The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ከሶርያ ምስቅልቅል ኢትዮጵያውያን ምን እንማራለን? – በአክሊሉ ወንድአፈረው

መግቢያ

በኢትዮጵያ ውስጥ በአገዛዙና በህዝብ መካከል የሚታየው ግብግብ እጅግ እየተካረረና ብዙ ህይወትም እያሰገበረ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ እነሆ ብዙ ሰዎች የሀገራችንና የሕዝቧ መጻዒ እድል ምን ይሆናል በማለት ያስባሉ፤ይጨነቃሉም።

መጭው ጊዜ ምን ሊሆን እንደሚችል ሙሉ በሙሉ በርግጠኛነት መናገር ባይቻልም፣ የሌሎች ሀገሮችን ልምድ መገምገምና ከሀገራችን ሁኔታ ጋር በማመዛዘን ከነዚህ ልምዶች ምን እንማራለን ብሎ መጠየቅ  በጣም ጠቃሚ ነው።  ከዚህም አንጻር፣ የዚህ አጭር ጽሁፍ አላማ የሶርያን የቅርብ ጊዜ ልምድ በመመርመር ይህ ልምድ ሀገራችን  ለገጠማት ፈታኝ  ሁኔታ  የሚቸረው ትምህርት ምንድነው?  ሀገራችን ከቀጣይ ጥፋት ለመዳንስ ምን መደረግ አለበት? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ የውይይት ሀሳቦችን ለማቅረብ ነው።

የአረብ ጸደይ አብዮትና በሽር አልአሳድ

በአውሮፓ አቆጣጠር  በዲሰምበር 2010 የተቀሰቀሰውና የአረብ ጸደይ ( Arab Spring ) እየተባለ የሚጠራው የመካከለኛው ምስራቅ  ህዝቦች አምባገነኖችን አይናችሁን አንይ ብለው በቁጣ  ያርበደበዱበትና ያፍረከረኩበት አርድ አንቀጥቅጥ የሆነው የህዝቦች አመጽ ሶሪያ ውስጥ የተከሰተው ትንሽ ዘግየት ብሎ ነበር።

የአረብ ጸደዩ እንቅስቃሴ በብዙ ሀገሮች በዋናነት “መንግስት ሰልጣኑን ይልቀቅ” ( Ash-sha`b yurid isqat an-nizam) በሚል መሪ መፈክር ስር ሲካሄድ፣ ሶርያ ወጣት፣ የተማረና ምናልባትም የተሻለ ስርአት ተግባራዊ ያደርጋሉ  ተብለው በተጠበቁት፡ መሪ ፣ በበሽር አልአሳድ ስር ይተዳደሩ ነበር። ለ40 አመት በፈላጭ ቆራጩነት ይገዙ የነበሩትን ሀፊዝ አልአሳድን በሞት ገላግሏቸው የተደሰቱት ሶርያውያን ከእርሳቸው  የባሰ አይመጣም ብለው በመገመት በአዲሱ ፕሬዝዳንት ላይ ተስፋ የጣሉ እጅግ ብዙዎች ነበሩ።

ምንም እንኳ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በአምናገነኑ አባታቸው ውሳኔ ስልጣን ላይ ቢወጡም አዲሱ መሪ በሸር አልአሳድ ሰላማዊ ለውጥ ያስከትላሉ የሚል ታላቅ ተስፋ ቢያንስ ከላይ ከላይ ሲናፈስ ይስተዋል ነበር። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን ሶሪያ በአጭር ጊዘ ውስጥ እጅግ የተካረር ባለብዙ ገጽታ የፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ገባች። እጅግ ለማመን በሚከብድ ሁኔታም በዓለም ዋናዋ የስደተኛ መፍለቂያ ሀገር ሆነች። ከተሞቿ፣ የታሪካ ቦታዎቿ፣ ቅርሶቿ መጋየት ጀመሩ። የሟች ሶርያውያንን ቁጥር ማወቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ። ሁሉም ታላላቅ ከተሞች፣ ዋና ከተማዋ ደማስቆን ጨምሮ በሁለትና ሶስት ተፋላሚ ድርጅቶች ስር መውደቅ ጀመሩ። በሶርያ የውስጥ ጉዳይም ዋናዎቹ ተደራዳሪወችና ተናጋሪዎች ሶረያውያን ሳይሆኑ እጅግ ብዙ የባእድ መንግስታትና የውጭ ድርጅቶች ሆኑ::

ለውጥ ያመጣሉ የተባሉት ወጣቱ መሪ፣ የሚመሩትም መንግስት ይሁን እርሳቸው ከተኳቸውና በጭካኔያቸው ከታወቁት አባታቸው ብሰው ተገኙ፤ ስርአቱን የሚቀናቀን ማንኛውንም ሰው ያለርህራሄ መጨፍለቅ የእለት ተእለት ተግባር ሆነ።  ፎሬይን አፊርስ (Foreign affairs) የተሰኘው መጽሄት አንድ ዘጋቢ በቅርቡ፡እንደጻፈው የበሽር አልአሳድ አገዛዝ፣ ጭካኔው፤ ንቅዘቱ፣ ወገንተኛነቱ፣ የማፊያ አይነት የአሰራር ስልቱ… ወዘተ ሲታይ በሽርና መንግስታቸው ከአረመኔያዊው አባታቸው፣  በብዙ እጥፍ እንደሚብሱ አሳይተዋል ነበር ያለው።

ታዲያ ሶርያ ለምን ወደዚህ አይነት የጥፋት ጉዞ ገባች? አዲሱ መሪና መንግስትስ እንዴት ከተጠበቁት በተጻራሪው ሆነው ተገኙ?

ጡንቻንና የከፋፍለህ ግዛን ተንኮል ዋና መመሪያው ያደረገ ስርአት ያሰከተለው እዳ

በአውሮፓ አቆጣጠር በኖቨምበር 1970 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ለስልጣን የበቁትና ለአርባ አመታት ያክል በስልጣን ላይ የቆዩት ሀፊዝ አላአሳድ እና የሚመሩት ሶሻሊስት ቀመሱ የአረብ ብሄረተኛ ፓርቲ በሀገር ውስጥ ይከተሉት የነበረው ፖሊሲ የህዝባቸውን ይሁንታ በማግኘትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ወዳጅ፤ ሌላውን ደግሞ እንደጠላት በመፈረጅ፤ የተወሰነውን ክፍል በማቅረብ ሌላውን ደግሞ የማራቅና የማጥቃት ፖሊሲን መሰረት ያደረገ ነበር። በዚህም መሰረት በተለይም የሱኒ እምነት ተከታዮችን፤ 10% የሚሆኑትን ክርስቲያኖችና፣ 3% የሚሆኑትን ድሩዞች (Druze) እንዲሁም የራሳቸው የሀፊዝ አልአሳድ ወገንና ተወላጆች የሆኑትን 10% የሚሆኑትን አላዋዮችን (Alawi)  የቅርብ ወዳጅ በማለት ያቀርቧችው ነበር::

በአንጻሩ 15% የሚሆኑትን የሶርያ ኩርዶችን፤ ቀደም ሲል በስልጣን ላይ የነበሩትን የሱኒ እምነት ተከታይ የነበሩትን ባለስልጣኖችና ወገኖቻቸውን፤ “ጨቋኝ” ብለው የመደቧቸውን የመሬት ባለሀብቶችና ነጋዴወችን፤ እንዲሁም ስርአቱ የሚመራበትን የአረብ ሶሻሊስት ራእይና ፖሊሲን የተቃወሙትን ሁሉ ከፖለቲካውም ሆነ ከኢኮኖሚው ምህዳር እንዲገለሉ አድርገዋል::  ህብረተሰቡንም ከላይ በተመለከተው ሁኔታ እርስ በርስ የወዳጅና የጠላትነት ስሜት እንዲኖረው እየቀሰቀሱ ነበር የገዙት። ሀፊዝ አልአሳድ በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን የኢኮኖሚና የተለያዩ ማህበራዊ ብሶቶችን በማራገብ፣ ህዝቡን ከሚያመሳስሉ እሴቶች ይልቅ በሚያለያዩት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ነበር ክፍፍሉ ስር እንዲሰድና አንዱ በሌላው ላይ የመረረ ቂም እንዲይዝ ያደረጉት። ሌሎቹ የህብረተሰብ ክፍል አባላት እርስ በርስ ሲናቆሩ፣ ከ1970ወቹ ጀምሮ በተለይም በሀገሪቱ ፖለቲካና፣ ወታደራዊ ስልጣን የበላይነትን አጠናክረው የተጓዙት 10% ከሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡት አላዋዮችን (Alawi) ናቸው። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን በእቅድ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የተደረገ ጉዳይ ነው።

በሀፊዝ አልአሳድ የሚመራው ባአዝ ፓርቲና  (Arab Socialist Ba’ath Party)  መንግስቱ ፖለቲካውን ለብቻው ሙጥኝ ብለው መቆየት ብቻ ሳይሆን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጥፍጨፋም በሶርያውያን ላይ በተደጋጋሚ አካሂደዋል። ከነዚህም ውስጥ በአውሮፓ አቆጣጠር  ከ1977 ጀምሮ እያደገ የመጣውን ተቃውሞ ለማፈን የተደገረገው ጭፍጨፋ፣ በጁን 1979 የተደረገውን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተከትሎ 50 የሚሆኑ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተካሄደው ግድያ፤ በ1980  ፕሬዚደንት አሳድን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ የ250 ሰወች መረሽን፣ በፌበርዋሪ 1982 የተነሳውን አመጽ ተከትሎ በሃማ ከተማ ከ10 እስከ 25 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የተካሄደው ጭፍጨፋ፤ እንዲሁም ከ1982 እስከ 1992 በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ እስር መወርወራቸው እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሌሎች መገደላቸው የስርአቱን ግፍ በከፊሉ ያሳያል።http://foreignpolicy.com/2011/08/05/massacre-city-2/

 

አዲሱ ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2000 አመተ ምህረት ስልጣኑን ከአባታቸው ከሀፊዝ አልአሳድ ሲወርሱ አብረው የወረሱት ደግሞ ሰጥ ለጥ ያለ የሚመስል ሁኖም ግን ውስጥ ውስጡን በምሬት የተቃጠለና እርስ በርስም እጅግ የተቃቃረ ህብረተሰብን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በሽር አዲስ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ የወረሱትና ከሞላ ጎደል እንዳለ ያስቀጠሉት ግን 40 አመት ሙሉ በጭቆና ህዝብን ያስተዳድር የነበረውን ፖለቲካ ፓርቲ ከነባለስልጣናቱ ነበር። ባጭሩ የተካሄደው ለውጥ በፕሬዚዳንቱ ወንበር ላይ እንጂ በገዥው ፓርቲና በስርአት ደረጃ አልነበረም። አዲሱ መሪ ያስቀጠሉትም የተለየ ራእይና አካሄድ ሳይሆን የአባታቸውን ሌጋሲ ነበር።

 

በደል ገደብ እንዳለውና የህዝብን በቃኝ ማለት ለመረዳት ያልቻለ ስርአት ውጤት

በሽር አልአሳድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ አንዳንድ ለውጦችን (ኢኮኖሚውን ዘመናዊ ለማድረግ፣ንቅዘትን ለመዋጋት፣ የራሷ የሶርያ ይዘት ያለው ዴሞክራሲን ማስፈን ብለው የሰየሙትን የዴሞክራሲ ሂደት ተግባራዊ ማድረግ ) ቢሞክሩም የተባለው ለውጥ የጠቀመው ግን ብዙውን ህዝብ ሳይሆን በሩቅም ሆነ በቅርብ የሚገኙትን የፖለቲካ ሽርኮቻቸውን ነበር። በአሳድ የመጀመሪያ ጥቂት የስልጣን አመታት ብቻ የፖለቲካ ታማኞቻችውና ሽርኮቻቸው ድንገት ከፍተኛ ቱጃሮች ሆኑ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ንቅዘት (ኮራፕሽን) ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፣ የኢኮኖሚ ችግሩ ተባበሰ፣ ሰራ አጥነቱ ተስፋፋ፣ በአውሮፓ አቆጣጠር በ2007 የተከሰተው ድርቅም እጅግ ብዙ ገበሬዎችን ወደከፍተኛ ምሬት ገፋፋቸው።

ያም ሆኖ ግን በማርች 2011 ዴራ (Deraa) በተሰኘችው በሀገሪቱ ደቡባዊ ከተማ ሕዝብ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርግ፤ የጠየቀው የፕሬዚደንት በሽርን ከስልጣን መውረድ ሳይሆን በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም ዘርፍ መለስተኛ ለውጥን እንዲያደርጉ ነበር። ሶርያን ለ40 አመት በፍጹም አምባገነንና ከፋፋይ ፖለቲካ ፍልስፍና የገዙት አባታቸው ሀፊዝ አልአሳድ ሲሞቱ እርሳቸውን የተኩት ልጃቸው በሽር አልአሳድ (Bashar al-Assad) ወጣት በመሆናቸው፤ በምእራቡ አለም (እንግሊዝ ውስጥ) የተማሩ ስለሆኑና ወታደር ስላልነበሩ፡ በጨፍጫፊነትም ሆነ በአድሎአዊነት ከአባታቸው የተሻለ ሰብአዊነትና ርህራሄ ያላቸው ይሆናሉ፤ የተሻለ አስተዳደርንም ያመጣሉ በሚል እምነት ህዝብ የተቀበላቸው በአክብሮት በጉጉትና በተስፋ  ነበር።

ሆኖም ግን በአውሮፓ አቆጣጠር  በማርች 2011 ዴራ (Deraa ) ላይ የተቀሰቀሰውን ሰላማዊ የህዝብ ተቃውሞ በሀይል ሰጥ ለጥ ለማድረግ የወሰዱትን እርምጃና በተከታታይም ለተነሳው የህዘብ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ከ9000 (ዘጠኝ ሺህ) ያላነሱ ዜጎችን መጨፍጨፍ ነበር። ይህን ያልተጠበቀ ዱብእዳ ተከትሎም የሶርያ ሕዝብ “በቃኝ” አለ። ወዳልፈለገውና ወዳላሰበው የመሳሪያ ግብግብም ፈጥኖ እንዲገባ  ሁኔታው አስገደደው።

በሽር አል አሳድ በዙሪያቸው ያሰባሰቧቸው የገዠው ቡድን አባላትም ከሞላ ጎደል ጠንከር ያለ አንድነት የነበራቸው ቢሆንም  በ 2011 ዴራ ላይ የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ በሀይል ለማንበርከክ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ተቃውሞውን ለማስቆም ምን መደረግ አለበት በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ቁልፍ የስርአቱ ሰዎች በውስጣቸው መከፋፈል መታየት ጀምሮ ነበር።

በበሽር አልአሳድ ታናሽ ወንድምና የ4ኛው ክፍለ ጦር ሜካናይዝድ ሀይል አዛዥ በማሂር አልአሳድ (Mahir) የሚመሩት አክራሪዎች “በውይይት ሰላም እናምጣ” ይሉ የነበሩትን የስርአቱ ባለስልጣኖች ድምጽ ረግጠው የአፈናው ዋና ተዋናይ ሆኑ። እነዚህ ክፍሎች የቀድሞው ፕሬዚደነት ሀፊዝ አልአሳድ በሰባዎቹና በሰማናያዎቹ የህዝብን አመጽ በጉልበት ሰጥ ለጥ ወዳደረጉበት የተጠላ አሰራር ስልት ተመለሱ። http://www.thenational.ae/world/middle-east/20130915/al-assads-merciless-brother-maher-key-to-regime-survival

ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የተጠበቁት በሽር አልአሳድም፣ የህዝቡን ሰላማዊ ተቃውሞ “የውጭ ቅጥረኞች እጅ ያለበት ነው፤ ወንጀለኞች ያነሳሱት ሁከት ነው፤ የእርስ በርስ ግጭትን ለማምጣት ሲባል የተጀመረ የፕሬዚደንቱ ወገን በሆኑት አላዋይቶች ላይ ያነጣጠረ (anti Alawi) መነሳሳት ነው፤ ያክራሪዎች ሴራ ነው…ወዘተ የሚል ያልሆነ ስም በመስጠት የህዝቡን ጥያቄ  ጭቃ መቀባቱን ተያያዙት።  መንግስታቸውና ፓርቲያቸው በሀገሪቱ የዜና ማሰራጫወች፤ በተደጋጋሚ ሲያሟርቱ እንደነበረው ሁሉ በመጨረሻ፣ ያ ሟርት ተግባራዊ ሆነ። እነሆ ሶርያም የጥላቻ ፖለቲካ፣ የውጭ ጣልቃገብነት፤ የሀይማኖት ግጭትና አክራሪነትም ተደበላልቀው ለስድስት ተከታታይ አመታት መንግስትም መግዛት አቅቶት፤ ተቃዋሚወችም ስርአቱን ማንበርከክ ተስኗቸው መላው አለም እጅግ ዘግናኝ እውነታን በየእለቱ እየተመለከተ ይገኛል።

የተቃዋሚው አለመተባበር ያሰከተለው አደጋ

የሶሪያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ በሀፊዝ አልአሳድ 40 የግፍ አገዛዝ አመታት ውስጥ ዋና ኢላማ ሆነው መሪወቻቸው ታስረዋል፣ ተገድለዋል፤ ተሰደዋል። ከስር ከስር በመከታተልም ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት የአሳድ የጸጥታ ሀይሎች እጅግ ሰፊ ስራ ሰርተዋል። ይህም በመሆኑ፤ ገና ከጅምሩ የተቃዋሚዎች አቅም እጅግ የተዳከመ ነበር። የሶሪያ ህዝብ ተቃውሞ የተቀሰቀሰውና አያደገ የመጣውም በተቀነባበር የፖለቲካ ድርጅት አመራር ሳይሆን ከህዝብ ብሶት በገነፈለ መስረታዊ ንቅናቄ ነበር።

ያም ሆኖ ግን የተፈጠረውን የህዝብ መነሳሳት በመጠቀም በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚወች የህዝብ መነሳሳቱ በታየበት የመጀመሪያ ወቅት የአካባቢ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን (Local Coordination Committees (LC) በህቡእ በመመስረትና ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ውጤታማ ስራ ሰርተው ነበር። እነዚህ አስተባባሪ ኮሚቴዎች የሚመሩት በሚስጥር በሚንቀሳቀሱ መዋቅሮች ስለነበር፤ መንግስት የትግሉን መሪወች ለይቶ ለማሰርና ትግሉንም ለማኮላሽት እጅግ አስቸግሮት ቆይቷል። ይሀም በመሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ በነበረበት ሁኔታ እንኳን፤ የተቃውሞ ሰልፎቹን ከአመት በላይ በቀጣይነት ማስኬድ ተችሎ ነበር።

ሆኖም ትግሉ እየተራዘመና እየተወሳሰበ ሲሄድ፤ በዋናነት የአለም አቀፉን ህብረተሰብ ድጋፍ ለማግኝት በተደረገው ሩጫ፤ በስደት ላይ የሚገኙ ተቃዋሚወች በቱርክ ውስጥ በአውሮፓ አቆጣጠር በኦገስት 2011 በተካሄደ ስብሰባ የሶሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት (Syrian National Council) የተሰኘውን የተቃዋሚወች ህብረት መሰረቱ። ይህ ህብረት ሰባት የተለያየ አመለካከት ያላቸው ድርጅቶችን ያሰባሰበ ነበር። ሆኖም ግን ይህ በውጭ የተመሰረተው ስብስብ ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የተመሰረቱትን የአካባቢ አስተባባሪ ኮሚቴወችን (Local Coordination Committees (LC) አይነት የማደራጀትም ሆነ ህዝብን የማነቃነቅ ውጤታማ ስራ ሊሰራ አልቻለም። በሶርያ ውስጥ በምድር ላይ ከነበሩት የተለያዩ ክፍሎችም ድጋፍ ማግኘት አቃተው፡ ለምሳሌም የኩርዶች ብሄራዊ ምክር ቤት፡ የተሰኘው ተቃዋሚ ክፍል (Kurdish National Council (KNC) የአዲሱ ህብረት አባል አልሆነም:: ቀስ በቀስም የሶሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት በምድር ላይ ከሚታየው ትግል ጋር ግንኙነት የሌለው ነው በማለት ብዙወች ድጋፋቸውን ነፈጉት።

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ ይህ ህብረት የተመሰረተውና ዋና ጽህፈት ቤቱም በቱርክ ውሰጥ በመሆኑ ቱርክ ደግሞ የሶሪያዊ ኩርዶችን እንቅስቃሴ በጥሩ አይን ስለማታይ፣ የሶሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት (Syrian National Council) በተቃዋሚወች ዘንድ የቱርክን አጀንዳ አስፈጻሚ ነው ከሚል በመነሳት በጥርጣሬ አይን የሚታይ አካል ሆነ። ይህ በመሆኑም በተቃዋሚዎች መቀራረብና በአገዛዙ ላይ የተቀነባበረ ተጽእኖ የማሳደር ሂደት ላይ ታላቅ እንቅፋት ፈጥሯል።

ሰለ ሶሪያ ተቃዋሚዎች ሲነገር ሌላው ጎልቶ የሚታየው ሀይል በጁላይ 2011 አገዛዙን ከድተው ወደ ቱርክ በገቡ ወታደሮችና የጦር መኮንኖች የተመሰረተውና ራሱን “የሶሪያ ነጻ ጦር” (free Syria Army FSA) በማለት የሚጠራው ድርጅት ነው:: ይህ በኮሎኔል ሪአድ አል አሳድ (Colonel Riad al-Asaad,) የሚመራው ደርጅት የሚያምነው ስርአቱን በወታደራዊ ፍልሚያ በማስወገድ ነው። ምንም እንኳን ይህ ድርጅት ከሳውዲ አረብያና ከኳታር ከፍተኛ ድጋፍ ቢደረግለትም በምእራቡ መንግስታት በኩል ግን “አልካይዳ ሰርጎ ሳይገባበት አልቀረም” በሚል ጥርጣሬ የተነሳ ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ እገዛን ሊያገኝ አልቻለም። ይህም በመሆኑ በዚህ ድርጅት እድገትና ወታደራዊ ብቃት ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ የተቃዋሚዎች እርስበርስ መደጋገፍ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን አሳድሯል። በመሆኑም በስርአቱ ላይ ወሳኝ ድልን ለማግኝት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ተቃዋሚው በመሰረታዊ መግባቢያ ነጥቦች ላይ ተስማምቶ በአንድ ልብ በአንድ አቋም አለመነሳቱ ሰፊ የተባበረ የህዝብ ድጋፍን አነሳስቶ የበሽር አልአሳድን መንግስት ለማስገደድም ሆነ ለመጣል አልቻለም። ለውጥ ፈላጊው በአንድ ላይ ቆሞ የተቀነባባረ ትግል ለማድረግ ባለመቻሉ ተራ በተራ ለጥቃት ተጋልጧል ። የአሳድ መንግስትም እያንዳንዱን ተቃዋሚ በተናጠል ሲያጠቃ ቆይቶ አሁን ደግሞ በሁሉም ላይ ታላቅ የጭፍጨፋ ዘመቻውን እያፋጠነ ነው። አሁን እንደሚታየውም አገዛዙ በባእዳን ታላቅ እርዳታ ወታደራዊ የበላይነትን ይዞ እርሱ ከሚፈልጋቸው ተቃዋሚዎች ጋር ብቻ ካልሆነ ለመደራደርም ፍላጎት እንደሌለው እያሳየ ነው::

የራእይ ዝብርቅርቅነትና ልዩነትን ለማቀራረብ አለመቻል ያሰከተለው አደጋ

በሶርያ ግጭት ውስጥ እጅግ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ከ40 በላይ ተፋላሚወች ይገኛሉ። እነዚህ ተፋላሚወች የሚያመሳስላቸው ጸረ በሽር አቌማቸው አንጂ በአብዛኛው አይን ለአይን የሚተያዩ አይደሉም:: ስለ ሀገራቸውና ህዝባችው የወደፊት እድልም ያላችው ራእይ እጅግ የተዘበራረቀና በተለያየ ጠርዝ ላይ የቆመ ነው::

የሶርያ ትግል በውስጡ የሞስሊም ወንድማማቾች እንቅስቃሴ ( Muslim Brotherhood)፤ ከሶርያ መገንጠልንና እጅግ የላላ ፌደራላዊ የራስ አገዛዝ ስርአትን በሚያቀነቅኑ የኩርድ ብሄረተኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴ (the Kurdish Bloc)፤ ስርአቱን በድርድርና በሰላም ለመቀየር የሚጥሩ ሀገር በቀል ድርጅቶችን ያቀፈው ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ (National Coordination Committee (NCC) ስር የሚንቀሳቀሱ  ድርጅቶች፡ በሀገር ቤት በህዝብ ውስጥ የሚነቃነቊና ስርአቱን ለመቀየር የሚቻለው በድርድርና በሰላም ሳይሆን በአመጽ ነው ብለው የሚያምኑ አብዮታዊ ሽንጎ (The Syrian Revolution General Commission (SRGC)) በመባል የሚታወቁ አካሎች፡ የአልካይዳ አካል ናችው የሚባሉት የአል ኑስራና አህራር አል ሽም (Ahrar al-Sham) እንቅስቃሴዎች፣ በስደት ላይ የሚገኙ ተቃዋሚዎችን ያቀፈው የሶሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት (Syrian National Council) እንቅስቃሴ፡ በወታደሮችና የጦር መኮንኖች የተመሰረተው “የሶሪያ ነጻ ጦር” (free Syria Army FSA) እንቅስቃሴ፡ እና ሌሎችም ይገኛሉ::http://www.understandingwar.org/report/syrias-political-opposition

ችግሩ የድርጅቶቹ መብዛት ብቻ ሳይሆን ከአመለካከታቸው መዘበራረቅና መራራቅ የተነሳ የጋራ ራእይ ሊቀርጹና ለህዝቡም ነገ ከዛሬ እንደሚሻል ተስፋ መሰጠት አለመቻላችውም ጭምር ነው:: ይህ ደግሞ ተቃዋሚው እርስ በርስ እንዳይተማመንና በጋራ እንዳይቆም፤ ህዝቡንም ለተቃዋሚው ድጋፉን ሙሉ በሙሉ ከመስጠት ወደ ኋላ እንዲል አድርጎታል:፡

በሴፕተምበር 2016 በኢንግሊዝ መንግስት አቀናባሪነት በተካሄደ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 30 የሚሆኑ ለዘብተኛ (ሞደሬት) የተባሉ ድርጅቶች ተሰባሰብው በድህረ በሽር ስርአት ሶሪያ በዴሞክርሲና የሀይማኖት ብዙሀናዊነትን የሚያክብር ስርአትን መመስረት እንደሚኖርባት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይሀ እንግዲህ የህዝብ ተቃውሞ ከተነሳ ከ6 አመታት በኋላ መሆኑ ነው። እነዚህ 30 ያክል ድርጅቶች አሁን የመሰባሰብ አዝማሚያ ያሳዩ ቢሆንም አሁንም ሀይማኖታዊ ስርአትን ለማምጣትና ከሌሎች ተለይቶ የኩርዶችን ነጻ መንግስት እውን ለማድረግ የሚታገሉ ክፍሎች እንቅስቃሴ በትግሉ ሜዳ የማይናቅ ቦታ ይዘው መገኘታችው  በድርጅቶች መሀል አለመተማመኑን እንዲቀጥል አድርጎታል::https://www.theguardian.com/world/2016/sep/07/syrian-opposition-coalition-to-announce-democratic-transition-plan

የጽንፈኞች መጠናከርና አለም አቀፍ እንደምታው

የመንግስት መዳክምና የህዝቡም ብሶት እጅግ እየሰፋ መምጣት ጋር ተያይዞ በሶርያ ውስጥ ሁሉም ቦታ ግጭት፤ ሁሉም ቦታ ጦርነት በመሆኑ የተፈጠረው ክፍተት ለተለያዩ ጽንፈኛ አካሎችም ስር መስደድ መንገድ ከፍቷል:: በዚህ አንጻር በዋናነት የሚጠቀስው  የእስላማዊ መንግስት (the Islamic State of Iraq and al-Sham (Isis) እየተባለ የሚጠራው ድርጅት በሶርያ ውስጥ ሰፊ ቦታ ተቆጣጥሮ መቆየቱና  እየተጠናከረም መምጣቱ ነው:: ይህ ደግሞ በተለይ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ አሳሳቢ ሆኗል:: http://www.npr.org/sections/thetwo-way/2015/12/20/460463173/60-percent-of-syrian-rebels-share-islamic-state-ideology-think-tank-finds

በመሆኑም የበሽር አል አሳድን መንግስት ለመደገፍ በተነሱት እንደ ራሽያና ኢራን ያሉ መንግስታት ላይ ጣልቃ ገብነታቸው ሊያስክትልባቸው ይችል የነበረውን አለም አቀፍ ውግዘት እጅግ ቀንሶላቸዋል:: የምእራቡም መንግስታት  በነዚህ ሀገሮች ጣልቃ ገብነት ላይ የሚያሳዩት ተቃውሞ ከቃላት የማያልፍ ሆኗል:: አሁን በተደረሰበት ደረጃ፤ ራሽያና ኢራንም ሆኑ ምእራባውያኑ፤ በሶርያ ውስጥ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ያሰፈልጋል የሚለውን የህዝብ አጀንዳ ጭራሽ ወደ ጎን ትተው አይን ባወጣ ሁኔታ ነገሩ ሁሉ አገዛዙን አጠናክሮ ማስቀጠልና “ጽንፈኛ ሀይሎች” ሶርያን መሰረት አድርገው በሌሎች ሀገሮች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥቃት በመቀነሰ እስትራተጂ ላይ ያተኮረ እየሰሩ እንደሆነ ግልጽ ሆኖ ይታያል:: http://www.bbc.com/news/world-middle-east-35144420 ይህ ደግሞ አገዛዙና ባእዳን አጋዦቹ ጽንፈኛነትን በመዋጋት ሰበብ በሁሉም ተቃዋሚወች ላይ ድብደባን በመፈጸም መላው ሶሪያ እንድትቃጠልና ድምጥማጧ እንዲጠፋ፤ ተቃዋሚዎችም እንዲዳከሙና፤ ከትግሉ ሜዳ እንዲወገዱ፤ በአጠቃላይ ሀገሪቱ በማያቋርጥ የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትቀጥል መደላድሉን እያመቻቸ ነው::

የሰላማዊ ትግል ትኩረት ማጣትና መዳከም ያሰከተለው ችግር

የሱሪያ ህዘብ ትግል ሲጀመር እጅግ ሰላማዊና ህዝብንም አሳታፊ ነበር። አገዛዙ ይህን የህዝብን በስፋት ያሳተፈ ሰላማዊ ተቃውሞ ለማፈን የሚወስደው እርምጃ ሁሉ፤ ከሁሉም አቅጣጫ የተወገዘ ነበር። አገዛዙ ጭፍጨፋውን እጠናከሮ ሲቀጥልም፤ በዚያው መጠን ለህዝቡ ሰላማዊ ትግል አለም አቀፉ ድጋፍ እየጨመረ ነበር የመጣወ።  ባዶ እጁን በሰላማዊ መንገድ መብቱን የሚጠይቅን ህዝብ፤ አገዛዙ ለምን በጉልበት ማፈን እንደመረጠ፣ ምንም አሳማኝ ምክንያት ሊያቀርብ አልቻለም ነበር። በመሆኑም አገዛዙን እጅግ ይቀርቡታል ከሚባሉት እንደነ ሩስያ ከመሳሰሉት መንግስታት ሳይቀር፤ ግልጽ ድጋፍን ሊያገኝ አልቻለም ነበር። እንዲያውም ከወዳጆቹ ሳይቀር የሚደርስበት ተጽእኖ ሁኔታውን በውይይትና በድርድር እንዲፈታ ነበር ።

በተጨማሪም ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት እንደ አልካይዳ የመሳሰሉት ከሌሎች ሀገሮች የሚመጣ ተዋጊ ሀይልን አቅፈው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ሚና ጎልቶ የሚታይ አልነበረም። ስለሆነም አለም አቀፉ ህብረተሰቡም የሕዝቡን ንቅናቄ በጥርጣሬና በፍራቻ አይን አይመለከተውም ነበር።

የስርአቱ አፈናና ጭፍጨፋ እየተጠናከረ ሲሄድ ሰላማዊ ትግሉ ውጤት ሊያሰገኝ አልቻለም ስለሆነም ጭፍጨፋውን ለማስቆምና የስርአት ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ በመሳሪያ ሀይል የሚጨፈጭፍን ስርአት በመሳሪያ መታገል ነው የሚገባው በማለት የተለያዩ ክፍሎች መሳሪያ አንስተው በዋናነት አገዛዙን አልፎ አልፎም እርስ በርስ መፋለም ጀመሩ። ይህ ሁኔታ እየጠነከረ ሲመጣም ምንም እንኳ የተቃዋሚው ወገን መሳሪያ ያነሳነው ተገድደን ነው ቢልም፣ የሞራል የበላይነቱ ግን ቀስ በቀስ በጥያቄ ውስጥ ገባ። እያደርም በአንዳንድ የታጠቁ ተቀቃሚ ድርጅቶቸ የሚወሰደው እርምጃ ከአሳድ መንግስት ሰራዊት ተግባር የማይተናነስ እየሆነ በመምጣቱ ስለተቃዋሚው በሀገርም  ሆነ በአለም አቀፉ ህብረተሰቡ ውስጥ የነበረው አመለካከት እየተቀየረ መጣ።

የሚካሄደው እንቅስቃሴ ሰላማዊ ትግልን በዋናነት ያላካተተ በመሆኑ እያንዳንዱ የአልበሽርም ይሁን የተቃዋሚው እንቅስቃሴ ከእለት ወደእለት ህዝብን ወደስደት እንዲያመራ፤ ከተሞች እንዲፈራርሱ፣ ታሪካዊ ቅርስ እንዲወድም…ወዘተ እያደረገ መጣ። ይህ ታዲያ የሀገሪቱን ችግር እጅግ አወሳሰቦታል። ህዝቡም የእንቅስቃሴውን ውጤት በጉጉት ከመጠበቅ ይልቅ፤ በየእለቱ በሚደርስበት ውድመትና መፈናቀል ተወጥሮ እንዲጨነቅ፤ ከሚታየው ምስቅልቅልም የተሻለ ነገር ይወለዳል ብሎ ለማሰብ እጅግ እየከበደው እንዲሄድ  አድርጎታል።

ሰላማዊ ትግሉን ትቶ ወደ መሳሪያ ትንቅንቅ ለመሸጋገር የተፈለገው በአጭር ጊዜ አገዛዙን ለማንበርከክ ነው እንዳልተባለ ሁሉ፣ አሁን የሚታየው ግን ከስድስት አመት የመሳሪያ ፍልሚያ በኋላ አገዛዙን የማስወገድም ሆነ የማስገደድ ተስፋ እጅግ እየጨለመ መጥቷል። እንዲያውም በሩሲያ፣ ኢራን፣ ቱርክና ህዝቦላህ (Hezbollah) ድጋፍ እነሆ አገዛዙ በተቃዋሚው ላይ አንጻራዊ የበላይነትን አግኝቶ በሽር አልአሳድና ግብራበሮቻቸው በሚፈልጉት ሁኔታ ከሚፈልጉት ጋር ብቻ  “ድርድር” ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። http://www.bbc.com/news/world-middle-east-38473702

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ፤ የአረብ ጸደይ አብዩት በተካሄደባቸው ሌሎች ሀገሮች የመሳሪያ ትግል ዋናውን ቦታ በያዘባቸው (ለምሳሌ ሊቢያና የመን) አስቸጋሪ ወደሆነ ምስቅልቅል እንዳሽቆለቆሉና በሰላማዊ ህዝበዊ እመቢተኛነት ላይ ያተኮሩት ደግሞ (ለምሳሌ ግብጽ፣ ቱኒስያ) ጨቋኙን ስርአት አስወግደው አንጻራዊ ሰላማዊ ሽግግርን እንዳስገኙ ግንዛቤ ውስጥ ማሰገባት ተገቢ ነው።

የብሄራዊ መግባባትና እርቅ  አጀንዳ ተግባራዊ የማድረግ ዳተኛነት ያሰከተለው አደጋ

በሶርያ ውስጥ የብሄራዊ መግባባትና እርቅ  አጀንዳ በበቂና ስርአት ባለው ሁኔታ ተገፍቷል ለማለት አይቻልም፡፡ በስድስቱ አመታት ግብግብ ውስጥ በአገዛዙም ሆነ በአብዛኛው ተቃዋሚው በኩል ብሄራዊ መግባባትንና ብሄራዊ እርቅን ሳይሆን የድርጅትን አጀንዳ ሌሎች በግድ እንዲቀበሉት ለማድረግ የተደረጉ ሙከራዎች እነሆ ያተረፉት አጥፊ ጦርነትን ማስቀጠልና በሚሊዮኞች የሚቆጠሩ ዜጎችንም መሞትና መሰደድ ነው። በአገዛዙም ሆነ በተቃዋሚዎችም በኩል ብሄራዊ እርቅን በተመለከተ የታየው እውነታ፤ በትክክል አስፈላጊነቱን ተቀብሎ ለዚህም ተግባራዊነት መታገል ሳይሆን፤ በተቃዋሚውም ሆነ በመንግስቱ በኩል ሀይላቸው ሲዳከም ብቻ የሚቀበሉት፤ ሀይላችው ሲጠናክር ደግሞ ወደጎን የሚገፉት ጉዳይ እንደሆነ ነው:: ይህ ደግሞ በአገዛዙም ሆነ በተፋላሚዎቹ መካከል ቀድሞውንም ደካማ የነበረውን የእርስ በእርስ መተማመን ይበልጥ እየሽረሽረው በመሄዱ፤ የብሄራዊ መግባባትና እርቅ አጀንዳ የትም ሊደርስ አልቻለም። እያንዳንዱ ወገን ትንሽ ጥንካሬን ሲያገኝ ሌላውን አበረታትቶ ወደ ሰላሙ ጠረጴዛ እንዲመጣ ሳይሆን ፣ ከነጭራሹ “እንዲወገድና እጁን እንዲሰጥ” ለማድረግ በመሞከራቸው ብሄራዊ መግባባና እርቅ የሚባለው ጉዳይ ከቃላት ያለፈ ዋጋ ሊኖረው እና ሊሳካ አልቻለም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በዚህ ላይ የባእድ መንግስታትም የየራሰቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም በሚያደርጉት የማማለል ተግባርና ጣልቃ ገብነት ከእርቅ ይልቅ ግጭትን ከመግባባት ይልቅ ይበልጥ መካረር ውስጥ መግባትን ነው ያበረታቱት።

የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመረምር

ሀገራችንን ላለፉት 25 አመታት እየመራ ያለው ህወሀት/ኢህአዴግና በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት አቶ ሐይለማርያም የወረሱት ስርአትስ ምን ይመስላል ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ከሶርያ ጋር እጅግ ሰፊ ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ነው። አንዱን የህብረተሰብ ክፍል የማቅረብ  ሌላውን የማራቅ  ፖሊሲ  ህወሀት/ኢህአዴግ የሚታውቀብት ዋናው መለያው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ህወሀት/ኢህአዴግ በመጀመሪያ ጥቂት የስልጣን  ዓመታቱ  የተለያየ  ስም በመለጠፍ የጥቃቱ ኢላማ ያደረገው አማራውን ሲሆን በመቀጠልም ሌሎት የህብረተሰብ ክፍሎችን ለምሳሌ የአሮሞን ማህበረሰብ፤ ሞስሊሞችን ወዘተ ነው:: እንደሶርያ ሁሉ በኢትዮጵያም ላለፉት 25 አመታት በፖለቲካ ምህዳሩና ወታደራዊ እዙ ውስጥ የበላይነት በመያዝ የሚቆጣጠረው ክፍል 7% የሚሆነውን የሀገሪቱን ማህበረሰብ መሰረት አድርጎ የተነሳው ህወሀት ነው።

እንደ ሶርያው ባአዝ ፓርቲ ሁሉ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚለው ፍልስፍና የሚመራው ህወሀት/ኢህአዴግ ስልጣንን ለብቻው አንቆ ለመኖር የሚቀናቀኑትን ሁሉ በሀይል እየደመሰሰ ነው 25 አመት የተጓዘው። በተቃዋሚዎች ላይ በሰሜን ሽዋ፣ በጎንደር አደባባይ እየሱስ ፣ በአዋሳ፣ በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች፣ በቴፒ፣ ሀረርጌ፣ በደሴ፣ በአምቦ፣ በአዲስአበባ፣ በባህርዳር፣ በኦጋዴን፣ በሲዳማ፣ በቦረና፣ በአርሲ፣ በከምባታ…ወዘተ ከፍተኛ ጭፍጨፋ አካሂዷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ህወሀት/ኢህአዴግን በብቸኛነት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለሰ ዜናዊ ሲሆኑ እርሳቸው ከሞቱ በኋላም በእርሳቸው የግል ውሳኔ ተመርጠው የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ ናቸው።

እንደ በሽር አልአሳድ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ በ 2012 ስልጣን ሲይዙ የወረሱትና ያስቀጠሉትም ያው ህወሀት/ኢህአዴግን ነው። እርሳቸው ደግመው ደጋግመው እንዳሉትም መመሪያቸውም ሆነ ፍላጎታቸው ፡”የመለሰን ሌጋሲ ማስቀጠል” ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ስልጣን ሲይዙ የተረጋጋ የመሰለ ሀገርና ሕዝብ ይውረሱ እንጂ፤ እውነታው ግን ህዝቡ በስርአቱ ላይ እጅግ ሰፊ ቅሬታ፣ ተቃውሞና ብስጭት ያለው የእርስ በርስ አለመተማመንም በሰፊው የሰፈነበት ህብረተሰብ ነበር።

ህወሀት/ኢህአዴግ የገጠመውን የህዝብ ተቃውሞ ልክ እንደ ሶርያው በሽር አልአሳድ ሽብርተኞች፣ የውጭ ጉዳይ አስፈጻሚወች፣ ወንጀለኞች ያሰነሱት ሁከት፡ የቀድሞ ስርአት ናፋቂወች፣ ትምክተኞች፣ ጠባቦች፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የተነጣጠረ…ወዘተ የሚል ቅጽል በመስጠት ትግሉን ለማጥቆር ጥሯል። ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም የሚመሩት መንግስት ስለህዝቡ ብሶትና ተቃውሞ የተሻለ አመለካከትና የቅራኔ አፈታት ከማሳየት ይልቅ ተቃውሞውን በሀይል ለመጨፍቅ ታላቅ ጥረት አድርጓል ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በቀደሙት  23 አመታት ውስጥ ከታየው በባሰ መልኩ ህዝብ ተጨፍጭፏል። ራሱ መንግስት  እንዳመነው እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ሲገደሉ ከ30ሺህ በላይ ታስረዋል።  ለመጀመሪያ ጊዜም መላ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ኮማንድ ፖስት በተሰኘው ወታደራዊ እዝ ስር ወድቃለች። እንደ ሶሪያው መሪ ሁሉ አገዛዙ  ሁሉንም ነገር በጉልበት ለመፍታት  በሚያደርገው ተግባር ተማሮና ተስፋ ቆርጦ  “በቃን እሾህን በእሾህ” ብሎ በብረት ለመፋለም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሀገር በቀል የትጥቅ ትግል ተቀስቅሷል፡፡

እንደሶርያው ሁሉ የሀገራችንም ተቃዋሚዎች አቅም የሚፈለገውን ያክል የዳበረ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስቴር መለሰ ዜናዊ አንድ ጊዜ ሲናገሩ “ተቃዋሚው እግር እስኪያወጣ እንታገሰዋለን ከዚያም እግሩን እንቆርጠዋለን” በሚለው መመሪያቸው በሀገሪቱ ወስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር ሰፊ ስራ፤ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ፈጽመዋል። ይህ ጥቃት በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሲቪክ ማህበራትም ላይ ያነጣጠረ ነው።

የስርአቱ በትር እንዳለ ሆኖ ግን ብዙ ጊዜ በተለያዩ ኢትዮጵያውያን   ደግሞ ደጋግሞ የሚነገረው ህወሀት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየት የቻለው በህዝብ ውስጥ ባለው ተቀባይነት ሳይሆን በተቃዋሞው አለመተባበር ነው የሚለው አባባል የተቃዋሚውን ምን ያህል በየራሱ ጎራ ተለያይቶ የቆመ ለመሆኑ በቂ አመላካች ነው። የተቃዋሚው ተለያይቶ መቆም፣ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነትን ለማግኝትና የትግሉ “መሪ” ሆኖ ለመውጣት የሚደረገው ሩጫ፣ በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በህጋዊነት መንቀሳቀስ የከተነፈጉት ጋር በአመርቂ ሁኔታ ለመተባበር የሚታየው ፍራቻ…ወዘተ ለትብብር መሳካት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ቀጥሏል።

እንደሶርያ ሁሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መሀል በተወሰነ ደረጃ የመሰባሰብ እርምጃ የሚታይ ቢሆንም (ለምሳሌ መድረክ፣ ሽንጎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥምረት) አሁንም ቢሆን  የሚታየው እጅግ የተራራቀ የአመለካከት መዘበራረቅ በትግሉ አካሄድ ላይ ትልቅ እንደምታን አስከትሏል። ከህወሀት/ኢህአዴግ በኋላ የሚከተለው ምንድነው? በሚለው ጉዳይ ላይ እጅግ የተራራቀ ጽንፍ ላይ የቆሙ አመለካከቶቸ ይታያሉ። የተወሰነው የተቃዋሚ ጎራ በተለይም የአንድነት ሀይሎች በኢትዮጵያ አንድነት ስር ሁሉንም የሚያሳትፍ ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሰርአትን እውን ማድረግ ራእያቸው እንደሆነ በግልጽ ሰፍሯል፤ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵየዊ አይደለሁም እንዳውም የኛ ነጻነት የሚረጋገጠው ይህች ሀገር ስትበታተን ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠል አለመቀጠላችንን አሁን አንወስንም በማለት በሀገሪቱ አንድነት ላይ ያላቸውን አቋም በእንጥልጥል ያስቀምጡታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የብሄር መብት፣ የጋራ መብት የሚባል ነገር በፍጹም አንስማ ይላሉ። በተቃዋሚው ጎራ ወደ ውስጥ የመመልከት ባህሪ ያለው የጎሳ ብሄረተኛነት ስሜት ካሁን በፊት በስፋት ባልታየባቸው ቦታወች ሳይቀር እየተከሰተና በፍጥነትም እያደገ ነው። የተወሰኑት ተቃዋሚዎች ኤርትራን ተገን አድርገው ስለተነሱ በአንድንት ሀይሎች በኩል በጥርጣሬ ይታያሉ። እነሱም የአንድነት ሀይሎችን እንዲሁ በ”አክራሪ ኢትዮጵያዊነት” ሲከሱ ይደመጣሉ። ይህ ሁሉ ትግሉን በተቀነባበረና በቀጣይነት ወደፊት ለመግፋት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል። ለአገዛዙም  በተደጋጋሚ ለመውደቅ ከተንገዳገደ በኋላ እንደገና  ለመነሳትና ለማንሰራራት  እንዲችል ትልቅ እድል ሰጥቶታል።

ታቃዋሚዎች ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ መቻልና በወደፊቱ የሀገር ጉዳይ ላይም መሰረታዊና አስተማማኝ መግባባት ላይ መድረሱ እጅግ አስፈላጊ ሂደት ነው። በዚህ ትግል ውስጥ ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃዋሚ ሀይሎች አንዱና ታላቁ  ፈተና ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

የአክራሪነትና የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት አደጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታወች እጅግ ሰፊ ናቸው። አገዛዙ በሰላማዊ ታጋዮችና አክራሪ ያልሆኑ ሀይሎች (ሞደሬት) ላይ በሩን በዘጋ ቁጥር ሁኔታው የሚጋብዘው ህዝቡም ሆነ ድርጅቶች እጅግ የከረረ መንገድን እንዲመርጡ ነው። ሀገራችን ከምትገኝበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ አለሸባብ ከሚንቀሳቀስበት ሶማሊያና ኬንያ ጋር ያለውን የድንበር ተዋሳኝነት፣ የጎሳ መወራረስ…ወዘተ በመመልከት በኢትዮጵያ ውስጥ ሁኔታዎች እየተባባሱ ግጭትም እየተስፋፉ ሲሄዱ ለአልሸባብና ለሌሎችም በር ሊከፈት አንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቀውስ አረንቋ ውስጥ እንድትማስን የሚሹ የሩቅም የቅርብም መንግስታት እንዳሉና በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሁኔታዎችን ቢቻል ለነሱ በሚጠቅም ሁኔታ መቅረጽ፤ ባይቻል ግን ሁኔታወችን ይበልጥ ከማወሳሰብ ። ወደኋላ እንደማይሉ መገንንዘብ ይገባል።

የውጭ መንግስታት ሁል ጊዜም የሚመለከቱት የየራሳቸውን ሀገር ጥቅም ስለሆነ ይህ ሁኔታ የምእራብ መንግስታትንም ከሀወሀት/ኢህአዴግ ጋር ተጣብቀው እንዲቀጥሉ ሊያደረጋቸው ከሚችሉት የተለያዩ ምክንያቶች አንዱ  እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው።

እንደሶርያ ሁሉ ስርቱን ለማስወገድና የተሻለ ሁኔታን ለማምጣት በምን ዓይነት ስልት እንሂድ የሚለው በኛም ሀገር ሁኔታ ደግሞ ደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው። በሀገራችን ውስጥ ባለፉት 25 አመታት ውስጥ የተካሄደውን ትግል ስንመለከት፣ በአብዛኝው የገዥውን ቡድን ጸረ ዴሞክራሲያዊነት ያጋለጠው ሰላማዊ ትግሉ ነው። ለዚህም ምርጫ 97 (2005) አንድ ምሳሌ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ከምን ጊዜውም በላይ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ የሚያካሂደው ትግል እጅግ ጎልቶ በተለይ “ኦሮሚያ”ና የ”አማራ” ክልሎች ተብለው በሚታወቁት አካባቢዎች ከፍተኛ ድልን አሰመስግቧል። በአንጻሩም የስርአቱን ደካማነት አጋልጧል።

ያም ሆኖ ግን አገዛዙ  በሚያካሂደው ጭፍጨፋ የተነሳ “ሰላማዊ ትግል የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም “ በማለት መሰሪያ በማንሳት የመፋለም ቁርጠኛነት በሰፊው እየታየ ነው።

አሁን ባለው የኢትዮጰያ ሁኔታ የመሳሪያው ትግል ሊያሰከትል የሚችለውን ውጤት መናገር መሉ በሙሉ ቢከብድም ከሌሎች ሀገሮች ትምህርት መውስድና አስፈላጊውንም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ያም ሆነ ይህ ሰላማዊ የህዝብ ትግል ምንም እንኳን አሰቸጋሪ ቢመስል ውጤቱ አስተማማኝና የሚያሰከትለውም ጥፋትና ውድመት ዝቅተኛ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

አንዳንዶች በሚታየው ጭካኔ ላይ ብቻ በመመረርኮዝ፣ ካሁን በኋላ ሰላማዊ ትግል እብቅቷል፣ አልቆለታል። ሁሉም ነገር ወደመሳሪያ ፍልሚያ ብቻ መዞር አለበት ይላሉ። ይህ ስህተት ነው፡፡ አዎስርአቱ ሰው ያስራል፣ ይገድላልም። ይህ ግን ከሰላማዊ ትግል ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። የመሳሪያ ትግል ሲካሄድም ቢሆን በአካባቢው ያለውን ህዝብ ያስራል፣ ንብረቱን ያቃጥላል፤ ይገድላል። ሆኖም አገዛዙ 100 ሚሊዮን ኢትዮጰያውያንን አስሮና ገድሎ መጨረስ እንደማይችል በርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ሰለማዊ ትግሉ ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ብዙሀኑን ሊያሰልፍ የሚችል፤ ምን ጊዜም የሞራል የበላይነትን እንደያዘ የሚያቆይ አለምአቀፍ ድጋፍንም ለማግኘት እጅግ የሚያግዝ የትግል ስልት ነው። ከዚህም ውጭ ዴሞክርሲያዊ መንግስትና ስርአት በመሳሪያ ከሚመጣው ይልቅ በሰላማዊ ትግል መወለዱ በተሻለ ሁኔታ አስተማማኝ ነውና ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል፡፡ ሰላማዊ ትግልን ሙሉ በሙሉ አሽቀንጥሮ መሄድ ሲጀመር ደግሞ ጎን ለጎን ሊኖሩ የሚችሉትን  አደጋዎች ማየት እጅግ ተገቢ ነው። ህዝብ በቀጣይነት በሰለማዊ ትግሉ ስርአቱን ሊሞግተውና አስፈላጊውን ጫና ሊያሳድርበት ይገባል።

ትልቁ ቁም ነገር በሰላማዊ ትግል ስም አንገት አቀርቅሮ መገዛት ወይም የተልፈሰፈሰ ተቃውሞን ማካሄድ ሳይሆን ከህዝብ ፍላጎት ጋር የሚመጥን ሰላማዊና ቆራጥ እንቅስቃሴን ለማድረግ የሚያስችል አቅም መገንባትና ተግባራዊ ማድረግ ነው። የአቅም ግንባታ ሰራ ለመሳሪያም ይሁን ለሰላማዊ ትግል ወሳኝ ነው። ያለበቂ አቅም የትግል ስልት ብቻውን የሚያስከትለው ፋይዳ የለም።

በሀገራችን እንደሚታየው ገዥው ቡድን እስካሁን ደግሞ ደጋግሞ የቀረበለትን የብሄራዊ እርቅና መግባባት ጥሪ በማፊዝ ከማለፍና ከማኮላሽት  ባሻገር በጎ ምላሽ ለመስጠት ከቶውንም አልቻለም።

አገዛዙ በተቃዋሚው በኩል የሚቀርበውን የብሄራዊ መግባባትና እርቅ ጥሪ

1ኛ “በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ “ የሚደረግ ጥረት እድርጎ ይመለከተዋል።

2ኛ  የሰው ህይወትን የሚቀጥፍ ግጭት እየታየ፣ “የምን እርቅ ነው? ማን ከማን ተጣላ” በማለት ያሾፋል

3ኛ  አሁን ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደጎን አድርጎ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት” ከህዝብ ጋር መወያየት ጀምሬአለሁ “ ይላል

4ኛ፤ ህብቡ ስርአቱ ላይ መሰረታዊ ተቃውሞ እያሰማና ራሳችን የመረጥነውንና የራሳችን የምንለው መንግስት እንፈልጋለን ኢህአዴግ በቃን በማለት ህይወቱን ሳይቀር እየገበረ ባለበት ሁኔታ፣ “ጥልቅ ተሀድሶ በማድረግ ላይ ነን” በማለት፤የሚጓዘው ለብሄራዊ እርቅ ሳይሆን ራሱን አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሆነ  በግልጽ እያሳየን ነው፡

 

ይህ ሁሉ  የአገዛዙ ፍላጎት የጦርነትና የአመጽ አዙሪትን ለመስበርና በቀጣይነትም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ በመስጠትና በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ፣ ሁሉም የኔ ብሎ የሚያከብረው የሚንከባበበው ስርአትና መንግስት በመፍጠር እቅድ ዙሪያ ያጠነጠነ ሳይሆን የራሱን አመለካከትና ዘላለማዊ ገዥነት በማስረገጥ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ነው። በመሆኑም በተደጋጋሚ እንደታየው አገዛዙ ለብሄራዊ እርቅ ተግባራዊነት እጅግ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ሀገራችንን ከጊዜ ወደጊዜም እጅግ የተወሳሰበ አስቸጋሪ ወደ ሆነ ሁኔታ ውስጥ እያስገባት ይገኛል። ይህ እጅግ አሳዛኝና ሁሉንም የሚጎዳ ታላቅ ስህተት ነው።

በዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዥው ቡድን ከሶርያ ትልቅ ትምህርት ሊቀስሙ  ይገባል። ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል የሚካሄድ መፈክር ወይም ራስን ለማጠናከር ጊዜ መግዣ እስትራተጂ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን “እዛም ቤት እሳት አለ” ነውና ውጤቱ የማያቋርጥና እያደገ የሚመጣ ምስቅልቅልና ጥፋት ነው የሚሆነው።

ሀቀኛ ብሄራዊ እርቅ አንዱ ወገን ባንዱ ላይ ጣት የሚቀስርበት መድረክ ሳይሆን የአገርና የህዘብ የወደፊት እጣ ፈንታ ቅድሚያ ተሰጥቶት ህሉም ወገኖች በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች የተሰሩ በደሎች ግፎችና ሰቆቃዎችን በጋራ ተመልክተውና መርምረው እነኚህ በደሎች ወደ ታሪክ ማህደር የሚሸጋገሩበትንና ዳግም የማይፈጸሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ታሪክን በታሪክነቱ ፖለቲካንም በፖለቲካነቱ መረዳት የምንችለው። ብሄራዊ እርቅ ባንድ ኮንፈረንስ ወይንም በጥቂት ስብሰባዎች የሚከናወን ሳይሆን ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚሰራ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ የረዥም ጊዜ ሂደትና ስራ ነው። የአገር ጉዳይ ያገባናል ወይንም ያሳስበናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ለሃቀኛና ለእውነተኛ የብሄራዊ እርቅና ዘላቂ ማህበራዊ መግባባት መጀመርና መሳካት ከፖሊቲካዊ አጀንዳቸው  በበለጠ እንጂ ባልተናነሰ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የታሪክ ምርኮኞች ከመሆን ድነን የወደፊት አገራዊ አቅጣጫ ቀራጮችና የአዲስ ምናብና የአዲስ ስርአት መሃንዲሶች መሆን የምንችለው።

ማጠቃለያ

ዛሬ በሶርያ የምናየውና የምንታዘበው የህዝብ ፍጅትና የአገር መፈረካከስ አደጋ  ስር መሰረቱ በወቅቱና በጊዜው መፍትሄ ያልተሰጠውና እልባት ያላገኘ ለዓመታተ ሲንከባለል የቆየና ስር የሰደደ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግር ውጤት ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ  የምንታዘበው አደጋም ከዚህ ብዙ የራቀ አይደለም። በአገራችን  የሚታየው ችግር በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ ካላገኘ አሁን ካለው በባሰ ሁኔታ የተወሳሰበና የተቆላለፈ ችግር ውስጥ አገራችን እንደምትገባ አጠያያቂ አይሆንም።  በስልጣን ላይ ያለው መንግስትና ተቃዋሚ ሃይሎች ከሶርያ ፈተና ትምህርት ቀስመው አገራችንን ከተጋረጠባት ፈተና የማዳን ሃላፊነት ማየት ያለባቸው ከፖሊቲካ ሂሳብና ስሌት አኩዋያ ብቻ ሳይሆን ከታሪክ ተጠያቂነት አንጻር መሆንም  ይኖርበታል።

የሶርያ ልምድ ለሀገራችን ታላቅ ትምህርትን ይሰጣል። የሶሪያው ፕሬዚደንት በሽር እልአሳድና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ የሚመሩዋቸው ስርአቶች አሰራር፣ የተከተሉት የፖለቲካ አካሄድ፣ ያሳለፉት ታሪክና፣  አሁን የሚገኙበት ሁኔታ የየራሳቸው ልዩ ባህሪ እንዳለ ሆኖ እጅግ ብዙ ተመሳሳይነት አላቸው። በሁለቱ ሀገሮች ተቃዋሚወች መሀልም እጅግ ብዙ ተመሳሳይ ጉዳዮች ይታያሉ።

ሀገራችን ኢትዮጵያና ወገኖቻችን እጅግ ፈታኝና አሰቃቂ በሆነ ሂደት ላይ ይገኛሉ። ስርአቱ ከህዝብ ጋር የገባበት ቅራኔ እጅግ እየተወሳሰበና እየተካረረ እንጂ እየረገበና እየተሻሻለ አልመጣም።

ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኝ በስልጣን ላይ ያለው መንግስታት ሀላፊነት ታላቁን ቦታ ቢይዝም የተቃዋሚው ጎራ አስተዋጽኦም ዝቅ ተደርጎ የሚታይ አይደለም። በሁሉም በኩል የተሰለፉት የፖለቲካ ተዋንያን እስካሁን የፈጸሙትና የተጓዙበት መንገድ  መርምረው በቀጣይነት የሚወስዱት እርምጃዎች ለሀገርም ሆነ ለህዝብ ደህንነትና ከራሷ ጋር እርቅ የፈጠረች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወይም የገባንበትን ምስቅልቅል ይበልጥ ለማወሳሰብ ታላቅ ሚና ይኖረዋል። ሁኔታውን ተገንዝቦና ከታሪክ ተምሮ እያንዳንዱ ባለድርሻ ሳይዘገይ (አንዱአለም አራጌ እንደሚለው ያልተኬደበት ጉዞን በመጓዝ) አሁን የሚታየውን አደጋ ለመስረታዊ ችግሮቻችን መፍትሄ መፈለጊያ አጋጣሚ አድርጎ  ይጠቀምበታል ወይስ ይህንንም አድል እንዳለፉት ሁሉ ያባክነዋል የሚለው እያንዳንዱ ዜጋ ሊመልስው የሚገባውና ውጤቱንም የምናየው ይሆናል። ለማንኛውም ልብ ያለው ልብ ይበል።

አስተያየትዎን በሚከተለው አድራሻ መላክ ይችላሉ፡ ethioandenet@bell.net

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: