The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

አገርንና ሕዝብን እያወረዱ ትናንሾችን ትላልቅ ማማ ላይ የሚያወጡት ተቃውሞዎቻችን (ሰርጸ ደስታ)

በቅድሚያ እነኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል አደረሳቸሁ!!

1960s and 70s Ethiopian Student movement ፋኖ ተሰማራ …..

1960s and 70s Ethiopian Student movement ፋኖ ተሰማራ …..

ከ50ዎቹና 60ዎቹ የተማሪዎች ተቃውሞ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እያደረግናቸው ያሉትን ተቃውሞና አመጾችን ሳስብ ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮዬ መጡ፡፡ አላማቸውም ስድብና ማዋረድን መሠረት ያደረጉ እንጂ ጥያቄን ለማቅረብና የሚቀርበውም ጥያቄ በትክክል መልስ እንዲሰጥበት የሚታቀዱ አይደሉም፡፡ ብዙዎቻችን የእነዚህ ተቃውሞና አመጽ ተሳታፊ የሆንን ስሜተኝነት እንጂ የተቀውሞዎቻችን መሠረታዊ አላማዎችን ተገንዝበን አይመስለኝም፡፡ በዚህ ግርግር ግን ምንም ላልሆኑ ትንንሽ ሰዎች ሽፋን ሆነናቸው ዛሬ ለአገርና ሕዝብ አደጋ የሆኑበትን ጉልበት የሰጠናቸው ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን ይባስ መደማመጥ ጠፋ፣ ትንንሾቹ ተመቻቸው፡፡ አገርና ሕዝብን የሚያስቡት አንደበት አጡ፡፡ በአጠቃላይ ዝብርቅርቅ አልን፡፡ ውሉ የጠፋን መሠለኝ፡፡ ፖለቲካኛው፣ የሀይማኖት መሪው፣ ሁሉም ብቻ የአገርና ሕዝብ ተቆርቋሪ እየመሰለ የአእምሮ ብስለትንና ማሰብን በማይጠይቀው የተቃውሞና አመጽ ቃላቶችና ድርጊቶች ራሱን ዝነኛ ሲሳካለትም ትልቁ የሥልጣን ማማ ላይ ያስቀምጣል፡፡ በእነደነዚህ ያሉ ሰዎች የሚመራን ተቃዎሞና አመጽ  እየተከተልን ግርዱን ከገለባው መለየት ተሳነን፡፡ የአገርንና ሕዝብን ክብር በሚያዋርዱ አመጾች ተሳታፊ ሆንን፡፡ ግርግሩን እያበዛን ለትናንሽ ሰዎች እድል ከፈትን፡፡

በአገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ውስጥ ውስጡን ከማጉረምረም ውጭ ብዙም ለመቃወም ዕድሉ ስለሌለው በዚህ ጉዳይ ብዙም አይወቀስም፡፡ ሲቃወምም ተቃውሞው መሠረታዊ እውነታዎችንና የሚፈልገውን ትክክለኛ ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡ በእርግጥ በአገር ውስጥም ብልጣብልጦች ይህንኑ አጋጣሚ ወደራሳቸው ፍላጎት ይዘውሩበታል፡፡ ብዙም ጊዜ ሕዝብን ለሞትና ሥቃይ እያጋፈጡ እነሱ ከኋላ እያጨበጨቡ በመጨረሻ ሕዝብ ያነሳውን ጥያቄ አፈር አልብሰው አጋጣሚውን ለራሳቸው ዕድል መፍጠሪያ ሲያደርጉት አይተናል፡፡  ሆኖም አነሰም በዛ የአገር ውስጡ ተቃዎሞ የተሻለ አላማና ግብ አለው፡፡ የቱንም ያህል በብልጣብልጦቹ እየተንሻፈፈ ያለ ውጤት ቢቀርም፡፡ በውጭ አገራት ኢትዮጵያውያን ነን በሚሉ የሚደረገው ተቃውሞና አመጽ ግን መነሻውም መድረሻውም ወይ ስሜት ብቻ የሆነ ወይም ሆን ተብሎ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት በፈለጉ ሰዎች የሚመራ ነው፡፡  ለመሆኑ እነዚህ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን የሚያነሷቸው አመጾችና ተቃውሞዎች እውን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን በሌላው አለም እያዋረዱ መሆኑን ምን ያህሎቻችን ተገንዝበናል; እስኪ ለማስተዋል ይረዳን ዘንድ አንዳንደ ምሳሌዎችን ልጥቀስ፡፡ በተቻለ መጠን ብዙ ሰው የሚውቃቸው ወይም በቅርቡ ተከስተው የምናስታውሳቸውን እመረጣለው፡፡

ኢትዮጵያዎያን መሪዎች ሌላ አገር ሊጎበኙ ሲሄዱ እንደሌላው ከዜጎቻቸው አበባ የሚቀበሉበትን ቀን እየናፈቅሁ እስካሁን ባለው ጉዞአቸው በገጠሟቸውን ተቃውሞዎች ልጀምር፡፡

በቅርቡ ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ ከተወዳጁ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ጋር በደረጉት ቃለ ምልልስ ንጉሱ አሜሪካንን ለመጎብኘት ሄደው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሳይቀር ታግቶ እንደ ጠበቃቸው ነግረውናል፡፡ ዓለም ይህን ሲያወሩልን በኩራት ይመስል ነበር፡፡ እኔ ግን አመጾቻችንና ተቃዎሞቻችን አብዛኛዎቹ አገርና ሕዝብን የሚያዋርዱ መሆኑን ያስተዋልኩት ይሄን ስሰማ ነው፡፡ ልብ በሉ እነ ዓለም ያደረጉት ተቃውሞ ትላልቅ የትምህርት ዕድል የፈጠሩላቸውንና እንደዛሬው በለማኝነት ሳይሆን እንድ ንጉስ ልጅ እየታዩ እንዲማሩ የላኳቸው ንጉስ እየተማሩበት ያለውን አገር ሊጎበኙ ሲመጡ የገዛ ንጉሳቸውን ለባዕዳን ለማሳጣት ነው፡፡ እኔን እንደሚገባኝ በዛን ዘመን ከዚህ በተቃራኒው እነ ዓለም ንጉሱን የሆነ መድረክ ፈጥረው በስነሥርዓቱና በክብር ሊጠይቁ የሚፈልጉትን ነግር ማቅረብ ይችሉ ነበር፡፡ ጥያቄያቸውም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት በቻለ ነበር፡፡ በተማሪዎቹና በንጉሱም መካከል የበለጠ መቀራረብን አገርና ሕዝብን ለመምራት ዕድል የሚፈጥሩበትን፣ በአባትና ልጅነት ሊወቃቀሱ፣ ሊተራረሙ፣ ሊወያዩ የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ይችሉ ነበር ባይ ነኝ፡፡ አሁንም እኔን እንደሚገባኝ ንጉሱ አሁን እንዳሉት ባለስልጣኖቻችን ለሕዝባቸው ሩቅ አልነበሩም፡፡ እንኳንስ ራሳቸው ንጉሱ መርጠው የላኳቸው በሚገበኙበት የሰው አገር ያሉ እንደብርቅ የሚታዩ ጥቂት ተማሪዎቻቸውን ቀርቶ አገር ውስጥም ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለማበረታታት በብዙ በድረኮች እየተገኙ ሲያናግሩ፣ ሽልማት ሲሰጡ እናያለን፡፡  ይህ አይነቱን ቅርርቦሽ ከደርግም ከኢሕአዴግም ባለስልጣናት አላየንም፡፡ እንግዲህ እንዲህ ቀርቦ የማነጋገርና ለጥያቄያቸውም ውጤታማ የሆነ መልስ ማግኘት የሚችሉት የእነ ዓለም ዘመን ተማሪዎች ነበሩ በዓም ሳይቀር ከፍትኛ ክብር የሚሰጣቸውን ለእነሱም እንደ ክብር የሆኑትን ንጉሳቸው የሚማሩበትን አገር ሊጎበኙላቸው ሲሄዱ ነበር በባዕዳን ፊት ለማዋረድ የተቃወሟቸው፡፡ እነ ዓለም አበባ በመያዝ፣ ቀይ ግምጃ በማነጠፍ ተቀብለው የሚፈልጉትን ነግር ቢጠይቁ ጥያቄያቸውም ዋጋ አግኝቶ እስከዛሬም ላለንው ተምሳሌት በሆነን፡፡ በወቅቱ እነ ዓለም ወጣትነቱም ስላለ ይህን ማስተዋል ዘንግተውታል ብዬ ለማሰብ ሞከርኩና ዛሬ ወደ አረጋዊነቱ ዕድሜ ያሉት በትምህርትም ትልቅ የተባሉት ዓለም ሀብቱ ያንን አመጽ ዛሬም እንደ ዝና ሲያወሩት አዘንኩ፡፡ በተቃራኒው ትክክል እንዳልሆኑ ቢነግሩንና ቁጭታቸውን ቢገልጹልን ለብዙዎች ትምህርት በሆነ እላለሁ፡፡

በደርግ ባለስልጣን በየትኛው ላይ በውጭ አገር ተቃውሞ እንደደረሰበት አላውቅም፡፡ ለነገሩ የደርግ ባለስልጣናት ብዙም ውጭ አገር አይሄዱም መሰለኝ፡፡ ከሄዱም ወዳጅ አገር ነው፡፡ እዛ ደግሞ መቃወም የሚፈልግ እንኳን ቢኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡ መከባበሩም ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዛሬ ያሉት የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ግን ትንሹም ትልቁም በተለይ በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በሄደበት አገር ሁሉ ማት ይቻላል ያለ ተቃውሞ በደህና ወደ አገሩ አይመለስም፡፡ ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ወደ መጨረሻ ስልጣን ዘመናቸው አካባቢ በአሜሪካን አገር በእንድ በእንግድነት የተጋበዙበት ስብሰባ ላይ ቃለ ምልልስ እየተደረገላቸው በስብሰባው አዳራሽ በተገኘ በአንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ የተደረገባቸው የተቃውሞ ድምጽ ብዙዎች የምናስታውሰው ነው፡፡ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይህ ጋዜጠኛ እንደ አንድ ልዩ ጀግና ተወድሷል፡፡ አመጽንና ሁከትን እንዲያወግዙ የክርስቶስን ስልጣን የተሸከሙ ትላልቅ የእምነት አባቶች ሳይቀር ጀግና በሚል ምህረት በሚነገርበት አወደ ምህረት ይህን ጋዜጠኛ አቆመው ሲያወድሱት ሰምተናል፡፡ ትልቅም ተጽዕኖ እንደፈጠረ ብዙዎች ያወሩለታል፡፡ አንዳንዶች እንደውም ጠ/ሚኒስቴሩን ወደሞት የወሰዳቸው በሽታ ራሱ የለከፋቸው በዚህ ጋዘጠኛ በተፈጠረ ድንገተኛ ድምጽ ድንጋጤ ነው ብለው ያምናሉ፡፡  በወቅቱ የነበረውን ምስል በትክክል እንደተመለከትነው ግን እውነታውና አንደምታው ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ጋዜጠኛው ይህን ድምጽ ሲያሰማ መድረኩን ይመራው የነበረው የተናገረው ጋዜጠኛውን ከጤነኞች አሳንሶ ነው፡፡ እርግጥም የተለመደውን ጨፍጫፊ፣ ገዳይ፣ እነሱ እንዲሰሙት ኪለር፣ ቡቸር ምናምን የሚሉ ጩኸቶች እንጂ በትክክል የተረጋጋ ሰው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አይደለም፡፡ ሌላው እውነታ መለስን እንኳን ለሞት የጠራቸውን በሽታ የሚያስለክፍ ድንጋጤ የፈጠረባቸው ሳይሆን የተከሰተውን ነገር ምንም እንደሆነ ሳይቆጥሩ እየተናገሩ የነበረውን ንግግራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ሲቀጥሉበት ነው፡፡ በእርግጥም ስንት አስደንጋጭ ድምጽ ያለፈ ሕወት ያላቸው መለስ እንዲህ ያለ የሰው ጩኸት ቢያስደነግጣቸው ነበር የሚገርመው፡፡ ይህ እንደሆነ አድርገው በምስል በማቀናበር ያቀረቡልን አሁንም የአመጻን ውጤት ናፋቂቆች ነበሩ፡፡  እዚህም ጋር ከላይ እንዳነሳሁት እንደ ንጉሱ ቀላል ባይሆንም መለሥንም ቀርቦ ለማናገር ዕድሉ ሙሉ በሙሉ ዝግ ነበር የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደውም የተጋበዙበትን መድረክ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በክብር ቀርቦ ጥያቄዎቹን በግል ቢያቀርብላቸው መለስም ቢሆኑ ጥያቄውን የሳንሱበታ የሚል እምነት የለኝም፡፡  በወቅቱ ደግሞ መለስ እውንም ከብዙ ዘመን በኋላ ወደ ሀገርና ሕዝብ ያደሉ መስለው በሚታዩበትም በሕዝብም ዘንድ ተሰሚ እየሆኑ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡  ብዙ አገር ቤት ያለውም ሕዝብ የጋዜጠኛውን ድርጊት የተቀበለው ሌሎች እንዳደረጉት በውዳሴ ሳይሆን በውግዘት ነበር፡፡ የቱንም ያህል ክፉ ቢሆን እንድን የአገር መሪ በባዕዳን ፊት መሳደብና ማዋረድ አገርንና ሕዝብን ማዋረድ እንጂ ግለሰቡን ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡

በየጊዜው በተከሰቱት በኢሕአዴግ ባለስልጣናት ላይ የተደረጉ ተቃዎሞዎች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ባለስልጣናትን እንደውም አገር ቤት ያለው ሰው አያውቃቸውም እና ብዙም ትርጉም የሚሰጡም አይደሉም፡፡ በዚሁ ወር በዩቲዩብ ተለቆ ያየሁት በውጭ ሚኒስቴሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ላይ በሲዊዲን አገር የገጠመው ተቃውሞ ለግንዛቤ እንዲረዳ እዚህ ሊንክ ላይ ብታዩት ጥሩ መስሎ ታየኝ https://www.youtube.com/watch?v=WJpYqNrXCt8  ብዙ የሚያበሳጩን የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አሉ፡፡ ቴድሮስ ግን አነዚህ ምድብ ውስጥ ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይልቁንም በብዙ ነገራቸው በሕዝብ ዘንድ መወደድን ያፈሩ የኢሕአዴግ ጥቂት ባለስልጣናት አንዱ ናቸው፡፡  ለብዙዎቻችን ያልተገለጸልን ድክመጽ ሊኖርባቻ ይችላል፡፡ ሆኖም መናገር የምንችለው የምናውቃቸውን ያህል ቴድሮስ ሕዝባዊ ከሁኑ በጣም ጥቂት የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አንዱ ለመሆናቸው ብዙ በተግባር የታዩ ሥራዎቻቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቴዎድሮስ የሚታወቁባቸው ብዙ በጎ ነገሮች አሉ ከሁሉም ግን የዛሬ አመት አካባቢ በሊቢያና ደቡብ አፍሪካ በደረሰቡን አደጋዎች ከሕዝብ ጋር ለማዘን ሕዝብ መካከል የተገኙ ባለሥልጣን ቴደሮስ ነበሩ፡፡ ይሄ ጉዳይ ቴድሮስ ለማስመሰል ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ባሕሪያቸው ወይም በብዙ ልምምድ በሕወታቸው ያዳበሩት እንጂ፡፡ በወቅቱ አንዳንደ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ቤተሰብ ሐዘን ተቀምጦ እያጣራን ነው ብለው ያፌዙብን በሐዘናችን ላይ ሐዘን፣ ሕመም ጨምረውብን እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህንኑ ድርጊት ለማውገዝ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተን ብዙ ልጆቻችን በመረረ ሐዘናቸውና በብሶታቸው ቀን የፓርቲ አባል ታርጋ ተለጥፎላቸው ለእስር ተዳረገው እንደነበርም፡፡ እንደ መንግስት፣ የሐዘኑ ባለቤት፣ የሕዝብ እንደራሴንት በእንዲህ ያለው ቀን የሚነሳ የትኛውንም የሕዝብ ተቃውሞ አሜን ብሎ መቀበልና ሕዝብን ከሐዘን ለማረጋጋት ሁሉንም አማራጭ መጠቀም ሲቻል ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ቴደሮስ ሐዘን ወደተቀመቱ የሟች ቤሰቦች በአካል ሄደው ለማጽናናት በግላቸው ትልቁን ሚና የተጫወቱት፡፡ ከዚያ በኋላ ዜጎችን ከየአገሩ ለማስመለስ፡፡ የሄ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነታቸው ግዴታቸውም ነበር፡ ግዴታውን የሚወጣ በራሱ ትልቅ ከበሬታ ይገባዋል፡፡ የግብጹ መሪ አልሲሲ የእኛን ልጆች በአውሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው እንዳጽናኑት የእኛው ጠ/ሚኒስቴር አላደረጉትም፡፡ በወቅቱ እንደ ተባለው ቴዎድሮስ ለሕዝብ ባደረጉት ቀረቤታ ጭራሽ ከሌሎች ባለስልጣናት ወግዘት ገጥሟቸው ነበር፡፡ ብዙዎች የኢሕአዴግ ባለስልጣናት እንዲህ ያለ ሕዝባዊነት ያማቸዋል፡፡ እነሱ ሕዝቡን መቅረብ ስላልቻሉ የሚቀረበው አይመቻቸውም፡፡ ከዚህም በተረፈ ቴድሮስ በነበሩባቸው የሚኒሰቴር መ/ቤቶች ሁሉ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ቀድሞ የነበሩበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በርካታ ሥራዎችን ያሳከዋ በእሳቸው ነው፡፡ አሁን ያሉበት መ/ቤትም አገሪቱ ውስጥ ካሉ መ/ቤቶች ለሕዝብ ክፈትና በፍትሐዊነቱ የሚመሰገን ነው፡፡ የኢሕአዴግ ባለስልጣን በመሆናቸው ካልተባለ ቴዎድሮስ ለብዙዎች መዳን ምክነያት ሆነዋል እንጂ ሞት አልሆኑም፡፡ ኪለር፣ መርደረር፣ ምናምን የሚባሉ ቃላቶች ለቴድሮስ አይደሉም፡፡ በባዕዳን ፊት እንዲህ ያሉ አገርን ወክለው በተገኙ ባለስልጣናት ላይ እንዲህ የሉ እነሱን ያዋረድንባቸው የመሰሉን ስድቦች አገርንና ሕዝብን ራሳችንንም እያዋረድን እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ከላይ ከአስቀመትኩት ምስል እንደምንረዳውም ቴድሮስ የሚቃወሟቸውን እጃቸውን በማውለብለብ ሰላምታ ሰጥተው ወደተዘጋጀላቸው መኪና ሲገቡ ነው፡፡  እንደ እኔ ቴድሮስ ኢሕአዴግ ውስጥ ካሉ መልካም ባለስልጣን ከጥቂቶቹ አንዱ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ተቃውሟችን እንኳን እንዲህ ሁሉንም በጅምላ እየሆነ ጥሩውን ከመትፎው መለየት ሳንችል እንዴት ለውጥ ይመጣል፡፡ እኚህ ሰው የሚነቀፉበት ነገር ቢኖር እንኳን በጎ ነገራቸ ተመስግኖ የሚነቀፉበትን አብሮ ማቅረብ ሚዛናዊነት ነው፡፡

እኝሁ ባለስልጣን በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት ጤና ድርጅት ትልቅ ኃላፊነት እንደታጩ ሲወራ ብዙ ተቃውሞዎች ተደምጠዋል፡፡ ቴዎድሮስ ከላይ እንደገለጽኳቸው በመልምነታቸው የሚታወቁ ሲሆን፡፡ ይህም ባይሆን እንኳንና ቴድሮስ አምባገነን ሆነው እድሉ ተገኝቶ በተባለው ድርጅት ከፍተኛ ስልጣን ቢያገኙ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ መቼም እኚህ ሰው የለ አንዳች ነገር ለዚህ ቦታ አይታጩም፡፡ ተሳክቶላቸውም የተባለው ቦታ ላይ ቢደርሱ እኮ የሚወክሉት ኢሕአዴግን አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው ኢትዮጰያን እንደ ተባበሩት መንግስታት ወኪልነታቸው ለኢትዮጰያም ክብር የሚሆናትን ኃላፊነት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን  ነገር ታዲያ በምን መስፈርት ሊቃወሙት ይቻላል፡፡ መቃወም ልማዳችን ስለሆነ እንጂ ከአገር ክብር አንጻርስ ይህን የመሠለ እድል ለኢትዮጰያዊው መሠጠቱ የቱንም ያህል ክፉ ቢሆን ስህተት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሌላው በብዙ መልኩ የተሻለ ነበር ብዬ የየሁት ግን እሱም ያላስደሰተኝ በኦሮምያ በቀርቡ ተከስቶ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በልጆቻችን ላይ በደረሰው ግድያና እስራት ምክነያት በአንድ ስብሰባ መድረክ ላይ በአሜሪካን የኢትዮጵያ አምባሳደር በሆኑት ግርማ ብሩ ላይ የተደረገው ተቃውሞ ነበር፡፡ እንዳልኩት ጥያቄውም ስሜትን የሚነካ ከመሆኑም አንጻር የዚህን ተቃውሞ ስነስርዓት ወድጄው አሁንም መደማመጥና አመባሳደሩንም እድል የሰጠ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ሆኖም እስከተከታተልኩት ምስል ድረስ ስድብና ማዋረድ የሌለበት በመሆኑ አድንቄዋለሁ፡፡ ምን አልባትም እንዲህ አይነቱ ተቃውሞ በስድብና ማዋረድ  ትልቅ የሚሆኑ ለሚመስላቸው ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም ተናጋሪዎቹ ጥያቄያቸው ተጽኖ ፈጥሮ ቢሆን፡፡ የዚሁኑ ልጆቻችን ለሞትና ሌሎች እንግልቶች የተዳረጉበትን የኦሮምያ አመጽን ተንተርሶ አንዳንደ ግለሰቦች የራሳቸውን ገበያ እንደፈጠሩበት ታዝበናል፡፡ ምንም እውቀት የሌላቸው ተራ ግለሰቦች ትልቅ ጆሮ አግኝተው ዋና ተንታኝና መሪ ሆነውበት አይተናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክነያቱ ኢሕዴግን መቃወም በሚል በሳልና ሰከን አስተሳሰብ ያላቸውን ምሁራንና የሕይወት ልምድ ባለቤት ግለሰቦቹን እያራቀ በግርግር የራሳቸውን ሕልም ለማሳካት ለሚጥሩ የተመቻቸ ፖለቲካ ስለምንከተል ነው፡፡ እንዲ ያሉ መርሆዎች 40 ዓመት ሙሉ ብዙ እዳ ውስጥ ከተወውን ዛሬም ማሰብ አልቻልንም፡፡

የከፋው የተቀውሞና አመጽ ልክፍት ቀስ እያለ ቀድሞ እንፈራው በነበረ አምልኮ ስፍራም አሁን አሁን መታየት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ አሁንም ይህ ተቃውሞና አመጽ በዝተን በምንገኝበት በአሜሪካ የጎላ ሲሆን አገር ውስጥ ጨምሮ በሌሎች አገሮችም ይታያ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው እንደውም ሌላ ቦታ ያሉ ተቃውሞዎቻችን ይሻላሉ፡፡ ቤተመቅደስ ውስጥ መሳዳደብ አልፎም መደባደብ እውን የምናያቸው ክስተቶች ሆነዋል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው የሚለው የፈላስፋው የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር ትንቢት ሆኖ እኛው ላይ ደረሰ፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ተቃውሞዎቻችንና አመጾቻችን የአገርንና ሕዝብን ጥያቄ የሚያነሱ ሳይሆን አጋጣሚውን ለመጠቀም አሰፍስፈው ላሉ አደገኛ ሰዎች እድል የሚሰጡ ሆነው አያቸዋለሁ፡፡ እኛ የአገርና ሕዝብ ክብር የሚለው ነገር ከአእምሮአችን የጠፋ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያሉት የሕንድ ጠ/ሚኒስቴር ናረንድራ ዲሞዳርዳስ ሞዲ ስልጣን የያዙ ሰሞን በአሜሪካ አድርገውት የነበረው ጉብኝትና በዜጎቻቸው የተደረገላቸው አቀባበል እንዴት አስቀንቶኝ ነበር፡፡ በእርግጥ ሞዲ ፍጹም ዲሞክራሳዊ በሆነ ምርጫ ስልጣን የያዙ ሰው ናቸው፡፡ እንዲህም ቢሆን እኛ ብንሆን የሚቃወማቸው ይኖራል የሚል ግምት አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ በተገኙበት አገር ሁሉ ፋናቸውን እየተከተል የሚቃወም እንደ እኛ ያለ አይመስለኝም፡፡ ምን አልባትም በተለይ በሰሜን አሜሪካ እንደ እኛ የአገርንና ሕዝብን ጉዳይ ያገባኛል በሚል ፖለቲከኛ የሆነ ያለ አይመስለኝም፡፡  ሌሎች ካልተደሰቱ እንኳን ዝም ይላሉ፡፡

ሌላው እኛ ከሌሎች ሕዝብች አንጻር እርስ በእርስ ምቀኞች ሳንሆን አይቀርም በዚሁ ሳምንት በተወዳጁ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ተጋብዘው የነበሩት ዶ/ር ተሾመ አበበም እርስ በእርስ ያለን ምቀኝነት ትልቁ ችግራችን እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡  ከብዙ ሌሎች ሰዎችም የሰማሁት ይሄንኑ ነው፡፡ ከ25 ዓመት በላይ ውጭ አገር የሚኖር እንድ ሰው በሚኖርበት አገር አግኝቼው የነገረኝ አበሻ ምቀኛ ነው ብዙም አትቅረበው የሚል ነው፡፡ አንድ እንደ ቀልድ የሚነገር የእኛ ነገር ትዝ አለኝ እግዚአቤሔር ሰውን ሁሉ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ጠይቀኝ ለጓደኛህ ግን ሁለት እጥፍ ነው የምሰጠው ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሁሉም እኔ የፈለኩትን ካገኘሁ ሌላው ለምን አስር እጥፍ አያገኝም እኔን ምን አገባኝ እያለ የሚፈልገውን እየጠየቀ ድርሻውን እየወሰድ ሐበሻ ጋር ደረሰ ሐበሻው ይህን ሲሰማ እጅግ ጨነቀው፡፡ የጓደኛው እጥፍ ማግኘት አስጨነቀው፡፡ ታዲያ በደንብ አሰበና አንድ አይኔን አጥፋው ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ ይባላል፡፡ አስደንጋጭ ነው እውንም እንዲህ ያለ ባሕሪ አለን ማለት ነው፡፡ ከራሳችን ማግኘት የጓደኛችን ማጣት የሚያስደስተን ነን;

ሌሎች ከእኛ የተለየ ባሕሪያቸው በፖለቲካ እርስ በእርስ ተቃዋሚ የሚሆኑት በመሠረታዊ አላማዊ ልዩነት እንጂ ከግል ቂም በቀል ጋር አይያያዝም፡፡ መድረክ ላይ በትር ሊማዘዙ ነው ያልናቸው ተቃዋሚዎች ከሰብሰባው ሲወጡ አብረው በጓደኝነት ምሳ የሚበሉ ናቸው፡፡ እኛ ጋር ያለው እርስ በእርስ የምንተያየው በጠላትነት ነው፡፡ ሲጀምር እኛ የምናነሳቸው ጉዳዮች አብዛኞቹ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ እንዳልሆኑ አሁን በጣም አየታዘብን ነው፡፡ ሁሉም ተማርን የሚሉ ሰዎች የየግል ወይም የቡድን ፍላጎት እንጂ አገርንንና ሕዝብን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በእኛ ፖለቲከኞች አይደረግም፡፡ እውነታው ተቃዋሚውም ገዥውም ብዙ የአላማ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሌዩነታቸው የጥቅምና የሥልጣን ሽሚያ ላይ ነው ባይ ነኝ፡፡ አገርና ሕዝብ የሚፈልጉት ግልፅ ነው፡፡ ለማት፣ፍትሕ፣ አስደዳራዊ በጎነት፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት የብሔረሰብም በሉት፣ ፌደራል ምናምን የሚባሉት ጥያቄዎች የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም፡፡ ፍትህ፣ መልካም አኗኗርሩን፣ ደህንነቱን የሚጠብቅለት መንግስት ሕዝቡ ይናፍቃል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ግን ሌሎች የሕዝቡ ባልሆኑ ተማርን በሚሉ ሰዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች ተጋርደው ዛሬም ድረስ ሕዝብ በሥቃይና ድህነት ይኖራል፡፡

መልካም የትንሳኤ በዓል!

እግዚአብሔር አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ! አሜን!

ሰርጸ ደስታ

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: