The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ቦካሃራም‬ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የአምስት አገሮች የጋራ መከላከያ ኃይል የገንዘብ እርዳታ ያስፈልገዋል ተባለ (የፍኖተ ዴሞክራሲ ራድዮ አጫጭር ዜናዎች)

ሚያዚያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም.

Ø ቦኮ ሃራምን ለመቋቋም የተቋቋመው የአምስት አገሮች የጋራ መከላከያ ኃይል አዛዥ ሚያዚያ 19 ቀን 2008  በሰጡት መግለጫ የጋራው ወታደራዊ ኃይል ውጤት ያለው ስራ እንዲሰራ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለዋል። በመጨረሻው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ረጅዎች ለጋራ ኃይሉ 250 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መመደባቸው የተገለጸ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ገንዘቡ ለጋራው ኃይል ያልደረሰ መሆኑኑ አዛዡ ተናግረዋል፡፡ ገንዘቡ ይሰጣል ተብሎ ቃል የተገባ ከመሆኑ ባሻገር እስካሁን የጋራው ኃይል የደረሰው የተወሰኑ የመገኛኚያ መሳሪያዎችና 11 ወታደራዊ መኪናዎች ብቻ ነው ብለዋል። 8500 ወታደሮችን የያዘው የጋራ ወታደራዊ ኃይል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝሮ ቦኮ ሃራምን አዳክሟል ቢባልም ውጤት ያለው ስራ ለመስራት እርዳታ ያስፈልገዋል ተብሏል፡፤

 

Ø ረቡዕ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓም. በደቡብ አፍሪካ በሚገኙት በጆሃንስበርግ፤ በኬፕ ታውንና በደርበን ከተሞች በርካታ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ፕሬዚዳንት ዙማ ከስልጣን እንዲነሱ በመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፎች አካሄደዋል። ሰልፈኞቹ ፕሬዚዳንት ዙማ በሙስናና እና በዝምድና ስራ ውስጥ የተዘፈቁ በመሆናቸው አገራችውን ለመምራት ብቃት የላቸውም የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበር ታውቋል። ከጥቂት ቀናት በፊት በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ  ከስልጣናቸው እንዲወገዱ ተካሄዶ የነበረውን እንቅስቃሴ በድል ያሸነፉት ፕሬዚዳንት ዙማ በደቡብ አፍሪካ ነጻ ምርጫ የተካሄደበትን 22 አመት ለማክበር በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ መሪዎች የሚለወጡት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንጅ በአቋራጭ እና በመፈንቅለ መንግስት አይደለም ብለዋል። በዴሞክራሲ ውህዳን የአብዛኛውን ሕዝብ ውሳኔ ተቀብሎ የመሄድ ግዴታ አለባቸው ብለዋል። በደቡብ አፍሪካ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱ እየታየ ያለ ክስተት ሲሆን ከተወሰኑ ወራቶች በኋላ የሚደረጉት የከተሞች አስተዳድር ምርጫዎች የሕዝቡን ስሜት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊያሳዩ ይችላሉ በማለት ታዛቢዎች አስተያየታችውን ይሰጣሉ። በሚቀጥሉት የከተሞች አስተዳደር ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ ከተሸነፈ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ በአገሪቱ ላይ ባለው የስልጣን ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ብዙዎች ይተቻሉ።

 

Ø በግብጽና በሊቢያ ወሰን ከሕገ ወጥ ስደተኞች ጋር በተደረገ ግጭት 16 የሚሆኑ ግብጻውያን ስደተኞች የተገደሉ መሆናቸውን ረቡዕ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ገልጿል። ግድያው የተፈጸመው ባኒ ዋሊድ በተባለችው ከተማ ውስጥ ሲሆን  ከአስተላላፊዎች ጋር በተነሳ ግጭት ስደተኞቹ የተገደሉ መሆናቸው ተነግሯል። በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ተልእኮ መስሪያ ቤት መሪ በሰጡት መግለጫ  12 ግብጻዉያን እና ሶስቱ ሊቢያውያን መገደላቸውን ተናግረው ድርጊቱን በጽኑ ኮንነዋል። በሊቢያ በተለያዩ ወገኖች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ከተጀመረና አለመረጋጋት ከተፈጠረ ወዲህ አገሪቱ ከልዩ ልዩ አገሮች የመጡ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚሰደዱባት ማዕከል ሆና የቆየች ስትሆን የስደተኛ ማስተላለፍ ንግድም ደርቶ የሚገኝባት ቦታ ናት።  በሊቢያ በኩል ከሚተላለፉ ስደተኞች መካከል በወያኔው ዘረኛና አምባገነን ስርዓት አፈናና ብዝበዛ ተማረው አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ኢትዮጵያን የሚገኙበት መሆኑም ይታወቃል። በዚህ አጋጣሚ ባለፈው አመት አይሲስ በሚባለው የአክራሪና የአሸባሪ ቡድን አባላት ግፍ በተሞላበት መንገድ በስለት የታረዱ  ኢትዮጵያን ሰማዕታት ወገኖችን የምናስታውሰው በከፍተኛ ሀዘን ነው።  

 

 

Ø ረቡዕ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓም. በሱዳን ካርቱም የዩኒቨርስቲ የተማሪዎችን ሰልፍ ለመበተን ፖሊሶች በተኮሱት ጥይት አንድ ተማሪ ተመቶ የሞተ መሆኑ ተነገረ። በኦምዶርማን የሚገኘው የአህሊያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ የሚማሩ ተማሪዎች ቀደም ብሎ በተደረገ ሰልፍ ተይዘው በቁጥጥር ስር የነበሩት ተማራዎች እንዲፈቱ ለመጠየቅ ሲያካሂዱ የነበረውን ሰልፍ ለመበተን ነጭ ለባሽ ፖሊሶች በፈጠሩት ግርግር አንድ ተማሪ በጥይት ተመቶ ወዲያውኑ የሞተ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል። ረቡዕ ማታ የገዥው ፓርቲ ቃል አቀባይ ተማሪው ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውጭ በሽጉጥ ተመቶ መሞቱን አምኗል። የሟቹን ተማሪ አስከሬን በርካታ ተማሪዎች ተሸክመው ወደ መኖሪያው አካባቢ በመውሰድ እንዲቀበር ያደረጉ ሲሆን በርካታ ተማሪዎች ተማሪ መግደል አገርን እንደመግደል ይቆጠራል ብለዋል። የዩኒቨርስቲው አስተዳደር የተማሪውን መገደል አውግዞ ዩኒቨርስቲው ላልተወሰነ ጊዜ የዘጋ መሆኑን ገልጿል። የካርቱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየጊዜው ከጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስባችውም አገዛዙን በመቃወም ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ መቆየታቸው  ይታወቃል።

 

Ø በሊቢያ የተባበሩት መንግስታት ተልእኮ መሪ በሰጡት መግለጫ የአይሲስ አሸባሪዎች በየጊዜው በአገሪቱ የነድጅ ማውጫ አካባቢዎች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ከፍተኛ ስጋት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። የአሸባሪዎቹ ጥቃት የነዳጅ ምርቱን የሚያስተጓግለው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ጥቃቱም የአገሪቱን ኢኮኖሚና በነዳጅ ምርቱ ገቢ በሚተዳደሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሊቢያ ዜጎችን የኖሮ ሁኔታ ይጎዳል በማለት ኃላፊው ተናግረዋል።

Ø በተያይዘ ዜና የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ከሊቢያ የአማጽያን አካባቢ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ነዳጅ ጭኖ መንቀሳቀሱ በተደረሰበት በአንድ በህንድ የተመዘገበ የጭነት መርከብ ላይ ማዕቀብ እንዲደርግ የወሰነ መሆኑ ታወቀ። ከሁለት ዓመት በፊት የጸጥታው ምክር ቤት በሊቢያ አማጽያን ቁጥጥር ስር ካሉ የነዳጅ ማምራቻ ቦታዎች ነዳጅ እንዳይጫን መከልከሉ የሚታወስ ሲሆን ይህንን  ህግ በመተላለፍ ነዳጅ ጭኖ ወደ ማልታ አቅንቷል የተባለው የጭነት መርከብ ማዕቀብ የተጣለበትና ጉዞው የቅርብ እየተደረገበት መሆኑ ተነግሯል። መርከቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለማይታወቅ ሰው የተሸጠ ሲሆን ስሙም የተቀየረ መሆኑ ተነግሯል።

 

 

 

ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

Ø የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ ለገባው ድርቅና ረሃብ እንደ ችግሩና መጠንና ስፋት አስፈላጊውን እርዳታ ባያቀርብም ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ መስጠቱ ይታወቃል። የወያኔ መሪዎች የእርዳታ እህሉን ከወደብ ለማንሳት እግራቸውን እየጎተቱ የራሳቸውን ማዳበሪያ እያጓጓዙ ሲሆን ወደ መሀል አገር የገባውን የእርዳታ እህልና ሸቀጣ ሸቀጥን ደግሞ በየመደብሩ በመውሰድ መቸብቸብ ጀምረዋል፡፤ በረሃብተኛ ሕዝብ ስም በተማጽኖ የመጣውን የእርዳታ እህል የወያኔ መሪዎችን ኪስ ማደለቡና የዘርና የቋንቋ ፖለቲካው ማራመጃ የፖለቲካ መሳሪያ እንደሆነ ተገልጿል፡፤

 

Ø በአሜሪካ የሚረዳው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሶማሊያ በየጊዜው ከአልሸባብ ጥቃት እየደረሰበት መሆኑና አሜሪካንም በድሮንና በጦር አውሮፕላን በአልሸባብ መሪዎችና የጦር አበጋዞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ስትፈጽም መቆየቷ ይታወሳል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በአልሸባብ ቁጥጥር ስር የነበሩ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሚታገዙ የሶማሊያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይዘገብ እንጅ አልሸባብ ከተሞቹን እንደገና በጦርነትና ያለ ጦርነት እየወሰደ መሆኑ ከሶማሊያ የሚመጣው ዜና አስረድቷል። ከታችኛው ሸብሌ ግዛት ከሞቃዲሾ ደቡባዊ ምዕራብ በ 110 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ጃናሌ ከተማ በአልሸባብ እጅ የወደቀች ስትሆን ከተማዋን ይቆጥጠሩ የነበሩ የኡጋንዳ ወታደሮች ያለ ምንም ጥቃት ከተማዋን ለቀው መውጣታችው ታውቋል። ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በጃናሌ ከተማ በርካታ የኡጋንዳ ወታደሮች መገደላቸው ይታወሳል።

 

Ø በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ህብረት ልኡክና የቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ሚስተር ቺሳኖ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ባሰሙት ንግግር በምዕራብ ሳህራ ያለውን ችግር አስመልክቶ  ተገቢ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ከፍተኛ ችግር ሊከተል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ጊዜ ችግር አነስተኛ ቢመስልም ትልቁን የደን እሳት የምታቀጣጥለው ትንሽ እሳት መሆኗን በማወቅ ለችግሩ ተገቢ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል ብለዋል። ከጥቂት ወራት በፊት የተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን የምዕራብ ሳህራን ግዛት በሞሮኮ የኃይል ቁጥጥር ስር ያለ ግዛት ነው በሚል ንግግር ማድረጋችውን ተከትሎ ሞሮኮ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ከ 20 የሚበልጡ የተመድ የሰላም አስከባሪ ሉኡካን ከምዕራብ ሳህራ ግዛት እንዲወጡ መደረጋቸው ይታወሳል። በ1983 ዓም በምዕራብ ሳህራ የተመደበው የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል የልዑካን ቡድን የአገሪቱን የወደፊት እድል አስመልክቶ ሕዝቡ በምርጫ እንድወስን የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና ለማደራጀት ኃላፊነት ቢሰጠውም  ድምጽ መስጠት የሚችለው ማነው በሚለው ላይ ልዩነት በመፈጠሩ እስካሁን ምርጫው ሳይካሄድ ቆይቷል። የሞሮኮ መንግስት ግዛቱ የሞሮኮ ነው ሲል ከ1967 ዓም. ጀምሮ የትጥቅ ትግል ሲያካሄድ የቆየው የፖሊሳሪዎ ድርጅት ደግሞ ሕዝቡ በውሳኔ ህዝብ መወሰን አለበት ሲል ቆይቷል። የአፍሪካ ህብረት የሳህራዊ አፍሪካ ሪፕብሊክ ግዛትን አባል አገር አድርጎ በመቀበሉ ሞሮኮ የአፍሪካ ህብረት እንደ ገለልተኛ አካል አታየውም። በምዕራብ ሳህራ የተመድ ተልእኮ ስለመቀጠል እና አለመቀጠሉ የጸጥታው ምክር ቤት በሚቀጥለው ሳምንት ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን የምክር ቤት አባላት የተከፋፈሉ መሆናቸው ታውቋል። ፈርንሳይ ስፔን ግብጽ እና ሴኒጋል ሞሮኮን ሲደግፉ ሌሎች ይቃወማሉ ተብሏል። የምዕራብ ሳህራ ጉዳይ ተገቢ መልስ ካላገኘ የማያባራ ጦርነት ሊከተል እንደሚችል ብዙዎች ይጠቁማሉ።

 

Ø በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው የኬፕ ቬርዴ ደሴት 8 ወታደሮችና ሶስት ሰላማዊ ሰዎች በጥይት የተገደሉ መሆናቸው ታውቋል። ግድያውን የፈጸመው አንድ ከስራ ገበታው ላይ ተሰውሮ የነበረ ወታደር ነው የሚል ጥርጣሬ ያለ ሲሆን ድርጊቱን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው ግን የታወቀ ነገር የለም። ከሞቱት ሰዎች መካከል ሁለቱ የስፔን ዜግነት ያላቸው ቴክኒሺያኖች ሲሆኑ አንዱ የደሴቷ ዜግነት ያለው ነዋሪ መሆኑ ታውቋል። መንግስት በሰጠው መግለጫ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ ያደረገ ሲሆን አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ በዋና ከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ዝግ ሆነዋል በሚል የተስፋፋው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው በማለት አስተባብሏል። የግድያው መነሻን ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ገልጾ እስካሁን ድረስ ያሉት መረጃዎች የሚያመለክቱት ግድያው የተካሄደው በግል ችግር ምክንያት ነው ብሏል። የቀድሞ የስፔን ኮሎኒ የነበረቸውና ከሴኒጋል ወደብ 500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የኬፕ ቬርዴ ደሴት  ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ የሚኖርባት አገር ነች ነው።

 

Ø የደቡብ ሱዳን አማጽያን መሪ ሚስተር ማቻር እንደተጠበቀው  ሚያዚያ 18 ቀን 2008 በአገሪቱ ዋና ከተማ  የገቡ ሲሆን ለምክትል ፕሬዚዳንትነቱ ስልጣን ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ በተናገሩት ቃል በሁሉም ወገን ላይ የተፈጠረው ቁስል ባስቸኳይ እንዲድን አድርገን ሕዝባችንን ወደ አንድነት ማምጣት አለብን ብለዋል። የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በሙሉ ልብ እንደሚሰሩና የእርቁ ሂደት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጥሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ሬክ ማቻርን ለመቀበል በተደረገው የአቀባበል ስን ስርዓት ላይ የደቡብ ሱዳን ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኬር በበኩላቸው “ ወንድሜን ማቻር ስቀበል ደስታ ይሰማኛል ካሉ በኋላ የአሳቸው ወደ ጁባ መመለስ የጦርነቱን ማብቃትና የሰላሙ ሁኔታን መጀመር እንደሚያበስር ጥርጥር የለኝም”  ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን የማቻር መመለስ ለሰላሙ ጥረት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸው የአንድነቱ መንግስት ባስቸኳይ ተመስርቶ ስራ መጀመር አለበት ብለዋል። ሁኔታው በሙሉ በሙሉ የተረጋጋ ባለመሆኑ የሰላሙን ጥረት ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። በየካምፑ ያሉት የሁለቱ ወገኖች ወታደሮች ከኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ማድረግ  ቀላል ስራ አይደለም።  ለሁለቱም ወገኖች ታዛዦች ያልሆኑ የሚሊሺያ ኃይሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ጦርነት እያካሄዱ ነው። በአንድነት መንግስቱ ውስጥ የሚነሱ ልዩነቶችንም በተገቢው መንገድ የማስተናገድ ኃላፊነትም ይኖራል። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች በአገሪቱ ውስጥ ውጥረቱ ከፍተኛ ውጥረት የሚታይ ሲሆን የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ወሳኝ ይሆናሉ በማለት አስተያየታቸው የሚሰጡ ወገኖች ብዙ ናቸው።

 

 

Ø በግብጽ በሲና ባህረሰላጤ መንገድ ውስጥ በተቀበረ ፈንጅ ሶስት የፖሊስ ሰራዊት አባላት የተገደሉ መሆናቸውን የግብጽ መንግስት የዜና ወኪል ገለጸ። ረቡዕ ሚያዚያ 19 ቀን 2008 ዓም በሲና ባህረ ሰላጤ የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አንድ ወታደራዊ መኪና የፈንጅው ጥቃት ደርሶበት የተገለበጠ ሲሆን ከሞቱት በተጨማሪ  8 ወታደሮች በጽኑ የቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል።  የቆሰሉት ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ለድርጊቱ ኃላፊነትን የወሰደ አካል የለም። ላለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው ጥቃት ሲፈጽም የቆየው የአይሲስ ቅርንጫፍ የሆነው ቡድን ድርጊቱን ሳይፈጽም አይቀርም ተብሎ ተጥርጥሯል።

በተያያዘ ዜና በግብጽ ዋና ከተማ በካይሮ ተገድሎ አስከሬኑ እንዳልነበር ሆኖ ተጥሎ የተገኘውን የጣሊያን ተወላጅ ጉዳይ አስመልክቶ የእንግሊዝ መንግስት ሰኞ ሚያዚያ 17 ቀን ባወጣው መግለጫ ላለፉት ሶስት ወራት የግብጽ መንግስት  ስለግለሰቡ ገዳዮች ያካሄደው ምርመራ ምንም ውጤት አለማስገኘቱ የእንግሊዝ መንግስትን ቅር ያሰኘ መሆኑን ገልጿል። መግለጫው የጣሊያን መንግስት ከግብጽ መንግስት የሚፈለገውን ትብብር አለማግኘቱ የእንግሊዝ መንግስትን ያሳዘነ መሆኑን ገልጾ ምንም እንኳ የግብጽ የጸጥታ ክፍሎች በግድያው ላይ አሉበት የሚለው ግምት የተረጋገጠ ባይሆንም ትክክለኛውን ገዳይ ለማወቅ ማናቸውም ጥረት እንዲደረግ ለዓለም አቀፍ ማህበርሰብ ጥሪ አስተላልፏል፡፤

 

 

 

ሚያዚያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም.

 

Ø ጋምቤላ 18 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባለው የደቡብ ሱዳን የጀዊ ስደተኞች ሰፈር የፈነዳው ግጭትና ግድያ ትላንትምቀጥሎ እንደነበር በቦታው ያሉ ምስክሮች ገልጸዋል ። በቦታው የሰፈሩት ስደተኞች መቶ በመቶ የደቡብ ሱዳንአማጽያን መሪ የሪያክ ማሻር ተከታዮችና የኑዌር ተወላጆች ሲሆኑ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሾፌርየነበረው ኢትዮጵያው ሁለት ስደተኛ ህጻናትን በመኪና ገጭቶና ገድሎ በመሰወሩ ኑዌሮቹ በሰፈሩ ያሉትንኢትዮጵያውያን ለመግደል ተነስተው ብዙዎችን እንደገደሉ ይታወቃል ። ከተገደሉት ውስጥ የስደተኛው ኮሚሽንኢትዮጵያዊ ሰራተኞችም እንዳሉበት ታውቋል። ጀዊ የአንዋኮች አካባቢ ስትሆን ወያኔ ኑዌሮችን በዚያ ያሰፈረውለተንኮል ነው ተብሎም ተጋልጧል። ወያኔ ከግድያው በኋላ ዜጎችን ለመከላከል ምንም እርምጃ ባለመውሰዱኢትዮጵያውያኑ ተደራጅተው የስደተኛውን ሰፈር ማጥቃታቸው ታውቋል። የሟቹ ቁጥርም ቀላል አልሆነም ።የተባበሩት መንግስታት የስድተኛ ኮሚሽን ሰራተኞቹን ከጀዊ አካባቢ አሽሽቷል። ግጭቱ ገና አልበረደም ሲል ዛሬምየደረስ ዜና ያረጋግጣል ።

 

Ø ወያኔ ለዘረፋና ለስርቆት እንዲያመቸው ከ 100 ሺ ሄክታር በላይ የጋምቤላ መሬትን ለጥጥ እርሻ በማለት ለንግድ ሸሪኮቹ በመስጠትና ለልማትም በማለት 3 ቢሊዮን ብድር በመፍቀድ የጥጥ ምርትን እናሳድጋለን በማለት ፕሮፓጋንዳውን ካሰራጨ ወዲህ የጥጥ ምርቱም ሳይኖር ልማቱም ሳይካሄድ ደን ተጨፍጭፎ ከቆየ በኋላ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ለምን ተግባር እንደዋለ እንኳ ለማወቅ አለምቻሉ ተገልጿል። ለጥጥ ልማት በማለት መሬት ወስደው ደን መንጥረው ገንዘብ ተበድረው ጠፉ የተባሉ ሰዎችና ኢንቬስተሮች እነማን እንደሆኑ ባይገለጽም  ወያኔ ምርመራና ማጣራት ጀምሬያለሁ ብሏል። ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች ግን ዘረፋውና  የተፈጥሮ ወድመቱ በወያኔ አባላትና በንግድ ሸሪኮቻቸው መፈጸሙን ይናገራሉ።

 

 

Ø በአባይ ወንዝ ግድብና አጠቃቀም ዙሪያ ወያኔና ግብጽ የገቡበትን የፖሊቲካና የዲፕሎማሲ ውዝግብ ለማብረድ በወያኔ ፓርላማ አፈጉባዔ የሚመራ አንድ የልኡካን ቡድን ግብጽንና ሱዳንን መጎብኘቱ ይታወሳል። የጉብኝቱ ዓላማ የታሰበለትን ግብ ይምታ አይምታ ባይታወቅም በወቅቱ የነበረውን የዲፕሎማሲ ውጥረት ግን ሳያለዝበው እንዳልቀረ ተገምቷል፡፤ ወያኔ ከሱዳን ጋር መልካም ወዳጀነት ፈጥሮ በድንበር አካባቢ ለም መሬቶችን አሳልፎ ከሰጠና ሱዳንም በአገሩ የሚገኙ የወያኔ ተቃዋሚዎችን እያፈነ ለወያኔ ለመስጠት ጥረት በሚያደርግበትና በሁለቱ አገሮች መካከል የድንበር ጥበቃ ውል ተፈርሞ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የሱዳን ሕዝብ ዲፕሎማሲ የተባለ ቡድን የወያኔን ባለስልጣኖችን እንደሚያነጋግር ተገልጿል። ጉብኝቱ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓም የሚጀመር ሲሆን የዲፕሎማሲው ቡድን ከወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ጀምሮ ከሌሎች የወያኔ ባለስልጣኖችን ያናገጋራል ተብሏል፡፤

 

Ø መጭውን የትንሳዔ በዓል አስታኮ የወያኔ አገዛዝ ሱቆችን በማደራጀት አባ ወራዎችን በቡድን እየመደበ እንደሚያሰማራ ታውቋል። ከአስራ አምስት እስከ ሃያ የሚደርሱ አባወራዎች በአንድና በሁለት ሱቆች ሸቀጦች እንዲሸጡ በማደራጀትና በማስገደድ ነዋሪዎንና የነጋዴው ህብረተሰብን ለማጋጨት እየተሞከረ መሆኑ ተገልጿል። ሱቆቹ በዋናነት ስኳርና ዘይት የሚያቀርቡ ሲሆን ሌሎች ሸቀጦችንም ሊጨምሩ እንደሚችሉ ተነግሯል። የወያኔ አገዛዝ በመላ ኢትዮጵያ ላንሳራፋው የኑሮ ውድነት ተጠያቂ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የችግሩ መነሻና ምንጭ የነጋዴው ህብረተሰብ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ ነጋዴዎችን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሸማቾች ማህበራትን ማቋቋሙ ይታወቃል። የፋሲካ በዓልን ተንተርሶ እንደ ቅቤ እንቁላል ዶሮ በግና በሬዎች የመሳሰሉ የምግብ አቅርቦቶች ዋጋ ጭማሪ እያሳየ መሆኑ ታውቋል።

 

Ø ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለወያኔ ማስረከብ የለመደበት የኬንያ መንግስት የታይዋን ተወላጅ ሆነው በህገወጥነትየወነጀላቸውን የታይዋን ተወላጆች አስሮ ለሀገራቸው ሳይሆን ለቻይና ማስረከቡ ተጋለጠ። ቻይና ታይዋን ግዛቴ ናትብትልም ቻይናና ታይዋን ሁለት የተለያዩ ሀገሮች ሆነው እንድሉ ይታወቃል። ወያኔ በበኩል ኬንያ እንደ የመንየሚመጡ ተቃዋሚዎችን አግታ እንድታስረክብ ዝርዝር ስሞችን ሰጧል ተብሎም መረጃ አለ ።

 

 

 

Ø ከጥቂት ቀናት በፊት በብሩንዲ አንድ የጄኔራል ማእርግ ያላቸው ከፍተኛ ባለስልጣን ከነባለቤታቸው ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን  ገዳዮችን አፈላልገው እንድይዙ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለወታደሮቻቸው የአንድ ሳምንት የጊዜ ገደብ ያለበት ጥብቅ መመሪያ የሰጡ መሆናቸው ታውቋል።  ፕሬዚዳንቱ ለሟቾቹ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን የአገሪቱ የጦር ኃይልም አንድነቱን አጠናክሮ ሁኔታውን በቁጥጥር ስር እንዲያደርግ ተማጽነዋል። የፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ በብሩንዲ እየተካሄደ ያለውን ግድያ ያፋፍማል የሚል ስጋት ፈጥሯል። የብሩንዲ የእርስ በርስ ግጭት ከጀመረ ወዲህ የመንግስት ባለስልጣኖች ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ሲገደሉ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ደግሞ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ እያካሄዱ ከመሆናቸውም በላይ በርካታ ሰዎችን አስረው ሰቆቃዊ ድርጊት እየፈጸሙባቸው መሆኑ ይነገራል። 

 

Ø በሱማሊያ ከዋናዋ ከተማ ከሞጋዲሾ ሰሜን ምዕራብ 250 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ከባይደዋ ከተማ አጠገብ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት እና የሱማሊያ መንግስት የጦር ካምፕ ላይ አልሸባብ ጥቃት ሰንስዝሮ ቢያንስ 20 ወታደሮችን የገደለ መሆኑ ከስፍራው የተገኘው ዜና ይገልጻል። ከተወሰነ የተኩስ ልውውጥ በኋላም የአፍሪካ ህብረት የሰላም አሰከባሪ ሃይሎች እና የሱማሊያ ወታደሮች የጦር ሰፍሩን መልሰው መቆጣጠራቸው ተነግሯል።  የአልሸባብ አጥቂዎችም ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ቢገልጽም ከአልሸባብ በኩል የተሰማ ዜና የለም።

 

Ø መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሰብአዊ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ በሱማሊያ የገባውን ከፍተኛ ድርቅና ረሃብ ለመቋቋም አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ድርጅቶቹ በጋራ መግለጫቸው ላለፉት አራት አመታት በሱማሊያ ዝናም በመጥፋቱ ምክንያት ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ መሰደዱን ገልጸው ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ከፍተኛ እልቂት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል። ከስድስት ዓመት በፊት በሱማሊያ በገባው ድርቅ ምክንያት ከ250 ሺ ሰው በላይ የሞተ መሆኑን አስታውሰው ተመሳሳይ የሕዝብ እልቂት እንዳይደርስ ከፍተኛ እርዳታ መሰብሰብ አለበት ብለዋል።

 

Ø ከጥቂት ቀናት በፊት ከአንድ የቱርክ የንግድ መርከብ ላይ በባህር ላይ አፋኞች ተጠልፈው ተወስደው የነበሩ ስድስት የመርከቡ ሰራተኞች የተለቀቁ መሆናቸውን የንግድ መርከቡ ባለስልጣኖች ገልጸዋል። ሚያዚያ 3 ቀን 2008 ዓም. ማንነታቸው ያለታወቀ የባህር ላይ አፋኞች መርከቧ ላይ በመውጣቱ ካፕቴኑ የሚገኝበትን ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማድረጋቸው የታወቀ ሲሆን ማክሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2008 ለቀዋቸዋል ተብሏል። የተለቀቁት የመርከቧ ሰራተኞች በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ መሆናቸው ቢነገርም ለመለቀቃቸው ካሳ መከፈሉ እና አለመከፈሉ የተገለጸ ነገር የለም። በዚህ ዓመት ብቻ በናይጄሪያ ወደብ አካባቢ ከ32 በላይ የመርከብ ጠለፋዎች የተካሄዱ መሆናቸው ከተባበሩት መንግስታ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አካባቢ የተገኙ ዜናዎች ይጠቁማሉ።

 

Ø የደቡብ ሱዳን አማጽያን መሪ ሪክ ማቻር ለአንድ ሳምንት ያህል ጉዟቸው ካዘገዩ በኋላ በዛሬው ቀን ጁባ ገብተዋል። የአማጽያኑ ድርጅት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ ሚስተር ማቻር ዛሬ ሚያዚያ 18 ቀን  ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ጁባ የሚገቡ መሆናቸውን ገልጾ የነበረ ሲሆን  በታቀደው መሰረት ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ቦታ ለመያዝ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል ተብሏል። ሚስተር ማቻር ጁባ ይገባሉ ተብሎ ታቅዶ የነበረው ሚያዚያ 10 ቀን የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ በታቀዱት ቀናት ወደ ጃባ ባለመለሳቸው  በዓለም አቅፉ ህብረተሰብ በሌሎች ላይ ከፍተኛ  ስጋት ፈጥሮ እንድነበር አይዘነጋም።

 

 

 

 

ሚያዚያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም.

Ø የእንግሊዙ ዕለታዊ ጋዘጣ ዘ ቴሌግራፍ የእርዳታ ድርቶችንና በመስክ ላይ ያሉ ሰራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ያለው ድርቅና ረሃብ ከ18 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን እያጠቃ መሆኑን ግልጽ አድርጓል። እስከ አሁን ድረስ በወያኔና በዕርዳታ ድርጅቶች በኩል የረሃብና የድርቁ ተረጅ ወገኖች ቁጥር እስከ 12 ሚሊዮን ይገመት እንደነበር ይታወቃል። በአዲሱ አሀዝ መሠረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ 20 ከመቶ የሚሆነው በአሁኑ ጊዜ የእርዳታ ፈላጊ አድርጎታል። የወያኔ ባለስልጣኖች የተረጅውን ሕዝብ ቁጥር መጨመር ደፍረው ባያናግሩትም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ  ለረሃብና ለድርቁ የሚሰጠው ዕርዳታ ከተረጅው ቁጥር ጋር አይመጣጠንም በማለት አድበስብሰው ለማለፍ ሙከራ እያደረጉ መሆኑ እየተነገረ ነው።

Ø በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች በመቶ የሚቆጠሩ ገድለው በመቶ  በሚቆጠሩ ህጻናት አፍነው ከወሰዱና በሺ የሚቆጠሩ ከብቶችን ከነዱ ወዲህ በጋምቤላ ያለው ዘግናኝ እልቂት የዓለም ሕዝብ ዓይንና ጆሮ እየሳበ ነው።  በጃዊ ስደተኛ ጣቢያ አቅራቢያ አንድ ኢትዮጵያዊ አሽከርካሪ የደቡብ ሱዳን ስደተኛ ላይ የመኪና አደጋ በማድረሰ ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል ምክንያት በካምፕ ውስጥ የነበሩት  ስደተኛች አብዛኞቹ የኦሮሞ እና የአማራ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን  በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው የሚታወስ ሲሆን ድርጊቱን ለመቃወም አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የወያኔ ፖሊሶችና ወታደሮች  በወሰዱት እርምጃ ግድያና የመቁሰል አደጋ ማድረሳችው ታውቋል። ለተቃውሞ ከወጡት መካከል 5 መገደላቸውና ከ 15 በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል። በጋምቤላ ውጥረቱ እየከረረ ሲሆን ቁጣውም እየባሰ መምጣቱ ይነገራል ወያኔ በስደተኞቹ ስም የሚሰጠው ገንዘብ እንዳይጓደልበት ጥቃቱን ችላ ከማለቱም በላይ እያባባሰው ይገኛል።

Ø በግብጽ በተለያዩ ቡድኖች የተድራጀና የተቀናጀ ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ ስልፍ መታቀዱን ተከትሎ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ሲሲ ሰልፉን ለማስቆም በቴሌቪዥን ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።  የግብጽ ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ መዳከምና እንዲሁም የጸጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ በሚወስዱት አፈና ምክንያት መማረሩን በመግለጸ ተቃውሞ እያሰማ ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሁለት በግብጽ ቁጥጥር ስር ያሉ ደሴቶችን የሲሲ መንግስት ለሳኡዲ አረቢያ መስጠቱ ደግሞ ምሬቱ ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል። የተለያዩ ቡድኖች የተቃውሞ ስልፍ ለማድረግ መወጣናቸው በመታወቁና ሰልፉም ሊያስከትለው የሚችለው ከፍተኛ ችግር ስጋት ስለፈጠረ ፕሬዚዳንት ሲሲ በይፋ ማስጠንቀቁያ መስጠት ተገደዋል። በንግግራቸው ላይ “የግብጽን መጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎች እንደገና ጸጥታዋን ለማድፍረስ እየተዘጋጁ ነው ካሉ በኋላ የኛ ተግባር የህዝቡን ደህንነትና ጸጥታ መጠበቅ ስለሆነ አስፈላጊውን ርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል። የጸጥታ ኃይሎች በተለያዩ ቦታዎች የተሰማሩ ሲሆን ሰላማዊ ስልፎችን ያደራጃሉ፤ ግለሰቦችን ይቀሰቅሳሉ ብለው የሚገምቷቸውን ግልሰሰቦችን ጋዜጠኞችንና የህግ ባለሙያዎችን ከየቤታቸው በመልቀም ያሰሯቸው መሆኑ ታውቋል።  በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከ 1000 ሰዎች በላይ የተገደሉ ሲሆን ወደ 40 ሺ የሚገመቱ ሰዎች መታሰራቸውም ይነገራል።

 

Ø በብሩንዲ የተናጠል ግድያው እየቀጠለ መሆኑ ተገለጸ። ሰኞ ሚያዚያ 16 ቀን 2008 ዓ..ም የብሩንዲ ምክትል ፕሬዚዳንት የጸጥታ አማካሪ የሆኑት ጄኔራል ካሩዛ እና ባለቤታቸው በመኪና ልጃቸውን ትምህርት ቤት ካደረሱ በኋላ ባልታወቁ ሰዎች የተገደሉ መሆኑ ተነግሯል። ለድርጊቱ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም። ባለፈው ነሐሴ ወር የፕሬዚዳንቱ የግል የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ጄኔራል ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም። እሁድ ሚያዚያ 15 ቀንም የብሩንዲ የሰብአዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከቤተክርስቲያን ሲወጡ ቦምብ ተወርውሮባቸው ሳይጎዱ በህይወት ሊያመልጡ ችለዋል።  በብሩዲ በተለይ በከፍተኛ ባለስልጣኖችና የጦር መኮንኖች ላይ የሚካሄደው የተናጠል ግድያ የብሩንዲን ፕሬዚዳንት አስተዳደር እያናጋው ነው ተብሏል። የብሩንዲ የውስጥ ችግር ከጀመረ ጀምሮ ከ400 በላይ የሆኑ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።

በተያያዘ ዜና ሄግ የሚገኘው የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በብሩንዲ እየተካሄዱ ባሉ ወንጀሎች ላይ ክስ ለመስረት አቃቤ ህጉ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናትና ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።  የመጀመሪያ ደረጃው ጥናት እንደተጠናቀቀ ሙሉ የሆነው የምርመራና ማስረጃ የማሰባብ ስራ የሚጀመር መሆኑና  ጥፋተኛ ናቸው ተብለው የሚከሰሱ ሰዎችም ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተነግሯል።

 

Ø በዳርፉር ለሶስት ተከታታይ ቀኖች በተካሄደ የውሳኔ ሕዝብ ምርጫ አብዛኛው ሕዝብ ዳርፉር  በአምስት ክልሎች መከፋፈሏን መደገፉን የሱዳን መንግስት ገልጿል። በመንግስቱ መግለጫ መሰረት በተካሄደው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው መካከል በምርጫው የተሳተፈው 97 በመቶ የሚሆነው እንደሆነ ሲነገር ድምጽ ከሰጠው መካከል ደግሞ 98 በመቶ የሚሆነው መራጭ ዳርፉር ለአምስት ክልሎች መከፋፈሏን መርጧል ተብሏል። በርክታ ተፈናቃዮች ድምጽ መስጠት በማይችሉበት ሁኔታና  ኃይልና ማስፈራሪያ በሰፈነበት ሁኔታ የሚካሄድ የውሳኔ ሕዝብ ምርጫ እውነተኛ የሕዝብ ፍላጎት አያንጸባርቅም በማለት አማጽያኑ ኃይሎች ምርጫው እንዳይካሄድ አድማ ያደረጉ ሲሆን የምዕራብ አገሮችም የጸጥታው ሁኔታ ለነጻና ርቱዓዊ ምርጫ ምቹ ባለመሆኑ ምርጫው መካሄድ የለበትም ማለታቸው ይታወሳል። የሱዳን መንግስት ባለስልጣኖች ምርጫው የአረብ አገሮችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ባሉበት የተካሄደ በመሆኑ የሕዝቡን እውነተኛ ስሜትና ፍላጎት ያንጸባርቃል እያሉ ናቸው።

 

 

 

ሚያዚያ 15 ቀን 2008 ዓ.ም

Ø በጋምቤላ ንጹሃን ዜጎች ድንበር ተሻግረው በመጡ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እልቂት ከተፈጸመባቸው አንድ ሳምንት ባስቆጠረበትና በታጣቂዎቹ ታግተው የተወሰዱ ህጻናት ጉዳይ አሁንም ምንም ምላሽ ባላገኘበትና እንዲሁም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ድርጊቱን አውግዞ ህጻናቱ አለምንም ቅደመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረበ ባለበት ሰዓት ደቡብ ሱዳናውያን አሁንም 14 ኢትዮጵያውያንን መግደላቸው ታውቋል። ግድያው የተፈጸመው ከጋምቤላ ከተማ 17 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ጃዊ የስደተኞች ካምፕ አቅራቢያ መሆኑ የተነገረ ሲሆን መንስኤው አንድ ኢትዮጵያዊ ሹፌር በአንድ የደቡብ ሱዳን ስደተኛ ላይ የመኪና አደጋ በማድረሱ ነው ተብሏል። በአራቢያው የነበሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ለአደጋው ምላሽ በአቅራቢያው የነበሩ 14 ኢትዮጵያውያንን በጭካኔ ገድለዋል። በስደተኛ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት ደቡብ ሱዳናውያን ግድያውን የፈጸሙት በገጀራ በድንጋይ በቢላዋ መሆኑ ሲታወቅ አንድም የወያኔ ፖሊስ ሆነ ወታደራዊ ኃይል ወደ አካባቢው አለመላኩ ብዙዎችን አስገርሟል።

Ø ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በተገኘው መረጃ በመንግስት ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ሲያገለግሉ የነብሩ 1500 የአዲስ አበባ መምህራን የስራ መልቀቂያ አስገብተው 700 ያህሉ መሰናበታቸው ተገልጿል። መምህራኑ በሚደርስባቸው የፖሊቲካ ጫና የደሞዝ ማነስና ዓይን ያወጣ የዘር መድልዎ የተነሳ በመማር ማስተማሩ ሂደት መቀጥል ባለመቻላቸው ሥራውን ለመልቀቅ መገደዳቸው ታውቋል። መምህራን ወያኔ ባሰማራቸው የደህንነት መስርያ ቤት ባልደረባ ምመህራንና በወያኔ ስር በተደራጀ የወጣት ማህበራት ሰላዮች ክትትል እንደመደረግባቸው ታውቋል።

Ø የታንዛኒያ ባለስልጣኖች በታንዛኒያ የእስር ዘመናቸውን የጨረሱትን 74 ኢትዮጵያውያን በኬኒያ ድንበር ላይ በመጣላቸው በኬኒያ እና በታንዛኒያ መካከል ውዝግብ የቀሰቀሰ ከመሆኑ በላይ የኬኒያ ፖሊስ ስድስት ኢትዮጵያውያንን በህገ ወጥ መንገድ አገር ውስጥ ገብተዋል በማለት ማሰሩን አርብ ሚያዚያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም.በሰጠው መግለጫ ገልጿል።  እንደ ኬኒያ ፖሊስ ከሆነ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሞምባሳ በኩል አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊጓዙ ሲሉ በጥቆማ መያዛቸው ሲታወቅ ከስደተኞቹ ጋር አንድ የኬኒያ ሹፌርም አብሮ ተይዟል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ያለ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ኬኒያ በመግባት ወንጀል ሲከሰሱ የኬኒያው ሾፌር ደግሞ ስደተኞችን በማስረግ ወንጀል እንደሚከሥ ተጠቁሟል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የከፋ መከራና ስቃይ ይደርስባቸው እንደነብር የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ ስደተኛነታቸው እንደ ጥፋት እየተቆጠረ መታሰር እየተለመደ በመጣቱ ድምጽ አልባ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁሉም ወገን በሚችለው አቅሙና መንገድ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ኤጄንሲ እንዲያሳውቅ ሀገር ወዳድ ዜጎች ጥሪ ያቀርባሉ።

Ø የሶማሊያው አልሸባብ ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ዓም ስድስት የወያኔ ወታደሮችን መንገድ ላይ በተቀበረ ፈንጅ መግደሉን አስታውቋል። የፈንጅ አደጋውን በደቡባዊ ባይ ግዛት ውስጥ አውደሊን ከተማ አቅራቢያ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በጥቃቱ ወቅት የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ያሰማራቸው ሰላም አስከባሪ በወታድር አጀብ ይጓዝ እንደነበረና ከሞቱት የወያኔ ወታደሮች ውስጥ ከፍተኛ አዛዦች እንደሚገኙበት አብራርቷል። በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል አልሸባብ አደረስኩ ስለሚለው ጥቃት የተናገረው ነገር የለም። የወያኔ አገዛዙም እንደተለመደው የተነፈሰውና ያለው ነገር አልተመዘገበም።

Ø የደቡብ ሱዳን አማጽያን መሪ ሚስተር ሪክ ማቻር ቅድሜ ሚያዚያ 15 2008 ዓ.ም.  ጁባ እንዲገቡ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሰጠውን ቀነ ቀጠሮ አሁንም ያልተከበረ መሆኑ ታውቋል። ባለፈው ዓመት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሚስተር ማቻር ጁባ እንዲገቡ ታቅዶ የነበረው ሚያዚያ 10 ቀን 2008 መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አጅበው በሚገቡ ወታደሮች ብዛት ላይ እና ሊይዟቸው በሚችሉ የመሳሪያ ዓይነቶች ላይ ከሱዳን መንግስት ባለስልጣኖች ጋር ስምምነት ባለመደረሱ ጉዟቸው የዘገየ መሆኑ ተነግሯል፡፤ ትናንት አርብ ሚያዚያ 14 ቀን 2008 ዓም በነፍስ ወከፍ ኤኬ 47 አውቶማቲክ መሳሪያ ከታጠቁ 190 አጃቢዎች  እና 20 መትረየሶችና ከ20 አርፒጂ ጋር እንዲገቡ ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ በሚቀጥለው ሳምንት ጁባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር እንደገለጹት ሚስተር ሪካ ማቻር የሚጓዙበት አውሮፕላን ወደ ክልሉ እንዲገባ የሚፈቀድለት ከጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ከመነሳቱ በፊት የሚመጡት ሰዎች ቁጥርና የያዙት መሳሪያ በስምምነቱ መሰረት መሆኑን የዓለም አቀፍ ድርጅት አባላት ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ ብቻ ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እንዲሁም አሜሪካ እንግሊዝ እና ኖርዌይ ሚስተር ሪክ ማቻር እንዲመለሱ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተነግሯል።

 

Ø በግብጽ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሀመድ ሞርሲ የካታር መንግስት ሰላይ ናቸው በሚል ቀርቦባቸው የነበረው ክስ ዛሬ ሚያዚያ 15 ቀን ሊታይ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ዝግጅት ያስፈልጋል በሚል ለሚያዚያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ያስተላለፈው መሆኑ ተነግሯል። ካታር የሚስተር ሞርሲን አስተዳደርና የግብጽን የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ስትረዳ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን  የፕሬዚዳንት ሲሲ አስተዳደር ካታር በግብጽ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች በሚል ክስ ትታሰማ መቆየቷም ይታወቃል። በፕሬዚዳንት ሲሲ እና በተባባሪዎቻቸው አማካይነት በተካሄደ ወታድራዊ መፈንቅለ  መንግስት በስልት ከስልጣናቸው የተነሱት ሞርሲ ከዚህ ቀደም በሶስት የተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የሞት ፍርድ፤ የእድሜ ልክ እስራትና የሃያ አመታት እስራት የተበየነባቸው መሆኑ ሲታወቅ ይህኛው ክስ አራተኛው መሆኑ ነው። ሞርሲ እና ሌሎች አስር ሰዎች የግብጽ የጸጥታ ሁኔታን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ ሰነዶች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብለው ከካታር ሸጠዋል የሚል ክስ አቃቤ ህጉ ያቀረበባቸው መሆኑ ታውቋል።

 

Ø በዚህ ሳምንት በማሊ በአማጽያን ታግተው የነበሩ ሶስት የቀይ መስቀል ሠራተኞች አለምንም ቅደመ ሁኔታ የተለቀቁ መሆናቸው ተነገረ። በሰሜን ማሊ የሚንቀሳቀሰውና ከአልካይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው አንሳር ዲን የተባለው ድርጅት ባለፈው ሐሙስ በሰጠው መግለጫ ሰራተኞቹን ያገተው ድርጅቱ መሆኑንና ሊፈቱ የሚችሉት በፈረንሳይ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ያለው ሚያቴን አግ ማያሪስ የተባለው የድርጅቱ አባል ሲፈታ ብቻ መሆኑን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል። አርብ ዕለት ታግተው የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች መለቀቃቸው የተነገገረ ሲሆን ሊለቀቁ የቻሉትበፈረንሳይ ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኘው ግለሰብ ስለተለቀቀ ይሁን አይሁን አልታወቀም። ሰላም በማስከበር ስም ፈረንሳይ በሰሜን ማሊ ከ3500 በላይ የሆኑ ወታደሮች እንዳላት ይታወቃል።

 

Ø በምስራቅ ሊቢያ ራሱን መንግስት ነኝ የሚለው ክፍል ፓርላማ በተመድ አማካይነት የተቋቋመውን መንግስት ለመደገፍ ውደ ኋላ ሲል መቆየቱ ይታወሳል። ባለፈው ሐሙስ 198 ከሆኑት የምክር ቤቱ አባላት መካከል 108 የሚሆኑት የአንድነት መንግስቱን መደገፋቸውን በመግለጽ መግለጫ ያወጡ ቢሆንም በዙዎቹ በግል ማስፈራሪያ ስለደረሳቸው ድምጽ ሊሰጥበት የሚችል ስብሰባ ማካሄድ ያልቻሉ መሆኑ ተገልጿል። አርብ ሚያዚያ 14 ቀን የምዕራብ መንግስታት አምባስደሮች በሰጠቱ መግለጫ ማስፈራሪያውን በጽኑ አውግዘው አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት የተደረገባቸውን ተጽእኖ ተቋቁመው ድምጻቸውን ለማሰማት መቻላቸውን አወድሰዋል። ምከር ቤቱ ተሰብቦ ውሳኔዎችን በህጋዊ መንገድ እንድያስወስንም ተማጽነዋል።

 

 

 

ሚያዚያ  14 2008 ዓ ም

Ø በጋምቤላ የደረሰውን አሰቃቂና ዘግናኝ እልቂት በመቃወም ዜጎች በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሰንጋ ተራ በሚባለው አካባቢ ተማሪዎች ፊታቸውን ጥቁር ቀለም በመቀባት በጋምቤላ የደረሰውን ፍጅት በመቃወወም አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግ እየጠየቁ ባለበት ሰዓት ከሆቴል ደ  አፍሪክ ከሚባለው ሆቴል አካባቢ የነበረው የወያኔ የፖሊስ ኃይል ተማሪዎቹን በዱላ በመደብደብ ማባረሩን በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ተናግረዋል። እነዚህ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡና  በራሳቸው ፍላጎት ለወገኖቻቸው ሞትና መታፈን የቆሙ ወገኖች መደብደባቸው ብቻ ሳይሆን ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል።

 

Ø በጋምቤላ የተፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት ተከትሎ ልዩ ልዩ አገራትና ድርጅቶች የውግዘት ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት ፍጅቱን በማውገዝ የታገቱት ህጻናት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ መጠየቁን የዘገብን ሲሆን ሀሙስ ዕለትም የአውሮፓው ህብረት በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት እንዲፈቱ ጥሪ አድርጓል። የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣኖች ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተው የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በአስቸኳይ የታገቱት ልጆች ወደ ቤተሰባቸው እንዲመለሱ ጥረታቸውን እንዲጨምሩና ፍጅቱን ያካሄዱት ለህግ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

 

 

Ø የጋምቤላውን እልቂት ተከትሎ የደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣኖች እርስ በርስ መካሰስ መጀመራቸው ታውቋል።የሱዳኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ጀኔራሎች ለጋምቤላውፍጅት የቦማ ግዛት ኃላፊዎችን ተጠያቂ አድርገዋል። የቦግዛት ገዥ ባባ ሜዳ ለጥቃቱ ጀርባ እንደሆኑ የመርሌ ጎሳአባል የሆኑት ሌ/ጄኔራል ዲቪድ ዋዩ ተናግረው መረጃውን ከአካባቢው መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የቦግዛት ኃላፊዎች ለእልቂቱ የጦር መሳሪያ በማቀበል በኑር ጎሳ አባላት ላይ ጥቃቱ እንዲፈጸም አስተባብረዋል በማለትየቦማ ባለሥልጣኖች የያገተቱን ህጻናት በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል። የቦማ ግዛት ኃላፊዎች ግን የተሰነዘረባቸውንክስ በማስተባበል በጋምቤላው ጥቃት እጃቸው እንደሌለና በግዛቱ ያሉ ታጣቂዎችም የደቡብ ሱዳን ጦር አባል ሆነውመካተታቸውን ተናግረዋል።

 

Ø ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ዓም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ባወጣው ዘገባ ባለፈው ታህሳስ ወር የናይጄሪያ ወታደራዊ ተቋም  350 የሚሆኑ የሺያ እስላም ተከታዮችን ገድሏል፣ አስከሬናቸውን በአንድ ጉድጓድ ውስጥ በጅምላ ቀብሯል፣ እንዲሁም ድርጊቱን ለመሸፈን የተለያይ እርምጃዎችን ወስዷል በማለት ወንጅሎታል። የሰብአዊ ድርጅቱ በመግለጫው ላይ ሟቾቹ የተገደሉት የአንድ ወታደራዊ ክፍል መሪ የነበሩትን ጄኔራል ለመግደል ሙከራ ሲያደርጉ ነው በሚል ከናይጄሪያ መከላከያ ተቋም የተሰጠውን ምክንያትም መሰረተ ቢስ ነው በማለት አጣጥሎታል። የናይጄሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል  በአምነስቲ የቀረበው ዘገባ ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የተዘጋጀ አለመሆኑን ገልጾ ዘገባውን ከማውጣቱ በፊት ስለዝርዝሩ ሊያሳውቀንና አስተያየታችንን ሊጠይቅ ይገባው  ነበር ብሏል። ትክክለኛ መረጃ አለን ካሉ ያቅርቡና ያሳምኑን የሚል ቃልም አሳምቷል።  ባለፈው ታህሳስ ወር የኢስላሚክ ሙቭመንት ኦፍ ናይጄሪያ የተባለው የሺያ ሙስሊም ድርጅት  አባላት በሰሜን ናይጀሪያ ውስጥ በጸሎት ላይ እያሉ በነበረት ወቅት የወታደራዊ ተቋም መሪ የየሆኑት ጄኔራልን አጅቦ የነበረው ኮንቮይ በአካባቢው እንዳያልፍ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ በማሰማታቸው  ወታደሩ በወሰደው የበቀል እርምጃ ከ350 ሰዎች በላይ ለመግደል ችሏል ተብሏል። ይህንንም ሀቅ ባለፈው ሳምንት አንድ የናይጄሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን የመሰከረ  መሆኑ ተገልጿል። አምነስቲ ኢንተናሽናል በዘገባው ላይ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ተካሄዶ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለው ቃል ቢገቡም እስካሁን የተወሰደ እርምጃ የለም ሲል  ዘግቧል። እንዲያውም በተጻራራው  የናይጀሪያ የዜና አውታሮች ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን  በዘገቡት ዜና ካዱና በተባለችው ከተማ 50 የሚሆኑ የሺያ እምነት ተክታይ አባላት አንድ ወታደር ገድለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የሞት ቅጣት እንዲፈጸምባቸው እየተጠየቀ መሆኑ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በተሰደዱ ዜጎች ካምፕ አጠገብ አንዲት የቦኮ ሃራም አጥፍቶ ጠፊ ባፈነድችው ቦምብ ሰባት ሰዎች የተደሉ መሆናቸውን የናይጄሪያ ወታደራዊ ተቋም ቃል አቀባይ ሐሙስ ዕለት ከሰጠው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል። የቦምቡ ፍንዳታ የደረሰው ባለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 12 ቀን 2008 ዓም በንጋቱ ላይ ሲሆን ማይዱጉሪ ከተባለው ከተማ 130 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የናይጄሪያና የካሜሩን ወሰን ላይ ነው። ቦምቦችን ለማፈንዳት  ቦኮ ሃራም ከላካቸው ሁለት ሴቶች መካከል አንደኛዋ የያዛቸውን ቦምብ ሳታፈንዳ እጅ ከፍንጅ ተይዛለች ተብሏል። ቦኮሃራም አእምሮ የሚመረዝ እጽን እየሰጠ ቦምብ እንዲያፈነዱ የሚልካቸው ሴቶችና ህጻናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ይታወቃል።

 

Ø ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ይፋ ባደረገው ዘገባ በግብጽ ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ያሉ እስረኞች ሰቆቃዊ ድርጊት እየተፈጸመባቸው መሆኑን አጋልጧል። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት ህጻናት መሆናቸውንም ገልጿል። የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ዘገባ ባለፈው የካቲት ወር ህገ ወጥ በሆኑ የተቃዋሚ ስልፎች ላይ ተሳትፋችኋል፤ የንብረትና መዝረፍና የማቃጠል ወንጀል ፈጽማችኋል ተብለው  በአሌክሳንድሪያ የታሰሩ ዜጎች በእስር ላይ እያሉ ከፍተኛ ድብደባና የአካል ስቃይ የደረሰባቸው መሆኑን ለቤተሰቦቻቸው መናገራቸውን ዘግቧል። ድርጅቱ ከ20 በላይ በሚሆኑ እስረኞች ላይ ድብደባ እንደተፈጸመ መረጃ የደረሰው መሆኑን ገልጾ የግብጽ መንግስት ከፍተኛ ድብደባ የፈጸመባቸው እስረኞች በቁጥጥር ስር መደረጋቸውን በመጀመሪያ ክዶ የነበረ መሆኑን የሰብአዊ መብት ድርጅት መግለጫ ያጋልጣል። የግብጽ ባለስልጣኖች ዘገባው የፈጠራ መረጃው የያያዘ ነው በማለት አጣጥለውታል።  ወታደራዊ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ በዜጎች ላይ የሚወስደው አሰቃቂ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በየጊዜው የተገለጸ ሲሆን ባለፈው ዓመት በቁጥጥር ስር የሚገኙ እስረኞችን በድብደባ  ገድላችኋል ተብለው በርካታ የግብጽ ፖሊሶች ክስ ተመስርቶባቸው የተፈረደባቸው መሆኑ ይታወሳል።

 

Ø የቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዲቢ ለአምስተኛ ጊዜ በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የተቀዳጁ መሆኑ ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ተነገረ። ኢድሪስ ዲቢ  የድምጹን 60 ከመቶ በማግኘት  17 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎቻቸውን አሸንፈው ነው ድል ተቀዳጅተዋል የተባለ ሲሆን ያገኙት ከድምጹ 50 ከመቶ በላይ በማግኘታቸው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄድ አላስፈለጋም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው የተጭበረበረ ስለሆነ አንቀበለውም ብለዋል። በርካታ የምርጫ ሳጥኖች የተሰረቁ መሆናቸውንና ፤ ወታደሮችን ጨምሮ ኢድሪስ ዲቢን  በመቃወም ድምጽ የሰጡ ግለሰቦች መታሰራቸውና መዳረሻቸው መጥፋቱን ተናግረዋል። የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ነው ቢሉም በርካታ ሰዎች ያልተዋጠላቸው መሆኑ ታይቷል። በምርጫው ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በሞባይል ስልኮች መልክቶችን መለዋውጥ ሳይቻል ቀርቷል። ከጥቂት ቀናት በፊት አራት የሲቪል ማህበራት መሪዎች ሕዝቡን ለስላማዊ ስልፍ አነሳስታችኋል በማለት መታሰራቸው ይታወሳል። ምርጫው የተካሄደው የሆስፒታል ሰራተኞች የትምህርት ቤት አስተማሪዎችና የዩቢቨርስቲ ፕሮፈሰሮች የተወዘፈ ደሞዛቸው እንዲከፈል የስራ ማቆም አድማ ባደረጉበት ወቅት ነው። ቻድ በ1995 ዓም በአገሪቱ የተገኘውን የነዳጅ ምርት መጠቀም ብትጀምርም 13 ሚሊዮን የሚሆነው የአገሪቱ ዜጋ ከድህነት በታች በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖር ሲሆን  ከቻድ ዜጎች መካከል ከ 10 ሩ  ሰባቱ መጻፍ እና ማንበብ እንደማይችሉ መረጃዎች ይፋ አድርገዋል።

 

 

Ø 36 የጋምቢያ  የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ሐሙስ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው በልዩ ልዩ ወንጀሎች የተከሰሡ መሆናቸው ተገለጸ፡፤ የዩናይትድ ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ሚስተር ዳርቦይ ከተከሰሱት መካከል አንዱ ሲሆኑ ተካሶቹ በስድስት የተለያዩ ክሶች የተከሰሱ መሆናቸውና በዋስ ለፈቱ መቻላቻውና አለመቻላቸው በሚቀጥለው ሳምንት እስከሚወሰን ድረሰ በእስር ቤት እንዲቆዩ የተደረገ መሆኑም ተነግሯል። የዩናይትድ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ጸሐፊ ሚስተር ሳንዴንግ እና ሌሎች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ያልተፈቀደ ሰላማዊ ስልፍ አደራጅታችኋል በሚል ሰበብ የታሰሩ መሆናቸው ሲታወቅ ግለሰቡና ሌሎች ሁለት ሴቶች በእስር ቤት በድብደባ ህይወታቸው ያለፈው መሆኑ ተነግሯል። የፓርቲው መሪ ሚስተር ዳርቦይ እና ሌሎች ተከሳቾች የታሰሩት ባለፈው ቅዳሜ ቀደም ብለው የታሰሩት አባሎቻቸው የታሰሩበት ምክንያት አለአግባብ አለመሆኑን ለመግለጽ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ነው ። የአፍሪካ የሂውማን ራይትስ ኮሚሽን እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የታሰሩትን  ለመጎብኘት እንዲችሉ ፈቃድ የጠየቁ መሆናቸው ታውቋል። 

 

 

 

ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም.

Ø ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የጋምቤላ እልቂት በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱ ሕጻናት ሊገኙ አለመቻላቸው አጠያያቂ እየሆነ ነው። ዓለም አቀፍ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሲኤፍም ከጋምቤላ የተጠለፉ ሕጻናት አለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አድርጓል። በጋምቤላው እልቂት ከ200 ሰው በላይ ተገድለው በመቶ የሚቆጠሩ ቆስለው ከ20 ሺ በላይ ከቀየው ተፈናቅሎ መሰደዱም ታውቋል። የወያኔ መሪዎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉት ዜጎች የሚያደርጉት እንክብካቤ በጋምቤላ ካሉት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በጣም ያነሰ እንደሆነ እየተገለጸ ሲሆን የወያኔ ወታደራዊ አለቆች ህጻናቱን ለማስለቀቅ ፍንጭ አግኘተናል አካባቢውን እየከበብን ነው ይበሉ እንጅ ዝርዝር ጉዳዮችን ግን አላብራሩም።

Ø የአባይን ግድብ አስመልክቶ በወያኔ በግብጽና በሱዳን መካከል የሚደረገው የዙር ንግግር ባለበት እርገጥ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት የወያኔ የግብጽና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ አንድ ዝግ ስብሰባ ማድረጋቸውን የሱዳን ሚዲያዎች ዘግበዋል። በዋናነት የአባይ ግድብን በሚመለከት መምከራቸው ታውቋል።

 

Ø ባለፈው ሳምንት በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ጋምቢያ ውስጥ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ አደራጅታችኋል በሚል ወደ 40 የሚጠቁ ዜጎች ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ መሆናቸው ተገለጸ። ባለፈው ሳምንት በጋምቢያ ውስጥ ሀገሪቱ የምርጫ አሰራርና ህግ እንዲሻሻል ለመጠየቅ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አደራጀነት ከፍተኛ የተቃውሞ ስልፍ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ፖሊስ ስልፉን ለመበተን ጥያት የተኮሰ መሆኑና በርካታ ሰዎችም ይዞ ተነግሯል። ተይዘው ከነበሩት መካከል ሶስት የተቃዋሚው ፓርቲ ነባር አባላት በእስር ቤት ውስጥ መገዳላቸው ይታወቃል። ጋምቢያ በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ ወር ውስጥ ብሄራዊ ምርጫ ለማካሄድ ማቀዷ ታካሄዳለች ተብሏል።

 

Ø በብሩንዲ ዋና ከተማ በብጁምብራ አንድ የኮሎኔል ማዕረግ ያለው ወታደራዊ መኮንን ባልታወቁ ሰዎች መገደሉ የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ኮሎኔል አማኑኤል ቡዙቦና የተባለው መኮንን የተገደለው ከአንድ ሌላ ሰው ጋር በሞተር ቢስክሌት እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ላይ ሲሆን አብሮት የነበረውም ሰው የተገደለ መሆኑ ታውቋል። በብሩንዲ ውስጥ የርስ በርስ ግጭት ከተጀመረ ወዲህ   ወታደራዊ መኮንኖች ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች በተደጋጋሚ እየተገደሉ መሆናቸው ሲታወቅ የመንግስቱን ስልጣን በያዘው ኃይልና በተቃዋሚዎች መካከል እርቅ እስካልሰፈነ ድረስ ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይናገራሉ።

 

Ø ባለፈው ማክሰኞ ሚያዚያ 11 ቀን 2008 ዓም ለረቡዕ አጥቢያ  የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች  በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ዳማቱሩ ከተማ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ በፈረስ ሆነው ወረራ ከአካሄዱ በኋላ 11 ሰዎች የገደሉ መሆናቸው በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለዜና ምንጮች ገልጸዋል። ከሁለት ሳምንት በፊትም ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽመው 20 ሰዎች መግደላቸው ተነግሯል። የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች እኩለ ሌሊት ላይ ወደ መንደሯ ገብተው የእሩምታ ተኩስ ሲከፍቱ ነዋሪዎች በመደናገጥ ቤታቸው እየጣሉ የወጡ ሲሆን በነበረው ተኩስ አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸውና እና ሌሎች ቀጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ነዋሪዎቹ ተናግርዋል፡፤  አጥቂዎቹ እህል ንብረትና ከብቶች ከዘረፉ በኋላ መንደሩን አቃጥለው የሄዱ መሆናቸው ታውቋል፡፤ አሸባሪዎቹ  የድብቅ ካምፖችን በመስራት የጦር ስፈር አድርገው ከቆዩበት ሳምቢሳ ከተባለው ጫካ ሳይመጡ አልቀረም የሚል ግምት አለ። የናይጀሪያ ወታደራዊ ተቋም ቦኮ ሃራምን ማጥቃቱንና ማዳከሙን በመግለጽ በተደጋጋሚ መግለጫ የሰጠ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ  ጎላ ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚያካሂዳቸው ጥቃቶች አለመዳከሙን ያሳያል የሚሉ በርካታ ናቸው።

 

Ø በደቡብ አፍሪካ ላለፉት አራት ዓመት ከመስሪያ ግዥ ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንት ዙማ እና ሌሎች ባለስልጣናት ከፍተኛ ሙስና ፈጸመዋል በሚል ቀርቦ የነበረው ክስ ሲያጣራ የነበረው ኮሚሽን ስራውን መፈጸሙንና ፕሬዚዳንቱን ነጻ ማውጣቱን ፕሬዚዳንት ዙማ በሰጠቱ መግለጫ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ ሐሙስ ሚያዚያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም በሰጡት መግለ ኮሚሽኑ ዘገባውን ያቀረበው ከአራት ወራት በፊት ቢሆንም አሁን ለሕዝብ ይፋ ሆኗል ካሉ በኋላ ባደረገው ምርመራ መሰረት በእሳቸውም ሆኖ በሌሎች ላይ ምንም ጥፋት ያላገኘ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ዙማ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በነበሩበት ወቅት እሳቸውና አማካሪዎቻቸው ከዓለም አቀፍ የመስራሪያ ሻጭ ድርጅቶች በርካታ ገንዘብ ወስደዋል ተብለው ተከሰው የነበሩ ሲሆን አማካሪያቸው በተመሳሳይ ክስ የአስራ አምስት ዓመት እስራት የተፈረደባቸው መሆኑና ተቃዋሚዎች በአቃቤ ህጉ ላይ ያልሆነ ተጽእኖ አምጥተዋል በሚል ምክንያት በዙማ ላይ የነበረው ክስ እንዲነሳ ተድርጎ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ዙማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ጉዳዩን እንዲመረምር አዲስ ኮሚሽን ቢያቋቁሙም፤ አካሉ ኃይል እና ስልጣን ኖሮት አለተጽእኖ  ስራውን ሊያከናውን የሚችል አይደለም በማለት አንዳንድ ወገኖች  ሲያጣጥሉት እንደነበር አይዘነጋም።

http://finote.org/

posted by Geremew Aragaw

 

 

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: