The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የእናቴ ልጅ ነኝ! በፍቃዱ ዘ ኃይሉ (ከቤቱ)

posted by Gheremew Araghaw

 

 53እቤቴ ከገባሁ ጀምሮ ወዳጅ ዘመዶቻችን ሁሉ ‹‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ›› እያሉኝ ነው፡፡ የ‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ› መልዕክቶቹ ግን ብዙውን ጊዜ በተጨማሪ ምክሮች ይታጀባሉ፡፡ በነገራችን ላይ፣ በተለይ እንደኔ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ላሉት ሰው መታሰር የሚከፋው የእነርሱ እንግልት ባሰበ ጊዜ ነው፡፡ እኔ ትልቅ ፈተና ገጥሞኛል ካልኩ፣ የእነርሱ፣ በተለይም በየሳምንቱ ‹‹አልቀርም›› እያለች የምትመላለሰው እናቴ ነገር ነው፡፡ እናም ‹እንኳን ተፈታህ› ባዮች ሁሉ የማይዘነጓት የእስር ቤት ሕመሜን፣ እናቴን ነው፡፡ ‹‹እባክህን፣ ለእናትህ ስትል እንዲህ ዓይነቱ ነገር ይቅርብህ›› ይሉኛል፡፡

እናቴ፣ የተወለደችው እና እስከ ዐሥራምናምን ዕድሜዋ ድረስ የኖረችው ሰሜን ሸዋ (መንዝ አካባቢ) ነው፡፡ በአካባቢው ባሕል መሠረት (አሁንም ድረስ) ሴቶችን ያለዕድሜያቸው በቤተሰብ ፈቃድ መዳር የተለመደ ነገር ነው፡፡ እናቴም ከዚህ ዓይነቱ ወግ ማምለጥ የምትችልበት ዕድል አልነበራትም፡፡ ወላጆቿ ገና በጨቅላነቷ ዳሯት፡፡ እናቴ፣ ዕኩያዋ ያልሆነውን ባሏን አልወደደችውም ነበር፡፡ በአካባቢው ባሕልና ወግ መሠረት አለመውደድ ደግሞ አይፈቀድላትም ነበር፡፡ ስለዚህ የወላጆቿን ፈቃድ ሽራ የራሷን ዕጣ ፈንታ በራሷ ለመወሰን ወሰነች፡፡ ይህ ውሳኔዋ ወላጆቿን የሚያስከፋ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሹኑ ተቀባይነት የማያገኝ ውሳኔ እንደሆነ አልጠፋትም፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈሪ ዕቅድ አውጥታ ተገበረችው፡፡ የልጅነት ስሟ ገበያነሽ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ያደረገችው ስሟን ወደ ዘነበች መቀየር ነው (በነገራችን ላይ በእኔና በአባቴ ስም መሐል የምጽፋትን ‹ዘ› የወሰድኩት ከሷ ስም ነው)፡፡

ከዚያም አገሯን ጥላ ኮበለለች፡፡ የኮበለለችው ደግሞ ምንም፣ ማንንም ወደማታውቅባት፣ ማንም ወደማያውቃት አዲስ አበባ ነው፡፡ ዝርዝሩ የማያልቅ ፈተና ያለበት ውጣ ውረድ ነው፡፡ የሆነ፣ ሆኖ ነፍሷን አትርፋ ራሷን አዲስ አበባ ላይ ማደላደል ቻለች፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ነበር ከአባቴ ጋር የተገናኙት፣ የተዋደዱት፣ የተጋቡት እና ልጆች ያፈሩት፡፡ ወላጆቿ በወቅቱ አዝነውባት ይሆናል፤ ነገር ግን ተጨንቀው እሷን ፍለጋ ብዙ ሲንከራተቱ እና ሲንገላቱ እንደነበርም በታሪክ ስትናገር አውቃለሁ፡፡ ሲያገኟትም ከአባቴ ትዳር ይዛ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ነበር፡፡ ከመደሰት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ለእናቴም የእራሷን ሕይወት ለመምራት፣ እነርሱን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሚያስከፋ እና የሚያስጨንቅ ውሳኔ መወሰን ነበረባት፤ መጨረሻውም አስደሳች ሆኗል፡፡ መጨረሻው ምንም ሆነ ምን እናቴ የማትፈልገውን ሕይወት ‹‹እምቢ አልኖረውም›› ብላ መጀመሯ ተገቢ ነበር፡፡

እኔም የወላጆቼ ልጅ ነኝ፤ ታሪካቸውን በተለያየ ቀለም በተደጋጋሚ እየሰማሁ ነው ያደግኩት፡፡ የተሠራሁትም ከነርሱ ታሪክ እና ከሌሎችም ብዙ የሕይወት ልምዶች ነው፡፡ የናቴን እምቢተኝነት፣ የማይፈልጉትን ላለመሆን አደጋ መጋፈጥ፣ ይመጥነኛል የሚሉትን ሕይወት እስከሚገኝበት አጥናፍ ድረስ መፈለግ ተፈልፍዬ የተቀረፅኩበት ‹ሳይኮአናሊቲካዊ› ሥረ-መሠረቴ ነው፡፡ እናቴ፣ ወላጆቿን ታከብራለች፣ ትወዳለች፤ ሕይወቷን ግን ስለነርሱ አልኖረችም፡፡ እኔም በሕይወቴ የምወስዳቸውን እርምጃዎች የምረዳቸው በዚሁ ቋንቋ ነው፡፡ እናቴን እወዳታለሁ፤ ነገር ግን ‹የሱን ሕይወት ትቶ የኔን ድርሻ ይኑርልኝ› ትለኛለች ብዬ አልገምትም፡፡ ማረሚያ ቤት እያመላለስኩ ባስቸገርኳት ግዜም ይሁን ሰዎች በወቀሱኝ ጊዜ ለራሴ የምሰጠው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እኔ የናቴ ልጅ ነኝ፤ እራሴን የምሆነውም ከርሷ በወረስኩት ባሕሪዬ ነው፡፡

(ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት እናቴን አስፈቅጄ ነው፡፡)

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: