The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብትና ነጻነትን ማን ይታደጋት? ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በጣም ተቸገርኩ! መጻፍ ወይም ሐሳቤን መግለጽ ማጋራት አልቻልኩም! በቀደም ለታ “እጅግ አስደንጋጩ የወያኔና የመናፍቃኑ የጋራ ዘመቻ ድል!” በሚል ወቅታዊና አንገብጋቢ ርእሰ ጉዳይ ላይ አንድ ጽሑፍ ጽፌ ነበር፡፡ ወዲያውኑ እንዲወርድ ወይም እንዲነሣ ተደረገ፡፡

ይሄ ጽሑፍ ብቻ አይደለም ከዚህ ቀደምም በብዙ ጉዳዮች ላይ የጻፍኳቸው ጽሑፎች በየድረ ገጾቹ ከተለጠፉ አንድ ሰዓትና ሁለት ሰዓታት እንኳ ሳይሆናቸው አንዳንድ አካላት ቡድኖችና ግለሰቦች በድረ ገጾቹ ላይ በሚያደርሱት ተቃውሞ ዛቻና ማስፈራሪያ የተለጠፉት ጽሑፎች እንዲወርዱ ወይም እንዲነሡ ተደርገዋል፡፡

ይሄንን ተቃውሞ ዛቻና ማስፈራሪያ በድረ ገጾቹ ላይ በማሰማት ጽሑፎቹ ከተለጠፉበት እንዲነሡ የሚያደርጉት አካላት ሁሉም የወያኔን አፋኝነትና አንባገነንነት የሚያወግዙ የሚኮንኑ የሚቃወሙ መሆናቸው ነው ይሄ ድርጊታቸው እኔን እጅግ እንዲገርመኝ እንዲደንቀኝም የሚያደርገኝ፡፡

ስለ ኦነግና ኦነጋዊያን የጻፍኳቸው ጽሑፎች ኦነጎቹ ባሳደሯቸው ተጽእኖዎች ወዲያውኑ እንዲወርዱ እንዲወገዱ አድርገዋቸዋል፡፡ ስለ ቤተክህነትና ሲኖዶስ የጻፍኳቸውም እንዲሁ ከመለጠፋቸው አስተሥተውታል፡፡ ሌሎቹም እንደዚያው ተነካሁ የሚሉት አካላት ጮኸው አስነሥተዋቸዋል፡፡ ኢሳት በመጽሐፈ ገጹ (በፌስቡኩ) አስተያየት እንዳልሰጥ ብሎክ ካደረገኝ (ካገደኝ) ሁለት ዓመታት አልፎታል፡፡

ድርጊታቸው እንዲህ ከሆነ የእነዚህ ወገኖች ዓላማና ፍላጎት ታዲያ ምንድነው? አፈናን ጠልተው ከአፈና መገላገልን ፈልገው እንደገና ደግሞ እነሱው እራሳቸው ያውም ሥልጣኑን ሳይጨብጡ እንዲህ አፋኝ ከሆኑ ወያኔ የፈለገውን እያለ ቢወነጅላቸው “ስም ሲያጠፋ ነው!” ማለት እንዴት ይቻለናል? ፍላጎታቸው “አይ! አፋኝነት ለወያኔ ሲሆን ብቻ ነው የማይፈቀደው!” ነው እያሉ ያሉት ወይስ ምንድን ነው?

የቻለ የጻፍኩት ነገር ሐሰት ከሆነና ሊያስተባብል የሚችል እውነት ካለው ሐሳብን በሐሳብ መሞገት መብቱና የሚጠበቀውም ይሄው ነው፡፡ ይሄንን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ተሸንፏልና እጅ መስጠት አዋቂነትና ጨዋነት ነው፡፡ የጨዋታው ሕግም የሚያዘው ይሄንኑ ነው፡፡ ከሁለቱ ውጭ ተሁኖ ግን ስለ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብቶች፣ ስለሰብአዊ መብቶች፣ ሐሳብን በነጻ ስለመገለጽ ነጻነት ወዘተረፈ. እንዴት መናገር ይቻላል? ስለ እነዚህ እሴቶች መከበር መጠበቅ መስፈን እታገላለሁ ማለትስ እንዴት ይቻላል?

እንዲህ በሆናቹህበት ሁኔታ እናንተን በፈረንሳዩ የቻርሊ ሒብዶ ጋዜጣ ላይ ጥቃት ከፈጸሙት አካላት እንዴት ለይቸ ልያቹህ? ያውም እኮ ቻርሊ ሔብዶ ጋዜጣ የሚጽፋቸው ጽሑፎችና የሚሥላቸው የሽሙጥ (የካርቱን) ሥዕሎች ከባሕል፣ ከሃይማኖት፣ በግብረ ገብ፣ ከሥነምግባር አንጻር ጸያፍና እጅግ ተጋፊ አዋራጅ ተውረኛ ሆኖ እያለ ነው ነገር ግን ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት መከበር አለበት ተብሎ ሥራውን እንዲሠራ የተደረገው፡፡

እኔ የምጽፋቸው ጽሑፎች ግን ከግብረብነት ወይም ከሥነምግባር አኳያ ከቻርሊ ሔብዶ ጋዜጣ በተቃራኒ አቅጣጫ በመጓዝ “የሀገራችንና የሕዝባችን መለያ፣ ባሕል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ አንድነት፣ ጥበብ፣ ሥልጣኔ፣ ሰላም፣ ህልውና፣ ነጻነት፣ መብት፣ ደኅነነት ወዘተረፈ. ይጠበቅ! ይከበር!” ባልኩና የእነኝህ እሴቶቻችን ጠላቶች የሆኑትን ዕኩያን ባወገዝኩ ዕኩይ ተግባራቸውን ባጋለጥኩ ነው እየታፈንኩ ያለሁት ለምን???

መጨረሻ ላይ መከሰሴ ባይቀርም መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ እጽፋቸው የነበሩ ጽሑፎች ወያኔ ባወጣቸው ፀረ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሕግጋቶቹ የተነሣ እነኝህ የኅትመት የብዙኃን መገናኛዎች እራሳቸው በራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ (self censor) እንዲያደርጉ የሚያስገድድ በመሆኑ በወያኔ ላለመከሰስ የምሰጣቸውን ጽሑፎች ቆራርጠው ጽሑፎቹ ዓይንና ጆሯቸው እየጠፋ  ለኅትመት መብቃቱ እጅግ ያሳዝነኝ ያማርረኝ የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡

ወያኔ ይባስ ብሎም እምጽፍባቸው የነበሩትን መጽሔቶች ዘጋና ከነሱውም ቀረ፡፡ እግዚአብሔር ታፍነህ አትፈንዳ ቆዝመህ ቆስለህ አትሙት ሲለኝ እንደ መጽሐፈ ገጽ (ፌስቡክ) ያለ ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛን (social media) ሰጠንና ነፍሳችን ተግ አለች፡፡ ሥልጣን የያዘውን አፋኝ አመለጥኩ ብየ ማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛ ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ካለው የራሱ መለያ ባሕርይውና ከሚሰጠው ነጻነት የተነሣ ያለ አንዳች ቅድመ ምርመራ (Censorship) በሙሉ ነጻነትም ሐሳቤን መግለጽ ቻልኩ ብየ ደስ ሲለኝ በዚህ በኩል ደግሞ ሥልጣን ያልያዙ ነገር ግን ኃይለኛ አፋኞች ነግሠው ቁጭ አሉ!

እንግዲህ ታዲያ ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብትና ነጻነትን ማን ያታደጋት??? በሀገራችን ጥፈት (press) እንደሞተች ሁሉ በመደበኛው የብዙኃን መገናኛ (On the conventional media) ላይ ሐሳባችንን መግለጽ ባንችል ደግሞ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (On the social media) እንኳ ሐሳባችንን መግለጽ ላንችል ነው ማለት ነው? እንዲያው ግን “ለራሳቹህ መብትና ነጻነት እራሳቹህ ጠላት ሁኑ!” ብሎ የረገመን ማን ነው?

በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (On the social media) ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብትንና ነጻነትን መቀበልና ማስተናገድ ያልቻልን፣ ያልፈቀድንና ያልፈለግን ከቶ እንዴት ብለን የትና መቸስ ነው ሐሳብን በነጻ የመብለጽ መብትንና ነጻነትን የምንፈቅደው፣ የምንቀበለውና የምናስተናግደው? እስኪ እባካቹህ “ሐሳብን በነጻ የመግለጥ መብት (Freedom of speech) ያለገደብ መከበር አለበት!” የምትሉና ለዚህም በሀቅ የምትታገሉ ወገኖች ካላቹህ ምን ይሻላል ትላላቹህ???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: