The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ዜና ፍኖተ ዴሞክራሲ (መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም.)

መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም.

Ø የወያኔ ቀኝ እጅ እና ጉዳይ ፈጻሚ የሆነው ኢሕአዴግ መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ የተባለለትን ስብስባ ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓም ጀምሯል። ስብሰባው ነገ መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓም ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጉባኤው በይፋ ያለፉትን ስድስት ወሮች የስራ ሂደት ይገመግማል ተብሎ ቢነገርም በዋናነት ግን በመላ ኢትዮጵያ ስለተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞና ቁጣ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ የድህረ ገጾች ግንኙነት መደናቀፍና የቴሌኮም መረጃ መለዋወጥ ላይ የተፈጠረውን ችግር ይመክርበታል ተብሏል። ለወያኔ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ኢሕአዴግ ምክር ቤት ወያኔ በኦህዴድ ላይ ስለሾማቸው ሰዎችና ታፍነው ስለተወሰዱ ሰዎች ውሳኔ የሚሰጡ ሲሆን ፍትህ ሚኒስትርን አፈርሰው ጠቃላይ አቃቤ ህግ ስለሚለው ህግና ማሪሚያ ቤት ለዓቃቤ ህግ ተጠሪ ስለሚሆንንበት ጉዳይ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የተባለው ተቋም  ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ስለሚያዘው ህግና የወያኔ ድርጅት ሰዎች የድህንነት ከለላና በተመለከተ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

Ø ስግብግብነት፣ አልጠግብ ባይነትና  ነጥቆ መውሰድ መለያቸው የሆነው የወያኔ ባለስልጣናት ጥቅም የሚገኝበትንና ገንዘብ አትራፊ የሆነውን ሁሉ መጠቀሚያ ማድረግ ባህሪያቸው ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ኢንተርኔትን በመጠቅም ከማንኛውም የዓለም ክፍል ጋር በነጻ ስልክ መገናኛ የነበሩትን ቫይበርና ዋትስ አፕን በክፍያ እንዲሰሩ ለማድረግ ያቀደ ከውጭ አገር የሚገቡ  ስልኮችም ለክፍያ እንዲያመቹ ልዩ ቁጥጥር ተደርጎባቸው ከውጭ የሚገቡ የግለሰስብ ስልክ ቁጥሮች ላይ ቀረጥ ይጣላል ተብሏል።፡ወያኔ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የቀረጥ ገቢም ለማግኘት ጭምር አዲሱን መመሪያ ማውጣቱ ተገልጿል። በዘመናዊ የዲጂታል ዘመን ዜጎች የቴክኖሎጂው ውጤትን ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የገንዘብ ክፍያ መጠየቁም ሆነ ዘመናዊ የስልክ ቀፎዎች ላይ ቀረጥ ለመጣል ማቀዱ የወያኔ አገዛዝ ቴክኖሎጂውን ሰው እንዳይጠቀምበት እያደረገ ያለ ሲሆን ከተጠቀመም ውድ ዋጋ በማስከፈል ሕዝብን ከማኅበራዊ ጎዳናና ከሶሻል ሚዲያ በማራቅ ደህንነቱን ለመጠበቅ ሆን ብሎ የተጠቀመበት ዘዴም መሆኑን ብዙ ዜጎች ይናገራሉ።

 

Ø የወያኔ ዘረኛና አምባገነን አገዛ በሕዝባዊ ተቃውሞና ቁጣ የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሰራቸው ሰዎች ደብዛቸው መጥፋቱና ቁጥራቸውን አለመግለጹ ይታወቃል። ጉዳዩን በደንብ የተከታተሉና መረጃ ያሰባሰቡ ወገኖች እንደገለጹት ከሆነ ደብዛቸው የጠፋ እስረኞችን ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንደተወስዱና በጦር ካምፕ ውስጥ ከፍተኛ እንግልት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ከ2800 በላይ ሰዎች በጦላይ እንደሚገኙና ከሀረር የመጡ የሰባት ልጆች እናትም እንደሚገኙበት አስታወቀዋል። ለወያኔ ታማኝ በመሆን የጦር ካምፑን የሚመሩና የእስረኞቹን ሁኔታ የሚከታተሉ በዙ ዋቅቤላ፤ ቀንአ ያደታ፣ ተሾመ ዱጋሳ ፤ ጸሐይ ነጋሽና የወያኔው ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መሆናቸው ሲታወቅ የወያኔ መሪዎችንና ኃላፊዎች ከእነዚህ ተላላኪ ግለሰቦች ጀርባ ሁኔታዎችን የሚዘወሩ መሆናቸው ተገልጿል። በጦር ካምፑ ውስጥ በተለይ የኦሮሞ ወጣቶች በብዛት ይኑሩ እንጅ ከመላ ኢትዮጵያ የተሰበስውና በወያኔ ላይ ተቃውሞና ቁጣ ያሰሙ የሕዝብ ልጆች የታጎሩበት የጦር ማሰልጠኛ መሆኑ ተብራርቷል።

Ø አንጋፋው የዘመናዊ ሙዚቃ የሳክሲፎን ተጫዋን ጌታቸው መኩሪያ ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሙዚቀኛው ጌታቸው መኩሪያ ዘመናዊ ሙዚቃን በኢትዮጵያ ስር እንዲሰድ ካደረጉና ሳክሲፎን መጫወት ከጀመሩ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚቀመጥ እንደነበረና በብሔራዊ ቲያትር በማዘጋጃ ቤትና በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ውስጥ ከሙዚቃ ተጫዋችነት እስከ ዋና መምህር በመሆን ለዘመናዊ ሙዚቃ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የተወጣ ሙዚቀኛ ነበር። ሙዚቀኛ ጌታቸው መኩሪያ በሳክሲፎን አጨዋወቱና የሙዚቃን መሳሪያ እንደልብ ማዘዝ በመቻሉ የሳክሲፎን ንጉስ የሚል ቅጽል ከሙዚቃ አፍቃሪዎች የተቸረ የተዋጣለት የሙዚቃ ባለሙያ ነበር። ሙዚቀኛ ጌታቸው መኩሪያ የዘጠኝ ልጆች አባትና የ81 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የነበረ ነው። የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ በዚህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሞት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፤ ለዘመዶቹ ለወዳጆቹ እና ለአድናቂዎቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

Ø ሞሳክ ፎንሴካ ከተባለ የፓናማ የሕግ ስራ ኩባንያ በድብቁ የወጡ 11.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ልዩ ልዩ ሰነዶች የተለያዩ መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች ታክስ ባለመክፈል እና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘቦችን በማስተላለፍ በኩል የሰሩትን ወንጀል ያጋለጡ መሆናቸው ተገለጸ። ምንጫቸው ካልታወቀ በአንድ የጀርመን የጋዜጣ ተቋም መጀመሪያ ተሰራጭቶ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተመራማሪ ጋዜጠኞች ተሳትፈውበት የወጣውና በርካታዎችን የሚያጋልጠው ዘገባ በወንጀሉ ውስጥ 140 የሚሆኑ ታላላቅ የፖሊቲካ ሰዎች 12 የወቅቱና የቀደሞ የአገር መሪዎችን ያጋልጣል። ከእነዚህም ውስጥ የአሁኑ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመዶች፤ የራሺያው የሚስተር ፑቲን የቅርብ ረዳቶች፤ የአይሳላንዱ ጠቃላይ ሚኒስትር፤ ሟቹ የእንግሊዙ መሪ የሚስተር ካምሪን አባት፤ የዩክሬኑ መሪ ፖሮሼንኮ፤ የሳኡዲ አረቢያ ንጉስ ተጠቅሰዋል። ከዚህ በተረፈ ለአርባ አመታት ያክል በኩባንያው የተስተናገዱ 214 ሺ የውጭ ኩባንያዎችን የሚያጋልጥ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሰሜን ኮሪያ የሶሪያ ኩባንያዎች፤ በእንግሊዙ HSBC በስዊዘርላንዱ Credit swiss በፈረንሳዩ ሶስይቴ ጄኔራል የተቋቋሙ ኩባንያዎች ከሞሳክ ፎንሴካ ጋር መስራታቸው ተጋልጧል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ለዚህ ዓይነት መሰረተ ቢስ ክስ የምንለው የለም ሲሉ የክሪምሊን ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ ደግሞ ሰነዱን አወጡት የተባሉት ብዙዎቹ ጋዜጠኞች የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሲአይ ኤ እና የልዩ አገግሎት ሰራተኞች መሆናቸውን ገልጾ ይህ በሩሲያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የተደረገ  የአሜሪካ ሴራ ነው ብሎታል። የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርም ስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ግፊት የተደረገባቸው ሲሆን ፓርላማው ፈርሶ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ እንዲያፈርሱ ፕሬዚዳንቱን ጠይቀዋል ተብሏል። አውስትራሊያ ፈረንሳይና ኒዘርላንድ ጉዳዩን እንመረምራለን ብለዋል።

Ø በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተሰማርተው የነበሩና ህጻናትን አስገድደው በመድፈር የተከሰሱ ሶስት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወታደሮች እስር ቤት እንዳሉ በአንድ ወታደራዊ  ፍርድ ቤት ላይ የቀረቡ መሆናቸው ተነገረ። ሁለቱ ህጻናትን አስገደደው ደፍረዋል የሚል ክስ የቀረባባቸው ሲሆን አንደኛው ለመድፈር ሙከራ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታል። ሶስቱም የቀረበባቸውን ክስ ሀሰት ነው በማለት ክደዋል። በማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ በተሰማሩ የተመድ እና የፈረንሳይ ወታደሮች ተፈጽማዋል የተባሉና ከተበደሉ ዜጎች አቤቱታ የቀረበባቸው ህጻናትን ጨምሮ ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች ከ100 በላይ የደረሱ ሲሆን ከእነዚህ ተከሳሾች ውስጥ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ለፍርድ ሲቀርቡ ይህኛው እስካሁን የመጀመሪያ መሆኑ ነው። የፈረንሳይ ወታደሮች በአዲስ መልክ የቀረበባቸውን ክስ እየመረመሩ መሆናቸው ኤኤፍ ፒ የተባለው የዜና ወኪል ቢያስታውቅም ከዚህ በፊት ለቀረቡት የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ይታወቃል። በሌላ በኩል በኮንጎ ዴሞክራቲክ ተሰማርተው የነበሩና አስገድዶ በመድፈር አቤቱታ የቀረበባቸው የታንዛኒያ ወታደሮች ልጆች ያስወለዱ መሆናቸውንም ተጎጅዎች ክስ አቅርበዋል። ክስ የቀረበባችው አስራ አንድ ወታደሮች ሲሆኑ 4 ቱ በቅርቡ የተሰማሩ የተቀሩት ሰባቱ ደግሞ ቀደሞ ባለው ስምሪት ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል። ባለፈው ዓመት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 69 የሚሆኑ ሰዎች በደል የተፈጸማብቸው መሆኑን ሲያመለክቱ ወንጀሉን የፈጸሙት ከ10 አገሮች የተውጣጡ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት መሆናቸው ተነግሯል። በዚህ ወር ውስጥ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አቤቱታ የቀረባባቸው የሰላም አስከባሪ ኃይል ቡድኖች ሁሉ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወሳል። አንድ ገለልተኛ የሆነ የጥናት ቡድን የተመድ ኃይላፊዎች ጉዳዩን በሚገባ አለመከታተላቸውና ለችግሩ መፍተሄ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ድክመት ያሳየ መሆኑ መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወርም በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተመድ ቋሚ መልክተኛ የሆኑት ከኃይላፊነት እንዲነሱ የተደረገ መሆኑ ይታወሳል።

Ø በሱማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ተልእኮ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ ህብረተ የሰላም አሰከባሪ ኃይል አባላትና የሱማሌ መንግስት ወታደሮች በጋራ ባካሄዱት የጥቃት እርምጃ ስድስት የአልሸባብ መሪዎችን የገደሉ መሆናችውን ገልጸዋል። ከተገደሉት መካከል አንዱ በዜግነት የመናዊ የሆነና ቦምብ በመስራት በኩል የተካነ ነው የተባለ ሲሆን ሌላኛው በስልጠና ስራ ላይ የተሰማራ ኬኒያዊ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያም አንድ ሌላ ወታደራዊ መሪ መገደሉ የተገለጸ መሆኑ ይታወሳል። አልሸባብ እስካሁን ለመግለጫው የሰጠው መልስ የለም።

Ø በሊቢያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዑክ ሚስተር ማርቲን ኮብለር ወደ ሊቢያ ተጉዘው በቅርቡ ከተመሰረተውና ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ወደሊቢያ ከገባው የአንድነት መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል። የአንድነት መንግስቱ በሊቢያ ውስጥ  ተቀባይነት እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት ወቅት  ሚስተር ኮብለር ወደ ዚያ ሄደው መገናኘት መቻላቸው ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኩል አጋዥ ሊሆን ይችላል ተብሏል። ባለፈው ወር ኮብለር ወደ ትሪፖሊ ለመግባት ጠይቀው በባለስልጣኖች የተከለከሉ መሆናቸው ይታወሳል። ባለፈው ረቡዕ ትሪፖሊ የገባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የአንድነት መንግስት ተወካዮች ቡድን እስከአሁን ድረስ በወደቡ አካባቢ በሚገኘው የባህር ኃይል ወታደራዊ ካምፕ ውስጥም በመሆኑ ለመስራት እየሞከረ  ሲሆን በተለያዩ የሊቢያ ክፍሎች ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ ይነገራል። የሊቢያ የኢንቬስትመንት ባለስልጣን፤ የሊቢያ የነዳጅ ኮርፖሬሽን እና የሊቢያ ማዕከላዊ ባንክ የአንድነት መንግስቱን የደገፉት ሲሆን 10 የሚሆኑ የሊቢያ የወደብ ከተሞችም የተለያዩ የሚሊሺያ ቡድኖች ድጋፋቸውን የሰጡት መሆኑ ተገልጿል፡፡

 

Ø በቦካ ሃራም ላይ ለመዝመት የተቋቋመው የጋራ ኃይል ለሶስት ቀናት ያህል በናይጀሪያ በካሜሩንና በቻድ ወሰን አካባቢ ባካሄደው አሰሳ 300 የሚሆኑ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ያደረገ መሆኑና ከ 2000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች አስሮ የፈታ መሆኑን በጋራው ኃይል ውስጥ የካሜሩን  ወታደራዊ ኃይል  አዛዥ የሆኑት ግለሰብ ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።  ዘመቻ የተካሄደው ኩምሸ ከምትባለው የሰሜን ናይጄሪያ ከተማ 35 ኪሎሜትር ላይ ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ መሆኑንና  በአሰሳውም የቦኮ ሃራም የማስልጠኛ ተቋሞችና ልዩ ልዩ መገልገያ መሳሪያዎች የተደመሰሱ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል። ቦኮ ሃራምን ለመደምሰስ ካሜሩን ናይጄሪያ እና ቻድ በጋር 9000 አባላት ማቋቋማቸው አይዘነጋም፡፤  

መጋቢት 26  ቀን 2008 ዓ.ም

Ø በኢትዮጵያ ያለውን ድርቅና ረሃብ ለማስወገድ ከውጭ መንግስታት በእርድታና በልገሳ የተገኘ እህልና ምግብ የጂቡቲ ወደብ በመጨናነቁ ምክንያት የእርዳታ እህል ለማራገፍ ያልተቻለ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። የወያኔ ቡድን መሪዎች የእርዳታ እህል በጂቡቲ ወደብ ለማራገፍ ባለመቻሉ በሱዳንና በበርበራ ወደብ ለመጠቀም መወሰኑን የወያኔ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ድርቅን ረሃብ አሳሳቢነት ወደ አስጊነት ደረጃ በደረሰበትና  የተረጀው ቁጥር እየጨመረ ነው በሚባልበት ሰዓት በሱዳን ወደብ በኩል የወያኔ መሪዎች የሚገግዱትን 100 ሺ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለማስገባት ውል ሲፈራረሙ ለተራቡና በድርቅ ለተገጎዱ ወግኖች ደግሞ በሱማሊያ በርበራ ወድብ በኩል 25 ሺ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ እህል ለማስገባት ወስኗል። ድርቅና ረሃብ በበረታበትና የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ለእርዳታ በሚረባረቡበት ሰዓት የወያኔ መሪዎች በንግድ ድርጅቶቻቸው አማኝነት ያስመጡትን ማዳበሪያ ከእርዳታ እህል ይልቅ ቅድሚያ መስጠታቸው የአገዛዙ ሆነ የመሪዎቹ አረመኔትን በግልጽ የሚያሳይ ሆኗል። በረሃብ የተጠበሰው ወገን የሚቀምሰውና የሚልሰው አጥቶ የእርዳታ እህል በየወደብ የሚያራግፈውና የሚያነሳው ባጣበት ሰዓት የወያኔ መሪዎች በየቀኑ 10 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ከሱዳን ወደብ እያነሱ ሲሆን የጭነት መኪናዎችም ቅድሚያ የወያኔን ማዳበሪያ እንዲያነሱ መታዘዛቸው ታውቋል።

Ø የወያኔ መሪዎች የነፍስ አድን ዕርዳታውን ከማስገባት ይልቅ  የንግድ ማዳበሪያዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ በማስነሳት በረሃብተኛው ሕዝብና በድርቅ ጉዳተኞች ህይወት ቁማር ሲጫወቱ በመሃል ሀገር የወያኔ ካድሬዎችና ሹማምንት የዕርዳታ እህልና አልሚ ምግቦችን ከተራቡ ወገኖች ጉሮሮ በመንጠቅና በመስረቅ እየሸጡ መሆናቸው ታውቋል። በስልጢ ወረዳ የወያኔ መሪዎች የመደቧቸው ባለሥልጣናት በረሃብና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እንዲፋፈል የተመደበውን 500 ኩንታል አልሚ ምግብ ማለትም ወተት ዘይትና በፕሮቲን የበለጸጉ ምግቦችን በቀጥታ ወደ ገበያ በመውሰድ እየቸበቸቡት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።  እነዚህ የአካባቢው  ባለሥልጣኖች ከወያኔ መሪዎች ጋር በመመሳጠር የእርዳታ እህሉንና አልሚ ምግብን ገበያ ማውጣታቸው የግለሰቦቹ ጭካኔና ስግብግብነት ብቻ ሳይሆን የወያኔ መሪዎችን ችላ ባይነትም አጋልጧል። የወያኔ መሪዎች ጫካ በነበሩበት ወቅት በድርቅና በረሃብ መነገድ የዘወትር ተግባራቸው የነበረ ሲሆን ስልጣን ከያዙ ወዲህም የእርዳታ እህልን እንደ ፖሊቲካ መሳሪያ በመጠቀምና በመሸጥ የግል ኪሳቸው ሲያደልቡ መቆየታቸው ይታወቃል። በኢትዮጵያ ከ450 ሺ በላይ ሕጻናትና አልሚ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ስልጢ ወረዳ ውስጥ ከ26 ሺ በላይ  እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው።

Ø ማኅበረ ቅዱሳን ከመጋቢት 15 ቀን 2008 ዓም እስከ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ሊያካሂድ አቅዶት የነበረውን ዐውደ ራዕይ በልዩ ልዩ ተልካሻ ምክንያትና ሰበብ እንዳይካሄዱ ካደረገ  ወዲህ ማኅበሩ ጉዳዩን በቅርብ በመከታተል ባደረገው ጥረት ዐውደ ራዕይ እንዲካሄድ ወያኔ የፈቀደ መሆኑ ተገልጿል። ፈቃዱ እንደገና ተሰጥቷል ይባል  እንጅ በተባለበት ቀንና ጊዜ ለምን እንደተከለከለና ማን እንደከለለከለ ወያኔ የሰጠው ምንም ዓይነት መግለጫ የለም። የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ደጋፊዎች አሁን ፈቃድ መገኘቱን ይናገሩ እንጅ ዕውደ ራዕዩ መቼና የት እንደሚካሄድ ገና በንግግር ላይ መሆናቸውን አልሸሸጉም።  የማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮትን  ድርሻችንን እንወቅ በሚል ርዕስ ዐውደ ጥናት አዘጋጆችን ዝግጁነቱን አጠናቆ ባለበት ሰዓት በወያኔ መሪዎችና ከፓትርያርኩ ጽ/ቤት ባሉ ሰዎች አማካኝነት መታገዱን በማስታወስ አሁንም የማኅበሩን ዓላማ ተሳክቶ ዐውደ ራዕዩ ተግባራዊ እስካልሆን ድረስ የወያኔ ሸርና የካባ ለባሽ ካድሬዎቹ ተንኮልን በተጠንቀቅ መጠበቅ ይገባናል ይላሉ።

Ø ዛሬ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓም በኮንጎ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ በብራዛቪል ከፍተኛ የጥይትና የከባድ መሳሪያ ድምጽ ሲሰማ መቆየቱን ነዋሪዎች ለዜና ምንጮች ካስተላለፉት መረጃ ለማወቅ ተችሏል። ማከለከሌ በተባለው ቀበሌ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ክፍሎች በአንድ የፖሊስ ጣቢያና በአንድ የመንግስት ህንጻ ላይ ጥቃት የፈጸሙ መሆናቸው ተነግሯል። የሬውተር የዜና ምንጭ በዘገባው እንደገለጸው የተቃዋሚ ደጋፊዎች የሆኑ ወጣቶች በአንዳንድ ቦታዎች “ ሳሱ ሥልጣን ልቀቅ” የሚል መፈክር ደጋግመው ሲያሰሙ እንደነበር ገልጿል።  ከ1971 ዓም ጀምሮ በሥልጣን ላይ የነበሩት ዴኒስ ሳሱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በድጋሚ ለሌላ አምስት ዓመታት የስልጣን ዘመን መመረጣቸውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ አይደለም  በማለት መቃወማቸው ይታወቃል። በዛሬው ግጭት ፖሊሶች  ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ የነበሩ መሆናቸው የዜና ምንጮች የዘገቡ ሲሆን ይኸው ታጣቂ ቡድን የኒንጃ ሚሊሺያ ቡድን ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ይሰጣሉ።

 

Ø 16 000 አባላት ያሉት የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሠራዊት ማህበር ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንቱ የሠራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ለመሆን ብቃት ስለሌላቸው ስልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው ብሎ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት የማህበሩን ውሳኔ በመቃወም የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይል አዛዥ ውሳኔው ለእርስ በርስ ግጭት የሚጋብዝ ከመሆኑም በላይ ህገወጥ ነው ብለውታል። ተቃዋሚዎች የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዙማ በስልጣን መባለግ ተከሰው ከስልጣን እንዲወገዱ ያቀረቡት ጥያቄ ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን በምክር ቤቱ ላይ ቀርቦ ውይይት የሚካሄድበት ሲሆን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ ፓርቲ አብዛኛውን መቀመጫ በመያዙ በተቃዋሚዎች የቀረበው ሀሳብ ውድቅ ይሆናል ተብሎ ተገምቷታል። በሌላ በኩል የጸረ አፓርታይድ ትግል መሪና ከሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ጋር በሮበን ደሴት ታስረው የነበሩት እውቁ አህመድ ካታራዳ ሚስተር ዙማ ከስልጣን መልቀቅ አለባቸው ብለዋል። ባለፈው ሳምንት ሚስተር ዙማ የተፈጸመው ስህተት ሆን ተብሎ የተደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።

Ø ከአልካይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውና አንሳሩ እየተባለ የሚጠራውን የጂሃዲስት ድርጅት ይመራ የነበረና በአሜሪካ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ሲፈለግ የቆየው ካሊድ አል ባርናዊ የሚባለው ግለሰብ በናይጄሪያ ውስጥ የተያዘ መሆኑ ተነገረ። ከአራት ዓመት በፊት አሜሪካ ግለሰቡን ዋና አሸባሪ ብሎ የሰየመ ሲሆን ግለሰቡን ለያዘ ወይም ለገደለ አምስት ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መዘጋጀቱን  ገልጾ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ከቦኮ ሃራም የተገነጠለውን ድርጅት አንሳሩን ይመራ የነበረው ካሊድ ባርናዊ በተለያዩ ጊዜያት በርከት ያሉ የውጭ አገር ሰዎችን በመግደል የሚጠረጠር ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ባለው ዋና እስር ቤት ላይ የተደረገውን ጥቃት አስተባበሮ በርካታ እስረኞች ያስፈታ መሆኑ ይነገርለታል።

Ø የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ትናንት መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓም በሰጠው መግለጫ በሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በዚህ ዓመት ወደ 400 000 (አራት መቶ ሺ) የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጿል። ድርቁ የተከሰተባችው አካባቢዎች ምስራቅ ሱዳን በምስራቅ ዳርፉር እና በመካከለኛው ኮርዶፋን ግዛት ሲሆን በድርቁ የተጎዳው በጠቅላላው 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ የተለያየ እርዳታ ሲደርግለት መቆየቱ ተነገርዋል። የምግብ እርዳታው በዚህ ዓመት በጠቅላላው 12.5 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑ ቃል አቀባዩ ገልጾ በጦርነት የተፈናቀሉትን ከመርዳቱ ጋር ተዳምሮ የበጀት ችግር ሊገጥም እንደሚችል ጠቁሟል።  

http://finote.org/April05EVE_Hr1.mp3

http://finote.org/April05EVE_Hr2.mp3

 

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: