The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ በእሥራ አንደኛው ሰአት – ይገረም አለሙ

ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት

ዶ/ር ታየ ወልደሰማያትን ቢያንስ በሁለት ጉዳይ የማያውቃቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንትነታቸውና ለአጭር ግዜም ቢሆን የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩ በመሆናቸው፡፡ ከእነዚህ ሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ግን ላለፉት ሰባት ዓመታት የሚወራውና በጥርጣሬ የሚነገረው ከግምት ሳይገባ በአደባባይ አይተናቸው ሰምተናቸው አናውቅም፡፡ ሰሞኑን ግን በዋሽንግተን ዲስ በአንድ መድረክ ብቅ ብለዋል፡፡ ይሄ ብቅታቸው በሶስት መንገድ መነጋገሪያ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ አንደኛው የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተብለው በ1999 ዓም ብቅ ያሉት ቢያንስ ከቅንጅት አንጻር 11ኛው ሰዐት ሊባል በሚችል ወቅት ነበርና ዛሬም የኢትዮጵያ ጉዳይ 11 ኛው ሰአት ላይ ነው በሚባልበት ወቅት ብቅ ማለታቸው መመሳሰሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሙያ ማህበርም የፖለቲካ ድርጅትም መሪ ሆነው የነበሩትና ለአመታት የጠፉት ሰው ብቅ ያሉት ከሲቪክ ደርጅት ምስረታ ጋር መሆኑ ሲሁን ሶስተኛው መድረክ ላይ የታደሙት ከአቶ አባይነህ ብርሀኑና ከወ/ሮ ንግስቲ ገብረህወት ጋር መሆኑ ነው፡፡ የሁለቱ ጉዳይ አስፈላጊ ከሆነ ከአቶ አሰፋ ጫቦ ቃል ልዋስና እመለስታለሁ፡፡

ዶ/ር ታዬ ጋር የግል ግንኙነት ባይኖረኝም በየስብሰባዎች ላይ እየተገኘሁ ንግግራቸውን በማዳመጥ አውቃቸዋለሁ፡፡ ከእስር ሲፈቱም ስልክ ደውዬ የማግኘት እድል ገጥሞኝ እንኳን ከቤተሰቦችዎ ለመቀላቀል አበቃዎት ብያቸዋለሁ፡፡በየመድረኩ ያሳዩት በነበረው ድፍረት፤ በኢመማ ፕሬዝዳንትነታቸው ከወያኔ ጋር ያደርጉት በነበረው ፊት ለፊት መጋፈጥ፣ ብሎም በእስር ቤት የነበራቸውን ጽናት በመስማት አድናቂያቸው ነበርኩ፡፡ በዚህ አድራጎታቸውም በዓለም ደረጃ ሊባል በሚችል መልኩ አድናቆትም አክብሮትም አትርፈው ነበር፡፡ ነበር ያልኩት በ1999 ዓም በአስራ አንደኛው ሰዐት በፈጸሙት ራሳቸውንም ቀድመው የነበሩበትን ኢመማንም ሆነ ኋላ የገቡበትን ቅንጅት ያልጠቀመ ተግባር ምክንያት እንኳን አክብሮቱና አድናቆቱ ራሳቸውም በመድረኩ ሊቀጠሉ ባለመቻላቸው ነው፡፡

በዚህ ሁኔታና ምክንያት ላለፉት ሰባት ያህል አመታት ከመድረኩ የጠፉት ዶ/ር ታዬ ዛሬም አስራ አንደኛው ሰአት ሊባል በሚችል ወቅት ብቅ ማለታቸው ነው የትናቱን አስታውሰን የዛሬውን እንዴትነትና ለምንነት መጠየቅ አስፈላጊ የሚያደርገው፡፡ ለምን ቢባል “ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ዝም ብለሽ በይ ተቀበይ የሰጡሽን ብቻ” መሆን ስለሌለብን፡

የኢመማው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታዬ፤

ዶ/ር ታየ ነባሩ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እየተባለ ይጠራ የነበረው የሙያ ማህበር ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ታግለዋል፣ የእስር መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡እንዲህ ብዙ ነገር የሆኑለትንና የሆኑበትን ኢመማን በአስራ አንደኛው ሰአት ወደ ፖለቲካው ገብተው ለመፍረሱ ከሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች አንዱ መሆናቸው ርሳቸውንም ሳይጸጽታቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡

በ1999 ዓም የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከመውጣቸው አንድ ወር ቀደም ብሎ የዶ/ር ታየ በድንገት የቅንጅት አለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መሆን በተለይ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አቧራ ባስነሳበት ወቅት ወደ ኢመማ ቢሮ ጎራ ብዬ ነበር፡፡ በወቅቱ የማህበሩ ዋና ጸኃፊ ከነበሩት አቶ ገሞራው ጋር ስንጨዋወት የዶ/ር ታየ ሰሞነኛ ነገር ተነሳና አየ ታየ ገደለን አሉኝ፡፡እንዴት በምን ምክንያት ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ደረደርኩ፡፡ አቶ ገሞራው በተረጋጋ መንፈስ ግን በቁጭት ስሜት ቅንጅት ሊገባ ነው ማለትን ሰንሰማ ተው ይቅርብህ አልነው፣ አይሆንም አለ፤እምቢ ካልክ ከመግባትህ በፊት በይፋ የመልቀቂያ ደብዳቤ ጻፍልን አልነው፣ ይህንንም አምቢ አለ፡፡ የእሱ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመሆኑ ዜና እንደተሰማ ዲፕሎማቶች በአካል በስልክ ጥያቄያቸው አላስቀምጥ አለን፡፡ መንግስት በሙያ ማህበር ሽፋን ፖለቲካ ነው የሚያራምዱት በማለት የሚያቀርብባችሁ ክስ እውነት ነው ማለት ነው ለሚለው ጥያቄአቸው ምን ብለን እንመለስ አንዴትሰ እናስተባብል በማለት በሰፊው አወጉኝ፡፡ አዎ ዶ/ር ታየ ለራሳቸውም ለቅንጅትም ያልበጀው በአስራ አንደኛው ሰአት ቅንጅት መግባት ኢመማን እንዲህ ጎድቶታል፡፡

ዶ/ር ታዬ የቅንጅት ኣለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤

ዶ/ር ታየ የቅንጅት አለም አቀፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆኑ እስከተባለበት ግዜ ድረስ የቅንጅት አባልም ደጋፊም አልነበሩም፡፡ለዚህ ደግሞ ቅንጅት ምርጫ መወዳደሩን እየኮነኑ እኔ ታየ ማንንም አልመረጥኩም የመራጭ ካርዴ ዛሬም በእጄ አለ እያሉ የአመራሮቹን አካሄድ እየተቹ በየመድረኩ ሲናገሩ የነበረው በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ሌላው እንቆቅልሽ ዶ/ር ታዬ የቅንጅት አለም አቀፍ ፕሬዘዳንት የሆኑት በኢ/ር ኃይሉ (ነብሳቸውን ይማር) የግል ውሳኔና ፈቃድ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ዝቅ ብየ ማስረጃ አቀርባለሁ፤ እንቆቅሎሹ ታዲያ ምኑ ላይ ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላልና ትንሽ ፈታ አድርጌ ላሳይ፡፡ አንቆቅሎሹ ዶ/ር ታየ ከመኢአድም ሆነ ከኢ/ር ኃይሉ ጋር ቅርበትም ሆነ ጤነኛ ግንኑነት ያልነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ ነገሩ ሰፊ ታሪኩ ረዥም ስለሆነ ለማስጃነት ያህል ከውቅያኖስ በጭልፋ በሚመስል መልኩ ጨለፍ አድርጌ ላቅርብ፡፡

ፕ/ር አስራት እንደሞቱ ከእስር የተፈቱት አቶ አሊ እንድሪስ የቀኝ አዝማች ነቅአ ጥበብን ቦታ ይዘው መአህድን እንደገና የማደራጀት የተባለው ስራ ተከናውኖ ኢ/ር ኃይሉ ከአሜሪካ ተጠርተው ፕሬዝዳንት ሆኑ፡፡ ከሁለት አመት በኋላ መአህድን ወደ መኢአድ ቀይረው ስሙን ምክንያት በማድረግ አባል አልሆንም ስትሉ የነበራችሁ ምሁራን አሁን ምክንያት የላችሁም በማለት ጥሪ አቀረቡ፡፡ በዚህ መሰረት ይመስላል እን ዶ/ር መኮንን ቢሻው (ነብሳቸውን ይማር) እነ ፕ/ር አየናቸው ወዘተ መኢአድ ሲገቡ ዶ/ር ታየ ይህን ጥሪ አልተቀበሉም፡፡ ያለመግባታቸው ምክንያት እየተባለ በወቅቱ ብዙ የተባለ ቢሆንም ማስረጃ የሌለው ነገር አሉባልታ ነውና ለዚህ ቦታ አይመጥንም፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ከዛ በኋላ ደግሞ ዶ/ር ታየ የምርጫ 9­7 ተሳትፊ አልነበሩም፣ የቅንጅትም ደጋፊ ሊሆኑ ቀርቶ አልመረጡትም፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ እንዴትና በምን ተለውጦ ነው ኢ/ር ኃይሉ ከቃሊቲ እስር ቤት ሆነው አሜሪካ ያሉትን ዶ/ር ታየን ያውም ከስልጣናቸው ውጪ ሄደው ፕሬዝዳንት ያደረጉዋቸው ዶ/ር ታየስ ላልመረጡት ቅንጅት ፕሬዝዳንት መሆንን የተቀበሉት፡፡

የዶ/ር ታየ ፕሬዝዳንት መሆን ቅንጅትንም ሆነ ርሳቸውን የጠቀመው ነገር እንደሌለ ርሳቸውም የሚክዱ አይመስለኝም፡፡ እንደውም ለመፍረስ ካበቁት በርካታ ምክንያቶ አንዱና ተጠቃሹ ካልሆነ በስተቀር፡፡ይሄ ብዙ ነገር ይቀሰቅሳልና በአጭሩ አንድ ነገር አስታውሼ ዝቅ ብዬ አሳያለሁ ያልኩትን ማስረጃ አቅርቤ ልለፈው፡፡ ኢ/ር ኃይሉ የቅንጅት ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ የሄደውን የልኡካን ቡድን በመምራት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ከእነ ብርቱካን ተለይተው ስብሳባዎችን እንዲያደርጉ ፕሮግራም ወጥቶ መድረክ ተዘጋጅቶ ማስታወቂያ የተሰራጨው በዶ/ር ታየ ፊርማ ነው ፡፡(ወረቀቱ በእጄ ይገኛል) በዚህ ሁኔታ የአስታራቂነት ሚና ሊጫወቱ ይገባ የነበሩት ዶ/ር ታየ በእሳት ላይ ቤኒዚን ይሉት አይነት ተግባር በመፈጸማቸው ለቅንጅት መፍረስ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ኢ/ኃይሉ አሜሪካ ተጉዞ የነበረውን የቅንጅት የልኡካን ቡድን አምስት አባላትን አግጃለሁ በማለት ታኀሣሥ 1/2000 ዓም ጽፈው በኢንተርኔት ባሰራጩት ሰባት ገጽ ጽሁፍ ውስጥ ዶ/ር ታየ ፕሬዝዳንት የተባሉበት የቅንጅት አለም አቀፍ ም/ቤት የተቋቋመው በርሳቸው የግል ውሳኔ መሆኑን አንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “ ..አመራሩ እስር ቤት ሆኖ ድርጅቱ በአገር ውስጥና በውጪ አገር በከፍተኛ ችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት የድርጅቱ ፕሬዝዳንት የወቅቱን ሁኔታ ግምት ውጥ በማስገባትና ያላቸውን የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን በመጠቀም ለችግሩ መፍቻ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ም/ቤት በውጪ ሀገር እንዲቋቋም ወስነው መመሪያ በሰጡበት ወቅት…፡”በማለት ይቀጥሉና ሌሎቹ ከርሳቸው ጋር በእስር ቤት የነበሩት አመራሮች ይህን የርሳቸውን ውሳኔ መቃወማቸውን አንደ ጥፋትም አንደ ክህደትም ይገልጡታል፡፡

ዶ/ር ታየ ወደ ቅንጅት መሪነት የወጡት በማንም ይሁን እንዴት አብዩ ጥያቄ ይህ ሳይሆን የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ዶ/ር ታየ በአስራ አንደኛው ሰአት የማይደግፎት በምርጫ ድምጻቸውን ላልሰጡት ቅንጅት አመራር በመሆን እንዴትና ለምን ይህን አይነት ስህተት ሰሩ የሚለው ነው፡፡ ይሄው ስህተት ይመስለኛል ሰባት አመት ያህል ከመድረክ ያጠፋቸው፡፡ አሁንስ በዚህ በአስራ አንደኛው ሰአት ብቅ ያሉት ከዛ ውድቀት/ክስረት ተምረው፣ እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስትነታቸው ያለፈውን ገምግመው፣ ያለንበትን ወቅት አጢነው ስለመጪውም ተንብየው ይሆን ወይንስ ዛሬም አንደ ትናንቱ የሚለው ደግሞ የአሁኑ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ?

EMF

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: