The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የደም አበባ Blood Flower (አገሬ አዲስ)

blood flower

“ የፍቅርና  የደስታ መግለጫ የሆነው አበባ በኢትዮጵያ ውስጥ የስቃይና የበሽታ ምክንያት  ሆኗል።” ዜምብላ የደች ቴሌቪዥን ፕሮግራም 18-05-2016

በአፍሪካ ውስጥ ከሚካሄደው ዓይን ያወጣ ዓለም አቀፍ ብዝበዛ ኢትዮጵያም አላመለጠችም።በላይቤሪያ፣በአይቮሪኮስት፣በኮንጎ፣በናይጀሪያና እንዲሁም በቀሩት የአፍሪካ አገሮች የአውሮፓውያን ኩባንያዎችና ባለጸጎች የሚካሄደው የማዕድን ብዝበዛው ጣራ ነክቶ፣ በባለጸጎቹ ቀስቃሽነት በአገር በቀሎቹ ተባባሪዎች መካከል በተነሳው የጥቅም ግጭት ምክንያት የብዙ ሕዝብ ህይወት ጠፍቷል።ለአገራቸው ጥቅምና ለሕዝባቸው መብት የተከራከሩት በዓለም አቀፍ የብዝበዛ ተቋማት ጥያቄና ትእዛዝ በአደባባይ ተረሽነዋል። እንደ ናይጀሪያ ባሉት አገሮችም በደችና በእንግሊዞች ንብረት በሆነው የሼል መልቲናሽናል የነዳጅ ኩባንያ ትእዛዝና ጥያቄ በስቅላት ተቀጥተዋል።በተለያዩት የአፍሪካ አገሮች እየተዘረፈ በሚወጣው ማዕድን ምክንያት በአገሮች የደረሰውን ቀውስና የጠፋውን የሰው ህይወት በሚመለከት በታዛቢዎች አጠራር ና ስያሜ የደም አልማዝ፣የደም ወርቅ፣የደም ዘይት(Blood Daimond,Blood Gold,Blood oil…)የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።በኢትዮጵያም ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ከሚካሄዱት የዘረፋ ክንውኖች መካከል አንዱና ትልቁ የደቾች የአበባ እርሻ ነው።ይህም እንደሌሎቹ የ ደም አበባ ተብሎ ቢሰየም ትክክልና አግባብ አለው ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ነው እርእሱን የመረጥኩት።

ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ማለትም በ2004 እ.አ.አ.የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ሸር/Share/በሚል ስም የተቋቋመው የአበባ እርሻ ኩባንያ ባለቤቱ ባርነሆልም/Baarnholm/ የተባለ ባለጸጋና ልጁ ናቸው፤ እናት ኩባንያው/Mother company/ አፍሪ ፍሎራ /Afri Flora/የተባለ ሲሆን አልስሚር/Aalsmeer/በተባለው የአበባ አምራችና አሰራጭ ማእከል (ሴንተር) አካባቢ የሚንቀሳቀስ ነው።

ይህ ኩባንያ በመጀመሪያ በ1997 እ.አ.አ.በኬንያ ውስጥ ተመሳሳይ የአበባ እርሻ ጀምሮ ከባቢውን ከበከለና ፣የውሃ ሃብቱን ካመከነ በዃላ የሥራው እንቅስቃሴ በመዳከሙ ንብረቱን በ50 ሚሊየን ኤሮ ሸጦ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።በመንግሥት ባለስልጣኖች ተባባሪነትና ሽርክና ብሎም የሙስና ሰንሰለት በዝዋይ ሃይቅ አካባቢ በ1000(አንድ ሽህ)የእግር ኳስ ሜዳ በሚሆን ሰፊ የእርሻ መስክ ላይ ስራውን ጀመረ።የከባቢውን የውሃ ሃብት እንደልቡ ካለምንም ቁጥጥር ለመጠቀም የከባቢውና የሃይቁ ባለቤት ለመሆን በቃ።

በመንግሥትና በኩባንያው ባለቤቶች የሚሰጠው መግለጫ ለከባቢው ልማትና ለነዋሪው የሥራ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተደርጎ ቢሆንም በተግባር ግን ሲታይ የዚያ ተጻራሪ ሆነ።በእርሻው መስክና በአበባው እንክብካቤ አስር ሽህ የሚሆኑ ሰራተኞች በተለይም ወጣቶች የተሰማሩ ሲሆን የሚከፈላቸው ደመወዝ ከዝቅተኛ መደብ ያነሰ ከመሆኑም በተጨማሪ ለእርሻው የተባይ መከላከያ ለሚረጨው መርዝ የተጋለጡና ለልዩ ልዩ በሽታ ሰለባ ሆነዋል።ይህን በሚመለከት ከአስር ዓመት በፊት “ትዝብት” በሚለው እርእስ  በተከታታይ አወጣው በነበረው ጽሁፍ የሚካሄደውን በደልና ሊያደርስ የሚችለውን የከባቢ አደጋ በማመልከት ላገርና ለወገን የሚቆረቆሩ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስቤ ነበር።በኔዘርላንድ የሶሻሊስት ፓርቲም ባለኝ ግንኙነት ሁኔታውን አስረድቼ ጉዳዩ በይፋ እንዲወጣና የሰራተኛው ደመወዝ፣የጤና እንክብካቤና መከላከያ እንዲሟላ እንዲከታተሉ ጥያቄ አቅርቤ ነበር። በወቅቱ ይፋ ማድረጉ በስራው የተሰማራውን ደሃ  በዛን ጊዜ የሚያገኘውን በቀን ስምንት የኢትዮጵያ ብር እንዲያጣና  ለችግር ሊያጋልጥ ስለሚችል ኩባንያው ገና ሳይጠናከርና ለመውጣት በሚቀልበት ሁኔታ ጉዳዩን ከማንሳት ይልቅ ብዙ ወጭ ካደረገና ከተንሰራራ በዃላ መጠየቁ ይጠቅማል የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። በደች ኤምባሲ ዙሪያ በኢትዮጵያኑ ላይ የሚደርሰው መንገላታትና እንደውሻ በአገራቸው መጠለያ በሌለው በራፍ ላይ ለጠራራ  መጋለጣቸውን አስመልክቶ ላቀረብኩት አቤቱታ ከብዙ ውጣ ውረድ በዃላ ባለጉዳዩ በኤምባሲው ግቢ ውስጥ መጠለያ ክፍል ተሰርቶለት እንዲስተናገድ ለማድረግ ተችሏል።

በአበባው እርሻ ዙሪያ ግን ምንም ስር ነቀል መሻሻል ሳይታይ አንዳንድ የጥገና ለውጦች ተደረጉ ፤ከነዚያም ውስጥ የሰራተኛው ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤትና የነጻ ህክምና አገልግሎት መቋቋማቸው ነው።ትምህርት ቤቱ ለከባቢው ኑዋሪ ልጆች የተከፈተ ሳይሆን ለሰራተኞቹ ልጆች ብቻ ነው፤ወላጆቻቸው ከኩባንያው ቢለቁ ወይም ቢባረሩ ልጆቹም ከትምህርት ቤቱ ይባረራሉ።የጤና አገልግሎቱም የተሟላ አይደለም።በሚረጨው መርዝ ሰውነታቸው የተጎዳው ሠራተኞች የህክምና እርዳታ ሲጠይቁ እርካሽና ቀላል መድሃኒት ተሰጥቷቸው ግፋ ቢል ከሶስት ቀናት እረፍት በዃላ ተመልሰው በዛው መርዘኛ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ።ካሳና ድጎማ የሚባል ነገር አይታወቅም፤ለሕዝቡም፣ ለሠራተኛውም ታምርና ባዳ ነገር ነው።

ከጧቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት በቀን ከአስራ አራት ሰዓት በላይ በሳምንት ስድስት ቀን ለሚደክሙበት ሥራ የሚከፈላቸው ደመወዝ በጣም የሚዘገንን ነው።በወር 700 የኢትዮጵያ ብር በኢሮ ሲሰላ € 29.00 ብቻ ነው። በደች ገበያ የአንድ ዘለላ ጽጌሬዳ ዋጋ አንድ ኤሮ ተኩል ማለትም ከ35 የኢትዮጵያ ብር በላይ እንደሆነ ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ከሰራተኛው የቀን ደመወዝ ጋር ሲነጻጸር የአንድ ዘለላ ጽጌሬዳ ሽያጭ ከፍተኛ እንሆነ እንረዳለን። ለአሁኑ የኑሮ ወጭ የሚበቃ አይደለም።አነሰ ሲሉ ተቀነሰ ነውና ከዚህም ላይ ግብር ተከፍሎበት በሰራተኛው እጅ ላይ በወር የሚገባው 650 የኢትዮጵያ ብር ይሆናል፡፤ለቤት ኪራይ ከአራት መቶ ብር በላይ ሲወጣ በቀሪው ገንዘብ በልቶና ጠጥቶ ለብሶ ለመኖር አለመቻሉን በቪዲዮው ላይ የተቀረጸውን ብሶት ማዳማጡ በቂ ነው።በጣም የሚገርመው ደግሞ ለአስር ሽህ  ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ 290.000 ሆኖ ሳለ ለ42 የደች ዜጎች የሚከፈለው ከሁለት ሚሊየን ኤሮ በላይ መሆኑ ነው።

የዚህን አይነት ሕገወጥ ተግባር በየአገሩ የሚፈጽሙ ድርጅቶች የሚያጭበረብሩበት መንገድ ፌር ትሬድ(fair trade) የሚል ሰሌዳ በመለጠፍ ነው። ይህ የአበባ እርሻ ተቋም በዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ መሰረት የተደነገገውን የዚህን የመልካም የንግድ አሰራር መመዘኛ የተከተለ አለመሆኑን ስለ ሰራተኛ መብት የሚከራከሩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሰራተኛውን ደመወዝ፣የስራውን ሁኔታ(salary and working conditions)በመከታተል የተሰጠው ስያሜ ትክክለኛና ተገቢ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። እርሻው በከባቢ፣ በሕዝቡ ጤናና ኑሮ ላይ ያመጣውን አደጋ በሚመለከት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፤አንድ ዘለላ ጽጌሬዳ ለማምረት ከአምስት እስከ አስር ሊትር ውሃ ፣ለአንድ ሄክታር የአበባ እርሻ ስድስት የኦሎምፒክ የዋና ገንዳ ውሃ፣ በየቀኑ እየተመረተ ወደ ሆላንድ ለገበያ ለሚቀረበው ሶስት ሚሊዮን ተኩል(3.5 ሚሊየን)፣በዓመት ደግሞ 1.5 ቢሊዬን ጽጌሬዳ ምርት በሄክታር 2000 የኦሎምፒክ የዋና ገንዳ ውሃ በዓመት እንደሚያስፈልግና ይህም ከዝዋይ ሃይቅ እየተሳበ/እየተመጠጠ እንደሚውል ባለሙያዎቹ  ባደረጉት ክትትልና ጥናት አረጋግጠዋል።የሃይቁ መጠን እየቀነሰ ከመምጣቱም በላይ በከባቢው የሚኖረው ሕዝብ ከሃይቁ የሚያገኘው ጥቅም በተለይም በአሳ ምርቱ ላይ ያደረሰውን ተጽእኖና ብከላ ብሎም ተመጋቢው የደረሰበት በሽታ ለአበባው መከላከያ ከሚረጨው መርዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ጉዳዩን ይፋ ያደረጉት  የዜምብላ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት የደች ጋዤጠኞችና በከባቢው ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች አጋልጠዋል።የጽንስ ማስወረድና ከዚህ በፊት የማይታወቁ በሽታዎች መከሰታቸውን ሃኪሙ አልደበቁም።የሃይቁ የውሃ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱም የመሬት ውስጥ ውሃ ለመሳብ ጉድጓድ በመቆፈር ላይ እንዳሉ የሚያሳየው ስእላዊ ማስረጃ በመታገዱና በመከልከሉ የተሟላም ባይሆን በጥቂቱ  በሪፖርቱ ውስጥ ቀርቧል።የሃይቁና የመሬት ውስጥ ውሃው ሲነጥፍ  በኬንያ እንዳደረጉትና እንደለመዱት ለሕዝቡ የዘላለም በሽታና ለከባቢው ውድመት ዳርገው ጓዛቸውን ጠቅለው መውጣታቸው አይቀሬ ነው። ቀደም ሲል በሃረር ከተማ ዓለም ማያ ሃይቅ ላይ በጫት እርሻ ምክንያት የደረሰው ጥፋት ውድመት ሊታወሰን ይገባል።

ዜምብላ የተሰኘው ፕሮግራም በየአገሩ የሚካሄዱትን ተንኮሎችና ዘረፋዎች የሚያጋልጥ ሲሆን ከዚህም ቀደም ሲል H₰M የተባለው የስዊድን የልብስና ሞድ ኩባንያ በርካሽ የሰራተኛ ደመወዝና ወጭ ምክንያት ከባንግላዴሽ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን እንዳጋለጠ በጊዜው ለኢትዮጵያውያን ማሳወቄ የሚታወስ ነው። የቻይናዎችም የጫማ ፋብሪካ ባልታደለው የኢትዮጵያ ወጣት ላይ የሚያካሂደውን ኢሰብአዊ ተግባርና ዘረፋ በወቅቱ ያስተላለፈውን ማጋለጥና መረጃ ኢትዮጵያኑ እንዲያውቁት አድርጌአለሁ፤አሁንም የዚህ መልእክት ዓላማ እንደኔና በኔዘርላንድ ውስጥ ተቀምጠው በቴሌቪዥን የቀረበውን ዝርዝር ለመመልከት ያልቻሉትን በሌላ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያን እንዲረዱት  ሲሆን ሰምተው እንዲቀመጡ ሳይሆን ተገቢውን የመከላከል እርምጃ ተባብረው እንዲወስዱም ለማሳሰብ ነው።እንዳለፉት ጊዜያቶች ሰምቶ መቀመጡ ለወንጀለኞቹ ድጋፍና ማበረታቻ ከመሆን ሌላ በወገናችንና በአገራችን  ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ወዶ መቀበል ይሆናል።በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የውጭ አገርና የአገር ውስጥ የንግድ ተቋማት ለሰራተኛው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ መክፈል የሚገባቸውን ግብርና ታክስ አይከፍሉም።ለማንኛውም ዝርዝሩን ከዚህ በታች ካለው የቪዲዮ ቅጅ ለመረዳት ይቻላል። በጣም የሚያሳዝነው በሆላንድ ውስጥ ይኖር የነበረውና ከጎሹ ወልዴ ጋር “መድህን”የተባለውን የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረተው ዶር.ፍስሃ ጽዮን መንግስቱ ለተጠየቀው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ በመስጠት ፈንታ የሃብታምና የደሃው ልዩነት ማደጉን ብቻ መግለጹ የሚያስተዛዝብ ሆኖ አገኝቸዋለሁ።ከሙስና ጋር የተቆራኘው የስርዓቱና የመንግሥቱ መመሪያ መሆኑ ሲታወቅ ያንን ለማለት አለመፍቀዱና አለመድፈሩን ሕዝብ የሚያውቀውን መልስ አድርጎ ማቅረቡን በፕሮግራሙ ውስጥ ልትገነዘቡት ትችላላችሁ።ይህ የግብርና ታክስ ምሁር የተለያዩ ኩባንያዎች  በተለይም ይህ የአበባ አምራች ኩባንያ ለአገሪቱ መክፈል የሚገባውን ግብር አለማሟላቱን በድፍረት መግለጽ ሲገባው መሸፋፈኑ የምሁር ስነምግባሩን ከጥያቄ ውስጥ ጨምሮታል።

አብዛኛዎቹ  በተቃዋሚው ጎራ የሚገኙት የከባቢና የጎሳ ድርጅት መሪዎች የውጭ አገር ዘራፊዎችን የሚቃወሙት የጥቅም ተካፋይ ባለመሆናቸው እንጂ  ስልጣን ይዘው ለዚህ ዕድል ቢበቁ ከወያኔ የልተለዬ መመሪያ ይከተላሉ ብዬ አላምንም። አሁንም በአውሮፓ፣በአሜሪካና በካናዳ እየተዘዋወሩ የውጭ ባለሃብቶች ገብተው እንዲዘርፉ ቅስቀሳና ጥሪ የሚያደረጉት የአማራ ክልል ባለስልጣኖች የዚሁ ተባብረህ ዘርፈህ ጥፋ ዓላማ አካል ነው።

ሙሉውን የዜምብላ ቅጅ ከዚህ በታች ባለው ሊንክ መከታተል ይቻላል፣

http://www.npo.nl/zembla/18-05-2016/VARA_101377865

ሰምቶ እየተበሳጩ ከመቀመጥ ተባብሮ ችግሩን ማሶገድ ይሻላል

አገሬ አዲስ

posted by Geremew Aragaw

 

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: