The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የእሳት እራት ራሷን ለመታደግ ቀለሟን ቀየረች – ማርእሸት መሸሻ

amara-revolution

ታላቁ የዝግመተ ለውጥ (evolution) ሳይንቲስት ቻርለስ ዳርዊን የነፍሳት ስነ ነገር (Origin of Species) በተባለው ምርምሩ ላይ የቀመረው ታሪክ አለ። ይህም አንዲት የትንሽ እሳት እራት ዘር (the peppered moth) በህልውናዋ ላይ የተደቀነባትን ድንገተኛ አደጋ እንዴት አድርጋ እንደተወጣችው የሚተርከው ነገር ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1880ወቹ ዓመታት የተቀሰቀሰው የኢንዱስትሪ አብዮት (industrial revolution) ብዙም ሳይውል ሳያድር የታላቋን ብሪታንያ ገጠር በውበት ኣልብሶት የነበረውን፤ ቀለሙ ነጣ ያለ ቅጠል የሸፈነው ደንና ጫካ ከየፋብሪካው የተነነው ቆሻሻ ተመልሶ ወደ ህዋ መጥቆ፣ ወደ መሬት ዝናብ ሆኖ ተመልሶ ወርዶ፤ አገሪቱን በጥቅርሻ አለበሳት። ደንና ጫካው ቅጠሉ ነጣ ያለ በነበረበት ጊዜ የምርምሩ አርዕስት የሆነችው እሳት እራት የነበራት ቀለም ነጣ ያለ ነበረ። ከመኖሪያዋና ከአካባቢዋም የሷም ቀለም በመዋሃዱ ምክንያት ራሷን ከወፍ ዕራት ለመሆን አድኗት ነበር። ቅጠሎች በጥቅርሻ ሲሸፈኑ ግን በድንገት ተጋለጠች። ከአካባቢዋ ቀለም የእሳት ራቷ ቀለም ነጥቶ በመታየቷም አዳኝ ወፎች በቀላሉ ይለቅሟት ጀመር። ዘሯ በሙሉ ህልውናው ለአደጋ ተጋለጠ።

ድንቅና አስገራሚ የሆነ ተፈጥሮ ግን ለዚች ህልውናዋ ለተጋለጠ እሳት እራት ዝግመተ ለውጥ እንድታካሂድ አደረጋት። ቶሎ ብላም ከአካባቢዋ ጋር ለማስማማት ቀለሟን ከንጣት ወደ ጥቁረት ቀየረችው። ከመኖሪያዋና ሳይፈልግ ከጠቆረው ቅጠል ጋር ስትመሳሰልም በኣዳኝ ወፍ ተለቅሞ ከማለቅ ራሷን አዳነች። ራሷን ከአደጋ ለማዳን ያሻሻለችው ተፈጥሯዊ ዘረ መልም (modified genes) ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ የህይወት ተሃድሶ በማድረግ ከአዳኝ ወፎች ለመትረፍ በቃች ይባላል።

ታዲያ አንዲት ታናሽ ፍጡር የእሳት እራት ራሷን ለውጣ ነፍሷን ስታድን፣ የተከታዩን ትውልድ ህልውናም ስታረጋግጥ፤ አማራው የተቀነበትን አደጋ ተገንዝቦ ያሁኑንም ሆነ የመጭውን ትውልድ ህልውና ለማረጋገጥ ራሱን ማዘጋጀት ያቃተው ለምን ይሆን? የአማራው ጥያቄ የህልውና ወይም የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው ተብሎ ብዙ መረጃ በድምጽ፣ በምስል፣ በመጽሃፍትና በእማኞች ቀርቧል። እነኝህ መረጃወች በአማራው ላይ በአማራነቱ ምክንያት የደረሰበትን ዘሩን ለማጥፋት የተፈጸመበት ድርጊት (genocide)፣ ሰብዓዊ ዕልቂት (crimes against humanity)፣ መፈናቀል (internal displacement)፣ የመሬትና የሌሎች ምጣኔ ሃብታዊ ዝርፊያና ነጠቃ፣ የፖለቲካና ማህበረ ሰብዓዊ / ባህላዊ መብቶች ገፈፋ ኣሁንም ያላቆመ መሆኑን ያመላክቱናል። ተጨማሪ መረጃ ለሚፈልግ http://www.aapo2nd.org ወይም http://www.moreshwegenie.org በመግባት መገንዘብ ይቻላል።

ይህን አጭር ፅሁፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ሰዓት አማራው ራሱን ከጥፋት ለመከላከል ከወያኔና ግብረ አበሮቹ ጋር ትንቅንቅ በተያያዘበት ወቅት፤ ከአብራኩ የተፈጠረው፤ የስጋውና የኣጥንቱ ክፋይ የሆነው የአማራ ልሂቅ ግን የእሳት እራቷን ያህል እንኳን መጠነ ሰፊና ስር ነቀል ለውጥ በሚያስፈልግበትና አማራው አንድ ወጥና ሁለገብ በሆነ የፖለቲካ ድርጅት ተሰባስቦ ያለውጭ ተጽዕኖ እንደ አንድ ዘር የመቀጠል ተፈጥሯዊ መብቱን የሚያረጋግጥበትን መድህን መስጠት ቀርቶ በአማራነት መደራጀት ስህተት እንደሆነ እየሰበከን ይገኛል። ይህንን የቅንጦት ሃሳዊ ልሂቅ (pseudo intellectual) ድምዳሜ ለደረሳችሁ አማራ ልሂቃን ወገኖቸ በሙሉ የማቀርብላችሁ አንድ ጥያቄ አለኝ። ለመሆኑ በየአቅጣጫው የተቀጣጠለው ፀረ ወያኔ ህዝባዊ አመጽ ምን አይነት ድምዳሜ እንደሚያጋጥመውና የወገናችሁ የአማራው እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ቆም ብላችሁ አስባችኋል? ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮች በዚህ አጭር ጽሁፍ በዝርዝር ማቅረብ የሰፊውን ህዝብ ስነልቦና ሊያስደነግጥ ይችላል። ነገር ግን የትግሉ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችልና ለያንዳንዱ ክስተት ዝግጅት የማድረግ አስቸኳይ ግዴታ እንዳለብን አምናለሁ። ያለፉትን ዘመናት የተለያዩ ሃገራት የነጻነትና የመብት ትግል ታሪክ ስንመረምር በሃገራችን እየተካሄደ ያለው ትግልም ተመሳሳይ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል መገመት የሮኬት ሳይንስ አይደለም።

አንዳንዶቻችን እንደምንመኘው ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድ ልብ አስበው ሁላችንም የምንመኘውን ዳር ድምበሯ የተከበረች ኣገር፤ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት የሰፈነበት መልካም አስተዳደር መመስረት ከተቻለ እሰየው። በፌዴሬሽንም ሆነ ማዕከላዊ መንግስት፤ ወደጥንታዊው አስራ ሶስት ወይም አስራ አራት ጠቅላይ ግዛትም ሆነ ዘጠና ስምንት አውራጃ ፤ ወይም በቋንቋና ዘር መስፈርት ያልተዋቀረ ዘመናዊ ክፍለ ሃገራዊ ኣስተዳደር በሰላም ለመድረስ ከቻልን ማንም የሚጠላው የለም። ተጨባጭ ሁኔታው ግን ያ አይደለም። ኢትዮጵያን አፈራርሰን በመቃብሯ ላይ አዲሱን ስርዓት (ስርዓት አልባነትን) እንገነባለን። ኢትዮጵያ የሚለው ቃልና ቅኝ ግዛት አንድ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ወይም ሃበሻ የሚባሉት ትግሬወችና አማራወች እንጅ ሌላውን አይጨምርም ወዘተ ከሚሉት ጀምሮ ለተበደልነው የዘመናት ታሪካችን ካሳ ይከፈለን እስከሚሉት ድረስ በመሃል ብዙ እርስ በርስ የሚጣረዙና ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ውጥንቅጥ ሃሳቦች ሞልተዋል።

ትግሉ ወዴት እንደሚያመራ ተራው ሰውም፣ ፖለቲካ ሳይንቲስቱም፣ ፈላስፋውም ሆነ ጠንቋይ ቀላቢውም መተንበይ እንጅ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ማንም የለም።። የአሜሪካዊው ስነመለኮታዊ ምሁር (Theologian) ራይንሆልድ ኒቡህርን ምክርና የፀጥታ ጸሎት ተግባራዊ ማድረግ ግን ግድ ይላል። ሲተረጎም እንዲህ ነው። “አቤቱ እግዚኣብሔር ሆይ፤ መለወጥ የማልችላቸውን ነገሮች ሁሉ እንድቀበል መረጋጋትን፤ መለወጥ የምችላቸውን ሁሉ እንድለውጥ ቆራጥነትን፤ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንድገነዘብ ደግሞ ጥበብን ስጠኝ – God, grant me the serenity to accept the things I cannot change, Courage to change the things I can, And wisdom to know the difference”.

አማራው ራሱን ማዳንና የምንወዳትን አገራችን ኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለበት በኢትዮጵያዊነትም ሆነ በአማራነት በመደራጀት የተሰለፈው ሁሉ የተቀበለው ታሪካዊ ግዴታና ሃላፊነት እንደሆነም መሰረታዊ ስምምነት አለ። ልዩነታችን፤ “ቤት ሲቃጠል፣ መጀመሪያ ባለቤቱ፣ ከዚያ ጎረቤቱ ወይም ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫየን አለች” በሚሉትና የትግል ሃሳባቸውን በሙሉ “በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ብቻ” በሚያጠነጥኑት መካከል ነው። ለዚህ ለሁለተኛው አስተሳሰብ ታዳሚ አማሮች ነው የሚቀጥለው መማጸን የሚቀርበው።

መማጸኛ ፩ ፡ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። አበይት ብዙሃን አማራው (overwhelming majority) ከኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ ኣገር አስቦም አልሞም አያውቅም። የአማራውን ህልውና ማስጠበቅ ማለት የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ማለት ነው። ሁለቱ የሚጋጩ ወይም የሚቃረኑ አይደሉም።

መማጸኛ ፪ ፡ አማራውን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር አንድ የሚያደርገው ሰነ ልቦናዊና ታሪካዊ ትስስር ቢኖርም ያለፉት ፵ ዓመታት የአማራው የብቻ ሰቆቃ ዘመን እንደነበረና አሁንም እንዳላባራ፤ በየጊዜውም የድረስልኝ ጥያቄ በወገኖቻችን እየቀረበ በመሆኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ማተበ ቢስነትና ኢኣማራነት ነው። ይህ ህዝብ ከልጆቹ ደረስኩልህ አይዞህ የሚል አወንታዊ መልስ ይፈልጋል፤ ይጠብቃልም። የአማራው ትግል በቁሳቁስ ዕጦት ከኮሰሰ፤ በወታደራዊ ሃይል ከተጨፈለቀ፤ ወይም ባጭሩ ትግሉን ስኬታማ ሊያደርግ የሚችል ስልትና ብልሃት ባለመከተል አላስፈላጊ የሆነ ደም መፋሰስና ንብረት መውደም ከመጣ ለዘለዓለም የማይሽር ቁስል እንደሚተከል ዕወቁት።

መማጸኛ ፫፡ ወያኔ ትወድቅ ይሆን? ሳይሆን ኣሁን መቸ ትወድቃለች፤ ስትወድቅስ ምን ልታደርግ ትችላለች? የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ወያኔ ቂም የማትረሳ መሆኗ፣ ለምትጓጓለት ስልጣኗ አለመመቸት፣ ድቀትና ውድቀትም በሃላፊነት የፈረጀችው አማራውን በመሆኑ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሽሽቷም ሆነ ትግራይ ውስጥ መሽጋ የተቃጠለች መሬት (scorched earth) ፖሊሲ ልትፈጽም እንደምትችል፣ አቅሙና ምኞቱም እንዳላት መገመትና መዘጋጀት ያስፈልጋል። ለዚህ ያጥፍቶ መጥፋት ሸሁራራ አስተሳሰብ ሰለባ የሚሆነውም በትግራይ ዙሪያ ያለው አማራ መሆኑን ማወቅ አያዳግትም። የአላማጣን፣ ኮረምን፣ ወልቃይትን፣ ጠገዴንና ጠለምትን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መገንዘብና ይህን ሊመክት የሚችል ሃይል ማዘጋጀት ግዴታ ነው።
መማጸኛ ፬፡ የትግሉ ድምዳሜ የወያኔ መወገድ ብቻ አይደለም። ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚደረገው ትብብር፣ ክርክርና ድርድር የአማራውን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችለው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚስተካከል ሃይል (symmetric power) ሲኖረው ብቻ ነው። ይህ ሃይል ሊገኝ የሚችለውም ከራሱ ከአማራው ልጆች እንጅ ከሞግዚት ድርጅት ጥብቅና እናገኛለን ብሎ መጠበቅ የራስን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ የሞኝ ስልት ብቻ ሳይሆን፤ አበው “ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዶሮህን በቆቅ ለውጣት” ብለው እንደተረቱት ይሆናል።

መማጸኛ ፭፡ የህዝብ አልገዛም ባይነት እየጠነከረ ከመጣና ወያኔ አገሪቱን ማስተዳደር ካልቻለ ሊከሰቱ ከሚችሉት ዕውነታወች መሃል እጅግ በጣም የሚያስፈራው በየአካባቢው የጦር ቡድኖችና አበጋዞች መፈጠር ነው። አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት እንኳን የሚጋሩት ሶማልያውያን በመካከላቸው ባሉ ንዑስ ልዩነቶች የፈጠሩት ሁከትና ተከታዩ የኣስተዳደር ውድመት የነሱ ብቻ የ፴ ዓመት አባዜ ከመሆን አልፎ የመላ ኣፍሪካ መንግስታት ብዙ ህይወትና ንብረት እስካሁን ድረስ እየገበሩ ያለበት መፍትሄ አልባ ቀውስ እንደሆነ የታወቀ ነው። ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ሩብ የማታክለውን ሶማልያ የአንድ አህጉር ወታደራዊ ሃብት ሊቆጣጠር ካልቻለ ኢትዮጵያን የሚያክል ኣገር መቆጣጠር የሚችል ሃይል ከየት ሊመጣ ነው? በአሁኑ ጊዜና ሰዓት ምንም ላዕላይ ሃይል እንደሌለ መገንዘብና ህዝባዊው ትግል እየከፈለ ያለው ከፍተኛ መስዋዕትና፤ የዲሞክራሲና የፍትህ ራዕዩ እንዳይቀለበስ መከላከል አንድ ወጥ የሆነ፤ ሁለገብ የአማራ ድርጅት መተግበር ያለበት ታሪካዊ ግዴታ ነው።

መማጸኛ ፮፡ አማራው ኢትዮጵያን ለመታደግ የነበረው አስተዋጽዖ በአማራነቱ እንዳይደራጅ መንፈሱን ስላገተው የአማራው ጉዳይ ወደጓዳ ተጥሎ የነበረና ለዚህም ሁሉም የአማራ ልሂቃን ሃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ስህተት እንደሆነ፤ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታም አማራውን ከሌሎች ጋር ያልተስተካከለ ሃይል (assymetric power) እንደፈጠረበት መገንዘብ ይገባናል። እንደ ፋሽን በየጊዜው ከሚለዋወጠው ከድርጅቶች ጥምረትና ውህደት አንጻር እንኳን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ ሁለት ድርጅታዊ ግዝፍናን በመፍጠሩ አማራው በፈቃዱም ይሁን ከሌሎች ድርጅቶች ፈቃድና ፍላጎት መጥፋት ከጥምረትም ሆነ ከውህደት ተሽቀንጥሮ ይገኛል። ባሁኑ ወቅት ያሉት ሁለት ግዙፍ ውህደቶች አንደኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ እንቅስቃሴ በመባል የሚታወቀው አርበኞች ግንቦት ሰባት (Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracy)፤ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (Oromo Democratic Movement (ODF) ፤ የሲዳማ (Sidama People’s Democratic Movement)፣ የአፋር (Afar People’s Party)ን ያጣመረው ድርጅት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቦች አንድነት ለነጻነትና ለዲሞክራሲ (People’s Alliance for Freedom and Democracy) በመባል የሚታወቀው የኦሮሞ ነጻ ኣውጭ ግንባርን (Oromo Liberation Front (OLF)፣ የጋምቤላን (Gambella People Liberation Movement (GPLM))፣ ቤኒ ሻንጉል (Benshangul People Liberation Movement (BPLM)፣ ኦጋዴን (Ogaden National Liberation Front (ONLF) ና ሲዳማ (Sidama National Liberation Front (SNLF) ነጻ አውጭ ድርጅቶችን የሚያጠቃልለው ነው። አማራ በአማራነቱ መደራጀት ያስፈልገዋል ኣያስፈልገውም፤ ተገቢ ነው አይደለም የሚል ያለቀ የደቀቀ፤ የሞተ፤ እርባና ቢስ ክርክር ሆኗል። ለምን ቢባል ሌሎች በሙሉ አማራውን አግልለውታልና።

መማጸኛ ፯፡ አሁን አገራችን ካለችበት የትግሬ ብሄር ከሚያራምደው፤ ግፍ የሞላበት የብዝበዛና ጭቆና ስርዓት ስንላቀቅ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን የፖለቲካና ወታደራዊ ስሌቶች ካሁኑ አጠንጥኖና በትኖ በመረዳት፤ ሌሎች አገሮች ካጋጠማቸው ተሞክሮወች ትምህርት በመቅሰም፤ ለሁሉም ገጠመኞች በየረድፋቸው ምላሽ ይዞ መጠበቅ የአማራው ልሂቃን ግዴታቸው ነው። ግብር ገብሮ፤ ታክሱን ከፍሎ ያስተማራቸው ባላገር ባሁኗ ደቂቃ ወያኔን እየተፋለመ፤ ከሚገባው በላይ ድርሻውን እየተወጣና ከፍተኛ መስዋዕት እየከፈል ይገኛል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የወከሉ ድርጅቶች ነገ የተባበረ መንግስት ቢፈጥሩ (ለምሳሌም ከላይ በመማጸኛ ፮፡ የተቀሱትን ግዙፍ ድርጅታዊ ስብስቦችን መመልከት ይገባል) የአማራ ልሂቃን የሚሰጧቸው አሉታዊ ወይም አወንታዊ መልስ አለ ወይ? ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽንስ ለአማራው ይበጃል ወይስ ይከፋል? የአማራውንስ ቁሳዊ ህይወት ለማሳደግና ለማበልጽግ ምን ዓይነት የምጣኔ ሃብት ስልት ብንጠቀም ነው ድህነትን ማጥፋት የምንችለው? አማራው በመላ ኢትዮጵያ ሃብቱን ጉልበቱንና አዕምሮውን ይዞ በነጻ በመዘዋወር ኑሮውን እንዲያበለጽግ የሚያስችል አስተሳሰብ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ተቀባይነትን አግኝቷል ወይስ አሁንም አማራው በራሱ አገርና በራሱም አካባቢ ባይተዋር ሊሆን ነው? እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ የአማራውን ልሂቃን ተሳትፎ የሚጠይቁና ከፍተኛ የሰው ሃይል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው።

አማራው በአማራነቱ መሰባሰብ፣ መምከርና መደራጅት አለበት ለሚለው ሃሳብ ከላይ የተዘረዘሩት መማጸኛወች ቀስቃሽ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ። ቤት ሲቃጠል መጀመሪያ ባለቤት፣ ቀጥሎም ጎረቤት ነውና። ይህችን አጭር ጽሁፍ ለመደምደም ያህል ሚስተር ስቲቨን ሶንድሃይም የመንጋ መንገድ ሰይጣን ጸጉር ቆራጭ (the demon barber of fleet street) በሚለው ቲያትራቸው “የኔ ጣፋጭ፤ የአለም ታሪክ ማለት ማን ማንን በላና ማን መብላት ቻለ ብቻ ነው” ያሉት በሳል አባባል ትዝ ይለኛል። ። አማራው ልጆቹ በወያኔ እንዳይበሉ፤ አማራው ልጆቹ በልተውም እንዲያድሩ የሚፈልግ ከሆነ በአማራነቱ ተደራጅቶ ህልውናውን ከማስጠበቅ ሌላ ምንም አማራጭ የለውም። አማራጭ አለ የሚሉም ቅንጦተኞች መሆናቸውን ተገንዝበው አማራውን ለመታደግ በቆራጥነት የተነሱትን ወንድሞቻቸውን ጉድጓድ ባይቆፍሩላቸውና ጭቃ ባይቀቧቸው ይመረጣል። ካልሆነም …….. “ጨው ለራስህ ብትል ጣፍጥ ካልሆነ ዲንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” ትልቅ የአበው ምክር ነው።

እግዚኣብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይጠብቅ!
የአማራው ህልውና በልጆቹ ይጠበቃል!
ጉራ ፈርዳ አይደገምም!

ታህሳስ ፳፻፱ December 2016
mareshetmeshesha@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: