አካል ለመሆን የፈለገ ይመስላል፡፡ አላማ አላቸው፡፡ ያ አላማም አብዛኛው ሰው በአለበት ቦታ ተገኝቶ ከእነሱ ጋር መደባለቅ ብቻ ነው፡፡

…መቆሚያም ጠፍቶ፣ የመጣው ሰው ሁሉ ተጨናነቆ ነበር፡፡ጥቁር ቅልጥ ያለ የሰው ክምችት ባህር ነገርም ይታይ ነበር፡፡”

ካኔቲ የመጽሓፉን አርስት “የአብዮት ፍንዳታ!” አላለውም፡፡ወይም… “የሕዝብ አመጽ”፡፡ ለመጽሓፉ መርጦ የሰጠው አርዕስት “ሰፊው ሕዝብና ያ ሕዝብ ያለው ኃይል…” የሚል ነው፡፡ በፈረንሣይ አብዮት፣…በሩሲያና በኢትዮጵያም የታየው ጉድ አንድ ዓይነት ነው፡፡

“…እኔንም ጨንቆኛል፣ ምን አባቴ ላድርግ!” የሚለውም የኃይለ ማሪያም አነጋገር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አብዮቱ አለጥርጥር ፈንድቶአል!

ቁም ነገሩ ያለው ምን ይመጣል የሚለው ዝግጅትና መልሱ ላይ ነው፡፡

ከሦስት ሺህ አመት በላይ የቆየውን የዘውድ አገዛዝ ሕዝቡ ተንቀሳቅሶ ጥሎት በእሱ ፋንታ ያገኘው “የወታደር አምባገነን መንግሥትን ነው”፡፡ ያውም ለአሥራ ሰባት አመታት፡፡ እሱን ተገላገልኩ ያለው ትውልድ ያጨደው “የወያኔና የሻቢያን ለጥቂት አመታትም ቢሆን የኦነግን አምባገነን ሥርዓትና ክፍፍልን ነው፡፡”

መጪው ጊዜ ግን በምንም ዓይነት፣ ከዚህ ሁሉ ዕብደት በሁዋላ ወደ “አምባገነን ሥርዓት…” እንዳያመራ ምን ማድረግ፣ ምንስ መሆን አለበት!

ክፍል ሁለት በእሱ ላይ ያተኩራል፡፡ስለ ግለሰብ ነጻነት ስለ እያንዳንዱ ዜጋ መብት አንስቶ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የወጣቱን ትውልድ ልብ በልቶ አንጎሉን አዙሮ እዚህ ስለአደረስው ርዕየተ ዓለሞች ያነሳል፡፡ጻሓፊው

 

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: