The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

“አቶ መለስ በታሪክ ሊጠየቁበት የሚችለው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረጋቸው ነው” ዶክተር ፍሰሃ አሰፋው

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ የአገሪቱን ፖሊሲ አውጭዎችና ህግ አስፈጻሚዎችን በድፍረት ከመተቸትም ሆነ መልካም ጎኖችን ከማበረታታት ታቅበው ይታያሉ። ቁጥራቸው በዛ ያሉ አይሁን እንጂ በገዥው ፓርቲ ጉያም ሆነ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ምሁራንም ምሁራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ እናያለን። ከተቃውሞውም ሆነ ከገዥው ጉያ ውጭ ሆነው ወቅታዊ ጉዳዮችን በአንክሮ እየተከታተሉ ሀሳባቸውን ለመገናኛ ብዙሃን የሚሰጡ ምሁራን ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ በጣም አነስተኛ ይሁን እንጂ አልጠፉም። ሀሳባቸውን በነጻነት ከሚሰጡ ምሁራን መካከል የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እና የስነ ምድር ምሁሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ይገኙበታል። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በቀድሞው መንግስት ተቋቁሞ በነበረው የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትና በቅርቡ የኢንስቲትዩቱን የጥናት ውጤት በመጽሃፍ መልክ አዘጋጅተው ለንባብ ያበቁት የስነሰብ ምሁሩ ዶክተር ፍሰሃ አስፋው ሀሳባቸውን በነጻነት ከሚሰጡ ምሁራን ጎራ ተቀላቅለዋል።

ለአምስት ዓመታት በአሜሪካን አገር አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አስተማሪ ሆነው ያገለገሉትና ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ወደ አገራቸው የተመለሱት ዶክተር ፍሰሃ አስፋው በወቅታዊ ጉዳዮች እና በተለያዩ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገዋል። ከተወያየንባቸው ፍሬነገሮች መካከል የኢትዮጵያን ወደብ አልባነት ፖለቲካዊ አንድምታዎች፣ የብሔረሰቦችን የማካለል ጽንሰሃሳቦች፣ ወቅታዊ የማንነት ጥያቄዎች ላይ ያላቸውን አረዳድ፣ ሶማሌ ጅቡቲና አፋር ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ስትራቴጂክ ግቦች እንዴት እንደሚቃኟቸው ተናግረዋል፡፡ ቃለምልልሱን ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አቅርበነዋል፡፡

ሰንደቅ:- የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና የአገሪቱን ሁኔታ እንዴት ያዩታል? 

ዶክተር:- ፍሰሃ ይህንን ጥያቄ የምመልስልህ ከፖለቲከኞች ወገን ሆኜ ሳይሆን ከፖለቲካ ምሁራን ወገን ሆኜ ነው። የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ትንሽ አስደንጋጭ ሆኖ ነው የሚታየኝ። አስደንጋጭ ነው የምልህ በየአካባቢው ግርግር ስለተፈጠረ ሳይሆን ግርግሩ የተፈጠረው በወጣቶች በመሆኑ ነው። እነዚህ ወጣቶች ደግሞ ዝም ብለው ከመንገድ ላይ የተሰባሰቡ ሳይሆን በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ናቸው። ከልምዴ ተነስቼ የምነግርህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በወጣቶች እንቅስቃሴ ነው። ዘውዱን አስወግዶ ደርጉን ያመጣውም ሆነ ደርጉን አስወግዶ ኢህአዴግን ያመጣው የወጣቶች እንቅስቃሴ ነው። ስለዚህ የወጣቱ እንቅስቃሴ መንግስት በሚሰጠው መልስ ሳይሆን በሰከነ መልክ በረጋ አመለካከት ሃቀኛ በሆነና ከልብ በመነጨ ውይይት ችግሩ ምን እንደሆነ አውቆ እና ተረድቶ መፍትሔ ካልተፈለገለት በስተቀር እያደር አንድ ደረጃ ላይ ይደርስና ውጤቱ የከፋ ይሆናል።

ስለዚህ መንግስት ከራሱ ጋር ሳይሆን ከሁሉም ጋር ውይይት አድርጎ ወደ መፍትሔው መሄድ አለበት ብዬ ነው የማምነው። ይህ ካልሆነ ግን የወደፊቱ ፖለቲካ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ግልጽ ነው። ምክንያቱም ዛሬ የተቀየሰውም ሆነ እንቅስቃሴ የተጀመረው በብሔረሰብ ነው። ይህ የብሔረሰብ ግጭት ውሎ አድሮ ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ጋር ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋል። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወደቀች ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ስንል ብዙ ብሔረሰቦች ተሰባስበው ዳር ድንበሯን አስጠብቀው ያኖሯርት አንዲት አገር ነች። እነዚያ ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው ግጭት ከፈጠሩ ኢትዮጵያ የምትላት አገር ላትኖር ትችላለች። በበጎ መንፈስ ውይይት ከተደረገበት እና እርስ በእርስ ምክክር ከተካሄደበት በወጣቱ የተነሳውን ንቅናቄ ወደ ፊት ለኢትዮጵያ እድገት እና ልማት እንዲውል በማድረግ አገራችንን ወደ ቀድሞ ገናናነት ይመልሳታል ብዬ በእርግጠኝነት እነግርሃለሁ።

ሰንደቅ:- የወጣቶች ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጤቱ ገዥዎችን በሌላ ገዥ ሲተካ እንጂ መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ በማምጣት አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲያሸጋግራት አልታየም። አሁን የተነሳው የወጣቶች እንቅስቃሴስ እንዳለፉት ዘመናት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ አገሪቱን ዋጋ እንደማያስከፍላት በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

ዶክተር:- ፍሰሃ ያነሳኸው ትክክል ነው። ነገር ግን የ1960ዎቹ የነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ በንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነበር። ማኦ እንዲህ ብሏል፣ ሌኒን እንዲህ ብሏል እና ማርክስ እንዲህ ብሏል በማለት ነበር የሚንቀሳቀሰው። ሌላው ቀርቶ ብሔረሰብ የሚለውን ቋንቋ እንኳ ከስታሊን ወርሰን ያመጣነው ነው። ያን ጊዜ የነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ “ይህ መንግስት ወድቆ ለውጥ ይምጣ” የሚል እንጂ ቁጭ ብሎ ከመንግስት ለውጥ በኋላስ በሚለው ነጥብ ላይ ውይይት አልነበረም።

እኔ ከምከታተለው ተነስቼ ያሁኑን እንቅስቃሴ ካለፈው ዘመን ለየት የሚያደርገው ነጥብ ሆኖ ያገኘሁት “ለውጥ ይምጣ ብቻ ሳይሆን ለውጡ ከመጣ በኋላም በዚህ መስመር መሄድ አለበት” የሚል ነጥብ የተጨመረበት ነው። ስለዚህ “ወጣት ነው” ብለን ያለፈውን ስርዓት በማየት ብቻ ወጣቱ የሚያመጣው ለውጥ አገሪቱን ወደ አደጋ ይጥላታል የሚለውን ሃሳብ እኔ አልጋራውም። ለምን መሰለህ የማልጋራው? እነዚህ ወጣቶች የሚንቀሳቀሱት ብቻቸውን አይደለም። ምሁሩም ተቀላቅሎበታል። ስለዚህ የምሁሩንም ሀሳብ ይሰማሉ።

ለምሳሌ እኔ ያየሁትን አንድ ሃሳብ ልንገርህ። “ይህ መንግስት በህገ መንግስት የአስተዳደር መብትን ሰጥቷል። በተጨባጭ ሲታይ ግን መብታችን አልተከበረም” የሚል ነው አንዱ እንቅስቃሴ። ያ ማለት እንግዲህ ዝም ብሎ የተነሳ ወጣት ሳይሆን ስርዓትን የሚያውቅ መሆኑን ነው የሚያሳየው። ያለፈውን ዘመን ወጣት እንቅስቃሴ ካየህ ግን “ኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግስት አያስፈልጋትም ማርክሲዝም ሌኒንዝም መመሪያችን ነው” የሚል ነበር።

ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ወጣቶቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ የቋንቋ ጥያቄ አለ የአስተዳደር ክልል ጥያቄ አለ የፍትህ ጥያቄም አለ። መሪዎቼን እኔ እንጂ ፓርቲ ሊመርጥልኝ አይገባም ብሎ የሚጠይቅ ወጣት አለ። ኢትዮጵያን የሚመራት ፕሬዚደንት ከሁሉም ብሔረሰብ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሁሉንም ብሔረሰብ የሚወክልና የሚያምኑበት አንድ ፕሬዚዳንት መሆን አለበት የሚል ነው። ለዚህ እኮ ነው የሁለቱ ዘመን ወጣቶች እንቅስቃሴና ጥያቄ የተለያዬ ነው ያልኩህ።

ሰንደቅ:- እርሰዎ አባል በነበሩበት የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ የብሔረሰቦች የአስተዳደር ግዛት አከላለልን ሰርታችኋል። በአሁኑ መንግስት በተሰራው የክልሎች አወቃቀር በርካቶች አገሪቱን እንዳትጠናከር የሚያደርግ “ከፋፋይ” የሆነ አወቃቀር ነው የሚሉ ቅሬታዎች አሉ። በዚያ ወቅት የነበረው የብሔረሰቦች የግዛት ወሰን ሲሰራ ምንን ታሳቢ አድርጎ ነበር?

ዶክተር ፍሰሃ:- የአስተዳደር ክልል ሲከለል ዓላማው የብሔረሰቦችን ችግር ለመፍታት ነው። የብሔረሰቦችን ችግር ለመፍታት ግን የተደረገው በብሔረሰብ ማካለል አይደለም ያደረግነው። እያንዳንዱ ህብረተሰብ ለልማት ያለው አመቺነት፣ ከአጎራባች ብሔረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡንና ቋንቋውን በማየት ነው የከለልነው። ለምሳሌ ኦሮሚያን ብቻ ብንወስድ በእኛ አከላለል ኦሮሚያን በሙሉ በአንድ የአስተዳደር ክልል ስር አልነበረም ያካለልነው። በአንድ አስተዳደር ስር ያልከለልነው ኦሮሚያን በአንድ የአስተዳደር ክልል ስር ብታካልለው በውስጡ ያለውን ሌላ ብሔረሰብ በሙሉ መደፍጠጥ ይሆናል። ስለዚህ ከላይ በጠቀስኳቸው የአከላለል መስፈርቶች መሰረት የሚከለልበትን መንገድ ነው የቀየስነው።

በዚህ መንግስት አከላለል ስትሄድ ግን አዲስ አበባን ብትወስድ ከተማዋ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ስትሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፌዴራል መንግስት ዋና ከተማም ነች። ኦሮሞው “ፊንፊኔ” ይለዋል የፌዴራል መንግስቱ ደግሞ “አዲስ አበባ” ይላል። በአንድ አገር ውስጥ በአንድ ከተማ ላይ እንዴት የተለያዬ ስም ሊኖር ይችላል? ለምሳሌ አንደ ሰው ስሙ “አበበ” ከሆነ በሌላ ሰፈር ሂዶ “አሰፋ” ነኝ ሊል አይችልም።

ሰንደቅ:- በእናንተ ጊዜ የተሰራው የብሔረሰቦች የግዛት ወሰን አከላለል ላይ ብንመለከት አንድን ቋንቋ የሚናገረውን ብሔረሰብ በተለያዬ የግዛት ስያሜ እንዲካለል አድርጋችኋል። ለምሳሌ ኦሮሚያን ብንወስድ በሰባት የግዛት አስተዳደር ክልል ነበር የከለላችሁት። ይህ ብሔረሰቦች እንዳይጠናከሩ አያደርጋቸውም ይላሉ?

ዶክተር ፍሰሃ፡- ዓላማው እኮ አንዱ ብሔረሰብ እንዲጠናከር ሌላው እንዲዳከም አይደለም። ዓላማው ኢትዮጵያ እንድትጠነክር ነው። ኢትዮጵያ የምትጠነክረው እንዴት ነው? ያልክ እንደሆን ብሔረሰቦቿ ሲጠነክሩ ነው። ብሔረሰቦቹ እንዲጠነክሩ ለማድረግ ደግሞ ብሔረሰቦቹን በአስተዳደር ክልል ስታካልል ቋንቋን መሰረት አድርገህ ከተነሳህ ለልማትም ሆነ ለአስተዳደር አመቺነት ተስማሚ አይሆንም። ቋንቋን ብቻ መሰረት የምታደርግ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግር ትፈጥራለህ። ለምሳሌ እኛ ስናካልል ኤርትራ እና ትግራይ ለየብቻ ራስ ገዝ የተባሉት ቋንቋን መሰረት አድርገን ባለማካለላችን ነው። የጎንደር አማራ እና የሸዋ አማራ አንድ ቋንቋ ይናገር እንጂ በስነ ልቦናም ሆነ ለልማት ባለው አመቺነት ሁለቱን አንድ አድርጎ ማካለል አይቻልም። የወለጋ ኦሮሞ እና የሀረር ኦሮሞም በተመሳሳይ ነው። ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ የአስተዳደር ክልል የሚካለለው የብሔረሰቦችን ችግር ለመፍታት እና ለልማት ማፋጠን እስከሆነ ድረስ ቋንቋን ብቻ መሰረት አድርገን ብናካልል ኖሮ መልካም አይሆንም ነበር።

በሌላ በኩል አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሀይማኖት እና አንድ ባህል ያለው አለ አፋር። የአፋር ህዝብ የአሰቡን አፋርም ሆነ የጺዮኑን አፋር በተለያዬ ጊዜ ብትጠይቃቸው አንድነታቸውን የሚገልጽ እንጂ በመካከላቸው ልዩነት የሌለ መሆኑን ይነግሩሃል።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ መንግስት የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ከሶላሜ ላንድ ገዥ ጋር በቅርቡ ስምምነት ላይ ደርሷል። ከዓመታት በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር “ወደብ ባይኖረንም ማደጋችንን አላቆምንም። የአሰብ ወደብ ለኤርትራ መንግስት ሊጠቅመው የሚችለው ለግመል ማጠጫ ብቻ ነው” ብለው የተናገሩ ቢሆንም አሁንም በወደብ አልባ መሆናችን አገሪቱ ዋጋ እየከፈለች ነው ተብሎ በስፋት ይነገራል። ለመሆኑ የአስተዳደር ክልል የሰሩ እንደመሆነዎ “አሰብ ወደብ” የኢትዮጵያ ነው የኤርትራ?

ዶክተር ፍሰሃ፡- ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠቴ በፊት ልጠይቅህ እስቲ “አሰብ ውስጥ የሚኖረው ብሔረሰብ ማነው?” ያልክ እንደሆነ የአፋር ብሔረሰብ ነው የሚኖረው። የአፋር ህዝብ እኮ ራሱን የሚጠራው የድንበር ጠባቂ (Gate Keeper) እያለ ነው። የአፋር ህዝብ አመለካከቱ ወደ ውስጥ እንጂ ወደ ውጭ ሆኖ አያውቅም። አሰብ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ኢትዮጵያዊ (አፋር) ከሆነ ወደቡ የኢትዮጵያ ነው ማለት ነው። በታሪክም ያየን እንደሆነ የኢትዮጵያ ነው። እንኳን አሰብ ጂቡቲም የእኛ ናት። ጂቡቲ ለ99 ዓመት በሊዝ የተያዘች አገር ነች በፈረንሳይ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት የነበረው ጄኔራል ደጎል ጂቡቲ ለእናት አገሯ እንድትመለስ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ነገር ግን አብዮት በመነሳቱና የደርግ መንግስትም ከሶማሌ ወረራ በተጨማሪ በአገር ውስጥም በጦርነት ስላለፈ የጂቡቲ ነገር መልስ ሳያገኝ ቀረ።

አቶ መለስ ብዙ ሊመሰገኑበት የሚችሉበት ስራ ሊኖር ቢችልም በታሪክ ሊጠየቁበት የሚችለው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ማድረጋቸው ነው። ኤርትራን ማስገንጠላቸው ሌላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሰብን ሲሰጡ እንኳ “እምቢ” ማለታቸው በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ያኔ የተሰራ ስህተት ውሎ አድሮ አገሪቷ ላይ ትልቅ ችግር አምጥቷል። ከዚህም በላይ ሌሎች ችግሮች ሊከተሉ ይችላሉ።

ሰንደቅ፡- አንድ አገር ወደብ አልባ በመሆኑ ከኢኮኖሚያዊ ትርፍ በዘለለ የሚያጣው ጥቅም ምንድን ነው?

ዶክተር ፍሰሃ የምታየው ነዋ። አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ። ቤት ሲሰራ ለምንድን ነው በር የሚሰራለት? አየህ ቤት ሰርተህ ዙሪያውን አሽገህ የምትተወው ከሆነ መውጫ መግቢያ የለህም ማለት ነው። አገርም እንደዚህ ነው። ወደብ ማለት በር ማለት ነው። የወደብን ጥቅም ለማወቅ እኮ የተማርክ መሆን ወይም የጂኦግራፊ ምሁር መሆን አይጠበቅብህም።

ሰንደቅ፡- የኤርትራ ወደቦች (አሰብን ጨምሮ) ሁሉም በአረብ አገራት እንዲተዳደሩ የኤርትራ መንግስት አድርጓል። የኢትዮጵያ አጎራባች አገሮች (ከኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን በስተቀር) የአረብ ሊግ አባል እና ታዛቢ (ኤርትራ ታዛቢ ናት) ናቸው። የአረብ አገራት ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ባላንጣ መሆናቸውን ስናስብ አካባቢያችን በአረቦች ቁጥጥር ስር መዋሉ የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

ዶክተር ፍሰሃ፡- በታሪክ የኢትዮጵያ ጠላቶቿ የቅርብ ጎረቤቶቿ ናቸው። የቅርቦቹን እንኳ በአጼ ዮሃንስ፣ በአጼ ምንሊክና በአጼ ኃይለሥሳሌ ጊዜ የነበሩትን ችግሮች ለማየት ብንሞክር እነዚህ ነገስታት ደማቸውን ያፈሰሱትና ህይወታቸውን መስዋዕት የከፈሉት መውጫ በራችን ስለሆነ ነው።

አረቦች ደግሞ የእኛን እድገት፣ሀያልነት እና አንድነት የማይሹ ሁልጊዜ የእኛን አካባቢ ስቃይ ለመጫን እና ለመዝጋት ነው የሚፈልጉት። ስለዚህ እነሱ አንድም ጥይት ሳይተኩሱ የእኛው የራሳችን መሪዎች ቃታውን ሳቡላቸው። አሰብ ተዘጋ ማለት ነው። አረቦች አሁን ተንደርድረው እነዛ ወደቦች ላይ የሰፈሩት ለምን ይመስልሃል? አቶ መለስ ወደቡ የግመል ማጠጫ ያሉት ወደብ ነው አሁን ወርቅየሆነው። ይህ አርቆ ባለማስተዋል የተፈጠረ ስህተት ነው። አቶ መለስ አርቀው ማሰብ ይሳናቸዋል ብዬ ሳይሆን “አቶ መለስ ኢትዮጵያ ላይ ጨክነውባታል” ነው የምለው።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት አገራችን ውስጥ የማንነት ጥያቄን ጨምሮ የፖለቲካ ጥያቄዎች በስፋት ሲነሱ ይታያል። ለአብነት ያህል ብናነሳ በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልል ወልቃይት አካባቢ እና የኦጋዴን አካባቢዎች እነዚህ ጥያቄ ተደጋግመው ይነሳሉ። ለመሆኑ ለጥያቄዎቹ መነሳት ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?

ዶክተር ፍሰሃ፡- በወልቃይት ጉዳይ እንጀምር። እኔ በታሪክ እንዳነበብኩትም ሆነ ባለፈው መንግስት የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት አባል ሆኜ ስሰራ በነበረበት ወቅት እንዳየሁት የወልቃይት ህዝብ የሰሜን ጎንደር አካል ነው። ወልቃይትን ወደ ትግራይ ያካለሉበትን ምክንያት ምን እንደሆነ ባላውቅም አሁን ግን በአዲሱ አስተዳደር ወደ ትግራይ አድርገታል።

የወልቃይት ህዝብ አሁን እየጠየቀ ያለው አነጋገራችን፣ አለባበሳችን፣ ባህላችን፣ አጠቃላይ ሁኔታችን እና ስነ ልቦናዊ አመለካከታችን ከአማርኛ ተናጋሪው እንጂ ከትግርኛ ተናጋሪው ወገን አይደለም እያለ ነው የሚጠይቀው። ቋንቋን በተመለከተ ግን ትግርኛ፣ አማርኛ እና አረብኛ እንናገራል ይላሉ። አየህ ቅድም ቋንቋን መሰረት አድርገን ያላካለልነው ለዚህ ነው። እነዚህ ሰዎች አንድ ቀን የሱዳን መንግስት መጥቶ “ሰዎቹ ሱዳንኛ ይናገራሉና ሱዳናዊያን ናቸው” ሊል ነው ማለት ነው? ሰዎቹ ትግርኛንም ሆነ አረብኛን የሚናገሩት ከትግርኛ ተናጋሪውም ሆነ ከሱዳን ጋር ተጎራባች በመሆናቸው ነው። ስለዚህ ይህ የወልቃይት ህዝብ የተያዘበት መንግድ ለትግራይም ሆነ ለአገር አይበጅም። ጠብመንጃ ማንንም አላተረፈም። ንጉሱ 40 ወይም 50 ሺህ ወታደር በስራቸው ቢኖርም አላዳናቸውም። በደርግ ጊዜም ያ ሁሉ መሳሪያ እና ጦር እያለ መንግስቱን አላዳነውም። ኢህአዴጎችም የአስተዳደር ክልሉን ዘወር ብለው መመርመር አለባቸው።

የኦጋዴን ችግር ያነሳኸውን እንመልከት። በታሪክ የተመለከትን እንደሆነ የእንግሊዝ ቅኝ ሶማሌ፣ የጣሊያን ሶማሌ እና የፈረንሳይ ቅኝ ወደብ የሚባል እንጂ ሶማሌ የሚባል መንግስት አልነበረም ጃንሆይ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) ናቸው የመሰረቷት።  እንግሊዞች ከቅኝ ግዛት ሲወጡ እንግሊዝ የተናገረችው የእንግሊዝ ሶማሌ እና የጣሊያን ሶማሌ ተብለው ለሁለት እንዲከፈሉ ነበር ሀሳብ ያቀረቡት። በዚህ ጊዜ በደንብ ያልተመለከቱት ነገር ኦጋዴን ውስጥ የሚኖረው ሶማሌዎች አሉ። ኬኒያ ውስጥ ሶማሌዎች አሉ። ኢትዮጵያ ስትረዳው የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ሸርማርክ የሚባለው ታላቋን ሶማሌ እንመሰርታለን ብሎ ኦጋዴን እና ኬኒያ ውስጥ ያሉትንም ማጠቃለል አለብን ብሎ ከተናገረ ጀምሮ ነው ይህ ነገር የተፈጠረው። ኬኒያ ውስጥ ባለው ሶማሌም ሆነ በኦጋዴን ሶማሌ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ የሚነሳ ቢሆንም በእኛ ላይ ጠንከር ብሎ የሚታየው የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ስላለ ነው።

የኦሮሚያ ችግር የተፈጠረው መንግስት መጀመሪያ አስተውሎ ካለማሰብ የፈጠረው ችግር ነው ብዬ ነው የማመነው። በእኔ እድሜ ያየሁትና የምነግርህ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ብሔረሰብ በቋንቋው እንዳይናገር የተደረገበት ጊዜ አልነበረም። ፍርድ ቤት እንኳ “አማርኛ አልችልም” ካለ ህጋዊ አስተርጓሚ ይመደብለት ነበር። በደርግ ጊዜ ህገ መንግስት ተቀርጾ ለህዝብ ውይይት እንዲደረግበት ሲደረግ የህገ መንግስቱ ረቂቅ የተዘጋጀው በ14 ቋንቋዎች ነበር።

ወደ ጥያቄህ ስመጣ በቋንቋ እንዲናገርና እንዲማር ሲደረግ ወጣቱ ተምሮ ከክልሉ ሲወጣ መናገር የሚችለው ኦሮምኛ ብቻ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ህዝብ መግባቢያ ቋንቋው አማርኛ ነው ትግራይ ብትሔድ፣ ሀረር ብትሔድ ህዝቡ የሚግባባው በአማርኛ ነው። ይህ የኦሮሞ ወጣት ከክልሉ በኦሮምኛ ብቻ ተምሮ በማደጉ ወደ ሌላ ክልል ሲወጣ ሊያሰራው የሚችል የቋንቋ መግቢያ የለውም። ስለዚህ ያለው አማራጭ ምንድን ነው ወደ አደገበት ቀዬ ሂዶ ከአባቱ ጋር መሬት ተጋርቶ ማረስ ነው። ይህን ለማድረግ ሲሄድ ደግሞ መሬቱ ተሽጦ (መንግስት በካሳ አስነስቷቸው) አባቱ በቀድሞ መሬቱ ላይ በተሰራው ሆቴል ጥበቃ ሆኖ ነው ያገኘው። እውነቱ ይህ ነው።

ሰንደቅ፡- የኢህአዴግን የ25 ዓመታት የስልጣን ዘመናት እንዴት ይመዝኑታል?

ዶክተር ፍሰሃ፡- እኔ አስበው የነበረው ኢህአዴግ ከ25 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ቀይሮ ነጻነትን አስከብሮ አገሪቱን ይመራል የሚል ነበር። ምክንያቱም ኢህአዴግን ከጫካ ጀምሮ ያስተላልፉ የነበረውን የሬዲዮ ፕሮግራማቸውን እከታተል ነበር። በወቅቱ አቶ መለስ ሲናገሩ የነበሩት ስሰማ በእውነት ለኢትዮጵያ አንድ ልጅ ተወለደላት ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ነገር ግን የአቶ መለስ ንግግር በየጊዜው እየቆረቆዘ እየቆረቆዘ በመሄድ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በሌላ በኩል ደግሞ የተሰሩ በጎ ስራዎችን ስመለከት ህንጻዎችና መንገዶች ተገንብተዋል። ከሞላ ጎደል በርከት ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች ተከፍተዋል ምንም እንኳ አብዛኞቹ የሚያስተላልፉት አሸሸ ገዳሜ እና ኳስ ቢሆንም።

እኔ በተደጋጋሚ ጊዜ የምናገረው የማይሞት ሀብት ቢኖር እውቀት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቱ በምን አይነት እውቀት ነው የተገነባው ብለን የጠየቅን እንደሆነ በትምህርት የተገነባ ሆኖ አላየሁትም። ወጣቱ የተገነባው በገንዘብ ላይ ነው። ስለዚህ መንግስት ትኩረት ሊያደርግ የሚገባው ወጣቶችን በእውቀት ላይ መገንባት ነው።

Sendek amharic newspaper

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: