The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ወያኔያን ሆይ! የሸአቢያን ሸአቢያነትማ እናውቀዋለን እኮ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርዳው)

Amsalu

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርዳው

 

መሰንበቻውን የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረውና በዘመነ ወያኔ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ዕድል ፍጹም ዝግና እየተጃጃሉ በከንቱ ጊዜን ማባከን እንደሆነ ተረድቶ የቀረውን አማራጭ በመጠቀም የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ሲል ከጓዶቹ ጋር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀለውን ወንድማችን ተስፋሁን ዓለምነህ መገደሉን የሚያረዳ ወሬ ሲናፈስ ነበር፡፡

አናፋሾቹ የተገደለበትን ምክንያት ሲናገሩ ““ተስፋሁን የሸአቢያን ዓላማና በሸአብያ ምክንያት ትግሉ የትም ሊደርስ የማይችል መሆኑንና የሸአቢያ መጠቀሚያ ከመሆን ያለፈ ምንም የማይፈይድ መሆኑን በመረዳቱ መጠቀሚያ መሆንን ስላልፈለገ ለመጥፋት ሲያስብ ተደረሰበትና ሸአቢያ “ለወያኔ ሲሰልል አገኘሁት” ብሎ ሰበብ ፈጥሮ ገደለው”” ይላሉ፡፡

ብዙ ጊዜ የወያኔ ካድሬዎች እውነቱ ነገ እንደሚወጣና እንደሚያፍሩ እያወቁም ለራሳቸው ጊዜያዊ ጥቅምና ዓላማ በሐሰት የሚያወሩት ብዙ ነገር አለና ይሄንንም ወሬ ከእነዚህ ዓይነት ወሬዎቻቸው እንደ አንዱ ቆጥሬው ነበረ፡፡ ሰሞኑን ግርማ ካሳ የተባለ ጸሐፊ ይሄንን ወሬ ሲያስተጋባ በማየቴ ግን ተስፋሁን መገደሉን ለማመን ዳዳኝ፡፡

ምክንያቱ ለምን መሰላቹህ እኔ ግርማ ካሳ የተባለው ሰው ወያኔ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ወያኔ “እወገድበታለሁ እነቀልበታለሁ” ብሎ የሚፈራውን ብቸኛውን የትግል አማራጭ የትጥቅ ትግልን እየተቃወመ አንዳች ለውጥ በሀገሪቱ እንዲያመጣ የጸጉር ቅጥነት ያህል እንኳን ስንጥቅ ክፍተት ያልተተወለትንና በተደጋጋሚ ተሞክሮ መንገድና ዕድል የሌለ በመሆኑና ዕድሉን እራሱን መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ ጨርሶ የሌለ ከመሆኑም በላይ ሰላማዊ የትግል አማራጮችን መጠቀም በአሸባሪነት አስከስሶ ወኅኒ የሚያወርድ ከፍተኛ ወንጀል እንደሆነ በታወጀበት ሀገር ሰላማዊ ትግል በሀገራችን ሊሠራ እንደሚችል በሰፊው ይሰብካል፡፡ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር እንዴት ሆኖ ሊሠራ እንደሚችል ሲጠየቅ ግን የሚናገረው አንድም ተጨባጭ ስልትና አሠራር የለውም፡፡

ለራሱ ካልመሰለው መቃወሙ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህም አልፎ ሰላማዊ ትግል በሀገራችን እንዲሠራ ጨርሶ ዕድል እንዳልተሰጠው እንዳልተፈቀደለትና ከወያኔ ማንነት አንጻርም ሊሠራ ሊፈቀድለት እንደማይችል ተረድተው የራሳቸውን ስልት ነድፈው የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ወገኖቻችንን ትግል ለማደናቀፍ ለማዳከም ተአማኒነት ለማሳጣት የቻለውን ያህል ይጥራል፡፡ ይሄ ድርጊቱ ከአቋምም ባለፈ ዓላማና ተልእኮ (mission) እንዳለው አሳየኝ፡፡

አቶ ግርማ ካሳ የአርበኞች ግንቦት 7 ትግል መቶ በመቶ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል እርግጠኛ ሆኖ ሲናገር ሰምቸው አላውቅምና እንደማይሳካ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሊሆን ባልቻለበት ጉዳይ ላይ ወያኔ ካልሆነ በስተቀር ለራሱ ለግሉ አቋም ከመያዝ ባለፈ ተልእኮና ዓላማ አንግቦ ለማደናቀፍ ሊንቀሳቀስ አይችልም ነበርና ነው ወያኔ መሆኑን እንድጠረጥረው ያደረገኝ፡፡ ከዚህ ቀደም እሱን በወያኔነት እንድጠረጥረው ላደረጉኝ ነገሮች

“ወያኔው ግርማ ካሳ ሆይ!” http://www.satenaw.com/amharic/archives/12120

በሚለው ጽሑፌ አንሥቸለት በዚያው ሰሞን በጻፈው ጽሑፉ “አንዳንዶቻቹህ እንደምታስቡኝ እኔ ከእናንተ ጋር የዓላማ ልዩነት የለኝም!” ከማለት በስተቀር ላነሣሁለት ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ አልቻለም አልፈለገም፡፡ አንድ ሰው የተለየ ዓላማና ተልዕኮ ካላነገበ በስተቀር አፉን ሞልቶ መልስ ሊሰጥ በማይችልበት ጉዳይ ላይ መቶ በመቶ እርግጠኛ እንደሆነ ሰው ሁሉ አሳቢ መስሎ በመንቀሳቀስ አቶ ግርማ እያደረገው እንዳለው ለማደናቀፍ ሊንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ስለሆነም ከዚህ አኳያ የአቶ ግርማን ወያኔነት ማረጋገጥ ይቻላል ማለት ነው፡፡ እናም ከዚህ ሰው ይህ ወሬ መስተጋባቱ ነው እንግዲህ “ተስፋሁን ሞቷል ማለት ነው!” የሚለውን ሥጋቴን ከፍ ያደረገው፡፡

ለምን መሰላቹህ “ተስፋሁን ትግሉ ከንቱ እንደሆነ ተረድቶ ለመጥፋት አሰበ” የተባለው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ ሸአቢያ ተስፋሁንን ሊያሳስረው ይችል ይሆናል እንጅ መግደሉ የሚያደርስበትን ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ኪሳራ የማያውቅ የማይረዳ ቂል ሆኖ እንዲህ ሰው እያወቀ “የወያኔ ሰላይ ነህ!” ብሎ ተስፋሁንን ይገለዋል የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ መግደሉን እርግጠኛ ባልሆንም ሸአቢያ አይገልም ወይም ገሎ አያውቅም እያልኩ አይደለም ባናይ ባንሰማም ሊገል እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ባይገል ኖሮ ስንት በስም የምናውቃቸው ወገኖቻችን ደብዛቸው ጠፍቶ ባልቀረ ነበር፡፡

እናም ይሄ ሰው ይሄንን ጉዳይ ሲያስተጋባ እንደቀላል ላልፈው አልቻልኩም፡፡ ተስፋሁን የሞተበት ምክንያት እንዳሉት ላይሆን ይችል ይሆናል እንጅ ሳይገደል አልቀረም የሚል ጥርጣሬ አየለብኝ፡፡ አሟሟቱ ሌላ ሆኖ አጋጣሚውን ግን ለራሳቸው ፍጆታ ለመጠቀም እየተሯሯጡ ያሉ መስለው ታዩኝ፡፡

ወያኔ አስርጎ በሚያስገባቸው ሰላዮቹ ታጋዮችን ለመግደል ጥረት እንደሚያደርግ የምናውቅ ይመስለኛል፡፡  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም ከዚህ አደጋ የተረፉ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ እናም ወያኔ ሸአቢያን ወንጅሎ የሚያገኘውን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ትርፍ አስቦ እራሱ ገሎት ሲያበቃ “ሸአቢያ… ብሎ ገደለው” ብሎ አስወርቶ ቢሆንስ? የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የትጥቅ ትግሉን እየተቀላቀለ ስለሆነ ይሄንን ጎርፍ ለመግታትና ወጣቱ እንዳይቀላቀል ወደዛ እንዳያስብ ለማድረግ ይሄንን ጥቅም ለማግኘት ዓላማ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ልጁን ገድሎት ሊሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ፡፡

እኔ ከተገንጣዮቹና ከትሕዴን በስተቀር ሌሎች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ኃይሎችን የምደግፍበት ምክንያት ሸአቢያ ቅን ደጋፊ እረዳት ተገን ነው ብየ በሸአቢያ ላይ እምነት በመጣል አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ደጋግሜ ጽፌበታለሁ፡፡ የሸአቢያን ዕኩይነትና ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ቀና እንደማያስብ እንደማይመኝ አሳምረን እናውቃለን፡፡ የበፊቱን ሁሉ ብንተወው አሁን በቅርቡ ነባርና አዳዲስ ተገንጣይ ኃይሎችን አደራጅቶ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማቸውን ለማሳካት ጥምረትና ትብብር ማድረጋቸውን ኖርዌይ ኦስሎ ላይ እንዲያውጁ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሁሉም መቀመጫቸው አስመራ ነው፡፡ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያደርግላቸውም ሸአቢያ ነው፡፡ ይሄንን እያደረገ ደግሞ በተመሳሳይ ሰዓት እኛን “ቀድሞም ሆነ አሁን ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አንድነት የጸና አቋም አለኝ!” እያለ ሊሸነግለን ይሞክራል፡፡

ይህ የሸአቢያ ተግባር የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራርን ለከባድ ፈተና እንደዳረገ እገምታለሁ፡፡ ባለፈው “ትግሉን ትተው በመመለስ አሜሪካ ገቡ ከእንግዲህ አይመለሱም!” ተብሎ ተወርቶ የነበረው ወሬ እኔ ውሸት የነበረ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከሕዝቡ የሚገጥማቸውን ምላሽ በመፍራት ምክንያቱም እነሱ የሚሉትን በመስማትና በማመን ከአውሮፓና አሜሪካ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በረሀ የገቡ ወገኖች ዘመዶችን፣ እዚህ ሀገር ቤትም ትግሉን አምኖ ለሀገሬ ደሜን አፈሳለሁ ብሎ በረሀውን ቆርጦ የተቀላቀለው ወገናችን ቤተሰቦችና የሕዝቡን “ልጆቻችንን ሰብካቹህ ወስዳቹህ እሳት ውስጥ ከከተታቹህ በኋላ እራሳቹህን አድናቹህ ልጆቻችንን እሳት ውስጥ ጥላቹህ የት ነው የምትመለሱት!” የሚለውን ሕዝባዊ ቁጣ በመፍራት “እዚያው ሔደን ሠራዊቱ እንደሚሆነው እንሁን!” በማለት ላይመለሱ ጥለውት ወተው ከነበሩበት በሕይዎታቸው ፈርደው ተማምለው እንደገና የተመለሱ ይመስለኛል፡፡

ለእነዚሁ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ወገኖቻችን ማስተላለፍ የምሻው መልእክት ቢኖረኝ እንዲህ ዓይነት ፈተና ውስጥ ወድቀው ከነበረ ለሸአቢያ ልባቸውን ሰጥተው እንደነበረ ያሳያልና ከባድ ስሕተት ፈጽመው እንደነበረ ሊያውቁት ይገባል፡፡ እንዴት ቢያስቡ ሸአቢያን ሊያምኑ ለሸአቢያ ልባቸውን ሊሰጡ እንደቻሉም ሳስበው ግራ ይገባኛል፡፡ ሊኖራቹህ ይገባ የተበረው አቀራረብ ለሸአቢያ በፍጹም ልባቹህን ባለመስጠትና ማስመሰልን በመካን ነገሮችን እንደሁኔታውና እንደአመጣጡ ለመመለስ በመገንዘብ ከእባብ ጋር የተኛቹህ ያህል በማሰብ ነበር ሸአቢያን ልትቀርቡት ይገባ የነበረው፡፡

እንዲህ ባለ አቀራረብ ብትቀርቡ ኖሮ ሸአቢያ ከእናንተ ዓላማና ፍላጎት እሱም በአደባባይ ከሚለፍፈው የሚቃረን ሥራ እየሠራ ፍጹም ተቃራኒ ዓላማ ያነገቡ ተገንጣይ የጥፋት ኃይሎችን ሲያደራጅና ድጋፍ ሰጥቶ ሲያቋቁም ስታዩ ድንጋጤ ባልተሰማቹህ ነበር፡፡ ይሄንን ድርጊቱን ከምንም ሳትቆጥሩ ጥበብ ብልሀት ማስተዋል በተሞላበት መንገድ የራሳቹህን ሥራ በመሥራት ጊዜያቹህን ለመጠቀም ጥረት ባደረጋቹህ ነበር፡፡ እርግጥ እንዲህ ባለ አቀራረብ ሸአቢያን ቀርቦ ዓላማን ማሳካት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ በጣም አድካሚና ጽናት ትዕግስት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና ከተቆረጠ ከተጨከነ ዓላማ ከተነገበ እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ለመክፈል ከተቆረጠ ቀላልና የሚቻል ነው፡፡ የተከፈለ ልብ ከተያዘ እንደነገሩ የሆነ ቁርጠኝነት ከተያዘና በጊዜ ገደብ ታጥሮ የጠሰነቀ ጽናት ብቻ ከተያዘ ግን አይቻልም! ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡

“ሸአቢያ ለኢትዮጰያ ቀና የማያስብና የራሱ የሆነ ዕኩይ ዓላማ ያለው ቢሆንም በሴራም በብልጠትም ሸአቢያን በልጠን በመገኘት ትግላችንን ማሳካት እንችላለን! የሚለው እልህና ቁርጠኝነቱ ካለን እዚያ ድረስ መሔድ ምን ያስፈልገናል? እዚሁ ሀገራችን ውስጥ ሆነን ይሄንን ሸአብያን በልጠን ትግላችንን ልናሳካበት ያሰብነውን ዘዴ ወያኔ ላይ ተግባራዊ በማድረግ ለምን ስኬታማ ለመሆን አንታገልም?” የሚሉ ወገኖች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ይሄ ቢቻልማ እዚያ ሔዶ እራስን ለአደጋ አጋልጦ መታገሉ ምን ያስፈልግ ነበር ታዲያ?

ወያኔስ ይሄንን ስለሚያውቅ አይደለም ወይ ከፍተኛ የጦር ሹማምንቱን ሙሉ በሙሉ ከራሱ ጎሳ ብቻ ያደረገው! ሌላው ቀርቶ ወያኔ የሆኑ አማሮችንና የሌሎችንም ብሔረሰብ ተወላጆች ሾሞ ያውቃል ወይ? በፊት የነበሩትን የይስሙላ ሥልጣን የነበራቸውን ከፍተኛ የጦር ሹማምንት እንኳን የግንቦት ሰባት ትግል መመሥረቱን ተከትሎ ገና ለገና አማራ ስለሆኑ “ከእነሱ ጋር ተባብረው አንዳች ነገር ያደርጋሉ!” ብሎ በመሥጋት ሐሰተኛ ክስ መሥርቶ በእነሱ ላይ በመፍረድ ወኅኒ እንደወረወራቸው የምናውቀው ታሪክ አይደለም ወይ?

ወያኔ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ለመክሰስና በእነሱ ላይ የፈለገውን እርምጃ ለመውሰድ አንዳች አጠራጣሪ ጉዳይ ሲፈጽሙ ማግኘት ለሱ ግድ አይደለም፡፡ ዘራቸው አማራ ኦሮሞ ወይም ሌላ መሆኑ ብቻ ለእሱ በቂው ከበቂውም በላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር በወሳኝነት ቦታ ላይ ከራሱ ተወላጆች በስተቀር ሌላ መቀላቀል የማይፈልገው የማይፈቅደው፡፡ ለይስሙላ የተሠየሙት ቢሆኑም ከስር በሚቀመጡላቸው ትግሬ የወያኔ አባላት የሚሽከረከሩ የሚታዘዙ እንጅ በራሳቸው ወሳኞች እንዳልሆኑ በግልጽ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡

እንደ ደርግ ዘመን ዘር ሳይለይ ሁሉንም ብሔረሰብ አሳታፊ አሥተዳደር ቢሆን ኖሮ ይቻል ነበር፡፡ በወያኔ ዘመን ግን እንደምታዩት ወያኔን በመጣል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ግብን ይዞ ተመሳስሎ በመግባት ሥራ ለመሥራትና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ምንም ዓይነት ዕድል ወይም ክፍተት የለም! ወያኔ ይሄ ክፍተት እንዳይኖር ለማድረግ እንኳንና የአመራር ቦታዎችን ሕዝቡን እንኳን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ በማሰር መተናፈሻ ለማሳጣት ምን ያህል ጥረት እያደረገ እንደሆነ የምናየውና የምናውቀው ነገር ነው፡፡

እናም እንኳንና ወያኔን ጥሎ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ዕድሉ ወይም ክፍተት ሊኖር ቀርቶ የቀበሌ ሊቀመንበር ለመለወጥ የሚያስችል ዕድል ወይም ክፍተት እንኳን ጨርሶ በሌለበት ሁኔታ ይሄንን ማሰብ አይቻልምና በከንቱ ለመድከም ጊዜን ለማቃጠል ካልሆነ በስተቀር ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ ነገር ግን የትጥቅ ትግልን በማደራጀት አንዳንድ ነገሮችን እያደረጉ ትግሉን ሊያግዙ የሚችሉ አንዳንድ የውስጥ አርበኞችን መጠቀም የሚያስችል ዕድል ግን ይኖራል እየተደረገም ይመስለኛል፡፡ ሕዝብና ታጋይ እንዲህ የተቀናጀና የተናበበ ትግል ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡

አምና ስለዚህ ሕዝባዊ ትግል በተለያየ ጊዜ ከጻፍኳቸው ጽሑፎች አራተኛው ጽሑፍ ላይ ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ውስጥ ለትግል የሚገባ ወገን እንዴት ባለ አቀራረብ ሸአቢያን ቀርቦ ተወዳጅቶ በመጠቀም ትግሉን ማሳካት እንደሚችል “በአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ትግል ላይ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ያሉ ፈተናዎችና ማርከሻ መድኃኒታቸው”

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45570

በሚለው ጽሑፍ ሰፊ ትንታኔ መስጠቴ ይታወሳል፡፡ አሁን እዚህ ላይ መድገም አልፈልግም፡፡  ነገር ግን ወደድንም ጠላንም አንድ ልናውቀው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ሸአቢያ የራሱ ዓላማ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ይሄንን ድጋፍ የሚያደርገውም ለራሱ እንጅ ለእኛ አስቦ እንዳልሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡

አውቀን ግን “አንተኮ ለራስህ እንጅ ለእኛ አስበህ አይደለም!” ማለት አይኖርብንም፡፡ እንዲያውም ለእኛ ብሎ እንደሚያደርገው እየመሰከርን ማመስገን ይኖርብናል፡፡ ከዚህም አልፎ ጥቅሜ የሚለውን ኢፍትሐዊ ጥቅም እንደምናስከብርለት ቃል ግቡልኝ ቢል የልባችንን በልብ አድርገን የውሸታችንን “እንዴ ላንተማ!” ከሚል ኩሸት ጋር ቃል መግባት ያስፈልጋል፡፡ ፈርሙ ቢለንም ሳናወላውል በዐሥር ጣታችን ግጥም አድርገን መፈረም ይኖርብናል፡፡ መቸም እሱ አያፍርምና የማይገባውን ጥቅም ቃል ገብታቹሀልና ብሎ የቀኑ ቀን አድርጉልኝ ሲል “ዞር በል!” ብንለው ከየት ሊያገኘን ይችላል? እነሱ እንዲህ እያደረጉ እየወሰለቱ ነው ለዚህ የበቁት፡፡ ከወስላታ ጋር ታማኝ ሆኖ የፖለቲካ ጨዋታን በመጫወት ጥቅምን ማስከበር አይቻልም፡፡ የበለጠ ወስላታ በመሆን እንጅ፡፡ ሲሆን ሲሆን ሸአቢያ ካሳለፈው ሁሉ ተምሮ ቀናውንና ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርገውን አማራጭ ይመርጥና አድርጉልኝ ብሎ ይለናል ብለን የምንፈራውና የሀገራችንን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጠውን ጥያቄ ትቶ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን መንገድ ይመርጥና ከመቀያየም እንተርፍ ይሆናል ማን ያውቃል!

በዚህ መንገድ ካልሆነ በስተቀር የዋህ ሆነንና ከልባችን ውስጥ ያለንን የሚንቀለቀል የሀገርና የወገን ፍቅር ስሜት እያሳየነው “በኢትዮጵያ የመጣብኝን ምሬ አልምረውም! ኤርትራ የኢትዮጵያ ናት!” እያልን በገጽታችን “አንተንም ነገ ድራሽህን ነው የምናጠፋህ!” የሚል መልእክት እያሳየን እያስነበብነው ደኅንነታችን ይጠበቃል ዓላማችንንም እናሳካለን የሚል ቂል ካለ ለሚደርስበት ችግር ሁሉ ተጠያቂው እሱና እሱ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ “ሞያ በልብ ነው!” የሚለው ብሒላችን የሚሠራው እዚህ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ እዚያ ሔዶ የሚታገል ሰው በዚህ ደረጃ ብልጥና ንቁ አድርጎ እራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

ለሞራል (ለቅስም) እና ለሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች ካለን ክብርና ከምንሰጠው ከፍተኛ ዋጋ፣ ካለን አዎንታዊ የሰብእና ደረጃችን አንጻር እንዲህ ዓይነቱን መሠሪነት ንቀንና ጠልተን ትተነው ነው እንጅ መሠሪ ለመሆን ብናስብበትማ፣ ሴራ ልጎንጉን፣ ክፋት ተንኮል ሸር ልሥራ ቢባልማ ማንን ያቅታል? ክፉ ስሜቶችን አሸንፎ ቀናና ጥሩ ሰው መሆን የምስጉን ሰብእና ባለቤት መሆኑ ነው እንጅ የሚያቅተው ለዚህ ለዚህ ሲሉትማ ሰይጣኑስ ያግዝ የለ እንዴ!

“እንዴ! ምነው ከዚህ ሁሉ ጭንቅና ጥብ አርፈን ቁጭ ብንልስ!” ከተባለ አርፎ ቁጭ ማለቱ የሚያስከፍለው ዋጋ የባሰ እንጅ የተሻለ አይደለም፡፡ ቀድሞም ቢሆን ከውስጡ የትግል ቋያ ላልተቀጣጠለበት፣ ሲያደርጉ ዓይቶ ተከትሎ ለሔደ፣ ባርነትን ጭቆናን ለመሸከም ችግር ለሌለበት የሀገርና የሕዝብ ጉዳትና ሰቆቃ ስለማይገደው መናቅ መዋረዱ ስለማይሰማው አርፎ መቀመጥ ይቻለዋል፡፡

ነጻነታቸውን ለድርድር ለማያቀርቡት፣ የእናት አባቶቹ አደራ እረፍት ለሚነሣው፣ የሀገርና የወገን የራሱም መዋረድ መደፈር ለሚያንገበግበው፣ የታሪክ የማንነት መጥፋት ለሚከነክነው፣ ሆድ ሳይሆን ኅሊና ለሚበልጥበት፣ ሰብአዊነት እንጅ እንስሳዊነት ለሌለበት ግን አይቻለውም፡፡ ከዚህ ሁሉ አሻፈረኝ ብለው ትግል ላይ እያሉ ነጻነታቸውን በእጃቸው እንደያዟት ማለፍን ሽህ ጊዜ ይመርጣሉ፡፡ ስለሆነም “እንዴ! ምንነው ከዚህ ሁሉ ጭንቅና ጥብ አርፈን ቁጭ ብንልስ!” ስለተባለ አርፈው የሚቀመጡ ባይጠፉም ጨርሰው የማያስቡት የማይሞክሩን ቆራጦችም አሉና ደፋርና ጭስ መውጫ ስለማያጣ ከእግዚአብሔር ጋር በእነኝህ በቆራጦቹና መውጫ በማያጡት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ለሌላው ወገንም ቢሆን እዚህ ሀገር ውስጥ ሆነን በችጋር በረሀብ ተቆልተን የበይ ተመልካች ሆነን ከምንሞት፣ በወያኔ አጋንንታዊ የሥነልቡና ጥቃቶች በየቀኑ እየጠቀጠቀጥን እየተዋረድን እየተሰቃየን ሥነልቡናችን ተቀጥቅጦ ደቆ ተሠባብሮ ሰብእናችን ተዋርዶ ሽህ ጊዜ ከምንሞትና በድን አካል ይዘን ከምንንቀሳቀስ፣ በተስፋ መቁረጥ የሥነልቡና ቀውስና ሑከት ሰምጠን ጭንቅላታችን ተነክቶ ተበላሽቶ ለምንም የማንሆን የፈዘዘ የደነዘዘ የነፈዘ ከንቱ ዜጋ ሆነን ሳንሞት ሞተን ለምንም የማይሆን የማይጠቅም ነሁላላ ሆነን ከምንቀር፣ ወያኔ ወጣቱ ጠያቂና ተቆርቋሪ ኃላፊነት የሚሰማው የሀገሩ የወገኑ ነገር የሚገደው እንዳይሆን ባመቻቸው በሸረበው የሱስ ወጥመድ ተጠምዶ ታንቆ ተይዞ ለሀገሩ ለወገኑ ለቤተሰቡ ለገዛ ራሱም የማይሆን የማይጠቅም ከንቱ ዜጋና ሸክም ሆኖ ከመቅረትና በቁም ሞቶ ከምንቀበር የወያኔን አፍዝዝ አደንዝዝ አዚም አሽቀንጥረን ጥለን ነጻነታችንን በማወጅ ታጋዮችን ተቀላቅለን መሞከሩ ሽህ ጊዜ አይሻልም ወይ? ሰው ያለቀኑ አይሞት!

ሸአቢያም ሆነ ወያኔ ቢገለንስ? ይግደሉና ታዲያ! ያለቀንህ አትሞት! ቀንህ ከሆነ እቤትህም ብትሆን ያችን ቀን አታልፋት! የምትሞትበት ምክንያት ቢጠፋም እንኳ በትንታ ትሞታለህ፡፡ የምንሞትባቸው ሰበቦች በተለይ በአደጋ ከሆነ ያለቀናችን የሞትን ያስመስላሉ እንጅ አትሳሳቱ ሰው ያለቀኑ አይሞትም! እርግጥ ነው ከተማ ውስጥ እቤቱ በሰላም ተረጋግቶ ካለ ሕዝብ ይልቅ በጦርነት መሀል ያለ ሠራዊት የመሞት ዕድሉ ብዙ ጊዜ እጥፍ ሰፊ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡

አዎ! በጦርነት ውስጥ ብዙ ሰው ይሞታል፡፡ ይሄ ማለት ግን ሟቾቹ ያለቀናቸው በጦርነቱ ውስጥ ስለተገኙ ነው የሞቱት ማለት አይደለም፡፡ ቀናቸው ያች ቀን የሆነች ሰዎች በዚያች ቀን በአንድ ላይ መገኘታቸው ነው በአንድ ቀን በዚያ ምክንያት ሊሞቱ የቻሉት እንጅ ጦርነቱ ውስጥ ስለተገኙ አይደለም፡፡ ጦርነቱ መንስኤ ነው፡፡ ሰው ያለመንስኤ አይሞትምና፡፡ ቀናቸው አንድ ዕለት የሆኑ ሰዎች በአንድ ላይ በአንድ ቦታ መሞት ካለባቸው ጦርነት የግድ አይደለም፡፡ በምድር መናወጥም፣ በመጓጓዣና ሌሎች አደጋዎችም፣ በወረርሽኝም፣ በረሀብም ወዘተረፈ. በጅምላ መሞት አለ፡፡ ይሄ የሚሆነው ለመሞት የግድ ሰበብ ስለሚያስፈልግ እንጅ በእነዚህ ሰበቦች ሰው በጅምላ የሚያልቀው ሰበቦቹ ሰውን ያለ ቀኑ መግደል ስለሚችሉ አይደለም፡፡ እንደዛ ቢሆን ኖሮማ ከእነዚህ ሰበቦች መሀል የሚተርፍ ሰው ባልነበረ ነበር፡፡ እናም አይምሰላቹህ ሰበቡ ይለያይ እንጅ ሰው ያለቀኑ አይሞትም፡፡ ያለቀናቹህ ላትሞቱ አትፍሩ! አትንቀጥቀጡ! ማድረግ ያለባቹህንና የሚገባቹህን ከማድረግ አትቆጠቡ፡፡

እናም በሸአቢያ በወያኔ በምንትስ ለሀገራችን ሳንዋጋ ቢገሉንስ? ካላቹህ እንሙታ! ሀገርን ወገንን ብለን ወጥተን ስንሞት ደማችን ከንቱ ፈሶ የሚቀር ይመስላቹሀል? እንደ አቤል ደም እኮ ፍረድልኝ እያለ በእግዚአብሔር ፊት ይጮሀል፡፡ እግዚአብሔር እኮ የንጹሐንን ደም በከንቱ ፈሶ እንደቀረ ሳይበቀልለት አይቀርም፡፡ ለዚህ የታመነ ነው፡፡ ስለሆነም በከንቱ ሞተን የምንቀር አይደለንም በሞታችን የእግዚአብሔርን ቅን ፍርድ እናፋጥናለንና፡፡

አላወቃቹህትም እንጅ በከንቱ ሞተው ቀሩ እያላቹህ የምትሏቸው ወንድሞች ደም እኮ ቢኖሩ የማያደርጉትን በዚያ መልኩ በመሞታቸው ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እኮ ነው፡፡ ሞታቸው በብዙ መንገድ በኋላ ለሚመጣው ለውጥም ሆነ ስኬት የራሱ ድርሻና አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዝም ብሎ በከንቱ ፈሶ የሚቀር አይደለም፡፡ አንድ ታጋይ ለሀገሩ ሲዋጋ ሲታገል መሥዋዕትነት ከፈለ ለማለት የግድ ጦር ሜዳ ውጊያ ውስጥ መሠዋት አለበት ማለት አይደለም፡፡ የትም ይሙት ታጋይ ሁሌም የሀገሩ መሥዋዕትና ጀግና ነው፡፡ እናም እነዚህንና ሌሎች የማይረቡ ምክንያቶችን እየጠቀስን ወደ ኋላ በማለት ነጻነታችንን ወደኋላ ማስቀረቱን ትተን በገፍ ወደ ትግሉ መግባት ብንችል ይሄንን ተከትሎ የኃይል ሚዛኑ ስለሚለወጥ አብሮ የሚለወጥ ብዙ ነገር ይኖራልና ያም ለውጥ ተፈላጊውን ውጤት ያመጣልና እንዲህ ብናደርግ መልካም ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወጥተው በትሕዴን ወታደሮችና ለትሕዴን በሚያደሉ የሸአቢያ ወታደሮች ድንበር ላይ እየተጠለፉ ወደ ትሕዴን እንዲቀላቀሉ የተደረጉ ወገኖቻችን ሊቀላቀሉት ወደ ፈለጉት የትግል ኃይል የሚቀላቀሉበት ዕድል እንዲፈጠር መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከትሕዴን ሠራዊት የትግሬ ተወላጅ የሆኑት ሠላሳ በመቶ አይሞሉም፡፡ የቀሩት አማራ አገው አፋር ኦሮሞና ሌሎችም ናቸው፡፡ ትሕዴን የወያኔ ግልባጭ ነው፡፡ ስሙ እንደሚያመለክተው የሚታገለው ለትግሬ ሕዝብ ነው፡፡ ትግሬ ያልሆነና ኢትዮጵያን ብሎ የወጣ ታጋይ የጎሳ ፖለቲካን (እምነተ አሥተዳደርን) እየተቃወመ ለትግሬ የሚታገልበት ምን ምክንያት አለ? ስለሆነም እነኝህ ታጋዮች ወደ ወገኖቻቸውና ዓላማቸውን ወደሚጋሩት ኃይሎች መቀላቀል የሚችሉበት ዕድል መፈጠር ይኖርበታል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርዳው

amsalugkidan@gmail.com

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: