The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ማንነትና የብሄር ማንነት መገለጫ መርሆዎች

የኢትዮጵያውያን የጋራ
ማንነትና የብሄር ማንነት
መገለጫ መርሆዎች
በኢትዮጵያ ጥናት ምርምርና ፓሊሲ ኢንስቲትዩት (EDF/ ERPI) ተዘጋጅቶ የቀረበ ፅሁፍ

ጥር, 2017

ዋሽንግተን ዲሲ USA

መግቢያ

በኢትዮጵያውያን የውይይት መድረክ EDF (Ethiopian Dialogue Forum) የኢትዮጵያ ጥናት ምርምርና ፓሊሲ ኢንስቲትዩት ERPI ( Ethiopian Research and Policy Institute) ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የፓለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ውስጥ ምላሽ ያጡና ግልፅነት የጎደላቸውን ጉዳዮች እየመዘዙ በማውጣት በጥልቀት ማጥናትና ከፍተኛ የሃሳብ ጥራትን ማምጣት እንዲሁም በአንዳንድ ወሳኝ የሚሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መርሆ የሚሆኑ አሳቦችን ማፍለቅና ለችግሮች አማራጭ መፍትሄዎችን ማቅረብ የፓሊሲ አቅጣጫዎችን ማሳየት ነው።

በዚህ መሰረት በዚህ በዛሬው ፅሁፋችን የምናቀርበው አሳብ በኢትዮጵያ የፓለቲካ ምህዳር ውስጥ በተለይም በአሁኑ ሰዓት የብሄራዊ ማንነት ወይም የኢትዮጵያውያን የወል ማንነት እና የብሄሮች ማንነት ጉዳይ ዋና የፓለቲካ ማጠንጠኛ ጉዳይ ሆኗልና ይህንን የፓለቲካ መጫወቻ ፅንሰ ሃሳብ በጥልቀት እንመረምራለን። በተለይ ባለፉት ሃምሳ አመታት ገደማ በብዙ ወገኖች ዘንድ ብሄራዊ ማንነትንና ዘውጋዊ ምንነትን ተገን ያደረገ የማንነት ክርክሮች ይካሄዳሉ። ነገር ግን ክርክሩ እምብዛም በአምክህኖትና በጥልቅ ጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ አይመስልም። ብሄራዊ ማንነት ምንድነው? የወል ማንነታችን ከምን ከምን ይገነባል? ለመሆኑ ቡድናዊ ወይም የብሄር ማንነት ከብሄራዊ ማንነት በምን ይለያል? እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሆነን ሳለን አንድ ነን ስንል ምን ማለታችን ነው? ብዙ የሆኑ ህዝቦች በአንድ የሃገር ጠገግ ውስጥ ራሳቸውን ሲያገኙ በምን መንገድ ነው ብሄራዊ ማንነታቸውና ቡድናዊ ማንነታቸው የሚገለፁት? ማንነቶች እርስ በርስ እንደ አፍራሽና ፈራሽ ሳይተያዩ ተደጋጋፊ ሆነው የሚኖሩት እንዴት ነው? የሚለውን አብጠርጥሮ ማየት በተለይ ከፓለቲከኞች የሚጠበቅ ትልቅ ጉዳይ ነው። በአንድ የፓለቲካ ጠገግ ውስጥ ያሉ ብሄሮች ራሳቸውን የሚገልፁበትን መርህ እና ብሄራዊ ማንነት የሚገለፅበት መርህ አንድ ዓይነት መስመር ውስጥ ከገቡ እነዚህ ሁለት ማንነቶች ፍክክር ውስጥ ይገባሉ። ሽሚያና ንጥቂያ እርስ በርስ መጋፈፍ ይጀምራሉ። ይህ ሲሆን ፓለቲካውም በዚህ ትርምስ ውስጥ ሲገባ ግልፅነት የሌለው ርእዮት ይመጣል። ፓሊሲዎችና የፓለቲካ ርእዮት ጥራት በሌላቸው በተምታቱ ፅንሰ ሃሳቦች ላይ ሲመሰረት የሚከተለው ነገር ትርምስ ነው። አንዱ ማንነት ሌላውን እንደ ባላንጣ እንዲያይ የሚያደርግ ድባብ ስለሚፈጠር የሃገሪቱ ማህበራዊ ሃብት ይፈርሳል። ሄዶ ሄዶም ሃገርን ለማሳጣት የሚችል ግጭት ያመጣል።

በሃገራችን የኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሄር ማንነት መገለጫዎች እየተምታቱ ያስቸገሩበት ምክንያት አንደኛ ብዙዎች የብሄራዊ ማንነትን መገለጫ የጋራ ባህል ከመሆኑ ጋር በሃይል ከማያያዛቸው ጋር የመጣ ችግር ነው። በኢትዮጵያ የባህል ሚዛኑ በብሄሮች መካከል ተመጣጣኝ ባለመሆኑና የአማራ ባህል በተወሰነ መልኩ የትግራይ ባህል ሃገሪቱን ስለተጫናት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት የሁሉን ብሄር እኩልነት የሚያሳይ መልክ የላትም የሚል ነው። በርግጥ ቡድኖች ሁሉ ከባህል አንፃር የወል መልክ አልታይ ቢላቸው እውነት አላቸው። ይህ የባህል እኩልነት ችግር በርግጥ በሰፊው አለ። ከዚህ ከባህል አንፃር ኢትዮጵያ የወል መልኳ ብዝሃነቷን አያሳይም ቢባል ትክክል ነው። ነገር ግን ለአንድ ሃገር ቡድኖች የብሄራዊ ማንነት መገለጫ የሚሆነው ነገር የጋራ እሴት ወይም ባህል ብቻ አለመሆኑን በሚገባ መረዳት አለብን። ሌሎች ዋና የሚባሉ የብሄራዊ ማንነት ወይም የኢትዮጵያዊነት የወል ማንነት መገለጫ መርሆዎች አሉ። ምን አልባትም የባህል ጉዳይ በብዙህ ህዝብ ሃገር ዋና የብሄራዊ ማንነት መገለጫም መሆን የለበትም። ብሄራዊ ማንነት ከባህል ማንነት ተነጥሎ መታየት የሚኖርበት ሲሆን ዋናዎቹ መገለጫዎች ከዚህ ስር የምንዘረዝራቸው ናቸው። ባህላዊ ማንነትን ከብሄራዊ ማንነት ጋር አጣብቀን ስንይዝ የሚፈጠረው ችግር ገበያ ላይ የሚታየው ባህል የአንድ ብሄር ባህል ከሆነ ብሄራዊ ማንነት የሚባል ነገር አይታየንም። በርግጥ አንድ ብዙህ ህዝብ በውስጡ ያሉት ብሄሮች ባህላቸውን ከገበያ ላይ ካጡትና በመሃል አካባቢ ህልውናቸው የማይሸታቸው ከሆነ ያ ማህበረሰብ የባህል እኩልነትን ለማምጣት መስራት አለበት። አለበለዚያ ይህ ስሜት ውሎ እያደረ መቻቻልን ማህበራዊ ሃብትን እያፈረሰ ሃገርን ያሳጣል። በዋናነት ግን ይህ የባህል ኢእኩልነት እያለም ቢሆን ሌሎች የብሄራዊ ማንነት መገለጫዎች ስለሚኖሩ የባህል ኢእኩልነት በአንድ ብዙህ ሃገር ተፈጠረ ማለት አንድ ሃገር ብሄራዊ ማንነት የለውም ማለት እንዳልሆነ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ እንዘረዝራለን። እንግዲህ በዚህ ፅሁፍ ስር የምናስቀምጣቸው መርሆዎች አንደኛ የብሄራዊ ምንነት መገለጫዎች ምን ምን እንደሆኑ ከመግለፅ ባሻገር በሁለተኛ ደረጃ ቡድኖች ራሳቸውን የሚገልፁባቸው መርሆዎች ምን ምን እንደሆኑ እናብራራለን። እነዚህ መርሆዎች በተለይ የፓለቲካ ዳስ ለሚሰሩ ወገኖች ሁሉ መነሻ ይሆናሉ ብለን እናምናለን። በጠራ መስመር የሚስተናገዱ ማንነቶችን የያዘ ፓለቲከኛ ለውጥን ያመጣል። በዋና ዋና የፓለቲካ መጫወቻ ፅንሰ ሃሳቦች ዙሩያ ግልፅ ብያኔ (definition) መኖሩ ሃገርን ከጥፋት ያድናል። አሁን ወደ መርሆዎቹ እንለፍ።

አራቱ የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ መርሆዎች

የሰው ልጅ ግላዊም ማህበራዊም ፍጡር ነው። በመሆኑም የዚህን ዓለም ኑሮውን ለማሸነፍ የመንፈሳዊና የስጋዊ እርካታን ለማግኘት የሚፈጥራቸው ስብስቦች ሁሉ ይህንን መስረታዊ
ፍላጎት የሚያሟላለት እንዲሆን ይፈልጋል። ወደ ትልቁ የሰው ልጆች ስብስብ ወይም አገር ስንመጣ ደግሞ ይህንን ጠገግ ከፈጠሩ ህዝቦች መካከል ጠገጉን ለማሳደግ ለማበልፀግ የሚነሱ የፓለቲካ ሃይላት ይህንን የሰው ልጅን ቡድናዊና ግላዊ ፍላጎት ለመንከባከብ የሚነሱ መሆን አለባቸው። ቡድናዊ ጉዳይ ላይ አጥብቀው የግለሰብን ጉዳይ ችላ የሚሉ ፓለቲከኞች ከተነሱና በአንፃሩ የግልን ጉዳይ አጥብቀው የቡድን ጉዳይን ችላ የሚሉ ከተነሱ በዚህ ጠገግ ውስጥ ያሉ የሰው ልጆች ምን ጊዜም አይረኩም። በመሆኑም ጉዳዩ አለመረጋጋትን ሊያመጣ ይችላል። በመሆኑም ተለጣጣቂ መንግስታት ይህንን ሃቅ ተረድተው ሚዛናዊ የሆነ የፓለቲካ ርዕዮት ሊከተሉ ይገባል።

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙህ ሆነን አንድ ነን ወይም ብሄራዊ ማንነት አለን ስንል በሚከተሉት አራት መሰረታዊ መርሆዎች ይገለፃል ወይም መገለፅ ይኖርበታል። እነዚህ የብሄራዊ ማንነት ቤት መስሪያ ዋልታና ማገሮች የሚከተሉት ናቸው።

መርሆ 1. አንድ የጋራ የፓለቲካ የፍላጎት ማእከል
ወይም የፓለቲካ ማንነት
መርሆ 2. መሬት
መርሆ 3. ታሪክ
መርሆ 4. የጋራ እሴት

በርግጥ እነዚህ የብሄራዊ ማንነት መገለጫ መርሆዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ብዙህ ለሆኑ ሃገራት ሁሉ የወል መገለጫ መርህ ናቸው። የአለምን የመንግስትና የሃገር አወቃቀር ስናይ ይህቺ ዘመናዊት አለም በጣም ብዙህ ናት። በዓለም ላይ እጅግ ብዙዎቹ ሃገራት ብዙህ ናቸው። ለምሳሌ ህንድ ወደ 21 የሚጠጉ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሃገር ናት፣ ኔፓል ወደ 123 የሚሆኑ ብሄሮች የገነቧት ሃገር ናት። ኢንዶኔሽያን የፈጠሩ ብሄሮች ከ300 በላይ ናቸው። ቻይና የተፈጠረችው 56 በሚሆኑ ብሄሮች ነው። ብራዚል የተፈጠረችው በነጮች፣በጥቁሮች፣በቅይጥ፣ በእስያውያንና በነባር ህዝቦች ነው። ደቡብ አፍሪካ አስራ ሁለት በሚሆኑ ብሄሮች የተፈጠረች ሃገር ናት የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት ናት። ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከ850 ቋንቋ በላይ በሚናገሩ ልዩ ልዩ ብሄሮች ነው የተፈጠረችው። ከአፍሪካ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታቸውና በኢኮኖሚ እድገታቸው ምሳሌነትን ያተረፉት ጋና እና ቦትስዋና ህብር ናቸው። በአንፃሩ የተባበረችው አሜሪካ በመላው ዓለም ከሚገኙ ሃገራት ህዝቦችና ከዓለም የተለያዩ ብሄሮችን አቅፋ ይዛ የምትኖር ልበ ሰፊ አገር ናት። ይህቺ ሃገር እነዚህን የተለያየ የአመጋገብ አመል፣ የአለባበስ ባህል፣ የአስተዳደርና ዴሞክራሲ አረዳድ፣ ቋንቋና የተለያየ ስነ ልቡና ይዘው የሚኖሩባት ሃገር ሰትሆን ይህን ልዩነት ሁሉ የተሸከመው የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ስላለ ነው። እስራኤልን ስናይ አንዷ የብዝሃነት መገለጫ ሆና እናያለን። ብሪታኒያ፣ አውስትሬሊያ፣ ካናዳ እና እጅግ ብዙ የዓለማችን ሃገራት ብዙህ ናቸው። በአጠቃላይ በዓለም ላይ እስከ 7 ሺህ የሚደርስ ቋንቋ የሚነገር ሲሆን ይህን ያህል ቋንቋ የሚናገሩ የሰው ልጆች ከሁለት መቶ በሚያንሱ መንግስታት ወይም የፓለቲካ ጠግግ ስር ተጠቃለው ይኖራሉ። በአማካይ 36 ገደማ የሚገመቱ ብሄሮች በአንድ የፓለቲካ ጠገግ ስር የሚኖሩባት አለም ናት ይህቺ ምድር። ዛሬ ወደ 1/3ኛ የሚጠጉት የዓለም ሃገራት ኦፊሽያል ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ሆኗል። ፕላኔት ምድር ከውጭ ወደ ውስጥ ስትታይ ደግሞ ብዙህ ናት። በአጠቃላይ አገሮች ሰፊ የሰው ልጆች ስብስብ መድረኮች ሲሆኑ እነዚህ ሃገሮች ደግሞ አንድ ግዙፍ የዓለም ጥላ ፈጥረው በአንዳንድ ጉዳይ ላይ አብረው ለመስራት ተስማምተው ይኖራሉ። መንግስታት ከሉዓላዊነታቸው ላይ እየሸረፉ በመስጠት ገና ይህን ጠገግ ያጠነክራሉ።የዓለም ህዝቦች በዚህ መድረካቸው ላይ አንድ ነን ይላሉ። ይህ ግዙፍ የፕላኔት ጠገግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው።

በአጠቃላይ ሃገር የሚባለው ነገር ሲመሰረት ብዙዎችን ቡድኖችን አቅፎ መያዝ የሚችል የፓለቲካ ጠገግ በመሆኑ በመልክዓ ምድር ተደጋግፈው የሚገኙ ቡድኖች አብረው ይኖራሉ። ብሄር ጠባብ ነው። በውስጡ ዝቅተኛ ልዩነቶችን ለማቀፍ ቢችልም ጎላ ያሉ የሰው ልጅ ልዩነቶችን የሚሸከም ተፈጥሮ የለውም። ሌላ እሱን የሚያክልን ብሄር አቅፎ መያዝ አይችልም። አገር በተፈጥሮው ግን ልዩነትን ሁሉ ተሸክሞ መኖር የሚችል ትልቅ ጠገግ ነው። ታዲያ እነዚህ በአንድ ጠገግ ስር አብረው የሚኖሩ ብሄሮች ሁሉ እኩል የሆነ የባህልና የቋንቋ አጠቃቀም ስላላቸው አይደለም አንድ ነን እያሉ የሚኖሩት። ከፍ ሲል እንደገለፅነው አራት የብሄራዊ አንድነት መገለጫዎች አሉ። በነዚህ ላይ አሁን በዝርዝር እንወያይ።

አንድ የጋራ የፓለቲካ የፍላጎት ማእከል
( common political center of interest)

እንግዲህ አገር የሚባለው ነገር በተለይም በብዙህ ህዝቦች አማካይነት ሲቆም ዋናው መሰረቱ ፓለቲካዊ ነው። አገር የሚባለውን ድንኳን ስንተክል እኛ ብዙ ብሄሮች አንድ ዓይነት ስነ ልቡናና ዓመል ስላለን ወይም አንድ ባህል አንድ ሃይማኖት ለመፍጠር አይደለም። አገር ባህላዊና ሃይማኖታዊ ልዩነታችንን ሳይነካ ከዚህ ልዩነት በላይ የጋራ ማንነት ማበጀት የሚችል ከፍ ያለ ጣሪያ ያለው ጠገግ ነው። ይሁን እንጂ የጋራውን ማንነት ለመገንባት የሚጠይቀን መስዋእትም አለ። ይህ መስዋእት ግን ማንነታችንን ጨርሶ አያስጥለንም። በመጀመሪያ ይህንን አገር የተባለውን ጠገግ ስንፈጥር እንደ ምሰሶ ወይም ካስማ የሆነው አንዱ ነገር ለዚህ ድንኳንና በውስጡ ለሚኖሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ህይወት መሻሻል ይህንን ድንኳን ለማጠናከር ጥሪ አለን የሚሉ ሰዎች በየዘመኑ ይነሳሉ። እነዚህ ግለሰቦች የፓለቲካ ለሂቃን ናቸው። የአስተዳደር መሃንዲሶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ የፓለቲካ ጥሪ ያላቸው መሪዎች የሚያመጡት ራእይ በዚህ ድንኳንና በውስጡ ለሚኖሩ ሁሉ የህይወት መሻሻልን ለማምጣት ያለመ መሆን አለበት። ሁሉም ፓርቲዎች ባህላዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ ማቋቋም አይኖርባቸውም። ቡድኖች ሁሉ አንድ ሃገር ፈልገው ሲኖሩ መስዋእት ሊያደርጉት ከሚገባቸው ፍላጎት ወይም ሊገቱት ከሚገባቸው ፍላጎት መካከል አንዱ የፓለቲካ ማንነት ጉዳይን ነው። ቡድኖች ሁሉ በየፊናቸው የፓለቲካ መስመር ከያዙ በተፈጥሮው ለሃገር መስዋእት መሆን የነበረበትን ሚና መጫወት ፈለጉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የብሄራዊ ማንነትን የሚጋፋው ስለሆነ ሃገሪቱ የሚና ግጭት (political role conflict) ውስጥ ትገባለች። ሚናው በሚገባ ያልለየለት የፓለቲካ ጨዋታ ልክ ሚናው ያልለየ የገና ጨዋታን ይመስላል። ትርምስና ግጭት ይበዛዋል። ብሄራዊ ማንነት የእኔን ድርሻ ወይም ሚና ተቀራመታችሁ ይህ የኔ መገለጫ ነው ይላል። ይቀናል። በርግጥ ዝቅ ሲል ኋላ ላይ የምናየው የብሄሮች መገለጫ መርሆዎችን እየዘለልን የብሄር የፓለቲካ ጥብቆ ካማረንና ለብሄር ፓለቲካዊ ተክለ ሰውነት ከሰጠነው ያኔ የዋናው ጠገግ ስብእና ይነካል። የብሄር ቅንዓት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች ለብሄር ማንነት መገለጫ መሆን የሚገባው አንዱ ጉዳይ የፓለቲካ ተክለ ሰውነት መልበሱ ነው ይላሉ። ያለ ፓለቲካ ተክለ ሰውነት ወይም ብሄርን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቡድን ካላደረግን ምኑን የብሄር ማንነት ይባላል? ብለው የብሄርን ማንነት ለጥጠው ማየት ይሻሉ። የብሄር ማንነት ከፓለቲካ ውጭ ነው መገለፅ ያለበት ሲባሉ የብሄር ማንነት ማለት ጭፈራና ዘፈን የምግብ አሰራር በሚለው ሊገለፅ አይገባም፤ ይህ ያንሰዋል ይላሉ። ብሄርን ክፓለቲካ ተክለ ሰውነቱ ውጭ ሲያዩት ማንነቱ አንሶና ኮስሶ ይታያቸውና የፓለቲካ ልብስ በማልበስ ዳጎስ እንዲልላቸው ይጥራሉ። እዚህ ጋር ችግሩ ምንድን ነው? አገር የሚባለው ጠገግ ይህን ተክለሰውነት መስዋእት እንዲሆንለት ይፈልጋል። በአሃዳዊም ይሁን በፌደራል ስርዓት ለመተዳደር ብሄራዊ ማንነት ይህን ተክለ ስውነት በጥብቅ ይፈልገዋል። ቡድኖች አንድ ሃገር ካማራቸው የግድ የፓለቲካ ዝንባሌዎቻቸውን በጋራ ሊሰሩ መስማማት አለባቸው። አገር ራሱ የሚቆመው አንድም በጋራ የፓለቲካ ማእከል ወይም በብሄራዊ ጥላ ሥር ላይ በመሆኑ ነው። እነዚህ የዓለም ሃገራት አርባ የሚጠጉ ቡድኖች እየሆኑ ሃገር ከመሰረቱ በኋላ እያንዳንዳቸው ብሄራቸውን ፓለቲሳይዝ ማድረግ ቢፈልጉ አለም ትፈርሳለች። በደም ሃረግ ላይ ፓለቲካ ከቆመ ብዙው ዓለም ያዘምማል። በመሰረቱ ባህላዊ ማንነት በፓለቲካ ተክለ ስውነትም አይገለፅም። አንድ ብሄር ተገንጥሎ የራሱን መንግስት መስርቶ ቢኖርም እንኳን ባህሉና ሃይማኖቱ ከፓለቲካው ይለያል። ለምሳሌ ኦሮምያን ብንወስድ በእንበል ገበያ ሆነን ይህ ብሄር ቢገነጠል ኦሮሞ እንደ ባህሉ በገዳ ስርዓት አይኖርም። የራሱን ዘመናዊ መንግስት መስርቶ ገዳን ባህላችን እያለ ነው የሚኖረው። ይህ የሚያሳየው በብሄር ላይ በፓለተካ መደራጀት በተፈጥሮው በብዙህ ሃገራት ውስጥ የብሄር ማንነት መገለጫ አለመሆኑን ነው። ፓለቲካዊ ተክለ ሰውነት ያለው ብሄራዊ ማንነት ነው። ፓለቲካዊ ጉዳይ ስንል አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መሆንን አንድ መሰረታዊ ህግ መኖርን አስተዳደርን የሚያሳይ ነው። በአንድ ህገ መንግስት ስር መኖራችን አንድ ፓስፓርት መያዛችን የአንድ መንግስት ልጅ መሆናችን የጋራ መገለጫ የሚሆኑት ቡድኖች ብሄራዊ አንድነት ላይ መሰረቱን የጣለ የፓለተካ ስርዓት ሲኖራቸው ነው። ፓለቲካው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወታችንን ለማበልፀግ ሲሰራ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲሰራ ነው አንድነት የሚገለፀው። በመሆኑም የኢትዮጵያ የፓለቲካ ለሂቃን ይህንን ሊገነዘቡ ይገባል። ቡድናዊ ማንነት የብሄራዊ ማንነት መገለጫን ገፍፎ መውሰድ ከፈለገ ይህ አካሄድ ከቡድናዊ ማንነት መገለጫ ክብ ውስጥ ወጥቶና ተንጠራርቶ ከብሄራዊ ማንነት ክብ ውስጥ መግባትንና አጉራ ዘለልነት ባህርይን ያሳይል። ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት ወይም አንዱ የብሄራዊ መገለጫ መርህ አንድ የፓለቲካ መነሻ መኖር ነው። በዜግነት የሚያሰባስብ የፓለተካ ጨዋታ መኖር ማለት ነው በሌላ አገላለፅ።

መሬት

አንዳንድ ፓለቲከኞች መሬትን እንደ አንድ የቡድኖች ወይም የብሄሮች መገለጫ ለማየት ይፈልጋሉ። ነገር ግን በአንድ የፓለቲካ ጠገግ ስር የሚኖሩ ቡድኖች የጋራውን ቤት ሲሰሩ መጀመሪያ ማዋጣት ካለባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ከቀየ ጋር ያላቸውን መጣበቅ አላቀው ሰፊ ከሆነው የሃገራቸው ግዛት ጋር ማንነትን ማጣበቅ ነው። ብሄራዊ ማንነት የምንለው ግዘፍ ነስቶ ማንነቱ በተግባር እንዲታይ የሚያደርገው ነገር የመሬት የግዛት የባለቤትነት አንድነት ነው። አንዳንድ የብሄር ለሂቃን የሚሉት ምንድን ነው? የብሄር ማንነት ዋና መገለጫ መሬት ነው ይላሉ። ልክ እንደ ፓለቲካ ተክለ ስውነት ግዛትንም ለብሄር ማንነት መገለጫ በሃይል ይፈልጉታል። ይህ ዝንባሌ ብሄራዊ ማንነትን እርቃኑን ያስቀራል። በርግጥ ይህ እምነት መስረታዊ የሰው ልጆችን የስብስብ አፈጣጠር ያልተረዳም ነው። በመሰረቱ ብሄር በአንድ ቀን ተፈጥሮ የሆነ መሬት ላይ ዱብ ያለ ስብስብ አይደለም። የሰው ልጅ ለኑሮው ሲል ትናንሽ የሆኑ ስብስቦችን በአብዛኛው እያሰፋ እያሰፋ ሄዶ መጨረሻ ላይ ያገኘነው ብሄር ተፈጥሯል። ይህ ብሄር አንዳንዱ ግዛቱን ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው እያሰፋ ሲሄድ አንዳንዴ አንዳንድ ቡድኖችን ጨርሶ እያጠፋ አንዳንዴም የማረካቸውን መስለው እንዲኖሩ እያደረገ እያደገ የመጣም ሊሄን ይችላል። ለምሳሌ የሃገራችንን የኦሮሞ መስፋፋት ስናይ በሃገሪቱ ከአንድ ጫፍ ተነስቶ ሌላ ጫፍ እስኪደርስ ድረስ ብዙ ጦርነት አድርጎ የማረከውን ኦሮምኛ አናግሮ ተስፋፍቷል። ደቡብ ኢትዮጵያ ብንሄድ ኮንሶዎች፣ ቡርጂዎች፣ ኬሌዎች የኦሮሞ ባህል ባህላቸውን ተጭኖት እናያለን። የጌዲኦ ብሄር የገዳ ስርዓትን ይከተላል። አማራውን ስናይ ከጎንደር ጎጃም ወሎ ሸዋ ድረስ ሲስፋፋ ሌሎች ቡድኖች ተውጠው ተፈናቅለዋል። በቁጥራቸው ትናንሽ በሆኑ ብሄሮች መካከል የጎሳ ጦርነት እየተካሄደ ግዛት ለማስፋፋት እየተዋጉ ኖረዋል። በአጠቃላይ ዓለምን ስናይ ደግሞ ዓለም በንቅናቄ የተፈጠረች ናት። መሬትን በእጁ ጠፍጥፎ የሰራ የለም። ሌሎች ባህሎቻችንን ቋንቋችንን እንደምንሰራው መሬትን አልሰራነውም። የተፈጥሮ ፀጋ ለሰው ልጆች የተሰጠ ሲሆን ቡድኖች በአንድነት ሲኖሩ ይህን ፀጋ የኔ የኔ ማለታቸውን ትተው የጋራ ሃገር መመስረት አለባቸው። በርግጥ የተፈጥሮ ፀጋ ነው ሲባል በሃገሮች መሃል ድንበር አይኑር አይደለም። ዓለም እንዳትተራመስ በአሁኑ ሰዓት ድንበር ያሻል። በመሆኑም ዛሬ ሃገሮች ሁሉ ካርታ ተሰርቶላቸው ግዛቶች ሁሉ በውስጣቸው ለሚኖሩ ህዝቦች የአንድነታቸው መገለጫ ሆነዋል። ዜጎች በአንድ ሃገር ልጅነት ራሳቸውን ይገልፃሉ። ነገር ግን ቡድኖች ይህን የሃገር መስዋእት ነጥቀዉ ከዚህ ወዲያ የኔ ነው ካሉ አንድነት ይጠፋል። ለነገሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ቡድኖች ለብዙ ጊዜ ከመኖራቸው የተነሳ የኔ የኔ የሚሉት ግልፅ ወሰንም የለም። ቡድኖች የከተሞችንና የቀበሌዎችን ስም ከቋንቋቸው ጋር መሄድ አለመሄዱን እያዩ ከተቦጫጨቁ ትልቁን የሃገር ድንኳን ካስማ እየነቀሉ ነው ማለት ነው። ፊንፍኔ ማለት ኦሮምኛ ነው። የለም ፊን ፊን ከሚለው የመጣ ኦማርኛ ነው። ወልቃይት ውስጥ አንዳንዶች ስሞች በትግርኛ ነው የተሰየሙት። የለም በአማርኛም አለ በአረብኛም አለ እሱ አይደለም ቁምነገሩ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክ የመጣ ነው ከተባለ በዚህ ስም ምክንያት ግሪክ ይውሰደን?።ስሥሥ ይውሰደን ወይ?። ይህ አይነት ተራ እና ስስታም አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ፓለቲካ ህይወት ውስጥ ጓዙን ጠቅልሎ መውጣት አለበት። የቡድኖችን ማንነት ዛሬ ከተፈጠረ ዘጠኝ ክልል ጋር ማያያዝ አገር ያፈርሳል። ረጅም ዘመን የኖረ ህዝብ የተነቃነቀና የተዋለደ ህዝብ በዘህ ደረጃ ወደ ኋላ ሊወሰድ የሚችልበት መሰረት የለም። ደግሞም በኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች በብሄር ከተሰሩ ከሁለትና በላይ ብሄሮች የተገኘው ቅይጥ ህዝብ ክልል አልባ ከቦታ ውጭ የሆነ ህዝብ ያደርገዋል። ብሄሮች መሬታቸውን አዋህደዋል። ከሁሉ በላይ ለብዙ ዘመንም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሃገራቸውን ሲጠብቁ ኖረዋል። አባቶች የሞቱት ኦሮምያ፣ ትግራይ ወዘተ ስለሚባል አገር ሳይሆን ስለ አንድነት ነው። አዲስ አበባ የኦሮሞ አይደለችም፣ የአማራም አይደለችም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም አይደለችም። አዲስ አበባ የዜጎች ሁሉ ናት። ልክ እንደዚሁ ባህርዳር መቀሌ አዋሳ አሶሳ ሃረር ድሬዳዋ ነቀምት ወዘተ ሁሉ የዜጎች ናቸው። እነዚህ ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ የሁላችን ስትሆን ነው ብሄራዊ ማንነት ስጋ የሚለብሰው። የብሄር ለሂቃን ይህን ሲሰሙ የለም የብሄር ማንነት ከመሬት ውጭ አይታሰብም ይሉ ይሆናል። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ነገር ቡድኖች ወይም ብሄሮች መሬትንና ፓለቲካዊ ማንነትን መስዋእት አድርገዋል ማለት መሬትንና ፓለተካዊ ተክለ ሰውነትን ተገፈፉ ማለት አይደለም። ይህ መስዋእት ያደረጉት ሁሉ በዝቶና ገዝፎ በዜግነት ያገኙታል። ኦሮሞው በኦሮምያ ክልል ሳይታጠር በአራቱም ማእዘን የመሬት ባለቤት ይሆናል። ግዛቱን ያሰፋል። በአራቱም ማእዘን የፓለቲካ ተሳትፎው ይሰፋል። በመሆኑም ቡድኖች መሬትን መስዋእት አደረጉ ማለት በረከትን ጨመሩ እንጂ የሚያጡት አይኖርም። ወደ ሶስተኛው እንለፍ።

ታሪክ

በርግጥ ብሄሮች በጦርነት ወይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አንድ የፓለቲካ ጠገግ ከመምጣታቸው በፊት የየራሳቸው ታሪክና አፈታሪክ አላቸው። እነዚህን ታሪኮች መጠበቅ አስፈላጊ ነው። በአንፃሩ አብረው መኖር ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የህይወት ውጣና ውረድን አልፈዋል። ከነዚህ ውስጥ ያጋጠማቸው መልካም ጊዜና ፈተና ሁሉ በጋራ ይዘክሩታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከሚኮሩበት ታሪክ አንዱ በቅኝ ግዛት አለመገዛታችን ነው። ይህ ታሪክ በተለይ ራሳችንን ከሌላው ዓለም ጋር ስናገኝ ብሄራዊ አንድነትን የሚሰጠን ነው። ኦሮሞው ጉራጌው ትግሬው አደሬው ኮንሶው ወላይታው ወዘተ ቅኝ አልተገዛም። ይህ ታሪክ የአንድነት መገለጫ ይሆናል። በአንድ መንግስት ስር ብዙ አመታት መቆየታችን የአንድነታችን መገለጫ ነው። በርግጥ ያሳለፍናቸው መንግስታት እንደ ቡድንም እንደ ግለሰብም ጨቁነዋል። ቤታችን ባይመቸን እንዲመቸን እንታገላለን እንጂ ኢትዮጵያዊነታችንን እንክድም። በሌላ በኩል ያሳለፍናቸው ድርቅና የጥጋብ ጊዚያት ሁሉ የጋራ ሆነው አንድ ሊያደርጉን ይገባል። በአጠቃላይ ታሪክን በሚመለከት በዋና ዋና ታሪኮች ላይ አንድነታችንን እያሳየን በዝርዝር ታሪክ አረዳድ ላይ የግለሰቦች መረዳት ቢለያይ ከልዩነት ጋር አብሮ መኖር ይቻላል። አፄ ቴዎድሮስ ወይም አፄ ዮሃንስ ወይም አፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበራቸውን ሚና በሚመለከት ግለሰቦች የተለያየ መረዳት ቢኖራቸው ተቻችሎ መኖር ነው የዴሞክራሲ ባህል የሚባለው። ስለዚህ በታሪክ ላይ መጋጨት ሳይሆን አሁን ባሉ ችግሮች ላይ አተኩሮ ለጋራ መፍትሄ በጋራ መስራት ነው አንድነትን የሚያጠናክረው።

4 የጋራ እሴት

እዚህ ጋር ትንሽ መወያየትና ሚዛናዊ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። ከፍ ሲል እንደገለፅነው በተለይ ብዙህ ሃገራት ብሄራዊ ማንነታቸውን ከባህልና ቋንቋ ጋር ማጣበቅ የለባቸውም። ሃገርም በተፈጥሮው ይህን አይጠይቅም። ብሄሮች ብዙህ ሲሆኑ የትኛውን ባህል የብሄራዊ ማንነት መገለጫ ያደርጋሉ? በርግጥ ባለ ብዙ ባህል መሆናቸውን ነው እንደ ሃብት ሊገልፁት የሚገባው። በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በህገ መንግስት ተፅፎ ብሄራዊ ባህላችን ይሄኛው ነው አልተባለም አይባልምም። ይሁን እንጂ የሰሜኑ ባህል መሃል አገርንና በተለይ ከተሞችን ገበያውን በጣም ተጭኖ ይታያል። ጥያቄው ታዲያ ቡድኖች በተለይ ወደከተማ ሲሄዱ ባህላዊ ማንነታቸውን አያዩም። የአማራ ምግብ የአማራ ቋንቋ ብቻ አይሎ ያያሉ። ጥያቄው ከማንነት ይልቅ የእኔ የጥበብ ስራ ገበያ ላይ አልዋለም። የእኔን ጥበብ ቅመስልኝ። እኔም በጥበቤ ልኩራ። በዚህች አገር ውስጥ አብረን ስንኖር እኔም የእኔ ስራ አደባባይ ወጥቶ የማይበት ሲስተም ይፈጠር ነው። ይህ ደግሞ ፍትሃዊ ጥያቄ ነው። እነዚህ የቡድናቸው ባህልና ቋንቋ የተጎዳባቸው ቡድኖች ጉዳቱን ኮንነው እንዲስተካከል ይታገላሉ እንጂ በወጥ አሰራርና በአለባበስ ወዘተ ኢትዮጵያዊነት የለም አይሉም። ከፍ ሲል እንደገለፅነው ብሄራዊ ማንነት የሚሰራው በአብዛኛው ከሌሎች ጉዳዮች በመሆኑ። በርግጥ ቡድኖች በተለይ ደግሞ ቋንቋን በሚመለከት በአፍ መፍቻ ቋንቋየ ፍትህ ላግኝ ልጄን ላስተምር የሚለው ጥያቄ የፍትህ ጥያቄ ነው። እነዚህን ጥያቄዎች የሚመልስ የቡድኖችን ጥበብ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ሲስተም እንዲቀርፁ የፓለቲካ መሪዎችን እየፈተነ ያለ የፍትህ ጥያቄ ነው። ነገር ግን አነሰም በዛም አብረን ስንኖር በንክኪ የፈጠርናቸው የጋራ እሴቶች እንደ የአንድ አገር ልጅነት ማስተዋወቂያ ሊሆኑን ይችላሉ። ማንነት ማለት ራስን መለየት ማለት ነው። በተለይ ከውጭው ዓለም ጋር ስንገናኝ ራሳችንን የምንገልፅበት አንዱ የጋራ እሴታችን ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ክትፎን ብንወስድ አንድ ውጭ አገር የሚኖር ትግሬ ወይም ኦሮሞ የእኔ የሃገር ባህል ምግብ ብሎ ራሱን ሊያስተዋውቅበት ይችላል። በሂደት የጋራ እየሆኑ የመጡ አንዳንድ ባህሎችና የጋራ እሴቶች ለብሄራዊ ማንነት መገለጫነት እየተጠቀምንባቸው ወደፊት የጋራ እሴት ግንባታ ስራዎቻችንን ማሳደግ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ፕሉራሊዝምን ወይም ብዝሃነትን እንደ የጋራ እምነት ወስደን ይህንን የአንድነት መገለጫም ማድረግ አለብን። ከሁሉ በላይ ባህሎቻችንን የእኔ ባህልና ቋንቋ የአንተም ነው የሚል የመቀባበል ከፍታን ማሳየት ነው የብሄራዊ ማንነት መገለጫ።

የብሄሮች ማንነት መገለጫ መርሆዎች ምን ምን
ናቸው።

በኢትዮጵያ ሁኔታ ብሄሮች ሁሉ ሁለት ዋና ዋና ማንነቶች ይኖሯቸዋል። ከፍሲል እንዳነሳነው በመሬት፣ በታሪክ፣በጋራ እሴትና በፓለቲካ የሚገለፅ ብሄራዊ ማንነት ወይም የወል ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚኖራቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሚከተሉት አራት ጉዳዮች በተናጠል ራሳቸውን ሊገልፁ ይችላሉ። እንዚህ አራት የብሄር ማንነት መገለጫ መርሆዎች የሚከተሉት ናቸው።

መርህ 1. ባህል

ቡድኖች ባሏቸው የባህል መልክ ራሳቸውን ማንነታቸውን ኮራ ብለው ቢገልፁ ሃገራዊ ማንነታቸውን አይጋፉም። አለባበሳቸውን፣ አመጋገባቸውን፣ ጥበቦቻቸውን ሁሉ ለመጠበቅ መደራጀት መቻል አለባቸው። እንደ ግለሰብም ባህላዊ ማንነታቸውን በእለት ተእለት ኑሯቸው ሊገልፁ ይችላሉ። በአንፃሩ ብሄራዊ ማንነት ራሱ ወደዚህ ማንነት መጥቶ ቡድኖችን ጨፍልቆ አንድ ቡድን ለማድረግ አይችልም። ብሄሮች ሁሉ በጥበባቸው መኩራት ብቻ ሳይሆን ባህልን መጠበቅም መብታቸው ነው። ይህ ጤናማ የብሄር ራስን የመግለጫ አንዱ መርህ ነው። ብሄሮች በባህላቸው ራሳቸውን መግለፅ ይችላሉ ሲባል በቃል እኔ ደራሼ ነኝ፣ እኔ ደግሞ ከምባታ ነኝ ከሚለው የቃል ትውውቅ አልፎ የባህል ማህበር መስርተው መኖርን የሚያጠቃልል ነው። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ታዲያ ራሳቸውን ሲገልፁ የባህል ማህበራት እየመሰረቱ መኖር ይችላሉ ማለት የፓለቲካ ፓርቲ ያቋቁማሉ ማለት አይደለም። የሚያቋቁሙት ማህበር ባህልን ለመጠበቅ የሚያስችል ከፓለቲካ ዝንባሌ የፀዳ መሆን ይኖርበታል።

መርህ 2. ቋንቋ

ቡድኖች አንዱ የማንነታቸው መገለጫ ቋንቋ ሲሆን ይህንን ሃብታቸውን መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል። ቋንቋቸው ሲጠፋ ማንነታቸው ይጠፋልና መንግስት ይህንን የማንነት መገለጫ መጠበቅ አለበት። ቋንቋዎች የፅሁፍ ቋንቋ እንዲሆኑ በትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ ቢሮ እንዲገቡ ማድረግ ነው ቋንቋን መጠበቅ ማለት። ብሄራዊ ቋንቋን በተመለከተ የሃገሪቱ ዋና የሥራ ቋንቋ እንደ መሳሪያ የሚታይ እንደ መግባቢያ የሚታይ ሲሆን የብሄራዊ ማንነት ወይም የኢትዮጵያዊነት ብቸኛ መገለጫ አይሆንም።

መርህ 3. የብሄሩ ታሪክ

ቀደም ብለን እንዳነሳነው ቡድኖች የየራሳቸው ታሪክ ይኖራል። ያ ታሪክ በኢትዮጵያ ጥላ ስር የቡድኖች መገለጫ መሆን ይችላል። በሌላ በኩል ቡድኑ በጋራ ታሪኩ እየኮራና ብሄራዊ ማንነቱን እየገለፀበት በሌላ በኩል ቀደምት ታሪኩን ትውፊቱን እያየ ራሱን እየገለፀበት ሊኖር ይችላል።

መርህ 4. የደም ሃረግ (ancestry)

በአንድ የዴሞክራሲ ማህበረሰብ ውስጥ ዜጎች በቤተሰብ በጎሳ በብሄር ወዘተ የመግለፅ በማህበራት የመደራጀት መብት አላቸው። ራሳቸውን በቃልና በተለያዩ ማህበራዊ ድርጅቶች መግለፅ ይችላሉ። በአንፃሩ ከአንድ በላይ ከሆኑ ብሄሮች የተፈጠረው ወገን ደግሞ ራሱን ባሰኘው መንገድ መግለፅ ይችላል። ኢትዮጵያዊነትን እንደ ብሄር የማየት መብትም አለው። ዋናው ነገር ቡድኑ ራሱን የሚገልፅበት መንገድ በብሄራዊ ማንነት መግለጫ መስመሮች እንዳይሆን ነው።

ማጠቃለያ

ይህችን ዓለው ውብ ያደረጋት ህብረ ብሄራዊ ተፈጥሮዋ ነው። ዓለም ሁሉ አንድ ዓይነት ቢሆን ውበትን አንረዳም ነበር። ህብረ ብሄራዊነት የውበት መለኪያ ብቻ አይደለም። ህብረ ብሄራዊነት የጥንካሬም ዋና መለኪያ ነው። የተለያየ ጥበብ የተለያየ መረዳት ውስብስብ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎት ለማርካት አማራጮችን ይሰጣል። ኢትዮጵያ ወደ መቶ የተጠጉ ብሄሮችና ነገዶች ያሏት ሃገር መሆኗ የውበትና የጥንካሬ ሃብት የሆነ ትልቅ ሃብት ነው። ይህንን ሃብት በቅጡ መያዝ በጅጉ ይጠይቃል። የኢትዮጵያን የማህበረ ፓለቲካ ጉዞ ስናይ ባለፉት ዘመናት የማንነት አያያዟ ችግር ስለነበረበት፤ በብሄሮች መሃል ሚዛኑን የጠበቀ የባህል ቅብብሎሽ ባለመኖሩ ብሄሮች በግድ የሆነ ምስለት (forced assimilation) ተፈፀመብን ብለው እንዲነሱ አድርጓል። ይህ የምስለት ዘመን አልፎ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የመጣው የብሄር ፓለቲካና የብሄር ፌደራሊዝም ደግሞ ሃገሪቱን ወደ ልዩነት(separation) አምጥቷታል። የኢትዮጵያን ማህበረ ፓለቲካ ጠቅለል አድርገን ካየነው ጉዞው ከምስለት ወደ ልዩነት ((from assimilation to separation) ነው። ኢትዮጵያ በነዚህ በሁለቱም የማህበረ ፓለቲካ ጉዞ አልተደሰተችም። ህብረብሄራዊ ተፈጥሮዋን ውበትና ጥንካሬዋን ተንከባክቦ የሚይዝ ሲስተም ያስፈልጋል። በመሆኑም በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ የመጫወቻ ምሰሶ የሆኑትን የብሄር ማንነትና የብሄራዊ ማንነት ጉዳይ በተገቢው መንገድ እንዲገለፁ ሲስተም መዘርጋት ያስፈልጋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄሮች ከፍ ሲል በዘረዘርናቸው መንገድ ራሳቸውን እንዲገልፁ ማድረግ መፍትሄ ነው። በዚህ ብሄርንና ብሄራዊ ማንነትን በመግለፅ ሂደት ዜጎች፣ ቡድኖችና መንግስታት መጠንቀቅ የሚገባቸው ብሄርም ይሁን ብሄራዊ ማንነት ራሱን ሲገልፅ መርሆዎችን እየዘለለ ለመግለፅ እንዳይሞክር ነው። ብሄራዊ ማንነት በዘር፣በባህል፣በሃይማኖት፣በቋንቋ ሲገለፅ የብሄሮች ማንነት ይጨቆናል። በዚህ ጊዜ ብሄራዊ ማንነት አጉራ ዘለል ስለሚሆን አለመረጋጋትን ያመጣል። በአንፃሩ የብሄር ማንነት ደግሞ አጉራዘለል መሆን የለበትም። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ሰዓት ያለውን የብሄር ፓለቲካ አራማጆች ስናይ ቡድናቸው ማንነቱን እንዲገልፅ የሚሹባቸው መስመሮች የሚከተሉት ናቸው። ባህል፣ ቋንቋ፣ ግዛት ወይም መሬት፣ፓለቲካዊ ተክለ ሰውነት፣ ታሪክ፣ እሴቶች፣ ዝርያ ወይም ሃረግ ናቸው። ከዚህ የምንረዳው ለጋራው ማንነት መስሪያ የሆኑትን ሁሉ ነው እየገፈፈ የወሰደው ማለት ነው። ምንም ለሃገር ግንባታ ያስቀረው አለባ (element) የለም። በሃገራችን ፓለቲካ ውስጥ ይህ የፓለቲካ መስመር ከአንድነት ሃይሉ ጋር ግጭት ውስጥ የከተተው ቡድኑን የገለፀበት መስመር ስለሳተ ነው። በአንፃሩ ደግሞ አክራሪ የሆነው የአንድነት ሃይል የብሄራዊ ማንነት ወይም አንድነት መገለጫን ከፍ ሲል የገለፅናቸውን ሁሉንም ማለትም ቋንቋን፣ባህልን፣እሴቶችን፣ታሪክን፣መሬትንና ፓለቲካዊ ማንነትን ሁሉ ዘርፎ ከወሰደ ቡድኖች ማንነታቸው እንደተዋጠ ይሰማቸዋል። እንዲህ አይነቱ አንድነትም በውስጠ ተዋዋቂ ቀድሞ የተስፋፋውን ባህል የበለጠ እንዲስፋፋ በር ለመክፈት ይመስላቸዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ምርምርና ፓሊሲ ተቋም አቅጣጫዎችን ያሳያል። ብሄሮች ከፍ ሲል በገለፅነው መርህ መሰረት ራሳቸውን እንዲገልፁ፤ብሄራዊ ማንነትም ከፍ ሲል ባነሳናቸው መርሆዎች እንዲገለፅ ግልፅ መርሆዎችን አስቀምጠናል። እነዚህን መርሆዎች መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ርእዮትና ፓሊሲም ቢቀረፅ ሃገሪቱ በተረጋጋ ማህበረ ፓለቲካ ምህዳር ላይ ታርፋለች። እነዚህ መርሆዎች የህግ ትርጉምና ማእቀፍ ቢያገኙ ምቹ ሲስተም ቢቀረፅላቸው ሃገሪቱ በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ልማት ታመራለች። ለምሳሌ በአንዳንድ ሃገራት በብሄር ላይ በፓለቲካ መደራጀት ወይም ይህን ተክለ ሰውነት ለብሄር ለማላበስ መሞከር በህግ ያስቀጣል፤ ወንጀል ነው። ለምሳሌ ኬንያን፣በስዊትዘላንድን እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። በብዙው ዓለም የማንነት ፓለቲካ የተወገዘና በህግ የሚያስጠይቅ የሆነበት ምክንያቱ ብሄራዊ ማንነትን ለመጠበቅ አገር እንዳይፈርስ ነው። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 ላይ ያለውን ሃሳብ ስናይ ይህ አሳብ ከምን ስነ ልቡና ይመነጫል ብለን እንድንደመም ያደርገናል። የብሄሮች መብት እስከ መገንጠል የሚለው ስሜት ራሱ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለብሄራዊ ማንነት ግንባታ የሰጠችውን ዝቅተኛ ግምት ነው። ይህ አንቀፅ የሚያሳብቀው ብሄራዊ አንድነት ያልረጋ እና በየትኛውም ጊዜ ፍርክስ ብሎ ሊሄድ የሚችል መሆኑን ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከፍ ሲል ያነሳናቸው የብሄራዊ አንድነት መገለጫ መርሆዎች ሁሉ በብሄር ማንነት ታጭደው መበላታቸውን ነው። ይህ ነገር በፓለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ትኩረት እንዲያገኝ ይገባል። እንግዲህ አገራችን ኢትዮጵያም የተሻለ ማህበረ ፓለቲካ ምህዳር ውስጥ እንድትገባ በነጠረና ግልጽ በሆነ መርህ መመራት ያሻታል። በሌሎች ፓለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደገና እስክንገናኝ የዛሬውን ጥናታችንን በዚሁ እንቋጫለን።

የኢትዮጵያ ጥናት ምርምርና ፓሊሲ ኢንስቲትዩት (ERPI) የኮሚቴ አባላት።

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: