The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሾተላይ – ይገረም አለሙ

oromo-protest

እናታችን ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሾተላይ ናት መሰለኝ። ዲሞክራሲን በስድሳ ስድስት ወልዳ በላች። አስቀድሞም በሃምሳ ሶስት አስጨንግፏታል። ብትወልድም ብትገላገለውም ለዘለቄታ አያደርግላትም። የማሕፀን መርገምት አለባት። የዲሞክራሲ ሾተላይ ናት ኢትዮጵያ። በስድሳ ስድስትማ ወዲያው ማግስቱን መፈክር ተፎከረላት። ‘አብዮት ልጆቿን ትበላለች’ ተባለላት ተሸለለላት። የዲሞክራሲ ሾተላይ እናት፣ በላኤ ሰውነቷን መላው የአለም ሕዝብ አስጠንቅሮ አውቀላት። ሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን

የዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያት ሰሞኑን እዚህ በሀገር ቤት አዲስ ፓርቲ ተመሰረተ የሚለው ዜና ነው፡፡ፓርቲ መሰረቱ የሚባሉት ሰዎች ደግሞ አዲሶች ሳይሆኑ ቀድሞ በተለያዩ ፓርቲ ውስጥ እናውቃቸው የነበሩ ለውጥ ማምጣት ቀርቶ የፓርቲያቸውንም ህልውና ማስጠበቅ ያልቻሉ ናቸውና ነው ይህችን አስተያየት ለመሰንዘር የተነሳሁት፡፡

ልጅ ተወልዶ የማይድግበት ወይንም ጽንሱ የሚጨነግፍበት ከወላጆች የሚመነጭ ችግር ሳይንሳዊ አጠራሩንና እንዴትነቱን ለባለሙያዎች ትተን በሀገራችን ልማዳዊ አጠራር ሾተላይ ይባላል፡፡ ሎሬት ጸጋየ በአንድ ወቅት አንደተናገረው ሀገራችን የዴሞክራሲ ሾተላይ ያለባት ይመስላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለዴሞክራሲ መሰረት የሚጥለውን ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሾተላይ መጠቃታቸውና በሽታቸውን ለማወቅና መድሀኒት ለመወስድ አለመቻላቸው ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን በሾተላይ ምክንያት ያጡ ወላጆች ዳግም ልጅ ለመውለድ ከማሰባቸው በፊት ወደ ሐኪም ጎራ ብለው ምክርም ሆነ መድሀኒት ተቀብለው ተዘጋጅተው ካልሆነ ሁለተኛውንም በተመሳሳይ መልኩ ያጣሉ፡፡ ለመውለድ እንጂ ለማሳደግ ያልታደሉ ይሆናሉ፡፡

የሀገራችንም ፖለቲከኞች ተግባር የዚህ ተመሳሳይ ነው፡፡ ፓርቲ ሲመሰርቱ እንጂ አሳድገው ለወግ ለማእረግ ሲያበቁ አይታዩም፤ ስለ ህብረት ውህደት ሲያወሩ እንጂ ተግባራዊ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ተባበርን ግንባር ፈጠርን ብለው አየሩን በወሬ ሲያደምቁ እንጂ ፈጠርን ያሉትን ህብረትም ሆነ ግንባር ቅንጅትም ይሁን ውህደት ለውጤት ሊያበቁት ቀርቶ እድሜውን ሲያስረዝሙት አይታይም፡፡

የቀደሙት ፓርቲዎች ወፌ ቆመች ሳይባሉ የጠፉበት ወይም የተዳከሙበት ምክንያት ሳይመረመር፣ በሽታው ታውቆ መድሀኒት ሳይፈለግ የእርስ በርስ ውይይትና ምክክር ሳይደረግና የባለሙያ ምክር ሳይጠየቅ የችግሩ መፍትሄ የሾተላዩ መድሀኒት አዲስ ፓርቲ መመስረት ይሆንና ያለፈውን ድክመት ያወገዙ፣ አካሄድ አሰራሩን የኮነኑ ይሰባሰቡና ፓርቲ ይመሰርታሉ፡፡ ነገር ግን ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ የምስክር ወረቀት በተቀበሉ ማግስት ስንጥቅ ማሳየት፣ ዋል አደር ሲሉ ደግሞ ርስ በርስ መናቆር ውስጥ ይገቡና አዲሱ ፓርቲያቸው ወግ ማእረግ ሳያይና ሳያሳይ ወይ ይከስማል ወይ ተሸመድምዶ ይቀመጣል ወይም ለወያኔ ሎሌ ሆኖ ይሰግዳል፡፡

ብዙዎቹ ፓርቲዎች በዚህ መንግድ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ ወደ ኋላ ሀረጋቸው ቢመዘዝ መዐህድ ላይ ነው የሚያርፈው፡፣ ሀገር ውስጥም ውጪም ያሉትን ፓርቲዎች ብንፈትሽ ብዙዎቹ በመለያየት የተፈጠሩ ናቸው፡አንድነትን በምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፖሊስ አስገዳጅነት ለመረከብ የበቃው አቶ ትዕግስቱ አዎሉ አባል የነረበት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ብዴህ) በ1997 ምርጫ ዋዜማ ከመኢአድ ተቀላቀለ ተባለ፡፡ በምርጫው ማግስት ደግሞ እነዚሁ ሰዎች ጥቂት ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ብርሀን ለኢትዮጵያ የተሰኘ ፓርቲ መሰረትን አሉ፡፡ በምርጫ 2002 ሰሞን ደግሞ ከአንድነት ተዋሀድን አሉ፡፡ አቶ ትዕግስቱ በዚህ ሁሉ ጉዞው በእጅጉ የሚፈልገውን ሥልጣን ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ በርግጥም የፓርቲ መሪ መሆን የሚገባው ሰው አይደለም፡፡ አንድነት ፓርቲ በሽታውን አውቆ መድሀኒት የሚፈልግለት ሰው አጥቶ የትእግስቱን የሥልጣን ጥም ማሳኪያ ሆነ፡፡ የአንድነት በሽታ በቅጡና በወቅቱ ቢመረመርና መድሀኒት ቢገኝለት ኖሮ አስቀድሞም ትእግስቱ የአንድነት አባል መሆን የሚገባው ሰው አልነበረም፡፡ የዛ በሽታ ሳይታወቅ ደግሞ አዲስ ፓርቲ!

መተባበርን በተመለከተም ኢዳቅ፤ ኢተፖድህ ፣ደቡብ ህብረት፣ጋፖመ፣ አማራጭ ኃይሎች ፤ኢዴኃህ፤ ቅንጅት ወዘተ እየተባለ አሁን በመኖርና ባለመኖር መካከል እስካለው መድረክ ድረስ ብዙ መተባበሮችን አይተናል ሰምተናል፡፡ ሁሉም ሲመሰረቱ ከእነርሱ ቀድሞ የነበሩ መተባበሮች ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑ፤ ሽባ ያደረጋቸው በሽታ ምን እንደሆነ ወዘተ ሳይፈተሽና ያለፈው የመናቆርና የመለያየት በሽታ በመጪው ላይ እንዳይደገም መፍትሄ ሳይፈለግ በመሆኑ አንዳቸውም ውጤት ማስመዝገብ ቀርቶ ህልውናቸውን ማቆየት አልቻሉም፡፡ ቅንጅት የተሻለ ውጤት ማሳየቱ አሌ የሚባል ባይሆንም እሱም እንደሌሎቹ መተባበርን የሚያስጨነግፈው በሽታ በውል ሳይታወቅና መድሀኒት ሳይገኝለት የተመሰረተ በመሆኑ በበሽታው ተጠቅቶ መሪዎቹ የሰሩትን መልካም ታሪካዊ ሥራ ኋላ በፈጸሙት የመለያየት ተግባር ኦቆሸሹት፡፡

ወያኔ መቶ በመቶ አሸነፍኩዋችሁ እያለ በሚመጻደቅበት በአሁኑ ወቅት እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያስጨነግፋቸውንና በአጭር የሚያስቀራቸውን ሾተላይ ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ቀርቶ ሀሳብ መኖሩ አይሰማም፡፡ ብቻ ከልብ ያልሆነ የወቅታዊ አጀንዳ ማስቀያሻ የመተባበር ወሬ እንሰማለን፡፡ የመድረክ አባል ፓርቲዎች በጉባኤያቸው ማግስት እስከሚቀጥለው ጉባኤያቸው ስለ ውህደት እንደሚነጋገሩ ገልጸው የነበረ ቢሆንም ባለፈው አንድ ዓመት ምንም አልተሰማም፡፡ ኢዴፓ ራዕይና አንድ ሌላ ፓርቲ ተባብሮ ለመስራት እየተነጋገርን ነው በማለት ለአንድ ሳምንት አወሩ ጠፉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ አንዴ ከኦብኮ ጋር አንዴ ከመድረክ ጋር እየሰራሁ ነው ቢልም ከአንድ ሰሞን ፕሮፓጋንዳ የዘለለ ነገር አይታይም፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለን ነው እንግዲህ የአዲስ ፓርቲ መመስረት ዜና የሚነገረን፡፡

ጥያቄው አዲስ ፓርቲ ለምን ተመሰረተ አይደለም፡፡ ፓርቲዎች በአጭር የሚያስቀራቸው ሾተላይ፣አለያም አንደፖሊዮ ሽባ የሚያደርጋቸው በሽታ ተጠንቶ ታውቆ መድሀኒት ሳይገኝ ፓርቲ መመስረት ቁጥር ከመጨመር ያለፈ የሚፈይደው ነገር አለመኖሩን ያለፉት ልምዶቻችን ስለሚያሳዩን እንጂ፡፡ ፓርቲ ከመታገያ መድረክነቱ ይልቅ ለግለሰቦች የሚያስገኘው ጥቅም በመኖሩ አንዱን እያዳከሙ ወይንም እያፈረሱ አዲስ መመስረት ወይንም የግል ንብረት አድር ሙጢኝ ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ችግሩን አስወግዶ ለበሽታው ፍቱን መድሀኒት አግኝቶ የግለሰቦች መጠቀሚያ ሳይሆን ሕዝብ አታጋይ ፓርቲ እንዲኖር ለማድረግ ከልብ ከታሰበበት በሽታው ግልጽ፣ መድሀኒቱም ቀላልና በቅርብ የሚገኝ ነው፡፡ ችግሩ ለምርመራ ፈቃደኛ ሆኖ የሚቀርብ መድሀኒቱንም ለመውሰድ የሚዘጋጅ አለመገኘቱ ነው እንጂ፡፡

ምርመራው ውይይት ነው፡፡ መድሀኒቱ የራስን ችግርና ድክመት በወያኔ እያሳበቡ በዛ ውስጥ ተደብቆ ለማለፍ ከመጣር ራስን ለማየትና ለመጠየቅ መድፈር ነው፡፡ የህክምናው ውጤት ለጋራ ድልና ለሀገራዊ ነጻነት የሚያበቃ ስልት ነድፎ ለግል ስልጣን መያዝ ሳይሆን ሕዝብን ከአገዛዝ ለማላቀቅ ተጨንቆ የቤተመንግሥቱ ወንበር ለአንድ ሰው ብቻ መሆኑን አምኖ ተባብሮና ተማምኖ መታገል ነው፡፡ ካልሆነም አንዱ ለአንዱ እንቅፋት አለመሆን ርስ በርስም አለመጠላለፍ ነው፡፡ የፖለቲካ ታሪካችን የሚያሳየን ሥልጣን ላይ ያለን ኃይል ተቃውመው በማናቸውም መንገድ ትግል የጀመሩ ኃይሎች ጠላታችን የሚሉት ካደረሰባቸው ጥቃት ባልተናነሰ ርስ በርሳቸው መጠቃቃት መጠፋፋታቸውን ነው፡፡ የአንድት አመራሮች የግዛቸው የበላይ ተባብለው ለአደባባይ የበቃ ጦርነት ባይገጥሙ ምርጫ ቦርድ በምን ቀዳዳ ገብቶ ትእግስቱን ያነግስባቸው ነበር? ከራስ በላይ ነፋስ እየተባለ፣ቃልና ተግባር ሀራምባና ቆቦ ሆኖ፣ የእኔነት አብሪት ነግሶ፤ በሥልጣን ጥም ታውሮ ወዘተ ሀገራዊ ትግል እንዴት ይሆናል፡፡

በትናንት መኩራት ዛሬ ሆኖ በመገኘት ካልተገለጸ አይፈይድም፡፡ የትናንት አስተሳሰብም ሆነ የትግል ስልት በዛሬ ካልተቃኘና ከዘመኑ ጋር ካልዘመነ ውጤታማ አያደርግም፡፡ በየዘመናቱ የተደረገው ትግል ያስከፈለውን መስዋዕትነት ያህል ውጤት ላለማስገኘቱ ደረጃው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር በወቅቱ የነበሩ ሁሉ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ለትውልድ መልካም ሀገር ለማቆየት ሲባል የድርሻ ድርሻ ተጠያቂነትን (አቶ አሰፋ ጫቦ ደጋግመው ይሉት እንደነበር) በመውሰድ ከትላንቱ መንገድ ወጣ ብሎ ያልተሞከረውን ሳያስቡ ያልተሄደበትን መንገድ ሳይቃኙ ሮጦ አዲስ ፓርቲ መመስረት ለትግል ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡

በንቀትም በእብሪትም፤በጉልበትም በማስቀየስም የወያኔ አገዛዝ መቀጠሉ የእኛ ድክመት ውጤት መሆኑ አስቆጭቶን ሂሳብ ለማወራረድ ሳይሆን የፖለቲካችንን ሾተላይ ለማወቅና መድሀኒት ለማግኘት በሀቅ በግልጽና በመተማመን መነጋገሩ ነው የሚበጀው፡፡ ፓርቲ ማብዛት ሳይሆን ያሉትን ማጠናከርና ማሰባሰብን ፣ ፓርቲን የግል ንብረታቸው ያደረጉ ግለሰቦችን ደግሞ በሀቅና በድፍረት በማጋላጥ በሀገርና በሕዝብ አትቀልዱ ማለቱ ነው የሚሻለው፡፡ ለወያኔ የምርጫ አጃቢነት እንደሆነ ያሉት ፓርቲዎች ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ እንደውም በዝተውበት ሰሞኑን የተወሰኑትን ከመዝገቡ ላይ ሰርዟቸዋል፡፡(መጀመሪያም በምርጫ ቦርድ መዝገብ ላይ እንጂ በመሬት ላይ አልነበሩም፡፡)

ከፖለቲከኞቹ በተጓዳኝ ደጋፊዎችም የጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ሾተላይ ተጠቂ በመሆናችን ለበሽታው መድሀኒት ማግኘት ሳይሆን ለመባባሱ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፈ ለመስፋፋቱ አስተዋጽኦ አድርገናል እያደረግንም ነው፡፡ የምንደግፈው አይነካብን እንላለን፤ የማንደግፈው ምን ጥሩ ቢሰራ አይታየንም፤ከዚህ በሽታ መላቀቅ ካቻልን ፖለቲካችን ፈውስ አያገኝም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከሾተላይ አይገላገሉም፡

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: