The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የብሔረሰብ እኩልነት ጥያቄ የኢትዮጵያ አብይ ችግር ነው; – ሰርጸ ደሰታ

ethiopian-montage23423

በ60ዎቹ አብዮት ከትነሱት አብይ ጥያቄዎች አንዱ የብሔረሰብ እኩልነት ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ይህ ጥያቄ ግን ዛሬም መልስ አግኝቶ ጠያቂዎቹን ያረካ አይመስለኝም፡፡ ሰሞኑን ለዘውጋዊው ፖለቲካ መፍትሄ በሚሉ ነጥቦች ላይ አንዳንድ ምሁራን ሀሳብ ሰጥተውም አንብበናል፡፡ እኔ ግን የብሔረሰብ እኩልነት የሚለው ጥያቄ ራሱ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የሕዝብ አብይ ጥያቄ ነው ወይ የሚል ጥያቄን ማንሳት እወዳለሁ፡፡ በእኔ እምነት የብሔር ማንነት ችግር ጎልቶ የመጣው ከሕዝብ ሳይሆን አወቅን በሚሉ (ኤሊትሰ) ሰዎች ነው ባይ ነኝ፡፡ ችግሩ የለም እያልኩ ግን አይደለም፡፡ የሕዝብ መሠረታዊ ችግር አይደለም ባይ ነኝ እንጂ፡፡ በምሁራንን አወቅን በሚሉ እጅግ እየገዘፈና ከጊዜ ወደ ጊዜም እየጦዘ መጣ እንጂ ሕዝቦች በሚኖሩበት አካባቢ ማንነታቸውን የሚጋፋ ሥርዓት ያን ያወካቸው አይመስለኝም፡፡ ቋንቋቸውንም፣ ሌሎች ባህሎቻቸውንም ለመጠቀም ብዙ የተቸገሩበት ጊዜም የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሕዝብ የአስተዳደር በደል፣ የልማት እጦት፣ በአጠቃላይ ለኑሮው መመቻቸት የሚፈልጋቸውን ነገሮች በማጣቱ ብዙ ይቸገራል፡፡ መሠረታዊ ጥያቄዎቹም ከእነዚህ ጋር የተያያዙ እንጂ ከማንነቱ ጋር የተያያዙ ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሆኖም እነዚህ ችግሮች ሳይሆን የብሔረሰብና የማንነት ጥያቄዎች ፖለቲካውን በሚዘውሩት እናውቃለን ባዮች (ኢሊትሰ) እና ተደማጭነት ባላቸው ሰዎች ትልቅ ቦታ ስሌዙ የሕዝቡን መሠረታዊ ችግር ቦታ የሚሰጠው የጠፋ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በከፋ ግን የሄው የዘውግን ጥያቄ መከታ አድርጎ ይሄው አወቅሁ የሚለው አካል ሕዝቡን ለራሱ መጠቀሚያ እያደረገውና ይልቁንም የኖረ ማንነቱንም በሚያመክን ሁኔታ እርስ በእርስ እንዲለያይ በማድረግ በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ እንደሚባለው ሌላ ተጨማሪ ችግር ፈጥሮበታል፡፡

ዘውጋዊ ሥርዓትን በይፋ አውጀን መተግበር ከጀመርን እንኳን ዛሬ 25 ዓመት አለፈን፡፡ ለተባለው የብሔር ጥያቄ መልስ ይሠጣል የተባለው ዘውጋዊነቱ ይሄው አሁን ጭራሻ የማንነት መሠረቱ የጠፋውን የባዘነ ትውልድ ፈጥሮ እናየዋለን፡፡ የሕዝብ መሠረታዊ ችግሮችን በዘውጋዊነት ቅብ ጀቡነናቸው ዓለም ቀኑን ሙሉ እያመነዠከ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበላው አጥቶ በረሐብ ይሰቃያል፡፡ አለም በብዙ ዘመኑ በሠጠው ቴክኖሎጂ በሚታገዝበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁሉም ተርፎ እንጥፍጣፊው ነው የሚደረሰው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም ድረስ ኑሮው የሚወዳደርለት ከሌሎች አገሮች አንጻር ሳይሆን ከዘመናት በፊት ካለፉ ሥርዓቶች ጋር ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ይሄ አልነበረም ዛሬ ይሄ አለ ነው ውድድሩ፡፡ በደርግ ሞባይል የለም ዛሬ አለ፣ ኢነተርኔት በደርግ የለም ዛሬ አለ፡፡ እንደህ ባለና በመሳሰሉ አስተሳሰቦች አገርንና ሕዝብን ከዚህ በላይ አያሰፈልጋችሁም እያልን የአገርና የሕዝብ ጠላት መሆናችን ትንሽም አልከበደንም፡፡ ረሐቡ፣ ችግሩ፣ በአስተዳደር ምክነያት እየደረሰበት ያው በደል ምናችንም አልሆነም፡፡ ዛሬም ትልቁ ጉዳያችን የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ረሐብም በሉት፣ ሰውኛው አስተዳደረዊ በደል ሳይቀር ግን የሁሉም ሕዝብ የጋራ ችግር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛ የሕዝብን ችግር መፍታቱ አቅሙ ስለሌለን ሌላ የሕዝብ ያልሆነ ጥያቄ አንስተን መደበቂያ እንዳደረግንውም ይሰማኛል፡፡

ረሐብ በብዙ አገሮች ተከስቷል፡፡ ብዙ ሕዝብም ጨርሷል፡፡ አውሮፓ ተርቦ ለስደት የተዳረገበት ዘመን አለ፣ በጦርነትም ምክነያት በመጣበት ረሓብ ተገርፏል፡፡ ቻይና፣ ሕንድ የቀርብ ጊዜ የሚባል የረሐብ ታሪክ አስተናግደዋል፡፡ ለምሳሌ ቻይና የዛሬ 60 ዓመት ገደማ ይመስለኛል በገጠማት ረሀብ ከ30ሚሊየን በላይ ዜጎቿን እንዳጣች ይነገራል፡፡ ሕንድ ከእኛ በፊት በየመዝገበቃላቱ ሳይቀር የረሀብ ምሳሌ የሚሰጥባት አገር ነበረች፡፡ ሁለቱም አገሮች ዛሬ በምግብ ራሳቸውን መቻል ብቻም ሳይሆን ዓለምን በቴክኖሎጂ እየመሩት ይገኛሉ፡፡ እኛ በኃ/ሥላሴ ተከሰተ የተባለው የወሎ ረሀብ መዝገበ ቃላት ላይ እንዳስመዘገበን ዛሬም እዛው ነን፡፡ ምንም ሊሰማንም አልቻለም፡፡ እጅግ ያማል፡፡ ረሐብ በራሱ እጅግ አሳቃቂ ገጠመኝ ነው፡፡ የአገር ቤቱ ረሐብ አብሮን ሥም ሆኖን ከእኛው ጋር በየአገሩ መጓዙንም ምናችንም አልሆነም፡፡ በቅርቡ እኔን እንቆቅልሽ የሆነብኝን የአቶ ኃ/ማርም ደሳለኝን ንግግር ሰምቼ ጤነኝነታችንንም ተጠራጠርኩት፡፡ እርግጥ ነው ጤነኛ አይደለንም፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ኃ/ማርያም ራሳችንን በምግብ ችለናል ማለታቸው ሳያነሳቸው በአንዱ ሌላው ንግግራቸው ድርቅ በአውስተራሊያም፣ በካሊፎርኒያም በሌሎችም አገሮች አለ በሚል የኢትዮጵያም እንደዛው ነው አሉን፡፡ እውነታው ደግሞ ከአውስተራሊያና ካልፎረኒያ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ተከስቶ አያውቅም ቢባል ማንም ባለሙያ የሚስማማበት ነው፡፡ እኛ አገር እኮ የወቅት መዛባት እንጂ እውነተኛ ድርቅ የለም፡፡ አንድ የሰብል ወቅት ከተዛባ በማግስቱ የሚራብን አገር 3 ዓመት ሙሉ ዝናብ ጠብ ሳይል (የካሊፎርኒያው ድርቅ እንዲህ ነው) ጠግቦ የሚያድርን ሕዝብ ማወዳደር ምን የሚሉት እንደሆነ እኔን አልገባኝም፡፡ የራሳችሁ ጉዳይ አይነት ንግግር ነበር፡፡

ሌላው ጋር ያለ የእድገት ሁኔታችን ሲታይ እንኳን ላለፉት 10 ዓመት ገደማ በሁለት ዲጂት ያደግን ኑሮው የተመሰቃቀለበትና በገዛ አገሩ የተማረረን ዜገ አቆይተናል፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር ዳቦ ፈልገው የወጡ ልጆቻችን  አንገታቸው ተቀልቶ በበረሀ የሰይጣኖቹ ግብር የሆኑት፡፡ በዛው ወቅት በደቡብ አፍሪካ አይናቸው እያየ በእሳት የጠቃጠሉ ወገኖቻችንን ተመለከትን፡፡ ሌላም ጊዜ በሌሎች አገሮች የእኛ መከራ ጽኑ፡፡ ሴቶቻችን በአረቡ አለም ብዙ መከራን ይቀበላሉ፡፡ እንዲህም እየሆነ ዛሬ አገር ቤት ያለው ከኢትዮጵያ ሲዖልም ይሻላል እየለ ተጨማሪ የሞት ግብር በሚሆንባቸው አደገኛ ቦታዎች ሳይቀር መሰደዱን አላቆመም፡፡ ይህ ሁሉ ለዜጎች መከራ የሆነ አስተዳደር ምክነያት ነው፡፡ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ ሳይሆን ዜጎችን በኑሮ ተማረው ከአገር ብን ብለው እንዲጠፉ የሚያደርጋቸው ጨካኝ የሆነ ሥርዓት በመገንባታችን ነው፡፡ ትዝ ይለኛል የዛሬ ዓመት በሊቢያ አንገታቸው የታረደውን ጨምሮ ብዙ ሌሎች ከአገር የወጡበት አንዱና ዋነኛው ምክነያት የኮንደሚኒየም ቤት ለማግኘት ክፈሉ የተባሉትን መክፈል ባለመቻላቸው ነበር፡፡  አገሪቱ የጥቂት ጨካኞች መኖሪያ ስልሆነች ዜጎች አቅማቸውን የሚመጥን ሁኔታ አይደለም የሚስተናገዱት፡፡ ለእነዚህ የወጣውን እጣ አሳልፈው ለሌላ ገነዘብ ላለው ይሰጡታል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ያለው ደግሞ በዘራፊዎችና ለሕዝብ ምንም ርሕራሔ በሌላቸው እጅ ነው፡፡ የአገሪቷም የኑሮ መሻሻል መለኪየዎች እነሱ ናቸው፡፡ በዛው ወቅት ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ በጓደኞቹ ሞት እጅግ ያዘነው ወጣት ብሶቱን ሲያሰማ ፖለቲካ ብለው ወደ እስር አጋዙት፡፡ ሲሆን ሊካስ በተገባው ከሙሉ ይቅርታ ጋር፡፡ የጭካኔው ልክ ሙልቶ የተረፈ ስለሆነ የልጆቹንም ሐዘን ለመገለጽ ብሶቱን ማሰማት አልቻለም፡፡ በደርግ ጊዜ ልጁን ገድለው አባቱን ልጅህን የገደልንበት ጥይት ዋጋ ክፈል የባል ነበር አሉ፡፡ እንዲህ ያለ አረመኔ የ60ዎቹ ትዎልድ ነው ዛሬም አገሪቱን የሚመራት፡፡

ሰሞኑን ደግሞ በየአገሩ የተበተኑ ልጆቻቸውን እንኳን እንዳያገኙ እነ ቫይበርንና የመሳሰሉትን እዘጋለሁ የሚል አዋጅ አውጥቷል፡፡ ከሌላው አለም በመለየትም ሕዝቡን ከቀዬው ውጭ እንደይመኝም ነው፡፡ በዚህና በምሳሰሉት ሁሉ ሁኔታ ታዲያ ብዙዎች ፖለቲከኞቻችንና ምሁሮቻችን ዛሬም ያረጁባትን ፍልስፍና ለጊዜውም ቢሆን ትተው የሕዝቡን እውነተኛ ችግር ላይ መወያየትና መፍትሔ መስጠትን አልመጣላቸውም፡፡ ችግሩ ደግሞ የትምህርት ግዙፍነታችንን እየተጠቀምን የምንፈጥረው ማሳሳት ሌሎች መፍሕትሔ የሚሆን ሐሳብ ያላቸውንም ማቀጨጩ ነው፡፡ በፍልስፍናው ታዋቂነትን ተጠቅሞ የሚፈጸምን ማሳሳት ፋላሲ ኦፍ አድፖፕለም ይባላል፡፡ ምሁሮቻችን በአብዛኛው እያደረጉ ያሉት ይሄንን ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አብይ ችግር ከኑሮና አስተዳደርና ጋር የተየያዘ እንጂ የብሔር ጉዳይ ዋና ችግሮች ውስጥ እንዳልሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ቢሆንም ቅሉ ሰሞኑን አንድ ምሁር የነገሩን አይነት መፍትሔ ሳይሆን ሌሎች የሕዝቡን ነባራዊ ሁኔታ የሚያማክሉ መፍትሔዎች አሉ ባይ ነኝ፡፡ ወረቀት ላይ እንደምናሰፍረው ያለ ሕዝብ የለም፡፡ አሁን ግን አላለሁ የኢትዮጵያን ጉዳይ በማነሸዋረር ብዙ በማንነትና በሕወታችን ላይ የመጡብንን ችግሮቻችንን ትኩረት እንዳንሰጥ የሚነሱ ሐሳቦችን ቢያንስ እንድናዘገያቸው አለምናለሁ፡፡ የሕዝብና የአገር ጉዳይ ይሰማን፣ ይመመን፡፡ ቢያነስ ብዙ የገዛ ሥጋ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች፣ ወላጆች እየተሰቃዩባቸው ያሉትን ችግሮች እኛው ምክነያት በመሆን በአረመኔነት አንሳተፍ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በምሕረት ይመልከት!

አሜን!

 

ሰርጸ ደሰታ

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: