The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ፍሌክስ ሆርን ‹‹ በኢትዮጵያ የታፈነው ድምጽ ››

ፈሌክስ

(ሳተናው) ከህዳር ወር ጀምሮ የመንግስት ወታደሮች ከኢትዮጵያ ክልሎች ትልቁ በሆነው የኦሮሚያ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩትን የመንግስት ተቃዋሚዎችን በመግደል ሺህዎችን አስረዋል፡፡  ከ1997ቱ አገር አቀፍ ምርጫ ወዲህ በአገሪቱ የታየ ትልቁ የፖለቲካ ቀውስ ቢሆንም አለም አቀፍ ሚዲያዎች የተዘገበው በጣም ውስን በሆነ ደረጃ ነው፡፡ተቃውሞው አምስተኛ ወሩን በደፈነበት በዚህ ወቅት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ መረጃዎች ታፍነዋል፡፡

በታህሳስ ወር ታስሮ የነበረ መምህር ‹‹በኦሮሚያ ስለተፈጸመው ነገር ዓለም ለወራት ወይም ለአመታት ወይም እስከወዲያኛው ላይሰማ ይችላል፡፡እኛን ለማናገር የመጣ አንድ ሰው የለም እኛም የእኛን ታሪክ ሊያዳምጠን የሚገባውን አካል እንዴት ማግኘት እንደምንችል አናውቅም››በማለት ነግሮኛል፡፡

የችግሩ አካል መንግስት በዜና ዘገባ፣በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚደረጉ ክትትሎችንና መረጃዎችን በማስተላለፍ ላይ የጣላቸው አፋኝ ገደቦች ናቸው፡፡ገደቦቹ በዋናነት ካለፈው ወር ጀምሮ ሁኔታዎቹን እያባባሱት ይገኛሉ፡፡የተወሰኑ የማህበራዊ ድረ ገጾች ተዘግተዋል፣በመጋቢት ወር ሁለት የውጪ አገራት ጋዜጠኞች ስለተቃውሞው ለመዘገብ በወጡበት ታስረው ነበር፡፡አንድ የውጪ አገር ዲፕሎማት ‹‹ምን እየተካሄደ እንደሆነ የምናውቅበት መንገድ የለም ፡፡የምናገኘው በጣም ትንሽ አስተማማኝ መረጃ ብቻ ነው፡፡በአጠቃላይ ነገሩ ጨለማ ውጦታል››በማለት ነግሮኛል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሂዩማን ራይትስ ዋች 100 ተቃዋሚዎችን አነጋግሯል፡፡ያናገርናቸው ሰዎች የጸጥታ ሰራተኞች በተቃውሞ አድራጊዎቹ ላይ መተኮሳቸውን፣የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ሳይቀር መታሰሩንና የኦሮሞ ተማሪዎች በታሰሩባቸው ቦታዎች ቶርቸር እንደሚፈጸምባቸው ነግረውናል፡፡የኢትዮጵያ ሚዲያ ግን ይህንን ታሪክ አይነግረንም፡፡ይህ ግን የእነርሱ ችግር አይደለም፡፡የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ከመመርመር፣ወህኒ ከመውረድና  ወይም ከመሰደድ አንዱን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአህጉሪቱ ግምባር ቀደሟ ናት፡፡በ2006 ከ30 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ ስድስት የግል የህትመት ውጤቶች እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡መንግስት አታሚዎችን፣አከፋፋዩችንና ምንጮችን ያስፈራራል ያጉላላል፡፡

የውጪ ጋዜጠኞችም ችግሮችን ይጋፈጣሉ ፡፡የተወሰኑት ወደ ኢትዮጵያ መሄድን አይፈልጉም ፡፡ምክንያቱም በእነርሱ፣በአስተርጓሚያቸውና በምንጮቻቸው ላይ የሚደርስን ችግር ያውቁታል፡፡ጋዜጠኞቹ ይህንን ተጋፍጠው ተቃውሞ ወደሚደረግባቸው አካባቢዎች ቢሄዱ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የመንግስትን ፖሊሲዎች በመተቸት ለመናገር አይደፍሩም፡፡ ለጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሰዎች ከቃለ ምልልሱ በኋላ የሚታሰሩባቸው አጋጣሚዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡

በአሜሪካን አገር የሚገኘው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ቴሌቭዥን ክፍተቱን በመሙላት ረገድ እገዛ እያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ የሚገኙ የኦሮሞ ተማሪዎች በሌሎች የኦሮሚያ ቦታዎች እየተከናወነ የሚገኘውን ተቃውሞ ለማወቅ የቻሉት በኦሜን አማካኝነት መሆኑን ነግረውኛል፡፡ነገር ግን ኦሜን በ2006 ስርጭቱን ከጀመረ በኋላ ለ15 ጊዜያት ያህል ስርጭቱን ታፍኖበታል፡፡እንደ ዶቼቨሌና የአሜሪካ ድምጽ ራዲዩ የመሳሰሉት የራዲዩ ስርጭቶችም ለአመታት ስርጭታቸው በአገር ውስጥ እንዳይደመጥ ሲታፈንባቸው ቆይቷል፡፡

ኦሜን ለአፈና የማይመች ሳታላይትን በመጠቀም ስርጭቱን በድጋሚ በታህሳስ ወር ሲጀምርም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በየቤቱ እየዞሩ የሳታላይት መቀበያ ዲሾችን ነቃቅለው ወስደዋል፡፡ መንግስት በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከሳታላይቱ ባለቤቶች ጋር በመነጋገር ኦሜንን ከሳታላይታቸው እንዲያወርዱት በማስደረጉ ላለፉት ሁለት ወራት ኦሜንን ማግኘት አልተቻለም፡፡

ማህበራዊ ድረ ገጾች በተወሰነ ደረጃ ክፍተቱን በመሙላት አስተዋእጾ አበርክተዋል፡፡ተጎዶ ተማሮዎችን ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎችን በተለይ በተቃውሞ የመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ በፌስ ቡክ እንዲለጠፉ ተደርገዋል፡፡ነገር ግን በተወሰኑ ቦታዎች ኃላፊዎች በስልካቸው ተቃውሞዎችን የሚቀርጹ ሰዎችን ትኩረታቸው አድርገዋል፡፡በኦሮሚያ በተለያዩ ጊዜያት ባለፈው ወር ብቻ ሶሻል ሚዲዎችና ዶክመንቶችን ማስተላለፍ የሚቻልባቸው  እንደ ፌስ ቡክ፣ትዊተርና ድሮፕቦክስ ያሉት አፕሊኬሽኖች ተዘግተዋል፡፡ዌብሳይቶችን መዝጋት ለመጨረሻ ጊዜ የተመዘገበው በ2005 ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከ37 የሚበልጡ በአብዛኛው በውጪ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚሰራጩ ዌብሳይቶች ተዘግተዋል፡፡

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምን እየተካሄደ እንደሆነ እንዳይዘግቡተመሳሳይ እገዳዎች ተጥለውባቸዋል፡፡በ2001 የወጣው የማህበራትና የመያዶች አዋጅ መንግስታዊ ያልሆኑ አገር በቀል ድርጅቶችን በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በመከልከሉም መረጃዎችን ማግኘት ዝግ ሆኗል፡፡ነጻው የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በመጋቢት ወር  ሪፖርቱን በተቃውሞውና መንግስት በወሰዳቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ማውጣቱ አዲስ አየር እንደመሳብ ተደርጎ ቢቆጠርም ካውንስሉ ሪፖርቱን ያወጣው ትልቅ አደጋን በራሱ ደቅኖ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ 100 ሚልዩን ህዝብ ባላትና በህዝብ ብዛቷም ከአፍሪካ ሁለተኛ መሆኗ በሚነገርላት ኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበሩ ሪፖርት መውጣት ለአገሪቱ ፖለቲካ ትልቅ ምልክትና ለመንግስት ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አፈና አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

መንግስት ምናልባት ከኦሮሚያ የሚወጣን መረጃ በመቆጣጠር የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ጫናና ትኩረት እንደሚወስነው ሊያምን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያን ልማት በመደገፍ ላይ የሚገኙ አገራትም ዝምታን ሊመርጡና ልጆችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግድያዎች ውግዘቶችን ሊያመልጡ ይችሉም ይሆናል፡፡

የመንግስት ጨካኝ እርምጃና የሚጠቀመው ታክቲክ መረጃዎችን ወደ ውጪ ለማውጣት እንዳይቻል ትልቅ ግድግዳ ይፈጥር ይሆናል፡፡ነገር ግን ተቃውሞውን ሊያረግበው የሚችለው የጅምላ እስራቱንና ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃውን  ከመውሰድ መቆጠብ ነው፡፡

መንግስት በአጋሮቹና በደጋፊዎቹ እገዛ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ገለልተኛ ቡድን እንዲመረምረው በመፍቀድ ጉዳት የደረሰባቸው ፍትህ እንዲያገኙና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ኢትዮጵያን ሐሳብን በመግለጽ ነጻነት ረገድ ከአፍሪካ አስቸጋሪዋ ያደረጋትን አዋጅና የደህንነት መስሪያ ቤቱን አሰራር ለመቀየር  ቁርጠኛ መሆን ይገበዋል፡፡

በኦሮሚያ የተፈጠረው ነገር በኢትዮጵያ መረጋጋትና የኢኮኖሚው እድገት ላይ የራሱ የሆነ የረዥም ጊዜያት ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ኢትዮጵያዊያንና ዓለምም ምን እንደተፈጠረ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

*ፍሌክስ ሆርን የሂዮማን ራይትስ ዋች ሪሰርቸር ናቸው ጽሁፋቸው ለአንባቢ በሚስማማ መልኩ በሳተናው ተተርጉሟል፡

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: