The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ሽሮ የለም ሽራሮ ግን ዛሬም አለ

( ሄኖክ የሺጥላ * )

ሲሳይ የጎንደር ልጅ ነው ። አማርካን ሃገር የሚኖሩ ቤተሰቦቹ እይሱዚ ገዝተውለት ከጎንደር አዘዞ እና ባህር ዳር እየተመላለሰ የእህል ጭነት ስራ ይሰራል ። ወቅቱ የ ኢትዮ ኤርትራ የድንበር ይገባኛል ግጭት ጦርነት የሚካሄድበት ጊዜ ነበር ። ሲሳይና ጓደኞቹ ( መሰል የአይሱዚ ባለቤቶች እና ሹፈሮች ) ከመንግስ ቀጭን ትዕዛዝ ይተላለፍላቸዋል ። ትዕዛዙም በቡሬ ፥ ፆረና እና ዛል አንበሳ ግንባር ከኤርትራ ( ሻዕቢያ) ሰራዊት ጋ ሲዋደቁ ህይወታቸው ያለፈ ፥ አደገኛ የአካል (መቁሰል) አደጋ የደረሰባቸውን ወታደሮች በመኪና ጭነው ወደ ሆስፒታል እንዲወስዱ የሚል ነበር ። እነ ሲሳይ ግዳጃቸውን ካልተወጡ ምን እንደሚጠብቃቸው በመስጋት በየ ድልድል ምድባቸው የተሰጣቸውን «የሀገር ሰራዊት» የማንሳት ፥ የማዳን እና መሰል ህይወት አድን ስራዎችን ለመስራት ይሰማራሉ ። ሲሳይ በቡሬ ግንባር ነበር የተሰማራው ። በአብዛኛው ወጣት ከጎጃም እና ጎንደር ተሰለፉበት ግንባር ነበር ። በፆረና እና በ ዛላምበሳ ግንባር ከሱማሌ ክልል ፥ ከ ደቡብ ፥ ከኦሮሚያ ፥ ከአዲስ አበባ እና ከወሎ የህይወትን ጥቁር እጣ ፈንታ ለማምለጥ ሲሉ የተሰለፉ እልፍ ወጣቶች የተሰለፉበት ግንባር ነበር ። ከትግራይ ክልል የመጡ በጦርነቱ ወቅት ከፊት እንዳይሰለፉ ይደረግ እንደነበረም እናስታውሳለን ።

ሲሳይ በቡሬ ግንባር የሆነውን ሲያጫውተኝ « ሬሳ በየ ሜዳው ላይ እንደ በረዶ ችምችም ብሎ ተከምሯል ፥ ለቦንም ማክሸፊያነት ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ፍየሎች በሙል ተጠቅመው ስለጨረሱ ፥ ወጣት ልጆችን ነበር ለቦንብ ማክሸፊያነት የሚጠቀሙባቸው ። ታስታውስ እንደነበር የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈውርቂ በወቅቱ የነበረውን ሁናቴ እና የኢትዮጵያም አሸናፊነት ሲናገር « በሰው ማዕበል ፥ በሬሳ ክምር ድል የተደረገ ጦርነት » ነበር ያለው ። እውነቱን ነበር ።

ግዳጅ ወደተላክንበት ቦታ እንደደረስን የማየውን ነገር ማመን አቃተኝ ። በፍጥነት ወድ ስራ እንድንሰማራ ታዘዝን ። ሁለት እግርና ሁለት እጅ እየያዝን (እያወዛወዝን) ወደ አይዙዙ ላይ እንወረውር ጀመር ። ከጠዋት እስከ ማታ ፥ ሬሳ ጭነን ስናመላልስ እንውላለን ። ሌሊት ላይ ሬሳውን ጭነን ከቆምንበት ቦታ ወደ ማንቀው ሰዋራ መንገድ መኪናችንን እንድንነዳ እንታዘዛለን ፥ ሬሳውን አድርሱ የተባልንበት ቦታ ፥ በምሽግ መቆፈሪያ ዶዘሮች የተቆፈሩ ሰፋፊ ጉድጓዶች አሉ ፥ በነዚያ ጉድጓዶች ውስጥ ሬሳዎችን እንድምጨምር ይነገረናል ። የተባልነውንም እናደርጋለን ፥ እንዲህ እያደረግን ለ አምስት ቀን ያለ ማቋረጥ የተቆረጠ እጅ ፥ ጭንቅላት ፥ የተበጠጠሰ ገላ ፥ አንጀት ፥ የተገመሰ ጭንቅላት ፥ ምኑን ልንገር ፥ በመጨረሻ አእምሮዬ ነገሩን መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ደረስኩ ፥ እዛው ጫካ ውስጥ ሁኔታዬ ተቀየረ ፥ ብቻዬን ማውራት ፥ መለፍለፍ ፥ መጮኽ ጀመርኩኝ ። ሙሉ በሙሉ ራሴን ባልስትም ( ባልረሳም ) ፥ እንደ ማበድ እያደረገኝ እንደሆነ ገብቶኛል ። እንቅልፍ ለአራት ቀን በአይኔ አልዞረም ። አንደኛው መቶ አለቃ ወደ ሰዋራ ስፍራ ወስደው እርምጃ እንዲወስዱብኝ አዘዘ ። በወቅቱ ህውሓቶች እርስ በእርሳቸውም የማይስማሙበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ስለነበር ይመስለኛል ፥ እርምጃ እንዲወስድብኝ የታዘዘው ሰው በወታደር ኦራል ጎነደር እንዲያደርሱኝ አዘዘ ። መኪናዬ ከምን እንደደረሰ አላውቅም ። ቤቴሰቦቼ በሁኔታው በጣም በመደናገጣቸው ፥ በፍጥነት አዲስ አበባ ይዘውኝ መጡ ። ኪዳነምህረት ጠበል ለሶስት ወር እየተጠመቅሁ ቁጭ አልኩኝ ። ብሎ ታሪኩን አወጋኝ ።

አዎ በዛ ጦርነት የሆነው ሁሉ ዛሬም ድረስ ከህዝብ ተደብቋል ። ያለም ሚዲያዎችም ስለ ጦርነቱ የሚያሳይ አንዳች ነገር ለማሳየት ፍቃደኞች አይደሉም ። መንግስትም ካሜራ ለመቅደም በሚያስመስልበት መልኩ ፥ ሟቾቹን ሰብስቦ በትልቅ ጉድጓድ ከቶ ለቤተሰቦች አግባብ ያለው መርዶ እንኳን አላረዳም ። የተወሰኑትን እና መደበቅ የማይችለውን እርግጥ ቤት ለቤት እየዞረ ተናግሯል ።

unnamed (2)
ኣዎ ያኔ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሽሮ የሰለቻቸው ፥ ምናልባት ስጋ የናፈቃቸው ወጣቶች «ከሽሮ ይሻላል ሽራሮ» በሚል መፈክር ፥ ህይወታቸውን የማገዱበት ፥ በሀገር ፍቅር እየተንገበገቡ የቦንብ ማክሸፊያ የሆኑበት ወቅት ነበር ። ድሮ ግን ዘንድሮ አይደለም ። ዘንድሮ ሽራሮ ያለ ሽሮ ነው ብቅ ያለው ። ዘንድሮ ፆረና ባህር እየገባ መሞት ታሪኩ ለሆነለት ወጣት ብስራት ሳይሆን ቅዠት ነው ። ቤቱ በጉልበት የሚፈርስበት ፥ መሬቱ የሚሸጥበት ፥ በስደት አለም በእሳት ተቃጥሎ ሲሞት መንግስቱ የሚስቅበት ሃገር ወጣት ፥ የሚሞትለት ሃገር ቢኖረውም የሚያምነው ስርአት ግን እንደሌለ እሙን ይመስለኛል ። አዎ በሊቢያ አንገቱ ሲቀላ « ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን እያረጋገጥን ነው » ላለ መንግስት እና ህገ መንግስት ወኔ ኖሮት ከጎኑ ሊቆም የሚችል ትውልድ ይናራል ለማለት በእርግጥ እንቸገራለን ። ትናንት በፍፁም ኢትዮጵያዊ ወኔ « ዘራፍ!» እያለ ራሱን ለቦንብ ገብሮ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር የተሰዋ ትውልድ ፥ ከሞቱ ባሻገር ፥ ካለፈለት ክብሩ ጀርባ ፥ ደሙን መቀለጃ ፥ ክቡር ህይወቱን ማላገጫ ፥ አከላቱን የጥይት መለማመጃ አድርገው « ድንበሩ ለኛ ተወሰነ » እያሉ ሲያላግጡበት ለኖሩ ተራ ወሮ በሎች የሚቆም እግርም ሆነ የሚፀና ክንድ ይኖረዋል ማለት ዘበት ነው ። « የዛሬዋን የአሰመራ ፀሃይ ፥ እንደትናንቱ በንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ደም ማስገባት አይቻልም !» ፥ የዛሬው « ዘመቻ ፀሃይ ግባት » ከጠለቀም የሚጠልቀው በህውሓት መንደር ይሆናል እንጂ ፥ ደጋፊ ባጡ ፥ ደማቸውን ገብረው ሬሳቸው የወግ ቀብር ባላገኘ ፥ ደመ ከልብ ኢትዮጵያዊኖች ደም አይሆንም ። ዛሬ ሽሮ የለም ፥ ሽራሮ ግን ተመልሶ መጥቷል ። ዛሬ ሃገር የለንም ፥ ሀገርህን አድን የሚለው የወያኔ ዘፈን ግን ተመልሶ መጥቷል ፥ ዛሬ ታሪክ የለንም ፥ መግቢያ ቀዳዳ ሲያጣ « በለው በለው » የሚያዘፍነው የወያኔ ወስላታ ፖለቲካ ግን ተመልሶ መጥቷል ፥ ዛሬ መብት የለንም ፥ ስለ መብት የሚያወራው የጭልፊቶች ዲስኩር ግን እንደገና አፈሩን አራግፎ « ህዝቤ » እያለን ነው ። እነሱ እንደጀመሩት ይጨርሱት ። ቢቆረስ ፥ ቢታረስ ፥ ቢወቃ ፥ ቢታጨድ ፥ ቢቆረጥ ፥ ቢታለብ ፥ ከገል ባነሰ ሽራፊ ጣባ እንኳ መቋደስ እና መጠጣት ያቃተን ምን አገባን ብለን ነው ባልተከበርንበት ሃገር ፥ ስለ ሃገር የምንቆመው ። ባለ ፎቁ ፥ ባለ ትራክተሩ ፥ ባለ ፋብሪካው ፥ ባለ ሱቁ ፥ ባላ ጭነት መኪናው እሱ ከነ ንብረቱ ሄዶ ይቁም ፥ ይቺ ሃገር የሱ ነች ፥ ስለዚህ እሱ ይሙትላት ፥ እኛ በወያኔ እልፍኝ ምን ቤት ነን !

ለጊዜው ሽሮም ሆነ ሽራሮም እኛን አይመለከትም !

 

* * ሄኖክ የሺጥላ ይህን ጽሁፍ ያሰፈረው በፌስቡክ ገጹ ነው:: የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ቢያነቡት ይጠቀማሉ ብለን ስላሰብን ወደዚህ አምጥተነዋል::

posted by Geremew Aragaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: