The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች – ሚያዝያ 2, 2016

dollar

ሚያዚያ 02ቀን 2008 ዓ.ም. (April , 2016)

  አጫጭር ዜናዎች

·       በርሀብ ከተጠቃው ሕዝብ የእህል እርዳታ እያገኘ ያለው እጅግ በጣም ጥቂቱ መሆኑ ተነገረ

·         በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙትን የኦሮሞ ገበሬዎች የማፈናቀሉ እቅድ አለመሰረዙ ታወቀ

·         በአዲስ አበባ አሰቃቂ የመኪና አደጋ ደረሰ

·        በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጎርፍና የእሳት ቃጠሎ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

·         ወያኔ በቫይበርና በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ሊያስከፍል እና ቁጥጥር ሊያደርግ ነው ተባለ

የውጭ ምንዛሪ ጠፋ እየተባለ ባለበት ሁኔታ ወያኔ በየኤምባሲው የአባይ ግድብ ግንባታ አምስተኛ ዓመት በዓል በሚል ፈንጠዝያ በማዘዙ በየኤምባሲዎቹ የወያኔ ባለስልጣኖች ቅዳሜ እለት በውስኪና በቢራ ሲራጩ ቆይተዋል ። ወያኔና አፈ ቀላጤዎቹ ልብወለድን በማጥንጠን ስራው ከቆመ ስምንት ወር የሆነውን የአባይ ግድብ ልክ ቀን ተሌት እንደተገነባ አስመስለው ሰዉን በማታለል ከገንዘቡ ሊለያዩ ደፋ ቀና ማለታቸውም መቀጠሉ ተዘግቧል ። የፖለቲክ ተንታኞች ግን በአሁኑ ዙር ለወያኔ ሰለባ የሚሆን ዜጋ የለም ሊኖር አይገባም ሲሉ አሳስበዋል ። በሙስና የሚጠየቀው የወያኔ ጄኔራል ክንፈ ሜቴክ በሚለው መበዝበዣ ተቋም አማካኝነት ግድቡ የሚያስፈልገውን 10 ትላላቅ ተርባይን ለመስራት ስራውን ከተረከበ በኋላ የግድቡን ስራ ለሁለት አመት እንዲዘገይ የተደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ ለስምንት ወር ያህል ስራው መቆሙ ይታወቃል። ለቻይናና ቡልጋሪያ በተሰጠ ኮንትራት የመጣው ተርባይን የሚገጥም ሆኖ ባለመገኘቱ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉ ተጋልጧል ። ሜቴክ( የሚሊቴሪ ቴክኖሎጂ ተቋም) በሚል ስም በመለስ ዜናዊ የተቁቋመውን መስሪያ የሚመራው ጄኔራል ምንም የቴክኒክ ዕውቀት የሌለው ሲሆን በመስሪያ ቤቱ የተቀጠሩት 95 በመቶ ወያኔዎችና የትግራይ ተወላጆች ደግሞ ለታጋይ ጡረታ በሚል የተመደቡ እንጂ እንኳን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከክላሺን መፍታትና መግጠም ውጪ ችሎታ የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል።

 ወያኔ አደገ ተመነደገ የሚለው ኤኮኖሚ ወደ ውድቀት እያመራ ነው በማለት የፖለቲካ ታዛቢዎች አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ ። ድርቅና ረሃብ፤የኑሮ ውድነት፤ በስፋት የሚታየው ስራ አጥነት፤ የመብራት ሀይል እጦት፤ የ ፋብሪካዎች ምርት መተጓጎል፤ የአርሶ አደሩ ከመሬቱ መፈናቀል፤ የጦርነት ሁኔታ መብዛት እና ሌሎች ሁኔታዎች ለዚህ የአይቀሬ ለተባለው ውድቀት አስተዋጾ እየሰጡ መሆናቸውም ተሰምሮበታል ። ከሁሉም በላይ ግን ሞኝ የያዘው ፈሊጥ እንዲሉ የወያኔ የዘረኝነትና የብሄር ብሄርሰብ አባዜ ብዙ ቀውስ ማምጣቱ ተጠቅሷል ። የብሄረሰብ ኮታ ተዋጾ በሚል ምንም ችሎታ የሌላቸው ሰዎችን በሀላፊነት ቦታ ተመድበው ስራን በየፈርጁ መበደላቸው ላለው ቀጣይ ለሆነው ሁለገብ ቀውስና ውድቀት ተጠያቂ ነው ብለዋል ። በየቁልፍ ቦታዎች የተመደቡት ወያኔዎች የዘር ኮታን ከማብዛት ውጪ ይህ ነው የሚባል ችሎታ እንደሌላቸው ተቋሞችን ለኪሳራ ማብቃታቸው ምስክር ነውም ተብሏል ።

national bank of ethiopia

 በፓናማ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ደብቀዋል ተብለው ከተጋለጡት መሪዎችና ባለሀብቶች ውስጥ በርካታ ገና ስማቸው ያልተገለጠ ወያኔዎች እንዳሉበት ለማወቅ ተችሏል ፡፤ በቅርቡም ማንነታቸው በይፋ ይታወቃል የተባለ ሲሆን በርካታ ወያኔዎች በማሌዚያ፤በለንደን፤በኒውዮርክና ስዊስም ገንዘብ ሰርቀው ማስቀመጣቸው ከዚህ በፊት መጋለጡ ይታወሳል ።

 በደቡብ ሱዳን ለወያኔ የተሰጠው የቀድሞ የጋምቤላ አስተዳዳሪ ኦኬሎ አኳይና አምስት አብረው ተከሳሾች በተከሰሱበት የሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ መባላቸው ታወቀ ። ኦኬሎ ተሰዶ የኖርዌይ ዜጋ ቢሆንም ኖርዌይ የረባ ጠበቃም እንዳልቀጠርችለት የሚያሙ ታዛቢዎችም አልጠፉም ተብሏል ። ኦኬሎ ወያኔ በጋምቤላ ባደረገው ጭፍጨፋ ዋናው ተጠያቂዎች መለስ ዜናዊ፤አባይ ጸሃዬና በወቅቱ ባለስልጣን የነበረው ኦክተር ባርናባስ ናቸው ብሎ በመክሰሱ ወያኔ ሲያሳድደው እንደነበር ታውቋል ። በሰው ፍጅት ወንጀል አባይና ባርናባስ አሁንም ቢሆን መከሰስና ለፍርድ መቅረብ ያለባቸው ግለሰቦች ናቸው በማለት የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ ከዚህ በፊት መግለጹ የሚታወቅ ነው ።

 ተጨማሪ የቤት እስራዔሎች ቤተሰቦች በዚህ አመት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ሊመጡ ስለሚችሉበት ሁኔታ የእስራዔል ገዥ ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ስምምነት የደረሰ መሆኑን በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ ገልጿል። በመመሪያ መሰረት 1300 የሚሆኑት እንዲመጡ የተፈቀደ ሲሆን ወደፊት ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊጨምር የሚችል መሆኑን ተገልጿል። ባለፈው ወር በእስራዔል አገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸው ወደ እስራኤል እንዲመጡ በመጠየቅ ከፍተኛ ትዕየንተ ሕዝብ ማካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን የእስራዔል መንግስት ነገሩን ችላ በማለት ኢትዮጵያውያኑን የፈቃዱን ውሳኔ ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወሳል። ባለፉት ጥቂት ቀናት አንዳንድ የፓርላማ አባላት ባደረጉ ጥረትና እንዲሁም ተቃውሞውና አድማው የጋራ መንግስቱን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መሆኑ ስለገባው ገዥው ፓርቲ ሀሳቡን ቀይሮ ቤተእስራኤሎቹ ወደ እእስራኤል እንዲመጡ ፈቅዷል።

 በአስመራ ከተማ በግድ ታፍሰው በካሚዮን ተጭነው ወደ ጦር ማሰልጠኛ ሲወሰዱ የነበሩ ወጣቶች ከተሳፈሩባቸው መኪናዎች ዘለው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሻዕቢያ ወታደሮች በጥይት የተገደሉ መሆናቸው ታውቋል። የተገደሉትና እና ምን ያህል እንደሆኑ ለጊዜው ባይታወቅም ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም ካሚዮኖቹ የሚሄዱበትን መንገዶ በአውቶቡስ አማካይነት ለመዝጋት ሙከራ ያደረጉ የወጣቶቹ ዘመዶችና ጓደኞች በሙሉ በጥይት የተገደሉ መሆናቸው ተነግሯል። የሻዕቢያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ የሰጠው መግለጫ የለም። በሻዕቢያ ውስጥ የወታደራዊ አገልግሎት የጊዜ ወሰን የሌለው መሆኑ ሲታወቅ አብዛኛዎቹ እድሜ ልካቸውን ሲያገለግሉ የሚቆዩ መሆናቸውና የኑሮው ሁኔታቸውም በጣም አሰቃቂ እንደሆነ ይነገራል። ይህ አሰቃቂ የኑሮ ሁኔታና የሻዕቢያን አፈና ለማምለጥ በርካታ ወጣቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች እና ወደ አውሮፓ መሰደዳቸው በየጊዜው የተገለጸ መሆኑ ሲታወቅ የሻዕቢያ አገዛዝ ከፍተኛ አፈናና ጭፍጨፋ ከሚያካሄዱ የአለም አገሮች ውስጥ ዋነኛው ነው በማለት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ድምጻቸው በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

 የጅቡቲው አምባ ገነን መሪ በ87 በመቶ ምርጫውን አቸነፍኩ ብሎ ራሱን ለአራተኛ ጊዜ ተመራጭ ቢያደርግም ወደ 75 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ድምጽ እንዳልሰጠ ታዛቢዎች ገልጸዋል ። ከምርጫው በፊት ገሊህ በተቃዋሚዎች ላይ፤በጋዜጠኞች ላይ አፈና ከማካሄዱ ባሻገር የየመን ስደተኞችን መዝግቦ መራጭ ማድረጉም ተጋልጧል ። ገሌህ የሀገሩን ወደብና መሬት ለፈረንሳይ፤ለአሜሪካ፤ለቻይና፤ ለጀርመን ና ለጃፓንም የቸበቸበ በመሆኑ በህገ ወጥ ስልጣን መቆየቱን ሁሉም ይደግፋሉ ተብሏል ። ይህ ቢባልም ግን ገሌህን ሊገለብጡት የሚፈልጉና ፊታቸውን ያዞሩበትም ከፈረንሳይ ጀምሮ አሉ እየተባለ ነው ። ገሊህ በ87 ከ መቶ ብቻ አሸነፍኩ ማለቱ ቢያንስ እንደ ወያኔ ሀፍረተ ቢስ አይደለም ሊያሰኝለት ይችላል ተብሏል። በርሀብ ከተጠቃው ሕዝብ መካከል የእህል እርዳታ እያገኘ ያለው እጅግ በጣም ጥቂቱ መሆኑ ተነገረ

File Photo

File Photo

 በርሀብ ከተጠቃው ሕዝብ እስካሁን የእርዳታ እህል እያገኘ ያለው ከሰላሳ ከመቶ በታች እንደሆነ ይፋ ሆኗል፡፡ ወያኔ የእርዳታ አሰጣጡን ከፖለቲካ ታማኝነት ጋር በማያያዝ በርሀብ እየማቀቀ ባለው ሕዝብ ላይ የግፍ ግፍ እየፈጸመ መሆኑ ታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከሰጠው መግለጫ መረዳት የተቻለው እስካሁን በርሀብ ለተጎዱ ወገኖች እህልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ለማቅረብ ያስፈልጋል ተብሎ ከተገመተው 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘው 46 ከመቶ ብቻ የሚሆነው ሲሆን ይህም 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ገለጻ መሰረት መረዳት የተቻለው የእርዳታ አሰጣጡ ላይ መደረግ የማይገባው መዘበራረቅ እንዳለ አውስቷል፡፡ ለአንዳንድ ተረጂዎች ባቄላ ብቻ ሲታደል ለሌሎች ደግሞ ዘይት ብቻ እንደሚታደል በመጥቀስ ትዝብቱን ይፋ አድርጓል፡፡ አሁን በክምችት ያለው እህልና ዘይት ከሚያዚያ አጋማሽ በላይ መሻገር እንደማችል እየተነገገረ ባለበት ግማሽ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በ2.2 ቢሊዮን ብር ለመግዛት ፐሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት የጨረታ አሸናፊ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ከሃያ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ ወያኔ ስንዴ ለመሸመት ጨረታ አወዳድሮ እንደጨረሰ ያወራል፡፡ ሕዝቡ ግን በርሀብና በጠኔ እየተሰቃየ ነው፡፡ በተመሳሳይ ዜና ህጻናትን አድን (Save the Children) የተባለው መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት አርብ መጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ህጻናት አስጊ የሆነ የምግብ እጥረት ውስጥ እንዳሉ ገልጿል። የዘንድሮ ድርቅና ረሃብ በጣም ሰፊና 30 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርበትን አካባቢ ያዳረሰ መሆኑን የጠቀሰው የሕጻናቱ አድን ድርጅት ከዚህ ውስጥ ሢሶው ማለትም አስር ሚሊዮን የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን ገልጿል። ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ 14 ሺህ በከብት እርባታ የሚተዳደሩ አባወራዎች አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን በመጥቀስ የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ርብርብ ካላደረገ አስጊ ና አደገኛ ሁኔታ እንደሚፈጠር በማስጠንቀቅ በተለይ ህጽናት በምግብ እጦትና በውሃ ወለድ በሽታ እየተጠቁ መሆናችውን ገልጿል። የተለያዩ ድርጅቶች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም እልቂት ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ እንዳለ ቢነገርም የተፈለገውን ያህል ለጋሽና ረጅ እንዳልተገኘ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሞ ገበሬዎችን የማፈናቀሉ እቅድ አለመሰረዙ ታወቀ  በኦሮሞ አካባቢዎች አፈናና እስራቱ እስካሁን እንደቀጠለ ባለበት ወያኔ ከመሬታቸው ለሚፈናቀሉ ገበሬዎች ከአሁን በፊት ይከፍል ከነበረው በላይ ለመክፈል እንዳቀደና ቀድሞ ከእርሻቸው ለተፈናቀሉትም ተከፍሏቸው የነበረው በቂ ባለመሆኑ አሁን የማካካሻ ክፍያ እንደሚፈጽም በመገናኛ ብዙሀኑ እየለፈፈ ይገኛል፡፡ ወያኔ ቀደም ሲል የአዲስ አበባን የቆዳ ስፋት ወደ አጎራባች የኦሮሞ አካባቢዎች ለመለጠጥ አቅዶት የነበረው እቅድ ሥራ ላይ እንዳይውል በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ወጣቶችና ገበሬዎች በአደረጉት አመጽ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን የገለጸ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የወያኔን መልቲነትና አታላይነት የጠረጠረው የኦሮሞ ሕዝብ በትግሉ ወያኔን ቢያሸማቅቅም ወያኔ አድብቶ ሊከፋፍለው እንደሚችል በመጠርጠር በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ በኦሮሞ ባህል መሰረት የወያኔን ቀንበር መሸከም እንደሌለበት በኦሮሞ ሽማግሌዎች ቃል እንደ ተግባባ የሚያስረዱ ወገኖች ይህ የኦሮሞ ገበሬን የእድሜ ልክ ሀብቱን ሀገንዘብ እንዲለቅ የተሴረው ደባ የመረረ የህዝብ አመጽ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል ብለው ሊያወናብዱ የሚጥሩት ሁሉ የወያኔ ሎሌዎች ናቸው ተብለዋል ።

በአዲስ አበባ አሰቃቂ የመኪና አደጋ ደረሰ  የመኪና አደጋ እያደረሰ ያለው የሞትና የአካል ጉዳት ወያኔ እያደረሰ ካለው ግድያና ድብደባ እንደማይተናነስ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱ ያስረዳሉ፡፡ ሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4 ሰዓት አካባቢ ኮልፌ በተለምዶ አስራ ስምንት ማዞሪያ ተብሎ የሚጠራው አዳባባይ እጅግ ዘግናኝ የመኪና አደጋ ደረሰ፡፡ ከአስራ ሁለት በላይ ሰዎች እዛው አደጋው የተከሰተበት ስፍራ ህይወታቸው አልፏል፡፡ በአስፋልቱ ላይ በአደጋው የተቆራረጡ የሰው ልጆች አካላት ተበታትነው እዚህም እዚያም ይታዩ ነበር፡፡ ከአደጋው አስከፊነት የተነሳ በግጭቱ የተጨረማመቱ መኪናዎች ውስጥ የታፈኑ ሰዎች የአትርፉን የሲቃ ጩኸት እየጮኹ የየመኪናዎቹን ብረቶን አላቆና ፈልቅቆ ማውጣት ባለመቻሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሁሉ እምባቸውን እንደጎርፍ ሲያጎርፉ ታይተዋል፡፡ አደጋው የደረሰው ከላይ ከአጠና ተራ ወደ ታች ይወርድ የነበረ አሸዋ የጫነ ገልባጭ መኪና ነበር፡፡ የዚህ መኪና ሾፌር የከባድ መኪና የመንጃ ፍቅድ ካወጣ አንድ አመት እንኳን እንዳልደፈነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወያኔ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡን መረን ለቆታል፡፡ ማንም ሰው በአንድ ጊዜ የፈለገውን ደረጃ የመንጃ ፍቃድ ለማውጣት ይችላል፡፡

በዚህ መሰረት ይህ አደጋውን ያደረሰ ሰው ከዚህ ቀደም በአነስተኛ መኪናዎች ላይ ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው በአንድ ጊዜ የደረቅ ከባድ መኪና የመንጃ ፍቃድ እንዳወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አደጋው የደረሰው ሾፍሩ የመጀመሪያውን መኪና እንደገጨ መኪናውን አቀዝቅዞ ማቆም ሲቻለው በመደናገጡ ለመኪናው የነዳጅ ኃይል እየሰጠ ስድስት መኪናዎችን እንደ ትናንሽ ጣሳዎች ጭርምትምት አድርጓቸዋል፡፡ እዚህ አደጋው የደረሰበት አካባቢ በየቀኑ አደጋ እንደሚደርስ የአካባቢው ኗሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ለእደዚህ ያለው ተደጋጋሚ አደጋ በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚገባው ችግር የመንገዱ አሰራር እንደሆነ የመንገድ መሀንዲሶች አስተያየታቸውን ይቸራሉ፡፡ እነዚህ መሀንዲሶች እንደሚሉት አስራ ስምንት አደባባይ ከስርና በላይ ተላላፊ መንገድ መሰራት ይገባው እንደነበር ነው፡፡ ከጦር ኃይሎች እስከ ዊንጌት የሚዘልቀው የቀለበት መንገድ ሲሆን እዚህ አደባባይ ላይ ሲደርስ ግን እንደ ቅል አንገት የጠበበ በመሆኑ ለአደጋ መከሰት ዋነኛ ሰበብ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የወያኔ የመንገድ እድገት በጥናት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን እረጋ ሰራሽ ለመሆኑ የሚከሰቱት አደጋዎች ማስረጃ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ የሚጠበቀው የመሬት መንቀጥቀጥ ሲመጣ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ሲሚንቶና የህንጻ መሳሪያዎች የተገነቡ ሕንጻዎች የሚንኮታኩቱ መሆናቸው ግልጽ ሲሆን አደጋውንም ለመቋቋም ምንም ዝግጅትና በቂ አቅምም እንደሌለ የሚታወቅ ነው ተብሏል ።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጎርፍና የእሳት ቃጠሎ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ 

የዜጎችን ህይወትና ንብረት መከላከልና ማስጠበቅ ሲቻል በወያኔው የአየር ንብረት ትንበያ ተቋም ድክመት ከሰላሳ ሰዎች በላይ ህወታቸውን በጎርፍ አደጋ ማጣታቸው ሲታወቅ እስካሁን ይሙቱ ይኖሩ የማይታወቁም እንዳሉ መረዳት ተችሏል፡፡ ሰሞኑን የተከሰተው ከባድ ዝናብ ባደረሰው ጎርፍ በወልዲያ፣ በአፋር፣ በራያና ቆቦ፣ በጂጅጋ ከሃያ ሺ በላይ ሰዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል፡፡ በሌላ አንጻር ደግሞ በሀዲያ በሰደድ እሳት ከሦስት መቶ የመኖርያ ቤቶች በላይ በእሳት ወድመው ኗሪዎች መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡

ወያኔ በቫይበርና በተመሳሳይ አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ሊጥልና ቁጥጥር ሊያደርግ ነው ተባለ

 የወያኔ ቴሌኮሙኒኬሽን ዓለም አቀፍ የነፃ ስልክ መደወያና መቀበያ የሆነውን የቫይበር እንዲሁም የነፃ የአጭር መልክት ማስተላለፊያ የሆነውን የዋትስአፐና ተመሳሳይ አገልግሎቶች ላይ ገንዘብ ለማስከፈል የሚያስችለውን መሳሪያ ተከላ ማጠናቀቁ ተሰማ፡፡ ወያኔ ከዚህም በተጨማሪ ኢንሳ በተባለው የመረጃ መረብ ደህንነት የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ጠልፎ የማዳመጥና የመከታተል ስልትም እንደቀየሰ በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ የነፃ ስልኮችን ማስከፈል የሚያስችል ሰልትንና መሳሪያን ማግኘት የተቻለው ከቻይናው ዜድቲኢ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ግምታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ለኢንተር የድረ-ገጽ ማገናኛ የሆነው ሲዲ ኤም ኤ የተባለው መሣሪያ ከኋዌይ ኩባንያ ውጪ የሆኑ መሣሪያዎች እንዳያገነግሉ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ የሆበት ምክንያት በሁለት ሰበብ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዋነኛው ምክንያት ድረ-ገጾችን ለመሰለል መሆኑ የሚያነጋግር አለመሆኑ ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ከቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ገበያ በመክፈት የጉቦ ጥቅም ለማግበስበስ መሆኑ የሚያጠራጥር አለመሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳን ወያኔ የቫይበርና የዋትስ አብ አገልግሎቶችን አግዳለሉ፤ የአገልግሎት ዋጋ አስከፍላለሁ በማለት ይመኝ ይደንፋ እንጅ ተቋሞቹ ይህን ማድረግ ፈጽሞ አይችልም የሚል መግለጫ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል ።

የውጭ አገር ዜናዎች  ሚያዚያ 2 ቀን 2008 ዓም. መጠኑ 6.6 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በአፍጋኒስታንና በታጂክስታን ወሰን አካባቢ የተከዛሬ ሰተ ሲሆን ርዝራዡ በመላው ደቡብ ምዕራብ እስያ የተሰማ መሆኑ ታውቋል። በካቡል በኢስላማባድ በላሆር እና በደሊሂ ከተሞች ነዋሪዎች በፍርሃት ቤታቸውን ለቀው የወጡ መሆናችው ታውቋል። እስካሁን ድረስ ያስከተለውን ጉዳት ለማወቅ አልተቻለም። የዛሬ ሁለት አመት በተመሳሳይ ቦታ የተከሰተው የኃይል መጠኑ 7.5 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ የ300 ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱ ይታወሳል።  እንዲሁ ሚያዚያ 2 ቀን በህንድ በአንድ የሂንዱ ገዳም ውስጥ በተነሳ እሳት የሃይማኖት በዓል ለመሰብስብ በመጡት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አማኞች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከቀረበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 100 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውና ከ200 በላይ የሚሆኑት የቆሰሉ መሆናችው ተነግሯል።  ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተው የነበሩት ፕሬዚዳንት ዙማ በይፋ ሕዝቡን ይቅርታ ቢጠይቁም በዚህ ሳምንት ውጥረቱ እና ቀውሱ ቀጥሎ ሰንብቷል። ፕሬዚዳንቱ በስልጣን መባለግ ከኃላፊነት እንዲነሱ የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት እንዲወስን ተቃዋሚ ኃይሎች ያቀረቡት ሀሳብ ውድቅ የተደረገ ቢሆንም በተለያዩ ክፍሎች ተቃውሞ እየቀጠለ መሆኑ ተገልጿል። 16 ሺ አባላት ያሉት የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሠራዊ ማህበር ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ አዛዥ ለመሆን ብቃት እንደለሌላችው መወሰኑ የተነገረ ሲሆን ምንም እንኳ የመከላከያ አዛዡ ውሳኔያቸውን ቢቃወሙትም በወታደሩ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩ ታውቋል። የጸረ አፓርታይድ ትግል መሪና ከሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ጋር በሮበን ደሴት ታስረው የነበሩት እውቁ አህመድ ካታራዳ፣ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስቴር ትሬቨር አማኑኤል እና እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ታዋዊ ምሁራንና በርካታ የብዙሃን ማህበራት ሚስተር ዙማ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። የሃይማኖት አባቶቹ ባወጡት በሰጡት መግለጫ የፕሬዚዳንት ዙማ የሙስና ተግባር ግለሰቡን የሞራል የበላይነትን ያሳጣቸው ስለሆነ አገር ለመምራት ብቃት የላቸውም ብለዋል። በሚስተር ዙማ ላይ የሚካሄደው ተቃውሞ በእሳቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በወዳጆቻቸው ላይ ተጽእኖ ሳያመጣ አላለፈም። ባለፈው ሳምንት ሚስተር ዙማ የተፈጸመው ስህተት ሆን ተብሎ የተደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው ይቅርታ መጠየቃቸው የሚታወስ ሲሆን ልጃቸው በከፊል ባለቤት ከሆነበት ኩባንያ ከኃላፊነት ቦታዎች ራሱን ማግለሉን ማስታወቁና ከሚስተር ዙማ ጋር ቅርብ የሆነው ጉብታ የሚባለው የህንዱ ቤተሰብ አባላትም እንዲሁ ከኩባንያው ኃላፊነት ቦታዎች መልቀቃቸው ይፋ ተደርጓል።

 ከአልካይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውና አንሳሩ እየተባለ የሚጠራውን የጂሃዲስት ድርጅት ይመራ የነበረና በአሜሪካ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ሲፈለግ የቆየው ካሊድ አል ባርናዊ የሚባለው ግለሰብ በዚህ ሳምንት በናይጄሪያ ውስጥ የተያዘ መሆኑ ተነግሯል። ከአራት ዓመት በፊት አሜሪካ ግለሰቡን ዋና አሸባሪ ብሎ የሰየመ ሲሆን ግለሰቡን ለያዘ ወይም ለገደለ አምስት ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መዘጋጀቱን ገልጾ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ከቦኮ ሃራም የተገነጠለውን ድርጅት አንሳሩን ይመራ የነበረው ካሊድ ባርናዊ በተለያዩ ጊዜያት በርከት ያሉ የውጭ አገር ሰዎችን በመግደል የሚጠረጠር ሲሆን ከአራት ዓመት በፊት በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ባለው ዋና እስር ቤት ላይ የተደረገውን ጥቃት አስተባበሮ በርካታ እስረኞች ያስፈታ መሆኑ ይነገርለታል።

 በተያያዘ ዜና የናይጄሪያ ወታደራዊ ተቋም ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ባካሄደው ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃ 11 ሺ 595 ሰዎችን ከቡድኑ ጥቃትና ቁጥጥር ነጻ ያወጣ መሆኑና በርካታ የቦኮሃራም አባላትን የያዘ መሆኑን ገልጾ የተያዙትንም ሆነ በነጻ እጃቸውን የሚሰጡትን የቦኮሃራም ታጣቂዎች ወደሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ የማስተማሪያና የማሰልጠኛ ካምፖች ያቋቋመ መሆኑን በዚህ ሳምንት በይፋ መግለጫ ሰጥቷል። ግለሰቦች ራሳቸውን ችለው በህብረተስብ ውስጥ ድርሻቸውን እንዲወጡ በካምፑ ውስጥ ልዩ ልዩ የሞያ ትምህርቶች የሚሰ መሆናቸውም ተገልጿል። እስካሁን ድረስ እጃውን ሰጥተው ወደ ካምፑ የገቡ የቦኮሃራም ታጣቂዎች ምን ያህል እንደሆኑ ባይታወቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቡድኑ ወደተሸሸገባቸው ቦታዎች ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዳይደርሱ መንግዶች በመዘጋታቸው በረሃብ የተጠቁ በርካታ የቦኮሃራም አባላት እጃቸውን የሰጡ መሆናችው ተዘግቧል። የናይጄሪያ ወታደራዊ ተቋም ቦኮ ሃራምን ለመደምሰስ ጫካውን ሁሉ ለማጠርና ለመቆጣጠር አቅም ባይኖረውም የምግብና መሰል ቁሳቁሶች የሚጓጓዙበትን መስመር መዝጋቱ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል ተብሏል።

 በዚህ ሳምንት ሞሳክ ፎንሴካ ከተባለ የፓናማ የሕግ ስራ ኩባንያ በድብቁ የወጡ 11.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ልዩ ልዩ ሰነዶች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች ታክስ ባለመክፈልም ሆነ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘቦችን በማስተላለፍ በኩል የሰሯቸውን ወንጀሎች ያጋለጡ መሆናቸው ተገለጸ። ምንጫቸው ካልታወቀ በአንድ የጀርመን የጋዜጣ ተቋም መጀመሪያ ተሰራጭቶ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተመራማሪ ጋዜጠኞች ተሳትፈውበት እየተመረመረ ባለውና በርካታዎችን የሚያጋልጠው ዘገባ በወንጀሉ ውስጥ 140 የሚሆኑ ታላላቅ የፖሊቲካ ሰዎች 12 የወቅቱና የቀደሞ የአገር መሪዎችን ያጋልጣል። ከእነዚህም ውስጥ የአሁኑ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመዶች፤ የራሺያው የሚስተር ፑቲን የቅርብ ረዳቶች፤ የአይሳላንዱ ጠቃላይ ሚኒስትር፤ ሟቹ የእንግሊዙ መሪ የሚስተር ካምሪን አባት፤ የዩክሬኑ መሪ ፖሮሼንኮ፤ የሳኡዲ አረቢያ ንጉስ ተጠቅሰዋል። ከአፍሪካ መሪዎችና ተዋቂ ግለሰቦች መካከል ደግሞ ክላይቭ ኩሉቡሴ ዙማ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት የወንድም ልጅ፤ ካልፓና ራዋል የኬኒያ ምክትል የፍርድ ሚኒስትር፤ ጆን አድዶ ኩፎር የቀድም የጋና ፕሬዚዳንት ልጅ፤ ማማዲ ቱሬ የቀድሞ የጊኒ ፕሬዚዳንት ባለቤት፣ ሙኒር ማጃዲ የሞሮኮ ንጉስ የግል ጸሐፊ፣ ጆዜ ቫስኮንሴሎስ የአንጎላ የነዳጅ ሚኒስትር፤ ኢያን ከርቡ የቦትስዋና የይግባኝ ፍርድ ቤት ኃላፊ፤ ጃኔት ካቢላ የኮንጎው ፕሬዚዳንት ካቢላ እህት፤ ኮጆ አናን የቀደሞ የተመድ ዋና ጸሐፊ የኮፊ አናን ልጅ ይገኙባቸዋል። ከዚህ በተረፈ ሰነዶቹ ለአርባ አመታት ያክል በኩባንያው የተስተናገዱ 214 ሺ የውጭ ኩባንያዎችን የሚያጋልጡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሰሜን ኮሪያ የሶሪያ ኩባንያዎች፤ በእንግሊዙ HSBC በስዊዘርላንዱ Credit swiss በፈረንሳዩ ሶስይቴ ጄኔራል የተቋቋሙ ኩባንያዎች ከሞሳክ ፎንሴካ ጋር መስራታቸው ተጋልጧል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ለዚህ ዓይነት መሰረተ ቢስ ክስ የምንለው የለም ሲሉ የክሪምሊን ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ ደግሞ ሰነዱን አወጡት የተባሉት ብዙዎቹ ጋዜጠኞች የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሲአይ ኤ እና የልዩ አገግሎት ሰራተኞች መሆናቸውን ገልጾ ይህ በሩሲያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የተደረገ የአሜሪካ ሴራ ነው ብሎታል። የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርም ስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ግፊት የተደረገባቸው ሲሆን ፓርላማው ፈርሶ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ እንዲያፈርሱ ፕሬዚዳንቱን ጠይቀዋል ተብሏል። አውስትራሊያ ፈረንሳይና ኒዘርላንድ ጉዳዩን እንመረምራለን ብለዋል።

 በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተሰማርተው የነበሩና ህጻናትን አስገድደው በመድፈር የተከሰሱ ሶስት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ወታደሮች እስር ቤት እንዳሉ በአንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ላይ የቀረቡ መሆናቸው ተነገረ። ሁለቱ ህጻናትን አስገደደው ደፍረዋል የሚል ክስ የቀረባባቸው ሲሆን አንደኛው ለመድፈር ሙከራ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታል። ሶስቱም የቀረበባቸውን ክስ ሀሰት ነው በማለት ክደዋል። በማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ በተሰማሩ የተመድ እና የፈረንሳይ ወታደሮች ተፈጽማዋል የተባሉና ከተበደሉ ዜጎች አቤቱታ የቀረበባቸው ህጻናትን ጨምሮ ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች ከ100 በላይ የደረሱ ሲሆን ከእነዚህ ተከሳሾች ውስጥ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ለፍርድ ሲቀርቡ ይህኛው እስካሁን የመጀመሪያ መሆኑ ነው። የፈረንሳይ ወታደሮች በአዲስ መልክ የቀረበባቸውን ክስ እየመረመሩ መሆናቸው ኤኤፍ ፒ የተባለው የዜና ወኪል ቢያስታውቅም ከዚህ በፊት ለቀረቡት የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ይታወቃል። በሌላ በኩል በኮንጎ ዴሞክራቲክ ተሰማርተው የነበሩና አስገድዶ በመድፈር አቤቱታ የቀረበባቸው የታንዛኒያ ወታደሮች ልጆች ያስወለዱ መሆናቸውንም ተጎጅዎች ክስ አቅርበዋል። ክስ የቀረበባችው አስራ አንድ ወታደሮች ሲሆኑ 4 ቱ በቅርቡ የተሰማሩ የተቀሩት ሰባቱ ደግሞ ቀደሞ ባለው ስምሪት ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል። ባለፈው ዓመት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 69 የሚሆኑ ሰዎች በደል የተፈጸማብቸው መሆኑን ሲያመለክቱ ወንጀሉን የፈጸሙት ከ10 አገሮች የተውጣጡ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት መሆናቸው ተነግሯል። በዚህ ወር ውስጥ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አቤቱታ የቀረባባቸው የሰላም አስከባሪ ኃይል ቡድኖች ሁሉ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወሳል። አንድ ገለልተኛ የሆነ የጥናት ቡድን የተመድ ኃላፊዎች ጉዳዩን በሚገባ አለመከታተላቸውና ለችግሩ መፍተሄ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ድክመት ያሳዩ መሆናቸውን መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወርም በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተመድ ቋሚ መልክተኛ የሆኑት ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረገ መሆኑ ይታወሳል።

 በተመድ አስተባባሪነት የተመሰረተው የሊቢያ የአንድነት መንግስት ተወካዮች ቀደም ባለው ሳምንት በትሪፖሊ የባህር ኃይል ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት መንግስታዊ ስራን መጀመሩን ተከትሎ የትሪፖሊ ከተማን ማዕከል አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ራሱን መንግስት ነኝ ብሎ ሲጠራ የቆየው አካል በአገሪቱ ተጨማሪ ደም መፋሰስን ለማስቀረት ስልጣን የለቀቀ መሆኑን የፍርድ ሚኒስትሩ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቆ ነበር። መግለጫው በተሰጠ በጥቂት ቀና ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር የተባሉት ካሊፋ ጋውሊ መግለጫውን ተቃውመው ከአንድነት መንግስቱ ጋር መተባበር የማይችል መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ነኝ ባለው አካል ውስጥ ምን ድጋፍ እንዳላቸው ባይታወቅም ግልጽ የሆነ ክፍፍል መኖሩ ግን ተረጋግጧል። ይሁን እንጅ የአንድነት መንግስቱ ከአንዳንድ ክፍሎች ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ ይነገራል። በተያያዘ ዜና በሊቢያ በፌስ ቡክ እና በሌሎች የማህበረሰባዊ መገናናዎች አማካይነት በድብቅ የሚካሄድ የመሳሪያ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ እየደራ መምጣቱን በዚህ ሳምንት የተሰራጨ አንድ ጥናታዊ ዘገባ አመለከተ። ለአርባ ዓመት ሊቢያን ሲገዛ የቆየው የኮሎኔል ጋዳፊ አገዛዝ በየጊዜው ያከማቸው መሳሪያ አገዛዙ ሲወድቅ በተለያዩ አማጽያን እጅ የገባው መሳሪያ ዛሬ በጥቁር ገበያ በሰፊው እየተሸጠ መሆኑን ጥናቱ ይዘረዝራል። በፌስ ቡክ፣ በኢንስታግራም፣ በዋትስ አፕ፣ እና በቴሌግራም አማካይነት በብዛት እየተሸጡ ያሉት መሳሪያዎች እንደሽጉጥና ካላሽንኮቭ የመሳሰሉት የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ሲሆኑ ለሽብርተኞች መገልገያ የሆኑ በትከሻ ላይ ሆነው የሚተኩሱ ጸረ አውሮፕላንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችም የሚሸጡ መሆናቸውም ተጠቁሟል። አንድ ካላሽንኮፍ መሳሪያ እስከ 1800 ዶላር ሲያወጣ በተለይ የመጓጓዣ አውሮፕላንን ሊመታ የሚችል ጸረ አውሮፕላን መሳሪያ ደግሞ እስከ 62 ሺ የአሜሪካን ዶላር እንደሚሸጥ ዘገባው ይገልጻል። የመሳሪያ ሽያጮቹ የሚከናውኑት በአብዛኛው እንደ ትሪፖሊ፣ ቤንጋዚ እና ሳብራታ በመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞች ሲሆን ንግዱ የሚካሄደው ወጣቶች በሆኑ የተለያዩ የሚሊሺያ አባላት መካከል መሆኑም ተድርሶበታል። የፌስ ቡክ ቃል አቀባይ በሰጠው መግለጫ ይህን የመሰለ ንግድ በፌስ ቡክ አማካይነት መካሄዱ ወንጀል ገልጾ መረጃውን እየፌስ ቡክ አገግሎቱን እንዘጋዋለን ብሏል። የአውሮፓ ባለስልጣናትም ጉዳዩ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፤ በተጨማሪም በሊቢያ የአይሲስ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም አዛዥ ተናገሩ። አዛዡ ላለፉት 12 እስከ 18 ወራት ባሉት ጊዚያት ወደሊቢያ የገቡት የአይሲስ አባላት ቁጥር ከ4 ሺ ወደ 6 ሺ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው አሸባሪዎቹ በብዛት ሊገቡ የቻሉት በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና የጸጥታ አለመረጋጋት ተጠቅመው ነው ብለዋል።

 ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ከሳልቫ ኪር ጋር ከጥቂት ወራት በፊት እርቅ የተፈራረሙት ሪክ ማቻር በሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓም ጁባ የሚገቡ መሆናቸውንና በዚያም ከሳልቫ ኬር ጋር በመሆን የአንድነነቱን የሽግግር መንግስት እንደሚያቋቁሙ ተገልጿል። ባሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ቦታዎች የሚደረጉት ጦርነቶች ሙሉ በሙሉ ያልቆሙ በመሆናቸው ስምምነት የተደረገበት የአንድነት መንግስት ስራ አለመጀመሩ ብዙዎችን ሲያሳስብ ቆይቷል። በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን መድኃኒት እና ሌሎች የህክምና አገልግሎት መሳሪያዎች ከፍተኛ እጥረት በመፈጠሩ ርዳታ ፈላጊዎችን ለመርዳት አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ድንበር የለሽ ሃኪሞች የተባለው ድርጅት በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ ገልጿል። መግለጫው የእርዳታ ድርጅቶችና ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋሞች ይህን ከፍተኛ የሆነ እጥረት ለማሟላት ባለመቻላቸው የብዙ ሰዎች ህይወት አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ ችሏል ብሏል። የአለም የምግብ ፕሮግራም እና የዓለም አቀፉ የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ማክሰኞ መጋቢት በሰጡት መግለጫ በደቡብ ሱዳን የእርዳታ እህል እጥረት በመኖሩ ከፍተኛ ረሃብ እየተከሰተ መሆኑን የገለጹ መሆናቸው ይታወቃል።

 የዳርፉርን ግዛት በአምስት የአስተዳድር ክልሎች ከፋፍሎ ለማስተዳደር ከበሽር መንግስት የቀረበውን ሀሳብ ህዝብ በውሳኔ ሕዝብ እንዲያጸድቀው ከሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀና ዳርፉር ውስጥ ሕዝቡ ድምጽ እንዲሰጥ ይደረጋል ተብሏል። በዳርፉር የሚገኙ አማጽያን ኃይሎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ ባለ አካባቢ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የድምጽ አሰጣጡ ተግባር ስለማይፈጸም ሕዝቡ በምርጫው እንዳይሳተፍ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ። የአስተዳድሩ በአምስት ክልሎች መከፋፈል በተገቢው መንገድ ለማስተዳደርም ሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማግኘት አስፈላጊ መሆኑ የበሽር መንግስት እየገለጸ ሲሆን የአስተዳድር ክልሉን ክሶስት ወደ አምስት ከፍ ያደረገው የበሽብር አገዛዝ ዳርፉር ላይ ያለው ቁጥጥር ከፍ እንዲል ለማድረገ ነው ይላሉ”” በተመሳሳይ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ በሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በዚህ ዓመት ወደ 400 000 (አራት መቶ ሺ) የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጿል። ድርቁ የተከሰተባችው አካባቢዎች ምስራቅ ሱዳን በምስራቅ ዳርፉር እና በመካከለኛው ኮርዶፋን ግዛት ሲሆን በድርቁ የተጎዳው በጠቅላላው 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ የተለያየ እርዳታ ሲደርግለት መቆየቱ ተነገርዋል። የምግብ እርዳታው በዚህ ዓመት በጠቅላላው 12.5 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑ ቃል አቀባዩ ገልጾ በጦርነት የተፈናቀሉትን ከመርዳቱ ጋር ተዳምሮ የበጀት ችግር ሊገጥም እንደሚችል ጠቁሟል።

 በዚህ ዓመት ህዳር ወር ውስጥ በፓሪስ ከተማ በደረሰውና የብዙ ሰው ህይወት ባጠፋው የቦምብ ጥቃት ቀንደኛ ተሳታፊ የነበረውና እስካሁን ሲፈለግ የነበረው ሙሀመድ አብሪኒ ብራስልስ ውስጥ በቤልጀየም ፖሊሶች ተይዟል ባለፈው ወር በብራስልስ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው ጥቃት ላይ ተሳትፎ ያመለጠው ሶስተኛው ግለስብ ይኸው ሙሀመድ አብሪኒ መሆኑንና አለመሆኑንም ፖሊሶች ምርመራ እያካሄዱ ነው ተብሏል። የፖሲስ ቃል አቀባይ አብሪኒ ከሌሎች ስማቸው ያልተገለጸ ሁለት ሰዎች ጋር የተያዘ መሆኑን አረጋግጠዋል። የአብሪኒ የጣት አሻራ በብራስልስ ከተማ በሁለት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እና እንዲሁም የፓሪሱን ሽብር ለማካሄድ አጥፍቶ ጠፊዎቹ የተጠቀሙበት መኪና ውስት የተገኘ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም በብራስልስ ከተማ በተካሄዱትና ለስላሳ ሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት በሆኑት የቦምብ አደጋዎች ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት ኦሳማ ክራየም የተባለ የስዊድን ዜግነት ያለው ግለሰብ እና ሌሎች ስማቸው ያልተገለጠ ሶስት ሰዎች መጋቢት 30 ቀን በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውም ተነግሯል። ኦሳማ ክራየም በብራሰልስ ማየልቤክ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ቦምቡን በማፈንዳት ራሱን የገደለው የካሊድ ባክራዊ ተባባሪ የነበረ እና ቦምቡ የፈነዳበትን የስፖርት ቦርሳ ከገበያ ቦታ ገዝቶ የሰጠ ነው ተብሏል።

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: