The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የጀዋርን ንግግር መጠቀም የዋህነት ተንኮለኝነት ድንቁርና ወይስ ብስለት? [አያሌው መንበር]

ይህንን ፅሁፍ ለመፃፍ የተገደድኩት ሰዎች ሲወዛገቡ ስላየው እንጅ ጊዜየን ማጥፋት አልፈልግም ነበር።

አቶ ጀዋር መሃመድ

ጀዋር ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለእኔ ለአንድ ብላቴና የአማራ ወጣት ማለትም በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ ወይም ማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች መረጃ ሲቆፍር ለሚውል ቀርቶ ለሚሊዮን የኢህአፓ ውላጆችም ሆነ ለዚህ ትውልድ ቀላሉ ጥያቄ ነው።ጀዋር ለምን ጉዳይ መቸ እና እንዴት ይናገራል የሚለውን ለማወቅ ግን የፖለቲካ ሳይንስ የሚጠይቅ ይመስለኛል።

እናም እኔ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ባልሆንም በጠልፎ ልጣልህ ፖለቲካ ተወልጀ የእድሜየን አጋማሽ ስለያዝኩ ጀዋር ሰሞኑን የአማራ ብሄርተኝነትን አስመልክቶ ስለተናገረው የ14 ደቂቃ ንግግር (ዘሀበሻ ላይ ስለታተመውና እኔ ገፅ ላይም ስለለጠፍኩት) ትንሽ ልበል።

ጀዋር በሰሞኑ ንግግሩ የአማራ ብሄርተኝነት እና ተጋድሎ አንቀሳቃሾች እንኳን ልንገልፀው በማንችለው መልኩ ተንትኖታል ብየ እገምታለው።አብዛኛዎቻችን ሰው ባቦከው እና በጋገረው ማጉረስ እና መወደስ እንጅ አብስለን እየተመገብን አልመሰለኝም።ለማንኛውም ከንግግሩ በጥቂቱ ልግለፅ እስኪ፦

ጀዋር ይናገራል፦ “የአማራ ብሄርተኝነት ባለፉት አመታት በአማራው ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለን ስቃይና ጭቆና የመቃወም ብሄርተኝነት ነው፤ጤነኛ ወይም ፖዘቲቭ ዲሞክራቲክ ብሄርተኛ ነው፤ዳር ድንበሬን፣ ማንነቴን እንዲሁም ከአማራ ክልል ውስጥም ይሁን ውጭ የሚኖሩ አማራዎችን መብት ይከበር ነው ያለው፤የኦሮሞ ደም የእኔ ደም ነው፤እውነታ ላይ የተነሳ ተጋድሎ ነው፤ ወዘተ….
የአማራ ህዝብ የተቃወመው መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋና ጦርነት ያደረገበትን የውጭ ሀይልን ወይም ህወሃትን እና ና የውስጥ ሀይልን (በአማራ ህዝብ ስም የተሾመን የአማራን ህዝብ ጥቅም ያላስከበረ ብአዴንና አማራ የለም ሲል የነበረ የአማራን ልሂቅ ጭምር ነው።ይህም ህወሃት አማራ እንዳይደራጅ የድሮ ስርዓት ናፋቂ እያለ ሲያዳክመው የነበረውንና የታላቋ ትግራይ የምስረታ ህልሙን ያከሸፈ ትልቅ የፖለቲካ ፎርስ ነው፤

ጃዋር የአማራ ተጋድሎ በሌሎች ሀይሎች እንዴት ይታያል ሲል የተናገረው ደግሞ ይህ ነው፦

“ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት፣በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ በማህበራዊ ..የተሳሰረ ህዝብ ያላት መሆኗን ረስተው ከሸክላ እንደተሰራች ገንቦ የሚያስቧት የሚበረግጉ አሉ፤የሌላውን ህዝብ ብሄርተኛ ሲሳደብ የነበረው አሁን የራሱ ህዝብ በአንድነት ብሄርተኛ ሁኖ ሲመጣ ደነገጠ፤የአማራ ህዝብ ተጋድሎ ከማለት ይልቅ ስላስፈራቸው የጎጃም፣የጎንደር፣የደብረ ብርሃን ይሉታል፤የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሜቴን እነ ኮሎኔል ደመቀን ጨምረው ለማሳነስ ይሞክራሉ፤የድሮ ስርዓት ናፋቂ የሚለው የአማራ ተጋድሎን የሚመለከት አይመስለኝም፣ መፈክሮቹ Reactionary ሳይሆን Realistic ናቸው፤ የአማራ ህዝብ ጠመንጃ መያዝ ባህሉ ስለሆነ እንጅ violent Resistance አልነበረም፤ መፈክሮቹ የተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ነበሩ፤የአማራ ብሄርተኝነት በሀይማኖትም ሆነ በሌሎች ኢንስትቱሽንስ መሰረት ያለው ነው፤ሚዲያውን ስለተቆጣጠሩት ብቻ ለማፈን ይፈልጋሉ ግን መሰረት ስለሌላቸው አይችሉም Idealist እንጅ እንደ አማራ ተጋድሎ Realistic አይደሉም፣”…..ወዘተ በማለት ይናገራል።

ንግግሮቹን ከሞላ ጎደል ቃል በቃል ነው የወሰድኳቸው።እንግዲህ ከዚህ ተነስተን እስኪ የጀዋርን ጉዳይ እንመልከት።(#አስታውሱ መነሻየም መድረሻየም በ14 ደቂቃው ንግግር ብቻ ነው)

እንግዲህ የጀዋር ይህ ንግግሩ ለእኔ እንከን የማይወጣለት ነው።አብዛኛው ሰው ንግግሩን ሳይሰማ፣ብዙው ሰምቶም ሳይዋጥለት፣ጥቂቱ የማህበራዊ ሚዲያውን ውዥንብር ተመልክቶ ለመወደስ ወይም ግራ ተጋብቶ የተዛባና ግራ የተጋባ አስተያየት ሰንዝሯል።ለሁሉም ይሆናል ባልልም ለጥቂቶች ግን ይህ ጀዋር የተናገረው ለአማራው ህዝብ ትክክለኛ መልዕክት መሆኑን ለመግለፅ እወዳለው።

ጀዋር ስህተት የሚሆነው ለሁለት አካላት ነው።በአንድ በኩል የጃዋር #የአሁኑ_አመጣጥ_ትክክለኛ_ማንነቱ ነው ብለው #ለሚያምኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጃዋርን ዘመዶች አምነው #የፖለቲካ_ጋብቻ_ለፈፀሙት ነው።ጀዋር ሶስት ነገር ይፈልጋል፦አንደኛው #የአንድነት ሀይሉን መምታት ሲሆን ሁለተኛው #የአማራን_ወጣት_ቀልብ መሳብ ሶስተኛው ደግሞ #ህወሃትን ስጋት ውስጥ መክተት።ሁሉም ለእኔ እንደ አመጣጣቸው ነው የምቀበላቸው። እኛን አትራፊ የሚያርደጉም ናቸው።የአንድነት ሀይሉን ባከብርም ካለው #አግላይ አስተሳሰብ አንፃር አልደግፈውም።ለዚህ ብዙ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም (ጀዋርም ተናግሮታል እኔም ሆንኩ ሌሎች ጓደኞቸ በየ አጋጣሚው እየተናገርነው ነው።)እዚህ ላይ በODF በኩል የሚመጣን አካል ትልቅ የቤት ስራ እየሰጠውም መሆኑ ነው።ይህንንም በብልጠት ይጠቀምበታል።የአንድነት ሀይሉ በአማራ ውስጥ ቤዝ የለለው መሆኑንም ለመግለፅ እንዲሁ አፅንኦት ሰጥቶበታል (Idealist ሲል)።የአማራ ወጣት ልብ ውስጥ ባይገባ እንኳን ቀልብ ለመሳብ መሞከሩም የሚገርም አይደለም።ከዚህ በፊትም ያቀራርባሉ ባላቸው ጉዳዮች ሲያናግሩትም ሲናገርም ነበር። እዚህ ላይ አንድ የተሳሳተው የአማራ ወጣት በነፋስ የሚነዳ አለመሆኑን አለመገንዘቡ ቢሆንም ቀልብ ለመሳብ ሲል የተናገረው ንግግር ግን ነባራዊ ሀቅ ስለሆነ ሊተፋም ሊገፋም አይገባውም፤ እንደ ሁኔታው እንጠቀምበታለን፣እየተጠቀምንበትም ነው።የመጨረሻው ህወሃት እና አሽከሩ ብአዴን ላይ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት አለ።እናንተ ያሰባችሁት የአጋጭተን እንሾም ፖለቲካ አያዋጣም የሚል ሲሆን ከውስጣችሁ የጠነከረ አመራር ያለው ተጋድሎ እና ተቃውሞ ነው እያደረግን ያለነው በሚል።

ለአብዛኛው ትልቅ የራስ ምታት የሆነው ጀዋርና ከውስጡ የበቀለው አመለካከቱ መድሃኒት ላይኖረው ቢችልም የሚሻለው ግን ማግለል ነው ብየ አላምንም።

የሚናገርለትና የሚናገርበት ያጣው፣ተናጋሪዎቹና አሳቢዎቹ በአውሬ እየተበሉ ወይም እንዳይራመዱ በሽቦ አጥር እየተከበቡ የውሸት ስም እየተሰጣቸው ከትግሉ የተገለሉበት የዋሁ፣ የወላድ መካኑ የአማራ ህዝብ አንዳንዴ እንኳን ጠላቱ ሌላን ጠላት ለመውጋት ሲል እውነቱን ሲናገርለት እደግ ተመንደግ ባይባል እንኳን የንግግሩ ትክክለኛነትና ጠቃሚነት መግለፅ መቻል ነውሩ አይታየኝም።ጀዋር ያደረገው ይህንን ነው።
በዚህ ንግግሩ ግራ የተጋቡት አካላት #ጀዋር ምን ተናገረ ከማለታቸው በፊት
1.ጀዋር ማን ነው?ለምን ስለ አማራ ያወራል?
2.ጀዋር ምን ፈልጎ ነው የአንድነት ሀይሉን የሚተቸው?
3.እርሱ እኮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አይወድም ወዘተ ይላሉ።የረሱት ግን የምናወራው ዛሬ ስለተናገረው መሆኑን ነው።
ጀዋር እንደ እስስት የሚገለባበጠው ዛሬ አይደለም።ይህ ለአንድነቱ ብቻ ሳይሆን ለአናሳውም ጭምር ግልፅ ስጋት ነው።የቅርብ ጊዜ ንግግሮቹ እኮ ቁጭ ብዲግ እያደርጉ በስሜት የሚይዙ ወኔ ቀስቃሽ ሳይሆኑ ለአፀፋ የመሳሪያ ምላጭ የሚያስቡ ናቸው።ከሀገሩ ብሄሩን የሚያስቀድም የአባቱን ገድል የካደ የዘመኔ ወጣት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ዓርዓያ ሊሆን እንደማይችልም ግልፅ ነው።

እነ Tamer Shaaban እንዲህ ሲሉ፦”we are Egyptian,We are human, let’s be human, let’s be free”

ጃዋር እንዲህ ነው ያለው፦” Oromia shall be free, I am Oromo first,addis ababa kegna…etc

እኔና ሌሎች ንስር የአማራ ወጣቶችም እንኳንስ ከአማራ ገዳይ አንዱ ከሆነው ኦነግ ጉያ ያደገውን ጀዋርን ቀርቶ ስንዴን ከእንክርዳዱ የምንለየው ወንፊት ሳያስፈልገን ነው።ይልቁንም ወቅታዊ እና የማያሻማ ንግግሩን ተጠቅሞ የአማራን አላማ ለማሳካት መሞከር ብልህነት ነው ብየ አምናለው።

እናም የጀዋርን የዛሬ ንግግር ትክክለኛነት ሳረጋግጥ የትናንቱን ንግግሩን እንዲሁም የዛሬውን ፍላጎቱንና የነገውን እቅዱን ባለማወቅ አይደለም።ይህም የዋህነት አልያም ቂልነት አይመስለኝም።ይልቁንም ብልጠት ይመስለኛል።የጎንዮሽ አንድነትን ሲያጠነክር የአማራን አንድነት የማይፈልጉትን ለመውጋት ደግሞ አይነተኛ መሳሪያ ነው።በፖለቲካዊ ትርፋማነት የተሰላ መሆኑ ሳይገባችሁ ያላዋቂነት ከመሰላችሁ መልሴ ከመናገራችን/ከመሞንጨራችን በፊት የተፃፈ ማንበብ ይልመድብን ነው። እቃ ብናጣ በአንድ በላን ሆነ እንጅ ነገሩ የዛሬ ወጣቶች ከራሳችን ጉያ እኮ ስንት በጎ መስለው ሲዶልቱ የሚውሉም እንዳሉም ያውቃል።

ሲጠቃለል ጀዋር የተናገረው ስህተት አይደለም።ፊትና ኋላውን የመመልከትና የመተንበይ ጉዳይ የእኛ እንጅ የእርሱ አይደለም። ሰይጣንም ይናገር ንግግሩን በአግባቡ መጠቀም እንጅ ለምን ተናገረ ብሎ ቡራከረዩ አያዋጣም።አባቱ በቀደደው ሰንደቅ እየተደራደሩ እዚህ ላይ መፈንጨት ያስገምታል።መደምደሚያውም በጥላቻ ያልተጀመረው የአማራ ብሄርተኝነት በፍቅር ለቀረቡት ሁሉ ወዳጅ ነው የሚል ነው።አማራም ግን በማንነቱና በሀገሩ አይደራደርም።

ለማንኛውም የአማራ ትግል ውጤታማ የሚሆነው በራሱ ትንታግ የአማራ ልጆች እንጅ በወንጭፍ ሊመሩት በሚፈልጉት ወይም በአይነ ቁራኛ በሚያዩት አይደለም።መነሻውም መድረሻውም እውነት ነው።እውነት ደግሞ ያሸንፋል!!!እውነት ሁሉንም ያንበረክካል።እውነተኛው አማራም አሸናፊ ነው።ገና ምኑ ተነካና?ሁሉም ስለአማራ ይናገራሉ።

የድሮ ስርዓት ናፋቂው ወንድማችሁ አያሌው መንበር

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: