The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ይህች ሀገር ወደፊት የማን ነች? | ግርማ ሠይፉ ማሩ

Girma Seifu Maru

ወዳጆቼ አንዳንዴ ግራ የገባው ሰው ግራ ያጋባል እና ጥያቄየን በቅንነት ተመልከቱት፡፡ ይህን ምልጃ የጠየቁት ወዳጆቼን ነው፡፡ የእኔ ነገር የማይጥማቸው የምፅፈውን ሳያነቡ ከተፃፈው ፅሁፍ ጋር የማይገጥም፣ ብቻ እኔ ከኢህአዴግ ጋር ሰለማልገጥም ወይም ደግሞ ሌላ እነሱ ከሚፈልጉት ቡድን ጋር ስለማልገጥም ተቃራኒ የሆነ አስተያየት የሚያሰፍሩ አሉ፡፡ ድሮስ አንተ ብለው ስድብ ይጀምራሉ፡፡ ለእነርሱ ትክክለኛው ነገር መሳደብ ነው፡፡ ከእነሱ ስድብ ለማደን መፍትሔው ደግሞ የእነርሱን ቡድን መቀላቀል ነው፡፡ እኔ በእውነቱ በድን አይደለሁም እና ይህን አላደርገውም፡፡

ለማነኛውም ጥያቄ ወደፈጠረብኝ ነገር ልመለስ፡፡ ይህች ሀገር ወደፊት የማን ነች? የሚል ርዕስ ያደረኩት ጥያቄ በእውነቱ አስገራሚ ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ የሚኖርባት ሀገር እንዴት የማን ነች? ይባላል ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እስኪ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ሀገራችን የእኛም የልጆቻችንም ነች? የኢትዮጵያ ግዛትም በግዛቱ ውስጥ የምንኖር ኢትዮጵያዊያንም ከልባቸን በዚህች ሀገር አለን ወይ? ይህን እንድል ያደረገኝ ገፊ ምክንያት ደግሞ በዚህ ሳምንት ውስጥ በሜዲትሪያን ባህር ሰጥመው ያለቁት ኢትዮጵያዊያን ሰደት ሁኔታ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያዊያን በስደት መድረስ የፈለጉበት ሳይደርሱ ቀሩ፡፡ ይህ ዘንድሮም ተደገመ፡፡ ዘንድሮመ ዘፈኑ ያው ነው፡፡ በደላሎች ተጭበርብረው ሀገር የሚለቁ የሚል፡፡

ከዚህ በፊትም እንዳልኩት አሁንም እንደምደግመው የዚህ የሰደት መንስዔ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር እና ኢኮኖሚው መፍትሔ እንዳያመጣ ወጥሮ የያዘው ፖለቲካው ነው፡፡ ሲደመር ግን ዋነኛው ምክንያት ፖለቲካዊ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ነው ሲባል ሰዎች የዚህ ፓርቲ አባል ደጋፊና ተቃዋሚ በመሆናቸው ሳይሆን አሁን ያለው የፖለቲካ ስርዓት ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ማረጋገጥ ያለመቻሉ ነው፡፡ ይህን ያደረጉት ደግሞ ገዢው ፓርቲና መንግሰት ናቸው፡፡ ሰለዚህ ኢትዮጵያዊያንን የሚያባርረው ወደ ስደት የሚልከው ደላላ ሳይሆን መንግሰት ነው፡፡ ደላላ የሚባሉት የሚሰሩት መንግሰት ልባቸውን ያሸፈተባቸውን ዜጎች ትክክል ይሁንም አይሁን በምድር ላይ ያሉትን የስደት አማራጭ ማሳየት ነው፡፡ ሰለዚህ መንግሰት አባራሪ መሆኑን እሰከ አልተረዳ ድረስ  መፍትሔውን ፍላጋ ቢደክምም አያገኘውም፡፡ ይህ እንግዲ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዜጎቿን የምታጣበት አንዱ መንገድ መሆኑ ሲሆን፤ ይህች ሀገር ወደፊት የማን ነች? የሚል ጥያቄ ካስነሱብኝ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

አስገራሚው ነገር እነዚህ ዜጎች ሲባረሩ አባራሪ ያልናቸው የመንግሰት ባለስልጣናትም ቢሆኑ ልጆቻቸው በሀገር የሉም፡፡ ከጅምሩ ልጆቻቸው በአውሮፓና አሜሪካ ይወለዳሉ፡፡ ከዚያም የውጭ ዜጋ ይሆናሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ምን ያደርጋል ብለው እያደጉ ነው፡፡ እነዚህ ባለስልጣኖች ይህን ቢያደርጉ ብዙ አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱም የሚሰሩት ስራ ልጆቻቸውን በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲኖሩ የሚያደርግ አይደለም፡፡ በውስጣቸው ባለው ሰላም ማጣትና በቀል የተነሳ፤ ሌላውም እነርሱን ይበቀላል ብለው ስለሚሰጉ ልጆቻቸውን ከውልደት እስከ እድገት የውጭ ያደርጓቸዋል፡፡ ድሮ ድሮ የመሪ ልጆች ተተኪ መሪ የሚሆኑበት እድል ነበራቸው፡፡ ምክንያቱም ወላጆቻቸው ባገኙት አጋጣሚ እነርሱም የመሪነት ክዕሎት ስለሚያዳብሩ ከሌላው የተሻለ እድል እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡ ምን ያደርጋል የመሪዎቻችን ልጆች በሜዲቴሪያን ባህር በኩልም ባይሆን ሀገረ የለሽ ሰደተኞች ናቸው፡፡

ሌላኛው አስገራሚ ነገር ደግሞ በሀገራችን አሉ የሚባሉት ባለገንዘቦችም (በሀገራችን ባለፀጋ መኖሩን አላውቅም) ልክ እንደ ባለስልጣኖቹ ልጆቻቸው ከውልደት እሰከ አድገት የውጭ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የሰሩት ህንፃ፣ የከፈቱትን ፋብሪካ ሊቆጣጠሩ ሊያስተዳድሩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ከብዙኃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሊሆኑ የሚችሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እያሳደጉልን አይደለም፡፡ አንዳንዶች በሀገር ውስጥ እያስተማሩ እንኳን ቢሆን ሲጀመር ትውልዳቸው ውጭ በመሆኑ እና ዜግነታቸው ሌላ በመሆኑ፣ ሲቀጥልም በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ጥሩ ባለመሆኑ ለከፍተኛ ትምህርት ሲደርሱ ወደ ውጭ የሚላኩ ናቸው፡፡ ለስደት፡፡ ይህች ሀገር የእነርሱ አይደለችም እና ወደ ሌላ ሀገር ለከፍተኛ ትምህርትና ስራ ይሄዳሉ፡፡ ይህ ነው እንግዲ ይህች ሀገር ወደፊት የማን ነች? ብዬ የጅል ጥያቄ እንድጠይቅ ያስገደደኝ፡፡

በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከሊቅ እሰከ ደቂቅ ወደ ውጭ ሀገር መሄድና መኖር እድል ቢያገኝ ያለምንም ማመንታት የሚሄድ ነው፡፡ የኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ ዓይነት ግልፅ የወጣ የእርስ በእርስ ጦርነት ሳይኖር ኢትዮጵያዊያን ሀገር ለቆ ለመሰደድ የወሰኑበት ሚሰጥር በሀገራችን የተንሰራፋው ድህነት እና ድህነቱን የሚዘራብን የፖለቲካ ስርዓት ነው፡፡ የዚህ ስርዓት ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ እንኳን ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እየሄዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ድሃው ዜጋ በእግሩ ድንበር አቋርጦ ያለ የሌለውን ጥሪት አሟጦ ከአውሬ እና ከባህር ማህበል ጋር ተጋፍጦ ሀገር ለቆ ይሰደዳል፡፡ የባለስልጣኑ እና የሀብታም ልጆች ደግሞ በቦሌ ደልቀቅ ብለው ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ የዚህ ድምር ውጤት በዚህች ሀገር ላይ ተሰፋ ያለው እየጠፋ መሆኑን ከማመላከት ውጭ ምን ሊባል ይችላል?

ለማነኛውም ግን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወጣቱ ትውልድ ጥሎት እየሄደ ያለውን ሀገር ሁኔታው ቢመቻች ወደ ሀገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ የሚመጡት ግን የመጨረሻ የህይወት ዘመናቸውን በደስታና በፍሰሃ ለማሳለፍ እንጂ ጠቃሚ የሆነውን የህይወታቸውን ክፍል ጥገኝነት ለሰጣቸው ሀገር አበርክተዋል፡፡

በዩኒቨርሲት የሚያሰተምረው፣ በትምህርቱ የላቀ ውጤት ያመጣው ተማሪ፣ ለስራ የተሻለ ቦታ አለ የሚለው ወጣት፣ ወዘተ ሀገሩን ለቆ በህጋዊም ሆነ ህገወጥ መስመር ሀገር ለቆ ሲሰደድ ቆም ብሎ አለመጠየቅ መሄጃ መንገድ አጥቶ የቀረው ይበቃል ካልተባለ በስተቀር አሁን ያነሳሁት ጥያቄ የጅል ሊባል የሚችል አይለም፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: