The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የጎሳ ዘረኝነት (ክልላዊነት) በኢትዮጵያ – ከፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Apartheid 2የጸሐፊው ማስታወሻ፡ ይህ “የጎሳ ዘረኝነት/አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ መደበኛ በሆነ መልኩ እያዘጋጀሁ የማወጣው ተከታታይ ትችት ሁለተኛው ክፍል ነው፡፡

የዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ጥንድ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡

1ኛ) በአሁኑ ጊዜ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ህወሀት) አድራጊ ፈጣሪነት ተመስርቶ እየተቀነቀነ ያለው አውዳሚ የፖለቲካ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰፊው  የጥቁሮች ህዝብ  የበላይ አገዛዝ ስርዓት ከመፈጠሩ በፊት በጥቂት ነጮች የዘረኝነት የበላይ አገዛዝ ከነበረው የአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ ተሞክሮ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ከምንም ጥርጣሬ በላይ ለማመላከት እና

2ኛ) ጥልቀት እና ስፋት ያለው ክርክር እና ውይይት በማካሄድ ከጎሳ ዘረኝነት የጸዳች አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንባቱን አስፈላጊነት ለመፍጠር እንዲቻል የኢትዮጵያን የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡

በዚህ “የጎሳ አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ተቀናብሮ በሚቀርበው ተከታታይ ጽሑፍ የፖለቲካ እና የሕግ ትንተና፣ የምሁራን እና የአካዳሚክ ሁኔታን ከመመርመር ባለፈ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሀት አገዛዝ ስር ወድቃ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ አጠቃላይ ሁኔታ መዳሰስን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት ለኢትዮጵያ አቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ጥሩምባ በመንፋት እንዲህ የሚል ጥሪ ለማቅረብ ነው፡ “ኢትዮጵያ በእናንተ መዳፍ ዉስጥ ናት፡፡ ጣቶቻችሁን በማስተባባር፣ በማጠንከር እና እንደ እንቁ ኢትዮጵያን በእጃችሁ መዳፍ ላይ የማድረግ  ምርጫው አላችሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የእጅ ጣቶቻችሁን በማዛል እና ጥንካሪያቸውን በማልፈስፈስ ኢትዮጵያን ከእጅ መዳፋችሁ ላይ አሽቀንጥራችሁ በመጣል እንደብርጭቆ እንክትክት ብላ እንድትሰበር የማድረግ ምርጫው በእናንተው እጅ ላይ የወደቀ ነው፡፡ እያንዳንዳችሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ እና መዳፎቻችሁን አጠንክራችሁ በመያዝ በአንድነት የመጓዝ ምርጫው የእናንተ ነው፡፡ መዳፎቻችሁን በመጨበጥ ጠንካራ ቡጢ በመፍጠር በቁጣ እና በወኔ በመነሳሳት ሀገራችሁን ከአውዳሚ አደጋ የመጠበቅ፣ ክብሯን እና ዝናዋን የማስመለስ ምርጫው በእናንተ እጅ ላይ የወደቀ ነው፡፡ የእኔ የጥሩንባ ጥሪ ኢትዮጵያ በእጃችሁ ላይ ናት፣ ሆኖም ግን “ኢትዮጵያ ኦጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘርጋለች“ የሚል ነው፡፡

ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ የማቀርበው ጥያቄ፣ 

መጀመሪያ ባቀረብኩት ትችቴ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች ስም ዝርዝር የመረጃ ቋት ውስጥ ስሙ በአሸባሪነት ተመዝግቦ በሚገኘው እና በአሁኑ ጊዜ አሸባሪ ቡድን እየተባለ በሚጠራው በዘ-ህወሀት ወሮበላ አምባገነናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ ተጭኖ የሚገኘው “የጎሳ ፌዴራሊዝም” ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ የሚሞግት ስልታዊ እና ወሳኝ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በማቅረብ ጀምሬ ነበር፡፡ በጎሳ ፌዴራሊዝም ላይ ያሉኝን የእኔን የመጀመሪያ የክርክር ጭብጦች አንጥሬ በማውጣት ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ በማቅረብ ወጣቱ የጎሳ ፌዴራሊዝሙን ሙሉ በሙሉ በመቃወም ወደ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ እንዲጥለው ተማጽዕኖ አቅርቤ ነበር፡፡

በዚህ በአሁኑ ትችቴ ላይ ደግሞ በዘ-ህወሀት “የጎሳ ዘረኝነት” ወይም ደግሞ “ክልላዊነት” በማለት ሀገሪቱን በዘጠኝ ክልሎች ወይም ክልላዊ መንግስታት ከፋፍሎ ባስቀመጠው ከፋፋይ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የትግል መንፈሳቸውን ለማጎልበት እንዲቻል የሕግ ማስረጃ እንዲኖራቸው በማገዝ ትግሌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ችግር የጎሰኝነት አገዛዝ ስርዓት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይህ የጎሳ አገዛዝ ስርዓት ተጸንሶ ያደገው በዘ-ህወሀት ማህጸን ውስጥ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ውድመትን እና ጥፋትን ለማምጣት በኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሰውነት ላይ ተወልዷል፡፡

የጎሳ ክፍፍል እና የጎሰኝነት ችግሮች ለኢትዮጵያ ወይም ለአፍሪካ አዲስ አይደሉም፡፡ ዋልተር ሮድነይ በአፍሪካ አህጉር የጎሳ ልዩነቶች ቢኖሩም ቅሉ የግድ የፖለቲካ ልዩነቶችን የሚያመላክቱ አልነበሩም በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፡፡ ሆኖም ግን የጎሳ መስመርን በሚከተሉ እና ስልጣንን ጨምድደው በመያዝ  እና የሀገሪቱን ሀብት ለግል እና ለተባባሪዎቻቸው ጥቅም ማጋበስ በሚፈልጉ በተወሰኑ የአፍሪካ ልሂቃን ተብዬዎች አማካይነት የጎሳ ልዩነቶች የፖለቲካ መልክ እንዲይዙ ተደርገዋል፡፡

ዘ-ህወሀት ስልጣንን በብቸኝነት ጨምድዶ ለመያዝ እና የሀገሪቱን ሀብት እርሱ እና ተባባሪዎቹ ብቻ ማግበስበስ እንዲችሉ በማሰብ የጎሳ ስርዓት መስመርን ዘርግቷል፡፡ አዲስ ነገር ነው ተብሎ ሊታይ የሚችለው ነገር ቢኖር የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ በዘር እና በጎሳ በመከፋፈል የፖለቲካ ስርዓቱን በበላይነት ተቆጣጥሮ ብዙሀኑን የአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ሲጨቁን እና የመሬትን ባለቤትነት፣ ተደራሽነት እና ጥቅም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይዞ ሲበዘብዝ ከነበረው ከጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይነት አገዛዝ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ዘ-ህወሀትም የጎሳ መስመሩን የመከተሉ ጉዳይ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ እንደነበረው እንደ ጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ሁሉ ዘ-ህወሀትም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉንም መሬት ሰብስቦ በመያዝ (የዘ-ህወሀትን ሕገ መንግስት አንቀጽ 40 ልብ ይሏል) የእራሱን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይሉን መስርቶ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ (እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተደረገ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ 100 በመቶ አሸነፍኩ በማለት እና አረመኔውን አገዛዙን በጠብመንጃ ኃይል አጠናክሮ የሚገኝ መሆኑን ያጤኗል)፣ እንደዚሁም ደግሞ የግል ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ (ዘ-ህወሀት በእራሱ የንግድ ድርጅቶች/ኮርፖሬሽኖቹ አማካይነት ሙሉ በሙሉ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ልብ ይሏል) እና የስራ ዕድል፣ የትምህርት እና ሌሎች ዕድሎችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ለፖለቲካ ደጋፊዎቹ እና ለታዛዥ ሎሌዎቹ በመስጠት ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አግልሎ በድህነት እና በስቃይ እንዲዘፈቅ አድርጎት ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የዘ-ህወሀት የበላይነት፣ የጭቆና አገዛዝ እና ጎሰኝነትን በፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም ብዙሀኑን ሕዝብ በመበዝበዝ እራሱን የሁሉም ነገሮች ፈውስ አድርጎ በማቅረብ ከእራሱ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ማዕከልነት ወደተሻለ ነገር መሻገር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡

መሬት እና የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ የአፓርታይድ ስርዓት የሕግ መሰረት፣ 

የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ/የጎሳ አፓርታይድ ስርዓት መሰረቱ መሬት ነበር፡፡ የመሬት ባለቤትነት፡፡ መሬትን የመጠቀም መብት፡፡ መሬትን የመያዝ መብት፡፡ መሬትን የመቆጣጠር መብት፡፡ መሬትን ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ የማከፋፈል መብት፡፡ ወደ 90 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን መሬት በጥቂት አናሳ ነጭ ገበሬዎች እንዲያዝ የማድረግ መብት፡፡ በነጮች የመሬት ነጠቃ እና ብዙሀኑን ጥቀር ሕዝቦች ከይዞታቸው የማፈናቀል መብት፡፡ ሕገወጥ በሆነ መልኩ ለተወሰደው መሬት የሚሰጥ ካሳን በጣም አሳንሶ የማቅረብ መብት፡፡ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከቀደምቶቻቸው ጀምሮ ይዘውት ከኖሩት መሬታቸው እና እርስታቸው የማፈናቀል መብት፡፡ ይኸ ሁሉ ሕገወጥ መብት/ድርጊት በጥቂት አናሳ ዘረኛ የነጮች አገዛዝ የተሰጠ ነበር፡፡ ስለሆነም በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ የነጮች አገዛዝ የመሰረት ድንጋይ እና ምሰሶ ሆኖ ሲያገለግል የነበረውን ሕግ በሕገወጥ መልክ በመሳሪያነት በመጠቀም ፍትሐዊ ያልሆነው የመሬት ክፍፍል እና ብዙሀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውን ንብረት የለሽ እንዲሆኑ በማድረግ የኢኮኖሚ ኃይልን ማዳከም ማደህዬት ነበር፡፡

የአፓርታይድ መሰረት የተጣለው “የተወላጆች መሬት ድንጋጌ፣ 1913 (አዋጅ ቁጥር 27/1913)“ ከሚለው እና ከአስርት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1948 በይፋ ከመውጣቱ በፊት ነበር፡፡ የመሬት አዋጁ በጥቂት ዘረኛ የነጮች አገዛዝ ቁጥጥር የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የመሬት ባለቤትነት መብት ለማሳጣት የተዘየደ ዋና የሕግ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ድንጋጌው በተከታታይነት በወጡት ሕጎች እየታገዘ ብዙሀኑ ጥቁር አፍሪካውያን የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን በእጅጉ በመገደብ ከተወላጆች መሬት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ 14 በመቶ ብቻ የሚሸፍነውን ለጥቁር አፍሪካውያኖች በመስጠት 87 በመቶ የሚሆነውን መሬት አናሳዎቹ ነጮች ብቻ እንዲይዙት ተደርጓል፡፡

የ1950 የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act በኋላ በቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act 36/1966 ተጠናክሮ በደቡብ አፍሪካ ኗሪዎች በዘር አድልኦ ላይ ተጠናክሮ ወጥቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ አናሳዎቹን የነጮች ዘረኛ አገዛዝ የገጠር እና የከተማ መሬትን ለነጮች፣ ለፉንጋ ጥቁሮች/colored እና ለሕንዶች የብቸኝነት የመሬት ባለቤትነት መብትን አጎናጽፏል፣ ሆኖም ግን ብዙሀኑ ጥቁር አፍሪካውያን የመሬት ባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ወይም ደግሞ በብቸኝነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ አልተደረገም፡፡ ሆኖም ግን ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ለሌሎች አካባቢዎች ቡድኖች ተብለው ከተከለሉት አካባቢዎች በተለይ መሬት ለመያዝ ወይም ደግሞ የመሬት ባለቤትነት መብት እንዳይኖራቸው ክልከላ ተደርጓል፡፡

እ.ኤ.አ በ1950 የወጣው የደቡበ አፍሪካ የሕዝብ ምዝገባ ድንጋጌ (ሕምድ)/Population Registration Act (PRA) በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ኗሪ እንደ ዘር እና እንደ ጎሳ ቡድኑ እንዲመደብ እና እንዲመዘገብ አስፈላጊነቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ያ ሕምድ/PRA በብዙሀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እና ነጭ ያልሆኑ ዜጎችን ለመከፋፈል እና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አድልኦን በማንሰራፋት የአፓርታይድ ስርዓትን በማፋጠን በመሳሪያነት በማገልገል ዋና መሰረት ሆኗል፡፡ (“አፓርታይድ” የሚለው የአፍሪካ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “መለያየት“ ማለት ሲሆን ከደች/ኔዘርላንድ ቋንቋ “መለየት” ሲደመር “ጎረቤት” ከሚሉት  ተጣምረው ሲነበቡ “ከጎረቤት መለየት” የሚለውን የሀረግ ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ በሕምዳ የአመዘጋገብ ስርዓት መሰረት ግለሰቦች እንደ ዜጋ፣ ፉንጋ ጥቁሮች፣ ኢሲያዊ ወይም ደግሞ ነጭ በማለት ይመደባሉ፡፡  የማንነት ማስረጃ ሰነዶች ፍጹም የሆነውን የዘረኝነት አድልኦ እና ጭቆና ለማስፈጸም በዋናነት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ነበሩ፡፡

የ1951 የባንቱ ባለስልጣኖች ድንጋጌ (ባባድ)/Bantu Authorities Act of 1951 (BAA) (የድንጋጌ ቁጥር 68/1951) የባባድን ድንጋጌ ወዲያውኑ የጥቁሮች ባለስልኖች ድንጋጌ (ጥባድ)/Black Authorities Act በሚል ስያሜ ተቀየረ፡፡ ጥባድ “የጥቁር አካባቢዎች”፣ “አለቆች”፣ “የጎሳ ባለስልጣኖች” የሚል ትርጉምን በመስጠት የስልጣን ኃላፊነታቸውን፣ ስራቸውን፣ የስራ ኃላፊነታቸውን እና የሕግ ማዕቀፎቻቸውን ትርጉም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ጥባድ በርካታዎቹን የጎሳ እና ቋንቋን መሰረት ባደረገ መልኩ የተደራጁትን ጎሳዎች ወደ ባህላዊ የአካባቢ ኗሪነት በመፈረጅ የጎሳ፣ የክልል እና የአካባቢ ባለስልጣኖችን ፈጠረ፡፡ የ1951ዱ የባንቱ ባለስልጣኖች ድንጋጌ (የ1951 የጥቁር ባለስልጣኖች ድንጋጌ) ጥቁሮችን ወደተመደቡላቸው ቦታዎች እንዲጋዙ በማድረግ የጎሳ፣ የክልል እና የአካባቢ ባለስልጣኖችን ፈጠረ፡፡

የ1950ው የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act (በ1966 እንደጸደቀው የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act) ሁሉ ደቡብ አፍሪካን ለነጮች እና ለጥቁሮች በሚል በመከፋፈል ሕዝቦች ካልተመደቡበት አካባቢ በተለይም ከዘራቸው እና ከጎሳቸው ውጭ መኖር እንደማይችሉ ለማባረር እንዲችል ለአገዛዙ ስልጣን ሰጠው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ማንም ቢሆን ባልተመደበበት “ስህተት” ቦታ ላይ የሚኖር ዜጋ ሁሉ ወደ ጎሳው/ሳዋ መኖሪያ አካባቢ ይጋዛል/ትጋዛለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ አፍሪካውያን ሕዝቦች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በማንኛውም ቦታ መሬት የመያዝ መብት የሌላቸው እንደሆኑ እና ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲታቀቡ የሚል የሕግ ክልከላ ተጥሏል፡፡ በዚህ ሕግ መሰረት ጥቁር አፍሪካውያን በግዳጅ ይጋዙ እና እንደ ከብት በበረት ውስጥ በባንቱስታንስ የጎሳ ቡድን ይታጎሩ ስለነበር 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወቶች ጠፍተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1959 የወጣው የባንቱ እራስን በእራስ ማስተዳደር ማበልጸግ ድንጋጌ 1959/Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959 (PBSA) (የድንጋጌ ቁጥር 46) 8 (ቆይቶም ወደ 10 ከፍ እንዲሉ የተደረጉ) በአሁኑ ጊዜ ካሉት እያንዳንዳቸው እራሳቸውን በእራሳቸው በምስለኔዎች፣ በአለቆች፣ በዋና አለቆች፣ እና በጥቁር አካባቢዎች ያሉ የክልል አስተዳዳሪዎች መሰረት ማስተዳደር እንዲችሉ በመፍቀድ ልዩ የሆኑ የባንቱ ክልሎችን ፈጥረዋል፡፡ የአካባቢዎች መንግስታት ውሱን የሆኑ የግብር አሰባሰብ፣ የሕዝብ ስራዎች ቁጥጥር፣ የፈቃድ አሰጣጥ ጉዳዮችን እና ውዝግቦችን በሕጋዊ መንገድ የመፍታት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ የPBSA ዋና ዓላማ ለአካባቢ አስተዳደሮች የመጨረሻ ስልጣን ለመስጠት፣ ከደቡብ አፍሪካ ዜግነት ለማስወገድ እና ለጥቂቶቹ የነጭ ዘረኛ ህዝቦች የብዙሀን ስልጣንን ጠቅልለው እንዲይዙ ለማስቻል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ የ971 የባንቱ አስተዳደር ሕገ መንግስት ድንጋጌ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግስት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ለጥቂት ነጭ የበላይነት አገዛዝ ለማንኛውም አስተዳደር አካባቢ ነጻ ስልጣን ሰጥቷል፡፡ የድንጋጌው ዓላማ ግልጽ እና እንዲህ የሚል ነበር፡ “እያንዳንዱ የአካባቢ መንግስት እራሱን በእራሱ እንዲመራ እና የእራሱ መንግስት እና ነጻነት ያለው መሆኑ የመንግስት ጽኑ አቋም እና ሊቀለበስ የማይችል ዓላማ ነው፡፡“ በሌላ አባባል የአካባቢ አስተዳደሮች ድንጋጌ የተለመደውን ተፈጥሯዊ የጎሳ መሬቶች የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን በሚል ለባንቱስታንስ መንግስታት ሙሉ ነጻነት ይሰጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት በመጨረሻ ነጻነት እ.ኤ.አ በ1976 እና 1981 ለትራንስኬይ፣ ለቦፉታትስዋና፣ ለቬንዳ እና ለሲስኬይ የአካባቢ መንግስታት ተሰጥቷል፡፡

ጨካኙ የደቡብ አፍሪካ ነጮች ዘረኛ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቬርወርድ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሕዝብ ምዝገባ ድንጋጌ (ሕምድ)/Population Registration Act (PRA)ን በመጠቀም  “የተናጠል ልማት” እየተባለ የሚጠራ ፖሊሲ ነድፎ በስራ ላይ አውሏል፡፡ አፓርታይድ የፖሊሲው ዋና ካርታ ሆኖ በመቅረብ የባንቱ የአስተዳደር አካባቢዎች የእየራሳቸው መንግስታት ወይም ባንቱስታን ለመሆን በቅተዋል፡፡ አናሳው የጥቂት ነጮች አገዛዝ የብዙሀኑን ጥቁር ህዝቦች ባንቱስታናዊ የማድረግ እንዲህ የሚል የፖለቲካ ስልት ዓላማ ነበረው፡

1ኛ) በዙሀኑን ጥቁር አፍሪካዊ በትንናንሽ የሕዝብ ስብስብ የመከፋፈል ስሌትን በመጠቀም የከፋፍለህ ግዛን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ፡፡

2ኛ) በባንቱስታናዊ ቅኝት የተዘጋጀ የጎሳ ማንነትን ተግባራዊ በማድረጉ ጥረት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው ፍቅር የማይኖራቸው መሆናቸውን በማየት ስኬታማ መሆን መቻላቸውን ካረጋገጡ ማንኛውንም የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን አንድነት በተጨባጭ ለማጥፋት እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡

ባንቱስታናዊ ከማድረግም የተነሳ አናሳው የጥቀቲ ነጮች የበላይ አገዛዝ ቀደ 14 በመቶ የሚሆን የባንቱስታንን የአስተዳደር አካባቢ ለብዙሀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካ ሕዝቦች በመስጠት ሌላውን ለሙን፣ የማዕድን ክምችት ያለበትን እና የከተማ ቦታዎችን በሙሉ ለነጮች ይዞታ አደረገ፡፡ ወደ 90 በመቶ ያህል የሚሆነው የደቡብ አፍሪካን የንግድ የእርሻ መሬት በሙሉ ለ50,000 ነጭ ገበሬዎች ወይም ደግሞ መንግስት ተሰጠ፡፡ በፖለቲካዊ አካሄድ ባንቱስታናዊነት ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ህዝቦች የእራስ አስተዳደር መብት እና ነጻነት ይሰጣል፣ ሆኖም ግን ለእነርሱ ከተከለለላቸው አካባቢ ውጭ እንደሌላ እንደ ባዕድ ዜጋ ነበር የሚታዩት፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን በእራሱ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የእኩልነት መብት ይከላከላሉ፣ የእራሳቸው የአካባቢ መንግስት የጎሳ ዜጋ ከሆኑ የዚያው የአካባቢያቸው መንግስት ዜጋ እንጅ እንደ ደቡብ አፍሪካ ሬፐብሊክ ዜጋ አይቆጠሩም፡፡

የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ/የጎሳ አፓርታይድ ስርዓት የጥቂት ነጮች ዘረኛ አገዛዝ ውሳኔ የተመሰረተው መሬትን በብቸኝነት ለመቆጣጠር እና መሬትን ተቆጣጥሮ በመያዝ በዚያ ስር የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ማንነት፣ ዜግነት፣ ኗሪነት፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶችን በመሉ ለመቆጣጠር ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካውያን ማንነት በዋናነት የሚወሰነው ከመሬት ጋር ባላቸው ግንኙነት ነበር፡፡ ጥቂቶቹ ነጮች ሁሉንም ምርታማ የሆነ ለም መሬት ተቆጣጥረው ሲይዙ ብዙሀኖቹ ጥቁር አፍሪካውያን ህዝቦች ግን በእርግጠኝነት ምንም ዓይነት መሬት አልነበራቸውም፡፡

መሬት እና የዘህወሀት የጎሳ አፓርታይድ ስርዓት የሕግ መሰረት፣

የዘ-ህወሀት ልዩ የሆነው ጉብዝናው እ.ኤ.አ በ1995 በጸደቀው ሕገ መንግስቱ ውስጥ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያጸደቋቸውን ሁሉንም የአፓርታይድ ሕጎች እና ፖሊሲዎች ልቅም አድርገው በመውሰድ በእነርሱ ሕገ መንግስት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማስገባት የጎሳ የአፓርታይድ ስርዓት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1995 በጸደቀው የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት የሕገ መንግስት አርቃቂዎቹ መሬትን እና ጎሳን በአንድ ላይ በማጣመር የደቡብ አፍሪካን ባንቱስታንስ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የባህል ስብጥር ባህሪያትን እንዳለ በመኮረጅ ወስደው ክልሎችን ለመፍጠር ተጠቅመውበታል፡፡ የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት በመግቢያው መንደርደሪያ ላይ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ መብቶቻቸውን እና ነጻነቶቻቸውን ሙሉ በመሉ ለመጠቀም፣ እስከ መገንጠል…“ ይላል፡፡ በአንቀጽ 8 (1) የዘ-ሕወሀት ሕገ መንግስት እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል፡፡“ የዘ-ህወሀት አንቀጽ 39 እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የእራሱን ዕድል በእራሱ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል“ ተሰጥቶታል፡፡ አንቀጽ 42 (2) እንዲህ የሚል መብትን አጎናጽፏል፣ “ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ 1 በግልጽ በተመለከተው መሰረት በማናቸውም ጊዜ የእራሳቸውን መንግስት የማቋቋም መብት አላቸው፡፡“

የሚያስገርመው ነገር የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግስት ድንጋጌ 110/1983 እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ዓላማን ያነገበ ድንጋጌን አጎናጽፎ ነበር፣ “ቡድኖች እና ሕዝቦች የእራሳቸውን ዕድል እራሳቸው እንዲወስኑ ውሳኒያቸውን ለማክበር፣ ለማጠናከር እና ለመጠበቅ“ ይላል፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ የ1959 የBantu Self-Government Act of 1959 (PBSA) ድንጋጌ ሁሉ መጀመሪያ 8 (ቆይቶም በማስፋት 10) ባንቱስታንስ (የጥቁር ሕዝቦች መኖሪያ መንደሮች) እንደፈጠሩ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስትም በአንቀጽ 46 (2) የአኗኗር ዘይቤዎችን፣ ቋንቋን፣ ማንነትን እና የሚመለከተውን ሕዝብ ስምምነት ከግንዛቤ በማስገባት ክሎችን ይፈጥራል ይላል፡፡ አንቀጽ 47 የአኗኗር ዘይቤዎችን፣ ቋንቋን፣ ማንነትን እና የሚመለከተውን ሕዝብ ስምምነት መሰረት በማድረግ  9 ክልላዊ መንግስታትን (ክልሎችን) መስርቷል፡፡

ለደቡብ አፍሪካ ጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ በአጠቃላይ መሬትን መቆጣጠር እንዳስቻለው እንደ ደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ሕገ መንግስት እና ሌሎች ሕጎች ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የዘ-ህወሀት ሕገ መንግስት በአንቀጽ 40 (3) ሁሉም የመሬት የባለቤትነት መብት በዘ-ህወሀት እና በዘ-ህወሀት ታዛዥ ሎሌዎች፣ ተባባሪዎች እና በክልል ያሉ ግብረ አበሮች አማካይነት መሬትን በብቸኝነት ለመቀራመት እና ለመቆጣጠር እንዲህ የሚል መብትን አጎናጽፏል፣ “የገጠር እና የከተማ መሬት እንዲሁም ሁሉም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች የመንግስት እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው፡፡ መሬት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ንብረት ነው፡፡ እናም አይሸጥም ወይም ደግሞ አይለወጥም“ ይላል፡፡ ሆኖም ግን ዘ-ህወሀት በክልሎች የሚገኘውን በመቶዎች እና በሺዎች ሄክታሮች የሚቆጠረውን አንጡራ የሀገሪቱን ለም መሬት ድብቅ ለሁኑት ሸፍጠኛ የቢዝነስ ሰዎች እየቸበቸበ በማቀራመት ላይ ይገኛል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ካሩቱሪ የተባለው የሕንድ ኢንቨስተር በመሬት ቅርምቱ ያገኘውን መሬት እና የዌልስን ግዛት የሚያህለውን እና በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ዘ-ህወሀት የሚነካበት ከሆነ የሕንድን ኃያልነት እንደሚያሳየው ድፍረትን በተላበሰ መልኩ ለህወሀት የዘራፊ ቡድን ስብስብ ነግሮታል፡፡  ወይ የካርቱርሪ በእራስ መተማመን ድፍረት እንነጋር!

ኢትዮጵያን ክልላዊ በማድረግ የዘ-ህወሀት አገዛዝ እና ታዛዥ ሎሌዎቹ በኢትዮጵያ ብዙሀን ሕዝብ ላይ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይ ጌቶች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች የበላይ የአፓርታይድ አገዛዝ በርካታ አስርት ዓመታትን የወሰደበት ድርጊት ዘ-ህወሀት ግን በ25 ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ችሏል፡፡ ዘ-ህወሀት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ክፍት በሆነ ከባቢ አየር ውስጥ አስሮ እና እንደ ከብት በበረት አጉሮ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መብት ገፍፎ ሀገሪቱን በክልላዊነት በጥጣሶ በማተራመስ ላይ ይገኛል፡፡

ሁልጊዜ እንደማቀርበው የክርክር ጭብጥ ሁሉ የጎሳ ክላልዊነት ዋና መሀንዲስ የነበረው እና አሁን በሕይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ የደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ሄንድርክ ቬርወርድ እንዳደረገው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ ክፍፍልን መሰረት ባደረገ ራዕይ በመገፋፋት ሀገሪቱን በጎሳ ከፋፍሎ በስቃይ ውስጥ እንድትሆን እና ለከፍተኛ አደጋ እንድትዳረግ አድርጓታል፡፡ አምባገነኑ መለስ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ያህል የኢትዮጵያን ሕዝቦች የግንኙነት ክር ለመበጠስ እና በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ እና በክልል እንድትቀነበብ ያለ  የሌለ ጥረቱን አድርጎ ነበር በተፈጥሮ ትዕዛዝ ተቀደመ እንጅ፡፡ አምባገነኑ መለስ ሙሉ በሙሉ በጎሳ እና በዘር ግንኙነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት አዋቅሯል፡፡

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ጥቂት የነጮች ዘረኛ አገዛዝ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ከአንድ የትወልድ ቦታ ወደ ሌላ ሲያዘዋውር እንደነበረው ሁሉ ዘ-ህወሀትም አንድ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ እና የ”አማራ” ጎሳ ቡድን አባላትን ከደቡብ ክልል (ከ9 ክልሎች አንዱ ከሆነው) በኃይል በማፈናቀል የጎሳ ማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከደቡብ ክልል በኃይል ላፈናቀላቸው የአማራ ብሄረሰብ ዜጎች የሰጠው ማሳመኛ እንዲህ የሚል ነበር፣ “…በታሪክ አጋጣሚ ላለፉት አስርት ዓመታት ከምስራቅ ጎጃም የመጡ በርካታ ህዝቦች ወደ 30,000 የሚጠጉ ሰፋሪዎች በቤንች ማጅ ዞን (በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍረው ይኖሩ ነበር፡፡ በጉራ ፈርዳ ወረዳ ከ24,000 በላይ ሰፋሪዎች አሉ“ ብሎ ነበር፡፡ በሰፈራ ፕሮግራም በዘለቄታዊ መንገድ ለዘመናት ቀደምቶቻቸው ሲኖሩበት ከነበረው አካባቢ ከጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል እና ከኦሞ ወንዝ ሸለቆ በኃይል በማፈናቀል መሬቶቻቸው በጫረታ አማካይነት ለሆዳም ስግብግብ ብዙሀን የግብርና ቢዝነስ ለሚያካሂዱ ድርጅቶች ተሰጥቷል፡፡

በዘ-ህወሀት ስቃይ እና ለመቋቋም የማይቻል ክልላዊ ደባን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የግጭቶች አስወጋጅ ቡድን/International Crises Group (ICG) በተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት አስደማሚ ጥናት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ “ኢትዮጵያ፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም እና ቅሬታዎቹ“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጥናቱ ICG በጎሳ ፌዴሪያሊዝም (በክልላዊነት) ምክንያት ዜጋዊነት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ማንነት በጎሳ መሰረት ላይ የሚሰጥ የመሆኑን ችግር ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ ያቀርባል፣  “የጎሳ ፌዴራሊዝም በሀገሪቱ መካከለኛው ከፍተኛ አካባቢዎች በሚኖሩት እና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ኦሮሚያ እና አማራ በጣም ትንሽ የሆነ የሕዝብ ብዛት ካላቸው እንደ ጋምቤላ እና ሶማሊ ካሉት ጋር የማይመሳሰል ፌዴሬሽን በእኩል ተሰጥቶ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጎሳ ፌዴራሊዝም ጥቂት ቡድኖችን በማጠናከር ደካማ ክልላዊ መንግስታትን በመፍጠር የብሄራዊነት ጥያቄን መመለስ ተስኖታል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ውይይት እና እርቀ ሰላም ለማውረድ የመለስ አምባገነናዊ አመራር ሊቀበል ባለመቻሉ ምክንያት በአሁኑ ወቅት እየታዬ ያለውን ሁኔታ እንዲባባስ በማድረግ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በመሄድ የኢህአዴግ የጎሳ ፖለቲካ ለስልጣን ስስ መሆን በቀጣይነት የጎሳ ግጭት ለመከሰት የሚያስችል ፍርሀትን አንግሶ ይገኛል፡፡“ የICG ዘገባ ግልጽ እንዳደረገው በረዥሙ የጊዜ እይታ የጎሳ ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መበተታተን እና መለያየት ሊያመራው ይችላል፡፡ አሁን ብሄራዊነት የሌለው ሀሰተኛው መሲህ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ስልጣን ሲይዝ ሀገሪቱ ወደ መበታተን አደጋ ላይ ወድቃ እንደነበር ጉራውን ቸርችሮ ነበር፡፡ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጡን አቅርቦ ነበር፣ “ማንም ትንታኔ የሚያቀርብ ባለሙያ እንደሚገምተው ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ እና ሶቪዬት ህብረት እንደሄዱበት ባለ መንገድ ላይ ልትጓዝ ትችላለች“ በማለት መተንበይ ይችላል ብሎ ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግን ኢትዮጵያ እንደነ ዩጎዝላቪያ፣ ሶማሌ፣ ኮንጎ ወይም ደግሞ ኤርትራ እንደሆነችው እንኳ  ስትሆን አልታየም፡፡

ሀሰተኛው መሲህ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው መለስ ሁልጊዜ እራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ ሕዝቡን በማስፈራራት ከእግሩ ስር ለማንበርከክ እንዲችል ማንኛውንም አስፈሪ የሆነ ነገረ ሁሉ እየቃረመ ያስፈራራል፡፡ እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን የጎሳ መለያየት፣ መበታተን፣ መከፋፈል እና ጽንፈኝነት የመለስ አገዛዝ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመኖር እና አንጡራ የሕዝብን ሀብት እየዘረፉ ለመኖር እንዲመቻቸው የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎቻቸው ናቸው፡፡ በእውነተኛ የፌዴሪያሊዝም ስርዓት ብሄራዊው መንግስት የክልል መንግስታት ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ክልላዊ መንግስታት የብሄራዊው መንግስት ፍጡሮች እና በዘ-ህወሀት እጅ ተጠፍጥፈው የተሰሩ መንግስታት ናቸው፡፡ በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ብሄራዊ መንግስት ውሱን የሆኑ እና የተቆጠሩ ስልጣኖች ተሰጥተውት የክልል መንግስታት የጋራ የሆኑ ነገሮችን ማስፈጸም ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘ-ህወሀት ስልጣን ሰፊ እና ያልተገደበ ነው፡፡ እናም በክልሎች ላይ ጣልቃ ለሚያስገባው ስልጣኑ ምንም ዓይነት ገደብ የሌለው በመሆኑ እንደፈለገው በማተራመስ ላይ ይገኛል፡፡ በዘ-ህወሀት ክልላዊ ስርዓት ዘ-ህወሀት እና ግብረ አበር ክልሎቹ በሕዝቦች መብቶች እና ነጻነቶች ረገጣ እና ለሚያደርጉት ጣለልቃገብነት ክልከላ ዘብ የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል የለም፡፡ በቀላል አገላለጽ የዘ-ህወሀት ክልላዊ ፖሊሲ የዘ-ህወሀት አምባገነናዊ አገዛዝ ቀጥተኛ ቅጅ ነው፡፡ ክልላዊነት በየራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል በሚል በማስፈራሪያነት ተወሽቆ ይገኛል፡፡

በደቡብ አፍሪካው በጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ አፓርታይድ እና በዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም አፓርታይድ መካከል ያሉት ተመሳሳይነቶች ለመመዝገብ ከሚያስቸግር በላይ በርካታ ናቸው፡፡ ዘ-ህወሀት ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ስልጣኑን፣ ውክልናውን እና የውሳኔ ሰጭነት ተግባሩን እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ አፓርታይድ ብሄራዊ ፓርቲ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ተቆጣጥሮ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ዘ-ህወሀት በክልላዊ ፖሊሲው የአማራ ብሄረተኞች (ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ ወታደሮች እያለ የሚጠራቸው) የድሮውን ስርዓት በማምጣት በብሄረሰቦች ላይ የአማራን አገዛዝ ሊጭኑባችሁ ነው በማለት በእርሱ ክልላዊ ፖሊሲ ላይ ትችት የሚያቀርቡትን ጸጥ ለማድረግ ይጠቀምበታል፡፡ ዘ-ህወሀት ሌሎችን ተቃዋሚዎች ጽንፈኛ አክራሪዎች እና እንደ ሩዋንዳ የኢንተር ሀሞይ እልቂትን ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው በማለት ይፈርጃቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ተቃዋሚዎቹን “የኮሙኒስት አሸባረዎች” ናቸው በማለት ይጠራቸው ነበር፡፡

ዘ-ህወሀት በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ያደርጋሉ፡፡ የዘ-ህወሀት መንግስት በመንግስት ላይ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፡፡ አምባገነኑ መለስ በህይወት በነበረበት ጊዜ በመንግስት ላይ መንግስት የሚለው ሸፍጣቸው ገና ከጫካ በነበሩበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረ እና ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ታማኞቹን እና እሺ የሚሉ ሰዎችን ብቻ ከገንዘብ ገንዳው ውስጥ የሚያሳትፍ ስርዓትን ዘርግቷል፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ሁሉ በክልሎች ስማዊ የነጻ ውሳኔ ሰጭነትን ይፈቅዳል፡፡ ሆኖም ግን እውነታው ሁሉም ውሳኔዎች በማዕከል ተሰባስበው የተያዙ እና በዘ-ህወሀት በመንግስት ላይ መንግስት ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ የዘ-ህወሀት የደህንነት እና የስለላ ኃላፊዎች በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንሶች ላይ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ላይ በመንግስት ላይ መንግስት እየሰለሉ ወሬ በማነፍነፍ ለዘ-ህወሀት አመራሮች የሚያቀብሉ ናቸው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ በባንቱስታንሶች ላይ ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዘ-ህወሀትም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ ለመሬት ቅርምቱ እና ለሌላው ሀብት እና ዘ-ህወሀትን ለመገዳደር ችሎታው ለሌላቸው እና በዘ-ህወሀት ላይ ጥገኛ የሆኑትን ክልሎችን ለመቆጣጠር እገዛና እና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

የዘ-ህወሀት የደህንነት መዋቅር በክልል ውስጥ ያሉ ባለስልጣኖችን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠሯቸዋል፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ መረጋጋት አይታይበትም በሚባል አካባቢ የዘ-ህወሀት የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንስ አፓርታይድ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ከክልል ባለስልጣኖች ነጻ በሆነ መልኩ ይሰራሉ፡፡ የዘ-ህወሀት ባለስልጣኖች የደህንነት እና የወታደራዊ ኃይሉን እንቅስቃሴ በክልሎች ይመራሉ፡፡ ማንም የክልል ባለስልጣን ለዘ-ህወሀት መስመር የማያጎበድድ ከሆነ ከስልጣኑ እንዲባረር ይደረግ እና የሙስና ክስ እንዲመሰረትበት ይደረጋል፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች አገዛዝ አፓርታይድ በባንቱስታንሶች ላይ ያደርጉት እንደነበረው ጥብቅ ቁጥጥር ሁሉ ዘ-ህወሀትም በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ላይ በርካታ ስልቶችን በመቀየስ ጥብቅ ቁጥጥር ያካሂዳል፡፡ ዘ-ህወሀት ፖሊሲዎቹን ሽፋን ለመስጠት፣ ለማስመሰል እና ለማስፈጸም ኢህአዴግ የሚባለውን የይስሙላ የፓርቲ ስብስብ በማስመሰያነት ይጠቀማል፡፡ ክልሎች ለበጀት እና ለሌሎች ድጋፎችም በዘ-ህወሀት ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ምክንያት ዘ-ህወሀት ክልሎቹ እና ሌሎች በእርሱ መስመር አጎብዳጅ ሆነው እንዲኖሩ ስልጣኑን ለቁጥጥር ይጠቀምበታል፡፡

እንደአፓርታይድ ጓደኞቻቸው ሁሉ ዘ-ህወሀቶችም በተመሳሳይ መልኩ የፈጠሯቸው የጎሳ-ቋንቋ ቡድኖች አንድ ዓይነት እና ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን አንድ ዓይነት ያልነበሩ እና ቀላል በሆነ መልኩ በአኗኗ ዘይቢያቸው፣ በቋንቋ፣ በማንነት መፈረጅ እና መወሰን አልነበረባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በውልደት የተዋኸደ፣ ተመሳሳይ ባህል እና ማንነት ያላቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ልብወለድ  ስታሊኒናዊ ዘ-ህወሀቶች ጥሩ ሊመስል ይችላል፣ ሆኖም ግን እውነተኛውን እና ታሪካዊውን የጎሳ ልዩነቶችን እና አንድነቶችን አያንጸባርቅም፡፡ የዘ-ህወሀት የጎሳ ሀሳብ ከታሪካዊ እውነታ ጋር የሚጣረስ እና ምንም ዓይነት ወጥነት የሌለው ድልዱም አስተሳሰብ ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ንጉሳዊ አገዛዝ እስከወደቀበት እ.ኤ.አ እስከ 1974 ድረስ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ገዥ የነበሩት ልዑል መንገሻ ስዩም በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዘ-ህወሀትን ክልላዊ መዋቅር የውሸት መሆኑን አሰተባብለዋል፡፡ ልዑል መንገሻ ወልቃይት ጠገዴ ከአማራ ይዞታነት ተነስቶ ወደ ትግራይ መካለሉን አስመልከቶ ወደ ትግራይ እንዲካለል የተደረገውን የዘ-ህወሀትን ውሳኔ በጽኑ ተቃውመውታል፡፡ በሌላ አባባል በወልቃይት ጠገዴ ወደ ተግራይ መካለል ዘ-ህወሀት አኗኗር ዘይቤ፣ በቋንቋ በማንነት እና ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው ሕዝቦች የሚለውን የእራሱን ሕገ መንግስት እንኳ የጣሰ እና በሸፍጥ የእራሱ ግዛት ለማድረግ ያደረገው እኩይ ምግባር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ክልላዊነት አከላል ኢትዮጵያውያንን በጎሳ መስመር በመከፋፈል ለዘ-ህወሀት አገዛዝ እንዲመቸው ዓላማ ያደረገ እና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የተቀየሰ የዘ-ህወሀት የጥፋት ዕቅድ ነው፡፡ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ቴደ ቬስተል “የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፡ መንግስት አቀፍ የጎሳ ጥላቻ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፋቸው እንዲህ በማለት የዘ-ህወሀትን የዘ-ህወሀትን ክልላዊ ስልት ጨምቀው አቅርበዋል፣

“የኢህአዴግ ሌላው ገጽታው [የብዙሀነት ቅርጽ ያለው ለማስመሰል በህወሀት የተፈጠረው የሸፍጥ ድርጅት] ዋና ስልት የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችን እና ሕዝቦችን መብት ትኩረት በሰጠ መልኩ የተዋቀረ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት አስተዳደርን ለመመስረት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ትልቅ የሚመስል መርህ ከሌኒን የተኮረጀው ከውሶኒያን ይልቅ የማኪያቬሊንን ሸፍጥ የተላበሰ ነው፡፡ እነዚህ ብዙ መስለው የሚታዩት እና ኢህአዴግ/ኢፌዴሪን የሚዘውሩት ትግራውያን ሌሎችን የጎሳ ቡድኖች እየከፋፈሉ እና በጥልቅ የጎሳ ጥላቻ እርስ በእርሳቸው እንዲናቆሩ በማድረግ ወይም ደግሞ እነርሱ ባለቻቸው ትንሽ እውቀት ላይ በመመስረት ትናንሽ ግዛቶቻቸውን በማስተዳደር ተግባር ላይ ተጠምደው ባሉበት ሁኔታ ታላቁ የአገር ጉዳይ በአንድ ፓርቲ መንግስት እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግ ታላቋ ኢትዮጵያ እያለ የሚያሰራጨው የውሸት የብሄራዊ ፕሮፓጋንዳ በቁጥጥር ስር ይውል እና የእርሱ ተቃዋሚዎች እንዲከፋፈሉ እና እንዲሸነፉ ያደርጋል፡፡“

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ፡ ኢትዮጵያ በእናንተ እጅ ላያ ናት፡፡

ከአሜሪካ የሕግ ዳኞች አንዱ እና እጅግ በጣም ታዋቂ የሆኑት ጌሪ ስፔንስ በአንድ ወቅት በወንጀል ጉዳይ ላይ ያደረጉት የመዝጊያ ንግግር ውስጣዊ ስሜቴን እና ቀልቤን ስለገዛው እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምን ማድረግ እንደሚችሉ እና ለእራሳቸው እና ለሀገራቸውስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ታላቅ ትምህርት ይሆናል በማለት ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ፡፡ ስፔንስ እንዲህ በማለት ሞግተዋል፡

“ክቡራት እና ክቡራን፣ ከእናንተ ልለይ ነው፣ ሆኖም ግን ከእናንተ ከመለየቴ በፊት ስለአንድ ብልህ ሽማግሌ እና ስለአንድ አጭበርባሪ ልጅ ታሪክ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ አጭበርባሪው ልጅ ሽማግሌው ምን ያህል ሞኝ እንደሆኑ ለማሳት ዕቅድ ነበረው፡፡ አጭበርባሪው ልጅ ከጫካ ውስጥ አንዲት ወፍ ያዘ፡፡ እርሷንም በእጆቹ ያዛት፡፡ የትንሿ ወፍ ጅራት ከጁ አልፋ ትታይ ነበር ፡፡ በእጆቹ ላይ ያለችው ወፍ በህይወት ነበረች፡፡ ዕቅዱ እንዲህ የሚል ነበር፡ ወደ ሽማግሌው እያመላከተ “ሽማግሌው በእጆቼ  ላይ ምንድን ነው ያለው?“ ሽማግሌው ሰው እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል፡፡“ ከዚያም ልጁ እንዲህ ይላል፣ “ሽማግሌው ወፏ በህይወት አለች ወይስ በህይወት የለችም?“ ሽማግለው ወፏ በህይወት የለችም ሞታለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ ልጁ እጆቹን ግራና ቀኝ በመክፈት ወፏ በነጻነት እንድትበር ሆኖ በዛፍ ላይ ታርፍ እና በደስታ መኖር ትጀምራለች፡፡ ሆኖም ግን ሽማግሌው ሰው ወፏ በህይወት አለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ አጭበርባሪው ልጅ በእጆቹ መካከል ወፏን አጣብቆ እና ደፍጥጦ እንድትሞት በማድረግ “ሽማግሌው ይመልከቱ ወፏ ሞታለች“ ይላል፡፡  በዚህም መሰረት ልጁ ወደ ሽማግሌው በመሄድ ቀረበ እና እንዲህ አለ፣ “ሽማግሌው በእጆቼ ላይ ምን ይዣለሁ?“ ሽማግሌው እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል፡፡“ ልጁ እንዲህ አለ፣ “ሽማግሌው ወፏ በህይወት አለች ወይስ ደግሞ በህይወት የለችም?“ ሽማግሌው ምናቸው ሞኝ  እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፏ በእጅህ ላይ ናት“ አሉ፡፡

እኔም ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኢትዮጵያ በእጃችሁ ላይ ናት እላቸዋለሁ፡፡ በህይወት ያለች ወይም በህይወት የሌለች ወይም ደግሞ ወደፊት የምትኖር ወይም የምትሞት ብቻ ከሆነ እናንተው ብቻ የምታውቁት ይሆናል፡፡ ለዘላለም የምትኖር መሆኗን ግን አረጋግጡ!

ይቀጥላል… (አንደትግሉ )

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: