The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ሰይጣናዊው የወያኔ ሸፍጥ በገዳ ሥርዓት የዓለም ቅርስነትና ሊመዘገቡ የሚገባቸው ቅርሶቻችን!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

 

ትናንትና 22, 3, 2009ዓ.ም. የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት

የትምህርት፣ የሳይንስ (የመጣቅ) እና የባሕል ተቋም (UNESCO) “የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ወካይ ቅርስ!” ተብሎ መመዝገቡን ከወያኔ ሹማምንት ወይም ባለሥልጣናት ከ”እንኳን ደስ አለን!” የስልክ መልዕክትና ከብዙኃን መገናኛዎች ዜና ሰማን፡፡ የእሬቻ በዓል

አከባበር ደግሞ ለመመዝገብ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

በዚህ ጽሑፌ ማየት የፈለኩት የገዳ ሥርዓት መመዝገቡ ያለውን ፋይዳ አይደለም፡፡ ችግር ባይኖርበት ኖሮ ጥቅሙ ምንም የሚያጠያይቅ ጉዳይ አልነበረም፡፡ መግለጥ የፈለኩት በዚህ ጉዳይ ላይ የወያኔ ሞቲቭ (ተነሣሽነት) እና ፍላጎት ምንድን ነው? የሚለውን ነው፡፡ ጉዳዩን ግልጽ በሆነ መንገድ ማየት አለብኝና ይሄንን ለማድረግ በምሞክርበት ወቅት የዚህ ባሕል ባለቤት ነው የሚባለውን “የኦሮሞን ሕዝብ” ለማነወር ወይም ለማንቋሸሽ በማሰብ እንዳደረኩት ተደርጎ እንዳይታሰብ አስቀድሜ ማስጠንቀቅ እወዳለሁ፡፡ ምን እኮ ወያኔ ባሸከመን የጎሳ ፖለቲካ
(እምነተ አስተዳደር) ምክንያት የምትነገር ነገር ሁሉ ተጣማ እየተተረጎመች ዕዳ ገባን እኮ ወገኖቸ! በአንድ
ጉዳይ ላይ ሞያዊ ትችትን በነጻነት ማቅረብ በፍጹም አልተቻለም እኮ!
ለነገሩ ከኦሮሞ ተወላጆች የገዳን ሥርዓት ኢሰብአዊ ገጽታ የማይቀበሉና የማይደግፉ የሚያወግዙም ይበዛሉና የዚህን
ባሕል ኢሰብአዊ ገጽታ ለመተቸት በምሞክርበት ወቅት የኦሮሞን ሕዝብ ለማጥላላት አስቤ እንዳላደረኩት ይታወቃል ብየ
ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንዲያው ድከሙ ቢላቹህ ነው እንጅ የሚያስነቅፍ ነገር እንፈልግ ከተባለማ እኮ ሁሉም ላይ
ሊባል የሚችል ነገር ይጠፋል ብላቹህ ነው? እንኳንና በማኅበረሰብ ደረጃ በግለሰብ ደረጃስ ቢሆን እንከን አልባነት
ወይም ፍጹምነት ይጠበቃል እንዴ?
ወደ ጉዳዩ ስገባ ግልጽና አጭር በሆነ አገላለጽ በዚህ ጉዳይ ላይ የወያኔ ተነሣሽነትና ፍላጎት ምንድን ነው?
ለሚለው ጥያቄ መልስ ስንሰጥ ወያኔ ለሀገርና ለሕዝቧ ቅርሶች አሳቢና ተቆርቋሪ ስለሆነ ሳይሆን የገዳን ሥርዓት
ለማስመዝገብ የደከመውና ያስመዘገበውም ለርካሽና ዕኩይ ፖለቲካዊ ትርፉ ሲል ነው ይሄንን ያደረገው፤ የሚለው ነው
መልሱ፡፡ እንዴት? ምንድን ነው ርካሽና ዕኩይ ፖለቲካዊ ትርፉ? ከተባለ ደግሞ መልሱ አሁንም ግልጽና ቀላል
ነው፡፡ ወያኔ ለኦሮሞ ሕዝብ ካለው ንቀት የተነሣ ምን ብሎ ያስባል መሰላቹህ “እንደምንም ብየ ገዳንና እሬቻን
በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት ካስመዘገብኩ የኦሮሞን ሕዝብ እንደሱ የከበረ ያለ እስከማይመስለው ድረስ ጮቤ
አስረግጥበታለሁ፣ ዓለምን የገዙ ያህልም እንዲሰማቸው አደርግበታለሁ! ፋታ ሳልሰጥ ይሄንን ጉዳይ ለራሳቸው
መላልሰው እንዲያስቡ ቢዚ (ባተሌ) በማድረግና በየጊዜው እየሰበሰብኩ በማስጨፈር በዚህ ብቻ እንዲረኩ በማድረግ
በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩትን መሠረታዊ ፖለቲካዊና የዜግነት መብታቸውን እንዳይጠይቁ እንዳያስቡ አዘናጋበታለሁ!”
ብሎ በማሰብ ነበር ሁለቱን የጠፉ ባሕሎች ከጠፉበት ፈልጎ በማውጣት
ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ያደረገው የነበረው፡፡
ነገር ግን ወያኔ ገዳን እና እሬቻን የሌላቸውን ገጽታ አላብሶ በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ የኦሮሞን ሕዝብ
ከመደለሉ፣ ከመሸንገሉ፣ ከማታለሉ በፊት የማስመዝገብ ሒደቱ  ረጅም ጊዜ ወሰደበትና ጸድቆ ለማታለል ከመቻሉ በፊት
የኦሮሞ ሕዝብ የወያኔ ሕገመንግሥት የፈቀደለትን የይስሙላ መብትና ጥቅም ማግኘት እንዳለበት ተገንዝቦ ባሳለፍናቸው
ሁለት ዓመታት ባያቹህትና በምታውቁት መልኩ በመጠየቅ ወያኔ እንደሚያስበው ቂል አለመሆኑን አስመሰከረ፣ የዘገየው
የወያኔ መደለያም የታሰበለትን ግብ ሳያሳካ ቀረ እንጅ እሬቻም ሆነ ገዳ በዓለም ቅርስነት የመመዝገብ አቅምና
ብቃት ስላላቸው አልነበረም ወያኔ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ ብዙ ደክሞበት የነበረው፡፡
ምክንያቱም ከዓመታት በፊትም እንደተናገርኩት በገዳ ሥርዓት በመሪነት የሚሾመው አባ ገዳ በመባል የሚጠራው ሰው
ቢያንስ ቢያንስ የሌላ ጎሳ ወይም ብሔረሰብ አባል የሆነን አንድ ሰው የሰለበ መሆን እንዳለበት ይደነግጋልና
ነው፡፡ ለአባገዳነት በሚደረገው የምርጫ ሒደት በርካታ ሰው የሰለበ ሰው የተሻለ የተመራጭነት ዕድል ያገኛል፡፡
ሌላው ቢቀር ግን አንድ ሰው ያልሰለበ ሰው ለአባገዳነት በፍጹም ብቁ አይደለም፡፡ አባገዳዎች የወንድ ብልት ቅርጽ
ያለው ምስል በጌጥ መልክ እንደ ቀንድ ግንባራቸው ላይ ቀስረው የሚያስሩት ይሄንን ለማመላከት ነው፡፡ አውሬ ወይም
ለማደን አስቸጋሪ የሆነን እንስሳ የገደለ አዳኝ የገደለውን አውሬ ወይም እንስሳ ጥርስ፣ ጎፈር፣ ቀንድ፣ ለምድ
ወይም አንዳች ነገር “የዚህ አውሬ ገዳይ ነኝ!” ለማለት ምልክቱን አንገቱ ላይ ወይም ጆሮው ላይ
እንደሚያንጠለጥለው ወይም ጭንቅላቱ ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ ማለት ነው፡፡ በዚሁ ልማድ እነዚህም ሰው የሰለቡ
መሆናቸውን ለማመላከት ለመግለጥ የወንድ ብልት ቅርጽ ያለውን ምሥል ግንባራቸው ላይ ያደርጋሉ፡፡
የዚህ በጌጥ መልክ የተደረገ የወንድ ብልት ቅርጽ ምሥል ምንነት፣ ዓላማና መልእክት ይሄው ነው ሌላ ነገር
የለውም፡፡ ዛሬ ላይ ያሉ የገዳ ሥርዓት አራማጆችና ትንሣኤ የሰጠው ወያኔ ሥራዓቱ የደነገገውን የመስለብን
ግዴታነት ቢሸፋፍኑትም በግልጽ በተቆረጠ የወንድ ብልት ቅርጽ ግንባር ላይ የሚቀሰረውን የወንድ ብልት ምስል
የባሕላዊ ትውፊት ግን መደበቅ አልቻሉም፡፡
እሬቻም እንዲሁ ችግር ያለበት ባሕላዊ ሥርዓት ነው፡፡ አሁን አሁን የሌለውና የማይፈጸምበት ለማስመሰል ጥረት
ይደረግ እንጅ እሬቻ ዋነኛ የባዕድ አምልኮ መፈጸሚያ መድረክ ነው፡፡ ወያኔ እሬቻን ከጠፋበት ፈልጎ ወደ መድረክ
ያመጣበትና ሰብስቦ እያስጨፈረ ሰፊ የብዙኃን መገናኛ ሽፋን በመስጠት እንደገና ለማስተዋወቅ ብዙ የደከመበት
ምክንያትና ዓላማም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የሆነውን ኦሮሞን ሕዝብ ክፍል “ምን የመሰለ የራሳቹህ ሀገር
በቀል ባሕላዊ እምነት አላቹህ! ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጣ መጤ ሃይማኖት አያስፈልጋቹህም!” እያለ በመስበክ
ከክርስትና ለማስወጣት ለመለየትና ከአማራ ጋር ያለውን ትስስርና አንድነት ለመበጠስ ለማራራቅ ነው ሌላ አይደለም!
በብዙ አካባቢዎችም የወያኔ/ኦሕዴድ ካድሬዎች በግልጽ ይሄንን ሲሰብኩ፣ በኦሮሞ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች ላይ
ሃይማኖታቸውን የሚያስጥል ጫና ሲያሳድሩ ተስተውለዋል፡፡
ወያኔ ከአናሳነቱ የተነሣ ባለበት በራስ ያለመተማመን ችግርና የሥነ ልቡና መታወክ ምክንያት የአማራና ኦሮሞ
ፍቅርና ስምም መሆን ለእሱ አደጋ እንደሆነ ስለሚያምን በተቻለው መጠን ሐሰተኛና የፈጠራ ታሪክ በመንዛትም ጭምር
ኦሮሞ አማራን በጠላትነት እንዲመለከትና ለመቸውም ፍቅር የማይሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከበረሃ ጀምሮ ጥረት
ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሸርና ሸፍጥ ሸአቢያንም ይመለከታል፡፡ ወያኔና ሸአቢያ “ሥልጣን
ልንይዝና በሥልጣን ላይ ልንኖር የምንችለው ሁለቱንም አብላጫ ቁጥር ያላቸውን ብሔረሰቦች አማራና ኦሮሞን ፍቅር
ስምም እንዳይሆኑ በጠላትነት እንዲተያዩ እንዲፈላለጉ ማድረግ እስከቻልን ጊዜ ድረስ ብቻ ነው!” ብለው በማመናቸው
ገና ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ጀምረው ነበር አማራና ኦሮሞ በጠላትነት እንዲተያይ የሚያደርግ ኢሰብአዊ የጅምላ
ጭፍጨፋ ወለጋ ባሉ አማሮች ላይ በኦነግ ስም እንዲፈጸም ያደረጉት፡፡
ኦነግ ግን ወያኔና ሸአቢያ ለእሱ በማይጠቅም መልኩ መጠቀሚያ እንዳደረጉትና ይሄ ድርጊትም ለእሱ፣ ለኦሮሞ ሕዝብና
ለሀገርም የማይጠቅም መሆኑን እንዲሁም በላዩላይ የተሠራበትን ሰይጣናዊ ሸፍጥ ከነአካቴው እስከዛሬ ድረስም የገባው
አይመስለኝም፡፡
እናም ወያኔ የአማራንና የኦሮሞን ቅርርብ ዝምድናና አንድነት የማይፈልግበትና እስከዚህ ድረስ ወርዶ
የሚያገናኛቸውን ገመድ ሁሉ ለመበጠስ የሚጥርበት ምክንያት ይሄው ነው፡፡
ወደቀደመው ነጥባችን እንመለስና አሁን ገዳ ተመዝግቧል እሬቻ ገና እየጠበቀ ነው፡፡ አንድ የማይዳሰስን ቅርስ
በዓለም አቀፉ ድርጅት ለማስመዝገብ ሁለት ዐበይት መሥፈርቶችን ማለፍ የግድ ይጠበቅበታል፡፡ እነሱም በሰብእና
ወይም በሰብአዊነት እና በሥልጣኔ ላይ አንዳችም አሉታዊ ውጤት የማያደርስ የማይፈጸምበት፣ ሰብአዊነትን
የሚያከብርና ለሥልጣኔ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆን የግድ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት እሬቻም ሆነ
ገዳ በማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ወካይ ቅርስነት የመመዝገብ ብቃት ፈጽሞ እንደሌላቸው መረዳት እንችላለን፡፡ ገዳ
የሰው ልጅ እንዲሰለብ የሚያደርግ፣ በሰው ልጅ ላይ ኢሰብአዊ ጥቃት እንዲፈጸም የሚያስገድድ ሥርዓት በመሆኑ
ሲሆን፡፡ እሬቻ ደግሞ የሰው ልጅን ሥልጣኔ ወደ ኋላ የሚመልስ የባዕድ አምልኮ ድርጊት የማስፈጸሚያ መድረክ
በመሆኑ፡፡ ወያኔ ግን የምታገኘውን ርካሽና ሸፍጠኛ ትርፏን ለማግኘት በመጎምጀት ይሄን ይሄን ጉድ ሸፋፍና ደብቃና
ጥሩ ጥሩ ቀለም ቀባብታ ስትለፍፍ ኖረች ኖረችና ገዳን “ድንቅ የሆነ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት!”
በማለት፣ እሬቻንም እንዲሁ “በባሕላዊ እምነት የሚፈጸም ድንቅ የምሥጋና ሥርዓት!” በማለት እንዳለቻቸው አስመስላ
በማቅረብ ለማስመዝገብ ብዙ ጥረት አደረገች፤ አንዱ ተሳክቶላታል አንዱ ይቀራታል፡፡
ከዚሁ በዓለም አቀፍ ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ጉዳይ ሳንወጣ እግረመንገዴን መመዝገብ ስላለባቸው ቅርሶቻችንን
ሳላነሣው የማላልፈው ጉዳይ አለ፡፡ ሀገራችን በርካታ ምናልባትም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅርሶችን የማስመዝገብና በላቀ
ደረጃ ከሌሎች ሀገራት ተለይታ ለመታየት የሚያስችላት ዕምቅ አቅም እንዳላት ይሰማኛል፡፡ አንዳንድ ሀገራት
የተመዘገበላቸውን የማይዳሰስ ቅርስ ስታዩ የእኛ እሴቶች በጣም የላቁና የበለጸጉ ከመሆናቸው የተነሣ “አሁን ይሄም
ዋጋ ኖሮት ነው ለመመዝገብ የበቃው?” ያሰኛቹሀል፡፡ ወደፊት እንዲያው “ወያኔ እንደማያደርገው በሚገባ ስለማውቅ
ነው፤ ጭራሽ እንዲያውም ሊያጠፋ እየታገለ ነው!” ነገር ግን ወደፊት ነፍስ ያለው መንግሥት ቢመጣ ሊያስመዘግባቸው
ይገባል! ብቃት አላቸው ብቻ ሳይሆን “የሚደርስባቸውም የለም!” ከምላቸው ሀብቶች ጥቂቶቹንና አሁን ስለዚሁ ጉዳይ
ሳስብ በቅርብ ትውስ ያሉኝን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
1ኛ. የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ያሬድ ልዩ የዜማ ሀብት ከነምልክቱ ለምዕራባውያኑ ኖታ (የዜማ ምልክት)
ጭምር መሠረት በመሆኑ፡፡
2ኛ. አሁንም ከቤተክርስቲያን ነው፤ የቅኔ ትምህርት በረቀቀና በተለየ ባሕርይው፣ ቃላዊ የአጠናንና የአቀራረብ
ስልቱ እንዲሁም የፍልስፍና መድረክነቱ፡፡
3ኛ. አሁንም ከቤተክርስቲያን ነው፡፡ ምን እኮ ይህቺ የኢትዮጵያ  ቤተክርስቲያን የሁለንተናችን መሠረት
የሥልጣኔአችን ምንጭ በመሆኗ ሌላው ቀርቶ ከባሕላዊ እሴቶቻችን እንኳ የእሷ አሻራ ያላረፈበት አንድም እሴት ሀብት
የለንም እኮ! እና ሦስተኛው የቁም ጽሕፈት በልዩ አጣጣሉና የአጻጻፍ ስልቱ ምክንያት ከነብራናና ቀለም
አዘገጃጀቱ፡፡
4ኛ. የዘመን አቆጣጠራችን፡፡ ዓመተ ምሕረትን (A.D) በተመለከተ ከእኛ ጋራ በአንድ ስንጠቀም ቆይተን የቫቲካን
መነኮሳት ለምሳሌ እንደ ፓፓ ጎርጎሪዮስ ሁለተኛ ያሉት አዛቡትና አቆጣጠራቸው ከእኛ ሊለይ ቢችልም መላው ዓለም
እየተጠቀመበት ያለው የደቂቃ፣ የሰዓት፣ የዕለት፣ የሳምንት፣ የወር፣ የዓመት ልኬትና ቀመሩ ከእኛ የተወሰደ
በመሆኑ እንደባለቤትነታችን በራሳችን ስም ማስመዝገብ ይኖርብናል፡፡
ይሄንን ሀብታችንን በተመለከተ “የኢትዮጵያ አይደለም የግብጽ ነው!” የሚሉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ አባባል
ስሕተት ነው፡፡ እሴቱ የእኛ የራሳችን ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው ግብጻዊው የዘመን አቆጣጠር ሊቅ አቡሻክር
(አቡሻኽር) በስሙ በተሠየመለት መጽሐፉ ላይ “የኢትዮጵያ ሰዎችም ዘመናቸውን የሚለውጡት በመስከረም ወር ላይ
ነው!” በማለት ለቀመረው የዘመን አቆጣጠር ትክክለኛነት ማረጋገጫዎችና ሪፈረንስ (ማጣቀሻ) አድርጎ ጠቅሶናል፡፡
ይሄ አነጋገሩም በተዘዋዋሪ የቀመረው የዘመን አቆጣጠር ምንጭ እኛ መሆናችንንና ከሱ ቀመር አስቀድሞ የዘመን
መቁጠሪያ ቀመር ያለን መሆኑን  ያረጋግጣል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠራችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ስንልም ምንጯ ከሕገ ልቡና ጀምራ የነበረችው
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ናት ወይም እግዚአብሔር ነው ማለታችን ነው እንጅ ዕብራውያን ናቸው ማለታችን
አይደለም፡፡ የዕብራውያኑ አባቶች የዘመን አቆጣጠር ስሌት ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን የቻለው የአቆጣጠራቸው ምንጩ
እግዚአብሔር በመሆኑ ነው እንጅ እኛ ከእነሱ ስለወሰድን አይደለም የተመሳሰለው፡፡ ይሁንና አይሁድ የሰቀሉት
ክርስቶስ መሲሕ እንደነበር ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የአይሁድ መምህራንን ሱባኤ ቆጥሮ፣ ዘመን ዘርዝሮ፣
ትንቢት ተርጉሞ በክርክር ስለረታቸው አፍረው፥ ሲወቀሱና ሲከሰሱ እንዳይኖሩ በማሰብ ዘመኑን ስላሳከሩት ሱባኤውን
ስላምታቱት አሁን አይሁድ የሚጠቀሙበት የዘመን አቆጣጠርቅ ቀመር ከእኛ የተለየ ሊሆን ችሏል፡፡ በመሆኑም
ያልተሳከረው የዘመን አቆጣጠር አሁንም ድረስ በእኛው እጅ ላይ ብቻ ይገኛል፡፡ ይህን በተመለከተ በርካታ ዝርዝር
መረጃዎችና የመከራከሪያ ነጥቦች በእጃችን ያለ በመሆኑ መዝጋቢው የዓለምአቀፍ ድርጅት ቅንነቱ ካለው ቤተክርስቲያን
ማሳመን ትችላለችና ሊመዘገብ ይገባል፡፡
5ኛ. ይሄኛው እሴት ደግሞ ከአማራ ብሔረሰብ የተገኘ ነው፡፡ በጣም ያሳዝናል! ይህ እሴታችን አሁን ላይ የጠፋ
ይመስለኛል፡፡ ለመጥፋቱ ደርግና ያ ትውልድ (ሀገሪቱን ከሥሯ ነቅሎ የትም የጣላት ደንቆሮው ትውልድ) ትልቁን
አስተዋጽኦ አበርከተዋል፡፡ ደርግ “የፊውዳል!” ወይም “ፊውዳላዊ ነው!” እያለ ካጠፋብን በርካታ እሴቶቻችን
አንዱና በመጥፋቱ በጣም የሚያንገበግበኝም ነው፡፡ እሴቱ ጥንታዊና ባሕላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት ሲሆን “በልሃ
ልበልሃ!” (Verbal debate) በመባል የሚታወቀው የእሰጥ አገባ (Give & take) ሙግት ነው፡፡
ደርግና ያ ትውልድ ይሄንን የበልሃ ልበልሃ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት ሥልጡን ወይም ዘመናዊ ባሉት ነገር ግን
እምኑም በማይደርስ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት ተክተው ነው እንዲጠፋ ያደረጉት፡፡ ይሄንን የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት
ባንደርስበትም ዋጋው (ቫሊዩ) የገባቸው ከያኔያን ለማስታወሻነት ጥቂት ተውኔቶች በዚህ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት
ዓይነት በቴሌቪዥን (በምርዓየ ኩነት) አስቀርጸውት ብዙዎቻችን እንዳየነው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ይሄንን ባሕላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት በሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች ከሚደረጉት የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓቶች ለየት
የሚያደርገው እሴቱ ምንድን ነው? ከተባለ ኪናዊ ገጽታው ነው፡፡ ሥነኪንን (በዘልማድ ኪነጥበብን) ከፍትሕ ሥርዓት
ጋር ያዋሐደ በመሆኑ፡፡ ዓለም ከሚጠቀምበት ተለምዷዊና አሰልቺ የፍትሕ አሰጣጥ ሒደት ብዙ እርምጃዎችን ወደፊት
በመሔድ ሥነኪንን በማዋሐድ የፍትሕ ሒደቱን አዝናኝ፣ መሳጭ፣ ማራኪ፣ አስተማሪ ወዘተርፈ. በማድረጉ ነው፡፡
ሙግቱ ብይኑና ውሳኔው የሚሰጠው ወይም የሚደረገው በቃል በሚቀርብ የግጥም ትወና ሲሆን ግጥሙም ዝግጅት ተደርጎበት
እቤት ተገጥሞ መጥቶ ለችሎት የሚቀርብ ሳይሆን እዛው ላይ ሙግቱ በሚቀርብበት ሰዓት ተሟጋቾቹ ወይም ምስለኔዎቹ
(ስለ ተበዳይ ወይም በዳይ ጥብቅና ቆመው የሚከራከሩት) በሚከራከሩበት ወይም በሚሟገቱበት ቅጽበት እዚያው ላይ
ጉዳዩን ፣ የመሟገቻ ነጥቡን በደንብ አድርጎ ሊገልጽ በሚችልበት መልኩ አእዚያው ላይ ገጥሞ ደቂቃ እንኳን ባልሞላ
ልዩነት ከተሟጋቹ አፍ ነጥቆ በቃል ያለ መዝገብ የሚቀርብ የሙግት ዓይነት በመሆኑ ነው፡፡
ጠንካራ ሐሳብን ወይም የሙግት ነጥብን ማቅረቡ አንድ ከባድ ሥራ ሆኖ እያለ እንደገና ደግሞ ይሄንኑ ሐሳብ ወይም
የመሟገቻ ነጥብ ጠንካራና ሳቢ በሆነ፣ በተመረጡ ቃላት በተከሸነ በሥነ ቃል በተዋበ ግጥም እዚያው ላይ ደርሶና
አጣፍጦ ማቅረቡ ምን ያህል እጅግ አስቸጋሪና የማይታመን የላቀ ብቃትና ችሎታ እንደሆነ ሁሉም መገንዘብ የሚችለው
እውነት ይመስለኛል፡፡ ይህ ብርቅየ ቅርስ የሰው ልጅ ድንቅና የላቀ የማሰብና ነገሮችን ያለ ሰነድ በጭንቅላት ብቻ
የመያዝ ችሎታው የታየበት ቅርስ በመሆኑ የዓለማችን ወይም የሰው ልጆች ድንቅ ቅርስ ነው፡፡ የእነዚህን
የጠቀስኳቸውን እሴቶች የሚያክል አስደናቂ ዓለም አቀፍ የማይዳሰሱ ወካይ ቅርስ የትም ቦታ ቢሆን ያለ
አይመስለኝም፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከመስቀል በዓል አከባበር በተጨማሪም የጥምቀት በዓልም አለ ወዘተረፈ.፡፡
እንግዲህ እነኝህ ናቸው በቅርብ ትውስ ያሉኝ፡፡ እኔ የማውቀውን ጠቁሜያለሁ እናንተ ደግሞ ከየብሔረሰቡ
የምታውቁትን ባሕልና እሴት ጠቁሙ፡፡ አደራ ግን በጎሳ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ስሌት ሔዳቹህ እንደወያኔ
አሳፋሪና አሸማቃቂውን ሁሉ የሌለውን መልካም ገጽታ እየሰጣቹህ፣ እያደሳቹህ፣ እየጠጋገናቹህ ወይም እየቀባባቹህ
እንዳታቀርቡ!
በሚዳሰሱ ቅርሶች (Tangible Heritages) ዘርፍ ግን በዓለም አቀፉ ድርጅት መሥፈርት መሠረት ሊደርስብን
የሚችል አንድም ሀገር አይኖርም! ተንቀሳቃሾቹ ተዘርፈው ካላለቁ በዐሥር ሽዎች የሚቆጠሩ ቅርሶችን ልናስመዘግብ
እንችላለን፡፡ ጨርሻለሁ!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: